March 19, 2023
43 mins read

“እባክህ እግዚአብሄር አንበሶች ነብሮችን እያባረርን በተኩላዎች የምንገዛ አታድርገን።”! ከበየነ

ዓለም እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ ዘመን ላይ ደርሳለች። አንበሳ የዱር አራዊነት ንጉሥነቱን አስነጥቆ ግዛቱን ለተኩላዎች ለቋል። ብልሆችና ጀግኖች ሸሽተው ምድርን ለግፈኞች ትተዋል። ሁሉም ግራ ገብቶታል፣ ሥርዓተ-አስተዳደር እየጠፋ አንዳች ደግ ውሳኔ የሚያደርግ አስተዋይ ጠፍቶ ፍጡራን ባዝነዋል። ኃጢዓት ብዙዎችን በርኩስ መንፈስ አርክሳ የማይረቡ አድርጋቸዋለች። ተኩላዎቹ ለዓላማቸው አካሄድና አፈፃጸም ሲሉ ሐሰቱን እውነት እያስመሰሉ እየሸነገሉ አስተሳሰብን ማዝቀጥ በመቻላቸው የሚያሸንፋቸው ጠፍቷል። እነሆ! ብዙዎቻችን መከላከል አቅቶን እንሸሻለን ወይንም በመንፈስ እስረኛነት እንማቅቃለን ።

abiy 98
እስከመቼ ነው እንዲህ የምንሆን? በሥጋም በዓዕምሮም ተበድለን፣ የየዕለት ኑሯችን የፈተናና የመከራ ምንጭ ሆኖ፣ መንፈሳዊ ኃይልና ብርታት አጥተን በየሕይወተ ሥጋ ሳለን እስከመቼ እንሙት? መች ይሆን ሥጋችንን አበርትተን፣ ዓዕምሯችንን አዘጋጅተን መከራን የምንቋቋም? ግፉ ሥጋችንን ከጎዳው ጭቆናም ገዝፎ እግዚአብሄር እጅግ እስከሚጸየፈው ኃጢዓት ድረስ በማደግ መንፈሳችንን ሠብሯል። መች ይሆን ጨዋ ባህላችን፣ እሴቶቻችን፣ ኢትዮጵያዊ ቅድስናንችን ዳግም የሚመለሱት? እስኪ ይህን መጣጥፌን በማርክስ ጽሁፍ ልጀምርና – ማርክስ ዛሬን በተለይም ኢትዮጵያን ቢያይ ኖር ምን ሊጽፍ ይችላል? የሚል ግምት ላስፍር።

ማርክስ ምን ብሎ ነበር፣ ምንስ አልሆነም?

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጣር 5 ግንቦት1811 ዓም ተወልዶ 14 የካቲት 1883 ዓም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ታሪክ አዋቂ፣ የፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪ፣ የህብረተሰብ ዕድገትና አደረጃጀት አጥኚ፣ ጋዜጠኛ፣ የምጣኔ ኃብት ጥልቅ አሳቢ፣ ሶሻሊስታዊና አብዮተኛ የነበረው ካርል ሃይንሪክ ማርክስ (Karl H Marx)፣ 1848 በታተመችው በዘመኑ ዝነኛ በነበረችው የኮሙኒዝም መግለጫ (Manifesto of the Communist Party) ትንሿ መጽሄት ላይ ይህን ጽፎ ነበር። የአማርኛ ትርጉሙ የራሴ ነው።

«A spectre is haunting Europe – the spectre of communism. All of the powers of old Europe have entered into a holy alliance to exorcise this spectre: Pope and Tsar, Metternich and Guizot, French Radicals and German police spice.»

አንድ የጣር አምሳል አውሮፓ እያወከ ነው – የኮሙኒዝም አምሳል። ከዚህ መንፈስ ለመላቀቅ የአርጌዋ አውሮፓ ኃይሎች የተቀደሰ የሚሉት ስምምነት ላይ ደረስዋል፤ ሊቀ-ጳጳሱና የራሽያው ንጉስ፣ ሜተርኒች (የአውሮፓን መንግሥት ለማራጋጋት እንዲሁም በመንግሥታቱ መካከል የኃይል ሚዛን ለማስተካከል የሚጥረው የቭየናውን ጉባኤ አዘጋጅ) እና ጌዦት (ህገ መንግስታዊ የዘውድ ሥርዓት የሚሻው ተፅዕኖ ፈጣሪው የፈረንሳዪ ወግ አጥባቂ ቡድን)፣ የአብዮቱ ዘመን የፈረንሳዩ ጽንፈኛ ስብስቦችና የጀርመኑ ሠላይ ፖሊስ።

«The history of all hitherto existing society is the history of class struggles. Freeman and slave, patrician and plebian, lord and serf, guild-master and journeyman to one another, carried on an uninterrupted, now hidden, now open fight, a fight that each time ended, either in a revolutionary reconstitution of society at large, or in the common ruin of the contending classes.»

