የወልዲያ ከተማ እና አከባቢው መንግስት በወሰደው ጠንካራ የማጥቃት እርምጃ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣት በመቻሉ እንኳን ደስ አላችሁ

በወራሪው የጠላት ሃይል ቁጥጥር ስር የነበሩ አከባdemeke 1ቢዎችን ነፃ የማውጣት እርምጃን ተከትሎ የወልዲያ ከተማ እና አከባቢው መንግስት በወሰደው ጠንካራ የማጥቃት እርምጃ ሙሉ በሙሉ ነፃ ማውጣት በመቻሉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን አብሮ ደስ አለን።
ጀግናው የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ እና አፋር ክልል ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ ላደረጋችሁት ብርቱ ርብርብ እና አኩሪ ተጋድሎ ከልብ እናመሰግናችኋለን፤ እናከብራችኋለን።
ለዚህ ታሪካዊ የድል ምዕራፍ ስላበቃችሁን ሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ለማለት እወዳለሁ።
አሁንም የድል ግለቱን ጠብቆ በወራሪው የጠላት ሃይል ቁጥጥር ስር ያሉ ቀሪ ጥቂት አካባቢዎችን በአጭር ጊዜ ነፃ የማውጣት እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ሃገራችን ኢትዮጵያን ከገጠማት ፈተና እንዳትላቀቅ ብሎም የከፋ ጫና ውስጥ እንድትወድቅ ከውስጥ እና ከውጭ ያሉ ሃይሎች ተባብረው እየሰሩ መሆናቸው በግልፅ ይታወቃል።
እነዚህ ለጥፋት ያበሩ ሃይሎች የኢትዮጵያን ውድቀት ለማብሰር ሁሉንም ምድራዊ የጥፋት እርምጃ ከመውሰድ ወደኋላ እንደማይሉ በገሃድ በሚፈፅሙት ጫና እና ሴራ መረዳት ይቻላል።
ይሁንና ኢትዮጵያዊነት የነሱን የጥፋት ድግስ ታግሶ ለማስተናገድ የሚፈቅድ የሞራል ስብራት እንደሌለው በየጊዜው የሚያስመዘግባቸው አኩሪ ድሎች በቂ ማሳያ ናቸው።
በዚህ አጋጣሚ በተለያዩ ክፍለ አለማት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በ”No More” አለም ዓቀፍ ንቅናቄ በተሰለፋችሁበት መድረኮች ለምታደርጉት ተጋድሎ ከልብ እናመሰግናለን።
የውጪውን ግንባር በደማቅ ኢትዮጵያዊ አንድነት እና ህብረት ለምታደርጉት ሁሉአቀፍ ርብርብ እና ትርጉም~አዘል ጫና ልዩ አክብሮታችን እና አድናቆታችን በያላችሁበት ይድረሳችሁ።
ሁሉም ለጥፋት ግንባር ፈጥረው ይባክናሉ፤ ይሁንና በጠንካራ የአንድነት መንፈስ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ዳር እስከዳር አኩሪ ድሎች እያስመዘገብን ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥላለን።

1 Comment

 1. እጅግ ኋላ ቀሩንና አስከፊውን የጎሳ/የቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት በእኩይ አስተሳሰብ ጠንስሰው ፣ በህገ መንግሥት ደንግገው ፣ በፖለሲና ፕሮግራም ቀርፀው ፣ በእቅድ ቀምረው እና በመዋቅር አደራጅተው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የህዝብን የጋራ ታሪክዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ሞራላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ክፉኛ ማጎሳቆላቸው አልበቃ ብሏቸው አሁን ደግሞ ከቤተ መንግሥት ካባረሯቸው የቀድሞ አሽከሮቻቸው ጋር በሚያካሂዱት የመንበረ ሥልጣን ሽሚያ የእርስ በእርስ እልቂት (ወንድም ወንድሙንና እህቱን፣ እና እህት እህቷንና ወንድሟን የመግደልና የመገዳደል አዙሪት) ውስጥ የዘፈቁን የህወሃት መሪዎች ተሸንፈው ህዝብ ቢያንስ ጊዜያዊ እፎይታ ማግኘቱ የማያስደስተው ቅን እና ነፃነትና ፍትህ ናፋቂ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
  ይህ ሲባል ግን ከእራሳችን አጠቃላይና አስከፊ የውድቀት አዙሪት ሰለባነት አልፎ የዓለም ማህበረሰብ ከንፈር መምጠጫ ፣ መሳቂያና መሳለቂያ የዳረገንን መሠረታዊ ምክንያት (main cause) ጠቅልሎ ለህወሃትና ተባባሪዎቹ በመሥጠት ብቻ ወደ ትክክኛና ዘላቂ መፍትሄ እየተጓዝን እንደሆነ አድርገን እያሰብን ከሆነ ፈፅሞ የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው።
