የአዲስ አበባ ጉዳይ በሕግ መነጽር ሲታይ – ባይሳ ዋቅ ወያ

addis ababa zehabesha
addis ababa zehabesha

የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳ መስማት ካቆምኩ ቆይቻለሁ። ወድጄ አይደለም። ከሞላ ጎደል ሁላቸውም የሚያነሱት የማንነት ጥያቄና ከብልጽግና ፓርቲ መሻላቸውን እንጂ ከሱ የተሻለ ምን የኤኮኖሚና የፖሊቲካ አጄንዳ እንዳላቸው በግልጽ ለሕዝብ ስለማይነግሩን ትግላቸው የፖሊቲካ ሥልጣን ለመያዝና ሕዝቡን ደግሞ ማማ በሰማይ እያሉ ሊተገበር የማይቻል የውሸት ተስፋ ሲሰንቁለት ታይቶኝ፣ የማናቸውንም የምርጫ ቅስቀሳ ላለመከታተል ወስኜ ነበር። ሰሞኑን ግን የአንዳንዶቹ በተለይም የኢዜማና የባልደራስ የምርጫ ቅስቀሳ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ለሕዝብ ቀርቦ ሳየው፣ እነዚህ ሰዎች ወይ ሞኝ አድርገውናል ወይም ደግሞ ራሳቸው ሞኝ ናቸው ከማለት አንዳንድ በቅስቀሳቸው ዙርያ በተለይም የአዲስ አበባን ማንነት በተመለከተ የሚያሰሟቸውን መፈክሮች ዋቢ አድርጌ የሚከተለውን ለማስፈር ተነሳሳሁ። ዓላማዬ ከሕግ አንጻር ጉዳዩን ለመመርመርና እውኔታውን ለመራጩ ሕዝብ ለማሳወቅ እንጂ፣ የአንድም የፖሊቲካ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ ሳልሆን አገራዊ ጉዳዮችን በገለልተኝነት ለማየት ከሚሞክሩት ዜጎች አንዱ መሆኔ ከወዲሁ ይታወቅልኝ እላለሁ።

የአዲስ አበባ የማንነት ጥያቄ በአገሪቷ ውስጥ ካሉ የፖሊቲካ ጥያቄዎች ሁሉ እጅግ በጣም የተወሳሰበ እንደሆነ ከገባን ሰንብቷል። ችግሩ የሚመነጨው ከተማዋ የፌዴራሉም የኦሮሚያም ክልል ዋና ከተማ ከመሆኗ ይመስለኛል። የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 49 እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት አንቀጽ 6 አዲስ አበባ ዋና ከተማቸው እንደሆነ ይደነግጋሉ። አንድ ከተማ የሁለት የሕግ አካላት ዋና ከተማ መሆን በራሱ ችግር ባይሆንም፣ የሁለቱን ባለቤቶች ድርሻ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ አለማስቀመጥ ግን የችግሮቹ ሁሉ መነሻ ይመስለኛል።

ሰሞኑን አንዳንድ የፖሊቲካ ድርጅቶች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ አዲስ አበባን በተመለከተ ከሚያነሷቸው መፈክሮች ሶስቱን ብቻ ላነሳ እወዳለሁ። የማነሳቸውም ችግር ላይ ተጨማሪ ችግርን ለመደረብ ሳይሆን፣ የችግሮቹን ምንነት ከሕግ አንጻር ለማሳየትና መፍትሔያቸውን በአጭሩም ቢሆን ለመጠቆም ነው። የማተኩርባቸው ሶስቱ መፈክሮች፣

