የዶ/ር አቢይ ፖለቲካ እንዴት እና ወዴት! (ናፍቆት ገላው)

“Power is not a means; it is an end. One does not establish a dictatorship in order to safeguard a revolution; one makes the revolution in order to establish the dictatorship”

George Orwell, 1984

“ስልጣን መንገድ አይደለም፤ በራሱ መዳረሻ ነው። ሰዎች አምባገነንነትን የሚመሰርቱት አዮትን ለመጠበቅ አስበው አይደለም። ቀድሞ ነገር አዮት የሚቀሰቅሱት አምባገነን ለመሆን ነው።”     

ጆርጅ ኦርዌል, 1984

abiy Ahmedመከላከያ ሰራዊት መቀሌን መቆጣጠሩን ተከትሎ፤ ዶ/ር አቢይ በፓርላማ ቀርበው ጦርነቱን አስመልክቶ የሰጡትን ሰፊ ማብራሪያ የሚጀምሩት፤ ከእሳቸው ወደ ስልጣን መምጣት ቀደም ብሎ ባሉት ጥቂት ወራት ወደ ኋላ ተመልሰው፤ በለውጡ ሂደት ከሕወሃት ሰዎች በኩል የገጠሟቸው ፈተናዎችን በማስቃኘት ነው።

ለውጡን ለማደናቀፍ በሕወሃት በኩል የተቃጡ ሙከራዎች ብለው ከዘረዘሯቸው ክስተቶች በመጀመሪያ ደረጃ የጠቀሱት፤ ኃይለማርያም ደሳለኝን ለማንሳት ታስቦ የነበረን መፈንቅለ መንግስት ነው። በመካከላቸው ሀሳቡን የማይደግፉ ሰዎች በመኖራቸው መፈንቅለ መንግስቱ መክሸፉን ቀጥለው ያነሳሉ። ከዶ/ር አቢይ ገለጻ በተመሳሳይ፤ በወቅቱ የመከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም የነበሩት ሳሞራ የኑስ፤ ከለውጡ በኋላ አውሎ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ፤ የመፈንቅለ መንግስት የማድረግ ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች እንደነበሩ እና እሳቸው ግን ወታደሩን ፖለቲካው ውስጥ ማስገባት ስላልፈለጉ ሀሳቡን እንደገፉት መናገራቸውን አስታውሳለሁ።

ዶ/ር አቢይ ቀጥለው፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቅ ተከትሎ፤ ሕወሃቶች በተሰናባቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ምትክ፤ እነሱ የሚፈልጉትን ሰው ለማስቀመጥ የለውጡ አመራር ላይ ያደርሱት ነበር ያሉትን የእስር ማዘዣ እስከማውጣት ድረሰ የዘለቀ ዛቻ እና ጫና ይገልጻሉ። ይህኛውም የሕወሃት እቅድ ሳይሰምር ቀርቶ፤ ዶ/ር አቢይ በኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ተመርጠው የጠቅላይ ሚኒስተሩን ስልጣን የተረከቡበትን ሁኔታ ሁላችንም የምናስታውሰው ነው።

የዶ/ር አቢይ እና የሕወሃት ሰዎች ሽኩቻ ግን በዚህ አይቋጭም። ዶ/ር አቢይ ቀጥለው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ከተረከቡ በኋላ፤ ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ ለማደናቀፍ በደህንነት ቢሮ በኩል ይደርስባቸው የነበረውን ጫና ያስረዳሉ። የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት የቤተ መንግስት ቆይታቸውንም “ዘመናዊ እስርቤት ቤት” ብለው ነው የሚገልጹት። የግል ጠባቂዎቻቸውን ቤተመንግስት ይዞ መግባት መከልከላቸውን፤ የቢሯቸው፤ አልፎም የመኖርያ ቤታቸው ቁልፍ በደህንነት ሰዎች ይያዝ እንደነበር፤ ቢሯቸው ስለሚሰለል በስልክም ሆነ በአካል ጠርተው ሰዎችን ለማነጋገር ይቸገሩ እንደነበር እና የቤተ መንግስቱን ግቢ እንኳን ተዘዋውሮ ማየት መከልከላቸውን በመጥቀስም ይደርስባቸው የነበረውን ጫና በዝርዝር ለማስቃኘት ይሞክራሉ።

በደህንነት ሹሙ በኩል የሚደርስባቸው ጫናም፤ በሀገሪቱ ከተሞች እየሄዱ ሕዝብ ለማነጋጋር እና የፖለቲካ እስረኞችን ለማስፈታት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ይቀጥላል። በስተመጨረሻ ዶ/ር አቢይ፤ በአንዳርጋቸው ጽጌ ፍች ዙርያ በተፈጠረ አለመግባባት መነሻነት፤ ከደህንነት ሹሙ ጋር የነበራቸውን እሰጣገባ ከተራ ጭቅጭቅ ወደ ለየለት፤ “ወይ እኛ ወይ አንተ” መባባል የደረሰ ጠብ እንዳደገ ይናገራሉ። ቀጥለው፤ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል የደህንነት ሹሙን ለማንሳት ውሳኔ ላይ መደረሳቸውን ይገልጻሉ። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ፤ የሰኔ 16 የመስቀል አደባባይ አደጋ ተከትሎ ተቋማዊ ለውጥ ስላስፈለገ፤ መከላከያን፣ ደህንነትን፣ ፖሊስን እና ኢንሳን ያካተተ የሲኩሪቲ ሰርቪስ ሪፎርም ወደ ማድረግ እንደተኬደ ያስረዳሉ።

ሁሉም ነገር ዶ/ር አቢይ ባቀረቡበት መልክ ተፍጽሟል ብሎ መደምደም ባይቻልም፤ በሕወሃት ሰዎች በኩል ለውጡን ለመግታት ጥረት መኖሩ የሚጠበቅ ነገር ነው። ማን ስልጣኑን እንዲሁ ያስረክባል? የሚያስደንቀው ምንም አይነት እንቅፋት አልጣሉም ቢባል ነበር። ሆኖም በሕወሃቶች በኩል የነበረው ጫና የለውጡን ሂደት ከማደናቀፍ አንጻር የነበረው ሚና፤ ዶ/ር አቢይ በገለጹት መጠን ልክ ነበር ወይ የሚለው ላይ ግን እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይመስለኝም።

የዶ/ር አቢይ ገለጻ፤ በዋናነት የሕወሃት መወገድ የግድ አስፈላጊ እንደነበር ለማስረገጥ፤ እገረ መንገዳቸውን ደግሞ  ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዳይወጡ የገጠማቸውን ተግዳሮት ለማሳወቅ ያለመ ይመስላል። ንግግራቸውን ልብ ብሎ ላዳመጠው ግን፤ የትረካቸው ይዘት፤ እሳቸው ሊሰጡት ከፈለጉት ምስል በተቃራኒ፤ የሕወሃት ቁመና ምን ያህል ተሽመድምዶ እንደነበር ነው አጉልቶ የሚያሳየው።

