የብልጽግና ሰልፍና የመለስ ለቅሶ (ከአሁንገና ዓለማየሁ) 

201927423 10220570568955987 2890336011685617116 n
201927423 10220570568955987 2890336011685617116 n

ብዙ ሰዎች ብልጽግና ኢትዮጵያን ወደ ትልቅ የሰው ቄራ ከቀየራት በኋላ ከበላተኛና ተጠቃሚ ካድሬ ውጪ ምን ዐይነት ሰዎች ናቸው ደግፈውት ሰልፍ የሚወጡት ብለው ግራ ይገባቸዋል። በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ከወጡ ብዙ ዘመናትን ያስቆጠሩና ተመላልስው ለመሄድ አጋጣሚው ያልነበራቸው ሰዎች።  ጠ/ሚ ዐቢይ አንድ ጊዜ ስለፖለቲካ ድርጅቶች ያደረጉት ንግግር ውስጥ መልሱን ማግኘት ይቻላል። ይህ ንግግራቸው የትኛው እንደነበር ለአንባቢ ለማስታወስ “ጠቅላላ ጉባኤ አድርጎ፣ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበርና ጸሐፊ ያልመረጠ ፓርቲ” በምርጫ አይወዳደርም ያሉበትና በአሁኑ ምርጫ ለምን ብልጽግና ፓርቲ ሕገወጥ እንደሆነ በአንደበታቸው የመሰከሩበት ንግግር ነው። ይህ የተጠቀሰው ክፍል በሚገኝበት ንግግራቸው ውስጥ ስለጀመርነው የብልጽግና ፓርቲ የድጋፍ ሰልፍ ርእስ አንዳንድ መረጃዎች የሚጠቁመን “የፖለቲካ ድርጅቶች እንግዶች ናችሁ፣ ከሀገር ከወጣችሁ ብዙ ጊዜ ሆኗችኋል፣ የሕዝቡ አኗኗርና ብዙ ነገሮች ተለዋውጠዋል” ያሉት እውነታ ነው። እውነታቸውን ነው፤ የሕዝቡ አኗኗር እጅግ ተለውጧል። በተለይም ከገዢው ፓርቲ ጋር የተቆራኘባቸው ስውር ገመዶች። የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቶ እጅግ ብዙ ሰው እያጣጣረ ቢሆንም ቀላል የማይባለው የሕብረተሰብ ክፍል ከተመዘገበው እለታዊ ገቢው ጋር እለታዊ ወጪው ሲተያይ ወጪው የትየለሌ ከፍታ አለው።

ለምን ሕዝቡ ለብልጽግና የድጋፍ ሰልፍ ግልብጥ ብሎ እንደሚወጣ በተለይ በብልጽግና ፖሊሲና አቋም ምክንያት እንደ አዲስ አበባ ክፍተኛ በደል የደረሰበት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ሽብርና የጥፋት ድግስ የተደገሰበት ሕዝብ ለምን እንዲህ ዓይነት የተገላቢጦሽ በሚመስል ተግባር ሊጠመድ እንደሚችል ለመረዳት የመለስን ለቅሶ ዞር ብሎ ማስታወስ ይጠቅማል። እዚህ ላይ የብልጽግና ሰልፍን መረጃ ቲቪ በጎንደርና አዲስ አበባ እንዳሳያቸው ዐይነቶች በአውቶቢስ ከከተማ ውጭ ተግዘው መጥተው እየተራገፉ ስለሚያደምቁት ሰዎች እያወራሁ አይደለም። ያ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣበት የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ በአበል ከገጠር አውቶቢሶች አሰማርቶ ገበሬዎችን እንደሚያመጣ እኔ ራሴ የዓይን ምስክር የነበርኩበት ልማዳቸው ነው። ያን ጊዜ አበሉ አሥራ አምስት ብር ነበር። ከዚህ በአውቶቢስ ተጭኖ ከከተማ ውጭ እየተጋዘ ሰልፍ ላይ ከሚራገፈው “የድጋፍ ሰልፍ” አድማቂ የተረፈው ላይ ነው ትኩረታችን።

የመለስ ለቅሶ ምን ይመስል ነበር?

