የትግሉ ዓላማ አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ተላላኪዎቹንም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆኑ ማድረግ መሆኑ ተገለጸ

gizachew

የትግሉ ዓላማ አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ተላላኪዎቹንም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆኑ ማድረግ መሆኑን የአማራ ክልል የመንግሥት ገለጸ፡፡
ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ መረጃ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ አሸባሪው ትህነግ በፈጸመው ወረራ የወገን ኀይል ተገቢውን ምላሽ እየሰጠው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በተለያዩ አካባቢዎች ከፈጸመው ወረራ ባሻገር በኦሮሚያ ክልል በተላላኪዎቹ አማካኝነት አማራ በብዛት በሚኖርበት አካባቢ ጥቃት ለመሰንዘር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
“አሁን የምናደርገው ትግል በጊዜያዊ ድል የምናቆመው አይደለም፤ ቦታን የማስለቀቅ እና የመያዝ ጉዳይም አይደለም፤ ትልቁ ዓላማ አሸባሪውን ሙሉ በሙሉ መደምሰስና ተላላኪዎቹንም የኢትዮጵያ ስጋት መሆን እንዲያቆሙ ማድረግ ነው” ብለዋል፡፡
የቡድኑ ዓላማ አማራን የማጥፋትና ኢትዮጵያን መበተን መሆኑን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ሽብርተኛው ትህነግን ለመቅበር መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ሕዝቡን ደጀን በማድረግ ትግል እያካሄዱ ነው፤ በዚህም ከትናንት ጀምሮ ባለው መረጃ መርሳ ከተማን ሙሉ በሙሉ ከሽብር ቡድኑ ነፃ ማድረግ መቻሉ ተገልጿል፡፡
የጠላት ኀይል በየግንባሩ እየተደመሰሰና በርካታ የቡድን መሣሪያዎች ሳይቀር እያስረከበ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ተዋጊዎች ብቻ ሳይሆን አዋጊ መሪዎቹም እየረገፉ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡
የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ሕይወቱን እየሰጠ ለሚገኘው የወገን ኀይል የስንቅ ዝግጅቱ ሳይቆራረጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ ግዛቸው አሳስበዋል፡፡
አቶ ግዛቸው ለህልውና ዘመቻው በሀገር ውስጥም ኾነ በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች መንግሥት በከፈተው ሕጋዊ የባንክ የሒሳብ ቁጥሮች ብቻ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ከጦርነት የተራረፉ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር ተመሳስለው መረጃን የሚያቀብሉ፣ ስንቅና መሣሪያ የሚሰጡ ሰርጎ ገቦችን ያሰማራ ስለሆነ በየአካባቢው ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥብቅ ፍተሻ ሊደረግ እንደሚገባ አቶ ግዛቸው አሳስበዋል፡፡
ፍተሻ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የጸጥታ ኀይሉ እጅ ከፍንጅ ካገኘ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ነው አቶ ግዛቸው የገለጹት፡፡
የሽብር ቡድኑን ማጥፋት ማለት ኢትዮጵያን መታደግ ስለሆነ ሁሉም በጋራ ሊረባረብ እንደሚገባ ጥሪ ማድረጋቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
አሚኮ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.