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ ላይ ታስቦ ነበር የተባለው መፈንቅለ መንግስት እንኳን ሊሳካ አልተሞከረም። በሀሳብ ነው የቀረው። ጠ/ሚ ኃይለማርያም ስልጣን በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ፤ በምትካቸው እነሱ የሚያዙትን ሰው ለማስመረጥ ያደረጉት ጥረትም አልተሳካም። የዶ/ር አቢይን መመረጥ ማስቆም አልቻሉም። ፈቀዱም ተባለ አልፈቀዱም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ተችሏል። ዶ/ር አቢይም ሊሄዱበት ካሰቡት የሀገርም ውስጥ ሆነ የውጭ ጉዞ አልተገቱም። ጭራሽ ኧረ ዙረት አበዙ እስኪባል ድረስ ሀገሩን አዳርሰውታል። ቁልፍ ያዙብኝ፤ አትወጣም አትገባም አሉኝ፤ አገቱኝ የሚሏቸውን የደህንነት ሰዎችም ጠና ሲል ከቦታው በማንሳት መገላገል ችለዋል። እንዲህ በቀላሉ ማንሳት የሚችሉት ሰው ከጅምሩ ምን ያህል አቅም ነበረው ማለት ይቻላል። የደህንነት ሰዎቹ፤ እውነት ዶ/ር አቢይን፤ በዛ ደረጃ ለመጠርነፍ ሞክረው ከነበረ፤ የከረመ የአለቅነት ልማዳቸው አለቅ ብሏቸው እንጅ ወቅታዊ ፖለቲካዊ አቅማቸውን ያገናዘበ እርምጃ የነበረ አይመስልም።

ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት፤ በለውጥ ኃይሉ እና በሕወሃት ሰዎች መካከል የተፈጠረው ፍትጊያ ሙሉ ለሙሉ ከስሞ ነበር ማለት አይቻል ይሆናል። ሆኖም፤ ኢሕአዴግ ውስጥ የነበረው የሕወሃት የእዝ ሰንሰለት ተቦርቡሮ ቀፎው ብቻ ከቀረ ትንሽ ሳይሰነባብት እንዳልቀረ መገንዘብ ይቻላል። ዶ/ር አቢይ ራሳቸው፤ እዚሁ የፓርላማ ንግግራቸው ላይ፤ በግዜው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር (ጠ/ሚ ኃይለማርያምን እና ምክትል ጠ/ሚ ደመቀ መኮነን መሆኑ ነው) ውስጥ ውስጡን ለውጥ ፈላጊ መሆን እና እነሱም ጋር፤ እኛም ጋር፤ እዚህም እዚያም የሚመላለሱ ሰዎች መኖር፤ ሕወሃቶች የሚፈልጉትን ሰው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦታ ለማስመረጥ ያደረጉትን ጥረት፤ በተቀናጀ ስራ ማክሸፍ እና ከሕወሃት ፍላጎት ወጭ እሳቸውን ማስመረጥ መቻሉን ይገልጻሉ።

አንድን አካል፤ አስታጥቀው፤ ሚዲያ ሰጥተው፤ ቀለብ ሰፍረው እና ሹመው ሲያበቁ በል የኔን ዙፋን ጠብቅ ማለት የሚቻለው፤ ጊዜ ሰጦት እጁ ላይ ያለውን አቅም ማየት እስኪጀምር ድረስ ብቻ ነው። ምን አልባትም የሕዝባዊ አመጹ እየከረረ መሄድ፤ የሕወሃት ውስጣዊ መዳከም እና ራሳቸው እህት ድርጅቶቹ በሂደት የፈጠሩት አቅም ተዳምሮ ውሎ አድሮ የሕወሃት የእዝ ሰንሰለት ሰብረው እንዲወጡ አግዟቸዋል። ሕወሃት የፖለቲካ የበላይነቱን የገነባው በኢሕአዴግ ትክሻ ላይ ነው። ስልጣኑን እንዲጠብቁ ያስቀመጣቸው ቡድኖች ከእነ ሙሉ ስንቅ እና ትጥቃቸው ሲሽፍቱ የሕወሃት አቅም በአንዴ መንኮታኮቱ የሚጠበቅ ነው። በተጨማሪ፤ የጀነራል ሳሞራ በመፈንቅለ መንግስቱ እቅድ አለመስማማት፤ ሕወሃት ውስጥም፤ ለውጡ ላይ እምብዛም ተቃውሞ ያልነበራቸው፤ ቢያንስ የተወሰኑ ሰዎች እንደነበሩ ማሳያ ይመስለኛል።

ያም ሆነ ይህ ግን፤ በሕወሃት ሰዎች በኩል ለውጡን ለማደናቀፍ የነበረው ሙከራ ምንም አይነት መልክ ኖረው ተባለ፤ ዶ/ር አቢይ ጫናውን ተቋቁመውም ቢሆን የአቀዱትን ከማድረግ አልተገቱም። ሕወሃትን ለመክሰስ ሲሆን፤ አላራምድ አላላውስ ብለውኝ ኃላፊነቴን መወጣት አልቻልኩም የሚል ወሬ አመጡ እንጅ፤ እሳቸውም ቢሆን ከዚያ ቀደምም በሚያደርጓቸው ንግግሮች፤ በፓርላማ ቃል የገቡትን ሁሉ እንዳሳኩ እና ለውጡን በታቀደለት መስመር እንደመሩ በሙሉ ልብ ነበር የሚናገሩት። ዶ/ር አቢይ ሌላ ኃይለማርያም ደሳለኝ አይደሉም። ከመነሻውም በስልጣናቸው የማዘዝ አቅም ነበራቸው። ይህ አከራካሪ አይሆንም። በተግባር የታየ ጉዳይ ነው። ጥያቄው ስልጥናቸውን ተጠቅመው በወሰዷቸው እርምጃዎች ምን ወጤት አስገኙ የሚለው ላይ ነው።

……………………………………..//……………………………………..

ከለውጡ ቀደም ብሎ በነበሩት ጥቂት አመታት፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በአንድ በኩል፤ ከጋራ ምሬት በዘለለ የሚያስተሳስር ራዕይ በሌለው የመረረ አመጽ፤ በሌላ በኩል፤ አቅም እየከዳው መሆኑን አምኖ ለድርድር በር ለመክፈት ፍቃደኛ ባልሆነ አገዛዝ ትንቅንቅ መካከል ተቀርቅሮ፤ ከዛሬ ነገ ሀገር በላዬ ላይ ተደረመሰ የሚል ሰቀቀን ውስጥ ሁኖ ነው ያሳለፈው። በዚህ የጭንቅ ሰአት፤ በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ነው፤ ያልታሰበ ገላጋይ እዚያው ኢሕአዴግ ውስጥ የተገኘው።

የሕወሃት/ኢሕአዴግ የስልጣን መሰረት ተቃርኖን በማጉላት ላይ እንደመዘርጋቱ፤ ባለፉት ሦስት አስርት አመታት በየጉራንጉሩ ያልተፈለፈለ ቅራኔ የለም። ነገር ግን፤ በዋነኝነት አገዛዙ የኃይል ሚዛኑን አስጠብቆ የተጓዘው፤ በኦሮሞ እና አማራ ልሂቃን መካከል ፍትጊያ በመቆስቆስ፤ አንዱን ተገን አድርጎ ሌላኛውን በማጥቃት፤ በአንዱ በኩል የሚቀሰቀስበትን ስጋት ሌላኛውን ጋሻ አድርጎ በመመከት እንደነበር ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው።