በአጭሩ ድብልቅልቅ ያለ፣ የሞቀ፣ የደመቀ፣ በሀገራችን ላይ ከፈጸማቸው የክህደት ሥራዎች አኳያ ፈጽሞ የማይጠበቅ ነበር።

የኢትዮጵያን ውስጣዊ ሁኔታ ለማይገነዘብ፣ በደርግም ዘመን የነበሩትን የድጋፍ ሰልፎች ላልታዘበ፣ የኮሚኒስት ድርጅቶችን ሕዝብ ወደ አደባባይ የማስወጫ ብልሃቶች ለማያውቅ እጅግ ግራ የሚያጋባ ትእይንት ነበር። ሕዝቡ መለስን አምርሮ እንደሚጠላው፣ የሥርዐቱም የሀገር ክህደት፣ ጥላቻና ከፋፋይ ተንኮል ዋና ቁንጮና መገለጫ አድርጎ እንደሚመለከተው ነበር የሚታወቀው። ታድያ የድጋፍ ሰልፍስ እሺ መቼስ ይሁን፤ እንዴት ለቅሶና ዋይታ በዚህ መጠን የሀገር ጠላትና ግፈኛ ለተባለ ሰው ሊቀርብ ቻለ?

የእውነት በሐዘን የወጣ ሰው የለም ብንል እጅግ የተሳሳተ ማጠቃለያ ይሆናል። ምክንያቱም ብዙ የትግራይ ተወላጆች መለስን ለመብታቸው የታገለ፣ ጨቋኝ ደርግን የጣለ ባላውለታ አድርገው ይቆጥሩታል። ሌላም እጅግ ብዙ ትግራዋይ ያልሆነ የዚህ ፕሮፓጋንዳ ሰለባ ወጣት ነበር። በሌላ በኩል ቀላል የማይባል የትግራይ ተወላጅም ሥርዐቱ እየተገለገለበት እርሱም በአንጻራዊነት እየተጠቀመ የነበረ አለ። መለስ ከሞተ ዓለም ወይም ዓለሜ ትጨልማለች ብሎ የሚያስብ ማለት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ለምሳሌ እንደ ጎጃም ባሉ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የሕዝቡ የኑሮ ደረጃ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የፖለቲካ ንቃተ ኅሊና እጅግ ዝቅተኛ ስለነበር፣ መቀመቅ የሚከታቸው ፖሊሲ ቀርጾ በመዋቅር ሲያደቅቃቸው ለኖረው ሰው የሀገራችን መሪ ሞተ ብለው  ከልብ አዝነው ለቅሶ ወጥተዋልየደብረ ማርቆስን የመለስ ለቅሶ የተመለከተ ለባንዳው ቁንጮ ለመለስ ሳይሆን ለበላይ ዘለቀ የሚለቀስ ነበር የሚመስለው። ታድያ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ቦታዎችስ? በሀገር ላይ የፈጸመው ደባ ቢቀር መቼም መለስ ለአዲስ አበባ የነበረው ጥላቻና የፈጸመውን ግፍ የአዲስ አበባ ሰው አያውቅም አይባልም። የአዲስ አበባ ልጆች በአግአዚ ተቀጥቅጠዋል፣ ተጨፍጭፈዋል። የአዲስ አበባ ሕዝብ ቤት ተቸግሮ፣ የከተማው ነዋሪ ያልሆኑ ሰዎች ቤትና ኮንዶሚንየም ሲታደላቸው ኖሯል። የአዲስ አበባ ወጣት መዋቅራዊ በሆነ ማግለል ከሥራ ገበታ ተገፍቶ ከወያላና ተራ አስከባሪነት ያለፉ የሥራ እድሎችን ተነፍጓል። እነዚህም ሥራዎች ከ97 በኋላ በኢህአዴግ ለተደራጁ “አደገኛ ቦዘኔዎች” ተለይተው የተፈቀዱ ነበሩ። የአዲስ አበባ ልጅ በተወለደበት ከተማ የፖሊስና የሌላ ሥራዎችን እንኳን ለመሥራት አይችልም።  ይህና ሌላም ብዙ ግፍ ተሰርቶበት ሕዝቡ ግን ግልብጥ ብሎ ነው የወጣው።

