በጭራቆች ተጨፍጭፈው በሞቱት ሰማእታት ሥም ይቅርታ ተቀባይና ምህረት አድራጊ እንድትሆኑ ማን ቀባችሁ?
በላይነህ አባተ ([email protected])
ይህ አድግ ቁጥር ሁለት ሳይመጣ “የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነን፣ የነፃነት ጋዜጠኞች ነን፣ ተቀዋሚ ድርጅት ነን፣ የህግ ባለሙያ ነን፣ የኢኮኖሚ ጠበብት ነን ወዘተርፈ” ሲሉ ኖረው ከአራት ዓመታት ወዲህ “የሙሴና ኢያሱ” ተከታይ ብቻ ሳይሆን አምላኪዎች ሆነው አረፉ፡፡
እነዚህ ጉደኞች “ የይህ አድግ ቁጥር ሁለት መሪዎች ይቅርታ ስለጠየቁና ኢትዮጵያን ከፍ ከፍ አድርገው ስለተናገሩ ምህረት በማድረግ ደግፈን ተክተልናቸው ነበር” እያሉ ጅብ የመሰሉ አድጎች በመንጋጋችቸውና በምግጭላቸው ግጠው በፈጠሩት የሕዝብ ቁስል ላይ ስንጥር እንጨት እየሰደዱ ይገኛሉ፡፡
የሙሴዎችና የኢያሱዎች ተከታይ “ወደ ይህ አድግ ሰዎች ሆይ?”
ባለፉት ሰላሳ አመታት ውስጥ በጋምቤላ፣ በኦጋዴን፣ በአምቦ፣ በአዋሳና አማራ በሚኖርበት በማንኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በአገዛዙ ታጣቂዎች እንደታጨደ፣ በወህኒ ተገርፎና ተጠብሶ አንዳለቀ፣ እንደመከነና ሲሰደድም የጅብ እራት ሆኖ እንደቀረ ታውቃላችሁ፡፡
እና በዚህ ለሰላሳ ዓመታት በተጨፈጨው ሕዝብ ሥም ይቅርታ ተጠያቂና ምህረት ሰጪ አድርጎ እናንተን ወደ ይህ አድግ ሰዎችን ማን ሾማችሁ? እግዚአብሔር በመንፈስ ታይቶ ተወካይ አደረጋችሁ ወይስ ሰማእታት ከመጨፍጨፋቸው በፊት ለጨፈጨፏቸው አረመኔ ጭራቆች ምህረት እንድታደርጉ ፊርማ ትተውላችሁ አለፉ?
ዓይናችሁን እንደ ወፈጥ አፍጣችሁ በሰማእታት ሥም ምህረት አድርገናል ስትሉ ህሊናችሁን የጉንዳን ያህል እንኳን አይቆነጥጣችሁም ወይ? እንኳን እናንተን ዓይነ ፈጣጣዎችን ቋሚ የሙታን ልጆች ወይም ወላጆችስ ይቅርታ እንዲያደረጉ ቃላቸውን ባልሰጧቸው የጭራቆች ሰለባዎች ሥም ምህረት የማድረግ መብት አላቸው ወይ?
ጭራቆቹን ሲታገል በአንቦ፣ በጎንደር፣ በባህርዳር፣ በዳንግላ፣ በወልዲያ፣ በአዲስ አበባ ወዘተርፈ በአረመኔ ባሩድ የተበረቀሰው ወጣት ጭንቅላት የእናንተ ጭንቅላት ነወይ? በአረመኔዎች ላይ ስታምጥ የተበሳው የሽብሬ ደረት የእናንተ ደረት ነወይ? በኦጋዴን እሬሳው የተጎተተው ጎበዝ ገላ የእናንተ ሬሳ ነውይ? ወለጋ እናቱ እንዲቀመጡበት የታዘዙት አስከሬን የእናንተ ነወይ? በጋምቤላ በመደዳ የተረፈረፈው የሬሳ ክምር የእናንተ ነወይ? የእናንተ ታልሆን እንደ ዝንብ ወተት ጥልቅ ብላቸሁ ይቅርታ ተጠያቂና ምህረት ሰጪ ያደረጋችሁ ማን ነው?
ናዚዎች ዛሬ እንኳን በዘጠናና በመቶ ዘመናቸው በዓለም ላይ እየተለቀሙ ለፍርድ በሚቀርቡበት ሰዓት ምነው እናንተ በክቡሩ የሰው ነፍስ እየቀለዳችሁ በሌላ ሰው ነፍስ ራሳችሁን ይቅርታ ተጠያቂና ምህረት አድራጊ ሾማችሁ ድግሷ እንዳማረላት ወይዘሮ ቂጣችሁን ወዲያ ወዲህ ተማማታት አልቆጠብ አላችሁ?
ወደ ይህ አድግ ሰዎች ሆይ! ፍትህ የሌለው እርቅና ሥራ የሌለው እምነት የሞተ መሆኑን መገንዘብ ምነው ተሳናችሁ? ፍትህን እንጦሮጦስ በመወርወር በሰማእታት ነፍስ ይቅርታ ተቀባይና ምህረት አድራጊ እንድትሆኑ ማን ቀባችሁ?
ጥር ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.