“አንድነታችንን ጠብቀን ያጋጠመንን የህልውና አደጋ በትግላችን እንቀለብሰዋለን”

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከአማራ ክልል መንግሥት የተሰጠ መግለጫ ቀጥሎ ቀርቧል።

የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነው ትህነግ ወያኔ እንደሀገር ባደረሰብን ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል እንዲሁም ለፈጸመብን ሀገራዊና ሕዝባዊ ክህደት የሀገራችንን የግዛት አንድነት በመሸርሸር ሉዓላዊነቷ የማይከበር፣ ራሷን ችላ መቆም የማትችልና በሁሉም መስክ ተንበርካኪ ሀገር ባለቤቶች እንድንሆን በርካታ ደባ ፈጽሞብናል፡፡ በዓለም አደባባይ የምንኮራበት ሀገራዊና ሕዝባዊ የጋራ ታሪክ ባህልና እሴት እንዳይኖረን አንድነታችንንና አብሮነታችንን በፈጠራ ታሪክ እየቦረቦረ እርቃናችንን እንድንቀር፣ አንዳችን ለሌላችን ጋሻና መከታ መሆን ሲገባን እርስ በእርስ በመጠራጠር አውሎ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንድንላጋና በጠላትነት እንድንፈራረጅ ከሰማይ በታች ያልፈጸመብን ግፍ የለም፡፡
ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተባብረንና ተፈቃቅደን የጸረ ጭቆና ትግሉን አንድ ብለን ስንጀምር በጋራ ያነሳነው የፍትህና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ በትህነግ መንደር የቱን ያህል መራር የሆነ የመደፈር ስሜት እንደፈጠረ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግ ከመንበረ ስልጣኑ ተምዘግዝጎ ሲወድቅና መቀሌ ሲከትም የነበረው ብቸኛ ምክንያት ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ የሚል ፖለቲካዊ ቁማር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በውሁድ ፓርቲ ደረጃ የተፈጠረውን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት የአህዳውያን ውጤት አድርጎ ያበሻቀጠው ፍላጎቱ በለመደው የአድራጊ ፈጣሪና የአዛዥነት ሚና ያልተሳተፈበትን መዋቅር ለማጣጣል ከማለም ባሻገር ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተጠቃሚነት ባለው ከፍ ያለ ንቀትና ጥላቻ ምክንያት መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ እንዳይንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ የልብ ልብ ሰጥቶት ጥቅምት 24 /2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውድ ልጆችን በግፍ ያለርህራሄ አሰቃቂ ግድያ ከፈጸመባቸው በኋላ የዕዙን ጠቅላላ ንብረት በመውረስ በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ማወጁ ይታወቃል፡፡ የአማራ ክልልን ወሰን ጥሶ በማለፍ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም በማይካድራ ንጹሐን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ይህንን ተከትሎም መንግሥት በየደረጃው የሕግ የበላይነት ለማስከበር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በሂደቱም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ይሁን እንጂ ይህ አረመኔና አሸባሪ ቡድን አይኑን በጨው አጥቦ ጥቃት የተፈጸመበት በማስመሰል ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በማጭበርበር ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ መሰረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህ አሸባሪ ቡድን የጀመረብንን ግልጽ ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያወግዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፍጹም ጥርጣሬ የለንም፡፡ በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ትግላችን ለሕዝባችን ህልውናና ለሀገር ሉዓላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ አረመኔና ጨካኝ ቡድን መሆኑ እንዲታወቅና ሁሉም የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከህልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተውና ከዚህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ጋር ቀጣይ የምናደርገው ሁሉ አቀፍ ትግል የህልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በህይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እንዲጠባበቅ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

አሸባሪው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ከሕጻን እስከ አዋቂ በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግጋትን በመቃረን ሕጻናትንና ሴቶችን በጅምላ ጦርነት እየማገደና ያለ የሌለውን አቅሙን ተጠቅሞ ክልላችን ላይ ወረራ የፈጸመ ሲሆን በተለይም ለዘመናት የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ አሁናዊ ሙከራ የጀመረ መሆኑ በአካባቢው የሚኖሩ አማራዎችንና የአማራ ክልል ተወላጆችን ፈጽሞ የማጥፋት ህልሙን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ይህንን አረመኔያዊ ድርጊትና ዳግም ወረራ የክልሉ መንግሥት በፍጹም የማይቀበለውና በጀመርነው የህልውና ትግል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን የምናረጋግጥ መሆኑን አበክረን እንገልጻለን፡፡
ስለሆነም፡-

1ኛ. በየግንባሩ የምትገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልላችን ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት፣ ሕዝባዊ ፖሊስና ሰላም አስከባሪ አባላት እንዲሁም ሀገርና ሕዝብን ለማዳን የተግባር እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ የምትገኙ የየክልሉ የጸጥታ አካላት በዚህ ታሪካዊ መድረክ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ለሀገራችሁ ሉዓላዊነትና ለሕዝባችሁ ህልውና የምትከፍሉትን ክቡር መስዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው ይኖራል፡፡ በቀጣይም የተሰጣችሁን ሕዝባዊና ሀገራዊ ተልዕኮ በጽናትና በቁርጠኝነት እንደምትወጡ እምነታችን የጸና ነው፡፡ ስለሆነም መላው የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ከጎናችሁ መሆኑን አውቃችሁ በጀግንነት ታሪካዊ ጠላታችንን በመደምሰስ ለሀገራችሁ ዳግም የኩራት ምንጭ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

