የመስቀል አደባባይ ታሪክ – ገለታው ዘለቀ 

Meskel squreበኢትዮጵያ የአርበኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራ ትተው ካለፉት አባቶች መካከል ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ይታወሳሉ :: ራስ ብሩ ወልደገብርኤል ያደጉት በአፄ ምኒልክ ቤተመንግስት ውስጥ ነበር :: ብሩ ወልደገብርኤልን አፄ ምኒልክ እጅግ ያቀርቧቸው ነበር:: እንዴውም ብሩ ወልደ ገብርኤል የአፄ ምኒልክ የሚስጥር ልጅ ነው ተብሎ በቀበሌው በሀገሩ ሁሉ ይወራ ነበር ::
ራስ ብሩ የራስ ማዕረግ እስኪያገኙ ድረስ በሀገሪቱ ጦርነት ውስጥ አንፀባራቂ ድል አስመዝግበዋል :: በማይጨው ከባድ ተጋድሎ ያደረጉ ጀግና መሪ ነበሩ :: የጦር ሚንስትር ሆነውም አገልግለዋል :: እኒህ መሪ እጅግ ሀብታም ነበሩ :: በዘመኑ የራስ ብሩን ያህል ግብር የሚያበላ አልነበረም ይባላል :: ግብር ማብላት እንደ ብሩ ወልደገብርኤል ነው ይባልላቸው ነበር :: ታዲያ የእኒህ ሰዉ ርስት የት ነው? ከተባለ አሁን መስቀል አደባባይ የምንለው ቦታና የኤግዝብሽን ማዕከሉን ሁሉ ያካተተ ነው :: መስቀል አደባባይ ቀደም ሲል የራስ ብሩ ሜዳ ነበር የሚባለው :: ራስ ብሩ በህይወት እያሉ ከይዞታቸው ላይ ቀንሰው የራስ ብሩ ሜዳ የሚባለውን ለመሰቀል ለደመራ ማክበሪያ ይሆን ዘንድ ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሰጡ :: ከዚያ በሁዋላ ኦርቶዶክስ ይዞታዋ ሆኖ ቆየ :: ስሙም ከራስ ብሩ ሜዳ ወደ መስቀል አደባባይ ተቀየረ:: ኦርቶዶክስ ራስ ብሩን ባርካ ይህንን ቦታ የአምልኮ ስፍራዋ አድርጋ ስትኖር ድንገት ደርግ መጣ :: ደርግ ሲመጣ መስቀል አደባባይን ለአብዮቱ ጥሩ አደባባይ ነው ብሎ አመነና ይህንን ቦታ ለራሱ መረጠው:: ስለሆነም ስሙን አብዮት አደባባይ ብሎ ሰይሞ የራሱ አደረገ :: በዚህ መሃል የራስ ብሩ ወልደግብርኤል ልጆች ሸፈቱ :: መስፍን ብሩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፖለቲካል ሳይንስ ያስተምር የነበረውና መርድ ብሩ የጦር ትምህርት ተምሮ የአፄ ሃይለስላሴ የቅርብ ሰዉ የነበረው የራስ ብሩ ልጅ ተያይዘው የአባታቸው ዘመዶች ሀገር መንዝ ገብተው ሸፈቱ :: መንዝ ውስጥ ባዶጌ የተባለች ቀበሌ ውስጥ የእኔን እናት ዘመዶች በሙሉ አስታጥቀው ከደርግ ጋር ተዋጉ :: እነ መርድ  የአባታቸው ዘመዶች ጋር ማለትም የእኔ እናት ወይዘሮ በቀለች ደባልቄ ዘመዶች ጋር ሆነው ደርግን አምስት ዓመት ተዋግተዋል:: መርድና መስፍን ሲዋጉ ቆይተው የተሰውት እዚያው እኛ አካባቢ ነበር:: ብዙ የእናቴ ዘመዶች ከደርግ ጋር በነበረ ውጊያ ተዋድቀዋል ::
ታዱያ ከፍ ሲል እንዳልኩት ራስ ብሩ ይህንን መስቀል አደባባይን ለኦርቶዶክስ ከሰጡ በሁዋላ ደርግ ወስዶ አብዮት አደባባይ አድርጎት ኖረና ኢህአዴግ ሲመጣ ይህ ቦታ የቤተክርስቲያንም የመንግስትም መጠቀሚያ ሆነ :: ኦርቶዶክስ ጠንከር ብላ ማምለኪያዋን አላስመለሰችም :: ኢህአዴግ ደርግ የወረሳቸውን አንዳንድ ማምለኪያ ቦታዎች ሲመልስ መስቀል አደባባይን ችላ ብሎት ቆየ :: እስከማውቀው ድረስ አሁንም ይህ ቦታ የኦርቶዶክስ ነው :: ቦታው ተመልሶ ለቤተክርስትያንቱ መሰጠት አለበት ብዬ አምናለሁ :: ታሪኩ ከራሴ ቤተሰብ ጋር የተያያዘ ነገር ስላለው ሃሳብ ልስጥ ብዬ ነው ::
ይህ ሁሉ ሆኖ ኦርቶዶክስ ይህንን ቦታዋን ሕጋዊ በሆነ መንገድ እስክትረከብ ድረስ ፕሮቴስታንቱ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ መቃወም ተገቢ አይደለም :: ሌሎች ሃይማኖቶችም ፕሮግራም ሲያደርጉበት አይተናል :: ደርግ የደም ቀለም ያለው ጠርሙስ ሰብሮ ቀይሽብር ያወጀበት ቦታ ነው :: ይህ ቦታ ለቤተክርስቲያን በግልፅ እስኪመለስ የኦርቶዶክስ አማኞች ሕጋዊ ፈቃድ ካገኙ የፕሮቴስታንት አባላት ጋር መጋጨት የለባቸውም :: እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ:: መንግስት የሃይማኖት ቦታዎችን በግልፅ ከለየ መጋጨት አይኖርም :: ማምለኪያ ቦታ እንደልብ አለና አንጋጭም::