እኔ በአጋጣሚ በዚያ ወቅት ኢትዮጵያ ነበርኩ። እርግጥ ከባሕላችን አንጻር መለስ እንኳን ሞተ ብሎ ከበሮ የሚደልቅ ባልጠብቅም እኔም እንደተሰማኝ ትልቅ እፎይታና የሆነ አውራ ጂኒ ከሀገሪቷ ትከሻ ላይ የተራገፈ ዓይነት የመገላገል ስሜት ነበር የጠበቅኩት። እጅግ ግራ ስለተጋባሁ ለቅሶ የሚሄዱትን ሰዎች ወደ ለቅሶው የሚሄዱበትን ምክንያት ለማወቅ ሙከራ አደርግ ነበር። ከጠየቅኳቸው ሰዎች መካከል አንዳንድ የሚገርሙ ታዳሚዎች እንደነበሩ የታዘብኩበት ነበር።

ቤተመንግሥቱን ዛሬ የከፈቱት ጊዜ ካላየሁት መቼ ላየው ነው? ያሉኝ አንድ አባት አጋጥመውኛል።

ሌላው ደግሞ “ኧረ እንኳን ሞተልኝ እንጂ ግብረ አበሮቹም ሁሉም አልቀው ደከመኝ ሳልል ሁሉንም ለቅሶ በደረስኳቸው!” የሚል ገራሚ መልስ ሰጥቶኛል።

በዋናነት ግን የመጀመሪያው የተረዳሁት ነገር የተወሰኑት ታዳሚዎች አበል እንደሚከፈላቸው ነው። ሰልፉ ላይ ለመቆም አርባ ብር ተሰጥቶናል ያሉኝ ብዙ ናቸው። የተቀሩትስ? ቀጥሎ የተረዳሁት የተወሰኑት ደግሞ በውለታ የታሠሩ መሆናቸውን ነው። ልዩ ጥቅም አግኝተዋል። ለምሳሌ አነስተኛና ጥቃቅን በሚባል አደረጃጀት ብድር ይወስዳሉ። ብድሩ በሥራና ንግድ ችሎታ ላይ ተመሥርቶ የማይሰጥ ስለሆነ አብዛኛው ተበዳሪ ከሣሪና ብድሩን መመለስ የማይችል ነው። ይህ ያልተከፈለ ብድር ፓርቲው ሲፈልግ የሚያወራርደው ውለታ ይሆናል ማለት ነው። ይህ ሂሳብ በድጋፍ ሰልፍ፣ በጆሮ ጠቢነትና በተለያየ መልኩ ተከፋይ የሚሆን ነው።  ሌላስ? ከዘጠና ሰባት ሽንፈት በኋላ ኢህአዴግ መለስ በቀረጸው ፖሊሲ አማካኝነት እጅግ ሰፊ ተጨማሪ የአባላት ምልመላ አድርጓል። ያገኘውን ሁሉ አባል ለማድረግ ሞክሯል። አባላት ደግሞ በድርጅት ተጠርንፈው ከገንዘብ መዋጮ ጀምሮ፣ ለቅሶና የድጋፍ ሰልፍ ብቻ ሳይሆን ለሌላም ግዴታ ሊሠማሩ የሚችሉ ናቸው። አባልነታቸውም ከሥራ እድልና እድገት ጀምሮ ከተለያየ ጥቅማ ጥቅም ጋር የሚመጣ ነው። በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚሠራው ሰው ሁሉ አባል፣ ደጋፊ ወይም ተቃዋሚ ተብሎ በደንብ ተለይቶ ተቀምጧል። የተቃዋሚ ይቅርና የመሐል ሰፋሪውም ቁጥር በየጊዜው ተመናምኖ የቀረው አባልና ደጋፊ እንኳን ባይሆን የእንጀራ ገመዱ እንዳትበጠስ ምንም ዐይነት ተቃውሞ የማያሳይና፣ እንዲያውም ባይፈልግም እንኳን የሚጠየቀውን ድጋፍ በእሺታ የሚሰጠው እየበዛ የሄደበት ዘመን ነበር።

