ለቸኮለ! ረቡዕ መስከረም 26/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ 22 ሚንስትሮችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስሹመዋል። ከተሹዋሚዎች መካከል፣ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚንስትር፣ አብርሃም በላይ መከላከያ ሚንስትር፣ አሕመድ ሽዴ ፋይናንስ ሚንስቴር እና ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ፍትህ ሚንስትር ይገኙበታል። ዐቢይ ተሿሚዎቹ ሌብነትንና ልመናን ማስወገድ እንዳለባቸውና የሀገር እንጅ የብሄራቸው ወኪል እንዳይሆኑ አሳስበዋል። የሚንስትሮቹ ሹመት በ2 ተቃውሞ እና 12 ድምጸ ተዓቅቦ ጸድቋል።

2፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ ስብሰባው የፈደራል ሥራ አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንደገና ለማሻሻል የወጣውን ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል። የምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ላይ በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ የረቂቅ አዋጁን ዝግጅት የመሩት የፕላን እና ልማት ሚንስትሯ ፍጹም አሠፋ እና ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ሰጥተዋል። አዋጁ የሥራና ክህሎት ሚንስቴርን እና ፍትህ ሚንስቴርን አዲስ ሚንስቴር አድርጎ ያቋቋመ ሲሆን፣ ሌሎች ሚንስቴሮች እንዲጣመሩ ወይም እንዲነጣጠሉ ተደርገዋል።

3፤ ዛሬ የተሻሻለው የፌደራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባርን የሚወስነው አዋጅ ከሚንስቴር በታች ያሉ 20 ተቋማትን ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳደረገ የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ከእነዚሁ ተቋማት መካከል፣ ብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ብሄራዊ ባንክ፣ ጸረሙስና ኮሚሽን እና ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይገኙበታል። ተቋማቱ ቀጥተኛ ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ መሆኑ ላይ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት ስጋታቸውን ገልጸዋል። ዐቢይም ተቋማቱ መብዛታቸውን አምነው፣ አዲሱ ተጠሪነት ግን ካንድ በላይ የሥራ ዘርፍ ያላቸውን ተቋማት በተማከለ መንገድ ለማስተባበር እንደሚያስችል አብራርተዋል። የአስተዳደር ወሰንና ማንነት ኮሚሽን እና የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ግን ለሰላም ሚንስቴር ተጠሪ ቢሆኑ እንደሚደግፉ ዐቢይ ተናግረዋል።

4፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ዛሬ ሦስት የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው አስሹመዋል። የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ትምህርት ሚንስትር፣ የአብን ሊቀመንበር በለጠ ሞላ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስትር እንዲሁም ቀጀላ መርዳሳ የባሕልና ስፖርት ሚንስትር ሆነው ተሹመዋል። የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበርን በአዲስ አበባ ካቢኔ ለማካተት ተፈልጎ፣ ፓርቲው እንዳልተቀበለው ዐቢይ ገልጠዋል። የፓርቲው ሊቀመንበር ግን ተሿሚውን የሚመርጠው ራሱ ፓርቲው መሆን ነበረበበት ሲሉ ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል።

5፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ በትግራይ ጉዳይ ላይ ለ10ኛ ጊዜ ለመምከር ስብሰባ እንደጠራ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጉዳዩ ላይ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሏል። ውይይቱ የሚካሄደው ሰላም እና ደኅንነት በአፍሪካበሚል አጀንዳ ስር እንደሆነ ተገልጧል።

6፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኅዳር 2013 .ም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ጦር መሳሪያ እንዳመላለሰ በምርመራ ዘገባዬ ደርሼበታለሁ ሲል ሲኤንኤን ዘግቧል። ሲኤንኤን የአየር መንገዱ ጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በአዲስ አበባ፣ አሥመራ እና ምጽዋ ከተሞች መካከል ቢያንስ 6 ጊዜ ጦር መሳሪያዎችን ስለማጓጓዛቸው ከሰነድና ፎቶግራፍ ማስረጃዎች እና ከዓይን ምስክሮች አረጋግጫለሁ ብሏል። የመንገደኞች አውሮፕላኖች ለዚህ ተግባር ስለመዋላቸው ግን ማስርጃ እንዳላገኘ ዘገባው ጠቅሷል። አየር መንገዱ በበኩሉ፣ እስከማውቀው ድረስ አውሮፕላኖቼ ጦር መሳሪያ ለማጓጓዝ አልዋሉም በማለት አስተባብሏል።

7፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር አዲስ የአፍሪካ ፖሊሲ ለመቅረጽ ጁድ ዲቬርሞንት የተባሉ የቀድሞ የስለላ ድርጅቱ ሃላፊ ለብሄራዊ ጸጥታ ምክር ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አድርጎ እንደቀጠረ ፎሬን ፖሊሲ መጽሄት አስነብቧል። ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት፣ ጸረ ሽብር እና ቻይና እና ሩሲያ በአፍሪካ ያላቸውን ተጽዕኖ በመግታት ላይ ትኩረት ያደረገው የባይደን አዲሱ የአፍሪካ ፖሊሲ፣ ከ4 እስከ 6 ወራት ውስጥ ይፋ እንደሚደረግ ዘገባው ጠቅሷል። የባይደን አስተዳደር ለመጀመሪያ ጊዜ ሞሊ ፊ የተባሉ ዲፕሎማትን በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ አድርጎ የሾመው ከቀናት በፊት ነው።

8፤ በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ 92 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞችን በታንዛኒያ ወደ ሀገራቸው እንደመለሰ ዛሬ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ፍልሰተኞች በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊሻገሩ የነበሩ ናቸው ተብሏል። ኢምባሲው ፍልሰተኞቹን መመለስ የተቻለው ከዓለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በመተባበር ነው። ዛሬ በሳዑዲ ዐረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ 335 ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ያስታወቀው ደሞ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ነው። 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.