እስከዛሬ ድረስ ያለው የማህበረሰብ ታሪክ የመደብ ትግል ታሪክ ነው። ነጻ ሰውና ባርያ፣ ከፍተኛው መደብና ዝቅተኛው መደብ፣ ጌታና ገባር፣ አሠሪና ሠራተኛ – አንድ ጊዜ ስውር፣ አንዳንዴ ደግሞ ግልጽ በሆነ የማያቋርጥ ትግል ውስጥ ናቸው። ትግሉ አንድ ወቅት ላይ በሚከሰት ማህበራዊ አብዮት ወይንም በተጻራሪዎቹ መደቦች መፍረስ ምክንያት ያከትማል።

ካርል ማርክስ ይህችን መግለጫ የጻፈው ላብአደሩ፣ ወዛደሩ፣ ሠራተኛው (proletariat)በዘመኑ በከበርቴው ሥርዓት የሚደርስበትን ቅጥ ያጣ ጭቆና ታግሎ ራሱን ነጻ እንዲያወጣ በተለይም ደግሞ ሳይንሳዊ ያልሆነ የትግል ዘይቤ በመከተል የፓሪስ ኮሙን (Paris Commune)ዓይነት አስከፊ ውድቀት እንዳይደርስበት ነበር። ማርክስና ኤንግልስክ ሠራተኛው ራሱን ነጻ እንዲያወጣ መንገዱን ቀና አድርገውለት ነበር። በከበርቴውና ሠራተኛው መካከል ያለው ቅራኔ የሚፈታው ከብርቱ ትግል በኋላ በሠራተኛው አሸናፊነት መሆኑን ሳይንሳዊ ኮሙኒዝም በሚገባ ያብራራል።

በ 1917 ዓም በሌኒን (Vladmir I. Lenin) የተመራው የመጀመርያው ሶሻሊስታዊ አብዮት – በሩስያ ኋላም በሶቭየት ህብረት አገሮች ላይ ማርክስ 1867 ዓም ላይ የጻፈውን ካፒታል (Das Kapital) ተንተርሶ ሶሻሊስታዊ ምጣኔ-ኃብታዊ ሥርዓት ዘረጋ። ሥርዓቱ ግን እያደር ከምዕራቡ ዓለም የሚሠነዝርበትን ፕሮፖጋንዳ እንዲሁም ውስብስብ ፈተናዎችን እየመከተ ወደፊት ሊራመድ አልቻለም። ሶሻዛሊዝም በጋራ የመሥራት፣ በጋራ የማሰብና ምርቱን እኩል የመከፋፈል ህግ ይከተላል። ግለኝነት ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ነው። ቀድሞ ክርስትያኖች ያላቸውን ሁሉ ሐዋርያት እግር ሥር አስቀምጠው እንደ አስፈላጊነቱ በጋራ ይጠቀሙበት ነበር። ምናልባት ማርክስ ይህን መልካም ሥብዕና እንደ ምሳሌ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ግን ግለኝነትና ራስን መውደድ ከከበርቴው ውስብስብ ሻጥር ጋር ተዛምዶ ሶቭየት ህብርትን ጨምሮ ሶሺያሊስት መርህን ተከትለው በነበሩት ፖላንድ፣ ሃንጋሪ፣ ምሥራቅ ጀርመን፣ ቼኮዝሎቫክያ፣ ቡልጌርያና አልባንያ ላይ ጉዳት በማስከተል ማርክስ ያለው ሁሉ እንዳይሆን ሆኗል።

ማርክስ የኮሙኒስት ማኒፌስቶን ከጻፈባት 1848 ዓም እስከዛሬ 175 ዓመቶች አልፈዋል። ሁሉም እንደታቀደው አልሆነም። ሌኒን ኤምፔርያሊዝም የከበርቴው ሥርዓት የመጨረሻው ደረጃ ነው (Imperialism is the last stage of Capitalism) ቢልም በብልህ ቢሮክራቶች የሚታገዘው የከበርቴው ሥርዓት ቀዝቃዛውን ጦርነት የመጨረሻው የሶሺያሊዝም ደረጃ (Cold war is the last stage of Socialism) አደረጉት። እነሆ ቀዝቃዛው ጦርነት መሠረታዊ ልማት እንዲኮስስ በማድረግ ሕዝቡ በሥርዓቱ ላይ እንዲያጉረመርምና እንዲያምጽ አደረገው። ከ 1947ዓም እስከ 1991 ዓም የዘለቀው ቀዝቃዛው ጦርነት ተብሎ የሚጠራው መልካዓ-ምድራዊ ፖለቲካዊ ውጥረት በሶቭየት ሕብረትና በአሜሪካ መካከል ነበር። የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የሶቭየት ሕብረትን ምጣኔ ኃብት ክፉኛ በመጉዳት ሌሎቹንም ሶሺያሊስት አገሮች አምሷል።

በሶሺያሊስት አገሮች ላይ ምጣኔ ኃብቱ አድጎ ህብረተሰቡን በጋራ ከመበልጸጉ ይልቅ – እያደር የመዝቀጡ ሁኔታ – ሰዎች ቀልባቸውን ወደ ምዕራቡ ዓለም እንዲጥሉ አደረገው። ወጣቱ አዛውንቱ “ድህነት ነው” ብለው የጠሉትን ሶሻሊዝም እየተዉ ወደ ምዕራብ አገሮች ይሰደዱ ጀመር። ምዕራቡ ዓለምም እጁን ዘርግቶ ተቀበላቸው። ስደተኞችም የምዕራቡን ዓለም አብለጭላጭነትና ደማቅነት ለየዘመዶቻቸው ደብዳቤ በመላክ አበሰሯቸው። ስደት እንደ ሥልጣኔ ተቆጥሮ ሚኒስቴሩ፣ ሃኪሙና የጦር ጠበብቶች ወደ አሜሪካ በመግባት እጅ መሥጠትን እንደ ታላቅ ድል ይቆጥሩት ጀመሩ። የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካም ሾሻሊስቱን ሥርዓት ስላንኮተኮተ ከበርቴዎች ልባቸው በእሳት እንደ ጋለ አሎሎ ፋመ። የቀዝቃዛው ዘመን ጦርነት ፖለቲካውን እያናጋ በመጨረሻ ሶቭየት ህብረት ስትፈራረስ ሶሺያሊዝም ከአውሮፓ ምድር እስከነአካቴው ተገረሰሰ። ዛሬ ላይ ሶሺያሊስታዊ የፖለቲካ መርህ በብቸኝነት የሚከተሉት ቻይና፣ ኩባ፣ ላኦስ፣ ቬትናም እና ሰሜን ኮርያ ብቻ ናቸው።

