እንታረቅ! – ገለታው ዘለቀ

እንደ መግቢያ

የምኖርባት ከተማ በሰሜን አሜሪካ ማሳቹሴትስ ውስጥ ያለች በጣም ትንሽዬ ደሴት ናት። ፕላም አይላንድ ትባላላች። ዙሪያዋን በውሃ የተከበበች ስትሆን ወደ ጎን ጠባብ ናት። ኣምስት መቶ ሜትርም ኣትሞላም። ቀጭን ረጅም ደሴት ናት። ቁመቷ ግን 18 ኪሎሜትር ይደርሳል። ይህቺ ደሴት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ጋለል ብላ ተኝታ እነሆ ታላቁ ውቅያኖስ አትላንቲክ መልካሙን ኣየሩን ዘወትር በዚችህ ሸንቃጣ ደሴት ገላ ላይ እፍፍፍ…… ሲልባት ስለሚውል የዚህች ከተማ ንጹህ አየሯ የውነትም ያውዳል። የተፈጥሮ ጸጋዋ የህዝቡ ጨዋነትና ሰላምታው የቤቶቹ ውበት ሁሉ ተደማምረው ፕላም አይላንድን ማራኪ አድርገዋታል ።

እንግዲህ ከኢትዮጵያ ከተመለስኩ ጀምሮ በዚህች የምድር ገነት ከተማ ውስጥ ሆኜ ለእኔ አልሞቀኝም። ኣድሮ ይከፋኛል። ለመሆኑስ የኢትዮጵያ ልጅ አይደለሁምን? ደርሶ የሚያስከፋ፣ ደርሶ የሚያሳዝን ነገር በየቀኑ የሚሰማባት ምድር ፍሬ ነኝና በዚህ ሁሉ በሞላበት ምድረ ገነት ከተማ ውስጥ ደስታ ርቆኝ ብታይ እውነት አለኝ። ወንድሞቹና እህቶቹ እርስ በርስ በጦርነት የሚተላለቁበት ሰው ስለሆንኩ፣ ወንድሞቹና እህቶቹ ዋይ ዋይ የሚሉበት ሰው ስለሆንኩ፣ ወገኖቹ የተራቡበት ሰው ስለሆንኩ ሁልጊዜ ብቆዝም ሁልጊዜ ብተክዝ ምንም አይፈረድብኝም። አንዳንድ ሰዎች ሰላም ይሉኝና ኢትዮጵያዊነቴን ስለሚያውቁ ዜና ሰማን ሶሪ ይሉኛል። እናም ባዝን ብቆዝም እውነት አለኝና ነዋ!……..
ዛሬ ማለዳ ፕላም ኣይላንድ የበረከት ደመና ከቧታል። እንደ አርሞኒኤም ጠል ከሰማይ ቀስ እያለ የሚወርደው ዝናብ በጥንቃቄ ምድሪቱን ያጠጣል። ዛፎቹና አትክልቶቹ ሁሉ ጠጥተው እንደረኩ ገጽታቸው ይሰብቃል። የአትላንቲክ ውቅያኖስ ከሰማይ የሚወርዱትን የዝናብ ጠብታዎች እንኳን ደህና መጣችሁ እያለ እየጨፈረ የሚቀበል ይመስላል። በታላቅነቱ ሳይኮራ እነዚህን ጠብታዎች ለመቀበል ሲንቀሳቀስ አየዋለሁ።
በሄድኩበት የማላጣውን የሃገሬን የይርጋ ጨፌን ቡና በማሽን ኣፈላሁና ለቤተሰቦቼ ካጠጣሁ በሁዋላ ከምኖርባት ከተማ ባሻገር ካለች ሌላ ከተማ ላይ አይኖቼና ልቤ በአንድ ላይ አረፉ……. ከዚህች ደሴት ማዶ ያለችውን ኒውበሪፖርትን እያየሁ ዛሬ የምሰራው ብርቱ ጉዳይ ታየኝ። የእጅ ስልኬን መታሁ……..

ሄሎ አልኩ ዝግ ባለ ድምጽ
ትህትና የተሞላበት ድምጽ ከኒውበሪፖርት ከተማ ላይበረሪያን ዘንድ ሰማሁ። ሰላም ተባባልና ጥያቄየን ቀጠልኩ።
ዛሬ እናንተ ላይብረሪ ውስጥ ኣንድ ነጻ ክፍል እፈልጋለሁ። ብርቱ ጉዳይ ኣለኝ የምጽፈውና ነጻ ክፍል ይገኛል ? ብየ ጠየኩ።

ከአንድ ሰዓት በሁዋላ ተዘጋጅቶ እንደሚጠብቀኝ ተነገረኝ። መዝሙሬን እያንጎራጎርኩ ሳማትር አዳዲስ ስካርፎች ተደርድረዋል። ባላቤቴ ቀደም ቀደም እያለች እነዚህ ስካርፎች አያምሩም? ትለኛለች። ያምራሉ…… ስል ጭንቅላቴን ወዘወዝኩ። ኢትዮጵያ የተሰሩ (Made in EThiopia) ናቸው እዚህ ከተማ ይሸጣሉ አክስቴ ደስ ብሏት ገዝታቸው መጣች አለችኝ። የውነትም ደርሶ አስፈገገኝ።
ኮምፒወተሬን፣ ደብተርና እርሳሴን ሸከፍኩና መኪናየን ቀሰቀስኩት። የሃገሬን ሙዚቃ ከፍቼ ከፈጣሪ ጋር እያወራሁ ያቺን መለሎ ቀጭን ደሴት ተሻግሬ ኒውበሪፖርት ከተባለችው ከተማ ገባሁ። ላይብረሪ ደረስኩ። ፕላም አይላንድ ላይብረሪ ስለሌለ ነው ወደዚህ ያመራሁት። ላይብረሪው ውስጥ ስገባ ላይብረሪያኑ ሙያዊ ፈገግታና አቀባበል ካደረገልኝ በሁዋላ የተዘጋጀልኝን ክፍል ጠቆመኝ።
“ክፍሉ ሰሌዳና ማርከር ኣለው ምን አልባት ማርከር የምትጠቀም ከሆነ?” ይለኛል አስተናጋጁ።

ጥቂት ካሰብኩ በሁዋላ ያስፈልገኛል…….. በማለት መለስኩለትና የተለያዩ ቀለማት ያሉትን የማርከሮች ቦርሳ ከዳስተር ጋር ሰጠኝ። አስተማሪነቴ ትዝ አለኝ…….።
ሁለተኛ ፎቅ የተዘጋጀልኝን ክፍል አገኘሁ። የማርከሩን ቦርሳ ከፍቼ በጸዳው ሰሌዳ ላይ ዛሬ ወደዚህ ያመጣኝን ዋና አጀንዳ በደማቁ ጻፍኩ። እንዲህ ስል ጻፍኩ። እንታረቅ! የጻፍኩትን ርእስ ትኩር ብየ አየሁ…….። ተባረኩት……..። ሰላምና ተስፋ በዚያች ልዩ ክፍል ሸተቱኝ። በወንበሬ ላይ ተቀምጬ እነሆ ይህንን የእርቅ ሃሳብ ከተብኩ። እግዚኣብሄር ረድቶን ለሃገሬ እርቅ ይዘንብላት ዘንድ እየተመኘሁ ይህንን ደብዳቤ ለወገኖቼ ከኣትላንቲክ ውቅያኖስ ጫፍ ላይ እነሆ ልኬያለሁ። ዝቅ ሲል ቁምነገሩን ስጽፍ መተረኩን አልመረጥኩም። ጠንከር ባሉ ቃላት ጽፌዋለሁ።

ሀ. ለመሆኑ ድርድርና እርቅ በኢትዮጵያ ለምን?