አንድ ምሳሌ እንይ። ትልቅ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው። መሥሪያ ቤቱ የመለስን ለቅሶ በማስመልከት የአንድ ቀን እረፍት እንደሰጠ እና ሠራተኞች ተመልሰው ወደየቤታቸው መሄድ እንደሚችሉ ያስነግራል። ሠራተኞቹ በከፍተኛ ደስታ ወደየቤታቸውና ወደተለያየ ጉዳይ ከሥራ ለመውጣት ሲተራመሱ የመሥሪያ ቤቱ ሰርቪስ አውቶቢስ በየቤታቸው እንደሚያደርሳቸው ይነገራቸዋል። ይበልጥ ደስ ብሏቸው በየቆሙት አውቶቢሶች ውስጥ ይገባሉ። ሁለቱ ሠራተኞች የሰፈሬ ልጆች ነበሩ። በአውቶቢሱ ተሳፍረው የተለያየ ቦታ ተቀምጠው እየሄዱ አውቶቢሱ ዘወትር ወደ ቀኝ ታጥፎ የአሥመራ መንገድን መያዙን ይተውና አብዮት አደባባይን ከቦሌ መንገድ ወደ እስጢፋኖስ አቅጣጫ መሻገር ይጀምራል። ድንገት ሴቷ የሰፈሬ ልጅ ጮኻ ወራጅ! ትላለች። ሹፌሩ ደንገጥ ብሎ እስጢፋኖስ ቤተክርስትያን አጠገብ ቆም ያደርገዋል።

“ እንዴ በየቤታችሁ አደርሳችኋለሁ አልነበር ያልከን?። የት እየወሰድከን ነው? “ አለችው ሹፌሩን። ፊት ነበር የተቀመጠችው።

“አዎ በየበቤታችሁ እኮ አደርሳችኋለሁ። በጊዜ ከወጣን አይቀር ሰብሰብ እንዳልን በዚያው ቤተመንግሥት ለቅሶ እንድረስ ብዬ ነው።” አላት።

“አልነገርከንም። ይቅርታ እኔ በታክሲ እሄዳለሁ። እዚህ ጋር አውርደኝ።” ትለዋለች ፍርጥም ብላ።

ሌላ ከኋላዋ ተቀምጣ የነበረች ሠራተኛ በመገረም  “ለቅሶ አትደርሺም?” ትላታለች።

አሁን የባሰ ቱግ ትልና “ስንት ጊዜ ላልቅስ? ውሰድልኝ ብዬ ለቅሶ፣ ወሰድክልኝ ብዬ ለቅሶ!”

ካለች በኋላ በተክፈተው በር “ደህና ዋሉ” ብላ ከአውቶቢሱ ትወርዳለች። መኪና ውስጥ የቀረው የሰፈራችን ልጅ ስለሁኔታው ሲነግረን እንዲህ ነበር ያለው።  ሠራተኛው ሁሉ በድንጋጤ መብረቅ እንደመታው እንጨት ክው ብሎ ሹፌሩ እንኳን ሳይነቃነቅ እየተራመደች ሄዳ የእስጢፋኖስን አጥር አልፋ ወደ ግራ እስክትታጠፍ አንገታችን አዙረን በዐይናችን ተከተልናት።  ምነው የሷን ድፍረት ቢሰጠኝ ብዬ ብመኝም ከወንበሬ መላወስ እንኳን አልቻልኩም። እዚህ ቦታ ለመቀጠር ያየሁት መከራና ሥራ ሳልይዝ ቤተሰብ ላይ ሸክም ሆኜ የነበርኩበትን ጊዜ አስቤ ጀግኒትን እያደነቅኩ በተጠለፈው አውቶቢስ ወደ ለቅሶው ሄድኩ ነበር ያለኝ። ከለቅሶው በኋላ በአጋጣሚ አንድ ሁለት ቀን ሥራ አልገባም ነበርና አሠልሶ ሲመለስ ልጅቷ መሥሪያ ቤቱን ለቅቃለች። አለቆቿ ያስለቅቋት በፈቃዷ ትልቀቅ ያወቀው ነገር የለም። እኔም ልጅቷን በዚያው ሰሞን አግኝቼ የግል ሥራ እንደጀመረች አስተውያለሁ።