የምዕራቡ ዓለም ሶሺያሊዝም ከተጨናገፈ በኋላ ድሆች አገሮች እንዲከተሉት በሶሺያሊዝም ወይንም በአዲሱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ምትክ – ልማታዊ ዴሞክራሲ – የሚል ውጤት-አልባ የምጣኔ ኃብት ፖለቲካ ቀረጸላቸው። በድሆች አገሮች ላይ ያሉ ዜጎችም ከመንግሥተ ሠማያት ይልቅ ተስፋቸውን በኃብታሞች ምጣኔ-ኃብት እና በብልጭልጩ ከተሞች ላይ በማድረግ የብሱን፣ ውቅያኖሱንና አየሩን አቆራርጠው ወደ አውሮፓና አሜሪካ ይሰደዱ ጀመር። በሶሺሊዝም መፍረስ አንጀቱ ቅቤ የጠጣው የምዕራቡ ዓለም ዛሬ ደግሞ በስደተኞች ብዛት እየታመሰ ነው።

ዓለም ወዴት ትሄድ ይሆን?

የዓለም ሥርዓት ከእግዚአብሄር ሥርዓት ጋር ይበልጥ እየተጋጨ መጥቷል። በ 1517 ማርቲን ሉተር (Martin Luther) ያፋፋመው ፕሮቴስታንቲዝምና ከዚያ በኋላ የፈሉት የኃይማኖት ዓይነቶች አማኙንና ካህኑን ስለሚለያይ የክርስትና እምነት በሰሜን አውሮፓ አገሮች እንዲጠወልግ አድርጓል። የማርክስና ኤንግልስክ የኮሙኒዝም ርዕዮተ ዓለም (Marxism)እግዚአብሄር አልባ ምሁራን አብዝቶ ነበር። በጆን ሎክና ቶማስ ሆብስ (John Locke & Thomas Hobbes) የተቀነቀነው የሊበራሊዝ አስተምርሆ የፈለከውን አድርግ ተብሎ እንደተለቀቀ ሕጻን ሰዎችን መረን ለቋል። ፍልስፍና፣ የኃይማኖት ዓይነቶች መብዛትና የሊበራል ነጻነት በአውሮፓ የእምነት ጠንቅ ሆኗል።

ሴት ከሴት፣ ወንድ ከወንድ ለመጋባት አልያም ከሁለቱም ዓይነት ፆታ ጋር ለመገናኘት ወይንም ፆታን መለወጥ እንዲቻል የምዕራቡ ዓለም ሥልጣኔና ዴሞክራሲ ህጋዊ ሰውነት ቸሯል። ሰው ሠራሽ ማህፀን መክተት፣ በእንኩቤተር ውስጥ ፅንስን ማስወለድ፣ አባለዘርና እንቁላል ባንክ ማስቀመጥ ወይንም እንደ ሸቀጥ መግዛትና መሸጥ፣ ወዘተ ሥልጣኔው የወለደው አድናቆት የተቸረው የቴክኖሎጂ ውጤት ነው። ሊበራሊዝም ለወሲብ ፊልም ምርት ፈቃድ ይሠጣል። ኢ-ግብረገባዊ ትዕይንቶች አስተሳሰብን ማጨናገፍያ ቢሆኑም ሥርዓቱ ክልከላ አያደርግባቸውም። አንዳንድ የምዕራቡ አገሮች ቤተ ክርስትያናት የተመሳሳይ ፆታ ግኑኝነትን እንደ ፍቅር ቆጥረው የጋብቻ ሥርዓት ፈቅደዋል። ኦርቶዶክስ ኃይማኖትን የሚያራምዱት የምስራቅ አውሮፓ፣ እስልምና ኃይማኖት ተከታዮቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች፣ እንዲሁም አፍሪካና እስያ ይህን አይቀበሉም። ይህ ልቅ ምግባር የእግዚአብሄርን ትዕግስት ይፈታተናል። ይህ አስነዋሪ ባህልና እንግዳ ነገር ወደ አፍሪካ እንዳይገባ የኡጋንዳው ፕሬዚዴንት ሙሴቬኒ ብዙ እየታገሉ ነው።

እንግዲህ ምን ይበጀን?