ጽሁፉን ስጀምር በዚህ ጥያቄ መጀመር ተገቢ መሰለኝ። እንግዲህ ሃገራችን ኢትዮጵያ በተለይ ባለፉት ሶስት አመታትና በላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሰላም ያጣችበት፣ የመፈናቀልና የጦርነት ማእበል በሃይል እያናወጣት ያለበችበት ከባድ ወቅት ላይ ናት። ነገሮች ኣድረው ይከፋሉ። አድረን መልካም ዜና የምንሰማበት ጊዜ ጠፋ። በተለይ የሰሜኑ ጦርነት በየቀኑ የኣፍላ ወጣቶችን ደም ሲያፈስ ውሎ ሲያፈስ ያድራል። ህጻናትን፣ ሽማግሌዎችን በየቀኑ ያፈናቅላል። የጦርነት ዜና ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ኑሮው ሁሉ በስጋት የተሞላ እንዲሆን አድርጎብናል። በኢኮኖሚው በኩል እንዳናንሰራራ አድርጎ እየደቆሰን ነው። መፈናቀል ረሃብ ከዚህ ጦርነት ጋር ተዳምረው ያቺን ውብየ ሃገር የምድር ሲኦል ለማድረግ እየሮጡ ነው።

እውነት ነው አንድ ሃገር የሚሊተሪ ተቋም የሚገነባው ዳር ድንበሩን ለመጠበቅና ከፍተኛ አሸባሪ ሲኖር የሃገርን ሉአላዊነት ለመጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚሊተሪ መፍትሄ (Military Solution) የሚገኝለት እንዳልሆነ በግልጽ እየታየ ነው። ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዩት ከባቢዎች ሁሉ ሃገራችን ጦርነቱን ኣቁማ ለድርድርና ለእርቅ እንድትንበረከክ የሚያስገድዱ ናቸው። በመሆኑም በዚህ ጽሁፌ ስር ሃገሪቱን ወደ ድርድር መግባባትና ብሎም እርቅ የሚገፉ ጉዳዮችን እያነሳሁ እንድንወያይ እጋብዛለሁ። ጦርነቱ ባስቸኩዋይ እንዲቆም የሚያስገድዱ ሁኔታዎች የሚከተሉት ናቸው።

1. ጦርነቱ የሲቪል ጦርነት መሆኑ

በአንድ ሃገር ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ከተነሳ ከፍተኛ የፖለቲካ ውድቀት እንዳለ ያሳብቃል። የፖለቲካ ኪሳራ ደግሞ በፖለቲካ ውይይት እንጂ በጦርነት አይፈታም። የኢትዮጵያ ጦርነት የሲቪል ጦርነት ነው ከሚያሰኙን ምክንያቶች አንደኛው የጦርነቱን ክተት ስናይ ነው። በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሞ ሃይሎች፣ በሶማሊያ ሃይሎች እካባቢ ያሉ የጦርነት የክተት አዋጆች ሁሉ ማንኛውንም መሳሪያ የታጠቀ ሰው እንዲዘምት የሚጠይቅ ነው። ፌደራል መንግስትም ይህንን ይሰብካል። ገበሬው፣ ተማሪው፣ ሃኪሙ፣ ነጋዴው ……ወዘተ. ሁሉም ያለውን መሳሪያ ይዞ ውጊያ እንዲገጥም በሁሉም ሃይሎች ክተት ታውጇል። ይህ አካሄድ በራሱ ከፍተኛ ኪሳራን ያመጣል። እጅግ ሁዋላ ቀር የጦርነት አዋጅ ነው። በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ በጥንት ጊዜ የነበረው ውጊያ እንዲህ ኣይነት ክተት ነበረ። መንግስታት የሰለጠነ የሚሊተሪ ተቋም ስላልገነቡ ጠመንጃ ያለውን ሁሉ ጦርነት ሲገጥማቸው ክተት ያዙት ነበር። ይህ ዘመን ኣልፎ ዛሬ አለም የባህር ሃይል፣ የኣየር ሃይልና የምድር ጦር አሰልጥኗል። በሃገራችን ያለው ክተት ሁሉን ኣሳታፊ ማድረጉ በራሱ የጦርነቱን ኣደገኛ ኣካሄድ ያሳያል። አንድ ሃገር አንዲህ አይነት ክተት ውስጥ ሲገባ ከፍተኛ እልቂትን አየጋበዘ ነው። ጦርነቱ በሙያተኛ የሚመራ ወታደር ከወታደር ሳይሆን ተማሪው ትምህርቱን ትቶ፣ ገበሬው ሞፈሩን ሰቅሎ፣ አስተማሪው ማስተማሩን ትቶ ክተት ውጊያ ከገባ ያቺ ሃገር ሲቪል ጦርነትን የደገሰች ሃገር ናትና ሃይ የሚል መካሪ ያስፈልጋታል። እንዴውም ያልሰለጠነ ሰው ጦርነት እገባለሁ ብሎ ቢያስቸግርም እንኩዋን ሊከለከል ይገባል እንጂ የትግራዩን ሲቪል፣ የአማራውን ሲቪል፣ የኦሮሞውን ሲቪል፣ የደቡቡን ሲቪል እየወሰዱ መማገድ ሲቪል ጦርነት (civil war) የሚባለውን መስፈርት እንዲያሙዋላ ያደርጋል። ይህ ደግሞ የእልቂቱን መጠን እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ የታሪክ ጠባሳው የከፋ ይሆናልና እንዲህ አይነት ጦርነት ባስቸኳይ መቆም አለበት ።

2. የሃገራችን ኢትዮጵያ ጦርነት ስሜት መኮርኮሪያው ማንነት መሆኑ

አንዱ የሲቪል ጦርነት ማሳያ ይሄ ነው። ዋናው የክተቶች ስሜት መኮርኮሪያ ዘዴው ትግሬውን ትግሬ ከመሆኑ ጋር በማያያዝ፣ አማራውን ከኣማራነቱ ጋር በማያያዝ፣ ኦሮሞውን ኦሮሞ ከመሆኑ ጋር በማያያዝ ነው የጦርነት አታሞ የምንደልቀው። ይሄ በጣም አስፈሪ የቅስቀሳ ዘዴ ነው። ማንነት እየነሸጠው ጦርነት ውስጥ የሚገባ ሃይል ከፍተኛ ውድመትን ከዚያም ከዚህም ያመጣል። ከሁሉ በላይ ግን ማንነቶች በተፈጥሮ የሚጋጩ አይደሉም። ማንነቶች እርስ በርስ ይከባበራሉ እንጂ አይጋጩም። የትኛውም ቡድን በባህሉ የኔ ምግብ ይጣፍጣል ያንተ ኣይጣፍጥም፣ የኔ ልብስ ያምራል ያንተ አያምርም ብሎ ጦርነት ኣይገባም። ኢንስትሩመንታሊስት የተባሉት ሃይሎች ይህንን የማንነት ስብሰብ ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ነው ማደራጃና ማጋጫ የሚያደርጉት። ታዲያ ማንነትን እየሰበቀ የሚመጣ ጦር ከሌላው ጦር የበለጠ መርዛማ ስለሆነ ሃገራችን ላይ የሚካሄደው ጦርነት ይህ ባህርይ ስላለው በፍጥነት ይቁም የሚል ጀግና ትውልድ ያስፈልጋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ''የመናፍቃኑ ተላላኪዎች መሠረተ ቢስ ውንጀላ ከአገልግሎታችን አንዲት ጋት ወደ ኋላ እንደማይመልሰን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን'' -ማኅበረ ቅዱሳን

ወደድንም ጠላንም የሰሜኑ ጦርነት በማንነት ላይ የተመሰረተ ነው። በሶማሌ ክልልና በኦሮሞ መካከል ያለው ግጭት ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው። ወለጋ ላይ ያለው እልቂት ማንነትን መሰረት ያደረገ ነው። በእንዲህ አይነት ከባቢ ውስጥ ያለ ሃገር በፍጥነት ይህንን እሳት ለማጥፋት ይረባረባል እንጂ የማንነትን ነጋሪት እየጎሰሙ ማጋጨት ማለቂያ የሌለው እልቂትን ስላመጣ በፍጥነት ተኩስ አቁመን ፖለቲካዊ መፍትሄ መፈለግ የግድ የሆነበት ምእራፍ ላይ ነን።

