የብልጽግና መንግሥት የተናጠል-ተኩስ-ማቆም እና ከትግራይ ጠርጎ የመውጣት ውሣኔ ምክንያቶች እና መዘዞቹ፣

የግል አስተያየት፡አያል ሰው ደሴ (ዘብሔረኢትዮጵያ)

ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ/

ባለፉት ጥቂት ቀናት በእኛው በኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረጉ የአሳብ ልውውጦችን በጥሞና ተከታትያለሁ። አብዛኞቹ የአሳብ ልውውጦች በእንግሊዘኛ ስለሆኑ እኔም ያለኝን አስተያየት በዚያው ቋንቋ መጻፍ ከጀመርኩ በኋላ በአማርኛ መጻፉን መረጥኩ። የአሳብ ልውውጡም የኢትዮጵያ መንግሥት በትሕነግ ላይ የሕግ ማስከበር ግዳጅ ብሎ በጠራው ዘመቻ ለስምንት ወራት ያኽል ተልዕኮውን ሲወጣ የነበረውን ሠራዊት በተናጠል የተኩስማቆም የፖለቲካ ውሣኔ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከትግራይ ማውጣቱን በተመለከተ ነው።

መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማቆም 1በእብሪተኞቹ የትሕነግ (ወያኔ) መሪዎች ውሣኔ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ/ም በአገራችን መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ጦር ላይ የተፈጸመውን ከፍተኛ የአገርክህደት ጥቃት ተከትሎ ማዕከላዊ መንግሥት ሕግማስከበር ብሎ የሰየመውን ወታደራዊ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱ ይታወቃል። በወቅቱ አሳቤን አካፍያለሁ።

ከሁሉ በፊት የዚኽን የአንድጎንዮሽ የተናጠል ተኩስ ማቆም የፖለቲካ ውሣኔ ባኅሪ መረዳቱ መልካም ይሆናል። እዚኽ ላይ ቁልፉ ቃል የፖለቲካ” የሚለው መሆኑን ልብ ይሏል። በመንግሥት ትዕዛዝ የሚደረግን ማንኛውም ጦርነት ለማስጀመርም ሆነ ለማስቆም በፖለቲካ ውሣኔ ተፈጻሚ እንደሚሆን ግልጥ ነው። ለወታደራዊ ግዳጅ መሣካትም ሆነ ሽንፈት የጦር መሪዎች ብቻ ሣይሆኑ ፖለቲካውን የሚቆጣጠረው ክፍል ውሣኔ ወሣኝነት እንዳለውም የሚካድ አይደለም። ችግሮች መኖራቸው ባይካድም፣ ጦሩ ከትግራይ እንዲወጣ የተደረገው የተሰጠውን ግዳጅ መወጣት አቅቶት ወይም በወታደራዊ ፍልሚያው ተቸንፎ ሣይሆን በፖለቲካ ውሣኔ መሆኑ በበቂ ግልጥ ሊሆን ይገባል።

መንግሥት በትሕነግ ላይ ጦርነት ሲያውጅ የመጨረሻ ግቡ ምን ነበር? ከሥልጣን ማውረድ ወይስ በይፋ እንደተነገረው በሕግየማስከበር ተልዕኮው መሪዎቹን እና ተባባሪዎቻቸውን ይዞ ለፍርድ ማቅረብ? ወይም መደምሰስ ነው? ለጥያቄዎቹ መልስ የማግኘቱ አስፍላጊነት የጦርነቱን ባኅሪ ለመረዳት ስለሚለጠቅም ነው። እንደሚታወቀው ወደ ጦርነት ሲገባ፤ (በተለይም መቸ? የት? እንዴት? የሚሉትን አውቆ እና ወስኖ በምርጫ የሚገባበት ጦርነት) ለምሣሌ በአጥቂነት ግዳጅ የሚሠማራ ከወዲሁ ማወቅ የሚኖርበት መቋጫውን (መውጫውን) እና እዚያ ግብ ለመድረስ የሚጠይቀውን እና የሚያስከፍለውን ሁለንተናዊ ዋጋ ይሆናል።

የሚከተሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች መጠየቁ አስፈላጊ ይሆናል።

. ትሕነግ ይኽን እኩይ የአገር ክህደት ወንጀል ለመፈጸም እንዴት ቻለ?

. መንግሥት በዚኽ ድርጅት ላይ ጦርነት ሲጀመር ልዕለግቡ ምን ነበር?

. የጦርነቱ ዋነኛ የሆነው የመጀመሪያ ምዕራፍ ከሦስት ሣምንታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ መቻሉ ይታወቃል። ቀጣይ ምዕራፎቹ ፯ ወራት የወሰዱበት ምክንያት፣ አልፎም አሁን ለተደረሰበት ውልአልባ የመቋጫ ይዞታ ላይ ለመገኘቱ እና በመንግሥት በኩል “አልቆለታል” “የተበተነ ዱቄት” ሆኗል የተባለው እና በአሸባሪነት የተፈረጀው ትሕነግ እንዴት መልሶ ሊያንሠራራ ቻለ?

. መንግሥት ጦሩን ከትግራይ ጠራርጎ ሲያወጣ ምን ዓላማ ለማሣካት ነው? ውሣኔውስ ምን መዘዞች ይኖሩታል? የተኩስ ማቆሙን ተከትሎ ለሚከሰቱ ችግሮችስ ተጠያቂው ማነው?

የመጀመሪያውን ጥያቄ በተመለከተ ለአሁኑ አስፈላጊ ስለማይሆን ለጊዜው አልፈዋለሁ።

ከሁሉም የመጀመሪያ ጥያቄ ሊሆን የሚገባው ትሕነግ ማዕከላዊ መንግሥትን ለሃያሰባት ዓመታት በበላይነት ሲመራ ከነበረበት ግንባር (ከኢሕአዴግ) በሕዝብ ግፊት የነበረውን የእልቅና ሥፍራ አጥቶ በሌሎቹ የግንባር አባላት ከተተካበት ጊዜ ጀምሮ ለውጡን አለመደገፍ ብቻ ሣይሆን በአንድ ሉዓላዊ አገር ሁለት መንግሥቶች እንዳሉ በሚያስመስል መልኩ እንደሚቃወም፣ አልፎም ለጦርነት እየተዘጋጀ እንደነበር በግልጥ ይታይ የነበረ ሃቅ ነው። የድርጅቱን መሪዎች መሠሪ ተንኮልና እብሪት ለሚገነዘብ ማንኛውም ሰው ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ለጦርነት ሙሉ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ በገሃድ የሚታይ እና ያም አገራችንን ለትርምስ እና ለኅልውናእጦት ሊዳርግ እንደሚችል መገመት ይቻል ስለነበር፣ አገራችንን ለዚኽ መዘዘብዙ አደጋ ተጋላጭ ላደረጋት ሁኔታ ተቀዳሚ ተጠያቂው ማነው? የሚለውን ማየቱ ነገሮችን አድበስብሶ ማለፍ ተገቢ ካለመሆኑም በላይ ተጠያቂነት ከሌለ በአገር እና በሕዝብ ዕጣፈንታ ላይ ኪሣራ የሚያስከትሉ ጥፋቶች በባሰ ሁኔታ እንዲቀጥሉ መፍቀድ ስለሚሆን ኃላፊነት ያለባቸውን ተጠያቂ ማድረግ አስፈላጊ ይሆናል።

ይኽን ጦርነት አሳሳቢ እና አስከፊ የሚያደርገው የአንድ አገር ዜጎችን የሚያገዳድል ከመሆኑ በተጭማሪ በቅርብ ታሪካችን ያልታየ ኅልውናተፈታታኝ አደጋዎች በውድ አገራችን ላይ ባንዣበቡበት ጊዜ መሆኑ ነው።

ጦርነት ክቡር በሆነው የሰው ልጅ ሕይዎት እና በንብረት ላይ ውድመትን ከማስከተሉም በላይ፣ በተለይ በአንድ አገር ውስጥ ባሉ ዜጎች መካከል የሚደረግ የእርስበርስ ፍልሚያ የጦርሜዳ ድልን በሚያስገኝ መልኩ ቢጠናቀቅም እንኳ በቀላሉ ሊጠገን የማይችል ጦስን ማስከትሉ የሚጠበቅ ስለሚሆን፣ በፖለቲካ አለመግባባት ምክንያት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት እስከተቻለ ድረስ ተመራጭ አይሆንም። የአገርን አንድነት እና ክብር፣ የሕዝብን ሉዓላዊነት እና ሰላም የሚወስኑ አደጋዎች ሲከሰቱ ግን ርቱዓዊ ስለሚሆን ጦርነት ውስጥ መግባት ምርጫ ሣይሆን ግዴታ ይሆናል። ወደጦርነት ሲገባ (በተለይም ችግሩ ከአገርበቀል ኃይል ጋር ሲሆን) ስለ አካሄዱም ይሁን ድኅረጦርነት እንዲኝ ስለሚፈለገው መዳረሻና ልዕለግብ ከወዲኹ ግልጥ ግንዛቤ ሊኖር፣ የተሟላ ዝግጅትና ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ለዚኽም ይመስላል የኢትዮጵያ ኅብረሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ (ኅብረሕዝብኢትዮጵያ) ጦርነቱ በይፋ ሲጀመር ባወጣው መግለጫ “በሕወሓት አመራር መረን የለቀቀ ግትርነት እና እብሪተኛ አቋም ምክንያት አሁን በአገራችን ሰሜናዊ ክፍል የተፈጠረው ደምአፋሳሽ አሣዛኝ ቀውስ ከቂምበቀል የፀዳ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያልታሰበ አደጋ እንዳይደርስ በተቻለ መጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ የተደረገበት እና ማኅበራዊ ችግሮችን የማያስከትል፣ አሰፍስፈው ለሚጥብቁ የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች መልካም አጋጣሚን እንዳያመቻች እና አንድነታችንን ከባድ ፈተና ላይ ለሚጥል አደጋ የማያጋልጥ ሊሆን ይገባል።” ሲል ያሳሰበው።