በዚህ ቁርቁስ መኃል፤ በጠባብነት የሚከሰሰው ኦህዴድ፤ ኦሮሞ ብሔርተኝነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር የሚያስታርቅ፤ ተክዶ የቆየውን የኦሮሞ ሕዝብ የሀገር ግንባታ ድርሻ መልሶ የሚያጸና፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አብሮ ለመኖር ብቸኛ ዋስትናቸው፤ ህገ መንግስቱ ያጎናጸፋቸው፤ ያሻቸው ቀን ሀገር በትኖ የመለያየት መብት ነው ከሚለው የሕወሃት/ኢሕአዴግ አስተምሮ እጅግ በተፋታ መልኩ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የኋላ የጋራ ታሪክን እና አብሮ የተገመደን የወደፊት እጣ ፈንታ በማያወላዳ መልኩ የሚያስረግጥ ትርክት እየገፋ መውጣቱ፤ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ የፈውስ አድል የፈጠረ አጋጣሚ ነበር።

በኦህዴድ በኩል፤ ወደ መኃል ፖለቲካው ገፍቶ ለመግባት የታየው ተነሳሽነት ለውጤት እንዲበቃ ግን፤ ከኦሮሚያ ባሻገር ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ራዕያቸውን የሚያደርሱበት መድረክ ያስፈልጋቸው ነበር። የብአዴን ሰዎች፤ ለኦህዴድ የለውጥ ኃይል ክንፍ መዘርጊያ ቦታ በማመቻቸት ይህን መልካም አጋጣሚ ከክሽፈት ታድገውታል። በለውጡ ዋዜማ፤ በባህር ዳር ከተማ፤ የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች ጉባኤ በሚል በኦህዴድ እና ብአዴን ከተዘጋጀው መድረክ በኋላ፤ ቲም ለማ ላይ የነበረው አመኔታ እና ተስፋ፤ በመላው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ እንዴት ፋፍቶ እንዳደረ ላስተዋለ፤ የባህርዳሩ ጉባኤ፤ የቲም ለማ የአራት ኪሎ ጉዞ የሕዝብ ይሁንታ የተቸረበት ወሳኝ ምዕራፍ እንደነበር ለመገንዘብ አያዳግትም። በመጨረሻም፤ ኦህዴድ እና ብአዴን፤ የለውጥ ኃይሉን ይዞታ ከክልል ወደ ፌደራል የማስፋት የተናበበ ጥረት ሰምሮ፤ በዶ/ር አቢይ መመረጥ ሲጠናቀቅ፤ የነበረውን እፎይታ ማንም ኢትዮጵያዊ የሚረሳው አይመስለኝም።

ኢሕአዴግ ከስሩ ተገንድሶ ሀገር ይዞ ከመውደቁ በፊት፤ ውስጡ ለውጥ ፈላጊ አካል በቅሎ፤ ነባሮቹ አለቆች ያለ ብዙ እንገጭ እንጓ ተሰናብተው አዲስ አመራር መተካቱ፤ ለግዜውም ቢሆን ከተፈራዉ ትርምስ ሀገርን ታድጓል። ከዛም ባለፈ፤ አጠቃላይ በሂደቱ የተፈጠረው የመቀራረብ እና የመተማመን መንፈስ፤ የከረምንበትን የመለያየት ዘመን ዘግተን፤ አዲስ የስምምነት ምዕራፍ ለመክፈት ምቹ ድባብ የፈጠረ አጋጣሚ ነበር። ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ፤ የዶ/ር አቢይ የቤት ሥራም የሚሆነው፤ ይህን የታደሰ ሀገራዊ አንድነት በተቻለ መጠን አስጠብቀው እና አጠናክረው፤ የዲሞክራሲ ስርአት መሰረት መጣል የሚያስችል፤ አንጻራዊ መተማመን እና መረጋጋት ላይ ማድረስ ነበር። ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል? መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ እውነታ መልሱን አውንታዊ የሚያደርገው አይመስለኝም። እንዴት እዚህ ደረስን የሚለውን ለማየት ግን፤ በለውጡ ሂደት የተከሰቱ አንድ አንድ አንኳር ሁነቶችን ማስታወሱ ጠቃሚ ይመስለኛል። 

……………………………………..//……………………………………..

ዶ/ር አቢይ፤ የሥራ ዘመናቸውን፤ በሀገሪቱ ከተሞች እየዞሩ ሕዝብ በማነጋገር መጀመራቸው፤ ሀገር ከማረጋጋት አንጻር በበጎ ጎኑ የሚነሳ ተግባር ይመስለኛል። የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፤ ሚዲያ መክፈት መሰል መሰረታዊ የለውጥ እርምጃዎችም፤ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ሄደዋል። በወቅቱ የተወሰዱ አበረታች የለውጥ እርምጃዎች የመኖራቸውን ያህል ግን፤ ስሜትን ከማናር ውጭ ብዙም ትርጉም የሌላቸው በርካታ ክስተቶቸም ተስተናግደዋል። ለሳቸው ድጋፍ የተወጣው ሰልፍ፤ ያስከትለው አደጋ እና ተያይዞ የቀሰቀሰው አለመረጋጋት ለዚህ ተጠቃሽ ነው። ከባህር ማዶ የተመለሱ ተቀዎሚዎችን ለመቀበል የተደረጉ ሰልፎችም እንዲሁ አላስፈላጊ መንገጫገጭ ፈጥረው ነው ያለፉት። በአጠቃላይ ወቅቱ የተሻለ ስክነት ይፈልግ ነበር። የዶ/ር አቢይ፤ ከልክ ያለፈ የሕዝብን ስሜት የመማረክ ፍላጎት፤ ለውጡ ከአነሳሱ፤ ቴምፖው ተመጥኖ፤ ቀስ በቀስ ስር እየያዘ ሊሄድ ይችል የነበረበትን እድል ነፍጎታል።

ከውጭ ተመላሽ ተቃዎሚዎች፤ የታጣቁትን ጨምሮ ያለ በቂ ዝግጅት እና መግባባት በወከባ እንዲመለሱ መደረጉ፤ የዶ/ር አቢይ መንግስት ገና በጠዋቱ ከሰራቸው አንኳር ስህተቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ይመስለኛል። ከዚሁ፤ ከተቃዎሚዎች ወደ ሀገር ቤት መመለስ ጋር በተያያዘ፤ በወቅቱ ያን ያህል አይን ውስጥ የገባ ጉዳይ ባይሆንም፤ በግሌ ትኩረቴን የሳበ እና አሁን ላይ ምን አልባት የበለጠ ትርጉም ሊስጥ የሚችል አንድ ክስተት ላጋራ።

በፈረንጅ 2016 መጨረሻ፤ በዋሽንግተን ዲሲ፤ ግንቦት ሰባት፤ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር(ኦዴግ)፤ የአፋር ሕዝብ ፓርቲ እና የሲዳማ ህዝቦች ንቅናቄ የተካተቱበት፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የተባለ ድርጅት ተመስረቶ፤ በተለያዩ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች፤ በጋራ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር። ከመንግስት ጋር የሚደረግ ማንኛውንም ድርድር በጋራ ማድረግ በወቅቱ ድርጅቶቹ ስምምነት ከደረሱባቸው ነገሮች አንዱ ነበር። የዶ/ር አቢይን ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ግን፤ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር(ኦዴግ)፤ ብቻውን ሀገር ቤት ሊገባ መወሰኑ ተሰማ። በወቅቱ የግንቦት ሰባት ሰዎች እንደተናገሩት፤ የኦዴግ ሰዎች ስለሁኔታው ቀድመው አላማከሯቸውም።