3. ይህ ጦርነት የሃገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑ

ጦርነቱ የጋራውን ቤታችንን የማፍረስ ሃይል ስላለው ሊቆም ይገባል። ከፍ ሲል እንዳልኩት ጦርነቱ በሃሳብ በተለያዩ ነገር ግን ጠንካራ ብሄራዊ ማንነትን በታጠቁ ሃይሎች መካከል አይደለም። የአካባቢ ማንነትንና የብሄር አርበኝነትን ስሜት በታጠቁ በማንነት ስሜት በሰከሩ ሃይሎች መካከል በመሆኑ በእውነት ኢትዮጵያን እሳት ላይ ጥዷታል።
ሌላው ችግር ጦርነቱ ውሎ ባደረ ቁጥር አንዳንድ ወገኖች ሃገሪቱ ወደ ኮንፌደሬሽን ትቀየር የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ። እጅግ በጣም ኣደገኛ ሃሳብ ነው። በነገራችን ላይ ኮንፌደሬሽን የተባለው የመንግስት ኣስተዳደር በኣሁኑ ሰዓት ከገበያ ውጭ ሆኗል። በኣለም ላይ በኮንፌደሬሽን የሚተዳደር አገር አንድም የለም። ሃገሮች ወይ በኣሃዳዊ አለያም በፌደራሊዝም ጥቂት ሃገራት ደግሞ በዘውድ ይተዳደራሉ። ሁሉም ሃገሮች እነዚህን ቅርጸ መንግስቶች አንደየ ሃገሩ ሁኔታ በልካቸው እየሰፉ የማይፈርስ ህብረት ፈጥረው ይኖራሉ። ኮንፌደሬሽን መተሳሰሪያ መርሆው ጥራት ስለሌለውና በተለያዩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበራት ስር የሚደረግ ቀጭን ትብብር በመሆኑ የጸና ህብረት ለመመስረት ኣያስችልም። ስለሆነም ኣለም እርግፍ ኣድርጎ ትቶታል። ሃገሮች ትብብር ሲፈልጉ አንዳድ ውል ይፈራረሙና የሚፈልጉትን ይሰራሉ፣ ሲፈልጉ ውሉን ያፈርሱታል። ኮንፌደሬሽን መመስረት አያስፈልግም። ከሁሉ በላይ አንድ ሃገር ወደ ኮንፌደሬሽን ለመግባት በመጀመሪያ የተለያዩ ሃገሮች ስብስብ መሆንን ይጠይቃል። ኢትዮጵያን ወደ ኮንፌደሬሽን እንመልስ ካልን የመጀመሪያው ደረጃ ሰማኒያ ሁለት ሉኣላዊ ሃገራትን መፍጠር አለብን። እነዚህ ሃገራት የየራሳቸው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት ፈጥረው ሲያበቁ ከዚያ በሁዋላ የፈለጉቱ በወታደርና በብር ጉዳይ የተወሰነ ስምምነት ኣድርገው በዚያ ስር መተዳደር የሚጀምሩት ስርዐት ነው ማለት ነው። ይህ ሂደት በኢትዮጵያ ሁኔታ አፍራሸ ነው የሚሆነው። ገና ትናንሽ ሰማኒያ ሁለት ሃገር ለመፍጠር ስንነሳ ጀምሮ ነው የምንጠፋው። ይህ አማራጭ በተግባር ሊሆን የማይችል ሃሳብ ነው። ስለዚህ የገባንበት ጦርነት ነገሮችን እያመረረ ወደመገንጠል ወደ ኮንፈእደሬሽን ተራ ሃገሪቱን ይዞ የሚሄድ ጦርነት ስለሆነ ባስቸኳይ ቆሞ ድርድር መደረግ ያለበት ኣንዱ ምክን ያት ይሄ ነው። ህብረታችንን የሚያፈርስ ጦርነት ነው።

4. ባልተረጋጋ የምስራቅ አፍሪካ ከባቢ ውስጥ ስለሆንን

ኢትዮጵያ ባስቸኳይ የርስ በርስ ጦርነቱን አቁማ ቀጣናዋን እንድትዋጅ የሚያስፈልግበት ምእራፍ ላይ ነች። ሱዳን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የታወቀ ነው። ከጎረቤት ሃገራት ሁሉ ሰፊ ድንበር የምንጋራው ከሱዳን ጋር ነው። አለም ያወቀው ወሰን ግን የለንም። የዚህ ቀጣና መታመስ በሃገራችን በቀጣናችን ላይ ተጽእኖ ኣለው። ሶማሊያ ሁል ጊዜም ባልተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ ያለች ሃገር ናት። ሶማሊያ ውስጥ የሚመጡ ለውጦች ሁሉ በሃገራችን ላይ ተጽእኖ አላቸው። ታሪካዊ ዳራችንን እያዩ ጊዜ ጠብቀው ሊያጠቁ የሚችሉ ሃይሎች በከባቢያችን ኣሉ። የጅቡቲና የኤደን ባህረ ሰላጤ ጉዳይ የአለም ኣቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት በመሳቡ ምክንያት ዛሬ ሃያላን ሃገራት በጅቡቲ ላይ ጦራቸውን ያሰፈሩበት ቀጣና ላይ ነን።

የመካከለኛው ምስራቅ የቀይ ባህር የቆየ እቅድና የወሃቢዝም መስፋፋት ቀጣናውን በአደጋዎች መሃል እንዲቆይ የሚያደርጉ ውጪያዊ ሁኔታዎች ናቸው። አልሸባብ ከፍተኛ አቅም አንዲገነባ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። የአፍጋኒስታን ፖለቲካ ከወዲያ ማዶ በአልሸባብ በኩል ያገኘናል። የሊቢያ ጉዳይ በአንድም በሌላም አያጣንም። የግብጽ የአባይ ወንዝ ዝንባሌ ሌላው የብሄራዊ ደህንነታችን ስጋት ነው። ዘጠና በመቶ የግብርና ምርቱዋን ከአባይ ደለል የምታፍሰው ግብጽ ኢትዮጵያ ስትረጋጋ ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍሉን መጠየቁዋ አይቀርም በሚል የርስ በርስ ጦርነቱን እንድንገፋበት ለሁሉም ሃይሎች መሳሪያ ማቀበሏ ኣይቀርም። በመሆኑም ጦርነቱን የውክልና ጦርነት (proxy war) ሙሉ በሙሉ ይቀልበውና የማያባራ ችግር ውስጥ እንገባለን:: ከዚህ በላይ በአሁኑ ሰዐት አፍሪካን ዘመናዊ ቅኝ ግዛት (neo-colonialism) እያሰጋት ነው። መንግስታችን ሲደክምና ጥንካሬያችን በርስ በርስ ጦርነት ሲመታ ቅኝ ያልተገዛችን ሃገር በአኛ ዘመን ለአዲሱ ቅኝ ግዛት ለ Neo-Colonialism አሳልፈን እንሰጥና እናርፋለን። የኢትዮጵያም እጣ ፈንታ የከፋ ይሆናል። ስለዚህ ችግሮቻችንን ከላይ ማየት አለብን። ከላይ ሆነን ስናይ የኛ የቤታችን ችግሮች ይቀሉና ይታዩናል።

ትላልቅ ፎቆች ላይ ስወጣ፣ በአውሮፕላን ስጓዝ ወደ ታች ማየት እወዳለሁ። ግዙፍ የተባሉ ነገሮች ሁሉ ትናንሽ ሆነው ሲታዩኝ ይገርመኛል። እርስ በርሳችን አማራ ትግሬ ኦሮሞ እያልን የምንጋጨው ነገሮችን ከታች እያየን እየገዘፉበን ነው። ከላይ ሆነን ስናይ፣ ከላይ ከሰባዊ ጉዳዮች፣ ከላይ ከዴሞክራሲ፣ ከላይ ከአለም አቀፍ ኝኙነት ማማ ላይ ሆነን ስናይ የወልቃይትና የጠገዴ ጥያቄዎች፣ የአፋርና የሱማሌ ውሃ ማጠጫዎች ኢምንት ጥያቄዎች ናቸው። እንተ ትብስ አንተ ትብስ የምንባባልባቸው ጉዳዮች ናቸው። ከፍ ብለን ለጋራ በሚሆን መላ ላይ ስንጠመድ የሁላችን ጥያቄ ይፈታል። ከላይ ቀጣናችንን ስናይ፣ ፓንአፍሪካኒዝምን ስናይ፣ የሌላውን ሃገር የዘርና የብሄር ግጭት ታሪክ ስናይ፣ የኛ የብሄር ጥያቄዎች ቀላል ናቸው።