እዚኽ ላይ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ አለ። ውድ አገራችን በሱዳን ወራሪ ጦር ዳርድንበሯ በተደፈረበት፣ የውስጥ ሰላማችን በነውጠኞች በታወከበት እና በጦርነት ላይ በምትገኝበት፣ ዜጎቿ በኮቪድ፲፱ ሣንባቀስፍ ወረርሽኝ ሥጋት ላይ ባሉብት እና ታይቶ በማይታወቅ የውጭ ኃይላት ጫና ሥር በምትገኝበት ዙሪያጥምጥም የውጥረት ሁኔታ ውስጥ እያለች ነው በብልጽግና የሚመራው መንግሥት (ምንም እንኳ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ይኸ ነው የሚባል ሕጋዊ ገደብ ባይኖርበም)፣ ትኩረት እና ቅድሚያ የሰጠው በተለይም በውጭ ግንኙነት (ዲፕሎማሲው) በኩል የታየውን እጅግ አሣፋሪ ክፍተት ለማስተካከልም ሆነ ሰላማዊ ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ለሚደርስባቸው በገፍ የመፈናቀልን እና በአሰቃቂ ሁኔታ በጅምላ የመጨፍጨፍን ከባድ ችግር በማስቆም፣ ወዘተላይ ሣይሆን በተለይም ባለፉት ፬ እና ፭ ወራት በምርጫ ጉዳይ መሆኑ የቅደምተከተል ዝንፈት እንዳለበት አሣይቷል።

የጦርነቱ የመጀመሪያው ደረጃ ብዙ መስዋዕት ተከፍሎ ከሦስት ሣምንታት ባጠረ ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ድሎችን በመቀዳጀት የድርጅቱን (የትሕነግን) አከርካሪ በመስበር ተጠናቋል። ከጦርነቱ ልዩ ባኅሪ አኳያ ሲጀመር በመንግሥት በኩል ሊደረጉ ያስፈልጋል ያልናቸውን አሳቦች፣ በተለይም ሁለት ነገሮችን ማድረጉ አስፈላጊ እንደሚሆን አንዳንዶቻችን አሳስበናል። አንደኛው ከጦርነቱ ባኅሪ አኳያ ሰላማዊ ሕዝብ እንዳይጎዳ አስፈላጊው ጥንቃቄ በተደረገበት ሁኔታ፣ በደንብ እና በዝርዝር በተጠና እቅድ፣ ፋታ የማይሰጥ እና በተቻለ ፍጥነት በአንድ መልኩይሁንበሌላ አመራሩን ከሕዝብ ነጥሎ በቁጥጥር ሥር ማድረግ ወይም ከጥቅም ውጭ ማድረግ እና የእዝ ሰንሰለቱን ከአገርውጭ ካለው ጋር ጭምር በአስተማማኝ መቆጣጠር ሲሆን ሁለተኛው ክልሉ የጦርነት ቀጠና ስለሚሆን፣ አስተማማኝ ሰላም እስከሚረጋገጥ እና በጊዚያዊነትም ቢሆን ሕዝብ በነፃነት በሚመርጣቸው መተዳደር የሚችልበት ሁኔታ እውን እስከሚሆን ድረስ እስከ ስድስት ወራት ለሚሆን ጊዜ ከአዲስ አበባ በሚሾሙ ወኪሎች ሣይሆን በወታደሩ የበላይ ኃላፊነት ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉ የአስተዳደር እርከኖች በተቻለ መጠን ከትሕነግ የጥርነፋ መዋቅር ውጭ የሆኑ ከሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከሴቶች፣ ከወጣቶቸ፣ ወዘተ.. በተውጣጡ ጊዚያዊ ኮሚቴዎች ከፌዴራል ፖሊስ እና ከሠራዊቱ ተወካዮች ጋር በመሆን እንዲተዳደር ማድረግ የተሻለ መተማመንን ያስገኛል የሚል ነበር።

በተናጠል ተኩስ ለማቆም በተወሰነው በዚኽ ውሣኔም ሆነ በሌሎች ተዛማች አገራዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያውያን አንድወጥ አመለካከት የለንም፣ ይኖራል ተብሎም አይጠበቅም። የአመለካከቶቹ ልዩነት ግን ተራ የሚባል አለመሆኑ ያንኑ ያኽል ግልጥ ነው። ሆኖም፣ ከጉዳዩ ክብደት አኳያ ሁላችንንም፣ በተለይም በአገራዊ አንድነት እና በሕዝብ ልዕልና የምናምን ወገኖችን የምር ሊያሳስበን ይገባል።

በመሠረቱ ተኩስማቆም አብዛኛውን ጊዜ በሦስተኛ ወገን አማካይነት በሚደረግ ድርድር አንዳንዴም ቀጥተኛ ባልሆነ መሥመር በሚደረስ ስምምነት በተፋላሚዎች መኻል አንድም ለጦርነቱ ምክንያት የሆነውን ችግር በድርድር ለመፍታት ሲባል ወይም በዓልን ለማክበር ለተወሰነ ጊዜ ጦርነት ቆሞ ፋታ የሚገኝበት መንገድ ነው። ተኩስ የማቆም ስምምነት ተፋላሚዎቹ ተስማምተው የሚያደርጉት ሲሆን የተሻለ ውጤት ይኖረዋል፣ በአንደኛው ወገን ብቻ በተናጠል የሚደረግ የተኩስ ማቆም ውሣኔ ግን አስተማማኝ የማይሆንበት እና አልፎም ተኩስ አቆማለሁ ላላለው ክፍል የመጠናከር ዕድልን ሊሰጥ እና ችግሩ ወደአዲስ ያልታሰበ አደጋን የሚጋብዝ አሉታዊ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ሊያደርግ ይችላል።

በትግራይ የሚደረገው ጦርነት በአንዲት አገር ላይ ባመጸ ኃይል እና በመንግሥት መኻል የሚደረግ፣ ድኅረጦርነትም አብሮ በሚኖር ኅብረተሰብ መኻል የሚካሄድ በመሆኑ ሂደቱ ከባዕድ ጋር ከሚደረግ ፍልሚያ የተለየ አስቸጋሪ ባኅሪ እንደሚኖረ ግልጥ ነው። በዚኽ ምክንያት እና ከትሕነግ አደረጃጀት እና ዝግጅት አኳያ ጦርነቱ ሦስት ደረጃዎች እንደሚኖሩትም ይታወቃል። የመጀመሪያው ከሞላጎደል እኩል በታጠቁ ኃይሎች መካከል የሚደረግ መደበኛ ሊባል የሚችል ነው። ሁለተኛው ፀረሽምቅ ባኅሪ ያለው ነው። ሦስተኛው ከሁለተኛው ጎንለጎን የሚሄድ እና ባለሁለትዘርፍ ግዳጅ፣ ማለትም በአመጽ ላይ የተሰማሩ እና ወንጀል የፈጸሙ ክፍሎችን ለፍርድ ማቅረብ (ሕግን የማስከበር) ሲሆን ሌላው ዘርፍ ሕዝብን በማረጋጋት የመልሶ ማቋቋም ተግባሮችን ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር አዳልቦ ተግባራዊ ማድረግ ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጨማሪ ጉርጓድ እየቆፈረ ነው | የተባበሩት የጋምቤላ ተቃዋሚ ድርጅቶች ግንባር አማካሪ የሕወሓትን ሴራ ያጋልጣሉ

የመጀሪያው ወሣኝነት ያለው እና ምናልባትም አሁን ለተደረሰበት ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከተው ችግር ከመጀመሪያው ወደ ሁለተኛው ደረጃ በተደረገው ሽግግር ሁኔታው በሚጠይቀው መልክ ሣይሆን በመጀመሪያው ዓይነት የቀጠለ መሆኑ ነው። ይኸ የግዳጅ ምዕራፍ ተግባራዊ የሚሆነው በመደበኛ ጦር ሣይሆን በፀረሽምቅ ውጊያ ልዩ ሥልጠና ባላቸው ታጣቂዎች በአየር ኃይልና በሰውአልባ የአየር አጥቂዎች (ድሮኖች) በመታገዝ በጠላትነት የተፈረጀው ክፍል ምንም ዓይነት ፋታ ሣያገኝ እግርበግር በመከታተል አስፈላጊው እርምጃ የሚወሰድበት ተልዕኮ ነው። መቀሌ ከተለቀቀ በኋላ የታየው ግን የጦርነቱ መጨረሻ እስከሚመስል ድረስ እጅግ አስፈላጊው የግዳጅ ምዕራፍ ያላስፍላጊ ጊዜ ስለባከ ይኽንን የጦርነት ምዕራፍ በአስፈላጊው ፍጥነት እና መጠን ተግባራዊ ሆኗል የሚል እምነት የለም። የሌለ እና ሊባክ የማይገባው ጊዜ በሚያስቆጭ መልኩ ባክኗል። በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሣይቀሩ የአሁናዊ ሁኔታዎች ቀጥታ ክትትል ክፍል (ሲቹዌሽን ሩም) በተገኙበት በሽሽት ላይ ያሉትን የትሕነግ አመራር “ሌትምቀንም በቀጥታ እይታችን ሥር ናቸው”

 በተባለ በጥቂት ቅናት ውስጥ ያሉበትን ለጠጥቆመ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ውለታ እንከፍላለን የሚል ማስታወቂያ ይነገር ነበር። አመራሩን እያየናቸው ነው ከእይታችን ውጭ አይደሉም በተባለበት ጊዜ እርምጃ ያልተወሰደው ምናልባት ከእነ ጋር የታገቱም ይሁን ሌሎች ሰላማዊ ዜጎች አብረው እንዳይጎዱ ከማሰብ ሊሆን ይችላል። ያ ግን የጦርነትን አስከፊ ገጽ እና የሁለተኛውን ምዕራፍ መሠረታዊ ባኅሪ የዘነጋ ንዝህላል አመለካከት ነው። ያንን ማድረግ ባለመቻሉ ለጦርነ ያላስፈላጊ መራዘም ምክንያት መሆኑን እና ከዚያ በኋላ የጠፋውን የተፋላሚዎችም ሆነ የሰላማዊ ሰዎች ሕይዎት ማሰቡ ሌላው ከባድ ስህተት መሆኑም በተገቢ ሊጤን ይገባል።

