ለቸኮለ! ቅዳሜ መስከረም 15/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

242920449 6474461325927387 2611980491318147400 n1፤ የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው መስራች ጉባዔ ሽመልስ አብዲሳን በሙሉ ድምጽ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መምረጡን አስታውቋል። ሽመልስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ ክልሉን የመሩ ሲሆን፣ በዛሬው ምርጫ ሌላ ተቀናቃኝ ዕጩ አልቀረበባቸውም። ሰዓዳ አብዱራህማን ደሞ አዲሷ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው ተመርጠዋል።
2፤ የኦነግ ሊቀመንበር አራርሳ ቢቂላ የኦሮሚያ ክልል ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ሆነው እንደተሾሙ የክልሉ ዜና አውታሮች ካሰራጩት የካቢኔ ሹሞች ዝርዝር ተመልክተናል። አራርሳ የክልሉን ካቢኔ በመቀላቀል ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የመጀመሪያው ናቸው። በኦነግ ውስጥ የአመራር ክፍፍል መፈጠሩን ተከትሎ፣ አራርሳ በዳውድ ኢብሳ ምትክ የግንባሩ ሊቀመንበር መሆናቸውን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
3፤ “ኤስ ኤንድ ፒ” የተባለው ዓለማቀፍ የሀገራት ብድር ከፋይነት ደረጃ አውጭ ተቋም የኢትዮጵያን የውጭ ብድር የመክፈል አቅም ከደረጃ B- ወደ ደረጃ CCC+ ዝቅ እንዳደረገው ሮይተርስ ዘግቧል። ድርጅቱ የሀገሪቱን የውጭ ብድር የመክፈል ደረጃ ዝቅ ያደረገው፣ ሀገሪቱ የገጠማትን ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እና የውጭ ዕዳ መክፈያ ጊዜ ሽግሽግ መዘግየቱን እንደ ምክንያት በመጥቀስ ነው። በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የሀገሪቱን በጀት ጉድለት የሚሸፍነው በዋናነት የውስጥ ምርት እንደሚሆን ድርጅቱ ገልጧል።
4፤ ኬንያ ኢትዮጵያዊው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም በድጋሚ ድርጅቱን እንዲመሩ ድጋፍ ሰጥታለች። ዓርዓያነት ያለው የድርጅቱ አፍሪካዊ አመራር ቀጣይነት እንዲኖረው ኬንያ ፍላጎቷ መሆኑን የኬንያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቋሚ ተጠሪ ማቻሪያ ካማው በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። ለድርጅቱ ዋና ዳይሬክተርነት ዕጩ የመጠቆሚያው ጊዜ ትናንት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሌላ ተወዳዳሪ ከቀረበ የድርጅቱ አባል ሀገራት በግንቦት በሚስጢራዊ ድምጽ አሰጣጥ ዋና ዳይሬክተሩን ይመርጣሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት በዶ/ር ቴዎድሮስ ዕጩነት ላይ አቋም ይዞ እንደሆን በይፋ አልገለጸም።
5፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከኒውዮርኩ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ በተጓዳኝ ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ ጋር እንደተወያዩ ድርጅታቸው ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ውይይቱ በትግራይ ክልል ግጭት፣ በሰብዓዊ ዕርዳታ እና በሕዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ያተኮረ እንደሆነ መረጃው ጠቅሷል። ጉተሬዝ የሰሜን ኢትዮጵያውን ግጭት በሰላም ለመፍታት መወሰድ ያለባቸውን አስፈላጊ ርምጃዎች በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
6፤ በኦፌኮ አመራሮች መካከል ክፍፍል ተፈጥሯል የተባለው መረጃ ሐሰት ነው ሲሉ የፓርቲው ዋና ጸሃፊ በቀለ ነጋ ለሸገር ተናግረዋል። ባሁኑ ሰዓት በፓርቲው አመራሮች መካከል በዓላማ ደረጃ ምንም ልዩነት የለም- ብለዋል ዋና ጸሃፊው። በፓርቲው ውስጥ ልዩነት አለ የሚሉ አመራሮች ካሉ በይፋ አደባባይ ወጥተው መናገር እንዳለባቸው በቀለ አክለው ገልጸዋል። ኦፌኮ ከሰኔው ጠቅላላ ምርጫ ራሱን ማግለሉ ይታወሳል። [ዋዜማ ራዲዮ]
ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: የብሔራዊ ቡድናችን አማካይ አዲስ ሕንጻ ለሱዳኑ ክለብ ለመጫወት በ$100 ሺህ ዶላር ፈረመ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share