ሁላችን ኢትዮጵያውያን እንደምናውቀው አሜሪካውያን ዲቪ የሚባል ብሄራዊ ፕሮግራም አላቸው። ከመላው አለም በየአመቱ እጣ እያወጡ እንግዶችን አሜሪካዊ ያደርጋሉ። ብዝሃ መሆንን ከመላው አለም ይለምናሉ። ከላይ ሆነው ማየት ችለዋል። የምትመጣውን አለም ዛሬ ላይ ሆነው አርቀው አይተዋል። እኛም መማር አለብን። ከፍ ብለን በማየት ትናንሽ ችግሮቻችንን እንፍታ። ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ስርዐት ፈጥረን ወደፊት እንራመድ እንጂ ብዝሃነትን ለጦርነት መሳሪያ አናድርግ።

5. ውጥረት ሲቆይ መፈንቅለ መንግስት ሊያስከትል ስለሚችል

አንድ ሃገር በሲቪል ጦርነት ውጥረት ውስጥ ውሎ ካደረ ማእከላዊ መንግስት ለመፈንቅለ መንግስት በጣም የሚጋለጥ ይሆናል። ጦርነቱ የሚያመጣው ተጽእኖ ከባድ ስለሚሆን፣ የኢኮኖሚ ኪሳራው ሰፊ ስለሚሆን፣ ጥያቄዎች ስለሚበዙ፣ የሰው ሃይል ኪሳራው ሰፊ ሰለሚሆን መፍትሄ ለመፈለግ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ እንደገና ለድርድርና ውይይት በር ለመክፈት የሚነሱ ሃይሎች ይኖራሉ። በደርግ ጊዜ ጀነራል ፈንታ ባላይ ሲናገሩ በመንግስቱ ሃይለማርያም ላይ ከፍተኛ መኮንኖች መፈንቅለ መንግስት የሞከሩት ሃገሪቱ አስራ ሰባት ኣመት ሙሉ ተዋጋች። ደቀቀች። በዚህ ጦርነት መቀጠል ኣይቻልም። ፖለቲካዊ መፍትሄ ይፈለግ ከሚል ነው። በተለይ በኣሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጦርነት ቅጥ ያጣ፣ ወጥነት ያለው እዝ የሌለው ከመሆኑም በላይ ሰባዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራው ፈጣንና ግዙፍ በመሆኑ የመፈንቅለ መንግስት ኣነሳሽ ጉዳዮችን በጣም ኣፋፍቷል። ይህ ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ ሌሎች ኣሁን የማናያቸውን ለውጦች ሁሉ ሊያመጣ የሚችል ነው። እንዲህ አይነት ጉዳይ ውስጥ ከመግባት ሁሉን ኣቀፍ ድርድርና ውይይት በጊዜ መጀመር ይሻላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  Green card lottery: US reviews 'diversity visa' glitch

6. አለም አቀፍ ግንኙነታችንን በፍጥነት እያበላሸ ነው

የርስ በርስ ጦርነት ስማችንን ሁሉ በመላው ኣለም እየበከለው ነው። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ምስል ላይ፣ በንግዳችን ላይ፣ በነበረን ክብር ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ኣለው። እኛ ኢትዮጵያውያን ነጻ ህዝብ መሆናችንን እንደ ቀላል ታሪክ እናየው ይሆናል። ነገር ግን ታሪካችን እስከ ላቲን ኣሜሪካ ድረስ አስከ አስያ ድረስ የገነነ ነው። የነጻነት ፈርጥ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ኩራት ምንጭ ነን። ይህ ታሪካችን በመላው ኣለም ዘንድ ክብርና ሞገስን ያጎናጸፈን ቢሆንም ኣሁን በገባንበት የርስ በርስ ጦርነት ግን ጭቃ እየቀባነው ነው። የአባቶቻችንን ታሪክ እያጠፋን ነው። የአድዋ ጀግኖች ልጆች ዛሬ እርስ በርስ ሰይፍ ሲማዘዙ የሚያይ ኣለም በሚዛኑ ላይ በጣም ያቀለናል። ከዚህ ከክብራችንና ዝናችን መንኳሰስ በተጨማሪ በቱሪዝማችን ላይ፣ በንግዳችን ላይ ከባድ ተጽእኖ እያመጣ ነው። ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ተጋጭተናል፣ ከምእራብ ሃገሮች ጋር ያለን ግንኙነት ጥሩ አይደለም። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ይጎዳብናል። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በሚኖራት ጥሩ ያልሆነ ግንኙነት ከኣገዋ (AGOA – African Growth and Opportunity Act) ብንወጣ ብሄራዊ ጥቅማችን ይጎዳል። ይህ ብቻ አይደለም በቀጥታ ንግዳችን ላይ እንከን ይበዛል። ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ አንችልም። ለልማት በምንሻው ብድር ላይ ከባድ ተጽእኖ ኣለው። በአጠቃላይ ልማታችንን የሚጎዳ ነውና ጦርነትን ኣቁመን የፖለቲካ መፍትሄ እንድንሻ አንድ ገፊ ምክንያት ነው።

7. የወደፊቱዋን ኢትዮጵያን ለማሳመር

የነገይቱ ኢትዮጵያ ሁኔታ የሚወሰነው በዛሬው ተግባራችን ነው። ዛሬ የምንዘራው ዘር ሁሉ ነገ ፍሬው ይታያል። ታላቁ መጽሃፍ ሰው የዘራውን ያንኑ መልሶ ያጭዳል ይላል። ጦርነትን ብናዘምር ጥላቻን ቂምና በቀልን ነው የምናጭደው። ሃገራችን ኢትዮጵያ በጦርነት ብትቀጥል የወንድሞቻችን ሞት ይቀጥላል፣ መፈናቀል ይቀጥላል፣ የኢኮኖሚ ድቀት ይቀጥላል ማለት ነው። የዚህ ሁሉ ችግር ምርት ደግሞ በነገይቱ ኢትዮጵያ ላይ ያለው ተጽእኖ ከባድ ነው። አንድን ህንጻ በአንድ መድፍ ማፍረስ ቀላል ነው። ይህንን ህንጻ መልሶ መገንባት ግን ከባድ ስራ ነው። ጦርነት ቀላል ነው። የጦርነትን ውጤቶች መቀልበስ ግን ከባድ ስራ ነው። ስለዚህ የጦርነቱን ጥላዎች በማሰብ ስለነገይቱ ኢትዮጵያ ሲባል ጦርነት መቆም አለበት። ብሄርን ከብሄር ለማጋጨት አንድ ቃል ሊበቃ ይችላል። ነገር ግን ማህበራዊ ሃብትን (social capital) ለማደስ ብዙ ድካምን ይጠይቃል።
ተወደደም ተጠላም በማንነት ተኮር የጦርነት ጊዚያዊ ድሎች ላይ የዴሞክራሲ መሰረት መጣል አንችልም። ለወደፊቱዋ ኢትዮጵያ የተሻለ መሰረት የምንጥለው በወንድማማቾች ደም ላይ አይደለም።

8 አሸናፊና ተሸናፊ ስለማይኖር

የርስ በርስ ጦርነት ችግሩ ይሄ ነው። ሶማሊያ እንድ ጊዜ ወረረችንና ተባብረን ልክ አስገባንና ሃውልት ተክለን ቁጭ አልን። አሁን ያለው ማንነትን መሰረት ያደረገ ጦርነት ማሸናነፍና መሸነፍ የለውም። ከተማ በተቆጣጠርን ቁጥር ብንፎክር አሸናፊነት በዚህ አይለካም። እንበልና ህወሃት አየተገፋ ሄዶ መቀሌ ተያዘች የሚል ዜና ቢሰማ ጦርነት አለቀ ማለት አይደለም። መንግስትም ከዚህ በፊት መቀሌ ገብቶ ነበር። ህወሃት እየገፋ መጥቶ አዲስ አበባ እንደገና ገባ ቢባል ዋጋ የለውም። ህወሃት ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ገብቶ ነበር። ማንነትን እየጎተተ ከተማን የሚቆጣጠር ሃይል ከጦርነት አዙሪት አይወጣም። ማንነቱ ተነካብኝ የሚል ሃይል ሸምቆም ቢሆን ሲዋጋ ይኖራል። በዚህ መሃል ወደ ልማት ማተኮራችን ቀርቶ እየደከምን….. እየደከምን … እየደከምን ….. ሄደን ተያይዘን እንወድቃለን። ስለዚህ ለሁላችንም መልካሙ ነገር የፖለቲካ መፍትሄ ነው። እንዱን አስከፍቶ አንዱን አስፎክሮ የሚመሰረት ህብረት አይጸናምና።

ለ. የድርድሩ የመጀመሪያ እርምጃ ምንድን ነው?

