ለቸኮለ! ማክሰኞ ኅዳር 7/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

 

1፤ ተመድ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት ብቻ አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ 1 ሺህ ያህል ሰዎችን አስሯል ማለቱን ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ተወካይ ሊዝ ትሮሴል ዛሬ ለጋዜጠኞች እንዳሉት፣ አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች እየታሠሩ ያሉት በአዲስ አበባ፣ ባሕርዳር፣ ጎንደር እና ሌሎች ከተሞች ነው። አብዛኞቹ ታሳሪዎች በተጨናነቁ ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙና አያያዛቸውም ጥሩ እንዳልሆነ ሃላፊው ጠቁመዋል። ፖሊስ ግን ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የሚያውለው ከአማጺው ሕወሃት ጋር ባላቸው ግንኙነት እንጅ በብሄር ማንነታቸው ለይቶ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አስተባብሏል። በቅርቡ የታሠሩ 10 ኢትዮጵያዊያን የተመድ ሠራተኞች እና 34 የተመድ ተቀጣሪ ሹፌሮችም እስካሁን አልተፈቱም።

2፤ በትግራይ ክልል 200 ያህል ሕጻናት በምግብ እጥረት ለህልፈት ተዳርገዋል ሲል አሶሴትድ ፕሬስ ጽፏል። መረጃ የተገኘው ከሐምሌ እስከ ጥቅምት ባሉት አራት ወራት በተደረጉ የናሙና ጥናቶች እንደሆነ የቀድሞው የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ መናገራቸውን ዜና ወኪሉ ጠቅሷል። ዜና ወኪሉ ለዘገባው የተጠቀመውን አሃዝ ያገኘሁት፣ በክልሉ ከሚሠሩ ሐኪሞች፣ ከ14 ሆስፒታሎች እና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በስልክ ቃለ ምልልስ በሰበሰብኩት መረጃ ነው ብሏል። የክልሉ ምንጮች ለሕጻናት ምግብ እጥረት ለመጋለጣቸው ተጠያቂ የሚያደርጉት ፌደራል መንግሥቱ በትግራይ ላይ ጥሎታል የሚሉትን እቀባ ሲሆን፣ ፌደራል መንግሥቱ ግን አስፈላጊ የምግብ አቅርቦቶች በተሟላ ሁኔታ ለተረጅዎች እንዳይደርሱ እንቅፋት የፈጠረው አማጺው ሕወሃት በአጎራባች ክልሎች ላይ የከፈተው ጦርነት እንደሆነ ይናገራል።

3፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ዓለማቀፍ ጫና በመቃወም በብራስልስ ከተማ በአውሮፓ ኅብረት ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት የተቃውሞ ሰልፍ እንዳደረጉ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የተለያዩ መፈክሮችን ያሰሙ ሲሆን፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት እና ጫና እንድታቆም ጠይቀዋል። ሰልፈኞቹ ከቤልጂየም፣ ሆላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔን እና ሉግዘምበርግ የተውጣጡ ናቸው። ሰልፈኞቹ በጽሁፍ ያዘጋጁትን መልዕክት የኅብረቱ ኮሚሽን ተወካይ በአካል ተቀብለዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: የፈረንሳይ እግር ኳስ በሞት አፋፍ ላይ ነው፤ 75% ታክስ ክለቦችን ለችግር ያጋልጣል

4፤ ፖሊስ በአሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ አዘጋጅ ክብሮም ወርቁ ላይ ያቀረበውን ይግባኝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዛሬ ውድቅ እንዳደረገው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። ፍርድ ቤቱ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪው በ15 ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ ባለፈው ሳምንት የወሰነውን ውሳኔ በማጽናት፣ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ውድቅ አድርጓል። የጣቢያው አዘጋጅ ክብሮም እና ዘጋቢ ልዋም አታክልቲ ከሦስት ሳምንት በፊት የታሠሩት ከአማጺው ሕወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው ሲሆን፣ ልዋም ባለፈው ሳምንት በ10 ሺህ ብር ዋስትና ተፈታለች።

5፤ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ከኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ራቼል ኦማሞ ጋር በትግራየ ግጭት፣ በሱማሊያ እና ሱዳን ጉዳይ ላይ ይመካከራሉ ተብሏል። ኬንያ በጉረቤቶቿ ኢትዮጵያ እና ሱማሊያ ላሉ ግጭቶች እንዲሁም በሱዳን ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሄ የማፈላልግ ሚና እንድትጫወት አሜሪካ ትፈልጋለች። ብሊንከን ወደ ኬንያ፣ ናይጀሪያ እና ሴኔጋል ያቀኑት፣ በቀጠናዊ ጸጥታ እና መረጋጋት፣ ከአሜሪካ አጋር ሀገራት ጋር በዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ፣ በኢንቨስትመንት፣ አየር ንብረት ለውጥ እና ኮሮና ወረርሽኝ ዙሪያ ለመነጋገር ነው።

6፤ የኢጋድ አባል ሀገራት መሪዎች በኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ አስተናጋጅነት ለትግራዩ ግጭት ሰላማዊ መፍትሄ ለማፈላለግ ዛሬ በኡጋንዳ ካምፓላ ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ ለሌላ ጊዜ እንደተራዘመ የተሉያዩ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ፣ የመሪዎቹ ስብሰባ ለምን እንደተራዘመ እና በቀጣይ መቼ እንደሚካሄድ ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒም ሆኑ ኢጋድ ያሉት ነገር የለም።

7፤ ዛሬ በኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ማዕከላዊ ክፍል በቦምብ የሽብር ጥቃት እንደተፈጸመ የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። አጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃቶቹን የፈጸሙት ከሀገሪቱ ፓርላማ እና ከማዕከላዊ ፖሊስ ጣቢያ አጠገብ ሲሆን፣ በፍንዳታው 3 አጥፍቶ ጠፊዎችን ጨምሮ 6 ሰዎች ተገድለዋል። ፖሊስ ለጥቃቱ የተባበሩት ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች የተሰኘውን የኡጋንዳ እስላማዊ አማጺ ቡድን ተጠያቂ አድርጓል። ኢጋድ የኡጋንዳውን የሽብር ጥቃት በትዊተር ሰሌዳው ባሰራጨው መግለጫ ያወገዘ ሲሆን፣ ጎረቤት ኬንያ ደሞ የጸጥታ ጥበቃዋን በከፍተኛ ደረጃ አጠናክራለች።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህዝብ መሳሪያ ባይኖረው እንኳን ድንጋይን መሳሪያ፣ አንድነትን ጥይት ማድረግ ይችላልል!

8፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በሱማሊያ ላይ ከ30 ዓመት በፊት የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ትናንት በድጋሚ ለአንድ ዓመት አራዝሞታል። ቻይና እና ሩሲያ ድምጸ ተዓቅቦ ሲያደርጉ፣ ኬንያ ግን የማዕቀቡ መራዘም የነውጠኛውን አልሸባብ ሽብር ጥቃቶች ለመግታት ያግዛል በማለት ለውሳኔ ሃሳቡ ድጋፏን ሰጥታለች። ሱማሊያ የጸጥታ ኃይሎቼን ለጠናክር እንድችል ማዕቀቡ ይነሳልኝ በማለት ያደረገችው ውትወታ ተቀባይነት አላገኝም። ሱማሊያ የጸጥታው ምክር ቤት መሳሪያ ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ሲፈቅድላት፣ አንዳንድ ጦር መሳሪያዎችን መግዛት ትችላለች።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.