ይኽ ችግር እንዳይከሰት ማድረግ ይቻል ነበር አልነበረም የሚለው ክርክር ለጊዜው አሁን ላለንበት ሁኔታ እርባና ስለሌለው፣ በትሕነግ ላይ የተወሰደው የአጸፋ እርምጃ፣ ሂደቱ እና አንድጎን (የተናጠል) ተኩስማቆም በሚል ጦርን ከትግራይ ጠቅልሎ የማስወጣት ውሣኔ እና አንደምታውን በተመለከተ ባለው ላይ ማተኮሩ የተሻለ ይሆናል።

በመንግሥት በኩል ይኽን ውሣኔ ለመወሰን የተሰጡ አራት ዋና ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። እነሱም፡

 • አንደኛ፡ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች በግዳጅ ላይ በተሠማሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ በሚጠጡት ውሃ መርዝ እየጨመሩ እና እያዘናጉ ከጀርባ በጥይት እና መጥርቢያን በመሣስሉ ድምፅአልባ መሣሪያዎች እየወጉ በአስቃቂ ሁኔታ ግድያ በመፈጸማቸው እና ይኽ ያልተጠበቀ እርምጃ በሕዝብ ውስጥ ተሰግስገው ጥቃት የሚያደርሱትን ወንጀለኞች ሰላማዊ ከሆነው ለይቶ ማየት ለሠራዊቱ አስቸጋሪ በመሆኑ እና በአጥቂዎቹ ምክንያት ወገኑ በሆነ ሕዝብ ላይ ጉዳት ላለማድረስ የተደረገው ተአቅቦ የበለጠ ጉዳት እያደረሰ መሄዱ በጦሩ አባላት ላይ የሥነልቦና ጫና እና የስሜት ስብራት በማስከተሉ ግዳጅን ለመወጣት ከባድ እየሆነ በመምጣቱ፣ በተለይም ለሕዝቡ የ‘ጥሞና ጊዜ’ ለመስጠት፣

 • ሁለተኛ፡ ትሕነግ በጣም ስለተመታ እና ስለተዳከመ በአገር ላይ የነበረው አደጋኛነት ቁጥር ውስጥ የማይገባ ስለሆነ፣ ጦሩን ከውጭ በኩል የበለጠ አደጋ ባንዣበቡባቸው ቀጠናዎች ማሰማራት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ፣
 • ሦስተኛ፡ ወቅቱ የእርሻ ጊዜ ስለሆነ አርሶአደሩ በእርሻው ላይ እንዲሠማራ ዕድል ለመስጠት፣
 • አራተኛ፡ በበረሃ ከሚገኙ የድርጅቱ አባላት መኻል በሰላም ወደድርድር ለመምጣት ፍላጎት ያሣዩ ስላሉ ለእነሱ ዕድል ለመስጠት፣ የሚሉት ናቸው።

ለምን እና እንዴት ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ከመሰጠቱ በፊት ለተወሰደው ውሣኔ በምክንያትነት የቀረቡትን አራቱንም በግልቡ ከመውሰድ አሳማኝ መሆን አለመሆናቸውን በበቂ መፈተሽ ያስፈልጋል። በቅድሚያ ጉዳዩን በብስጭት ቁርሴን አልበላም ያለን ሕጻን እስኪበርድለት ድረስ ምሣውንም እራቱንም የሚከለክል እርምጃ ይመስል፣ የአገርን ዕጣፈንታ በብዙ አሉታዊ መልኩ ሊወስን የሚችልን ያኽል ክብደት ያለውን ጉዳይ ጦርነቱን ድንገት አቋርጦ ጠቅልሎ የመውጣትን ውሣኔ አቃልሎ የጥሞና ጊዜ ለመስጠት ማለቱ የሚያስከትለውን ጦስ ያገናዘበ ነው ማለት አይቻልም።

. የመጀምሪያው ምክንያት ምንያኽል የተስፋፋ ችግር መሆኑን ማወቅ ባይቻልም፣ ሠራዊቱ ሲገባ ቢያንስ ትሕነግ እንደጠበቀው የትግራይ ሕዝብ ከሱ (ከድርጅቱ) ጎን ተሰልፎ ጦሩን አለመውጋቱ እና እንዲያውም መሣሪያውን በሰላም ሲያስረክብ እንደነበር ይታወቃል። ያ ደግሞ ምናልባት ለጦርነቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ በአጭር ጊዜ ስኬታማ ለመሆኑ ትልቅ አስተዋጽዖ ማድረጉ አጠያያቂ አይሆንም። ታዲያ ያው ሕዝብ በምን ምክንያት ወደአመጽ ሊሄድና እንደተጠቀሰው ሠራዊቱን ሊወጋ ቻለ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት። ለዚኽ ሰበብ የሚሆኑ ሁለት ምክንያቶች አሉ ማለት ይቻላል። አንደኛው የጦርነቱ ሁለተኛ ምዕራፍ በአግባቡ አለመካሄዱ እና የድርጅቱ ዋናዋና መሪዎች እና ተፈላጊ ተባባሪዎቻቸ

በቁጥጥር ሥር ሣይውሉ የጦርነቱ ጊዜ መራዘሙ ለድርጅቱ (ትሕነግ) አፈርልሶ ለመነሣት ፋታ ስለሰጠ፤ በተጨማሪም ለ፵፭ ዓመታት በዘረጋቸው መዋቅሮች አማካይነት በአገርውስጥም በውጭም ካደረገው ያላሰለሰ እና የተቀናበረ የቅስቀሳ (የፕሮፓጋንዳ) ዘመቻ አንጻር በመንግሥት በኩል እጅግ በሚሣዝን መልኩ ድርጅቱ (ትሕነግ) ሌላው ቀርቶ በሰሜን ዕዝ ጦር አባላት ላይም ሆነ በማይካድራ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስለፈጸማቸው ዘግናኝ የወንጀል ድርጊቶች የነበሩትን መረጃዎች ዓለም እንዲያውቅ የማድረግ የተቀናበረ የማጋለጥ ሥራ አለመሠራቱ እንኳን በጦርነት መኻል ፍዳውን እያየ ያለ የትግራይ ሕዝብ የውጭው ዓለም እውነቱን ለማወቅ ያልቻለበት ሁኔታ ስለነበር፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሙሉ ተስፋውን እንዳይጥል አድርጎታል። ሁለተኛው እና ዋነኛው ግን የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ መግባቱ እና በሕዝብ ላይ በሠፊው የተዘገቡ የግፍ ተግባራት በመፈጸማቸው ነው ማለት ይቻላል።

ከውሣኔው በፊት ሕዝብ ይኽን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደበትን ምክንያት ለማወቅ እና ለመረዳት የተደረጉ ሙከራዎች ነበሩ? ክስተቱ በአንዳንድ የተወሰኑ አካባቢዎች ከሆነስ ከመንግሥት ጎን ተሰልፈው ወይም ገለልተኛ አቋም የነበራቸው፣ እንዲሁም ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሄዱ ዜጎች በተለያዩ የመንግሥትም ሆነ የግል መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው የሚሠሩ፣ በትምሕርት ተቋማት ውስጥ ባሉ አስተማሪዎች እና ተማሪዎች ላይ በዚኽ ውሣኔ ምክንያት በትሕነግ ሊደርስባቸው ስለሚችለው ሰቆቃ ታስቧል? በእነዚኽ ዜጎች ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ያለበት ኃላፊነትስ? የሚሉት እና ሌሎች ተዛማች ጉዳዮች ምላሽ ያስፈልጋቸዋል።

ብዙ ወገኖች የኤርትራ ወታደሮች መግባታቸውን እና በጦርነት ተሣታፊ መሆናቸውን አጠንክረው በመደገፍ ያለምንም ማጠየቂያ መከራከራቸው ይታወቃል። አዎ፣ ትሕነግ ለትግራይ ሕዝብ ደጀን ሆኖ በኖረው የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ጦር ላይ አሣፋሪ የክህደት ወንጀል ሲፈጽም፣ በራሣቸው ወገን በአሰቃቂ ሁኔታ ተወግተው እና ተዋርደው ወደ ኤርትራ ለሄዱ ወታደሮቻችን በጣም የሚመሰገን አቀባበል በማድረግ ተመልሰው ለማጥቃት እንዲችሉ እረድቷል። ያን በጎ ተግባር መዋሉ ጠቀሜታው የጋራ መሆኑ ባያጠያይቅም ውለታው ግን ሊዘነጋ አይገባም። ያ በጎ ተግባር እንዳለ ሆኖ ግን፣ በተለይ በትሕነግ ቁርሾ ያለው የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ መግባት የሚኖረው ችግር በሚገባ የተጤነ አይመስልም። የኤርትራ ጦር ያለመንግሥት ቀጥታ ጥያቄ ከሆነ የገባው ሉዓላዊነትን የተጋፋ ግልጥ ወረራ ይሆናል። ድንበር ጥሰው የገቡት በመንግሥት ጥያቄ ከሆነ ግን በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ ተፈጸሙ ለተባሉት የወንጀል ድርጊቶች ተጠያቂው የኤርትራ መንግሥት ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ጭምር ይሆናል። ምክንያቱም የኤርትራ ጦር (ምንምያኽል እንደወገን ተደርጎ ቢቆጠር)፣ ዞሮዞሮ የውጭ ጦር ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን ጦር ድጋፍ ከፈለገ አንድም ድንበር ሣይሻገር የተወሰኑ እርዳታዎችን እንዲሰጥ ማድረግ፣ መግባት ካለበት ግን እንደማንኛውም የውጭ እርዳታ ሰጪ የታጠቀ አካል ከአገባቡ ጀምሮ መንቀሳቀስ የሚችልባቸው ቀጥናዎች፣ ማድረግ ስለሚችለው እና ስለማይገባው (Rules of Engagement) እንዲሁም የሚቆይበት የጊዜ ገደብ፣ ወዘተ. ዝርዝር ውል ሊኖር ይገባል። ይኸ ነበር ወይ? ግልጥ አይደለም። ደርስዋል ተብለው ከተዘገቡት ወንጀሎች መረዳት የሚቻለው ከንብረት ዘረፋ ጀምሮ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ነፃእርምጃ እስከመውሰድ የደረሱ ግፎች ተፈጽመዋል። ጨርሶ ተቀባይነት የሌላቸው እኒኽ ድርጊቶች ትሕነግን በማይፈልጉ ወገኖች ጭምር ከፍተኛ ቅሬታን እንደፈጠሩ እና መንግሥቴ የሚለው ክፍል ሊከላከልለት እንደማይችል፣ አልፎም እንደማይፈልግ እየቆጠረ ወደአመጽ እንዲያመራ ተቀዳሚ አስተዋጽዖ እና ገፊምክንያቶች ሆነዋል ማለት ይቻላል። ትግራይ በገባው የኤርትራ ጦር ተፈጽመዋል በተባሉ ተቀባይነት የሌላቸው ተግባራት ምክንያት በሕዝብ ዘንድ ብቻ ሣይሆን አንዳንድ የኢትዮጵያ ሠራዊት ክፍሎችን እንቅስቃሴ እስከመቆጣጠር የደረሰ እብሪት አሳይተዋል መባሉ በሠራዊታችን ዘንድ ቅሬታን መፍጠሩ እና ‘በባድመ ጦርነት ባቸነፍነው ሠራዊት ተዋረድን’ የሚል ቁጭትአዘል ተገቢ ቅሬታ ማሳደሩ ይነገራል። በተጨማሪም የኤርትራን ጦር መግባት የተቃወሙ አገሮች፣ በተለይም አሜሪካ እና እንግሊዝ፣ (በአብዛኛው ከኤርትራ መንግሥት ጋር ባላቸው ቁርሾ ይመስላል) ጦሯን እንድታስወጣ የከረረ አቋም ይዘው በኢትዮጵያ ላይ ያልተጠበቀ ጫና እንዲያደርጉ ሰበብ እንደሆነም ይታወቃል።