ሀ) “አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው”፣ ይህን የባልደራስን መፈክር በግርድፉ ካየነው ግልጽ ያልሆነና ዝም ብሎ የመራጭን ቀልብ ለመሳብ የታቀደ ይመስለኛል። ባልደራስ ለመራጩ ሕዝብ ግልጽ ያልሆነ ለሱ ግን በምስጢር የደረሰው አንድ የጎረቤት አገር ርዕሰ ከተማችንን ለማውደም ማቀዷን የጸጥታ መረጃ ደርሶት ይሆናል ብሎ መገመት ይቻላል። ይህ ከሆነ ደግሞ እናት አገራችንና ዋና ከተማችንን ከወራሪ ኃይል የመከላከሉ ኃላፊነት የባልደራስ ብቻ ሳይሆን የመላው ዜጋ ግዴታ ስለሆነ ወራሪው ኃይል ማን እንደ ሆነ በግልጽ መነገር አለበት። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግሥት የዚህን የዋና ከተማችንን በውጪ ኃይል የመወረር ጉዳይ የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶት መከላከያ ሠራዊታችንን ከያሉበት መልሶ በአምስቱም የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች ላይ አሰልፎ የመከላከል ዝግጅቱን መጀመር አለበት። አዲስ አበባን ከውጭ ወራሪ ኃይል ማዳን እውነትም ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ኃይል ማዳን ነው። ባልደራስን የምንጠይቀው ግን እንደው ዝም ብሎ አዲስ አበባ ልትወረር ነው ከማለት ወራሪው ኃይል ማን እንደሆን አስቀድሞ ቢነግረን፣ የጠላታችን ማንነትና፣ ጠንካራና ደካም ጎኑን፣ ብሎም ደግሞ ከሱ ጋር አብረው ሊወጉን የሚዶልቱትን አካላት ገምግመን የመከላከል አቅማችንን በዚያው ልክ እንድናዘጋጅ ይረዳን ነበር።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከፋውንዴሽኑ ጀርባ... (ክፍል ፩) - ከተመስገን ደሳለኝ

ለ) “አዲስ አበባ ላይ ማንም ልዩ ጥቅም አይኖራትም”። ይህ የባልደራስም የኢዜማም መፈክር ነው። ሁለቱም ያነጣጠሩት

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49(5) ሥር የሰፈረውን “የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም” ላይ ነው። የአማራ ክልል በባሕር ዳር ላይ፣ የሶማሌ ክልል በጂግጂጋ ላይ፣ የቤንሻንጉል ክልል በአሶሳ ላይ ወይም የትግራይ ክልል በመቀሌ ላይ ያላስፈለጋቸውን “ልዩ ጥቅም” የኦሮሚያ ክልል በራሱ ክልል ዋና ከተማ ላይ ለምን “ልዩ ጥቅም” እንዳስፈለገው ባይገባኝም፣ “ልዩ ጥቅም” የተባለው ሓረግ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧልና አንድ ቀን መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ፣ ለጊዜው ዛሬ ባለው ሁኔታ ጉዳዩን በደንብ ለመረዳት ሶስት ተጓዳኝነት ያላቸውን ጉዳዮችን ጠቅሶ ማለፉ ጠቃሚ ይመስለኛል።

 • የልዩ ጥቅሙ ተጠቃሚ ማነው? የዚህ ልዩ ጥቅም ብቸኛ ተጠቃሚ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ እንደ ተቀመጠው የኦሮሚያ ክልል ነው። አንዳንዶች ግን አውቀውም ሆነ በስሕተት “የኦሮሞዎች ልዩ ጥቅም” ብለው ሕዝቡን ሲቀሰቅሱበት ይስተዋላል።

 

 • ልዩ ጥቅሙ ለምን አስፈለገ? ልዩ ጥቅሙ ያስፈለገበት ምክንያት ደግሞ፣ ሀ) አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎቹ የዘጠኝ ክልሎች ዋና ከተማ በተለየ መልኩ ሁለት ሕጋዊ ባላቤት ስላላት፣ ለ) የምትገኘው በኦሮሚያ ውስጥና በሁሉም አቅጣጫ በኦሮሚያ የተከበበች ስለሆነች እና ሐ) ከ “ሀ” እና “ለ” ጋር የተያያዙ፣ የአገልግሎት አቅርቦት፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና ሁለቱን ባለቤቶች የሚያስተሳስር አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስላሉ ነው።

 

 • ይህንን አወዛጋቢ እየሆነ ለመጣው ጉዳይ መፍትሔውስ ምን ይሆን? ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ነው ተብሎ ከታመነበት፣ መፍትሔውም ሕገ መንግሥቱ ውስጥ መገኘት አለበት። ዛሬ ይህንን ልዩ ጥቅም ከሕገ መንግሥቱ

ለመሠረዝ የሚፈልጉ ቡድኖች በለስ ቀንቶአቸው አራት ኪሎ ቢገቡ፣ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105 ላይ በተቀመጠው መሠረት ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል የሚወክሉትን ሕዝብ ጥያቄ ሊመልሱ ይችላሉ። ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ሊያስኬድ የሚችል ጎዳና የለም። አብዮት እናካሄዳለን ካልተባለ በስተቀር!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ልማት ወይንስ ውድመት? (አክሎግ ቢራራ (ዶር))

