እኔ ከራያ ልጅ እኔ ከዲቢ ልጅ ፈሪ ቢገኝብኝ፣ በመኪናው መንገድ ኦራል ይነዳብኝ

Fano 4ከዞብል ተራራ ግርጌ፣ ከመንጀሎና አራዱም ተራራዎች ባሻገር፣ ከጎሊና እና ከሆርማት ወንዝ መገናኛ ላይ ነኝ። በተራራዎቹ ውበት እየተደነኩ፣ በጋራና ሸንተረሩ መውዜራቸውን አንግተው፣ ጩቤያቸውን በወገባቸው ሸጉጠው፣ ሽርጣቸውን አገልድመው የሚሄዱትን ጀግኖች እየተመለከትኩ፣ በጎሊና እና በሆርማት ውኃ መንፈሴን እያደስኩ፣ የጀግኖችን አረማመድ እየታዘብኩ ነው። በራስጌዬ ያለው ዞብል፣ በአሻገር ያሉት መንጀሎና አራዱም ተራራዎች ለአያሌ ዘመናት ጀግኖች ተመላልሰውባቸዋል። በጀግንነት ተረማምደውባቸዋል። በዙሪያ ገባቸው ባለው ዱር ውስጥ ኖረውባቸዋል። ጀግንነት ሠርተውባቸዋል። ጠላት መትተውባቸዋል።

የዞብል ተራራ ዝም ብሎ ተራራ ብቻ አይደለም። ነገሥታቱ ፣ መኳንንቱ እና መሳፍንቱ የሚሥፍሩበት፣ ለሀገር አንድነት የሚመክሩበት፣ ድንኳን የሚጥሉበት፣ ግብር የሚያበሉበት፣ ደስታ የሚያዩበት፣ ፍርድ የሚሰጡበት፣ ሃይማኖት፣ እሴት፣ ጀግንነት ያለበት ሥፍራ ነው። ተራራው አይደፈርም፣ ሰላቶ በአጠገቡ ውሎ አያድርም። የተራራው ግርማ ያስፈራል፣ ልብን ያርዳል። ከተራራው ግርማ በላይ ጀግኖች ሲመላለሱበት፣ ዓልመው ሲመቱበት፣ ጠላትን ሲያራውጡበት የበለጠ ግርማ አለው። ባለግርማ ሞገሶቹ ተራራዎች ሀገር ላለማሰደፈር በተጠንቀቅ የቆሙ ወታደሮች ይመስላሉ። ከዘመን ዘመን በግርማ ቆመው በምድሩ የሆነውን ሁሉ ተመልክተዋል። ጀግኖች አልፈው ጀግኖች ሲተኩ ጥላና ከለላ እየሆኑ ዘመናትን ተሻግረዋል። አንደበት ኖሯቸው ቢናገሩ፣ ከዘመን ዘመን የተተካኩትን ጀግኖች ጀብዱ ቢመሰክሩ ምንኛ ደስ ባለ ነበር። ዳሩ ይታዘባሉ እንጂ አይናገሩም። ለዘመናት በፅናት ይመለከታሉ እንጂ አይመሰክሩም። ብቻ ግን ሀገርና ወገን ሲደፈር የአባቱን ጋሻ እያነሳ ዘራፍ ወንዱ ለሚለው ጀግና ሁሉ መክተቻ ቤት ናቸው። ፈሪ አይወዱም እንጂ ጀግና ያቅፋሉ። ጀግንነት ያፈቅራሉ። በዙሪያ ገባቸው እንዳሻ ያደርጋሉ።

መልካሙ ምድር ራያ ጀግና መፍጠር ያውቃል፣ ጀግና ኮትኩቶ ያሳድጋል፣ አጀግኖ ያኖራል። የራያ ጀግኖች ቢያሻቸው በተራራው ፣ ቢያሻቸው ደግሞ በሜዳው እየተንጎማለሉ በግርማና በሞገስ ይኖራሉ ። አንጥረው እየተኮሱ ይፎክራሉ፣ ጠላትን ጥለው፣ ምሽግ ተረማምደው ሀገር ያስከብራሉ፣ ወገን ያኮራሉ። ጠላትን ያሳፍራሉ። ከአለውኃ፣ አሚድ ውኃ፣ ወይለት ፣ ከጎሊና እና ከሆርማት ወንዞች ውኃ እየተራጩ፣ እንደ ምንጭ ከሚፈስሰው ወተትና ማር እየተጎነጩ፣ ጤፍ እንጀራ በእርጎ እየጎረሱ፣ ድግና ጎፊያቸውን እየለበሱ፣ ጥርቅ ጫማቸውን እየተጫሙ የሚኖሩ ደጎች፣ ጀግኖች ፣ ሩቅ አሳቢዎች ፣ አስታዋዮች፣ ሩህሩሆች ናቸው።