. ሁለተኛው ሁለትዘርፍ ያለው ምክንያት ትሕነግ ሰለተመታ እና በጣም ስለተዳከመ በአገር ላይ የሚያሰጋ አይደለም የሚለው አንድም ከመጀመሪያው ምክንያትም ሆነ የመንግሥት ጦር ትግራይን ለቅቆ ሲወጣ እንኳን መዋቅራቱ በሙሉ ያልፈራረሱበት እና የውጭ እርዳታን የማግኘት ዕድል ያልነጠፈበት ትሕነግ ቀርቶ ለአዲስ ጀማሪም ቢሆን ቢያንስ ችግር ለመፍጠር እንደሚያስችለው አለማጤን ይሆናል። ጦሩን በአገር ላይ የበለጠ ሥጋት ባሉባቸው ቀጥናዎች ማዛወር አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ የሚለው አሣማኝ ቢሆንም፣ ያ የተሻለ ተመራጭ የሚሆነው ትግራይን ጠቅልሎ ለትሕነግ አስረክቦ እና ጀርባን ክፍት አድርጎ ባይሆን ይመረጥ ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የፋኖ እና የመንግስት ስምምነት - ለገሰ ወ/ሃና

. “አርሶአደሩ የእርሻ ወቅት እንዳያልፍበት” የሚለው ድክመትን ቢያሣይም ለሕዝብ መራብ ደንታ የሌለው ብቻ ሣይሆን ርሃብን የዓላማው ማስኪያ መሣሪያ አድርጎ የመጠቀም ልምድ ላለው ትሕነግ ሰበብ ላለመስጠት ስለሆነ ሻል ያለ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

. “በበረሃ ከሚገኙት መኻል በሰላማዊ መንገድ መደራደር የሚፈልጉ ስላሉ ለእነሱ ዕድል ለመስጠት” የሚለው ምክንያት ግን የማያሣምን ብቻ ሣይሆን የቅጥጥብ አባባል ሆኖ አገኘዋለሁ። እንዲያው ይሁን ቢባል እንኳ፣ ለመሆኑ እነዚኽ ሰላም ፈላጊ ናቸው የተባሉት በድርጅቱ አባላትም ይሁን በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ምን ያኽል ተቀባይነት አላቸው/ይኖራቸዋል?

ይኸ እውነት ከሆነስ ክልሉን ጠቅልሎ አስረክቦ ነወይ ድርድር የሚደረገው? በምን ዓይነት መተማመኛ? የማያሳምን ምክንያት ነው።

በመንግሥት የተወሰደ ይኽ የአንድጎንዮሽ (የተናጠል) የተኩስ አቁም እወጃ “የፖለቲካ ውሣኔ” እና “ስትራቴጅካዊ ማፈግፈግ” እንደሆነ፣ “ካስፈለገ በ፫ ሣምንታት ውስጥ ትግራይን መልሰን መያዝ እንችላለን” የሚሉ አባባሎች በአንዳንድ ባለሥልጣናት ሲነገሩ ይሰማል። ቀደምሲል እንደተጠቆመው ተኩስማቆም ማለት ይዞታን በሙሉ ሣይለቁ ለድርድር ዕድል ለመስጠት ሲባል ወይም ዓመትበዓል ለማክበር አብዛኛው በስምምነት የተኩስ ልውውጥ አለማድረግ ማለት ነው። ስትራቴጅካዊ ማፈግፈግ ከተፋላሚ ጋር የግድ ስምምነትን ሣይጠይቅ እና ውጊያም ሳይቆም በደንብ የታሰበበት እና የተሟላ ዝግጅት ተደርጎበት፣ አስቀድሞ መውጣት ያለባቸው ሰዎችም ሆኑ መሣሪያዎችና እና መገልገያዎች በተቻለ መጠን እንከን ሣይገጥማቸው እና በተጻራሪው እጅ የማይወድቁበት ሁኔታ ተረጋግጦ፣ ከአንድ የጦርነት ቀጠና ወደ ተሻለ የውጊያ ሥፍራ በመዛወር ጊዜ ገዝቶ ተጠናክሮ መልሶ ለማጥቃት ወይም በበቂ ለመከላከል ወይም የማያዋጣ ሲሆን ኪሣራን ለመቀነስ አንድን ይዞታ ለቅቆ መሄድ ሊሆን ይችላል።

አሁን በትግራይ የተደረገውን ሰዶማሳደድን የመረጠ እርምጃ ግን ተግድዶ ማፈግፈግ ነው ሊሆን የሚችለው። ይኽን ውሣኔ በውስጥም በውጭም ያሉ ሁኔታዎችን በአሉታዊ መልክ ሊቀየሩ መቻልን ያላገናዘበ እና አሁን የተቸናፊአቸናፊ እንዲሆን ዕድል የተሰጠው ትሕነግ በተለመደ አምባገነን ባኅሪው እና በተመሰከረለት ጭካኔው አይደግፉኝም የሚላቸውን ወገኖች እና መንግሥትን ደግፋችኋል በሚል ሰላማዊ ዜጎች ላይ በሚወስደው አረመኔኣዊ እርምጃ ምክንያት በመስጋትም ሆነ መንግሥት ዳግም ለሕይዎቴ ዋስትና አይሰጥኝም በሚል ድምዳሜ፣ ተስፋ የቆረጠው ወገን እንደባለፈው ጊዜ እንኳን በደስታ በዝምታም ሊቀበል የሚችልበት ሁኔታ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ለተወሰደው የአንድጎን የተኩስአቁም ውሣኔ አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ካልተወሰደ የሚከተሉትን ጦሶች ሊያስከትል ይችላል።

 • ጦሩን ከትግራይ ለማውጣት በምክንያትነት እንደቀረበው በአንዳንድ አካባቢዎች በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ከአርሶአደሮች መኻል በተሰገሰጉ የትሕነግ ታጣቂዎችም ሆነ ከዚኽ በላይ የተጠቀሱ በደሎች ስለደረሱባቸው በመንግሥት ላይ ተስፋ ቆርጠው ልባቸው በሸፈተ እና ቂም በቋጠሩ ዜጎች በሠራዊታችን አባላት ላይ በቀልአዘል ጥቃት ስለተፈጸመ መላውን የትግራይን ሕዝብ በጅምላ ‘ባወጣያውጣህ’ ብሎ አሸባሪ ተብሎ ለተሰየመ እና በጭካኔው ለተመሰከረለት ድርጅት (ትሕነግ) አሳልፎ መስጠት፣ አንድም የዜጎችን ደኅንነት ከአደጋ የመከላከል ግዴታን አለመወጣት ስለሚሆን ከዚኽ በኋላ በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖረው ያደርጋል።

 • ውሣኔው ማዕከላዊመንግሥት አገራዊ አንድነትን እና የሕዝብን ደኅንነት ለማስከበር ያለበትን ኃላፊነት መወጣት እንደማይችል የሚያሣይ ስለሚሆን፣ ለማፈንገጥ እና የራሣቸውን ‘አገር’ ለመመሥረት ለሚከጅሉ ክፍሎች ተመሣሣይ እርምጃ ለመውሰድ እና የሱን አርኣያ የሚከተሉ ብቅብቅ እንዲሉ ያደፋፍራል። ያ ዓይነት ሁኔታ በሚከሰትበት ውስጥ የሚኖረው ሕዝብም የትግራይን ሕዝብ ከትሕነግ ያልታደገ መንግሥት ለኔም ያው ይሆናል ከሚል እምነትማጣት የተነሳ ምርጫው አካባቢውን ለቆ በመውጣት ለጅምላ መፈናቀል መዳረግ፣ አለበለዚያም እመራሃለሁ ከሚለው የአካባቢ ባለጉልበት ጎን እንዲቆም መገደድ ይሆናል። ድርጊቱም በሌላ አካባቢ ለሚኖሩ እና ለተመሣሣይ ሁኔታ ለሚዳረጉ ወገኖች መጥፎ አርኣያ ይሆናል።

