ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ሊሰርዙት ይገባል

242214460 3028373360738456 5631204355876820411 n የአሜረካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ሊሰርዙት ይገባል ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ጠየቀ።

የኢትዮጵያ ሁኔታን በሚገባ ያልተገነዘበ ነው ያለውን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የማዕቀብ ትዕዛዝ አጥብቆ እንደሚቃወም ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንቱ ማዕቀብ እንዲጣል ያስተላለፉትን ትዕዛዝ የሚያወግዝ መግለጫ አውጥቷል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሀገሪቱ የሰላም እንቅፋት ሆኖ ሳለ፤ መንግስት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት እና የህግ የበላይነት ለማስጠበቅ በወሰደው እርምጃ ምክንያት ማዕቀብ መጣል ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት አባል እና አለም አቀፍ ሕግን በማክበር የውስጥ ጉዳይን በራስ የመፍታት ሙሉ መብት ያላት ሉዓላዊ ሀገር ነች ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።

የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ባስተላለፈው ውሳኔ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ ጥሷል ያለው ምክር ቤቱ ለዚህም ማሳያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ብሎ ከፈረጀው ቡድን ጋር መንግስት እንዲወያይ መጠየቁ ነው ብሏል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የሀገር መከላከያ ሰራዊትን ድንገት በማጥቃት ከትግራይ ክልል አልፎ በጎረቤት ክልሎች ላይ ጥቃት በመክፈት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመፈታተን ላይ ይገኛል ነው ያለው ምክር ቤቱ።

የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ለማጠናከር የተኩስ አቁም ቢያውጅም አሸባሪው ቡድን የተኩስ አቁም ውሳኔን እራሱን በማደራጀት ተጠቅሞበታል ያለው ምክር ቤቱ ፤በዚህም በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ የሲቪል ዜጎች ግድያ ፈጽሟል እንዲሁም የመሠረተ ልማቶችን አውድሟል።

አሸባሪው ቡድን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማይካድራ ጭና፤ጋሊኮማ፤አጋምሳ ከመጨፍጨፉ በተጨማሪ በወረራቸው ክልሎች ውስጥ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲከሰት አድርጓል።

እንዲሁም ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናትን ፣ ሆስፒታሎችን እና ትምህርት ቤቶችን አውድሟል ሲል የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአሸባሪው ህወሃት ቡድንን አጥፊ አካሄድ ከመከላከል አልፎ ቡድኑ ለፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ለሰጠው ምላሽ ከባይደን አስተዳደር አድናቆት ይገባው ነበር ሲል ገልጿል።

የባይደን አስተዳደር የአሸባሪው ቡድንን ማውገዝ ሲገባው የማዕቀብ ትእዛዝን መስጠቱ ስህተት ነው ያለው ምክር ቤቱ የተላለፈውን የማዕቀብ ውሳኔ ሊሰርዝ ይገባል ሲል ጠይቋል።

በመሆኑም የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ከአሸባሪ ቡድን ጋር ድርድር እንደማይኖር ተገንዝቦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግስት ጋር ያለውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ቢያጠናክር የተሻለ ይሆናል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው የፕሬዝዳንቱ የማዕቀብ ውሳኔ የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ ይጎዳዋል ያለ ሲሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምም የሚያበረክተው አስተዋጽዎ አይኖርም ብሏል።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.