❝እነርሱን ቀርቶ እነርሱን መሰል ቡድን በኢትዮጵያ ምድር ዳግም እንዳይበቅል መሥራት ይገባል❞ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

242115530 1634560976718890 8446469509555246963 nከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው እና ለወገናቸው ቀናዒ ልቦናን የታደሉ ስለመሆናቸው የሀገር ውጭ ጸሐፍት ሳይቀር በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ስለሀገራቸው ክብር፣ ስለወገናቸው ፍቅር ሲሉ የማይወጡት ተራራ፣ የማይወርዱት ሸለቆ፣ የማያሳልፉት መከራ እና የማይቀበሉት መራር ተጋድሎ አልነበረም፡፡ ከስንዴ መካከል እንክርዳድ፣ ከአበባ መካከል እሾህ ተፈጥሯዊ የመሆኑን ያክል እነዚህኞቹ እንደዚህ የበቀሉ ናቸው፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን አባላት ከኢትዮጵያውያን ደጋግ ልቦች መካከል የበቀሉ እርጉማን አረሞች ናቸው፡፡

በየዘመኑ እልፍ አዕላፍት ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ትጉሃን የመሆናቸውን ያክል ጥቂት ሰነፎችም አይጠፉም፡፡ በየዘመናቱ ስለሀገራቸው ክብር በሠሩት ገድል ስማቸው ከፍ ብሎ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚወሳላቸው እንዳሉ ሁሉ ደማቁ የኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ በጥቁር ያቀለማቸው አበያዎች እና ባንዳዎችም ነበሩ፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ ቡድን አባላት በእርግጥም የዚህ ዘመን የኢትዮጵያ አበያዎች ናቸው፡፡

በሴራ ተዘርተው በክህደት የበቀሉ፤ በቂም ተጸንሰው በጥላቻ የተወለዱ፤ በልዩነት በቅለው በክፍፍል ያደጉ፤ ብቻቸውን በልተው እልፍ ሆኖ መሞት የሚሻቸው፤ ለራሳቸው ያልበቁ ለሌሎችም የማይተርፉ ናቸው፡፡ መዓዛቸው ሀሴት አልባ፣ የተናገሩት የማያምር፣ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከእምነት ይልቅ ክህደት፣ ከአብሮነት ይልቅ መነጣጠል እና ከሚያሻግር ድልድይ ይልቅ የልዩነት ግንብ ማቆም የሚቀናቸው ሆነው ተፈጥረዋል፡፡

በንስሃ ዘመናቸው እንኳን ከአርምሞ ይልቅ ዳንኪራ እና ሁካታ ቀንቷቸው ብቻቸውን መውረድ ሲገባቸው ሀገር እና ትውልድን አብረው ሊያወርዱ ሲዳዱ አይተናል፡፡

ከፍ ያለችውን ሀገር ለማውረድ፣ ውጋግራ ለመነቅነቅ እና ማገር ለማላቀቅ በእርጅና ዘመናቸው ሲበረቱ ላየ እውነትም እነዚህን የገንጣይ አስገንጣይ ቡድኖች ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሎ ለመጥራት ምን ያክል እንደሚከብድ ይረዳል፡፡ሰዎቹ ከመመረቅ ይልቅ ለመረገም ተፈጥረዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጄኔራል ሰዓረና ጋዜጠኛ እስክንድር - ከኢየሩሳሌም አረአያ

በሠሩት ግፍ የኢትዮጵያውያን አንድነት እየታየ ነው የሚሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ብረት የሚቀጠቀጠው እንደጋለ ነውና በዚህ ወቅት የቀጣዩን የኢትዮጵያ መንገድ በውል ማበጀት ይገባል ብለዋል፡፡

አሁን የታየውን ሀገራዊ አንድነት በዚህ ፍጥነት ማምጣት ይከብዳል የሚሉት ዲያቆን ዳንኤል፤ አዲሱ ትውልድ በየወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቶቹ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ ሲያነባ ከማየት በላይ ምን ሌላ ተዓምር ይጠበቃል ይላሉ፡፡

የሽብርተኛው ትህነግ አባላት ወደ ስልጣን እርካብ ሲመጡ ኢትዮጵያን ያሳጧትን አንድነት ሲወርዱ አስረክበዋታል፤ ትውልዱ ይህ እንደሚሆን ቢያውቅ ኖሮ ከዚህ ቀድሞ ባስወጣቸውም ነበር ነው ያሉት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል፡፡ ይህንን አንድነት ለመጠበቅ ሁለት ዐብይት ሥራዎች ይጠብቁናል ብለዋል፡፡

የመጀመሪያው ❝እነርሱን ቀርቶ እነርሱን መሰል ቡድን በኢትዮጵያ ምድር ዳግም እንዳይበቅል መሥራት ይገባል❞ ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ነጮችን ከምንስብበት የኢንቨስትመንት እንክብካቤና አማራጭ በተለየ የአንዱ ክልል ባለሃብት ወደ ሌሎች ክልሎች ሄዶ የሚያለማበት መንገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ባይ ናቸው፡፡

እንደ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ማብራሪያ ምናልባትም ከውጭ የሚመጡ ባለሃብቶች ለችግራችን ደራሽ እና ለክፍተታችን ቀናሽ ገንዘብ ይዘው ይመጡ ይሆናል፤ የአንድ ክልል ባለሃብት ሌላ ክልል ሄዶ ሲያለማ ግን ከገንዘብ ባሻገር ወንድማማችነትን ይዞ ይመለሳል ነው ያሉት፡፡ በመሆኑም ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ የብዙኃን መገናኛ ተቋማት እና ወጣቶች ለዘመናት ጠፍቶ የቆየውን እና አሁን ፍንጩ የተገኘውን ኢትዮጵያዊ አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ በማቆም መትጋት ግድ ይላቸዋል ብለዋል፡፡ ከሀገራዊ አንድነት በኋላ ብሔራዊ ጥቅምን እና ሀገራዊ እድገትን ለማምጣት የሚኬደው ጉዞ ያን ያክል አድካሚ አይሆንም ነው ያሉት፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ! - ማላጅ

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

መስከረም 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ)

1 Comment

  1. “ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን” እንዴት ነው የመንግሥት አማካሪ ለመሆን የበቊት? ስላልገባኝ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share