 • ይኽ ውሣኔ በከፍተኛ መስዋዕት ከሥልጣን እና ከትግራይ ሕዝብ ጫንቃ የተወገደው ትሕነግ “ተቀብሯል፣ ዱቄት ሆኗል” ከተባለበት አዘቅት ተነስቶ በጦርነት ያጣውን ሥልጣን ዳግም ሕይዎት እንዲዘራ እና የታሰሩ የአመራር አባላቱን ሣይቀር ለማስለቀቅ የሚችል የበለጠ ተጽዕኖፈጣሪ ሊሆን የሚችልበትን ዕድል ሊፈጥርለት ይችላል።

 • የመጠናከር ዕድል ካገኘ፣ ጦርነቱን ከትግራይ ውጭ ለማሸጋገር አጋጣሚውን ይፈጥርለታል።
 • በተፈጠረው ጊዚያዊ ክፍተት የአካባቢውን ቀጠና ፖለቲካዊ ይዞታ እና የኃይልአሠላለፍ ለመቀየር እና ጥቅማችንን ያስከብርልናል ብለው ባሰቡት መልክ ለመቅረጽ የሚፈልጉ ኃያላን የውስጥ አንድነታችንን አሳጥተው ለመከፋፍል ተኝተው ከማያውቁ በቅርብ ካሉ ጠላቶቻችን ጋር በማበር፣ ትሕነግን በመሣሪያነት ለመጠቀም አስፈላጊውን እርዳታ በመለገስ ሊያጥናክሩት ይችላሉ። ከሞላጎድል መንግሥት በፈቃዱ ለጊዜውም እንኳ ቢሆን ከቀጥተኛ ቁጥጥሩ ውጭ እንዲሆን ባደረገው በዚኽ ክልል በእርዳታ ስም ይሁን በሌሎች የተለያዩ መንገዶች እና ዘዴዎች ጣልቃ ሊገቡ፣ የአየር በረራ እስከመከልከል እና ከውጭአገር የሚያገኛኝ የተለየ መተላለፊያ በር እንዲኖር በማድረግ የበለጠ ችግር እንዲፈጥሩ መልካም አጋጣሚ አድርገው ይጠቀሙበታል። የትሕነግ ድርጅታዊ ተፈጥሮ እና በአሁኑ ጊዜ ተስፋቸው የመነመነ የመሪዎቹ ደግሞ ባዕዳንን ጎትቶ ለማስገባት ችግር እንደማይሆንባቸው አጠያያቂ አይሆንም ማለት ይቻላል።

 • በአንድ መልኩ ይሁን በሌላ ይኽ ተፈጻሚ ከሆነ ትግራይ ከማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ የመሆን ሁኔታን ሊፈጥር እና ሌሎችም የእነሱን መንገድ ለመከተል እንደሚከጅሉ አያጠራጥርም። በተለይም በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ ክልሎች የሚገኙባት አገራችን የትሕነግን ዓይነት አመጽ ቢካሄድ እና በሠራዊታችን ላይ ተመሣሣይ ጥቃት ቢፈጸም ክልሉን እየለቀቁ አካባቢውን እንወክላለን ለሚሉ ክፍሎች ትቶ መውጣት መፍትኄ ሆኖ ከተወሰደ፣ ኢትዮጵያችን እንዴት አገር ሆና ትቀጥላለች ብሎ ማሰብ ይቻላል? አጉልኛ ነው።

 • በዚኽ እኩይ ሴራ ከእኛው እኩል የጥቃት ዒላማ የሚሆነው የኤርትራ መንግሥት እንደሚሆን ያንኑ ያኽል የሚያጠያይቅ አይሆንም። አንዳንድ አገሮች በኤርትራ ገዥዎች ላይ ቀደምሲል ካላቸው በጎያልሆነ አመለካከት በተጨማሪ አሁን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመሆን በትግራይ ጦርነት ባደረገው ተሣትፎ እና በሕዝብ ላይ ተፈጽሟል በተባለው የሚያስጠይቅ ተግባር ደስተኛ ካለመሆናቸው በተጨማሪ በአፍሪቃ ቀንድ ያለውን የኃይልአሠላለፍ ለመቀየር ላላቸው አሳብ እንደአደፍራሽ ስለሚታዩ፣ ከትሕነግ ጋር ያላቸውን የከረረ ጠላትነት በመጠቀም የመንግሥት ለውጥ እንዲኖር ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። ያ ከተሣካላቸው አንድም የትሕነግ ቅጅ የሆነ የወኪል መንግሥት ይቋቋማል፣ ካልተሣካም ኤርትራ ያልተረጋጋች የመሆን ዕጣ ሊገጥማት እና ምናልባትም ለድንበርተሻጋሪ ጽንፈኞች መነሃሪያነት ተጋላጭ ሊያርጋት ይችላል። ሁለቱም ለኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን ለቀጠናው ጭምር ከፍተኛ አደጋ ይሆናል።

 • በዚኽ ውሣኔ ምክንያት አልቆለታል የተባለ ይኽ ድርጅት ‘ማረኳቸው’ ባላቸው የሠራዊት አባላት ላይ በሚፈጽመው አረመኔኣዊ ተግባርም ሆነ በአንድመልኩይሁንበሌላ መልሶ የማንሠራራት እና ጥቃት የመፈጸም አቅም ከፈጠረ፣ ብዙ መስዋዕት በከፈለው ሠራዊታችን (ከአዛዥ እስከ ታችኛው እርከን ባሉት አባላት) ላይ የሚያሳድረው የሥነልቦና ስብራት የምር ሊያሳስበን ይገባል። በየደረጃው በደንብ የታሰበበት ሙያዊ ምክክር ሊደረግ ይገባል።

አንዳንድ ወገኖች ትሕነግ በኢትዮጵያ እና በሕዝቧ ላይ በፈጸመው በደል በመማረር ሊሆን ይችላል የትግራይን ሠፊ ሕዝብ ድርጅቱን በሚያዩበት ደረጃ በመመልከት “ከፈለጉ ይገንጠሉ” እስከማለት መድረሣቸው ይደመጣል። ያን ዓይነት በጥሬ ስሜት የሚሰነዘር አባባል የትግራይን ሕዝብ ትክክለኛ ገጽታ የማያንፀባርቅ እና ባልፉት ፵፮ ዓመታት በዚኽ አፋኝ ድርጅት የደረሰበትን መጠነሠፊ ስቃይ ያላገናዘበ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ይኽ ዓይነቱ ደፈናዊ ፍረጃ ማንም ፀረአንድነት እና ፀረሕዝብ ቡድን በሚፈጽመው ወንጀል በመማረር በተለያዩ ምክንያቶች እወክለዋለሁ ያለውን የአገር ክፍል ‘ይዞ ይሂድ’ የሚል ፍርደገምድል ብይን ስለሚሆን ትክክልም ተገቢም ያልሆነ እና ኃላፊነት የጎደለው መሆኑ ሊታወቅ እና ሊታረም ይገባል።

በአብዛኛው በመንግሥት ድክመት ምክንያት በደረሱ ከፍተኛ የውጭ ጫናዎች እና ጊዚያዊ የውስጥ ችግሮች ምክንያት የተወሰደ የሩቁን ያላየ ይኽ ውሣኔ ማዕከላዊ መንግሥትን ከክልሎች ጋር ወደደምአፋሳሽ ጦርነት የሚወስድ እና በእጅጉ የሚያዳክም ብቻ ሣይሆን የአገርን አንድነት ለከፍተኛ አደጋ የሚያጋልጥ አደገኛ እርምጃ ነው ማለት ይቻላል። ይሁንናም፣ በተለይ አገራችን ባለችበት እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ኢትዮጵያችን መንግሥትአልባ እንዳትሆን ብቻ ሣይሆን መንግሥት ደካማ እንዳይሆን የሚቻለው ድጋፍ ሊሰጠው ይገባል። ያ ግን እንዲሁ በጥሬው የሚሰጥ ሣይሆን መንግሥት ያሉበትን ድክመቶች ተረድቶ ስህተቶቹን እንዲያርም አስፈላጊው ጉትጎታ እየተደረገ ሊሆን ያስፈልጋል። አንዳንድ መንግሥታት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉም ሆነ በሠሩት ስህተት ከተጠያቂነት ለመሸሽ በማሰብ የሕዝብን አስተሳስብ በፈለጉት አቅጣጫ ለመውሰድ ያሉ ቀውሶች እንዲቀጥሉ ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ቀውሶችንም እንደሚፈለፍሉ ይታወቃል። ቁምነገሩ የአገር እና የሕዝብ ዕጣፈንታ በጊዜው ሥልጣን ላይ ካለ መንግሥት ጋር ባለን ቀረቤታ ይሁን ቅሬታ የሚመዘን አይደለም ሊሆንም አይገባም። በኢትዮጵያችን ላይ የተጋረጡ ኅልውናተፈታታኝ ችግሮችን ለማስወገድ ሁላችንም የየአቅማችን ልናደርግ ይገባል። ወቅቱ በአልባሌ ጊዜ የሚጠፋበት ወይም ተስፋ ቆርጦ የሚቆዘምበት ሣይሆን ኢትዮጵያ ለአገርወዳድ ልጆቿ ሁሉ አገራዊጥሪ እንዳቀረበች እና ብሔራዊተልዕኮ እንደሰጠች ተደርጎ ሊቆጠር ይገባል። ይኽን ፈታኝ ሁኔታው ከዚኽ አሳንሰን ልናይ አንችልም።

አገራችን ከምትገኝበት የተሸረሸረ የውስጥ ይዞታ እና ከሩቅም ከቅርብም እያንዣበበ ካለ ርብርብ፣ ይኽ በአብዛኛው ከአመራር ድክመት እና የቅደምተከተል መዛባት የመጣ ውሣኔ የሚያስከትለውን ጦስ የምር ተገንዝበን ካልተረባረብን፣ ትግራይ የመጀመሪያ እንጅ የመጨረሻ አትሆንም።