ከፍ ሲል እንዳልኩት ዋናው ጉዳይ ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደ ድርድር ብሎም ወደ እርቅ መግባት አለባት የሚለው ሃሳብ ተገቢነቱን ከማመኑ ላይ ነው። ይህንን ካመንን በሁዋላ ሁሉም የታጠቁ ሃይሎች ወደ ድርድር ለመግባት የመጀመሪያው እርምጃቸው መሆን ያለበት በጊዜ የተገደበ ተኩስ ኣቁም ነው። ይህንን ለማድረግ የቅድመ ሁኔታዎች ጥያቄ ከየትኛውም አካል መምጣት የለበትም። በቅድመ ሁኔታነት የሚነሱ ጥያቄዎች በዋናው ድርድር ላይ ተነስተው መፍትሄ ያገናኛሉ። የቅድመ ሁኔታ ጥያቄዎችን እንድ የድርድር አካል ማድረግ ተገቢ ነው። ስለሆነም ድርድሩን በቅድመ ሁኔታ ወጥሮ ማሰናከል ተገቢ ኣይሆንም። ቅድመ ሁኔታዎችን በቀጣይ በኣጀንዳ መልክ ለማንሳት ተስማምቶ ለድርድርና ለእርቅ ተንበርካኪ በመሆን ብረት ማውረድ የመጀመሪያው ደረጃ ይሆናል።

ታዲያ ሁሉንም ወገን ተኩስ ኣቁምና ለድርድርና እርቅ ተንበርከክ የሚል ጥሪ የሚያነሱ ሃይሎች እነማን ናቸው ካልን ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከምሁራን፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከወዳጅ ሃገራት ሰዎች የተውጣጡ ግለሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ። የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማውረድ የሚያስችል አስማሚ ግብረ ሃይል ለመገንባት በተለይ የሲቪክ ድርጅቶች በፍጥነት ሃላፊነት መውሰድና ይህንን ሃይል ማቆም አለባቸው። የተኩስ ኣቁም ስምምነቱ ከተጀመረ በሁዋላ የሚቀጥለው ስራ ሰፋ ያለ ተግባር ይጠይቃል።
1. ተደራዳሪ ሃይሎችንና ኣደራዳሪዎችን መለየት የድርድር ስነ ስርዐት ማርቀቅ

ይሄ ኣንድ ወሳኝ ምእራፍ ነው። ድርድርና እርቁ እንዲሰምር ሁሉን ኣሳታፊ የሆነ ድርድር ማድረግና ገለልተኛ አደራዳሪ መምረጥ በጣም ወሳኝ ምእራፍ ነው። ድርድሩ በሁለት የገነኑ ሃይሎች መካከል ብቻ መሆን የለበትም። በሶማሊያና በአፋር ክልል አካባቢ ያሉ ችግሮች የሚፈቱት፣ በኦሮሞ አካባቢ ያሉ ችግሮች የሚፈቱት፣ በደቡብ አንዳንድ ኣካባቢዎች ያሉ ችግሮች የሚፈቱት በድርድር ነው። ስለዚህ ድርድሩ የሃገራችንን ሁለንተናዊ ህመም የሚዳስስ መዋቅሩዋን የሚዳስስ እንዲሆን ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎች ያሳተፈ መሆን አለበት። ብልጽግና እና ህወሃት ብቻ ተደራዳሪ ቢሆኑ ድርድሩ ፍሬ ቢስ ሆኖ ከጦርነት አንወጣም።

ስለዚህ የታጠቁ ሃይሎችን ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትና ተሳታፊ ማድረግ ያስፈልጋል። የባልደራስ አመራሮች መፈታት አለባቸው። ጃዋር መሃመድና ሌሎች የኦፌኮ አመራሮች መፈታት አለባቸው። ህዝብ የሚጸጸትባቸው የፖለቲካ እስረኞች መፈታት አለባቸው። ድርድሩ ሃገሪቱን ወደ አዲስ ምእራፍ የሚወስድ መሆን አለበት።
በሌላ በኩል ገለልተኛ አደራዳሪ በማስመረጡ ረገድ ከፍ ሲል የተኩስ ኣቁም ስምምነት እንዲደረግ ያገዙት ሃይሎች ተደራዳሪዎች በአንድ ላይ ከቀረቡ በሁዋላ ዋናውን ኣጀንዳ የሚያደራድሩዋቸውን ሰዎች እንዲመርጡ ቢያደርጉ መልካም ነው። አደራዳሪዎች የሽምግልና ስራ እየሰሩ በሃቀኝነት የሚያደራድሩ ሊሆኑ ይገባልና ተደራዳሪዎች ጊዜ ወስደው አደራዳሪ እሚመርጡበት ሁኔታ መመቻቸት አለበት ። እነዚያ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያወረዱና ኑ ተደራደሩ ያሉቱ የሽግግር ስራ ሰርተው አድራሽ ሆነው ቢቆዩ መልካም ነው። ሌላው ጉዳይ የድርድሩን መርሆዎችና ስርዐቶች ማርቀቅና ማጽደቅ አስፈላጊ ነው። ፍሬአማ ውይይት ለማድረግ ሳይንሳዊ ውይይት ማድረግ ጠቃሚ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰሞኑን በቁጥጥር ስር የዋሉትን ግለሰቦች በተመለከተ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች አስተያየታቸውን ሰጡ

1. ኣጀንዳ መሰብሰብ

ከዚህ በሁዋላ ተደራዳሪዎች ኣጀንዳቸውን እንዲያቀርቡ በማድረግ ረጋ ባለ መልኩ አጀንዳዎችን መመዝገብ መሰብሰብ ተገቢ ይሆናል። እነዚህ ኣጀንዳዎች አብዛኞቹ ብሶቶች ቢሆኑም ተደራዳሪዎች ሳይሸማቀቁ የሚሰማቸውን እንዲያቀርቡ መደረጉ ለፈውስ ወሳኝ ነው። አደራዳሪዎችም ተደራዳሪዎች የሚያቀርቡትን አጀንዳ መዝግበው በቅጡ ማስተናገድ የሚችሉ አቅም ያላቸው ናቸው።

2. አጀንዳ የማጥለልና የማደራጀት ስራ መስራት

የሚቀርቡ ብሶቶች ሁሉ አጀንዳ ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለታሪክ በመጀመሪያ ደረጃ አጀንዳነት ተቀርጸው ይቀመጡ። ከዚህ ቀጥሎ ግን አጀንዳዎቹን ግልጽነት እንዲኖራቸው የማጥለል፣ የማርቀቅ፣ ሃሳቡን የማጠቃለልና የማደራጀት ስራ ያስፈልጋል። ግልጽነት በጎደላቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜ ማጥፋት ጉንጭ ማልፋት ከመሆኑም በላይ ድርድር ሊያቆራፍድ ይችላል። ስለሆነም ተቀራራቢ ሃሳቦችን በማጠቃለልና ስርዐት በማስያዝ አጀንዳዎቹን መቅረጽ ያስፈልጋል።