2ኛ. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትህነግ ወያኔ ላይ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ርብርብ ሁሉ ማድረግ አለበት ብለን እናምናለን፡፡ አሸባሪው ትህነግ ሀገር ከማፍረስ እኩይ ተልዕኮው ሊታቀብ የሚችለው የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በጽናትና በዓላማ ቁርጠኝነት በጋራ መጠበቅ ስንችል ስለሆነ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ በጋራ እንድንቆም የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

3ኛ. በየትኛውም ዘመን ሰልጥናችሁ፣ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ለማስከበር በማንኛውም የመንግሥት ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ተሰልፋችሁ ስታገለግሉ የቆያችሁና በታሪክ አጋጣሚ የሙያ ዘርፍ የቀየራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች ለህልውናችን የምናደርገውን የትግል ጥሪ ተቀብላችሁ በክልሉ ጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እያቀረብን ከዛሬ ጀምሮ በየአካባቢያችሁ ሰላምና ደኅንነት ጽሕፈት ቤት በአካል ተገኝታችሁ በፈቃደኝት እንድትመዘገቡ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

4ኛ. መላው የክልላችን ወጣቶች ከፊት ለፊታችን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ያለበቂ ዝግጅትና ደረጃውን ከጠበቀ ስልጠና ውጭ የምንጋፈጠው አይደለም፡፡ ስለሆነም ከማንኛውም ግብታዊ እንቅስቃሴ ታቅባችሁ በየደረጃው ለሚኖረው ምልመላና ስልጠና በመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጋችሁ የመንግሥትን ጥሪ እንድትጠባበቁ እናሳስባለን፡፡

5ኛ. መላው የክልላችን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች የጀመርነው የህልውና ትግል የሁላችንንም አንድነት፣ ህብረትና ተቀራርቦ መሥራት የሚጠይቅ ነው፡፡ በሩቅ ሆኖ ስህተት በመፈለግና እርስ በርስ በመነቋቆር ከጠላት መንጋጋ ፈልቅቀን የምንታደገው አንዳችም ህልውና የለንም፡፡ በቂ መረጃ ባገኘንበትም ባላገኘንበትም ጉዳይ ላይ ተሳፍረን በተለያዩ አቅጣጫዎች መክነፍ ለጠላቶቻችን ተጨማሪ ጉልበት ከመሆን ባለፈ ለሕዝባችን የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ስለሆነም የጋራ ዕጣ ፋንታችንን በጋራ ጥረት የምናስከብርበትና አደጋ የተጋረጠበትን የሕዝባችንን ህልውና ከጠላት ጥቃት የምንታደግበት የታሪክ መድረክ ላይ ስለምንገኝ ከመቸውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው የሕዝባችንን አንድነት ጠብቀን በጋራ እንድንረባረብ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

6ኛ. መላው የክልላችን ሕዝብ፣ በከተማና በገጠር የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትገኙ ምሁራንና የክልላችን ተወላጆች፣ በተለያየ ሙያ ተሰማርታችሁ ሀገርና ሕዝብ በማገልገል ላይ የምትገኙ የክልላችን ነዋሪዎችና ባለሀብቶች የጀመርነውን የህልውና ትግል በማገዝ የትግል ሂደት አዎንታዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

በመጨረሻም የጀመርነው ትግል እልህ አስጨራሽ በጣም መራርና ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ የእኛ አንድ መሆንና ለጋራ ግብ በጋራ መተባበር በመድረኩ አሸናፊ ሆነን እንደምንወጣ ያለምንም ጥርጥር ልናረጋግጥልችሁ እንወዳለን፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን የአማራ ክልል ሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ተጠቃሚነት ውጭ እንደማይሳካ ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ የምናደርገው ትግል ለሀገራችን ሉዓላዊነት መከበርና የጭቁን ሕዝባችን የህልውና ትግል እንጂ እላፊ ጥቅም ለማግኘት የምናደርው ትግል በፍጹም አይደለም፡፡

የአማራ ሕዝብ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ከእብሪት ይልቅ ድርድርን የሚያስቀድም በፍትሕ ከሄደች በቅሎየ ያለፍትሕ ያጣኋት ጭብጦየ ትቆረቁረኛለች ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው፡፡ ስለሆነም ዛሬ የምናደርገው ትግል ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው የኩራትና የክብር ምንጭ እንደሚሆን አንጠራጠርም፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የወሰደው ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ የጠላት ኃይል ሀገርና ሕዝብ ለማዋረድ የሚያደርገውን እብሪተኛ እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት እናሳስባለን፡፡

 

ትግላችን ለህልውናችን !
ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

1 Comment

  1. መቼም እንዲህ ያለ መልእክት አገኘሁ ተሻገር ያስተላልፋል ብዬ ለቅንጣት አላስብም ሽመልስ ይቆጣዋልና።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.