አጠያያቂው ሹመት – አበበ ገላው

245292007 10228212382474423 4007513069427497292 n

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ አነጋጋሪ መሆኑ ብዙም አይገርምም። ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ገዢው ፓርቲ ጥቂት ወንበሮች በችሮታ ለተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ማጋራቱ እድልም ችግርም ይዞ መምጣቱ ግልጽ ነው። እድሉ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንበር ተቀብለው የገዢውን ፓርቲ ካቢኔ የተቀላቀሉ ጉምቱ ተቃዋሚዎች ከብልጽግናዎች በላይ ስራ ይበዛባቸዋል። በአንድ በኩል የገዢውን ፓርቲ ፖሊሲዎችና እቅዶች ያለምንም ማቅማማት ማስፈጸም ሲኖርባቸው በሌላ በኩል ደግሞ የሚያገለግሉትን መንግስት ህዝብ አሳምነው በሚቀጥለው ምርጫ ለማስወገድና ለመተካት የተሻለ አማራጭ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል። ለሁለት ተጻራሪ አላማዎች መስራት ግን ትልቅ ፈተና ነው የሚሆንባቸው።

ወደ ተነሳሁበት ዋና ጉዳይ ልመለስና እኔን ከሁሉም ጥያቄ ያጨረብኝ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሹመት ነው። ሹመቱ የተሰጠው ለትግራይ ብልጽግና ቁልፍ ሰው ዶ/ር አብራሃም በላይ ነው። ዶ/ር አብራሃም የብቃት ማነስ ችግር ይኖርባቸዋል ብዬ አላምንም። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ሰው የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በኢንሳም በውትድርናውም እስከ ኮሌኔልነት ማዕረግ ያገለገሉ በመሆኑ መከላከያን መምራት ይሳናቸዋል የሚል እምነት የለኝም።

ችግሩ ያለው እስካሁን ሚናው በግልጽ ያለየውና ከህወሃት ተጽዕኖ ያልተላቀቀው የትግራይ ብልጽግና ጋር ነው። የትግራይ ብልጽግና ከሌሎቹ ብልጽናዎች በላይ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው። ዶ/ር አብርሃምን ጨምሮ አብዛኛው አባላቱ የህወሃት የነበሩ ናቸው። በመሆኑም ስብስቡ ከዋናው ህወሃት ተቆርጦ የቀረ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ ስብስብ ውስጥ ሶስት ዋነኛ ቡድኖች አሉ። አንደኛው እናሳ ቢሆንም ለውጡን ከልብ የተቀበለ ቡድን ነው። ሁለተኛው መሃል ሰፋሪ ሆኖ ግራና ቀኝ የሚወዛወዝ ነው። ሶስተኛውና አብላጫ ቁጥር ያለው ሙሉ በሙሉ የውስጥ አርበኝነት ሚና የሚጫወት የህወሃት ስብስብ መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ በተለይ ከጥቅምት 24 በሁዋላ ይሄ ቡድን ቁጥሩም ተጽዕኖውም እየጨመረ መምጣቱ ይነገራል።

/ር አብርሃም ከመጀመሪያው ስብስብ እንደሚመደቡ አያጠራጥርም። ይሁንና በዶ/ር አብርሃም ላይ ጥያቄ ያጫረብኝ ነገር ከሊላይ ሃይለማሪያም ጋር ያላቸው የቅርብ ቁርኝት ነው። አቶ ሊላይ ቀልቤን ከሳበው ጀምሮ ግለሰቡ “ማን ነው? ምንስ ይፈልጋል? ሚናውስ ምንድን ነው?” የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመመልስ ሞክሬ ነበር። በዛው አጋጣሚ ነበር አቶ ሊላይን ከአሜሪካን አገር ድረስ አጓጉዞ ጥቅማ ጥቅም አመቻችቶ ዶላር የሚከፈለው የብልጽግና ፓርቲ “ቁልፍ” ሰው፣ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን በማድረጉ ሂደት ዶክተሩ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ለመረዳት የቻልኩት፡፡ ሊላይ ኢትዮጵያን ከህወሃት ሊያድን የመጣ መሲህ ነው ብሎ የሚያምን ካለ መልካም እድል። አክቲቪስት ስዩም ተሾመ በሊላይ ጉዳይ በተደጋጋሚ ጩኸት ያሰማው የለምክንያት አይደለም። እኔም ይሄን ጉዳይ የማነሳው አቶ ሊላይ በሃሰት ስለወነጀለኝ አይደለም። ከዚያ በላይ የብሄራዊ ደህንነት ስጋት እንዳለ በመገንዘብ ነው። ሌላው ቢቀር ሰውዬው “ደብል ኤጀንት” መሆኑን መዘንጋት አይገባም?

ምንም እንኳን ከሊላይና መሰሎቹ ጋር ቅርርብ ያለው መከላከያ ሚኒስቴር መሆን አይችልም የሚል እምነት ባይኖረኝም የመረጃ ክፍተት (loophole) ሊፈጠር የመቻሉ እድል ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ጦርነት ያለ ወታደራዊ መረጃ በቀላሉ በድል አይጠናቀቅም። በሌላም በኩል ሚኒስትሩ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደርን ከዶ/ር ሙሉ ነጋ የተረከቡ በመሆኑ ትኩረታቸው ከመከላከያ ይልቅ ክልልሉ የገጠመውን ህወሃት ሰራሽ ቀውስ ለመፍታት መፍትሄ ወደ ማፈላለጉ ላይ ቢሆን የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል እምነት እለኝ።

ነገር ካለፈ በሁዋላ ቢሆንም ወቀሳውና ጣት መጠቁዋቆሙን ታዝበናል። የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ውስጥ ቦታ የተሰጣቸው ግልሰቦች ሰራዊቱን ለአደጋ ሲያጋልጡ እንደ ነበርና ህወሃት እንደገና እንዲያንሰራራ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን፣ ሃብት ንብረት ማበካናቸውን፣ አሻጥር መስራታቸውን፣ አንዳንዶቹም በድፍረት ለአለም አቁፉ ሚድያ የተሳሰሰተ መረጃ በይፋ ሲያቀብሉ እንደ ነበር የአደባባይ ሚስጢር ነው።

ለምሳሌ ያህል የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል አበበ ገብረሂወት፣ የዶክተር አብርሃም ምክትል ማለት ነው፣ መከላከያ የትግራይ ገበሬዎች እርሻ እንዳያርሱ ሆን ብሎ የመከልከል ዘምቻ (campaign) እያረገ ነው የሚል የሃስት ፕሮፓጋንዳ አሳራጭቶ CNN ጨምሮ በርካታ ሚድያዎች ሲያስተጋቡትና የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይን ህዝብ ሆን ብሎ እያስረበ ነው የሚል ዘገባ እንዲሰራ ቢያደርግም አሁን ድረስ የብልጽና ሹመኛ ነው።

በአጭሩ የትግራይ ብልጽግና ያልጠራና ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት ስለሚታወቅ እስኪጠራ ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነው። ብልጽግና ከኢህአዴግ ግሳንግስ በቀላሉ ይላቀቃል የሚል እምነት ባይኖረኝም ቢያንስ እራሱን በየጊዜው እየፈተሸ ማረም ያስፈልጋዋል። በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያናውጣት ችግር ምንጩ የኢህአዴግ መራር የለውጥና የስልጣን ትግል መሆኑንና ትግሉም ገና ባለማለቁ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ገደል ይዟት እንዳይገባ ጥንቃቄ ቢደረግ ለአገርም ለህዝብም መልካም ነው ባይ ነኝ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.