ሐ) “አዲስ አበባ እስካስፈለጋት ድረስ ትሰፋለች”፣ ይህ ደግሞ የኢዜማ መፈክር ነው። አዎ ከተሞች ይሰፋሉ፣ ይጠባሉ፣ ወይም ደግሞ ከናካቴው ከምድረ ገጽ ላይ ይጠፋሉ። የሰው ልጅ ታሪክ ሶስቱንም ዓይነት አሳይቶናል። ዛሬ ካለንበት ቦታ ላይ ሆነን ስንገመግመው፣ አዲስ አበባ የመስፋት ዕድሏ የሰፋ ነው። ከተሞች ሲሰፉ ወደ አንድ ጎረቤት ወደ አለው አካል ነው። በአየር ላይ አይደለም። ዋናው ጥያቄ ጎረቤት ያለው መሬት ባዶ ሜዳ ነው ወይስ ባለቤት አለው? አዲስ አበባን የወሰድን እንደሆነ፣ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ በሁሉም አቅጣጫ በኦሮሚያ የተከበበች ስለሆነ፣ በአራቱም አቅጣጫ ብትሰፋ ወደ ኦሮሚያ ክልል ነው። ከተሞች ደግሞ ልክ እንደ ማንኛውም በዚህ ምድር ላይ እንደሚተከሉ ሰው ሰራሽ ግንባታ/ተቋሞች የተከለለ የራሳቸው የሆነ አስተዳደራዊ ድንበር አላቸው። የአስተዳደራዊ ድንበር መኖር ጥቅሙ፣ በውስጣቸው ለሚኖሩ ዜጎች ሕጋዊ መብታቸውን ለማስጠበቅና፣ ለአስተዳደሩ ደግሞ ለኗሪው ሕዝብ አስፈላጊውን አገልግሎት ለማቅረብ ነው። ባጭሩ ከተሞች የመስፋታቸውን ያሕል፣ የግድ አስተዳደራዊ ድንበር ደግሞ ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው።

አዲስ አበባን ከመስፋት የሚያቆም ኃይል አይኖርም። እንደ ማንኛውም ከተማ ስሟን ይዛ ታድጋለች፣ ትሰፋለች። ለወደፊትም እስከ ቢሾፍቱና አዳማ፣ ሰበታና አምቦ ድረስ ልታድግ ትችላለች። የከተማዋ አስተዳደራዊ ድንበር ግን በህግ ተወስኖ ከተከለለት ውጭ ሊሰፋ አይችልም። የአዲስ አበባን የመስፋት ጥያቄ በበለጠ ለመረዳት የፌዴራል አሜሪካን ዋና ከተማ የዋሺንግተን ዲሲን ሕጋዊ ሰውነት ለአብነት መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል። ዋሺንግተን ዲሲ በ1790 ዓ/ም የሜሪላንድና የቪርጂንያ ስቴቶች

በመዋጮ በሠጡት 68 ስኩዌር ማይል ላይ የተፈጠረችና ዛሬ 700,000 ዜጎች የሚኖሩባት የፌዴራል አሜሪካ ርዕሰ ከተማ ስትሆን፣ በሂደት ግን ወደ ሜሪላንድና ቪርጂኒያ ስቴቶች ሰፍታ ዲሲ ሜትሮ ተብላ ትታወቃለች። ህጋዊ የአስተዳደር ድንበሯ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የማህበረሰባዊ ድርጅቶች ጉባኤ መግለጫ

ግን በ1790 ዓ/ም የፌዴራሉ ርዕሰ ከተማ እንድትሆን በህግ ተደንግጎ ከተከለለላት 68 ስኩዌር ማይል ውጪ በአንዲት ኢንች እንኳ አልጨመረም። ከተማዋ ግን ወደ ጎን ሰፍታ ዛሬ ከ 6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ “የዲሲ ሜትሮ” ነዋሪዎች የሚተዳደሩት፣ ግብር የሚከፍሉና የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ህጋዊ መብታቸውን የሚጠቀሙት በሜሪላንድና በቪርጂኒያ ስቴቶች ሕግና ደንብ መሰረት ነው። ከዚህ የምንረዳው ዋናው ቁም ነገር፣ ከተሞችን እንዳይሰፉ ማድረግ አይቻልም። አስተዳደራዊ ድንበር ማበጀት ግን ግዴታ ነው የሚለውን ነው። አስተዳደራዊ ድንበር የሌለው በምድራችን ላይ አንድም ከተማ የለምና!