 

የከበርቴው ሥርዓት የመደብ ትግሉን አጨናግፏል። ዛሬ የመደብ ትግል ቆሟል። ካፒታሊስቱ ዘመናዊ መኪና አለው፣ ሠራተኛውም ሁለተኛ-እጅ መኪና ይነዳል። ካፒታሊስቱ የግል አውሮፕላን አለው፣ ሠራተኛውም የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጦ ያሻው አገር ለጉብኝት ይሄዳል። ሠራተኛው በኅሊና እስር ውስጥ ስለሚገኝ፣ አሁን ትግል ለማድረግ አቅም የለውም። ኢትዮጵያ ደግሞ ልዩ ነች። በጨቋኝና ተጨቋን መደብ መካከል ያለው ትግል አድጎ – ጨቋኝ ብሄርና ተጨቋኝ ብሄር – ወደሚባል የትግል ደረጃ ተሸጋግሯል። ዳርዊን (Charles Darwin – On the Origin of Species)) በሚለው መጽሃፉ ስለ ፍጥረታት አዝጋሚ ለውጥ እንጂ ስለ አማራ አልጻፈም። ማርክስም አማራ ጨቋኝ ብሄር መሆኑን በፍጹም አያውቅም ነበር። ኤንግልስክም ቢሆን አማርኛ ቋንቋ ሌሎቹን ቋንቋዎች አታውሩ ብሎ ይቆጣቸው እንደነበር አላስተዋለም። እነዛ የኮሙኒዝም ሃሳብ አመንጭዎች – Guy Debord, Leon Trotsky, Antonie Pannekoek, Rosa Luxemberg, Karl Korsch – አንዳቸውም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሌሎች ኃይማኖቶችን ስለ መጨቆኗ አልጻፉም ነበር። ታድያ ስለ አማራ የተጻፈው የሠማሪ ስባሪ ያህል ስህተት ከየት ዱብ አለ?

የሚገርመው ይህ አዲሱ የብሄር ጭቆና ሳይንስ የተገለጸላቸው ተኩላዎች ነበሩ። ተኩላዎች አስበው፣ አውጥተው አውርደው፣ በሸንጎ ተቀምጠው አዲስ የማህብረሰብ ንድፈ ሃሳብ ላይ ደረሱ። “አማርኛ ጨቋኝ ነው” አማራ ጨቋኝ ነው” “ኦርቶዶክስ ጨቋኝ ነች” የሚል አዲስ ግኝት። “ቋንቋ የመጨቆኛ መሳርያ ነው” ሲሉ ተኩላዎች የዋሆችን አሳሳተው የቋንቋ ገጀራ አሰሩ።

እንግዲህ ምን ቀረ። ተኩላዎች በቁም ሲያባሉን “ሕይወት አለን” ብለን ልንዋሽ? ወደፊት መራመድ አቅቶን ወደ ኋላ እየተጓዝን ብናነባ ማን ሊደርስልን? የሚድን በሽታን መርቅዞብን እየተሰቃየን ነው። የዘር መድሎ አገዛዝ አበሳችንን እያሳየ ነው። ተኩላዎቹ ሥልጣናቸውና ሙስናቸው እንዳይጎድልባቸው ለልጆች የቋንቋ ገጀራ ሠጥተው “በሉት” ይላሉ። ተኩላዎች ልጃገረዶች የጋንግስተሮች መጫወቻ በሆነባት ሕጻናት በሚደፈሩባት አገር አሸሼ ገዳሜ ይላሉ። አሁንስ ግራ ግባን። ኃላፊነት የማይሰማቸው ባለሥልጣን መሬት ሲቸበችቡ እኛም ጥሬ ሥጋ እንመትራለን። ኢትዮጵያ አኬል ዳማ፣ የለቅሶ ምድር ሆና ሳለ ጓሮ ተሸሽገናል። እረ ምን ያልሆነ አለ፣ ተኩላው አስልቶ ሲሰለቅጥ የኃይማኖት አባቶችም ዝም ብለዋል። ኢትዮጵያ የትዕቢተኞች መሳለቅያ፣ የሃሰተኛ ሰባኪዎች መቀለጃ ስትሆን ምሁራን ምን አገባን ብለዋል። ተኩላዎቹ አፋቸው ላይ ያለው ደም ሳይደርቅ ለሌላ ጥቃት ሲዘጋጁ – ሲቀልቧቸው የከረሙት ፈሪዎች አሁንም መኖ ያቀርቡላቸዋል።

ዓለም ጉደኛ ሆናለች። አሳፋሪ ነገር አሰማምረው የሚዘግቡ ይወደሳሉ። የተፈጥሮ ህግ የሚጻረረውን ፍትህ ያላዘለውን ክስተት አንቆለጳጵሰው ማቅረብ የማይችሉ ጋዜጠኞች ይተቻሉ። ማህበራዊ መገናኛዎች አሳፋሪ ባህልን፣ እግዚአብሄር የሚጠየፈውን ነውር ይበትናሉ። ምዕራቡ ባነጠፈላቸው ቀጭን መንገድ የሚጓዙት ባለሥልጣናት ቪዛ ይታደላቸዋል። ሃቀኞች ማዕቀብ ይደረግባቸዋል። በዘመኑ ሥርዓት በጎች ሲያዝኑ ተኩላዎች ተስማምቷቸው ፈንጥዘዋል።