ስለሆነም፤

መንግሥት ሣይዘገይ እና በ‘ካፍርኩ አይመልሰኝ’ ድርቅና ጊዜ ሳያባክን ነገሮች አገራችንን ጨርሶ መመለሻ ወደሌለው አዘቅት ሣይወስዱ የሚከተሉትን አስቸኳይ የእርምት እርምጃዎች ሊወስድ ይገባል።

 • ይኽ የአንድዮሽ የተኩስ ማቆም ውሣኔ የአጭርጊዜ ገደብ እንዲኖረው ማድረግ፤
 • ሁኔታዎች ለአፈጻጸም አስቸጋሪ ቢያደርጉትም በትሕነግ ምክንያት የትግራይ ሕዝብ ለረሃብ እና ለችግር እንዳይዳረግ በመንግሥት በኩል አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሰው መንገዶች እና ዘዴዎችን መፈለግ፤
 • ትሕነግ ከይዞታው ወጥቶ መልሶ እንዳያንሠራራ እና በሌሎች አካባቢዎች የውክልና ጦርነት እንዳይጭር ምንም ዓይነት መፋዘዝ ሣይኖር እና ጊዜ ሳይባክን ሰላማዊ ዜጎችን በማይጎዳ መልክ ቀጥታ ጥቃቶችን ፋታ ሣይሰጡ መቀጠል፤

 • ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቁልፍ ቦታዎች ሲቻል በአካል፣ ካልሆነም በተለያዩ መንገዶች መቆጣጠር፤
 • እያንዳንዷ ቀን ለትሕነግ እና ለባዕዳን ደጋፊዎቹ የትግራይንም ሆነ የቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለበለጠ አደጋ እና ቀውስ ለመዳረግ ይኽንን ክፍተት ለመጠቀም እንደሚጣደፉ ግንዛቤ ሊወሰድ እና ምንም ጊዜ ሣይባክን በሁሉም ረገድ ቅድሚያን አሣልፎ ላልመስጠት የሚያስችሉ እና የአጥቂነት ይዞታን የሚያረጋግጡ በቅጡ የታሰበባቸው እቅዶችን ተግባራዊ ማድረግ፤

 • በምንም ምክንያት እና ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ላይ ያለውን ፌዴራላዊ ግዴታ አሳንሶም ሆነ አሳልፎ ሊሰጥ ወይም ያንን ግዴታውን ሊሸረሽሩ የሚችሉ ጥያቄዎችን አለመቀበል እና አለማስተናገድ፤
 • በምንም ምክንያት የውጭ እርዳታ ከኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ውጭ ለትሕነግ አለመድረሱን ማረጋገጥ፣
 • ከሙስና የፀዳ እና ብቃት ያላቸው ልዩልዩ ባለሙያዎችን ያቀፈ የቁጥጥር አካል በማቋቋም በእርዳታ ስም ለትግራይ ወገናችን ተብለው ከውጭ አገር የሚላኩ የምግብ እና ሌሎች ግባኣቶች በተገቢና በሥርዓት ሣይፈተሹ እና ሳይመረመሩ እንዳያልፉ ማድረግ፤

 • ሁኔታዎች ተቀይረው ፌዴራል መንግሥት በትግራይ ላይ ያለውን ኃላፊነት መልሶ ማረጋገጥ እስከሚችል ድረስ፣ ከትሕነግ አፈና ለመውጣት ለሚፈልጉ ዜጎች ለደኅንነታቸው ዋስትና የሚያገኙባቸው ቦታዎች በአቅራቢያ ክልሎች እንዲዘጋጁ ማድረግ፤

 • መንግሥት በውጭ ግንኙነት በኩል እስካሁን ያሣየውን አሣፋሪ ድክመት ለማስወገድ አዲስ ቅኝት ሊይዝ፣ ተግባራዊእቅዶች (ፖሊሲዎች) እና የአፈጻጸም መመሪያዎች ሊኖረው፣ እንዲሁም እነኝኽን ተግባር ላይ የሚያውሉ ተቀዳሚ ተኣማኒነታቸው ለኢትዮጵያ ብቻ የሆኑ በሙያው ብቃት ያላቸው ተወካዮችን (ዲፕሎማቶችን) ማሠማራት፤

 • ትሕነግአዊ አመለካከት እና እምነት ያላቸው፣ የእሱንም ፀረአገር ፈለግ የሚከተሉ እና ሁኔታውን አመቺ እንደሆነ በመገመት እኩይ ዓላማቸውን ለማሣካት የተናበበ ጥቃት ከመፈጸም ወደኋላ የማይሉ ኃይሎችን በጥብቅ መከታተል እና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ሙሉ ዝግጅት መኖሩን ማረጋገጥ፤

 • ሕዝብ አገሩ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ (ያላስፈላጊ መረበሽ እና ሥጋትን በማያሣድር መልክ) የሥነልቦና ዝግጅት እንዲኖረው ማድረግ፤
 • በየአካባቢው የሐይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ከተለያዩ የማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ስለ ሰላምና አንድነት ነፃ ምክክሮች እንዲያደርጉ፣ ያሉ ብሶቶችን ለመረዳት እና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ መዋቅሮች ጋር ችግሮች እግርበግር እንዲፈቱ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤

 • በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሁሉ አንድወጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሊኖራቸው እንደማይችል ይታወቃል። አገራችን አሁን ባለችበት ፈታኝ ወቅት ሕዝብ እንደአንድ ሰው በጋራ ሊቆም እና ሁሉም የየአቅሙን እንዲያደርግ ዕድል ሊሰጠው ይገባል። ስለሆነም፣ መንግሥት ከያዘው እና ከሚያራምደው የተለየ አሳብ ስላላቸው ብቻ የታሰሩ ዜጎችን መፍታት፤

 • ቀጣዩ የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ከመሰየሙ በፊት በክብርት ፕሬዝደንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የበላይ ሰብሳቢነት የሚመራ በምርጫ የተሣተፉም ሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች መሣተፍ ያልቻሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሙያና የማኅብራዊ ስብስቦች፣ የሐይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች፣ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የቀድሞ ሠራዊት አባላት፣ በአገርውስጥም በውጭም የሚገኙ ምሑራን፣ ወዘተተወካዮች የሚገኙበት አገራዊ የሰላምና የአንድነት ምክክር ጉባዔ እንዲጠራ እና በአገራዊ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ለብሔራዊ መግባባት ፈርቀዳጅ ውይይት ማድረግ፤

 • መንግሥት ምናልባትም በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት የሚኖረውን የሁኔታ ለውጥ በመገምገሞ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አገራዊ የተጠንቀቅ ጥሪ (ቅድመአገራዊ የክትት ጥሪ) በማቅረብ ሙሉ እና ተቀዳሚ ትኩረቱን ሰላም እና መረጋጋትን በማስፈን እና አገራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ላይ ሊያደርግ፤ ያስፈልጋል።
ተጨማሪ ያንብቡ:  ሌሊቱን የ13 የአጋዚ ወታደሮች አስከሬን ወደ አዲስ ዘመን ተወሰደ | በምስራቅ ጎጃም የሚኒሻ ኃላፊው ቤት ላይ እርምጃ ተወሰደ

ክቡራት እና ክቡራን ወገን ኢትዮጵያውያን፤

አንዳንድ ወገኖች የዚኽን የተናጠል የተኩስ ማቆም ውሣኔ ክብደት ከአሳማኝ ምክንያታዊ አግባብነቱ፣ በአገር ላይ ከሚያስከትለው ዘለቄታዊ ሳንካ ወይም ጥቅም እና ከአጠቃላይ አንደምታው አኳያ በገለልተኛ መንፈስ ጥሞናዊ ግምገማ በማድረግ ድምዳሜ ላይ የደረሱ ቢኖሩም፣ አብዛኛው ግን በዚያ መልክ ሣይሆን በተለይ “ከለውጡ” ወዲኽ ለመንግሥት ካላቸው ደፈናዊ ድጋፍም ይሁን አሉታዊ አመለካከት ላይ የተመሠረተ ሆኖ ይገኛል። ከዚኽ አባዜ መላቀቅ ካልቻልን እና ዋነኛ እና ተቀዳሚ ተኣማኒነታችንን ለጋራ አገራችን በማድረግ ቢያንስ በሌላው ጎራ ከተሠለፈው ባልተናነሰ ቁርጠኝነት፣ የዓላማ ጽናት እና አንድነት ኢትዮጵያችን እና ሕዝቧ ላይ የተደቀኑ ኅልውናተፈታታኝ ችግሮችን ለመመከት ጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ሳናተኩር በሙሉ ወኔ መሠለፍ ካልቻልን በየጊዜው በሚደርሱ እና እየበረከቱ በሚሄዱ አሳዛኝ ክስተቶች እሮሮ በማሰማትም ይሁን በቀላሉ ተስፋ በመቁረጥ፣ ተጠያቂው ላይ ባዶ እርግማን በማዥጎድጎድም ሆነ ሌላው ይሠራዋል ብሎ በመዘናጋት መፍትኄ ሊገኝ አይችልም። አገርን እና ሕዝብን እንታደግ ካልን ያን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ይሆናል። በተለይም የመንግሥት ኃላፊነት ያለባቸው ወገኖች የአገር እና የሕዝብ ጉዳይ ለእነሱ ብቻ የሚተዉ የግል ጥሪት ሣይሆን የዜጎች ሁሉ የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ተረድተው በግድፈቶች ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችንም ሆነ የሚቀርቡ አሳቦችን በቀና መንፈስ ማስተናገድ አስፈላጊ መሆኑን ቢረዱ መልካም ይሆናል።