1 Comment

  1. ሃይማኖት ሲባል ሁሌ አተካራ አመንጪ ነው። ሰው እንደማተቡ ቢያድር ኑሮ ችግር አይፈጠርም ነበር። ግን የእኔ እምነት ከእናንተው ይሻላል እየተባባለን ስንዣለጥ ዓለም ጥሎን አለፈ። የማንም አምልኮትና አምላክ ከማንም አይበልጥም። ግን ያው ሁሌ መናቆር ልምዳችን በመሆኑ መስቀልና ሽጉጥ የያዘው ቄስና ዲያቆን፤ ነብይ ነኝ ብሎ ሰው የሚያታልለው፤ ፈዋሽ ነኝ ብሎ ይህን አምጡ የሚለው አታላይ የተጠራቀመባት ሃገር በመሆኗ የቦታ ግፊያው እንታይ ለማለት እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም። ሥፍራው ለሁሉም እምነቶች ይበቃል። በእቅድ፤ በወረፋ፤ እስላሙም ሆነ ከርስቲያኑ ቢሰበሰብበት ችግር አይኖረውም። ደግሞስ ስንት የማምለኪያ ስፍራ በሃገሪቱ ሞልቶ በዚህ ግርግር ማስነሳት ካለብን እብደት ላይ አብሾ መጠጣት ነው። በምድሪቱ ማንም የተቀደሰ የለም። አረከሱት ገለመሌ ማለት ጸያፍ ነው።
    እረፉ እናንተ የሃይማኖት ሰዎች። ኡኡታ ባይ ላላገኘው ለወሎ ለአፋር፤ ለጎንደርና ለሽዋ ህዝብ ድምጽ አሰሙ። ሌላው ጥሩንባችሁ ሁሉ ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን ግን አላይ አይነት ነው። እስከ መቼ ነው በሰው ላይ የምትነግድት? መቼ ነው ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን የምትጀምሩት? ፓለቲካና ሃይማኖት ሲቀየጥ የሚፈጥረው ሃበሳ ዘግናኝ ነው። ተው! መጋጨትን ከመጠማት ነገርን ማርገብ አስፈላጊ ነው። በእኔ እይታ ሁሉ ነገር አሻሮና ለራስ ብቻ ቋሚ ነው። የሰማይ ቤት አለ እያለ የራሱን ቤት የሚሰራ፤ ምንም ክሌላቸው ምስኪኖች እየሰበሰበ የሚዘርፍ የእምነት ተቋማት የራስን ኑሮ ከማመቻቸት ዘለው ልክ እንደ “ማዘር ቴሬሳ” መኖር እስካልቻሉ ድረስ ለእኔ ኦርቶዶክስ በለው ፕሮቴስታንት በሰው ላይ ሸክም ማብዛት እንጂ ሰማይ የሚያደርስ ነገር የላቸውም። በቃኝ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.