በርካታ የኦርቶዶክስ ልጆች በመሰደዳቸው ምክንያት እንዲያገለግሉ ወደ ውጭ የተላኩ አባቶችም ብዙ ናቸው ። ከመሃከላቸው ምሳሌዎች እንዳሉ ሁሉ በግል ኑሮ ላይ ተደምጠው ከምድራዊ ሥርዓት ጋር እያሸረግዱ ስደትን የሚያስዋቡ አባቶችም አልጠፉም። እንደ እውነቱ ከሆነ የኃይማኖት አባቶች ከማርክስም በላይ እኮ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ሊሆኑ በተገባ ነበር። ጎስቋላ የመሰሉ እውነተኛ አባቶች ኃይላቸው መንፈሳዊነታቸው ነው። የእውነተኛ አባቶች ምግብር ተኩላን ሲከላከል ያስመሳዮቹ ደግሞ ተኩላዎች ያበዛል። እየሱስ አስመሳይነትን (religious phonies) አይቀበልም። ግብዞችን፣ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ብዙ ጊዜ ተቃውሟቸዋል። (የማቴዎስ ወንጌል 23: 25-32)። ይህን ቁልፍ ቃል ያላነበበ አባት አይገኝም። አባቶች ጸጋቸውን እርግፍ አድርገው ትተው እሊበራሉ ዓለም ቢቀመጡ ምን ያገኛሉ?

አባቶች ካልገሠጹ አጥፊዎች ይበዛሉ፣ ኃይማኖት መቀለጃ ትሆናለች። ባተሌ ሥርዓት – ምርኮኛ ትውልድ፣ ዛሬን በልቼ ነገ ልሙት የሚል የመንፈስ ረሃብተኛ፣ እጎረቤቱ ያለውን ችግር የማያዳምጥ፣ እማዶ ያለው እሳት እርሱ ዘንድ የማይደርስ መስሎት ለማጥፋት የማይተጋውን በዋል ፈሰስ ቁጥር ይበዛል። አባቶች ካላስተማሩ ዓዕምሮውን አኮስሶ ለስጋው የሚሳሳ፣ ለነፍሱ አንዳች የመይጨነቀውን ፎቶግራፍ ተነሺና ሸቀጥ አምላኪ ሰው ይበዛል። ኃይማኖት ነች ከዚህች ዓለም የመረብና ቆቅ ኑሮ የምታሳርፈው።

ከመንግሥት ሙሰኞች አንስቶ እምልኮ ቤቶች እስከመሸጉ የበግ ተኩላዎች ድረስ ስግብግብነት አይሏል። ኢትዮጵያ የመዝባሪዎች መንፈላሰሻ፣ የወራሪዎች መቦረቅያ የተወራሪዎች መሰቃያ ሆናለች። አጭበርባሪዎች ወንጌሉን፣ የምስራች ቃሉን ምስኪን ማሳሳቻ፣ እንደ መሬትና ጉልበትና ተረፈ ምርት መዛቅያ፣ የማምረቻ መሳርያ (means of production) አድርገው ሲቀልዱ የሚገስጽ የሚቆጣ ጠፍቷል። ግብረገብና ሥነ-ምግባር ሲደበዝዙ ማን ይጠየቅ ታድያ? ሃላፊነትስ የማን ነው?

ተኩላው ዘመኑ እንዲጨቀይ በራስ ወዳድነት ላይ ንፉግነት ነስንሷል። ሃገር እየተቃጠለች “የቤት ግዙ ማስታወቅያ” ምንስ ሊፈይድ? የምስኪኑ ቤት በግፍ መፍረሱን እየሰማን የፈረሰው ቤት የነበረበትን መሬት ለመግዛት እንደምን ደፈርን? ተኩላው አዙሮ ማየትን እንኳን ሰልቦ እውር ማድረግ ችሏል። ተኩላው ምንስ ያላረገው አለ?ቤት አቃጥሎ ውሃ ያቀርባል፣ ገድሎ ሃዘን ይቀመጣል፣ ሰርቆ ያፋልጋል። ተኩላ እንደ አንበሳ ደፋር አይደለም፣ እንደ ነብር አትኩኝ ባይ አይደለም፣ እንደ እርግብ የዋህ አይደለም ወይንም ደግሞ እንደ እባብ ብልጥ አይደለም። ተኩላ ዓይን አውጣ ነው፣ በበጎች ማህከል የበግ ለምድ ለብሶ በማር የተለወሰ መርዝ ይረጫል። በስጋም በመንፈስም ፈሪ የሆነው ተኩላ አፍዝዞ አዘናግቶ በጎች በበላ ቁጥር ጥጋብና እብሪቱ ይጨምራል። እየሱስ የበግ ለምድ ከለበሰው ተኩላ ራሳችሁን ጠብቁ ያለው ለዚህ ነው።

ከንዋይም ከድሎትም ይልቅ የመንፈሠ-ሕይወት ልምላሜ ብቻ መፍትሄ መሆኑን ተረድተን ራሳችንን ከተኩላ ተገዥነት አላቀን ወደፊት ካልተራመድን በቀር ነፍሳችን በሕይወት ሳለን እንደታፈነች ትቀራለች። የበላን ቢመስለን አልበላንም፣ የጠጣን ቢመስለን አልጠጣንም፣ የለበስን ቢመስለን አለበስንም። ከመንፈሳዊ እርካታ ውጭ ሥጋ ከንቱ ነች። እውነትን የሚናገሩ፣ ለሃቅ የሚታገሉ፣ የተኩላዎችን መሠሪ ተግባር የሚያጋልጡ፣ ለሕዝብ ሲሉ ዘወትር የሚጮሁት፣ ለሃገር ሲሉ ራሳቸውን የጣሉ ብቻ ናቸው የውስጥ ደስታን የሚላበሱት። ለኩርማን እንጀራ ሲሉ መንበርከክ ውርደት ነው። ራስ ወዳድነት ደስታ አትጨምርም፣ ጭንቀትንና የኅሊና ወቀሳን እንጅ።