ከነበረው ሁኔታ እንደገባኝ፤ ኦዴግ ሀገር ቤት ለመገባት የወሰነው፤ ከአዲሱ መንግስት የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ነው። የሆነው ይህ ከሆነ፤ ዶ/ር አቢይ ኦዴግን ነጥሎ መጥራት ለምን አስፈለጋቸው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ስለ ንቅናቄው አያውቁም እንዳይባል፤ ዶ/ር አቢይ፤ አይደለም በእድሜ ጠገብ ፖለቲከኞች የታጨቀ ድርጅት፤ የፌስ ቡክ አክቲቪስት ስም ሳይቀር ልቅም አድረገው እንደሚያጠኑ አሳይተውናል። በርግጥ፤ የገቡትን ቃል አክብረው ከውሳኔ በፊት ሁኔታውን ለተቀረው የንቅናቄው አባላት የማሳወቅ ተቀዳሚ ኃላፊነት የኦዴግ አመራሮች ነበር። ሆኖም፤ በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ፤ ተቃዎሚው እንዲሰባሰብ ምክር እና ተግሳጽ ከመለገስ ቦዝነው የማያውቁት ዶ/ር አቢይ፤ ከአስተምሮታቸው በተቃረነ መልኩ፤ የተሰበሰበ ተቃዎሚ የሚበትን ነገር ማድረጋቸው ለምን የሚል ጥያቄ የሚያጭር ነበር።

በወቅቱ የነበረኝ  መላምት፤ ምን አልባት ኢሕአዴግን ሊገዳደር የሚችል ሌላ ሀገር አቀፍ ግንባር መኖሩን ከመፍራት ወይም የኦሮሞ ድርጅቶችን በአንድ ለማሰባሰብ በነበረ እቅድ ምክንያት አድርገውት ይሆናል የሚል ነበር። ያም ሁኖ ግን፤ ነገሩን አግዝፌ አላየሁትም። ለሰላምም ለጠብም ትንሽ ነገር ነው የሚበቃው። ብዙም ሳይቆይ፤ ለግንቦት ሰባት እና በአጸፋው በሳምንቱ ለዳውድ ኢብሳ ኦነግ በተደረገው አቀባባል የተፈጠረው የፉክክር መንፈስ፤ የአዲስ አበባን ፖለቲካ እንዴት በአንዴ እንደቀሰቀሰው ሳይ፤ ንቅናቄው ባይበተን እና ብርሃኑ ነጋንም፤ ሌንጮ ለታንም የሚሉ ወጣቶች፤ አንድ ላይ አቀባበል ለማድረግ እድል አግኝተው ቢሆን ኖሮ፤ ምን አልባት፤ ኋላ ላይ ለዳውድ ኢብሳ ኦነግ የተደረገው አቀባበል ቢደረግ እንኳን ወደ ፍክክር መድረክነት መቀየር አያስፈልገውም ነበር። ተያይዞም የለውጡን ደስታ አጣጥመን ሳንጨርስ በአዲስ አበባ ጉዳይ አተካራ ውስጥ ከመግባትና፤ ተያይዘው ከመጡ አለመረጋጋቶች ይታደገን ይሆን ነበር ብየ እንዳስብ አድርጎኛል።

……………………………………..//……………………………………..

የኢሕአዴግ መለወጥ እውን እየሆነ፤ ለግዜውም ቢሆን ሀገርም፤ ኢሕአዴግም መትረፋቸው ሲረጋገጥ፤ ብቅ ካሉ አጀንዳዎች መካከል፤ በቀደመው የኢሕአዴግ ዘመን የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ሆነ ሌሎች አስተዳደራዊ በደሎች እንዴት ይሰተናገዳሉ የሚለው አንዱ ነበር። በግሌ ተቃርኖ ላይ የተመሰረተው የኢሕአዴግ ፖለቲካ ያስከተለው ሀገራዊ ኪሳራ ላይ መግባባት ላይ መድረስ እስከተቻለ ድረስ፤ የእርቅ እና ይቅርታው መንገድ የተሻለው አማራጭ ነበር ባይ ነኝ። መጀመርያ ላይ በለውጥ ኃይሉ የተንጸባረቀው አቋምም በይቅርታ ይታለፍ የሚል ነበር። ዶ/ር አቢይ ራሳቸው፤ ካልተሳሳትኩ ፓርላማ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ባለፉት ዓመታት ለደረሰው ጥፋት ወንጀለኞችን እንቅጣ ብንል፤ ሌላ ስራ መስራት አይቻልም፤ ለሰላም ሲባል ያን ምዕራፍ በይቅርታ ብንዘጋው የተሻለ እንደሚሆን አስረገጠው መናገራቸውን አስታውሳለሁ። በኋላ ላይ፤ ከየት መጣ ሳይባል፤ አንድ ቀን ተኝተን ስንነቃ፤ ቃላቸውን አጥፈው በሕወሃት/ኢሕአዴግ ስታይል በቴሌቪዥን ዶክመንታሪ የታጀበ ክስ እና እስር ጀምረው አገኘናቸው።

ለውጡ፤ በአደራ ተሰጣቸው እንጅ፤ እንዳሻቸው ሊወስኑበት፤ የዶ/ር አቢይም ሆነ የፓርቲያቸው ንብረት አልነበረም። ወደ ፍትህ መሄድ ካስፈለገ፤ መጀመሪያ ሂደቱ ምን ሊመስል እንደሚችል ሁሉንም ወገን ባሳተፈ ምክክር እና ገለልተኛ ኮሚሽን መመርመር ነበረበት። የብሔሄር ማንነት፤ ከፖለቲካ ፖርቲ ጋር አብሮ በተለወሰበት በዚህ ዘመን፤ እንደ ደርግ ግዜው፤ የፓርቲውን አውራዎች ሰብስቦ በማጎር፤ በቀላሉ ሒሳብ ማወራረድ አይቻልም። በዚያ ላይ፤ አዲሱ መንግስት፤ ከቀደመው መንግስት ማህጸን የወጣ እንደመሆኑ፤ የከሳሽ እና ተከሳሹን መስመር መለየት ሌላ ፈተና ነው። ዶ/ር አቢይ፤ እኒህን እና መሰል ጥያቄዎች ግልጽ አቅጣጫ ሳይቀመጥላቸው፤ ጥቅምና ጉዳቱ ሳይፈተሽ፤ በዘፈቀደ ጀምረው አዝረክረከው የተውት እስር እና ክስ፤ ለውጡ የፈጠረውን የእርቅ እና የመተማመን ድባብ አላግባብ አደፍርሶ ነው ያለፈው።