በሰፈራችን ሁለት የለቅሶ ቦታዎች ነበሩ። አንደኛው ሃያ ስምንት ሜዳ የሚባለውና ከካዛንቺስና አቧሬ መካከል የሚገኘው ቦታ ላይ ነበር። ትላልቅ ድንኳኖች ተዘርግተው የቴሌቪዥን ስክሪን ተዘጋጅቶ ነበር ሙሾው የሚወርድው። ቦታው ትልቁ የባልደራስ የመከላከያ ካምፕ አጠገብ እንደመሆኑ እጅግ ብዙ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ አባላትና ቤተሰቦች ስላሉ የደመቀ ለቅሶ ቤት መስሏል። በእግር ስሄድ ከመከላከያ ካምፕ በትግርኛ እያወራ የሚጎርፈው ጥቁር ለባሽ ለቀስተኛ ብዙ ቁጥር እንደነበረው ታዝቢያለሁ። አማረኛ የሚያወሩም ነበሩባቸው። ሌላው በሰፈራችን የነበረው የመለስ ለቅሶ ማእከል በወረዳው ግቢ ነበር። ይሄ ለኛ ቤት ቅርብ ስለነበር ቤታችንን እያለፉ የሚጎርፉትን ለቀስተኞች በቅርብ ለመከታተል አስችሎኛል። የሚበዙት ሴቶች ሲሆኑ እንደ አረብ ሴቶች ዐይናቸውን ብቻ አስቀርተው ሙሉ በሙሉ በጥቁር ተሸፋፍነዋል። ያልተሸፋፈኑትም ሲተያዩ እንደመደንገጥና እንደማፈር ያደርጋቸዋል። አንዱን የሰፈር ልጅ እዚያው የኖረ ይሄንን ነገር ጠየቅኩት። የመሸፋፈኑን እና የመተፋፈሩን ነገር።  ሠፈራችን ደማቅ የገበያ ማእከል እንደመሆኑ ብዙዎቹ ለተለያየ ሥራ ገንዘብ የተበደሩና ከፊሉ በመሽቀርቀርና በሌላ አጥፍተውት መልሰው መክፈል ባለመቻል ባለእዳ ናቸው። እዳው ይሰረዝላቸዋል ግን አይረሳም። ነበር ያለኝ። ሁሉም አንዷ ለሌላዋ ሌላ የገቢ ምንጭ ለምሳሌ ውጭ አገር ያለ ዘመድ፣ ወይም እጮኛ እንዳላቸው ያስመስላሉ እንጂ የኢህአዴግ ባለእዳ ሆነው የእለት ጉሮሮ ደፍነው፣ ለብሰውና ተኩለው እንደሚኖሩ እርስ በእርስ አይተዋወቁም። ላይ ላዩን ሁሉም የኢህአዴግ ፖሊሲዎች ተቃዋሚ ናቸው። ታድያ እንዲህ ድርጅቱ ሂሳብ ሲያወራርድ ድንገት ጎን ለጎን ሲተያዩ መተፋፈር! ትርፍ ነገር ለማግኘት ሳይሆን መብትህን ለመጠቀም አባል፣ ሰላይ ወይም ደጋፊ መሆን የግዴታ የሚሆንበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ሰፊ ግቢ ያለው ሰው ኑሮውን ለመደጎምና ገቢውን ለመጨመር አንድ ሁለት ክፍሎች ሰርቼ ላከራይ ቢል አባል፣ ደጋፊ ወይም ሰላይ ከሆነ በጠራራ ጸሐይ በፕላንም ያለፕላን ሁለት ክፍል ቤቱን ሠርቶ ለኪራይ ማዘጋጀት ይችላል። ካልሆነ ደግሞ ፕላንም አውጥቶ ሕጉንም ተከትሎ የፈለገውን ለማድረግ እጅግ ብዙ ውጣ ውረድና ዳጎስ ያለ ጉቦ ሁሉ ሊያስፈልገው ይችላል። ያለፕላንማ ገና አንድ ሚስማር ሲመታ የታጠቀ የወረዳ ግብረ ሃይል ነው በሩን በርግዶ ቤቱን የሚወረው። ጉልት ለመጎለት፣ የሬሳ ሳጥን የምታክለዋን የአርከበ ሱቅ ለመከራየት፣ ለትንሹም ለትልቁም ነገር የድርጅቱ ድጋፍ ያስፈልግ ነበር። ሕዝቡ ለእለት ጉርሱ በተወሳሰበ የጥቅም ገመድ ከፓርቲው ጋር እንዲተሳሰር ተደርጓል። እንደ ደርግ ዘመን ቀላል የማይባለው ከተሜ ደግሞ ለዘይትና ስኳር ሳይቀር ከቀበሌ ጋር ታንጎ ለመደነስ የሚገደድ ነው።

በቅርቡ በብልጽግና ሰልፍ ላይ ካያቸው እናቶች አንደኛዋን አንድ ዮቱዩበር “ማዘር በእርሶ እድሜ እቤት ቢቀመጡ አይሻልም ነበር?” ይላቸዋል። ሴትዮዋ ምንም ሳያመነቱ “እና ማን ያስቀምጥሃል?” ነበር ያሉት። የልብሳቸው ሳሙና፤ የጧት ቁርሳቸው ሻይ ስኳር ከብልጽግና ፓርቲ መንግሥታዊ ካዝና የተገኘ ለመሆኑ የሚያሳብቅ ድምጸት ነው።  በእርጅና እቤት ያላስቀመጣቸው እዳ!