ባለፉት ዘመናት የሰው ልጅ ከጭቆና ለመውጣት ከገዥ መደቦች ጋር አንገት ላንገት ተያይዞ መብቱን አስከብሯል። ዛሬም መንፈሳዊ ኃይል ተላብሰን በሥጋ በርትተን በዓዕምሮ ተዘጋጅተን ሥጋችንን ቆርጥሞ መንፈሳችንን ከታትፈው ከሚበሉን ተኩላዎች መታደግ ይኖርብናል።

ማርክስ ዛሬ ላይ ቢኖር ምን ሊጽፍ ይችላል?

ምሁሩ ካርል ማርክስ ይህን ሁሉ ጉድ ቢያይ ምን እንደሚጽፍ አላውቅም። እርሱ ከጂዊሽ ቤተሰብ ተወልዶ ኋላ አባቱ ሥራ ለማግኘት ሲል ፕሮቴስታን እንደሆነ አንብቤአለሁ። ማርክስ ክርስትና እምነቱን ሙሉ ለሙሉ ይተው አይተው አላውቅም ግን የድሆች ስቃይ እንደሚቆረቁረው እገነዘባለሁ። ጀርመናዊው ማርክስ ዛሬ ቢኖር በተባ ብዕሩ ብዙ ይጽፍልን ነበር።

ካርል ማርክስ ኮሙኒስት ማኒፌስቶውን በጻፈበት ዘመን የመደብ ልዩነቶች ነበር የሚንጸባረቁት። ዛሬ ዓለም የተለየች ሆናለች። አንኳሩ ልዩነት – ሥልጣኔ በወለዳቸው ነውር ባህሎችና የቆዩት ጨዋ ባህሎች መካከል ሆኗል። እነሆ በዓይን አውጣው ተኩላና በዓይን አፋሩ በግ መካከልም ያለው የምግባር ልዩነት ጎልቶ ይታያል። ትግሉ በሠራተኛውና ከበርቴው መካከል መሆኑ ቀርቶ በሃገር ወዳዶችና አገር አፍራሾች መካከል ሆኗል። ቀድሞ ምሁራን ለጭቁኖች ሲሉ እስከ መስዋዕት ይታገላሉ። ዛሬ ምሁራን ለሥልጣን ሲሉ ደሆችን ያስፈጃሉ። ዘመኑ አስመሳይና እውነተኛ ምሁራንን ከጽንፍ እስከ ጽንፍ አራርቆአቸዋል። ማርክስ ይሄን ሁሉ አላየም ነበር። ማርክስ ይህችን ዓለም ከተሰናበተባት ቀን ጀምሮ ሥነ-ምግባር ላሽቋል ግብረገብ ጠውልጓል።

ሌኒን ዛሬ ነገ ይሰናበታል ያለው ካፒታሊዝም አምሮበት በማናህሎኝነት ተወጥሯል። ኢምፔርያሊዝም ድሮ ጥሬ ኃብት ፍለጋ ነበር ወደ አፍሪካ የሚመጣው። ዛሬ ነውር ባህሎችንም ጭምር አስከትሎ ነው ሠተት የሚለው። ማርክስ ይሄን ሁሉ አላየም። ሠለጠንን በሚሉት አገሮች ላይ ነውርም ሠልጥኗል። በኢ-ገብረገባዊ ነውርና ባህላዊ ሥነ-ምግባር መካከል የሚታይና የማይታይ ትግል መኖሩ ዛሬ ላይ ነው ገሃድ የወጣው። ማርክስ ይሄንንም አላየም ነበር። በኔቶና ሩስያ መካከል ያለው ግብግብ ጋብ ካላለ ዓለም አስፈሪ መከራ ውስጥ ልትዘፈቅ ትችላልች። በማርክስ ዘመን ይሄ ነገር ጎልቶ አይታይም ነበር።

በዓለም ላይ “አስነዋሪ ባህሎችን በሚጠየፉ ባህላዊ ወግ-አጥባቂ ወይንም ኃይማኖታዊ በሆኑ ሰዎችና “ፆታዊ መብቱ የግለሰቡ ምርጫ ናቸው” በሚሉት ሊበራል ሰዎች መካከል ያለው የመንፈስ ውጊያ ጠንካራ ሆኗል። ማርክስ ይህ መንፈሳዊ ክስተት አውሮፓን እንደሚያምስ እምርምሩ ውስጥ ያካተተ አይመስለኝም። ማርክስ ዛሬ ቢኖር በቅኝ ገዥዎች ሲጨቆኑ ለነበሩ አገሮች ምሳሌ የሆነች ኢትዮጵያ እንዲህ በዘር ተከፋፍላ የአርበኞች ልጆች በተኩላዎች የሚበሉባት መሆኗን ሲያይ ምን እንደሚሰማው አላውቅም። ማርክስ ስለ መደብ ትግል ነበር የጻፈው።