እንደ አንድ ተራ አገርውዳድ ዜጋ በአገሬ ምንጊዜም ተስፋ ቆርጨ አላውቅም፣ ወደፊትም እንዲሁ። ትግራይን ለትሕነግ ያስረከበ የዚኽ ውሣኔ ጠንቅ የበለጠ ባለብዙዘርፍ መስዋዕትነትን የሚያስከፍል ስለሚሆን ኢትዮጵያችንን በምናውቃት እና እንድትሆንልን በምንፈልጋት መልክ አንድንቷ የተከበረ፣ ሰላሟ የተረጋገጠ፣ የበለጸገች እና ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሣትሆን የተለየ ቅርጽ እና ይዞታ ያላት የማናውቃት አዲስ አገር ሊያደርጋት እንዳይችል ሥጋት አለኝ። ስለሆነም ነው ይኽን በመንግሥት የተወሰደ የተዛነፈ እና መዘዘብዙ ውሣኔ የሚቀለብስ በደንብ የታሰበበት አስቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል የምለው።

አሁን የተከሰተውን ሁኔታ ሳስብ እና “መልሶ መያዝ” የሚለውን ስሰማ፣ ማድረግ ጨርሶ አይቻልም ባይባልም፣ የታሰረን አደገኛ ወንጀኛ ፍትቶ አፋልጉኝ እንደማለት ወይም ቁልፉን ከውስጥ ትቶ የተዘጋን በር ከውጭ ሆኖ ክፈቱልኝ የሚል አድማጭያጣ ተማጽኖ ሆኖ ይታየኛል፤ ምናልባትም ኢትዮጵያችን በትሕነግ መሠሪነት ኤርትራን እንድታጣ እንደተደረገው፣ ቅደምተከተሉ በተዘበራረቀባቸው፣ የአገር ጉዳይ ድርጅታቸውን ብቻ የሚመለከት የሚመስላቸው እና እነሱ ካሰቡት ውጭ ምንም ዓይነት ምክር የማይሰሙት ባለሥልጣኖች በሚወስዱት የተዛባ ውሣኔ ትግራይንም እንዳታጣ ያጠራጥራል።

ለአገራችን አጠቃላይ አደገኛ የውጥረት ሁኔታ መፍትኄ ለማስገኘት በቅድሚያ የተደቀኑትን ችግሮች ውስብስብነት፣ ስፋት እና ጥልቀት በጥሞና መረዳት ያስፈልጋል። በመቀጠል ዘለቄታዊነት ያለው መፍትኄ ለማስገኘት ምን እንደሚጠይቅ እና እንደኅብረተሰብም እንደ ዜጋም ምን እንደሚጠበቅብን ጠንቅቆ ማወቅን፣ በተግባር ለመተርጎምም ቁርጠኝነት ሊኖረን ይገባል። የሩቁን አይተን ከሌላው ሣይሆን በቅድሚያ ከየግላችን የሚጠበቅብንን ለመወጣት ካልቻልን፣ እንዲሁ በየጊዜው በሚደርሱት ላይ ብቻ ከተጠመድን ችግሮች አዳዲስ ችግሮችን እየወለዱ አገራችንን መመለሻ ወደሌለው አዘቅት ውስጥ ለማስገባት እንደወሰን ይቆጠራል። ያልፉትን ሰላሣ ዓመታት ብናይ እንኳ የተረጋጋ የሥርዓት ሽግግር ማድረግ የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች ብቅ እያሉ እንዲከስሙ ሆኗል። ለዚኽ አንዱ ምክንያት ዋና ትኩረታችን የምንፈልገውን ሥርዓት እውን ለማድረግ ድርሻችንን በመወጣቱ ላይ ሣይሆን በሥራው የምንጠላውን ገዥክፍል በማስወገዱ ላይ መሆኑ እና መወገዱን ለአዲስ ሥርዓት ግንባታ መነሻ አድርጎ በማየት ፋንታ በራሱ እንደ ግብ እየቆጠርን፣ ወርቃማውን የለውጥ ጊዜ የሄደውን በመርገም እና በመሄዱ እየጨፈርን፣ የመጣውን በባዶ ተስፋ በታጀለ ጊዚያዊ ደስታ በመነሁለል እነሆ አሁን ለምንገኝበት የአገራዊ ኅልውናእጦት ተዳርገናል።

አገራችን ለምትገኝበት ሁኔታ በተናጠል እና በተሰበጣጠረ አካሄድ መፍትኄ ማስገኘት ቢያንስ አስቸጋሪ ስለሚሆን አገራዊ የክተት አዋጅን የሚጠይቅ ነው። በዓለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን በያሉበት አኅጉር የቀወጢጊዜ አሰባሳቢ አካል በማቋቋም እና በአካባቢ ግብረኃይሎች አማካይነት ተደራጅተው በዲፕሎማሲው ረገድ ይሁን የገንዘብ እና የተለያዩ እርዳታዎችን በማሰባስብ ተጠያቂነት ባለው የኃላፊነት መንፈስ እና ሥርዓት ባለው ሁኔታ ተግተው ሊሠሩ ይገባል። በአገር ውስጥም በውጭም የምንገኝ ኢትዮጵያውያን በየፈርጁ በመደራጀት አገር ለመታደግን ዋነኛ ብሔራዊ ተልዕኮ አድርገን ብንንቀሳቀስ አሁን የተደቀኑ ችግሮችን ጉዳት ሣያደርሱ በብቃት ከመወጣት ባሻገር ኢትዮጵያችንን ወደሚገባት ከፍታ እንድትደርስ ማድረግ ይቻላል። ይኽ የሚረጋገጠው ግን ቅድሚያ ተኣማኒነታችንን እና እምነታችንን ከጎጥ እና ማንነት ከሚሉት አባዜ ከፍ ላለው የሁላችን የጋራ አኩሪ እሴት ለኢትዮጵያዊ ማንነት ስናደርግ ነው።

ኢትዮጵያውያን ምንምይሁን ምን፣ የተደቀነውን ፈተና የምንሽሽበትም ሆነ ተስፋ መቁረጥን የምናስተናግድበት ጊዜ ሣይሆን ጠላት እቤታቸው እስኪደርስ ቁጭብለው ሣይጠብቁ በባዶ እግራቸው ከጫፍጫፍ ተጉዘው፣ በራሣቸው ስንቅ እና ቅጠል እየበሉ አንጀታቸውን አሥረው በክቡር መስዋዕትነታቸው ይኽችን አኩሪ አገር ጠብቀው ያቆዩልን የአባቶቻችን/እናቶቻችን ልጆች ከሆንን አደራቸውን ሳንበላ፣ አገርንም የወላድ መካን እንዳልሆነች በተግባር ለማረጋገጥ በያለንበት የምንችለውን ብቻ ሣይሆን የሚጠብቅብንን በማድረግ ኢትዮጵያችንን ልንታደግ ይገባል። እንደ ኢትዮጵያውያን አሁን ቁርጠኛ ውሣኔ የምናደርግበት ጊዜ ነው። ያን የምናደርገው ለመንግሥት ብለን ወይም ለግል ጥቅም አይደለም፣ በኅሊና አስገዳጅነት ልንወጣው የሚገባ የዜግነት ግዴታ ስለሆነ እንጅ።

ኢትዮጵያችንን ምንጊዜም የማይለያት አምላክ በቸርነቱ ይታደግልን፣ ለእኛ ለልጆቿም ቀና ልቦና ያድለን!! ክብር ለአገራቸው አንድነት እና ለሕዝባቸው ልዕልና ውድ ሕይዎታቸውን መስዋዕት ላደረጉ ዜጎቿችን!!!

