ለቸኮለ! ቅዳሜ ታኅሳስ 9/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

268294312 3093264030916055 8996128079583299970 n1፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎች እና ሕዝባዊ ሚሊሻዎች በአማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች ላይ በወሰዱት መጠነ ሰፊ ማጥቃት የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ ወልድያን ነጻ እንዳወጡ የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ከቀትር በኋላ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ከወልድያ በተጨማሪ ሐራ፣ ጎብዬ፣ ሮቢት እና ቆቦ ከተሞች መሉ በሙሉ ከሕወሃት ታጣቂዎች ነጻ ወጥተዋል። ጥምር ኃይሉ በላሊበላ ከተማ አካባቢ ያሉትን ታጣቂዎች በማጽዳት፣ በዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞን ዋና ከተማ ሰቆጣ አካባቢ የሠፈሩ ታጣቂዎችን ወደመምታት እንደተሸጋገረ ተገልጧል። ባለፉት ጥቂት ቀናት ጥምር ኃይሉ ከአየር ኃይሉ ጋር በመቀናጀት በተወሰደው የኃይል ርምጃ ሰሜን ወሎ ዞን ከታጣቂዎቹ ነጻ እንደወጣ መግለጫው አመልክቷል።

2፤ ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ካውንስል በትግራዩ ግጭት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር ከሚያቋቁመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓለማቀፍ መርማሪ ኮሚሽን ጋር እንደማትተባበር ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ካውንስሉ በትናንቱ ውሳኔው በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን እና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ነጻነት መጣሱን የጠቀሰው መግለጫው፣ ከሀገሪቱ ፍቃድ ውጭ የጸደቀው መርማሪ ኮሚሽን ችግሩን ከማባባስ የዘለለ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብሏል። ካውንስሉ በልዩ ስብሰባው በትንሹ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ዓለማቀፍ መርማሪ ኮሚሽን ለማቋቋም ነው በድምጽ ብልጫ የወሰነው።

3፤ ፖሊስ ሰሞኑን አንዳንድ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ያዋለው በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ስለጠረጠራቸው እንደሆነ የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች መንግሥት በመላ ሀገሪቱ የደነገገውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጣሳቸው እና በአሸባሪነት ከተፈረጁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው መታሰራቸውን አንዳንድ አካላት ሌላ ገጽታ ለመስጠት እየሞከሩ እንደሆነ መግለጫ ጠቁሟል። መግለጫው አያይዞም፣ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ጋዜጠኞች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ እና በሕግ ፊት አቅርቦ ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ ያደርጋል ብሏል።

4፤ ሦስተኛው የቱርክ-አፍሪካ አጋርነት የመሪዎች የጋራ ጉባዔ ዛሬ በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ ተጀምሯል። የዘንድሮው የቱርክ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ጭብጥ “ለጋራ ልማት እና ብልጽግና ትብብርን ማጎልበት” የሚል ነው። በጉባዔው ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን ጨምሮ 16 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እና ከ100 በላይ ሚንስትሮች ተሳታፊ ናቸው። ቱርክ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከበርካታ አፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ፣ የንግድ ግንኙነት እና የጸጥታ ትብብር በማጥበቅ ላይ ናት።

5፤ ቱርክ ከአፍሪካ ጋር ያላት ንግድ ልውውጥ 30 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ዛሬ በተጀመረው የቱርክ-አፍሪካ የጋራ የመሪዎች ጉባዔው ላይ መናገራቸውን አናዶሉ ዜና ወኪል ዘግቧል። አፍሪካ በተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ውክልና አለማግኘቷ ኢፍትሃዊ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፣ በኮሮና ቫይረስ ክትባት ሥርጭት ጭምር አፍሪካ ላይ የሚታየውን ኢፍትሃዊነት ለመቅረፍ ሀገራቸው ለአፍሪካ ሀገራት 15 ሚሊዮን የክትባት ጠብታዎችን እንደምትለግስ ቃል ገብተዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.