ማርክስ ተኩላዎች የጨቋኝና ተጨቋኝ ብሄረሰቦች ትግል ቀምረው አማራ የሚሉትን ዘር ሊያጠፉ ሲያደቡ ሲያይ ሊገረም ይችላል። እርሱ የዓለም ሠራተኞች፣ ወዛደሮች ወይም ላብ አደሮች ተባብረው አዲሲቱን የጋርዮሽ ዓለም ይመሰርታሉ የሚል እምነት እንጂ የዘረኝነት መንፈስ ነግሶ ኢትዮጵያን የመሰለ ጥንታዊ አገር እንደሚበታትን ጨርሶ አላሰበም። ዞሮ ዞሮ ማርክስ ዛሬ ላይ ቢኖር ኢትዮጵያን በሚያምሰው የዘር አምሳልና ስለ ኃያሉ የኢግዚአብሄር ቁጣ እንዲህ ብሎ ይጽፋል ብዬ ገመትኩኝ።

A Holy Ghost is haunting wolves in sheep clothing – the Ghost of the Spirit of God. All the powers of New tribalist Ethiopia have entered a group alliance to fight the Holy Ghost. PP and OLF, TPLF and secession advocates, Fake Pastors and Glutton Amharas.

The history of all hiterto existing Ethiopia is the history of God (neither the tribalists nor the corruptors can divert the flow of God history) The beatitude and the misery (cursitudes), the honest(the just) and the cheater(unjust), the true teacher (the good) and the imposter (the evil), the sheep of God and the wolf of Satan, in a word, the blessed and the sinner, stood in constant opposition to one another, carried an interrupted, now hidden, now open fight, that each time ended, either by the wrath of God (the wrath of God will be a day of distress to the wicked. God will do this in perfect justice) or by common ruin of the sinful world by its own wicked decisions (Gods anger is always a response to human betrayal and evil, and it is expressed through handing humans over to the logical conquence of their decisions. In other words, Gods anger is expressed by giving humans what they want, or at least, what they have choosen) and the wolf of satan shall forfeit.

 

አምላካችን እባክህ ፊትህን መልስልን፣ እኛንም አበርታን፣

እንግዲህ ማርክስ የተመኘው – የዓለም ወዛደሮች ተባበሩ – (workers of all countries – UNITE) መፈክር አልሠራምና በዓለም ያላችሁ ለማህበራዊ ፍትህ፣ ግብረገብና ሥነ-ምግባር የምትቆረቆሩ ሁሉ ተባበሩ። (Advocates of social justice, moral and ethics of all countries – UNITE!!!) ተኩላዎቹ እነዛን በጎች ሲበሉ እኛ ዘንድ አይደርስም ያሉ በጎች የዋህ ናቸው። ሌሎቹ በጎች ሲራቡ እኔ እየበላሁ ነው የምትሉ በጎች ተሳስታችኋል። ተኩላው ማንንም የበግ ዘር አይመርጥም። ዘረኝነት ገደብ የለውም። ሁሉም ተባብሮ ተኩላውን ማባረርያ ቀን ዛሬ ነች። ምን እስከሚኮን ነው ዳተኛነቱ። እግርና እጃችንን አጣምረን በመቀመጥ ጨዋ ባህላችን፣ እሴቶቻችን፣ ኢትዮጵያዊ ቅድስናንችን ዳግም ማስመለስ አንችልም። ለመደብ ትግል የተነሳን ብርቱ ሕዝብ ዘረኝነትን መታገል አያቅተንም። እዚያና እዚህ ሁከት እየፈጠሩና ሥራ ፈት እያደረጉ ሥጋና ዓዕምሯችንን ደካማ የሚያደርጉንን ተኩላዎች የምናሸንፈው በመንፈስ በርትተን ስንቋቋማቸው ነው።

ሃገራችን – መሪዎቿ – መርህ-አልባ፣ ርዕዮተ-ዓለም የለሽ፣ ምግባረ-ቢስ እና እውቀት-ያጡ – ሆነውባታልና እነሆ መከራዋ ጸንቷል። ኢትዮጵያ ምጧ በዝቶ ጎንበስ ብላለች፣ ሃዘንና ጽልመት ለብሳለች። ኢትዮጵያዊ በየቀኑ በሚከሰተው የዋጋ ንረትና (high inflation)የገንዘብ የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል (weak currency) ሳብያ ቆሞ መሄድ ተስኖታል። ምርቱን ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቂት ባለጊዜዎችና መዝባሪዎች ይከፋፈሉታል (unfair distribution of wealth)። ኢንዲስትሪዎች በአቅርቦት መቋረጥ ሳብያ የምርት ውጤታቸው አሽቆልቁሏል (total output declining)። በሃገሪቱ ሥራ አጥነት እጅግ ከፍ ብሏል (high unemployment)፣ የደሞዝ ጭማሪ አይደረግም (no wage increase) የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ ተጨናግፏል (stagnant economy)። ኢትዮጵያውያን የመኖር ዋስትና አተዋል። በዚህ ሁሉ ሰው ሠራሽ ግፍ ላይ – ግድያ፣ መፈናቀል፣ ቤት ፈረሳ፣ እስር፣ የዘር መድሎ፣ ሙስና፣ ቅርስን ማጥፋት፣ እብሪት፣ ጥጋብ፣ ወዘተ፣ ሲጨመር ሕዝብ እምን ሲዖል ውስጥ እንዳለ ማንም መገመት ይችላል። ትላልቅ ነጋዴዎችና ሸሪኮቻቸው ባለሥልጣናት የኢትዮጵያን ኃብት አሟጠው እውጭ እያሸሹ ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንደምን ድሆች ልጆቻቸውን ማሳደግ ይችላሉ? ትግል ብቻ ነው ከሲዖል ኑሮ የሚገላግለው።