  ለጊዜው ስለተገኘው እፎይታ የተሰማንን ስሜት በአግባቡ መግለፅ ትክክል ነው። የፖለቲካ ካንሰሩ ዋነኛ መነሻ (main cause) የሆነው ሥርዓተ ኢህአዴግ /ብልፅግና ከሚያስከትለው የህመም ስቃይና ሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገላገል እንዴት ይቻላል? ብሎ ሳይጠይቁና ተገቢውን መልስ መመለስ በሚያስችል ቁመና ላይ ሳይገኙ በጊዜያዊ የድል ስሜት መክነፍ ግን ጨርሶ ትክክል አይደለምና ልናስብበት ይገባል።
  በመካከላቸው (በኢአዴጋዊያን ውስጥ) የተፈጠረውን የሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ መከራና ውርደት የበዛበትን ህዝብ ምሬትና ቁጣ ተጠቅመው ጌቶቻቸውን (ህወሃቶችን) አሸንፈው እና ከቤተ መንግሥት (ከበላይነት ፖለቲካ) አስወግደው ህወሃት ሠራሹንና ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉበትን ሥርዓተ ኢህአዴግ ግን ምንም አይነት ትርጉም ያለው ለውጥ ሳይደረግበት ያስቀጠሉ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) የሚሰጡንን የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ተከትለን በስሜታዊነት ፈረስ የምንሸመጠጥ ከሆነ እጅግ አደገኛ ከሆነ ከተሞክሮ ያለመማር አዙሪት ውስጥ ነንና ልብ ልንል ይገባል ።
  በተናጠል የተኩስ አቁም ስም ትግራይን ለቀው ከመውጣት አልፈው እጅግ ቅጥፈት በተሞላበት ወታደራዊ ስትራቴጅ ስም ለህወሃቶች መንገድ እየጠረጉና መሣሪያ እያስረከቡ (እያቀበሉ) እስከ ሰሜን ሸዋ (ቤተ መንግሥት አቅራቢያ) ካደረሱ እና እጅግ ለማሰብ የሚከብድ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት እንዲደርስ ካስደረጉ በኋላ ይህ ወይም ያኛው ሥፍራ ነፃ ወጣ ሲሉን ” እሰየው ፤ ነገር ግን ለጠፋው አሰቃቂ ጥፋት ሁሉ ተጠያቂዎች ህወሃቶች ብቻ ሳይሆኑ የህወሃትን ሥርዓተ ፖለቲካ በተረኝነት በማስቀጠላችሁ እና አሁን የደረሰው አስከፊ ውድመት እንዲደርስ በማድረጋችሁ የእናንተም ሃላፊነትና ተጠያቂነት በፍፁም የሚታለፍ አይደለም” ለማለት ወኔው ካቃተን የምናሰማው እልልታና የድል ነጋሪት ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም በአስከፊ ሁኔታ ተዘፍቀን ከቀጠልንበት ክፉ አዙሪት ፈፅሞ መውጫ የለንም።
  ሸፍጠኛ፣ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ ኢህአዴጋዊያንን በፖለቲካ አግባብ አስገድደን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል ከተጨማለቀና ከበሰበሰ ሥርዓታቸው ተላቀው ከህዝብ ጥቅም አንፃር አግባብነትና አዋጭነት ወደ ሚኖረው ዴሞክራሲያዊ መንገድ እንዲገቡ ለማድረግ ሳንችል በመቅረታችን በመካከላቸው በፈጠሩት የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት የገባንበትን የእርስ በርስ ጦርነት (መገዳደል) ከአድዋ ድል ጋር እያነፃፀሩ ይህን ትውልድ የማሳሳቱ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ጡዘት ፈፅሞ አይጠቅምም።
  ከመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሥርዓት ጥያቄ ተንሸራተን የሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን (ብልፅግናዊያን) ርካሽና አደገኛ የፖለቲካ ቁማር ሰለባዎች የመሆናችን ውድቀት ካስከተለውና እያስከተለ ካለው ታይቶ የማይታወቅ ሁለንተናዊ ቀውስ ከምር ተምረን አሁንም በግለሰቦች ወይም በቡድኖች መቀያየር ሳይሆን በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ትግል ዙሪያ ካልተሰባሰብንና ትግሉን ካላስቀጠልን በስተቀር የአልቃሽና ዘፋኝ ፖለቲካ ሰለባዎች ሆነን እንቀጥላለን (እርሱም የሚያስቀጥለን ከሆነ ነው) ።
