የእንጦስን መመነን በታሪክ የማውቀው፣
በእስክንድር ነጋ ዘንድ አጅግ ደምቆ ሳየው፣
በምን ቋንቋ ጥፌ እንዴትስ ልግለጠው፣
አጥሮኝ የምያውቅ ቃል ዛሬ እያጠረኝ ነው፡፡
እንጦስ ድሎት ትቶ ገዳም የመነነው፣
ዓለምን ታዝቦ ለራስ ንስሃ ነው፡፡
ቅምጥሉ እስክንድር ምነና የሄደው፣
የሕዝብን አበሳ መከራ ሊገፍ ነው፡፡
እንደ ኢዮብ ጽናትን ክንብንብ ያረገው፣
እንደ ጴጥሮስ አለት አርጎ የፈጠረው፣
እንደ እስጢፋኖስም ብሩህ ያደረገው፣
በዚህ በእኛ ዘመን እስክንድር ነጋን ነው፡፡
ስንቱ እባብ ሰይጣንን አምኖ ሲከተለው፣
ሰባኪን በሥራው መዝኑ ሲልም ያስተማረው፣
አምላክ የመረጠው እስክንድር ነጋ ነው፡፡
በእስር ቤት ምስሉ ብር የሰበሰበው፣
አዳራሽ ውስጥ ሞልቶ ተጎንህ ነን ያለው፣
ጓደኛ ትግል አጋር ሲለው የነበረው፣
ዶሮ አንዴ እንኳን ሳይጮህ ደጋግሞ ሲከዳው፣
ተይሁዳ ብሶም አቃጥሮ ሲሰጠው፣
ተእምነት ተማተቡ ዝንፍ እንኳ እማይለው፣
ቃሎች የማይገልጡት እስክንድር ነጋ ነው፡፡
እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ስንቱ እሚያሳድደው፣
ፌስታል ያዥ እያለ ከብቱ የሚሰድበው፣
በዚህ ክፉ ዘመን የተመረጠው ሰው፣
አምነን እንቀበል እስክንድር ነጋን ነው፡፡
ጳውሎስ በእምነት ፀንቶ በምድር የታገለው፣
አንደ እስክንድር ነጋ ሲከሰስ ሲታሰር ሲፈታ የኖረው፣
ለሰላሳ አራት አመት ታሪክ እንደሚለው፡፡
ጳውሎስና ጴጥሮስ በተፈጥሮ ሰዎች የነበሩ ናቸው፣
ዛሬ የሚኖሩት ከአጥናፍ አጥናፍ ገዝፈው፣
ይህችን አላፊ ዓለም ከልባቸው ንቀው፣
አንገት ስለሰጡ በእምነታቸው ጸንተው፣
ዝንፍ ስላላሉ ጓደኛ ተከታይ በጥቅም ቢከዳቸው፡፡
በጳውሎስ በጴጥሮስ የተፈጸመውን አሕዛብ እንዳይደግመው፡፡
ሴቷ መቀነቷን ወንዱ ቀበቶውን አጥብቆ ይሰረው::
ህፀፅ ነው ህፀፅ ነው ህዝብ ሆይ ህፀፅ ነው፣
ዝም ብሎ መቀመጥ ጻድቅን እርጉም ሲያስረው፣
እርሱስ ይችለዋል ሕዝብ እዳው የኛ ነው፡፡
በላይነህ አባተ ([email protected])
የካቲት ሁለት ሺ አስራ አምስት ዓ.ም.