የአማራ ሕዝብ መልዕክት ለአዲሱ ፕሬዝዳንት አሳዬ ደርቤ

yilekal Kefyalewክቡር ፕሬዝዳንት፡ብአዴን የሚባል ድርጅት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ደስ ብሎኝ አላውቅምና ‹‹እንኳን አብሮ ደስ አለን›› እንዳይሉኝ አስጠንቅቄ ‹‹እንኳን ደስ አለዎት›› እልዎታለሁ፡፡

በማስከተል ሥነ ልቦናዊ ሥሪቴ ከመንግሥትና ከሥርዓት ውጭ ሆኖ ለመኖር የማይስችለኝ ሕዝብ ብሆንም ላለፉት ሠላሳ ዓመታት ግን ግብር የሚቀበለኝ እንጂ የሚጠብቀኝ መንግሥት አግኝቼ እንደማላውቅ ላስታውስዎ እፈልጋለሁ፡፡ ከሥልጣን ሽግግሩ በኋላም ተለወጥኩ ያለኝ ድርጅት ተከብሮ ያስከብረኛል ብዬ ሳስብ ሥሙን እና ጌታውን ቀይሮ በብር ፈንታ ሕይወት ስገብር ቆይቻለሁ፡፡

አሁን ግን ክቡር ፕሬዝዳንት የቀረኝ አቅም የጥንቱን አይነት አመራር ለመሸከም የሚያስችለኝ አይደለምና ሸክሜ እና ሕመሜ በመሆን ፈንታ ሐኪሜ ይሆኑ ዘንድ እመኛለሁ፡፡ ሕዝብ እንደመሆኔ መጠንም የመሪዎቼ ጌታ መሆን ባልችልም ተላላኪ ድርጅትዎን ከባርነቱ አላቅቀው ጌታዬ ያደርጉልኝ ዘንድ እለምነዎታለሁ፡፡

ክቡር ፕሬዝዳንት፡ባለፉት አመታት በእኔ ውድመትና ሕልፈት ላይ የኢትዮጵያ አንድነት ሲረጋገጥ የነበረ ቢሆንም፣ ከእንግዲህ ግን ጥቃት ሲፈጸምባት ከሌሎች ወገኖቼ ጋር የምሞትላት እንጂ በገዛ ወገኖቼ እኔን እያስገደለች የምትፈረጥም አገር መሸከም በቅቶኛል፡፡

ስለሆነም እርስዎም እንደ ቀድሞ ጓዶችዎ ክልል ላይ ተቀምጠው ‹‹ፌደራል ፌደራል›› የሚጫወቱ ከሆነ መግባባት ስለማንችል ‹‹አማራዊ ማንነት ያለዎት የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት›› መሆንዎን እንዲሸመድዱት እፈልጋለሁ፡፡ ባሕር ዳር ላይ ተቀምጦ የአገር መሪ መሆን አይቻልምና በእኔ ሕልፈትና ውድመት ላይ ሳይሆን በእኔ ሕይወት፣ በእኔ እኩልነት፣ በእኔ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ለምትቀጥል አገር የሚተጉ ፕሬዝዳንት ይሆኑ ዘንድ እሻለሁ፡፡

ሌላው ደግሞ ክቡር ፕሬዝዳንት… ወረራ የፈጸመብኝን ሽፍታ እንደ እሱ ሸፍቼና በጎበዝ አለቃ ተደራጅቼ ብመክት ኖሮ እስካሁን ድረስ ነጻነቴን ከማስከበርም ባለፈ ተከዜን መሻገሬ እርግጥ ቢሆንም ‹‹መንግሥት አለኝ›› በሚል አስተሳሰብ ውስጥ ተሸብቤ መቀመጤ እኔን ቀርቶ ከብቶቼን ማንነት ሰጥቶ በጥይት ከሚደበድብ ወራሪ እጅ ወድቄ ለወራት እንዲቆይ አድርጎኛል፡፡ ስለሆነም ይሄን ሐሳቤን ተረድተው የመጀመሪያ እቅድዎ ‹አሸባሪን መደምሰስ›› እና ‹‹የተፈናቀሉን መመለስ›› የሚል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሄን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ የእራሴን አደረጃጀት ሠርቼ ዘላለማዊ እረፍት ይነሳኝ ዘንድ ጎትተው ከምድሬ ላይ የጣሉትን ጠላት አፈር ድሜ የማበላበትን ነጻነት መስጠት ግድ ይልዎታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዲሱን የብር ለውጥ አስመልክቶ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ከኢቲቪ ጋር ያደረጉት ቆይታ

ክቡር ፕሬዝዳንት፡ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብቴን ነጥቀው የመሞት መብቴን ያስከበሩ ጠላቶቼ አማራ በመሆን ወንጀል በርካታ ግፍ ሲፈጽሙብኝ ቢኖሩም የክልሌ መንግሥት ግን እራሴን በምታደግበት ማንነቴ ፈንታ ከፍ ሲል የምገደልበትን ዜግነት እያቀነቀነ፣ ዝቅ ሲል ጠላቶቼ በማያውቁትና እርሱ ሥልጣን ላይ በሚቆይበት ዞናዊ ማንነት እያሸነሸነ ሞትን እና መፈናቀልን ሲያለማምደኝ ነበር፡፡ የጎጡን ወንበር ይዞ ክልል ላይ የሚቀመጥ አመራር መርጦ በማምጣት ለእኔ የሚታገለውን ጀግና ጠልፎ እየጣለ፣ ከሸንጎ ኮሚቴ እና ከውጫዊ ጠላቴ ጋር የሚሠራውን ሲቀፈቅፍ ነበር፡፡

ስለሆነም በአዲስ መልክ የተደራጀው የእርስዎ አመራር የትውልድ ሥፍራውን መታወቂያ ወርውሮ የክልሉን ያወጣ ዘንድ በማስገደድ በመጠላለፍ ፈንታ የሚደጋገፍ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡ መጠላለፉ አይቀሬ ከሆነ ደግሞ ‹‹የዞን ተቆርቋሪ ፥ ክልሉን ቀባሪ ማን ነው?›› በሚል መስፈርት እንዲጠላለፍ አደራ እልዎታለሁ፡፡

አማራ!

1 Comment

  1. The same banana hulum temama !!! Noting is new but just the same political caner in a different body and name !! Very sad to the Amhara people in particular and the people of Ethiopia in general!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.