ይሄንን ነው ጠ/ሚ በሾርኔ ከውጭ ለገቡ ድርጅቶች የሀገሬው ኑሮ መቀየሩን ሊነግሯቸው የሞከሩት። አብዛኛው ኅብረተሰብ በኢህአዴግ/ብልጽግና ፓርቲ የቅሌት ደብተር የተመዘገበ ነው። እንደሚታወቀው የቅሌት ደብተር የሚባለው የሰፈር ባላሱቆች ገንዘብ ሳይከፍል በዱቤ ሸቀጥ የሚወስደውን የደምበኛ ዝርዝር እና እዳውን መዝግበው የሚይዙበት ደብተር ነው። ልዩነቱ የሰፈር ሱቆች እዳውን በገንዘብ የሚቀበሉ ሲሆኑ ኢህአዴግ/ብልጽግና በጉልበት፣ በስለላና በሌላም ድርጅታዊ ድጋፍ በዐይነት የሚቀበል መሆኑ ነው። ድህነት ኅሊናን አይደለም ገላን ያስሸጣል። መፍትሔው ከሁለንተናዊ ድህነት መላቀቅ ነው። በብልጽግና ፓርቲ መንገድ ደግሞ ከድሃ እንጂ ከድህነት የምንላቀቅ አንመስልም። እንዲህ በአደባባይ ሰልፍ የወጣው ኢትዮጵያዊ ሀገሩን በስፋትና በድፍረት ስለወረረው የሱዳን ጦር አንድ ቃል ሳይተነፍስ መመለሱ እንኳን ወገንን ጠላትን የሚያስገርም ነው። ገላ መሸጥ ማለት በሀገር ደረጃ ይኸው ነው።

በነገራችን ላይ ሌሎች ብዙ የኅብረተሰብ ክፍሎች በብዛት የተገኙበት ቢሆንም የጠ/ሚ የሰኔ 16 የድጋፍ ሰልፍ ላይ ከተገኘው ሕዝብ እጅግ አብላጫው ቁጥር በዚህ የቅሌት መዝገብ ስሙ የሰፈረው ነው የሚል ግምት አለኝ። ለምን? አዲስ ዘመን ይመጣል፤ ይህ የቅሌት መዝገብም ይቃጠላል። ነጻም እወጣለሁ ብሎ ተስፋ በማድረግ። የቅሌቱ ደብተር የገንዘብ እና የጥቅማ ጥቅም ብቻ ሳይሆን የኅሊናም እዳ አለበት። ሥርዐቱ ሀገርን የበደለ ነበርና። ከራስም ከሃገርም ከኋላ ታሪክም ታርቆ ነጻ የመሆን ፍላጎት የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል ለማለት ነው። ጥቂት አስቡበት። ኢትዮጵያ የሚለውን ድምጽ ሰምቶ በደስታና በተስፋ ከወጣው ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኢህአዴግ አባል፣ ደጋፊና የአምስት ለአንድ ጠርናፊ በሰኔ አሥራ ስድስት መስቀል አደባባይ ወጥቷል። ውጣ ተብሎ ሳይሆን ከዚያ ካልፈው የኅሊና እዳ ነጻ የምወጣበት ቀን መጣልኝ ብሎ። አልሰምሮም።

ይቺኛዋን የጨረባ ምርጫ ደግሞ እስኪ በሰላም ያሳልፈን!

 

1 Comment

  1. ይሄ ሰውዬ ከገሀነም ውጭ የት ይሂድ ነው የምትሉት ከሳጥናኤል ጋር ይጣልልን ከሆነ ስብሀት ነጋ ብርሀኑ ነጋ አብረሀ ደስታ ከተባሉት ነብሰ በላዎች ጋር መምከር ያስፈልጋል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.