ማን ያርዳ የቀረበ ማን ይናገር የነበረ ነውና ወንድማችን አርቲስት ዱባለ መላክ በራያ ግንባር ተገኝቶና ተሳትፎ ያየየውንና እየሆነ ያለውን በአሻራ ሚዲያ ቀርቦ ገልጾታል።


ማን ያርዳ የቀረበ ማን ይናገር የነበረ ነውና ወንድማችን አርቲስት ዱባለ መላክ በራያ ግንባር ተገኝቶና ተሳትፎ ያየየውንና እየሆነ ያለውን በአሻራ ሚዲያ ቀርቦ ገልጾታል።
እኛም ገና በጠዋት መከላከያ ከትግራይ ነቅሎ እንደወጣ በደካማውና አጎብዳጁ ብአዴን አመራር ሰጪነት የአማራ ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ ይከፍላል አሻጥርም(sabotage) ሊሰራበት እንደሚችል አንድ ሺህ አንድ ጊዜ ተናግረናል። አሁንም ቢሆን ህዝቡብአዴንን ትቶ በየአካባቢው በራሱ የጎበዝ አለቆችና የአመራር ጥበብ ባላቸው ሰዎች እየተመራ ራሱን ሊያደራጅና ህልውናውን ሊያስጠብቅ ይገባል።
———————-

1፤ በአፋር ክልል በተፈናቃዮች ጊዜያዊ መጠለያ ላይ ባለፈው ሐሙስ በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ከ100 በላይ ሕጸናት ሞተዋል መባሉ ክፉኛ አስደንግጦኛል ሲል የተመድ ሕጻናት ድርጅት ዩኒሴፍ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሕጸናትን ጨምሮ ሌሎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞትና ለምግብ ዕጥረት የዳረገው ግጭት ባስቸኳይ እንዲቆም ድርጅቱ ጠይቋል። ልዩ ስሙ “ጋሊኮማ” በተባለ ቦታ የጦርነቱ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ላይ በተፈጸሙ የከባድ መሳሪያ ጥቃቶች፣ 107 ሕጻናትን ጨምሮ ከ240 በላይ ሰዎች እንደተገደሉና በመጋዘን የተከማቸ የዕርዳታ ምግብ እንደወደመ የክልሉ መንግሥት ባለፈው ዐርብ መግለጹ ይታወሳል።

 

2፤ የሕወሃት ተዋጊዎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልድያ ከተማ ላይ የተኮሷቸው ከባድ መሳሪያዎች በሼክ አል አሕሙዲን ስታዲዬም እና በሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ ማረፋቸውን የአማራ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ ቢሮን ጠቅሶ የክልሉ ብዙኀን መገናኛ ዘግቧል። በጥቃቱ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰውን ጉዳት ቃል አቀባይ ግዛቸው ሙሉነህ በአሃዝ ባይገልጹም፣ በንጹሃን ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ግን ተናግረዋል። የሕወሃት ተዋጊዎች ከባድ መሳሪያዎችን እስከዛሬ ረፋዱ ድረስ ወደ ከተማዋ ሲተኩሱ እንደነበር የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ በአካባቢው እስካሁንም ውግያ እየተካሄደ መሆኑን ገልጠዋል።

 

3፤ መንግሥት ከሕወሃት አማጺያን የከባድ መሳሪያ ጥቃት እንዲታደጋቸው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች መጠየቃቸውን የከተማዋ ኮምንኬሽን ቢሮ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። ትናንት እና ዛሬ የሕወሃት ተዋጊዎች ወደ ከተማዋ ከባድ መሳሪያዎችን በተደጋጋሚ ተኩሰዋል ተብሏል። መንግሥት በመከላከያ ሠራዊት አማካኝነት በሕወሃት ተዋጊዎች ላይ የኃይል ርምጃ መውሰድ እየቻለ፣ በከተማዋ ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በዝምታ መመልከቱ እንዳሳዘናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

 

4፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የትግራዩን አማጺ ሕወሃትን እና ፌደራል መንግሥቱን ለማደራደር እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ ማለቱን ሪፖርተር ዘግቧል። የትግራዩ ግጭት በንግግር እንዲፈታ ለማስቻል የጋራ ምክር ቤቱ አመራሮች ሁለቱን ወገኖች ወደ ድርድር ለማምጣት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት፣ ባለፈው ዓርብ በአዲስ አበባ ለሚገኙ የውጭ ዲፕሎማቶች ስለ ምክር ቤቱ ሚና በሰጡት ገለጻ እንደሆነ ዘገባው ጠቅሷል።

 

5፤ በአዲስ አበባ የሕንድ ኢምባሲ በትግራይ ክልል በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያስተምሩ የነበሩ ሕንዳዊያን የታገደ የባንክ ሒሳባቸው እንዲከፈትላቸው ለመንግሥት ጥያቄ እንዳቀረበ ዋዜማ ሰምታለች። ኢምባሲው ጥያቄውን በደብዳቤ ያቀረበው ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር እና ለውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ሲሆን፣ ለመምህራኑ ያልተከፈላቸው የሰኔ እና ሐምሌ ወር ደመወዛቸውም እንዲከፈላቸው ዋዜማ ካየችው የኢምባሲው ደብዳቤ ተረድታለች። ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የሄዱ ከ50 በላይ ሕንዳዊያን መምህራን በኢምባሲው ወጭ ሆቴል ተቀምጠው ጉዳያቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

 

6፤ አንድ የአሜሪካ ዶላር በጥቁር ገበያ የሚመነዘርበት ዋጋ ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ የ48 በመቶ ልዩነት እንዳሳየ ሪፖርተር አስነብቧል። ባለፈው ሳምንት በ5 ቀናት ውስጥ ብቻ በመደበኛው እና በጥቁር ገበያው መካከል የነበረው የ28 በመቶ የምንዛሪ ልዩነት ወደ 48 በመቶ ከፍ ማለቱን ዘገባው ጠቅሷል። ባሁኑ ወቅት ባንዳንድ የጥቁር ገበያ ምንዛሬዎች አንድ ዶላር በ67 የኢትዮጵያ ብር እየተመነዘረ ስለመሆኑ ታውቋል። ባለፉት 3 ዓመታት ሕገወጥ የዶላር ምንዛሬ ከእጥፍ በላይ፣ ሕጋዊው ምንዛሪ ደሞ በአማካይ 36 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ዘገባው ከባለሙያዎች መስማቱን ገልጧል።

 

7፤ ሱዳን በኢትዮጵያ የወከለቻቸውን አምባሳደሯን ለምክክር እፈልጋቸዋለሁ በማለት እንደጠራች ሮይተርስ ዘግቧል። ሱዳን አምባሳደሯን ወደ ካርቱም የጠራችው፣ የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ የትግራዩን ግጭት ለማሸማገል ባለፈው ሳምንት ያቀረቡትን ጥያቄ ኢትዮጵያ ውድቅ በማድረጓ እንደሆነ የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ሱዳን ምን ልታደርግ እንደምትችል ኢትዮጵያ ብታውቅ፣ አቋሟን ልታስተካክል ትችላለች- ብሏል መግለጫው። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም።

 

[ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.