  የገንዛ እራሳችን እርስ በርስ የመገዳደል አስከፊ የፖለቲካ ባህል ፍፃሜ ያገኝ ዘንድ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓተ ኢህአዴግ/ብልፅግና ወደ መቃብር አውርዶ የጋራ እና እውነተኛ በሆነ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ዴሞክራሲያዊት የሆነች አገር እውን ከማድረግ ይልቅ እርስ በርስ የተገዳደሉትን ወንድማማቹች እና እህትማማቾች አንዱን/አንዷን ጀግና ሌላውን/ሌላዋን አሸባሪ ወይም ወራሪ የሚል ስያሜ እየሰጠን እስከ መቼ እንደምንቀጥል ሲያስቡት በእጅጉ ህሊናን ያስጨንቃል ።
  እኩይ መሪዎችንና ፖለቲከኞችን ለይቶ መምታትና ማስወገድ ይቻላል እንዳንል ጦርነቱ በሁለቱም ወገን የህዝብ ወይም የሲቪሊያን እንዲሆን በመደረጉ አልተቻለም። እናም እየገደሉና እየተጋደሉ ያሉት ስለ ዘመናችን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨርሶ የማየውቁ ንፁሃን ወገነኖች ናቸው። ለዚህ ነው ገድሎና ተጋዳድሎ በድል አድራጊነት መፎከርና መኩራራት በእጅጉ አስቸጋሪ የሚሆነው። እናም ከዚህ አይነት አስከፊ አዙሪት ወጥቶ በዴሞክራሲና በጋራ እድገት የአርበኝነት ተጋድሎና ድል መሸለምና መሸላለም እንዲቻል እንዳይፈወስ ሆኖ የተበከለውን ሥርዓተ ፖለቲካ እንደ ሥርዓት ማስወገድ ግድ ነው።
  እንዴት ጥቂት እኩያን የጎሳ/የጎጥ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞችን አደብ ማስገዛት ወይም ማስወገድ እና የሚበጀንን የጋራ ሥርዓት እውን ለማድረግ አቃተን? እስከ መቼ እና እስከ የትስ ነው በዚህ እጅግ አሳፋሪና አስከፊ የፖለቲካ ምህዋር ላይ እየተሽከረከርን የምንቀጥለው? ፣ ወዘተ የሚሉትን መሪር ጥያቂዎች አጥብቀን እየሸሸን ዴሞክራሲያዊትና ከእራሷ ጋር የታረቀች ኢትዮጵያን መመኘት ቅዠት እንጅ የገሃዱ ዓለም ራእይ አይደለም።
  ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ታሪካዊ የተባለለትን ምርጫ እንዳሸነፈ” የአገራዊ ምክክር መድረክ አዘጋጅቸ እጥራችኋለሁና ታዳሚዎች ለመሆን የምትሹ ሁሉ በጉጉት ጠብቁኝ” ባለው መሠረት የአገራዊ ምክክር አዘጋጅና አስተባባሪ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ መውጣቱን ከሰሞኑ ሰምተናል ወይም አንብበናል ።
  በመርህ ደረጃ (in principle) ይህ ሸጋ ሃሳብ ነው ። እንዲህ አይነት ሸጋ ሃሳብ ለሦስት ዓሥርተ ዓመታት ሙሉ በሸፍጥ፣ በሴራና በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተበከለ ሥርዓት ከነ ሙሉ የካድሬ ሠራዊቱ በቀጠለበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ እንዴትና በምን እውን ሊሆን ይቻለዋል? ብሎ አለመጠየቅና ተገቢውን መልስ ለማግኘት ጥረት አለማድረግ ግን ከትናንት አስከፊ ስህተትና ውድቀት ያለመማር ክፉ አባዜ ነው የሚሆነው።
  መቸም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የብልፅግና ሰዎችን የውሸት ልክፍት ልብ ለማለት ለሚችል ወገን ይህ አዋጅ እና ይቋቋማል የሚባለው ኮሚሽን በነፃነትና በራስ መተማመን ላይ ተመሥርቶ ሽርፍራፊ ሳይሆን ለአገር አንድነትና ዴሞክራሲያዊነት ጠንቅ (መጋኛ) የሆኑትን አገራዊ ጉዳዮች (በዋናነትን የህገ መንግሥት ጥያቄዎችን ) ወደ ምክክር መድረክ አምጥጦ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የሚሆንበትን ሁኔታ ያመቻቻል ብሎ ማመን የሚያስችል አንዳችም አሳማኝ ምክንያት ያለ አይመስለኝም።
  እናም ከፊታችን የተደቀነው ፈታኝ ሁኔታ ከቶ የዋዛ አይደለምና ከዚህ ከሰሞኑ የጊዜያዊ እፎይታ እልልታ ጎን ለጎን ነገ ወደ የመከራና የሰቆቃ እንባ (እርሱም ይቸግራል) ላለመመለስ የሚያችለንን የቤት ሥራ መሥራት ግድ ይለናል።
  ይህ እንደሚሆን ተስፋ እያደረግኩ አበቃሁ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.