3. የድርድር መቼት

ተደራዳሪዎችና አደራዳሪዎች ጊዜንና ቦታን መወሰን ኣለባቸው። የሃገራችን ጉልህ ችግር ለቁም ነገሮች ጊዜ ኣንሰጥም። ለማይሆኑ ነገሮች ደግሞ ኣንሰለችም። ይሄ መለወጥ አለበት። በተለይ ይህ ድርድር አመርቂ የሚሆነው ሰፊ ጊዜ ሰጥተን ስንመክርበት ነው። ለእከሌ 10 ደቂቃ ሰጥቻለሁ፣ ለእከሌ 5 ደቂቃ ሰጥቻለሁ……… በሚል ኣይከናወንም። ለረጅም ቀናት ቁጭ ብለን ሃሳቡን መውቀጥ፣ መሰማማት፣ ህማም መካፈል ያስፈልጋል። ከፍ ሲል እንዳልነው ሃገራችን ጦርነትን የምትመርጥበት በሮች ዝግ ስለሆኑ ከውይይት ከድርድር መፍትሄ ይገኝ ዘንድ ሰጥቶ መቀበልን መርህ ኣድርጎ መደራደር ያስፈልጋል። ጊዜ በጣም ወሳኝ ነው። በሌላ በኩል ቦታም ወሳኝ ነው። በዚሁ መሰረት ታርካዊ የሃገራችን ቦታዎች ኣካባቢ እየተዘዋወሩ መወያየት በጣም ተገቢ ነው ብየ አምናለሁ።

4. በተመረጡ ኣጀንዳዎች ላይ ድርድር ከተደረገ በሁዋላ የመፍትሄ ሃሳብና ሮድ ማፕ ማዘጋጀት

የሃግራችን ችግሮች ሁሉም በአንድ ጊዜ አይፈቱም። አንዳንዶቹ ዝግ እያለ በሚያድግ ዴሞክራሲ የሚፈቱ ናቸው። አንዳንዶቹ በመዋቅር ለውጥ የሚፈቱ ናቸው። አንዳንዶቹ በህግ ማሻሻያ የሚፈቱ ናቸው። ኣንዳንዶቹ በሰው ሃይል ድልድል የሚፈቱ ናቸው። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የጋራ ሮድ ማፕ ማዘጋጀት ይጠይቃል። ይህ ሮድ ማፕ በድርድሩ ወቅት የተነሱትን ጉዳዮች ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት።

5. የተዘጋጀውን ሮድ ማፕ ወደ ተግባር ለመቀየር የሽግግር ጊዜ መፍጠር

ኢትዮጵያ ሃገራችን እስካሁን የሽግግር ጊዜ አይታ አታውቅም። ይህ ደግሞ ጎድቶናል። ባለፈው ጊዜ ለውጥ መጣ ሲባል ሁላችን የሽግግር ሃሳብን ተቃውመን አሁን ስልጣን ላይ ያለው የኢሃዴግ ክፋይ የሆነው ሃይል ለውጡን ይምራ ብለን ነበር። እንደ ሃገር ተሳስተናል። ያለ ሽግግር መንግስት ሽግግር ሊኖር አይችልም። የሽግግር መንግስት በጣም ኣስፈላጊ የሽግግር ዋና ኣካል ነው። እኛ ይህንን ምእራፍ መዝለል ፈለግን። ይህ ደግሞ ውሎ ሳያድር ጥያቄ ኣመጣ። ወደ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ የሚወስደን ዋና የሽግግር ኣካል የሽግግር መንግስት ነው። ስለሆነም ከድርድሩ በሁዋላ የተውጣጣ የሽግግር ጊዜ በመፍጠር ሃገሪቱ ወደ ተሻለ ምርጫ እንድትሄድ ማድረግ ከተቻለ ድርድሩ በእግሩ ቆመ ማለት ይሆናል።

6. እርቅና ካሳን የሚያካሂድ ተቋም መፍጠር

በጦርነቱ ጊዜም ይሁን ከዚያም በፊት ተጎድተናል የሚል ቡድን አለ። ቁስሉን እያሳየ ጉዳቱን ይቆጥራል። አንዳንዱ ጉዳት ማንነት ተኮር ይሆናል። ሌላው ደግሞ ከጦርነት ጋር በተያያዘ ይሆናል። ብቻ እንዳንዶቹን ጉዳቶች በሚያደግ ዴሞክራሲ እየፈቱ መሄድ፣ አንዳንዶቹን ጉዳቶች የተለያዩ የመካሻ ዘዴዎችን (Affirmative actions) በመፍጠር እየካሱ ማህበራዊ ፈውሶችን ማውረድ፣ የሪስቶረቲቭ ፍትህንና የሪትሪቢዩቲቭ ፍትህን (restorative and retributive justice) ተግባራዊ በማድረግ ቁስሎችን ማከም ያስፈልጋል። ከሁሉ በላይ ለቡድንም ለግለሰብም ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ ሮድማፕ ወይም ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ኢትዮጵያን መካስ ያስፈልጋል። የተሻለ ቅርጸ መንግስት፣ ህገ መንግስት በመፍጠር እርቅ መውረድ አለበት ለዚህ ደግሞ ተቁዋም ያስፈልጋል። የድርድር ሃሳቡ መሬት እንዲቆነጥጥ ተቁዋም ያስፈልጋል።

ሐ. ድርድሮች ባይሳኩስ?

ድርድሩ በተለያየ መንገድ ላይሳካ ቢችል የአለም ፍጻሜ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የመጀመሪያው ዙር ድርድር ካልሰራ ድርድሩ የወደቀበትን አቅጣጫ መመርመርና የሚቀየረውን ቀይሮ እንደገና ሁለተኛ ዙር ድርድር ማድረግ ብልህነት ነው። ዋናው ጉዳይ ጦርነቱን ከቦምብና ከመድፍ አውርደን በአንድ አዳራሽ ውስጥ በሃሳብ ላይ የሚደረግ ጦርነት ከማድረጉ ላይ ነው አጥብቀን ማመን ያለብን። ከአደራዳሪዎች የተነሳ፣ ከተደራዳሪዎች ባህርያት የተነሳ ድርድሩ ባይሳካ እነዚህን ችግሮች ቀርፎ እንደገና ለሁለተኛ ዙር መዘጋጀት አንጂ የሰቀልነውን ጠመንጃ አውርደን መደባደብ መጀመር የለብንም። ጠብመንጃ የምንይዘው ተኩስ ማቆም በአንድ አካል ብቻ የሚከወን ሊሆን ስለማይችል ነው። ማንም ቢሆን የመከላከል መብት አለው። ስለዚህ ድርድሮች ሲሰናከሉ እንደገና መሞከር ዋና ገዳይ ነው። በሁለተኛ ደረጃ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ቀጥታ የህዝብ ነጻ ፈቃድ የሚያስፈልግበት አጀንዳ ላይ ህዝብ ገላጋይ ይሆናል።

መ. የድርድሩ ሳንካዎች?

በሃገራችን ውስጥ ድርድር አንዳይኖር አጥብቀው የሚሹ ሃይሎች አሉ። እነዚህ ሃይሎች የተለያየ ዝንባሌ አላቸው። አንደኛው ድርድርና እርቅ ጠል የሆነው ሃይል ገንጣይ ነው። ነገሮች እንዲካረሩ ይፈልጋል። ነገሮች ሲካረሩና ዘርማጥፋት ሲመጣ በዚህ ምሬት ላይ የተለያዩ ትናንሽ ሃገራት የመፍጠር ህልም ያላቸው አሉ። ሌሎች ደግሞ የኢትዮጵያን ሰላም ከማይሹ ጋር ተመሳጥረው ሃገር ሲበጠብጡ የሚኖሩ ሃይሎች ናቸው። ድርድሩ በነዚህ ሳንካዎች የተከበበ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ነቅተን መታረቅ አለብን። ሌላው በድርድር ሃሳቡ ላይ የሚነሳው ጥያቄ ደግሞ ጨርሶ የሃላፊነት ስሜት የጎደለው ነው። አንዳንዶች ድርድር አሁን ጊዜው አይደለም ብዙ ንብረት ወድሞ ብዙ ሰው አልቋል ይላሉ። አነዚህ ሃይሎች የሚሉት አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር ነው መዋጋት ያለብን የሚሉ ይመስላሉ። ይሄ ተገቢ ጥያቄ አይደለም። ያለፈው አልፎ አሁን ወደነፍሳችን መመለስ ተገቢ ነው። ሩዋንዳ ከዚያ እልቂት በሁዋላ ወደ ነፍሱዋ ተመልሳ ዛሬ በብዙ ነገር በልጣናለች ። አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር እንዋጋላን ድርድር ጊዜው አልፉዋል የሚሉት ጨካኞች ናቸው።

አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ። ከብዙ አመታት በፊት የሆነ ቦታ የሰማሁት ነው። በደርግ ጊዜ መንግስቱ ሃይለማርያም ብዙ ጊዜ አንድ ሰውና አንድ ጥይት አስኪቀር ድረስ እንዋጋለን ይል ነበር አሉ። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን አንዱ ደፋር በሆነ አጋጣሚ መንግስቱን ያገኝና አንድ ሰውና አንድ ጥይት አስኪቀር አንዋጋለን ለመሆኑ ያ አንድ ሰው ማን ይመስልዎታል? ብሎ ጠይቆ ብዙ ሰው አስፈግጎ ነበር ይባላል።

ይሄ አደገኛ ሃሳብ ነው። ትግሬው አማራውን ገድሎ ቢፎክር፣ አማራው ትግሬውን ገድሎ ቢፎክር፣ ኦሮሞው ሱማሌውን ገድሎ ቢፎክር የሁላችን እናት ሃገር ኢትዮጵያ አትደሰትም። አንዲት እናት ልጆቿ ተጣልተው በሰይፍ ቢተላለቁ የግራውም የቀኙም በወደቀ ቁጥር ሃዘን ላይ ናት። ስለሆነም መላው ኢትዮጵያዊ ድርድርና እርቅን የሚገፉ ሃይሎችን መታገል አለበት ። ደም በደም አይጠራም ይቅር እንባባል ማለት ያስፈልጋል።

ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የፖለቲካ ለሂቃኑ ወደ ድርድር መጥተው ብሄራዊ እርቅ ወርዶ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከነበራት ህብረት ምንም ሳትጎድል እንዴውም ወደ ተሻለ አንድነትና ህብረት እንድትገባ ሁላችንም ወደ ፍጹም ህብረት (Towards Forming A More Perfect Union) ግባችን አድርገን መታገል አለበን። የተባበረችውን ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ሳንካውን ማንሳት አለብን። ከሁሉም በላይ እግዚአብሄር ይርዳን። እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

እንታረቅ !

5 Comments

  1. በማንነት ላይ የሚደረጉ ግጭቶች ሁሉ ፍጻሜአቸው እርስ በእርስ መተላለቅ ነው። ሌላው ነዳጅ አርከፍካፊና በግጭቱ ዙሪያ ትርፍ ፍለጋ ተርመስማሽ ሃይል ነው። ይኸው እንሆ የግብጽ ፍላጎት በሱዳን መፈንቅለ መንግስት በመደረጉ ተሳክቶላታል። ይህ ግን ለግብጽ ህዝብም ሆነ ለሃበሻይቱ ምድር መልካም አይደለም። የአፍሪቃው ፓለቲካ ውሻነቱ እዚህ ላይ ነው። ለዚህ ለዚህ እማ አልባሽርስ ምን አጠፋ? አፍሪቃዊው ፓለቲካ ሲመች የእድሜ ልክ ( አዲስ ንጉስ) ካልሆነ ደግሞ የመለዪ ለባሽ መንጋ የሚነዳት መሆኗ በሌላው ዓለም እንድንናቅና እንድንጠላ አድርጎናል። ገና ይህ ሁሉ ጉዳይ በትግራይ፤ በአማራና በአፋር ሳይከሰት እናቶች እያለቀሱ የለመኑት ደብረጽዪን ዛሬ ምን ይል ይሆን? ወያኔዎች እብዶች ናቸው። የትላንትናው ታሪካችው ዛሬም ያው የሆነ። አፈናና ደም ማፍሰስ። የአረመኔዎች ስብስብ። ፈጣሪ ከምድረ ገጽ ያጥፋችሁ።
    እውቁ የወሎ ታጋይ ሃጂ ሃሰን ከረሙ በቅርብ እንዲህ አሉ። “ህዝባችን ከጂኒ (ሰይጣን) ጋር እየኖረ ነው። ኑ ተከተሉኝ እናጥፋቸው”። ትክክለኛ አባባል ነው። የዚህ ማጠናከሪያ ሃሳቡን ላቅርብ። በቅርቡ ከመቀሌ አምስት ገጽ ሙሉ የተጻፈ ደብዳቤ በውጭ ሃገር ቴምብር አሸብርቆ ደረሰኝ። ትንሽ ግራ ከተጋባኝ በህዋላ ከፍቼ ሳየው የቅርብ ጓደኛዬ የትግራይ ተወላጅ የጻፈልኝ ደብዳቤ መሆኑ ገባኝ። ይድረስ ለምወድህ ወንድሜ እንዴት ከርመሃል? እኛ በሲኦል ውስጥ ነን። የጻፍኩልህን ደብዳቤ ረጋ ብለህ አንበህ ለወገኖቻችን ድምጻችን አሰማልን። አደራ። ከጻፍኩት ስለቆየ ይህ ደብዳቤ ከእጅህ ሲገባ ነገሮች ሊከፉ ይችላሉ። ያም ሆነ ይህ ዝም እንዳትል ይልና ከብዙ ነገሩ የሚከተለውን ይላል።
    ወያኔ የትግራይን ህዝብ እየጨረሰና እያስጨረሰ ነው። በአይኔ ከተመለከትኩት ጥቂቱን እንሆ።
    1. በየቤቱ እየተዞረ ምንም የሌለውን ህዝብ 2 ወይም ከዚያ በላይ እንጀራ እየለመኑ ለጸሃይ በማስጣት ድርቆሹ ተወቅጦ ወደ ሜዳ ይላካል። እንጀራው የተወሰደባቸው ጾማቸውን ያድራሉ።
    2. ልጆቻችሁን ለትግል ስጡ እየተባለ ታፍሰው በአጥር ከታጠረ ስፍራ ይወሰዳሉ። ግማሹ ሊጠፋ ሲሞክር በጥይት ተደብድቦ ይሞታል (ይህን በአይኔ አይቻለሁ) ሌላው ጥያቄና ቁጣ ቀላቅሎ በመጠየቃቸው የት እንደተወሰድ አይታወቅም። ተረሽነዋል ብለን እናምናለን።
    3. ወጣቶችን ጦርነቱን አሸንፈናል በማለት እያታለሉ የሳምንት በዛ ከተባለም የሁለት ሳምንት ስልጠና በመስጠት ያላሰቡት የጦር ቀጠና ውስጥ በማስገባት ከህዋላ ሌላ ሃይል አሰልፈው እንዳይመለሱ ይተኩሱባቸዋል። አፈገፈጉ የተባሉትም ይገደላሉ። በወረራ ቦታዎች ጭካኔ ያሳዩትን ልዪ ጥቅም በመስጠት ለሌላ ጥፋት ይገፏፏቸዋል።
    4. በመቀሌ ከተማ ችግሩ በጣም በመስፋፋቱ ሰው ይሰርቃል። አስቁሞ ይዘርፋል። ህግና ስርዓት የለም። ትላንት መከላከያውና የኤርትራ ወታደር ሴቶችን ደፈሩ እያለ ይጮህ የነበረው ወያኔ ዛሬ የትግራይ ሴቶች በወሮበላዎችና ጠበንጃ ባነገቱ የወያኔ ካድሬዎች ይደፈራሉ። በጣም የሚያሳዝነኝ ግን በውጭ ያሉ የትግራይ ልጆች አሁን ይህን አውሬ ድርጅት አምነው መከተላቸው ነው። ግን አይፈረድባቸውም። ብዙዎቹ የወያኔ ጥቅም ተካፋዪች ናቸውና። አንድ ነገር ልበልና ይብቃኝ ይላል ብዙ ልብን የሚነካ ከዚህ ላይ መጻፉ አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ካስነበበኝ በህዋላ እንዲህ ይላል። ጊዜው ምሽት ነው። በመኪና የሆኑ ሰዎች ወድ 5 ሺህ ወጣቶች በግድና በመዋጮ የታፈሱ ታጉረዋል። በድንገት የሰዎች ስም መጠራት ጀመረ። ከዚያም ከመኪና ላይ እያስወጡ ይዘዋቸው ሄድ። በህዋላ ስንሰማ ወላጆቻቸው በብዙ ሺ የሚቆጠር ገንዘብ ከፍለው እንዲለቀቁ ያደረጓቸው የሃብታም ልጆች መሆናቸውን አወቅን። ይህ ነው በትግራይ ያለው እውነታ። ግን ማን ይሰማን ይሆን በማለት ደብዳቤውን ይዘጋል።
    ልብ ያለው ሰው ከግጭትና ከጦርነት እርቅ ማድረጉ መልካም ነበር። ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረስን እንወርዳለን የሚሉ እብዶች ባሉባት የትግራይ ምድር እንዴት ባለ ሂሳብ ነው እርቅ የሚኖረው? እናትና አባቱ በደሳሳ ጎጆአቸው በወያኔ አረመኔዎች ከውጭ ተዘግቶባቸው በእሳት የተቃጠሉት አጽም እርቅ አናርግ ያስብላል? አንዲት ወጣት ለአራት ይዘው እረ ድረሱልኝ እያለች የተደፈረችው እናትና አባት ወያኔን ይቅር ይላሉ? አማራ ጨካኝ ነው እየተባሉ በአደንዛዥ እጽ ተሳክረው እየገደሉ የሞቱት የወያኔ ጀሌዎችና ትራፊዎቻቸው የአማራ ህዝብ ጭራቅ እንዳልሆነ የተማረኩ የትግራይ ተወላጆች ይናገራሉ። ግን ወያኔ ከራሱ የሙታን ፕሮፓጋንዳ ሌላ የትግራይ ህዝብ ሌላ የዜና ማሰራጫ እንዲያዳምጥ አይፈቀድለትም። አሸንፈናል፤ ድል አድርገናል። በሁለት ሳምንት አዲስ አበባ ገብተን ጦርነቱ ይጠናቀቃል የሚሉት ወያኔዎች ምን ተቃምሰው እንደሆነ ጤነኛ ሰው ሊረዳው አይችልም። ግን እኮ የተቃመሱት ጥላቻን ነው። እንደ ቅጠል የሚረግፈውን የወያኔ ጄሌና ታጣቂ ከሰው አይቆጥሩትም። አይ ወያኔ ውሸቱን ተግቶ ሌላውን የጋተ የሞተ ድርጅት ነው። አንድ ነገር ልጨምርና ላቁም።
    ጊዜው ቆይቷል ወያኔ ተሳክሯል። ትንሽ ለዘብ ያለ እይታ አላቸው የተባሉ የአመራር አባሎችን ለማስወገድ መንገድ እየፈለገ ነው። ሳይታሰብ አትፈለጉም ተብለው ነባር የወያኔ የአመራር አባላት ይሰናበታሉ። ከተሰናባቾች መካከል የዛሬው ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ይገኙበታል። ከዚያም ወደ ሱዳን ይሻገራሉ። አረጋዊ በሜዳ እያለ የሴት ጉደኛ ነበረችው። ወያኔ አረጋዊን ካባረረ በህዋላ እሷን በባዶ ስድስት እስር ቤት ያደረሱባት ገመና የወያኔን አውሬነት በግልጽ ያሳያል። ይህች ሴት አሁን በሆላንድ ትኖራለች። የደረሰባትንና በአይኗ ያየችውን ለምን እንደማትናገር አይገባኝም። ወያኔ ከጎኑ ለዘመናት ተሰልፈው ለተዋጉትም አይራራም። አዲስ አበባ እንደገቡ 30 ሺህ የትግራይ ታጋዪችን ነው ወደ ሃገራችሁ ሂድ በማለት ያባረሯቸው። ስንቶች ናቸው በንዴት ወደ አልፈለጉት ገብተው የሞቱት? የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት? ያን ያየና የሰማ የትግራይ ተወላጅ ለዚህ አጥፊ ድርጅት እንዴት እንደገና ታጣቂ ይሆናል። የትግራይ ህዝብ ወያኔን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እስካላስወገደ ድረስ ሰላምን አያገኝም። ከዚህ ድርጅት ጋርም እርቅ የሚታሰብ ነገር አይሆንም። በቃኝ!