ሕወሃት ለውጡን አሜን ብሎ ይቀበላል? ወይስ ያልሞት ባይ ታጋዳይ ሆኖ ሀገር ያተራምሳል? የሚለው ጥያቄ በለውጡ ዋዜማ የብዙዎች ጭንቀት ነበር። እግዜአብሄር ቀርቦን፤ የተፈራው ሳይሆን፤ ያለብዙ ትርምስ የስልጣን ርክክብን ማድረግ የተቻለበት አጋጣሚ ተፈጠረ። ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን፤ የሕወሃት ሰዎች አንዴ የፌደራል መንግስቱን ለቀው ከሄዱ በኋላ፤ የዶ/ር አቢይ መንግስት፤ ከሕወሃት ጋር ያለውን ልዩነት አስታሞ አብሮ መቀጠል ቢችሉ፤ ለሀገር መረጋጋት የተሻለው መንገድ ነበር። አልሆነም። ለዚህ ደግሞ ተጠያቂው ሕወሃት ብቻ አይደለም። ዶ/ር አቢይም፤ ከሕወሃት ጋር ግብ ግብ መግጠሙን የፈለጉት ነው የሚመስለው። “የቀን ጅብ”፤ “ጸጉረ ልውጥ” እያሉ በነገር መውጋት የጀመሩት እሳቸው ናቸው። በሜቴክ እና በደህንነት ሰዎች ላይ የከፈቱት ድንገቴ እስርም፤ የሕወሃት ስዎችን ከማስደንበር ውጭ ሌላ እርባና ነበረው ለማለት ያስቸግራል። ለክሱ ማጀቢያ የተለቀቀው ዶክመንታሪ ላይ፤ የገራፊዎቹ ትግራኛ ተናጋሪነት፤ የተሰጠው አጽኖት እና መሰል ሁኔታዎችን ላስተዋለ ደግሞ፤ ከሕወሃት ጋር ብቻ ሳይሆን ከትግራይ ሕዝብ ጋርም መላተም ተፈልጓል ያሰኛል።

ይህን ስል፤ ዶክመንታሪው ላይ የቀረቡትን፤ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ወገኖች እየኮነንኩ አይደለም። እነሱ፤ ታሪካቸውን በሚያውቁት መልኩ መናገራቸው ጥፋት የለውም። ችግሩ የዶ/ር አቢይ መንግስት በደሉን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ያዋለበት ሁኔታ ነው። ያን ማድረግ ለምን እንዳስፈለገ ግራ ያጋባ ነበር። የዶክመንተሪው አጠቃላይ ድምጸት ሕዝብ ለማቃቃር እንጅ የማንንም ቁስል ለመሻርም ሆነ ፍትህ ለማስፈን ያለመ አይመስልም። ምጸቱ፤ ይህ የሚደረገው፤ ስለ ፍቅር እና ይቅርታ አብዝተው በሚሰብኩት ዶ/ር አቢይ በሚመራ መንግስት መሆኑ ነው።

……………………………………..//……………………………………..

ገዥው ፓርቲ፤ ከኢሕአዴግ ወደ ብልጽግና ያደረገው ጉዞ፤ ለውጡ ካስተናገዳቸው አበይት ክስተቶች፤ ግንባር ቀደም ተጠቃሹ ይመስለኛል። በመርህ ደረጃ፤ የፖለቲካው ጡዘት ማዕከል ከብሔር ማንነት ወደ ሀሳብ ልዩነት እንዲሻገር ለሚመኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ፤ የኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ወጥ ፓርቲነት መቀየር በመርህ ደረጃ የሚኮነን ነገር አልነበረውም። ተጨባጭ አተገባበሩን ካየን ግን፤ ጊዜውን የጠበቀ እና እውነተኛ መግባባት ላይ የተመሰረተ አልነበረም። ውህደቱ ነጻ እና ግልጽ ውይይት ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን የዶ/ር አቢይ ፍላጎት ላይ ተንጠልጥሎ የተቀናበረ ነው። ከጽንሰቱ ጀምሮ፤ ከስም ለውጡ እና በቀድሞው ግንባር ውስጥ ያልተካተቱ አጋር ይባሉ የነበሩ ድርጅቶችን ከመጨመሩ ውጭ አዲስ ይዞት የመጣው ሌላ ነገር ምን እንደሆነም ግልጽ አልነበረም።

ኢሕአዴግ የዘረጋው ክፍፍል ድርጅቱ ላይ የተንጠለጠለ ብቻ አይደልም። የፖለቲካ ትርክቱ፤ ህገ መንግስቱ፤ የመንግስት መዋቅሩ እንዳለ ሁሉም ነገር የብሔር መስመርን ተመርኩዞ የታነጸ ነው። ሌላው ነገር በቦታው ባለበት፤ ኢሕአዴግ ፈርሶ ወጥ ፓርቲ ስለሆነ፤ ያን ያህል የሚቀይረው ነገር ይኖራል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል። ከሆነም ግን፤ ቅድሚያ የተዘበራረቁ እይታዎችን መሰብሰብ፤ የሚጋጩ ሀሳቦችን ማስታረቅ እና እውነተኛ መተማመን መፍጥር ላይ ማተኮር ያስፈልግ ነበር። ያ ሳይሆን፤ አንኳር በሆኑ ጉዳዮች ዙርያ የተደረሰ ስምምነት፤ የተቀየረ አቋም፤ ቢያንስ በልዩነት ተለይቶ አቅጣጫ የተቀመጠለት አጀንዳ በዝርዝር ባልተገለጸበት ሁኔታ፤ የተደረገ “ውህደት”፤ ከፈረሱ ጋሪውን፤ ከይዘት በፊት የቅርጽ ለውጥን ያስቀደመ በመሆኑ፤ የተባለውን ወጥነት ሊያመጣ የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም።

ውህደቱ ተጀምሮ ተቋጨ የተባለበት ግዜ፤ ከነገሩ ክብደት ጋር በፍጹም የሚመጣጠን አልነበረም። በጣም ተካልቧል። የልዩነት እጥረት በሌለበት ሀገር፤ ምንም ኮሽታ ሳይሰማ ውህደቱ ተጠናቀቀ ሲባል፤ መድረኩ ነጻ እንዳልነበረ መገመት አያዳግትም። መጠነኛም ቢሆን፤ የቅሬታ ፍንጭ የተሰማው ከሶዴፓ በኩል ነበር። በተለየ በወቅቱ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት የህግ አማካሪ የነበሩት አቶ ጀማል ዲሪዬ፤ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ ስብስባው ውስጥ የነበረው ሂደት ከውይይት ይልቅ “ዲክቴሽን” እንደሚያጠቃው፤ ሀሳብ ለማንሳት በቂ እድል እንዳልነበረ እና ለውይይት የተዘጋጀውን ዶክመንት እንኳን ከስብሰባው አዳራሽ ይዞ መውጣት የተከለከለ እንደነበር ጠቅሰው፤ በመርህ ደረጃ ሶዴፓ ውህደቱን ባይቃወምም እነዚህ ሁኔታዎች ብልፅግናን ለመቀላቀል አስቸጋሪ እንዳደረጉባቸው የሰጡት ማብራሪያ ሰለ ውህደቱ ሂደት ባህሪ ትልቅ ፍንጭ የሰጠ ነበር። ይህ ቃለ መጠይቅ ከተላለፈ ከጥቂት ቀናት በኃላ ግን ቅሬታው በምን አኳኋን እንደተፈታ ሳይታወቅ፤ ሶዴፓ ውህደቱን ተቀላቅሏል የሚል ዜና ተለቀቀ።

በአጠቃላይ፤ የብልፅግና ምስረታ ሂደት ወካባና ማድበስበስ የተጠናወተው ነበር። የሆነው ሁሉ ሆኖ ግን፤ ከሂደቱ መጠናቀቅ ጥቂት ግዜ በኋላ፤ ለማ መገርሳ በቪኦኤ በኩል ያሰሙትን የተቃውሞ መልእክት ያክል፤ የውህደቱን ስንጥቅ ያጋለጠ ነገር ያለ አይመስለኝም። ለማ መገርሳ እዚህ አቋም ላይ የደረሱበትን ምክንያትም ሆነ ዝርዝር ሀሳባቸውን ባላውቅም፤ በደፈናው ግን “በውህደቱ አልተስማማሁም፤ መደመርም አይገባኝም” ሲሉ እውነት ነበራቸው።

