መንግስት አገራዊ ጥሪ ያቀረበው አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን መመከትን የሚመለከት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሀሴ 06 ቀን 2013 (ኢዜአ) የፌዴራል መንግስት አገራዊ ጥሪ ያቀረበው አሸባሪውን የሕወሓት ቡድን መመከትን የሚመለከት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ። ጥሪው “የትግራይ ሕዝብ ላይ ያተኮረ ነው” በሚል በተሳሳተ መልኩ የሚነሳው ሃላፊነት በጎደለውና ከአውዱ ውጭ የተወሰደ ነው ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የፌደራል መንግስት ከትናንት በስቲያ ያወጣው መግለጫ አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን እንቅስቃሴ ኢትዮጵያዊያን በጋራ እንዲመክቱ መሆኑን አብራርተዋል።
ዜጎች ለአገራቸው ዘብ እንዲቆሙ የቀረበ ጥሪ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሆኖም የመንግስትን ጥሪ አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን “በትግራይ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው” በሚል በተሳሳተ መልኩ ተርጉመው ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
“የትግራይ ሕዝብ ላይ ያተኮረ ነው በሚል እያቀረቡበት ያለው መንገድ መንግስት ለመግለጽ የፈለገውን ነገር ላለመረዳት የሚፈልጉ ሃላፊነት የጎደላቸው አንዳንድ አካላት ናቸው” ብለዋል።
በሌላ በኩል የመንግስትን መግለጫ ከአውድ ውጪ አዛብቶ የማቅረብ አዝማሚያም መታየቱን አመልክተዋል።
“አካፋን አካፋ ማለት ያስፈልጋል፤ ህወሓት አሸባሪ ቡድን ነው፤ ቡድኑ የሚፈጽመውን ድርጊት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማውገዝ አለበት” ብለዋል ሃላፊዋ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አገር በመከላከል ዘመቻው ለመሳተፍ እድሜያችሁና አቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የአገር ዘብነታችሁን አሳዩ ማለቱ ይታወቃል።
ኢዜአ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.