  2. What one collects from ato Geletaw`s long piece is that he is an appeaser. What he misses or omits in his piece is the fact that the TPLF is a fascist organization whose track records show that it is against any reconciliation. In addition, the TPLF leaders are responsible for the mayhem in Northern Ethiopia and opened war fronts. Appeasing fascism is the worst political blunder as one learns from history.

  3. ወንድሜ ደም በደም አይጠራም ያልከው ትክክል ነው ልብ ማለት የሚያስፈልገው አሁንም ሁሌም እንደሚባለው መሬት ላይ ያለው ሀቅ እንደሚያሳየው ጦርነቱ ማንነት ከማንነት ጋር አይደለም ከተወሰኑ ቡድን ጋር ነው ሰው መሆናቸውን እጠራጠራለሁ በፍፁም ሰው እኔ ካልገዛሁ አትኖርም ብሎህ ይህን ሁሉ ህይወት እንዲቀጠፍ ያደርጋል ወንድሜ በዚህ በጀመርከው ብእር ጁንታው ከተደመሰሰ በሁዋላ የነበረው ሰላም እንዲቀጥል ምን አይነት ስራ መሰራት አለበት ህዝቡን እንዴት እናገናኘው እንዴትስ ቁስላችንን እናክመው የሚል ስትራተጂ ፃፍልን ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃት አመሰግናለሁ

  4. ውድ አቶ ገለታው ዘለቀ
    ነገሩን ሰፋ አድርገህና ትኩረት ሠጥተህ፤ ባንተ ግምት ተገቢ ጥናት አድርገህ የጻፍከው ስለሆነ፤ እኔ መልስ በአዲስ ጦማር በሚከተሉት ቀናት ለዘሃበሻ እልካለሁ። አንተ ከዚህ በፊት የጻፍካቸውን እከታተል ስለነበር፣ በተጨማሪም ለውውጦች ስላደረግን፤ ያሰፈርከው ሃሳብ፤ ከልብህ አገርህን እና ወገንህን ከመውደድ የጻፍከው እንጂ፤ የራስህ የግል ተጠቃሚነት እንደሌለበት ምስክር ነኝ። ይሄን ብዬ፤ ያቀረብከው መፍትሔ ብዙ የጎደለውና ቋሚ ሰላም የማያመጣ መሆኑን፤ ይልቁንም አገራችንን ወዳልሆነ መንገድ የሚመራ መሆኑን በጽሑፌ አሳያለሁ። ለመጠቆም ያህል፡
    “ጦርነቱ . . . የአካባቢ ማንነትንና የብሄር አርበኝነትን ስሜት በታጠቁ በማንነት ስሜት በሰከሩ ሃይሎች መካከል በመሆኑ በእውነት ኢትዮጵያን እሳት ላይ ጥዷታል።” በማለት ገልጠኸዋል። በመጀመሪያ፤ የሁለቱን አካላት መነሻቸና ዓላማ አንድ አድርጎ ማስቀመጥ ትክክል አይደለም። ይህ ከእውነት የራቀ ነው። አንዱ ወራሪ ሌላው ተወራሪ ነው። አንዱ የሌሎች የበላይ ለመሆን የሰነዘረው ጥቃት፤ ሌላው ደግሞ ራሱን ለመከላከልና አገር ለመጠበቅ የሚያደርገው ተከላካይነት ነው። ለሁሉም ጽሑፌን ላዘጋጅ።

  5. ፀሀፊው ችግሩን በአፅንኦት የተረዳ አይመስልም:: ይህ የፖለቲካ ጡዘት ጊዜ አይደለም:: ምን አይነት እርቅ ነው የሚኖረው ከአረመኔ ወራሪና ሰላማዊ ተወራሪ ህዝብ ጋር? እስቲ የወሎ ህዝብ ትግራይን ምን በደለ ለዚህ ሁሉ ጥፋት?
    ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ናት:: ማንም ጤናማ አእምሮ ሰላም የማይፈልግ አይኖርም:: ሆኖም ከአረመኔው ወያኔ ጋር ሰላም ሳይሆን መስዋእትነት ተከፍሎ ነፃ መሆን ነው ተቀዳሚው ጥያቄ:: ማዘናጊያህን እዚያው ጏደኞችህ ጋር ተዝናኑበት

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share