“መደመር” የሚለው የዶ/ር አቢይ ቋንቋ፤ መለያየቱ አልጠቀመንም፤ የሚያዋጣን አብሮነት ነው የሚለውን ሀሳብ፤ ቅልብጭ ባለ አማርኛ የሚገልጽ አባባል በነበረበት ጊዜ ትርጉም ይሰጥ ነበር። ወደ ፖለቲካል ፊሎዞፊነት አድጎ፤ የፓርቲ መርህ ከሆነ በኋላ ግን፤ የሚያዝ የሚጨበጥ ነገር አልሆነም። ከፖለቲካው የሚጠበቀው፤ እንዴት እንደመር፤ እንዴት ፍላጎቶቻችንን አቻችለን አብረን እንጓዝ ለሚለው ጥያቄ ተጨባጭ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንጅ የአንድነትን ጥቅም አብዝቶ እና አስፍቶ መስበክ አይመስለኝም። እሱንማ ልቦናው ያልታወረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያውቀዋል። የቸገረው በተግባር የሚደምረው ነው።

ብልጽግናም ለምን እንደዚያ በጥድፊያ ለመመስረት እንደተፈለገ ግልጽ አልነበረም። የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችን ወደ አባልነት ለመቀላቀል፤ ኢሕአዴግን ማፍረስ የግድ ይጠይቅ የነበረ አይመስለኝም። ግንባሩንም እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይቻል ነበር። የሆነው ሆኖ፤ የነሱ በውህደቱ መካተት እንደ አንድ በጎ ጎን ሊጠቀስ ይችላል። ከዛ በተረፈ ግን ውህደቱ ይዞት የመጣው አዲስ ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ አዳጋች ነበር። በኦዲፒ እና በኦሮሚያ ብልጽና ወይም በአዴፓ እና በአማራ ብልጽና መካከል፤ በሌሎቹም ከስም ለውጡ ውጭ፤ ምንም የርዕዮትም ሆነ የመዋቅር ለውጥ አልታየም። እንዲያውም መለያየቱ ብሶባቸዋል። ከውህደቱ በኋላ የተቀየረ አንድ ነገር ቢኖር፤ ሊቀመንበሩ ዶ/ር አቢይ፤ የድርጅት አጥር ሳያግዳቸው ሁሉም ቦታ ጣልቃ ለመግባት ያገኙት ህጋዊ ሽፋን ነው። የውህደቱ ዋና አላማም ይኸው ብቻ ይመስላል። በመለስ ዜናዊ ልክ የተሰፋውን ኢሕአዴግ፤ የአቢይ አህመድን ወርድ እና ቁመት እንዲመጥን ቀዶ መስፋት።

……………………………………..//……………………………………..

ከብልጽግና ምስረታ ጋር በተያያዘ፤ በዶ/ር አቢይ እና በለማ መገርሳ መካከል የተፈጠረው ግጭት፤ ስለ ዶ/ር አቢይ እና ፓርቲያቸው ብልጽግና ባህሪ ብዙ እውነታ ገልጾ ነው ያለፈው። ከለማ መገርሳ የቪኦኤ ቃለመጠይቅ መገመት የሚቻለው፤ የለማ መገርሳ አቋም ለዶ/ር አቢይ አዲስ አይደለም። በውስጥ ብዙ የተነጋገሩበት ጉዳይ ነው የሚመስለው። ነገር ግን፤ ዶ/ር አቢይ አለመግባባቱ ሳይፈታ ወደ ውህደት ለመሄድ እንደወሰኑ ነው የገባኝ። ዶ/ር አቢይ አንድ መግባባት ላይ እስኪደረስ ድረስ ቢታገሱ ለሁሉም ጥሩ ነበር። ካልሆነ ግን፤ የለማ መገርሳን ሀሳብም እንደ ዶ/ር አቢይ በመንግስት ሚዲያ ልንሰማው ይገባ ነበር። ይህን ማድረግ ስላልቻሉ ይመስለኛል በቪኦኤ በኩል የመጡት። የለማ መገርሳ የቪኦኤ ኢንተርቪው ተለቆ፤ የተፈጠረው አለመግባባት ይፋ ሆኖ አቧራ ሲያስነሳ፤ በኦዲፒ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ፤ ተረጋጉ መሪዎቻችን ታርቀዋል የሚል ይዘት ያለው አጭር መልእክት ተለጥፎ ነበር። ለማ መገርሳ ከፓርቲው በይፋ ከታገዱ በኋላ የኦዲፒ ሰዎች እንደነገሩን ግን፤ ለማ መገርሳ ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደረገ እንጅ፤ የወረደ እርቅ አልነበረም።

በወቅቱ፤ እግዱን አስመልክቶ የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፤ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፤ ለፋና በሰጡት መግለጫ፤ ለማ መገርሳ፤ ከፓርቲው መስመር ውጭ፤ ለቪኦኤ በሰጡት ሕዝብን የሚያደናግር መረጃ፤ በኦዲፒ ስራ አስፈጻሚ በአካል ተጠርተው ስለጉዳዩ ሲጠየቁ፤ ስህተት መሆኑን አምነው፤ ተጸጽቻለሁ፤ ድርጅቴ፤ ፓርቲየ ይቅርታ ያድርግልኝ ያሉበት ጉዳይ ላይ፤ ተመልሰው መገኘታቸው ለእገዳው ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል። ወ/ሮ ጫልቱ ጨምሮ እገዳውን በተመለከተ ከኦሮሚያ ብልጽግና አባላት የተሰጡት መግለጫዎች፤ የፓርቲ መስመር… ሂስ…ግለ ሂስ…እርምጃ….መረጃ ለጠላት አሳልፎ መስጠት….ይቅርታ…ጽናት…..ቁርጠኝነት እና መሰል ኮሚኒስታዊ ቃላት መታጨቁ፤ ምቾት የሚነሳው የመጀመሪያው ነገር ነው። ሲቀጥል፤ ለማ መገርሳ ላይ የቀረበው፤ ከፓርቲው ፈቃድ ውጭ የግል አቋም ማንጸባረቅ እና ለፓርቲ አለመታዘዝ ክስ፤ የኢሕአዴግ ወራሽ የሆነው ብልጽግና፤ ልክ እንደ ኢሕአዴግ፤ በማዕከላዊነት ለመጠርነፉ ሌላው ምስክር ነው። የፓርቲ አቋም…የፓርቲ ፈቃድ..ፓርቲውን ይቅርታ መጠየቅ ገለመሌ ገለመሌ መባል መጀመሩም፤ ፓርቲው ውስጥ አንድ ፈላጭ ቆራጭ አሸንፎ ለመውጣቱ ምልክት ነበር።

ለማ መገርሳን ያስገፋቸው የአዲሱን አለቃ፤ የዶ/ር አቢይን ውሳኔ እንደወረደ ለመቀበል ማንገራገራቸው መሆኑ ነው የሚገባኝ። ዶ/ር አቢይ ግን በእገዳው ሰሞን  አንድ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ስለ ኦሮሚያ የጸጥታ ጉዳይ አንስተው፤ “ማንንም አልማርንም…መጨከን በማንችልባቸው ሰዎች ሁሉ ጨክነን እርምጃ እየወሰድን ነው” በማለት የለማ መገርሳን እገዳ፤ ህግ ከማስከበር እርምጃ ጋር ለማስጠጋት ሲሞክሩ ተደምጠዋል። ነገሩ፤ ታምራት ላይኔን፤ ለውስጥ ጉዳያቸው፤ ውቃቤ አሳጥተው እስር ቤት ከወረወሩ በኋላ፤ “ከታምራት የቀረበ ወንድም የለኝም…ነገር ግን…ከግል ስሜት…ህግ ይቀድማል…የሕዝብ አደራ ይቀድማል” አይነቱን የመለስ ዜናዊን ስላቅን የሚያስታውስ ነበር።

……………………………………..//……………………………………..