በተኩላዎች የሚመራው የጨቋኝና ጨቋኝ ብሄረሰቦች ትግል አማሮችን ለማጥፋት እጅግ አሰቃቂና ለማውራት የሚዘገንን ጥቃትና መፈናቀል እያካሄደ ነው። ጥንታዊቷ እግዚአብሄር አጽንቶ ያቆያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ከገዥዎች ጋር በተባበሩ የበግ ለምድ ለባሾች እየታመሰች ነው። መከራ ተሸካሚው ሕዝብ ወደ እግዚአብሄር ልመናውን ለማቅረብ እቤተ ክርስትያን ሲጠጋ መግቢያው ላይ የቆሙት ጠብደሎች አትገባም ይሉታል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊነት ወንጀል ሆኗል እንዴ? ተኩላዎቹ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ለማፍረስ የሚያደርጉት ክፋት ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ መጋፋት እንደሆነ ፈጽሞ አልተረዱም። ዋ! ለባለ ጊዜዎች – እየሱስ በመቅደስ ውስጥ በሬዎች፣ በጎች፣ ርግቦች ሲሸጡ ተመልክቶ ጅራፍ አበጅቶ አስወጥቷቸዋል። “እየሱስ ቤቴ የጸሎት ቤት ነው” ነበር ያላቸው። እግዚአብሄት ለቤቱ ቀናዒ (zeal for His house) ነው። ዛሬም ጅራፉን ያነሳል። (የዮሐንስ ወንጌል 2: 13-17)፣ ( የማቴዎስ ወንጌል 21: 12-17)

እግዚአብሄር ትዕግስተኛ ነው እንጂ ሉዓላዊነቱን አያስደፍርም። ታሪክ ከእግዚአብሄር ሥራ ውጭ ባዶ ነች (History without God`s Action is Nothing)። ይህች ዓለም የእርሱ ናት፣ በአምላካዊ ጥበቡ ነው ካለምሰሶ ያጸናት። ቢያፈርሳትም፣ ቢያንዳትም እርሱ ሲል ብቻ ነው። የእርሱን ሥራ መርምረን አንደርስበትም። የዚህች ዓለም ጭነት ከባድ መሆኑን እንዲሁም ጽድቃችን እንኳን መርገም እንደሆነብን ያወቀው ቸር አምላክ ነው ጸሎታችን እርሱ ዘንድ ይደርስልን ዘንድ ነበልባሉንና ሐመልማሉን ያዋሃደች ቅድስት እናታችን ድንግል ማርያም አማላጅ ትሆነን ዘንድ የሠጠን። ፍጥረትን፣ ግዑዝም ሆኑ ሕይወት ያላቸው፣ ሁለት ሁለት አድርጎ በአንድነትና በልዩነት (same and difference) ፈጥሯል። ይህ አምላካዊ ሥራው በሠይጣን ሲደፈር ዝም ብሎ አያይም።

ተኩላዎችን የወከለው ሠይጣን ዓላማው ኢትዮጵያን ከፋፍሎ፣ ዘርን ከዘር አባልቶ፣ ሕዝብን ከእግሩ ስር አድርጎ ማስራብ ነው። በእርግጥ ተኩላዎች እንዳሻቸው ሲዘባነኑ እግዚአብሄር ቁጣውን ያወርዳል። ካልታገልናቸው በቀር ተኩላዎቹ አይራሩልንም ።

ቅዱስ መንፈስ የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎችን እያመሰ ነው – የእግዚአብሄር መንፈስ አምሳል። ይህን መንፈስ ለመዋጋት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዘረኞች የዘር ፍጅት ስምምነት ላይ ደረስዋል፤ ብልጽግናና ኦነግ፣ ሕወሃትና የመገንጠል ተሟጓቾች፣ ሃሰተኛ ፓስተሮችና ሆዳም አማሮች።

እስከዛሬ ድረስ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ ባለቤት እግዚአብሄር ነው። ብፁዓንና ክፉዓን – ሃቀኛውና መንታፊው – ትክክለኛው መምህርና አስመሳዩ – የእግዚአብሄር በግና የሠይጣን ተኩላ – ባንድ ቃል ጻድቃንና ኃጥዓን – አንዳንዴ በሚታይ አንዳንዴ ደግሞ በማይታይ መንፈሳዊ ትግል ውስጥ ናቸው። እግዚአብሄር ጻድቃንን አሸናፊ ሲያደርግ ኃጥዓንን ደግሞ በገዛ ራሳቸው ክፋት ይጥላቸዋል፣ የሠይጣኑ ተኩላም ይሸነፋል።

አምላካችን ሆይ! መጨረሻው ይህ ሆኖ ሳለ ራስ ወዳድ፣ ዳተኛ፣ አስመሳይ፣ ፈሪ፣ አታድርገን። መች እንዲህ ነበር ፈጣሪ! የአናብስት ምድር ኢትዮጵያ እኮ እንደዋዛ የተኩላዎች መፈንጫ ሆነች። እባክህ እግዚአብሄር አንበሶች ነብሮችን እያባረርን በተኩላዎች የምንገዛ አታድርገን። አምላካችን እባክህ የቀደመ ኃይላችንን መልስልን፣ አበርታን፣ አሜን።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop