የአማፂያንን የጦር አውርድ ለመግታት ዜጎች በጋራ መቆም ይኖርብናል! (ኢዜማ)

መንግሥት ሁሉን አቀፍ «ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማስከበሪያ ዘማቻ ግብረ ኃይል»እንዲያቋቃም ጥሪ እናቀርባለን!

ከ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

ኢትዮጵያ ሀገራችን በሕዝቦቿ ተጋድሎ ሉዓላዊነቷን ከውጭ ወረራ በማስከበር ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ምሣሌ የሚሆን ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሀገር ድንበር ከውጭ ወረራ ተከላክሎ ለማስከበር ባለን ቀናይነት ልክ የውስጥ ችግሮቻችንን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት የምናደርገው ጥረት ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡ በዚህ የተነሣ በየጊዜው በሚነሱ ውስጣዊ አለመግባባቶች መነሻነት የዜጎች ሕይወት ማጣትና ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ መግባት የሰርክ ተግባር ሆኖ ቀጥሏል፡፡

አሁን ባለንበት ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሕወሃት ጦረኝት በተለይ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ በፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት መነሻ የተፈጠረውን የሕግ ማስከበር የመንግሥት እርምጃን ተከትሎ የተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ ሳይበቃ፤ ሕወሃት ወደ ሌሎች የሀገራችን ክፍል ለማስፋፋት በግልፅ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህም በቅርቡ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያደረገው ይፋዊ ስምምነት የሚታወቅ ሲሆን ከሌሎች ተመሳሳይ ዕኩይ ተልዕኮ ካላቸው በሀገር ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ጋር ቀውሱን ለማስፋት እንደሚሠሩ በይፋ እየገለፁ ይገኛሉ፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በቁጥጥሩ ስር ከነበሩ ቦታዎች ለቆ መውጠቱን ተከትሎ ኢዜማ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ ባደረገው የቢሆንስ (Scenario) ትንተና፥ ሕወሃት ሀገራችንን ለማተራመስ ከሌሎች አክራሪ ብሔርተኞች ጋር ጥምረት መመስረት የሚችልበት ሁኔታ የሚፈጠር ከሆነ ለሀገራችን አንድነት እና ሰላም በራሱ ከሚፈጥረው አደጋ በተጨማሪ ለኢትዮጵያ የውጪ ጠላቶች መሣሪያ በመሆን በሀገራችን እና በምንገኝበት ቀጠና ከፍተኛ አደጋ ሊደቅን እንደሚችል ገልፀን የኢትዮጵያ አንድነት እና ሰላም እንዲረጋገጥ የምንፈልግ ኃይሎች በሙሉ አቅማችን ተረባርበን አደጋውን እንድንቀለብስ ጥሪ አስተላልፈን ነበር።

ኢዜማ ችግሮች በኃይል አማራጭ ብቻ በዘለቄታው ይፈታሉ የሚል እምነት የለውም፡፡ አሁን ያለንበት ችግር በተለይ ደግሞ በዜጎች ላይ እየተፈጠረ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እንዲቆም ሠላማዊ መፍትሔዎች እንዲገኙ ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ነገር ግን ሕወሃትና አጋሮቹ የሆኑ የውስጥም ሆኖ የውጭ የጥፋት ኃይሎች እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሠላም ያለንን ፅኑ አቋም ተረድተው የጦር እንቅስቃሲያቸውን እንዲያቆሙ ማስገደድ ያለብን ጊዜ አሁን ነው፡፡ ወደ ሠላማዊ መስመር እስኪመጡ ድረስ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማሰጠበቅ በዋነኛነት የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም ሁላችንም ግዴታ ያለብን መሆኑን እንረዳለን፡፡

