የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ አስተዳደር ከሥልጣን እንዲለቅ ጥሪ

 

የሱዳን ጦርን የሚደግፉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት ተቃዋሚዎች ዛሬ ቅዳሜ በኻርቱም አደባባይ ወጡ። በዋና ከተማዋ በሚገኘው ፕሬዝደንታዊ ጽህፈት ቤት ደጃፍ የተሰበሰቡ ተቃዋሚዎች “የረሐብ መንግሥት” ያሉት የጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ አስተዳደር ከሥልጣን እንዲለቅ ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል። የተቃውሞ ሰልፉ የቀድሞው የሱዳን መሪ ኦማር አል በሺርን ከሥልጣን ለማውረድ ያመጹ ቡድኖችን ጨምሮ ለጦሩ በሚወግኑ የነፃነት እና የለውጥ ኃይሎች ስብስብ አንድ አንጃ የተጠራ ነበር።

“ወታደራዊ መንግሥት ያስፈልገናል። አሁን ያለው መንግሥት ፍትኅ እና እኩልነት ሊያመጣልን አልቻለም” ሲሉ በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፉት የ50 አመቱ አባውድ አሕመድ ተናግረዋል። ተቺዎች ሰልፉ በጦሩ እና በጸጥታ ኃይሎች ግፊት የተደረገ እና የቀድሞው መንግሥት ናፋቂዎች የተካተቱበት ነው ሲሉ ይወነጅላሉ።
ተቃዋሚዎቹ መንግሥት እንዲበተን የሚጠይቁ መፈክሮች ይዘው የታዩ ሲሆን “አንድ ጦር፤ አንድ ሕዝብ” እንዲሁም “ጦሩ ዳቦ ያመጣልናል” ሲሉ መደመጣቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ኢናም መሐመድ የተባሉ የኻርቱም ነዋሪ የቤት እመቤት “ሰላማዊ ተቃውሞ ለማሰማት ነው የወጣነው። ወታደራዊ መንግሥት እንፈልጋለን” በማለት ከአባውድ አሕመድ የተስማማ አስተያየት ሰጥተዋል።
ከተቃውሞው በፊት ማንነታቸው ያልተለየ ታጣቂ ቡድኖች በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዙሪያ ለጸጥታ ጥበቃ የተዘጋጁ ማገጃዎችን ማንሳታቸውን እና ፖሊስ እና የጸጥታ ኃይሎች ወደ ሥራ እንዳይሔዱ መከልከላቸውን የኻርቱም ግዛት አስተዳዳሪ አይማን ኻሊድ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ትናንት አርብ የሱዳኑ ጠቅላይ ምኒስትር አብደላ ሐምዶክ አገራቸው ወደ ሲቪል አስተዳደር የምታደርገው ሽግግር “የከፋ ቀውስ” እንደገጠመው አስጠንቅቀው ነበር።
DW
ተጨማሪ ያንብቡ:  ካላመረርን፣ ካልጨከንን እንጠፋለን - ግርማ ካሳ

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share