“መቼም ቢሆን በድል ሰክረን አንተኛም ” ሜጀር ጄነራል ሙሉዓለም አድማሱ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ

አዲስ አበባ፡- አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስካልተወገደ ድረስ የኢትዮጵያ ስጋት መሆኑ ስለማይቀር መቼም ቢሆን በድል ሰክረን አንተኛም ሲሉ የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄነራል ሙሉዓለም አድማሱ ገለጹ።

ሜጀር ጄነራል ሙሉዓለም አድማሱ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እስካልተወገደ ድረስ የኢትዮጵያ ስጋት መሆኑ አይቀርም።የሽብር ቡድኑ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስለማይተኛ እኛም መቼም ቢሆን በድል ሰክረን አንተኛም ብለዋል።

ጦርነት ለሽብር ቡድኑ የመኖርና ያለመኖሩ ጉዳይ ስለሆነ ከዚህ በኋላም ቢሆን ወረራ ለማካሄድ ሊሞክር ይችላል ያሉት ሜጀር ጄነራል ሙሉዓለም፤ የሽብር ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ በሰው ኃይል፣በትጥቅና በመሳሪያ ተዳክሟል፤የሞራል ውድቀትም ደርሶበታል፤በተቃራኒው በወገን ኃይል የድል ባለቤት በመሆኑ የበለጠ መነሳሳትና ወኔ ተፈጥሯል፣በቂ ዝግጅትም ተደርጓል፤፤ ከአሁን በኋላ የሽብር ቡድኑ ከስህተቱ ሳይማር ቀርቶ ወደ አፋርም ሆነ አማራ ክልሎች እስፋፋለው ቢል ፍም እሳት ይጠብቀዋል ብለዋል።

አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተንና መንግሥትን ለመጣል ዕቅድ ይዞ ያለ የሌለ ኃይሉንና የቀበረውን መሳሪያ አሰባስቦ አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ያደረገው መፍጨርጨር መና እንደቀረና በጀግናው መከላከያ ሠራዊትና በጥምር የጸጥታ ኃይሎች ተቀጥቅጦና ድባቅ ተመትቶ ወደ ኋላ የተመለሰ መሆኑን አውስተዋል።

አሁንም ቢሆን የሽብር ቡድኑ ለኢትዮጵያ አይተኛላትም ያሉት ሜጀር ጄነራሉ፤እኛም ሁሌም በተጠንቀቅ ላይ ነን።የጸጥታ ኃይላችን በየጊዜው እያደራጀን፣ እያሰለጠንና በቂ አቅም እየገነባን መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጎናችን አሰልፈን አሸባሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ እናደርሰዋለን ብለዋል።

‹‹ባለንበት ግንባርም የሕዝቡ ፣ የሠራዊቱና የአካባቢው የጸጥታ ኃይል ወኔና አቅም ከፍተኛ ነው፤የሕዝባችንና የአካባቢውን የጸጥታ ኃይሎች አቅም ተጠቅመን አሸባሪው ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላምና ስጋት እንዳይሆን በንቃት እንሰራለን፣መቼም ቢሆን በድል ሰክረን ቁጭ አንልም›› ብለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለነጭ ፈረስ አትሁን - ድምፃዊ አቡሽ ዘለቀ እያለቀሰ ያስተላለፈው መልዕክት -ጦቢያ

ሰሞኑን ለመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች የተሰጠው የማዕረግ ሹመት ለተጨማሪ ድል የሚያነሳሳ መሆኑን አመልክተው፤የማዕረግ ሹመቱ በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን ላይ ድል ተቀናጅተን ኢትዮጵያ ላይ ተቃጥቶ የነበረውን አደጋ በቀለበስንበት ማግስት መካሄዱ ይበልጥ የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል።

አሁንም የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን በድል ሳንዘናጋ እየሰራን ነው ያሉት ሜጀር ጄነራል ሙሉዓለም፤አሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ የምናጠፋበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል።

ጌትነት ምህረቴ

አዲስ ዘመን ጥር 4/2014

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share