የለውጡ መጀመርያ ላይ፤ ኢሕአዴግ ውስጥ፤ በተለይ ኦህዴድ እና ብአዴን አካባቢ ብዙ ተስፋ ሰጭ ነገሮች አይተን ነበር። ባለስልጣናቱ የሚያስተላልፉት መልእክት፤ በግድ ወጥ እንዲሆን ያልተጨፈለቀ፤ ግን ከሞላ ጎደል የተናበበ ነበር። በኢሕአዴግ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፤ ድርጅቶቹ ለሕዝብ ቅርብ መሆን ጀምረው ነበር። አዲሱ የነጻነት እና የግልጽነት መንፈስ ግን ብዙም አልዘለቀም። ቀስ በቀስ ነገሮች መልካቸውን መቀየር ጀመሩ። ከመነሻው፤ ዶ/ር አቢይ አዛዥ ናዛዥ የመሆን ዝንባሌ የሚያጠቃው ስብእና እንዳላቸው ፍንጭ የሚሰጡ ብዙ ነገሮች ነበሩ። ሆኖም በግሌ፤ በአባል ድርጅቶቹ እና ለውጡን በመሩት ግለሰቦች መካከል የሚኖረው የእርስ በእርስ መሳሳብ፤ በዛ አቅጣጫ ከመጓዝ ይገታቸዋል የሚል ተስፋ ነበረኝ። አልሆነም። ዶ/ር አቢይ፤ የፌደራል ስልጣን የሰጣቸውን ክንድ ተጠቅመው፤ ከሕወሃት ጫና ተላቆ፤ ገና ወፌ ቆመች ማልት የጀመረውን ፓርቲ፤ የደርግ ስብስብ የሚወገደው ተወግዶ፤ የሚንበረከከው ተንበርክኮ ወደ መንግስቱ ኃይለማርያም ጀሌነት በተቀየረበት ፍጥነት፤ በአንድም በሌላም መልኩ ፓርቲያቸውን ተላላኪያቸው ማድረግ ተሳክቶላቸዋል። ምናልባትም፤ ዶ/ር አቢይ፤ ውለው ሳያድሩ፤ በለውጡ ሂደት ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸውን፤ ለማ መገርሳን እና ገዱ አንዳርጋቸውን፤ በሹመት ስም፤ ከፖለቲካው ጡዘቱ እምብርት እና ከሕዝብ አይን አርቀው፤ እሳቸው ሙሉ በሙሉ በሚቆጣጠሩአቸው የፌደራል መስሪያ ቤቶች ውስጥ መወሽቅ ያስፈለጋቸው ለዚህ ነበር።

የዶ/ር አቢይ በዚህ መልኩ ፓርቲያቸውን ማኮላሸት፤ ፓርቲው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሊጫወት ይችል የነበረውን በጎ አስተዋጽዖ በአጭሩ ቀጭቶታል። በተለይ ከለማ መገርሳ ጋር የፈጠሩት መለያየት፤ በኦዲፒ በኩል የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ወደ መኃል ለመሳብ የነበረውን እድል አጨናግፏል። ድልድይ ሆነው ወደ ዲሞክራሲ ያሻግሩናል ብለን እምነት የጣልንባቸው ሰው፤ የገዛ ፓርቲአቸውን አፍነው መገኘት፤ ለዲሞክራሲ የተሰነቀው ተስፋ ላይ ውሃ የሚቸልስ አሳዛኝ ክስተትም ነበር። በተጨማሪ ግን ሆኔታው ሌላ አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳትን ያስገድደናል። ዶ/ር አቢይ፤ ፓርቲውን በማዕከላዊነት ከጠረነፉ፤ የክልል ርዕሰ መስተዳድሮችን ሳይቀር ነቅሎ ለመትከል የረዘመ እጅ ካላቸው፤ በተጽእኖ ፈጣሪነት አቻቸው የነበሩትን ለማ መገርሳን አሽንቀጥሮ መጣል ከተቻላቸው፤ ቀደም ብሎ በለውጡ መጀመሪያ ላይ አዲስ አበባን በተመለከተ፤ ከኦዲፒ ጽህፈት ቤት የተለቀቀው አደናጋሪ መግለጫ፤ ለማ መገርሳ የአዲስ አበባ ዲሞግራፊን ስለመቀየር የተናገሩት፤ የሽመልስ አብዲሳ የመስቀል አደባባይ “ነፍጠኞቹን ሰባበርናቸው” ፉከራን ጨምሮ ስለ የ”ኮንቪንስ” እና የ”ኮንፊውዝ” የቁማር ፖለቲካ የዘረገፉት ዲስኩር እና መሰል ነገሮች ከዶ/ር አቢይ እውቅና ውጭ ሊደረጉ ይቻላል ብሎ ማሰብ ይቻላል ወይ?

የፍቅር እስከ መቃብር ደራሲ፤ ሀዲስ አለማየሁ፤ በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ፤ ለአንድ ባልንጀራቸው፤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፊት ቀርበው ስለገጠማቸው ያጫወቱትን እና የመለሰላቸውን መልስ ሲያጋሩ፤ “ጃንሆይ ሥራዬን አመስግነው….ሽልማት፤ ስጦታ አዘውልኝ ነበረ…ባለሟሎች ግን….ዛሬ ና….ነገ ና….እያሉ…ምክንያት እያበዙ ከለከሉኝ…እኔም ምልልሱ ሲሰለቸኝ ተውኩት” ብየ የሆነውን አዝኘ ለአንድ ባልንጀራዬ አጫወትኩት፤ እሱም መልሶ፤ “አይይ…የዛን ቤት ሥራ አታውቅም ማለት ነው፤ ጃንሆይ ካልመሰላቸው፤ አንተን ካሰናበቱ በኋላ፤ ትዕዛዝ የተቀበለውን ባለሟል..”ማነህ አንተ” ብለው ጠርተው፤ “አሁን የተናገነውን ነገር እርሳው” ብለው ነው ወደ ውስጥ የሚገቡት” አለኝ ይላሉ። ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ ንጉሥ መናገር የማይፈልገውን በምስለኔ አፍ ማናገር፤ ፈረንጆቹ “ዘ ኦልደስት ትሪክ ኢን ዘ ቡክ” እንደሚሉት፤ የቆየ የኖረ ማወናበጃ ነው። ለምን ይህን ማድረግ አስፈለጋቸው የሚለው ሌላ ርዕስ ሆኖ፤ ተጨባጭ ሁኔታው፤ አይደለም ከዶ/ር አቢይ እውቅና ውጭ፤ ያለ እሳቸው መመርያ ፓርቲው ውስጥ የሚሆን ነገር ነበር ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም።

……………………………………..//……………………………………..