ለመደምደም ያሕል፣

የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን እንደው ፈርዶባቸው መፈክር ይወዳሉ። የሚያሰሙት መፈከር ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ወይም አይሆንም ብለው አስበውበት ሳይሆን የመራጩን ሕዝብ ድምጽ ለማግኘት ሲባል ብቻ “ይህን ወይም ያንን አደርግልሃለሁ” በማለት የሕዝቡን ቀልብ ይስባሉ። ሊሳካም ላይሳካም ለሚችል ነገር ሕዝቡን የውሸት ተስፋ ከመመገብ፣ “ብትመርጡንና

ተሳክቶልን ፓርላማ ብንገባ ለምሳሌ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 49 ለማሻሻል ጥረት እናደርጋለን” ቢሉ የሚሻላቸው ይመስለኛል። ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ደግሞ ቀላል ነገር አይደለም። የሕገ መንግሥቱን አንዲት አንቀጽ ለማሻሻል ይቅርና የማሻሻል ሃሳቡን እንኳ በአጄንዳ ለማስያዝ የአሥሩንም ክልል ሕዝቦች አዎንታዊ መልስ ስለሚጠይቅና፣ አንዳንድ ክልሎች ደግሞ አንቀጹ እንዳይነካባቸው ሊፈልጉ ስለሚችሉ፣ ገና ፓርላማ ሳትገቡና ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ያላችሁን አቅም ሳትገመግሙ፣ የመራጩን ሕዝብ ልብ ማንጠልጠል በለስ ሳይቀናችሁ ቀርቶ አንቀጹን ማሻሻል ሲያቅታችሁ፣ በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ ያሳጣችኋልና በጥብቅ አስቡበት እላለሁ። ያ እንዳለ ሆኖ ግን፣ በለስ ቀንቶአችሁ “የተከበሩ” ለመባል ያብቃችሁ እላለሁ።

******

bayisa wak woya `^
bayisa wak woya `^

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14 ቀን 2021 ዓ/ም

ባይሳ ዋቅ ወያ

[email protected]

 

 

 

5 Comments

 1. The current constitution is the handwork and document of the TPLF and was not approved and accepted by all Ethiopians. It should be presented to the public discussion and every citizen should have a say on it.

