እንደሚታወቀው ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ መንግስት ዋና ጻሕፊ አንቶኒ ብሊንከን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነገር አበላሽተው ነው የሄዱት፡፡ ኢትዮጵያዊያን እርስበርስ እንዲጨፋጨፉ የቅኝ ግዛት ሴራ ሰርተው ነው የሄዱት፡፡
ነገር ግን የአማራው ማህበረሰብ ልጆች ምን እያደረጉ ነው፡፡ የአማራን ሕዝብ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመታደግ የአማራ ልጆች ምን እያደረጉ ነው? የሚለው ያሳስበኛል፡፡ አፍሪካን ያስተባበረ ሕዝብ ልጆች እንዴት ዛሬ በጉያው ያሉትን ወገኖቹን ማስተባበር ያቅተዋል?
እንደሚታወቀው ከአምስት መቶ ሺህ በላይ አማራዎች በአሜሪካ ይኖራሉ፡፡ እንዴት እነዚህ ሰዎች የአሜሪካ መንግስት የያዘውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲቀይር ማድረግ ይሳናችዋል?
አንቶኒ ብሊንከን አይሁዳዊ ነው፡፡ ቤተሰቦቹ ከናዚ ጭፍጨፋ የተረፉ ናቸው፡፡ የዘረኝነት ክፋትን የሚረዳ ይመስለኛል፡፡ ህወሓት ዘረኛ ድርጅት ነው፡፡ በራሱ በወገኑ ላይ ጥላቻን የሚዘራ እና ጥፋትን የሚያውጅ እና ሽብርን የሚፈፅም ድርጅት ነው፡፡ ህወሓት የፈፀመው ናዚ ከፈፀመው የሚተናነስ አይደለም፡፡ ነገር ግን ህወሓት እንደ ናዚ በዓለም ሕዝብ አልተወገዘም እርምጃም አልተወሰደበትም፡፡ ይልቁንም እየተሸሞነሞነ እና እየተደገፈ ይገኛል፡፡ ይህ ለዓለም ሕዝብ ሞራል እና ፍትህ ጎጂ የሆነ ተግባር ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ አይሁዳዊነትን የጠበቀ በሃይማኖታዊ እና በመንግስታዊ ስርዓቱ ያከበረ ታሪካዊ ዝምድናን ያኖረ ሕዝብ ነው፡፡ የአማራ ነገስታት እስራኤልን ነጻ ለማውጣት ሲመኙ የነበሩ እና የጣሩ እስራኤልንም በመጠበቅ በጎ ተፅዕኖ ያሳደሩ እና ተሰማኒት ያገኙ ነበሩ፡፡ የአማራ ሕዝብ ለእስራኤላዊያን ለአይሁዳዊያን ባለውለታ ነው፡፡ ዛሬም ቀላል የማይባል የእስራኤል ሕዝብ የአማራ ሕዝብ ነው፡፡ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎችም እስራኤልን እያገለገሉ እና እያሳደጉ ይገኛሉ፡፡
እንደሚታወቀው ብዙ አይሁዳዊያን በአሜሪካ መንግስት ውስጥ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥም ዋና ዋና ቦታዎችን ይዘው ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን አይሁዳዊያንን የሚያሳምኑ አማራዎችን እንዴት እናጣለን? አንቶኒ ብሊንከን የሚያሳምኑ አማራዎች እንዴት ልናጣ ቻልን?
የአማራ ሕዝብ እንዲጎዳ ማድረግ የአሜሪካን መንግስት ፍላጎት እጅግ እንደሚጎዳው የኢትዮጵያ መዳከም ለአሜሪካም አደጋ እንደሆነ እንዴት ማስረዳት ያቅተናል? አሜሪካ በእስራኤል ያላትን ፍላጎት የሚያስጠብቀው በተዘዋዋሪ አማራው ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ያለው አማራ እንዲዳከም ማድረግ የተጣረሰ ፖሊሲ አይሆንምን?