ራያዎች “አህሚና በለው” ፣ “ባሕር ጉማ” እያሉ እየጨፈሩ፣ በአንድነት እየፎከሩና እየሸለሉ ፣ ስለ ሀገር እየዘመሩ፣ ሀገር የሚጠብቁ፣ ከጠላት እጅ ላይ ጠመንጃ የሚነጥቁ፣ እንደ አንበሳ ጀግኖች፣ ሲነኳቸው እንደነብር ቁጡዎች ናቸው።

ከዞብል ተራራ ግርጌ ከመንጀሎና አራዱም ተራራዎች በአሻገር ከጎሊና እና ሆርማት ወንዝ መገናኛ የተገኘሁት ጀግኖችን ለማዬት አቅንቸ ነው። የዲቢን ጀግኖች ለማየት። የዲቢ ጀግኖች ወራሪ ቡድን በመጣባቸው ጊዜ ነፍጣቸውን አንስተው ማነው ወንዱ ያሉ ጀግኖች ናቸው።

እንዲህ ሲሉም ይቀኛሉ:-

“እኔ ከራያ ልጅ እኔ ከዲቢ ልጅ ፈሪ ቢገኝብኝ፣

በመኪናው መንገድ ኦራል ይነዳብኝ ” ከዲቢ ልጅ ፈሪ አይገኝም። መገለጫቸው ጀግንነት ፣ አሸናፊነት፣ እምቢ ባይነት ነው። ከራያ ልጅ ከድቢ ልጅ ፈሪ እንደማይገኝ እርግጠኞች ስለሆኑም ነው እንደዚህ መቀኘታቸው። እንደዚህ ማለታቸው። ከእነርሱ ጎራ ፈሪ አይፈጠርም እና።

እኒህ ጀግኖች አሸባሪውን የትግራይ ወራሪ ና ዘራፊ ቡድን ወረራ ሲፈፅም በጀግንነት ታግለው፣ ቀያቸውን ያስከበሩ፣ የጠላትን አንገት የሰበሩ፣ ወገናቸውን ያኮሩ ናቸው። እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፣ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነው ርስት ሊወርስ፣ ቀዬ ሊያረክስ የመጣውን በገባበት እንዲቀር አድርገውታል። የሚቃጥል እሳት ሆነውበታል። እንደ አመጣጡ መለሱት፣ በጥይት ምጣድ ቆሉት፣ መውጫ መግቢያ እስኪያጣ ድረስ አሰቃዩት። ጀግኖችን ነክቷልና ምህረት አልነበራቸውም። አገላብጠው ወቁት። ክንዳቸው እንደሚያቃጥል፣ አፈሙዛቸው ነጥሎ እንደሚጥል አሳዩት።

“ውረድ እንውረድ ከቁልቁለቱ፣

የዛን ጊዜ ነው የጠላት ሞቱ” እየተባባሉ ውረድ እንውረድ ተባብለው በጀግንነት ተዋጉት፣ በጀግንነት መቱት፣ በጀግንነት ደመሰሱት፣ በጀግንነት አጠፉት፣ በጀግንነት አሳፈሩት።

የዲቢ ጀግኖች ስለ አሳለፉት ትግል ነገረውኛል። የዲቢ ጀግኖች የሻለቃ አዛዥ መሐመድ አስፋው አሸባሪው ቡድን ወረራ እየፈፀመ ሲመጣ እነርሱ፣ ሀብትና ንብረታቸውን እንዳይዘርፍ፣ ልጆቻቸውን እንዳይደፍር በተጠንቀቅ እንደጠበቁት ነው የነገሩኝ። ጀግኖችን በማደራጀት ሌትና ቀን ሳይመርጡ፣ ብርድና ሙቀት ሳይበግራቸው በጀግንነት አካባቢያቸውን ጠበቁ። ጠላት ወደ ዲቢ ለመግባት በተደጋጋሚ ጥቃት ፈፀመ። የድቢ ጀግኖች ግን ሆ ብለው ወጥተው አቀመሱት። ለጠላት አልቀመስ አሉ። ጠላት በተነኮሳቸው ቁጥር ድባቅ እየመቱ መለሱት። ሙት ደረደሩለት።