2 Comments

 1. በቅድሚያ ሃሳብህን በአማርኛ ማጋራትህ ማለፊያ ነው። ለሰሜን እዝ ከትግራይ መውጣት ምክንያት የሆኑ አያሌ ነገሮች ቢኖሩም ወያኔም ሆነ መንግስት የሚሏቸው ግን ግማሽ እውነቶች አለዚያም ሁሉም ውሸቶች ናቸው። ጠ/ሚሩ በመውጣቱ ሃሳብ ላይ ተከራክረንበት ወር በፈጀ እቅድና ፕላን ነው ትጥቅና የጦር መሳሪያችን ያወጣነው ብልዋል። ይህ ግን ክፍተት ያለበት አባባል ይመስላል። ለምሳሌ በትግራይ ውስጥ በተለያዪ የትምህርት ተቋም ያሉ መምህራንና ተማሪዎችን ለማስወጣት የተደረገ ነገር የለም። በተጨማሪም ከዘመናት በፊት ከቤታቸው እየታነቁ የአይናችሁ ቀለም አላማረንምና ውጡ የተባሉት ኤርትራዊያን አሁን ደግሞ ስደተኛ ሆነው በተጠለሉበት ለወያኔ አስረክቦ መውጣት ተገቢ አይደለም። አሁን የምንሰማው ሰቆቃ ብቻ ነው። ቢቻል ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልል ቢዛወሩ ኑሮ ከሞት ይተርፉ ነበር። ከዚህ ባሻገር ከልባቸው የወያኔን አስተዳደር ጠልተው ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ ይደግፉ የነበሩ የትግራይ ልጆችን ለአውሬ ጥሎ መውጣት እቅድን ሳይሆን ፍርጠጣን ነው የሚያሳየው። ለስሜን እዝ ከትግራይ መውጣት ግን ምክንያቱ በሚዲያ የተነገረን አይደለም። በእኔ እምነት የሚከተሉት ናቸው።
  1. የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ያላቋረጠ ጫና
  2. በትግራይ እናቶች ሳይቀሩ አፍቃሪ ወያኔ ሆነው ጦሩን በተናጠልም ሆነ በአናሳ ቡድን ሲያገኙት መግደል በማብዛታቸው
  3. ትጥቅና ስንቅ አቀባዪች የነበሩት የወያኔ ስንሰለቶች አሁንም በሰራዊቱ ላይ ጉዳት እንዲደርስ ከሚጠጣ ውሃ ጀምሮ በማዘግየትና ሰራዊቱ እንዲጎዳ በማድረጋቸው
  4. በትግራይ የጊዜአዊ አስተዳደር የተባሉት ሁሉም ባይሆኑ ይበልጡ ገዳይ፤ አፋኝ፤ ጠቋሚና አስጠቋሚ፤ መንገድ እንዲዘጋ የሚያዝና መልሶ የሚያስከፍት በሁለት ቢለዋ የሚበሉ ሽንኮች በመሆናቸው
  5. ግብጽና ሱዳን መጣንባችሁ ድንበራችሁ ውስጥ ነን እያሉ በማስፈራራታቸው ውጊያው አይቀሬ መሆኑ ስለታመነበት ነው።
  ከዚህ ውጭ ገበሬው እንዲያርስ፤ የትግራይ ህዝብ የጽሞና ጊዜ እንዲያገኝ፤ ከወያኔ መካከል መደራደር የሚሹ ስላሉ ወዘተ የሚለው ጡሩንባ ሁሉ ውሸት ነው። በጸረ ሽብርተኝነት የፈረጅከው ሃይል ጋር እንዴት ነው ቁጭ ብለህ የምትደራደረው? አብሮ ለዘመናት የኖረውን የሰሜን ጦር ታንክ በቁመናው የነዳ፤ ገደል የከተተ፤ እጅና እግራቸውን አስሮ በጥይት በመደብደብ ገድሎ አስከሬናቸው ዙሪያ የሚጨፍር የአውሬ ስብስብ ጋር በምን ሂሳብ ነው ለድርድር ቁጭ የሚባለው? የአኖሌን ሃውልት ለመከፋፈል የፓለቲካ ስራው ያቆመው ወያኔ የወታደር ሴቶችን ጡት መቁረጡ እንዴት ለኢትዮጵያ ህዝብ ይዋጥለታልና ነው ድርድር የሚባለው? ወያኔ ማለት ዲያብሎስ ማለት ነው። በማይካድራ፤ በወልቃይት፤ በራያ የተሰራው ግፍ ብቻ ዓለምን ያስለቅስ ነበር። ግን አሁን ምሾ የሚወረደው ለወያኔ ነው። የአለም ፍርድ ሸውራራና ወልጋዳ ለመሆኑ ኢራቅን፤ ሶሪያን፤ የመንን፤ ሊቢያን፤ አፍጋንስታንን እንዲሁም ያለፈን ታሪክ መርምሮ ማየት ነው። በቅርቡ አንድ መጽሃፍ እጄ ላይ ገባና ማንበብ ጀመርኩ። የመጽሃፉ አርዕስት Killing Hope by William Blum ይህን መጽሃፍ ረጋ ብሎ ላነበበ አሁን የአሜሪካ እሪታ ለትግራይ ህዝብ ሰላም አለመሆኑን ማየት ይቻላል። የሚነግሩንና የሚያደርጉት የተለዬ ነው። ሴራቸው ረቂቅ ነው። እኛ ግን መስሎን እንደ ጥንቸል በሜዳ እንፈረጥጣለን። እስቲ አሁን የሰሜን ጦር በስፍራው የለ ለምን አሁን አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ጉዳይ እንደሚያላዝኑ የሚያስረዳኝ አለ? ማንም አይኖርም። ተንኮላቸውና ሴራው ስር የሰደደ ነውና!
  ለትግራይ ህዝብ የሚበጀው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሆኖ በመከራም በደስታም አብሮ መኖር ነው። ያ ግን ወያኔ እያለ የማይታሰብ ጉዳይ ነው። የምዕራባዊያን ታላቁ ሴራ የአስመራውን መንግስት በወያኔ ማበራየት ነው። ይህም አይሆንም። ወዲ አፎም አፍሪቃ ውስጥ ከሚገኙ የሃገር መሪዎች ውስጥ ብቸኛ የዋሽንግተንን ሴራ የተረዳ ጀግና ነው። እንዴት እስከ ዛሬ ሳይገድሉት እንደቆዪ ፈጣሪ ይወቅ። ፕሬዝደንት ኢሳያስ በዚህ ጉዳይ ሊደነቅ ይገባዋል። የጠ/ሚ አብይ ህሳቤም ከዚሁ አይርቅም። አስተዋይና ለሃገሬ የሚል መሪ ሲነሳ ቶሎ ብሎ መቀንጠስ የምዕራባዊያን ሴራ ነው። እኛ የምንልህን ብቻ ፈጽም ነው የሚሉት። ወያኔ 27 ዓመት በስልጣን ላይ የኖረው የአሜሪካ ተላላኪ ስለነበር ነው። ሰርቆ ያበላቸው ነበር። ስንቶ ዶላር ነው በልዪ ልዪ ዘይቤ ተመልሶ ወደ አሜሪካ የገባው? የሚያስብ ጭንቅላት ፈትሾ እውነቱ ላይ መድረስ ይችላል።
  የሚገርመው የሰሜን እዝ ከወጣ በህዋላ ስመ ተራዶኦ ድርጅቶች ሰላም ጠፋ፤ ቢሮየን ልዘጋ ነው፤ ተዘረፍክ፤ ሰራተኛዬ ተገደለብኝ ወዘተ እያሉ ሲቀልድ መስማት ያስጠላኛል። ወያኔ ማለት ሞት ማለት ነው። ታሪካቸው መግደል፤ መሰወር፤መዝረፍ፤ ሃብት ወደ ውጭ ማሸሸት፤ በዘር የፓለቲካ ስካር ከወርቃማው ህዝብ ተወለድኩ ብሎ ማጓራት ናቸው። ለአንድ ህዝብና ሃገር ለኢትዮጵያ ድንበርና አንድነት አንድም ቀን አስበው አያውቅም። የትግራይ ህዝብ ሁሉ ወያኔ ነው። ለዛም ነው የሰሜንን ጦር ከህዋላም ከፊትም ሲወጋው የነበረ። የሰሜን ጦር በእነርሱ ሥር እስካለሆነ ድረስ ለትግራይ ህዝብ የሰሜን ጦር ወራሪ ሃይል ነው። እሺ እኮ አሁን ለቆ ወጣ አይደል። እስቲ ወያኔ የሚያደርግላችሁን ንገሩን። ማህል ሃገር በተንጣለለ ቤት ተቀምጠው (በተሰረቀ ሃብት የተገዛ) ልባቸው መቀሌ ሆኖ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የወያኔ ድጋፍ አቀባዪች እንዳሉ መረጃ አለ። ግን የአዲስ አበባ መንግስት ከጊንጥ ጋር እያደረ አሁንም በህዋላም ተነደፍክ ቢል ምን ጥቅም አለው? ትግራይን የናፈቀ ወደ ትግራይ ሂዶ ይኑር። ኢትዪጵያዊነትን የሚወድ ሁሉ ደግሞ ሃገሪቱ ክፍት ናት የትም ሂዶ ለመኖርና ለመስራት ይችላል። የ 45 ዓመቱ የጥላቻ መርዝ ግን በቀላሉ ትግራይንና ትግራዋይን ጥሎ ይወጣል ብሎ ማመን ጅልነት ነው። እብድ ብቻ ነው አማራንና ኤርትራን እንወጋለን በማለት ከተደበቀበት ጉድጓድ በወጣ በማግስቱ ቱልቱላ የሚነፋ። ወያኔ የእብዶች ጥርቅም ነው። ጭንቅላታቸው እንዳያስብ በሰው ልጆች ደም ተነክሯል፤ ሰክሯል።
  በመጨረሻም የተኩስ ማቆም አርገናል የሚለው የዶ/ር አብይ መንግስት ወታደሩ በስፍራው ከሌለ ማን ላይ ነው የሚተኩሰው? ከፈለግን ተመልሰን እንገባለን የሚባለውም ቧልት ቢረሳ መልካም ነው። እንደገና 100 ቢሊዪን ብር ለማባከን? ስንት የሚሰራበትን ነገር ከሞተው ወያኔ ጋር ለመፋለም። ተዋቸው ሀገራቸውን ያስተዳድሩ። ዝምታም እኮ መልስ ነው። ያው ሞሶሎኒን የኢጣሊያ ህዝብ ሆ ብሎ በአደባባይ ዘቅዝቆ እንደ ሰቀለው ስቃዪና መከራው ሲበዛበት የትግራይ ህዝብም የወያኔን ሽንኮች ከጀርባው ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ግባተ መሬታቸውን በመፈጸም አሽቀንጥሮ እንደሚጥላቸው አልጠራጠርም። በተረፈ የትግራይ ህዝብ በስሙ ሲነግድበት እያየ ከነጻነት ይልቅ አፍቃሪ ወያኔ ሆኖ የሰሜን እዝን መውጋቱ ዘግናኝ ነው። ስለሆነም በሃገራችን አባባል ” ሲኖሩ ልጥቅ ሲለዪ ምንጥቅ” ነውና ተለዪና ሃገር ሁኑ እንይ። ትግራይ ከሄደች ሌላውም ይከተላል የምትሉ ይሁና ዝም ብሎ ሁሌ ድሪቶ ይዞ ከመኖር ክልሎች ሁሉ የፈለጉትና ያርጉና መገዳደላችን እንቀጥላለን። የምናወቀው መግደልና መዝረፍ ነው። የኋላ ታሪካችንም የሚያመላክተው የሰላም ጊዜን ሳይሆን ሁሌ ፍትጊያን ነው። ያም ሆነ ይህ የሰሜን እዝ ከትግራይ ነቅሎ መውጣቱ ማለፊያ ውሳኔ ነው። ያወጣጥ ስልቱንና ጥሏቸው የወጣውን ስደተኞች፤ ተማሪዎችና ሌሎችንም ሳስብ ቅሬታ ይሰማኛል። በመዝጊያው ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ የሚባል ነገር የለም። ፓስተሩ፤ ቄሱ፤ ሼሁ፤ ጠንቋይና መተተኛው ሌባና አታላይ በሆነባት ምድር ላይ ፈጣሪ ዝም ካለ ቆየ። የችግሩ ፈጣሪዎች እኛው ነን። መፍትሄም ከእኛው ነው። ስለሆነም የእግዜሩን ስም በከንቱ ባናነሳ መልካም ነው። ወደ ሰማይ ማየት ትተን ራሳችን እንመልከት። በቃኝ!

 2. ተስፋ ነብስህ ተጨነቀች ተረጋጋ ብሮ የሻቢያ ነገር ዉስጥህ ካለም ቀን ይፈታዋል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.