ቅኝ ገዥዎች ስለ አማራ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ማስቀየር የምንችለው መቼ ነው? የአማራ ሕዝብ መልካም ሕዝብ እንደሆነ እንዲያውቁት የምናደርገው መቼ ነው? ጥላቶቻችን ሳይሆኑ አጋሮቻችን የምናደርገው መቼ ነው? መስጠት የምንችለው ምንድን ነው? እንደ ወያኔ እና ኦነግ የሀገራችን ብሔራዊ ጥቅሞች እና ሉዓላዊነት አሳልፈን በመስጠት እና ወገናችንን በማጥቃት ሳይሆን የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስከበር እርስበርስ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ቅኝ ገዥዎችን ማሸነፍ የምንችለው እንዴት ነው? መስጠት የምንችለው ምንድን ነው? ምን ብናደርግ ነው ምን አይነት ፖሊሲ ብንከተል ነው ጠላትነታቸውን መፋቅ ወዳጅነታቸውን የምናገኘው?
እነዚህ ጥያቄዎች በደንብ የተዘጋጀ ዕቅድ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይፈልጋሉ፡፡
ነገር ግን ዋናው ራሳችን ነን፡፡ አፍሪካን ያስተባበረ ሕዝብ እንዴት ራሱ አንድ መሆን ያቅተዋል? ትግረዋትን ከጎኑ የማያሰልፍ የአማራ ትግል ኦሮሞዎችን ከጎኑ የማያሰልፍ እና አብሮ የማይሰራ የአማራ ትግል ሌሎችንም ብሔሮች ከጎኑ የማያሰልፍ የአማራ ትግል ፍሬ አያፈራም፡፡ ወገኖቻችንን ለአንድ ዓላማ እንዴት ማስተባበር አቃተን? ጠንካራ መንግስት እና ሀገር መገንባት ለምን አቃተን? የአማራ ሕዝብ ላለፉት አርባ ሃምሳ ዓመታት መከራን የተቀበለው አንድ ሀገር ብሎ እኮ ነው፡፡ ያ ካልሆነማ እንደ ሩዋንዳ አጻፋ በመመለስ መጠፋፋት ይቻል ነበር፡፡ እንዴት ነው ይህን መስረዳት ያልቻልነው? የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ በታሪኩ አለኝታ እንጂ ጠላት ሆኖ እንደማያውቅ እንዴት ማስረዳት አቃተን? የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በጋራ የደመቀበት እና ሀገር የገነባበት እንጂ የጠላትነት ታሪክ እንደሌለው ይልቁንም “ወደፊት እንዴት እንቀጥል” በሚለው መወያየት፣ መግባባት እና መረዳዳት አቃተን? እስከ መቼ ነው የቅኝ ገዥዎችን አጀንዳ የምንጎትተው?
በቅኝ ገዥዎች በተለይም በአሜሪካ እና በእንግሊዝ አማራው እየተጠቃ እንዲቀጥል እና እንዲዳከም ፍላጎት ያለ ይመስላል፡፡ ላለፈው አንድ ክፍለ ዘመን የተካሄደው ፀረ አማራ ጥላቻ እና ቅስቀሳ እንደቀጠለ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህን ተንኮል እስከ አሁን ድረስ ቆም ብለው ማሰብ እና ማጤን የቻሉ አይመስልም፡፡ ሌሎች ብሔሮች አማራን ማጥቃት ራስን ማጥቃት እንደሆነ ደካማ እና ድሀ ሀገር መፍጠር እንደሆነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ድጋፍ ስለተደረገልህ አድርግ ስለተባልክ እንዴት ወገንህ የሆነውን ሕዝብ ታጠቃለህ?
የአማራ ሕዝብ ትግል ሀገራዊ እና አለም አቀፋዊ ትግል የሚያካሄድበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እጅግ ከፍተኛ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አይዞን ሁላችንም እንበርታ፡፡ ከዚያም ሀገራችንን እንዴት እንደታደግን ለዓለም የምንነገረው ታሪክ ይኖረናል፡፡
ይህ የአማራው ትግል ብቻ አይደለም የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል ነው፡፡ ከአማራ ሕዝብ እና ሃይላት ጋር መቆም አማራጭ የሌለው መንገድ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ማዳን የምንችለው አማራው ለዘመናት ሲጮኽ የነበረውን ሀሳብ በመረዳት እና በጽኑ አንድነት እና ፍቅር ከጎኑ ሆኖ በመታገል ነው፡፡ ሀገራችንን ማሳነስ እና ሕዝቧን ማሰቃየት የሚፈልጉ ሁሉ ይጠፋሉ፡፡ ባንዳነት ታሪክ ይሆናል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
‹አንድነት፣ ወገንተኝነት፣ መተባበር፣ ክብር ያለው ኑሮ፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማት!›