አሁን ጦርነቱ ያለው ትግራይ ውስጥ አይደለም: አማራ ምድር እና አፋር ምድር ነው! – ባየ ተሻገር

231844348 975072589730765 3360721185381364699 n

ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስተር ቢሮ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም የሰጠችውን press briefing ተከታትዬ ነበር። የመንግሥት ሙሉ ትኩረት በጠላት ፕሮፓጋንዳ ላይ ሲሆን “የትግራይ ሕዝብ እርዳታ እንዴት ይድረስለት” ከሚለው አጀንዳ ውጭ የሚያስጨንቃቸው ነገር ያለ አይመስልም።

አሁንኮ ጦርነት ውስጥ ያለው የትግራይ ሕዝብ አይደለም። ጦርነቱ ያለው አማራ ምድር እና አፋር ምድር ነው! በወሎ ግንባር ፣ በጎንደር ግንባር፣ በአፋር ግንባር ነው። የትግራይ ሕዝብ ተርቧል ሲሉት የአማራ ሕዝብም የአፋር ሕዝብም ተርቧል እርዳታ ለሁሉም ያስፈልጋል አግዙኝ አይልም። በቃ ጥረቱ ሁሉ ፕሮፓጋንዳውን ማርገብና አስርበሃል እንዳይባል ራሱን መከላከል ብቻ ነው።
የአማራ ሕዝብ በይበልጥ ከአላማጣ እስከ ወልዲያ ባለው ቀጠና አሸባሪ በተባለ ቡድን እየደረሰበት ያለው መፈናቀል፣ ግድያ እና ዘረፋ ለምን ትኩረት አይሰጠውም?! ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆነ ሕዝብ መፈናቀል አንሶ ነው?! የአማራ ገበሬ ማረስ አይፈልግም? የአማራ እናቶች መሰደድ የሰብዓዊነት ጥያቄ አያስነሳም? በኢትዮጵያ ውስጥ የአማራ ሕዝብ ግድያና መፈናቀል ተንቆ መታለፍ አለበት? የአማራ ሕዝብ ስቃይ እንደ ተራ ነገር እየታዬ እስከ መቼ ይቀጥላል?
በአማራ ሕዝብ ላይ ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየደረሰ የፌደራል መንግሥቱ አሁንም የዘወትር እንቅስቃሴውን በማድረግ ላይ ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ መንግሥት በአሁኑ ጦርነት ምንም ዓይነት Urgency እያሳዬ አይደለም። የጎረቤት አገር ውስጥ ካለ ጦርነት ራሴን እንዴት ልከላከል ይገባል ከሚል የቅድመ ጥንቃቄ ያነሰ ዝግጁነት ነው በአደባባይ እየታየ ያለው። ለሕዝብ ያልተገለፀ በውስጥ የተደረገ ዝግጅት ካለ ደግሞ ወራሪውን ኃይል ደምስሱትና እንየው።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል የክተት አዋጅ ቢያውጅም ሕዝቡ በዚያ መጠን ዝግጁ ሆኖ ሲዋጋ አይተነዋል የሚል መረጃ አልመለከትም። ከአላማጣ ጀምሮ እስካሁን ወራሪው ቡድን የሚጠቀመው ታክቲክ አንድ ዓይነት ነው። በጥቂት ወታደሮቹ የሆነ ቦታ ሰርጎ ይገባል፣ አንድ ፎቶ ተነስቶ ፕሮፓጋንዳ ይለቃል፣ የውስጥ ጠላትም የትህነግ አባላትም ያቺን ፎቶና ፕሮፓጋንዳ ያራቧታል፣ ሕዝቡ ይሸበርና ይሸሻል፣ ወራሪው ኃይል ከኋላ ሰው ያመጣና ሙልጭ አድርጎ ይዘርፋል። ከዛ ሁለት ሶስት ሆኖ የገባውን አካል መልሰነዋል ደምስሰነዋል ይባላል፣ እንደገና በሌላ አቅጣጫ የሆነ ቦታ ላይ ይታያል ይገድላል ይዘርፋል። ይኼው ነው።
ችግሩ የዚህኛው አካል ነው የዚያኛው ነው ለማለት ሳይሆን ሁላችንም የምናወራውንና የምንመኘውን ያክል እንደ ሕዝብ ኅልውናችን አደጋ ላይ ተጋርጧል ብለን የምር በቁርጠኝነት እየተዋጋን አይደለም ለማለት ነው። ሰበብ ከማብዛት ሕዝባችንን ገድለህ ውደቅ ብንለው ያደርገዋል። በየአካባቢው ቅስቀሳ አድርጎ ሁሉም ነገር ዘግቶ ትህነግን መደምሰስ ይቻላል።
አዎ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት አለ፣ አዎ የአማራን ሕዝባዊ ጦር ከመከላከያ ሰራዊቱ ጋር ለማዋጋት የሚደረግ ፕሮፓጋንዳ አለ፣ አዎ የተወሰኑ አማራ የሆኑ ሰዎች ትህነግ ተመልሶ እንዲመጣ ይፈልጋሉ፣ አዎ የሕዝቡን ሥነ-ልቦና ሊጎዳ የሚችል መረጃ መሰራጨት የለበትም። ግን ደግሞ በተጨባጭ የመመከት ሥራ መሰራት አለበት። ስለዚህ ማሳሰብ ያስፈልጋል። ማሸነፍ ሲባል ደግሞ ጠላትንም ባንዳንም የቅርቡንም የሩቁንም ነው።
ጠላት በሕዝባችን ላይ ከዚህ በላይ ጉዳት ካደረሰ በኋላ ኡ ኡ ኡ ማለት ዋጋ የለውም። የፌደራል መንግሥቱ በአስቸኳይ የተናጠል የተኩስ አቁም የሚባለውን ቀልድ ማቆም አለበት። እኛም አቁምና በሙሉ ኃይል ግጠም ማለት አለብን። ሕዝቡም ያለውን ሙሉ አቅም እንደግሞዋለሁ ያለውን ሙሉ አቅም በጦርነቱ ላይ ማዋል ይገባዋል።
በሙሉ አቅማችን ብንንቀሳቀስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትህነግን እና የእሱን ተላላኪዎች መደምሰስ እንችላለን።
እናሸንፋለን
ባየ ተሻገር

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.