ሕወሃት አሁን ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ያለው እና አደጋ የደቀነው በአማራ እና በአፋር ክልሎች ቢሆንም ይህን ጉዳት እና አደጋ አሁን በአስቸኳይ ማቆም ካልቻልን ሳይውል ሳያድር በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች መከሰቱ የማይቀር ነው። ይህ ሁላችንም ላይ የተጋረጠ አደጋን በብቃት ለመመከት እና ለማስቀረት ሁላችንንም በአንድነት አሰባስቦ ማሰለፍ የሚችለው የፌደራል መንግሥት በመሆኑ መንግሥት ይህን ግዴታውን ከምንግዜውም በላይ በከፍተኛ ውጤታማነት መወጣት እንዲችል የወታደራዊ፣ የዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ የፕሮፖጋንዳ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ እና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ማገዝ እንዲሁም የሀብት ማሰባሰብ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ መሠራት ያለባቸው ሥራዎችን ስትራቴጂ እየነደፈ እንዲፈፀሙ ውሳኔ የሚያስተላልፍ «ብሔራዊ የሀገር ሉዓላዊነት እና የሕዝብ ደህንነት ማሰከበር ዘመቻ ግብረ ኃይል» ከመንግሥት መዋቅር ውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር በማሳተፍ በአስቸኳይ እንዲያቋቁም እና ወደ ሥራ እንዲገባ እንጠይቃለን። ይህ የዘመቻ ግብረ ኃይል በዋነኛነት በፌደራል መንግሥት የሚመራ ሆኖ በሁሉም የመንግሥት እርከኖች በተዋረድ የሚደራጅ እና ከላይ የተጠቀሱ ዘመቻው ጋር በተያያዘ ያሉ ሥራዎችን ብቻ የሚያስተባብር ሆኖ እንዲዋቀር እንጠይቃለን። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና የተለያዩ አደረጃጀቶች ሕወሃትን ከዚህ እኩይ ተግባር ለመግታት እና ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝብ ደህንነት ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ እናደርጋለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  መሐሪ ደገፋው በወቅታዊ የሃገራችን ጉዳይ ላይ "አመመኝ" የተሰኘ ነጠላ ዜማ ለቀቀ | ይዘነዋል

የመከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የፀጥታና ደህንነት አባላት በዚህ ፈታኝ ወቅት ያለባችሁን ተደራራቢ ኃላፊነት እና የሕይወት መስዕዋትነት የሚያስከፍል ስምሪት ውስጥ እንዳላችሁ እንረዳለን፡፡ ዘወትር ለሀገራችን ኢትዮጵያ እና ለሕዝቦቿ ደህንነት መስዋዕት ለመሆን ላሳያችሁት ቁርጠኝነት ኢዜማ ከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት አለው፡፡ ሀገራችን ከተደቀነባት አደጋ በአጭር ጊዜ እንድትወጣ ጉልህ ሚና እንደምትጫወቱ እናምናለን፡፡ በዚህ እጅግ ፈታኝ በሆነ ግዳጅ ላይ በምትገኙበት ሁሉ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ጀግንነትን አዋዳችሁ ኢትዮጵያዊያንን እና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ እንደምታደርጉ እንዲሁም ሀገራችንን ከተጋረጠባት አደጋ በአጭር ጊዜ እንደምትታደጓት አንጠራጠርም፡፡ ኢዜማም ተልዕኳችሁ እንዲሳካ የሚችለውን ሁሉ ተሳትፎ የሚያደርግ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደገለፅነው፥ የሀገር ሰላምን እና አንድነትን የማስከበር ኃላፊነቱ በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ በመሆኑ አሁን የተደቀነብንን አደጋ ለመቀልበስ የሚወሰደው እርምጃ የዛሬውንም ሆነ የወደፊቱን ወቀሳም ሆነ የድል ሽሚያ ማስቀረት በሚያስችል መልኩ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥት እና በኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ መወሰድ እንደሚገባው አበክረን እናሳስባለን።

ውድ ኢትዮጵያዊያን፣ በግንባር ለተሰለፉት የሠራዊት አባላት የምናደርገው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ በያለንበት አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅ፣ ከሰርጎ ገቦች እና አንድነታችንን ለማላላት የሚደረግን እንቅስቃሴ በትኩረት በመከታተል ከአድሎና ወገንተኝነት በፀዳ መልኩ በአካባቢ ለሚደራጅ የዘመቻ ግብረ ኃይል ጽሕፈት ቤት በማሳወቅ ሀገር ለማዳን በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የድርሻችንን እንድንወጣ እና ሀገርን ከሚጎዱ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ራሳችንን እንድንጠብቅ እንጠይቃለን፡፡

በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የኢዜማ አመራር እና አባላት፤ ለሀገር አንድነት እና ሰላም እስካሁን ያደረጋችሁትን የማይተካ አስተዋፅዖ በመቀጠል በምትገኙበት ቦታ ሁሉ እንደ ዜጋ የሚጠበቅባችሁን ከማድረግ በተጨማሪ፥ በሥነ ምግባር ምሣሌ በመሆን አርአያነት ያላቸውን ተግባሮች እንድታከናውኑ፣ በምንም ዓይነት ሀገርን ከሚጎዱ አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ራሳችሁን ከመጠበቅ በዘለለ ከሕዝብ ጎን በመሆን አካባቢያችሁን በንቃት እንድትጠብቁ እና በምታደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሀገር እና ሕዝብን እንድታስቀድሙ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦሮሞ ሕዝብ ትግል ስም ቁማር የሚጫወቱ የወያኔ ተላላኪዎች በጋዜጠኛ ኢዮብ ባይሳ ተጋለጡ | ጊዜ ወስደው ሊያዩት የሚገባ

የሚዲያ አካላትና ሠራተኞች እንዲሁም የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች፤ ሀገራችን በምትገኝበት በዚህ የፈተና ወቅት ጥሬ ዜናዎችን ከማቅረብ በዘለለ፥ ዜጎችን ማረጋጋት፣ ዜጎች የሀገር ሉዓላዊነትን እና የሕዝብ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ በንቃት እንዲሳተፉ እና ለሚደረግላቸው ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጡ መቀስቀስ ይጠበቅባችኋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ እውነት ይዛ፤ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ብዛት የውጭ ኃይሎች ጭምር በተቃራኒ እንዲቆሙ የሆኑበትን ሁኔታ እውነቱን በማጋለጥና ትክክለኛ ዘገባዎችን ወደ ሕዝብ በማድረስ በሕዝባችን ውስጥ የተፈጠረውን ብዠታ እንድታጠሩ እና እንድትቀለብሱ፣ በሥራችሁም የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ እንድታደርጉ አደራ ማለት እንፈልጋለን፡፡

የንግድ ማኅበረሰብ አባላት፤ በዚህ ፈታኝ ወቅት በተለያየ መንገድ ሠራዊቱን እና የሠራዊቱን ቤተሰቦች መደገፍ እንደምትቀጥሉ እንተማመናለን፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ሊፈጠሩ በሚችሉ ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረቶች እና እሱን ተከትሎ በሚመጣው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ዜጎች እንዳይማረሩ፣ አሁን ሀገራችን የገባችበትን ክፉ ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመውሰድ በሸማች ዜጎች ኪሳራ እና ችግር ለመክበር ከሚደረግ እንቅስቃሴ እንድትቆጠቡ እና የዜጎች አለኝታ መሆናችሁን በክፉ ቀን ከሀገራችሁ እና ከሕዝባችሁ ጎን በመቆም እንድታረጋግጡ ጥሪ አናቀርባለን፡፡

ወጣቶች፤ የሀገራችን ባለቤት እና ጠባቂ መሆናችሁን ተረድታችሁ ሀገራችሁን በማንአለብኝነት ለማፍረስ ከተነሱ አማፂ ኃይሎች ለመከላከል ቀዳሚ ተሰላፊ እንደምትሆኑ አንጠራጠርም፡፡ ወጣቶች በግንባር ከመሰለፍ በመለስ በያላችሁበት ሁሉ አካባቢያችሁን ደህንነት እና ፀጥታን በንቃት የመጠበቅ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ከመንግሥት እና በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በሕወሃትም ሆነ በሌሎች ሸሪኮች ሊፈጠር የሚችል ስጋትን በተጠንቀቅ መከታተልና መመከት ይኖርባችኋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በመሃከላችሁ ክፍፍልን እና ጥላቻን ለመፍጠር ለሚፍጨረጨሩ ኃይሎች እጅ ባለመስጠት ግዴታችሁን በፍፁም ጀግንነት እንደምትፈፅሙት ሙሉ እምነት አለን፡፡

በተለያየ መስክ የተሰማራችሁ ሠራተኞች በተለይ የመንግሥት ሠራተኞች ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ብቻ ሳይሆን ተገቢውን ክብርና መስተንግዶ በመስጠት ዜጎች በመልካም አስተዳደር እጦት እንዳይማረሩ የማድረግ ኃላፊነት አለባችሁ፡፡ ዛሬ የምናደርጋቸው አያንዳንዱ እንቅስቃሴ ዜጎችን በማማረር የሚያበቃ ሳይሆን ሰርተን የምንኖርበት ሀገር ሊያሳጣን እንደሚችል ተገንዝባችሁ፤ ኃላፊነታችሁን በአግባቡ በመወጣት የሕወሃትን ሴራ ማክሸፍ ይጠበቅባችኋል፡፡ በኃላፊነት ላይ የምትገኙ የመንግሥት ሹሞች ከምንጊዛም በላቀ ዲስፕሊን ምሣሌ ሆናቸው አመራር በመስጠት የዜጎቸን እንግልት መቀነስ ይኖርባችኋል፡፡

ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣነው መግለጫ፥ ሕወሃትን ደግፋቹኻል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እና በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎባቸው የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥት እና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቃችን ይታወሳል። አሁንም ቢሆን በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተጋረጠው አደጋ ለመቀልበስ የሚደረገው እርምጃ ዘላቂ አብሮነታችንን በማይጎዳ መልኩ ሕግ እና ሥርዓትን ተከትሎ መወሰድ እንዳለበት እያስታወስን የዜጎች ሁሉ ሰብዓዊ መብት ያለምንም ልዩነት በእኩል እንዲከበር የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “በአቶ ጃዋር መሐመድ እጅ የተገኘው የሳተላይት መሣሪያ የጉምሩክ ሥርዓትን ሳይከተል ወደ ሀገር የገባ ነው” - ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

ዘንድሮ ያለው ክረምት ከሞላ ጎደል መደበኛ የሆነ ሲሆን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ያለውን የተፈጥሮ ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በጦርነት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያስችል ምርት በማምረት ገበያውን እንዲያረጋጉ፤ በግንባር ለሚፈለጉ የምግብ አቅርቦት የበኩላችሁን እንደወትሮ በጥንካሬ እንደምትሰሩ እንተማመናለን፡፡ ወደ ግንባር ለተንቀሳቀሱ የአርሶ አደርና አርብቶ አደር ማሳዎችን ቅድሚያ በመስጠት የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ወጣቶች ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ፍሪያማ እንዲያደርጉ በዚህ አጋጣሚ አደራ እንላለን።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸውን ልዩነቶች ወደጎን በማለት የሀገር ህልውና ፈተና ላይ መውደቁን በቅጡ በመረዳት፤ አባሎቻቸውም የአማፂያኑን እብሪት ለማስተንፈስ በሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ ጥሪ እንዲያደርጉ ከአደራ ጭምር እንጠይቃለን፡፡ ኢዜማ እንደ ሀገራዊ ፓርቲ የሀገር ህልውናን ለማስከበር እና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ በዚህ አጋጣሚ እያረጋገጠ በቀጣይ ከአባላት ጋር በመመካከር የሚያደርጋቸውን ተጨማሪ ነገሮች እንደተጠበቁ ሆኖ አሁን ብር 250,000.00 (ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር) ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከመኖሪያቸው ለተፈናቀሉ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲውል ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ያስረክባል።

የሲቪክ ማኅበራት እና የተራዕዶ ድርጅቶች፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚጠበቅባችሁ ሲሆን፤ በሚኖራችሁ የጋራ መድረክ ሁሉ የሀገር ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ደህንነት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ግንዛቤ ማስገባት ይኖርባቹኋል ብለን እናምናለን፡፡ በተለይ በሠላምና እርቅ ዙሪያ የምትሠሩ ሲቪል ማኅበራት የአማፂዎቹ የጦርነት ጉሰማ እንዲቆም እና በቀጣይም የሕዝብ ለሕዝብ ቁርሾ እንዳይፈጠር በስፋት መሥራት ይጠበቅባችኋል፡፡ የሀገር ሉዓላዊነት እና አንድነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢዜማ ለሠላማዊ መፍትሔዎች የሚደረጉ ጥረቶችን ሁሌም የሚደግፍ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል፡፡

የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፤ ከዚህ በፊት ከምታደርጉት በላቀ፣ በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ ኢትዮጵያዊነት ከፍ በማድረግና በዜጎች ውስጥ በማስረፅ ለትውልድ የሚተላለፍ የፈጠራ ሥራዎችን እንድታቀርቡልን ጥሪ እናቀርባለን፡፡ በግንባር ጭምር በመገኘት ሕይወቱን ለሀገር ለመክፈል ፈቃደኛ ለሆነው ሠራዊታችን የተለያዩ ማነቃቂያዎች በማድረግ ሞራሉን በመገንባት አጋርነታችሁን በተግባር ማሳየት ይኖርባቹኋል፡፡

ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ

No photo description available.

Comment
Share

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.