ጀግኖቹ እንደማይቀመሱ ያየው ጠላትም የዲቢ ጀግኖች እንዲተውት ሽምግልና መላኩን የሻለቃ አዛዥ መሐመድ ያስታውሳሉ። ጀግኖቹም አይሆንም አሉ። ዲቢን የምትረገጠው እኛ ሞተን ስናልቅ ነው፣ የእኛን መሳሪያ ጠላት የሚነካው፣ ቀያችንን የሚደፈረው ስንሞት ብቻ ነው ብለው አሻፈረኝ አሉ። የዲቢ ጀግኖች ከመከላከል አልፈው ወደ ማጥቃት እየተሸጋገሩ በጠላት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ያደርሱ ጀመር። መሳሪያ ይማርካሉ፣ ጠላትን በአገኙት ሥፋራ ሁሉ ይደመስሳሉ። ትጥቅ እየማረኩ መታጠቅ ጀመሩ። በገደመዩና በሌሎች አካባቢዎች ጠላትን እያሳፈሩ ደመሰሱት። ይዞ የሚመጣውን ማረኩት።

ራያ በጀግንነቱ የተመሰከረለት ነው፣ ክብሩን አሳልፎ አይሰጥም፣ ሁሉም በማንነቱ ላይ የሚመጣውን ጠላት ለመመከት ተዘጋጅቶ መቀመጥ አለበት ነው የሚሉት። አማራ በጀግንነት ከጠላት ከፍ ያለ ስለሆነ ተደራጅቶ መጠበቅ አለበት፣ አማራ እና መላው ኢትዮጵያዊ ከተደራጀ ጠላት ያፍራል እንጂ የምንደፈርበት ምንም አይነት ምክንያት የለምም ብለዋል።

የራያ ጀግኖች ረሃብና ጥሙን ችለው በአንድነት በጀግንነት ታገሉት። የዲቢ ጀግኖች በመከባበር እና በመመካከር ለወራት በፅናት ታግለው ድል አመጡ። ጠላት በከባድ መሳሪያ ምሽጋቸውን ለመሥበር በተደጋጋሚ ጥረት አድርጎ አልተሳካለትም ነው ያሉት የሻለቃ አዛዥ መሐመድ አስፋው። በባሕላዊ መገናኛዎች እየተገናኙ ጠላታቸውን አሳፈሩ። በድል ተረማመዱ።

የድቢ ጀግና ተዋጊ ካሰው አማረ በጀግንነት ተዋግተው አካባቢያቸውን ሳያስደፍሩ መቆዬታቸውን ነው የገለፁት ። የዲቢ ጀግኖች ከሌሎች የራያ ጀግኖች ጋር በመተባበር ቆቦ ከተማ ውስጥ የነበረውን ጠላት እየሄዱ ያጠቁት እንደነበርም አስታውሰዋል። ጀግኖቹ እኔ እቀድም፣ እኔ እቀድም ነው እንጂ መሸሽ እንደማያውቁም ነግረውናል።

የራያ ጀግና በጦር የማይመለስ ልበ ሙሉ መሆኑንም ገልፀዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ ለጀግኖቹ ስንቅ በማቀበል፣ ሴቶች ምሽግ ድረስ እየገቡ አይዞህ በለው፣ እሰይ የኔ ጀግና እያሉ ያዋጉ እንደነበርም ነግረውናል። እናቶች ሂድ ለሀገርህ ሙት፣ ሂድ ለክብር ተዋደቅ እያሉ ጀግኖችን ያበረታቱ ነበር።

የራያ ጀግኖች ጠላትን እስከመጨረሻው #ለመደምሰስ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በክንዳችን ድል አምጥተናል እና ደስተኞች ነንም ነው ያሉት።

ሌላኛው ጀግና አማረ ሲሳይ ቀበሌያችን እንዳይደፈር በጀግንነት ታግለናል፣ ትግላችንም ፍሬ አፍርቷል ብለዋል። የእኛን ቀዬ ባናስደፍርም ጠላት በአማራ ክልል የዘረፈው ሀብት ያንገበግበናልም ብለውናል። የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ያበረታቷቸው እንደነበርም ነግረውናል። የራያ ጀግንነት ከዘመን ዘመን የመጣ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የዲቢ ጀግኖች በፅናት ታግለው ቀያቸውን ሳያስደፍሩ የድል ቀን አምጥተዋል። በአሸናፊነት ተወጥተዋል። በጀግንነታቸው አይዟችሁ ሲሏቸው የነበሩትን ሁሉ አኩርተዋል። ራያ የጀግኖች ምድር። ዲቢዎች ከድል በኋላ በጎሊና እና በሆርማት ወንዝ መገናኛ “ባሕር ጉማ”እያሉ እየጨፈሩ፣ ደስታቸውን እያጣጣሙ፣ ጠላታቸውን እስከመጨረሻው #ለማጥፋት ቃል ኪዳን እያሰሩ ነው።

በታርቆ ክንዴ
ወልድያ፡ ታኅሣሥ 23/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

 

https://fb.watch/aka9_X_EzV/

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.