 2. ውድ አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ፣
  አዲሳባን ለፖለቲካ ፍጆታ በማዋል ከህወኃት ቀጥሎ የእስክንድር ነጋ ባልደራስ ነው። ህወኃት ዓላማው ኦሮሞን ለመከፋፈልና ከአማራ ጋር ለማጋጨት ነው፤ በሚፈጠረው ግርግር ለመበዝበዝ ነው። ለልማት ያስፈልጋል በሚል ሰበብ ኗሪውን አባርሮ ለራሱ ዘረፋ ሲያመቻች ኖሮ በሕዝብ ብሶትና መነሳሳት ወደ መቀሌ ሸሽቷል። እስክንድር ፖለቲካ ማወቅ ቀርቶ ቊምነገር ያለው ሥራ ሠርቶ አያውቅም። ያደረጋቸውን ንግግሮች ማድመጥ በቂ ነው፤ እዚህ የተናገረውን ፈንጠር ብሎ ያፈርሳል። ፈረንጆች ፖፒዩሊስት ወይም ዴማጎግ የሚሉት ዓይነት ነው። የሚገርመው ባልደራስን ያቋቋመው ከጓደኞቹ ጋር ሆቴል ቤት የራሱን ፎቶ ከኋላው በትልቁ ሰቅሎ እርሱ ራሱ ዋነኛ ተናጋሪ በሆነበት ነው! ባልደራስ “ለእውነተኛ” ዲሞክራሲ ብሎታል! ትንሽ ታሪክ ያነበብን ቢራ ቤት ተሰባስቦ ፓርቲ ሂትለርን ያስታውሰናል። የኔ ብቻ ፓርቲ “ለእውነተኛ ዲሞክራሲ” የቆመ ነው ማለት ሌላኛው የአምባገነኖች ባህርይ ነው። እስክንድር የጃዋር ግልባጭ ነው! ሁለቱም እስር ቤት መግባታቸው አደባባዩን እንዴት እንዳሳረፈ እያየን ነው! የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኮሮና ምክንያት ከአሥር በላይ አይሰብሰብ ባለበት እስክንድር አጠና ተራ ሄዶ ከመቶ የሚበልጡ ሰዎችን አሰባስቦ እስቲ የሚነካኝን አያለሁ ይላል፤ ይኸ ነው ሕዝብን የሚያገለግል? ከሟቹ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ የደርግ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊ እና ሌሎች ሆነው በአገራችን የዘር ማጥፋት እየተካሄደ ነው ብለው ለተባበሩት መንግሥታት የክስ ሰነድ ያገቡ ናቸው። እስክንድር ልክ እንደ ተጠቃሾቹና እንደ ህወሓት ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ ዶ/ር ዐቢይ ወርዶ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ማለት ከጀመሩ ሦስት ዓመት አልፏቸዋል፤ የሚመስለኝ ከህወሓት ጋር ድርድር ሊያደርጉ መሆን አለበት እንጂ ዶ/ር ዐቢይ ህወሓትን ለማስወገድ ያደረገውን ለማድረግ ብቃቱም ልምዱም የላቸው! እስክንድር ማዘጋጃ ቤት እየሄደ ከንቲባ ታከለ ኡማ ሲያልፍ ሲያገድም ጠብቆ ለማዋረድ ሲሞክር ነበር፤ ባለጌ መሆኑን በራሱ የመሰከረ ሰው ነው። ታከለ ኡማ ብሔራዊ ቲያትር አጠገብ የተተከለውን የአንበሳ ሐውልት ነቅሎ ሊጥል ነው አለ፤ ምንም መረጃ የለም፤ ሕዝብ ለማነሳሳት ግን ተጠቀመበት። የሚገርመው እስክንድር ባዲሳባና ባካባቢዋ በተነሡ ብጥብጦች (ቡራዩ፣ ሰዓረና ሃጫሉ በተገደሉበት ሤራ ውስጥ (ስውር) ተዋናይ ነበር። አዲሳባ ሸገርም ፊንፊኔም እንበላት፣ ያው አዲሳባ ነች፤ የሁሉም መናኻርያ ነች። ዙሪያዋ (አምቦ፣ ሱሉልታ፣ ቡራዮ፣ ወዘተ) የሠፈረው ባብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ሰሞኑን የመጣ አይደለም። እንደ እስክንድርና ጃዋር ዓይነቶች ባያበጣብጡት አብሮ የኖረ ነው! ያደረሱት ውዥንብር ሳያንስ እነ እስክንድ አዲሳባ ጥንት በራራ ትባል ነበር፤ የአማራ ነች ማለት ጀመሩ! በራራ የሚባል ካዲሳባ ወዲያ ማዶ እንዳለ ጥናታዊ ግምት እንጂ በውል የተጠናቀቀ መረጃ የለም! እነ እስንድር ዓይነቶች ግራ ቀኙን የማያውቀውን ሕዝብ ያወናብድላቸው እንጂ ከእውነት ጋር ብዙም ቍርኝት የላቸውም! ለማንኛውም ከህግ፣ ከታሪክና ከዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች አንጻር ስለምትጽፋቸው ጽሑፎችህ አመሰግናለሁ። ለሚጠቀምበት አስተማሪ ናቸውና ቀጥልበት።

 3. አቶ ባዬሳ አንድ ሰሞን እነ ጃዋርና OMN በአገረ ቤት ያዙኝ ልቀቁኝ ባሉበት ሰዐት ሁሉን የተቆጣጠሩ መስሎት በበይነ መረብ ሲዘባርቅ ነበር። ዛሬ ጃዋር እስር ቤት OMN ደግሞ ተባሮ ሄዷል።

  ወደ እነ አብይ ጠጋ ጠጋ ለማለትና ብልፅግናን እጅ ለመንሳት ደግሞ ይህው ተቃዊሞችን ሊያሳጣ ደግሞ በተለመደው ሾካካ ባህሪው ብቅ ብሏል።

  በTPLF ዘመን ያራምዳቸው የነበረው አቛሙ ደግሞ የጄኔቫዉ OPDO እንለው ነበር።

  ትምህርትና እድሜ እንዲሁም የውጭ አገር ኑሮ ከልጅነት ጀምሮ የያዘውን የአንድ ዘር ጥላቻ እንዲቀይር ያላስቻሉት የተቸገረ ሰው ቢኖር ይሄ ወንድማችን አቶ ባይሳ ነው።

  ጨዋ በሚመስል አማርኛው ግን ሁሌም ሬትን በማር ለውሶ የሚያጎርስ ፤ ንሳሃን ሳይቋደስ ግን እርጅና ወደ ሞት መንገድ እየወሰደችው መሆኑ ግን ያሳዝናል።

  • “ቶሎሳ”፣ በጭፍኑ እንጂ ከአቶ ባይሳ ጋር ያልተስማማህበትን አንዱንም አልነገርከንም፤ ብትችል ንገረንና እኛም እንድንጠነቀቅ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.