ኢሕአዴግን አፍርሶ ብልጽግናን በመመስረቱ ሄደቱ ላይ ጡንቻቸው አይሎ የወጣበት ሁኔታ፤ ዶ/ር አቢይ በሕወሃት እግር ተተክቶ ሀገር የመጠቅለል እንጅ ተስፋ እንደተጣለባቸው ለዲሞክራሲያዊ ስርአት መንገድ የመጥረግ ሀሳብ እንደሌላቸው የማያወላዳ ፍንጭ የሰጠው የመጀመሪያው ትልቅ ክስተት ይመስለኛል። ዶ/ር አቢይ ከሕወሃት የወረሱት ግን አምባገነንነትን ብቻ አይመስልም።  የጫሩትን ጠብ እየገላገሉ ስልጣን የማራዘም ስልትንም ጭምር እንጅ። ካልሆነ፤ በአንድ በኩል ተቃዋሚ እንዲስበሰብ እየመከሩ፤ በሌላ በኩል መኃል እየገቡ ተቃዋሚውን መሰነጣጠቅን ምን ይሉታል? ደህና ለቆን ከሄደ በኋላ፤ ሕወሃትን ኋላ ኋላው እየተከታተሉ መተንኮሳቸውስ፤ የሞት የሽረት ሲፈራገጥ የሚፈጥረውን አቧራ ፍለጋ ካልሆነ ሌላ ምን ትርጉም ነበረው? እሳቸው ሌላ እየተናገሩ፤ ባለስልጣኖቻቸውን ሌላ እያናገሩ ማወናበድ የመረጡበት ምክንያትስ፤ አለመረጋጋት እና አለመተማመን ለመፍጠር ካልሆነ ሌላ ለምን ሊሆን ይችላል?

የዶ/ር አቢይ እርምጃዎች መልካቸውን ቀይረው፤ ከታሰበው በተቃራኒ ሀገራዊ አንድነትን ማደፍረስ የጀመሩትም በጊዜ ነው። በለውጡ ሂደት ተፈጥሮ የነበረውን የስምምነት እና የትብብር መንፈስ ሳንጠቀምበት እንደ ጉም ነው የተነነው። “ነፍጠኛ” እና “ጽንፈኛ” እየተባባሉ መጣረሱ በአዲስ መልክ ተፋፍሞ ለመምጣት ግዜ አልወሰደበትም። ዶ/ር አቢይ፤ ላይ ላዩን ኢትዮጵያዊነት ድንኳን ውስጥ፤ ውስጥ ውስጡን ኦሮሞ ብሄርተኝነት ድንኳን ውስጥ እየዋዥቁ፤ በኢትዮጵያ ብሄርተኛው እና በኦሮሞ ብሄርተኛው መካከል የተንጋለለውን ገደል፤ እንደታሰበው ሊደፍኑት ቀርቶ፤ ይባስ ቦርቅቀውት ነው ያረፉት። አሽሙር፤ ትንኮሳ እና ሽንገላ የሚያጠቃው ንግግራቸው፤ ይበልጥ እያራራቀን እንጅ እያቀራረበን አልመጣም። ባለሀብቱን ሰብስበው ምሁሩን ያብጠለጥላሉ። ሲቪክ ሶሳይቲውን ሰብስበው ተቃዋሚውን ያበሻቅጣሉ። ካልጠፋ ቦታ፤ ቤተክርስቲያን ደጃፍ ለመስጊድ ቦታ ይሰጣሉ። የተምታታ መልእክት “ሚክስድ ሲግናል” እየለቀቁ ያደናብራሉ። አላስፈላጊ የጥቅም ግጭት እየፈጠሩ ሕዝብ ያቃቅራሉ። ብቻ በጥቅሉ፤ የዶ/ር አቢይን፤ እምዬ ሀገሬ…ቀለሜ ህልሜ ሙዚቃ፤ ወደ ጎን አግልለን ካየነው፤ ከመነሻውም ያደርጉት የነበረው ሁሉ፤ ከሕውሃት/ኢሕአዴግ ዘመኑ የከፋፍለህ ግዛ ፖለቲካ የተለየ ነገር አልነበረውም።

……………………………………..//……………………………………..

መጀመሪያ ላይ፤  በቲም ለማ ይገፋ የነበረው የኢትዮጵያዊነትና የአንድነት እሳቤ ሁሉንም ወገን ወደ መኃል ማሰባሰብ ችሎ ነበር። እያደር ግን፤ በተለይ ዶ/ር አቢይ ስልጣኑ ላይ መደላደል ከጀመሩ በኋላ፤ ኢትዮጵያዊነት፤ ሀገራዊ አንድነት የሚለው አስተሳሰብ፤ ሁሉንም ወገን የመቀራረቢያ፤ የማግባቢያ ሳይሆን፤ ብሔርተኛውን የማስበርገጊያ፤ የብሔር ፖለቲካውን የሚቃወመውን ክፍል ደግሞ የማደንዘዣ መሳርያ ነው የሆነው። የኢሕአዴግ መፍረስ እና የብልጽግና መመስረት፤ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያሰፋው ተቃርኖ እና ፖለቲካው ላይ የፈጠረው አላስፈላጊ ውጥረት፤ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።

ምንም እንኳን ብልፅግና፤ ፓርቲውን ለዶ/ር አቢይ የአገዛዝ እቅድ አመቻችቶ ከማዋቀር ውጭ ሌላ ሀገራዊ ፋይዳ ባይኖረውም፤ ከኢሕአዴግ የተሻለ የመዋቅርም ሆነ የርዕዮት ወጥነት ባይታይበትም፤ ከዶ/ር አቢይ የዕዝ ሰንሠለት ውጭ የብልጽግና ቅርጫፎችን የሚያስተሳስራቸው ሌላ ነገር መኖሩ ከጅምሩ አጠራጣሪ የነበረ ቢሆንም፤ ዶ/ር አቢይ ብልፅግናን ለብሔር ክፍፍሉ የሆነ ሁነኛ መድሃኒት አስመስለው ነው ያስተዋወቁት። በዚህም፤ የብሔር ክፍፍሉን እና በብሔር መደራጀቱን ከሚኮንነው ወገን በጎ ምላሽ አገኝተውበታል። በቀጣይ መንግስታዊ መዋቅራዊ ለውጦች ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አላቸው የሚል እምነት እንዲጣልባቸው አድርጓል። ዶ/ር አቢይም ይህን ስሜት ለመፍጠር አስልተው እንደተንቀሳቀሱ ነው የማስበው።

በግልባጩ፤ ምንም እንኳን ብልፅግና፤ በተግባር ከኢሕአዴግ የተለየ ነገር ባይኖረውም። በይዘት ደረጃ የብሔር መስመሩ ባይፈርስም። የኢሕአዴግን መፍረስ፤ የብሔር ተኮር ፌደራሊዝሙ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው የወሰዱ ወገኖችን የመደናበር ስሜት ውስጥ እንዲገቡ፤ ወደ ጠርዝ እንዲወጡ እና እንዲሰባስቡ አድርጓቸዋል። በወቅቱ፤ የብሔርተኛው፤ በተለይ የሕወሃት እና የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አንድ ጎራ መሰባሰብ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛውን በተራው ሽብር ውስጥ እንዲገባ እና ዶ/ር አቢይ ጋር ይበልጥ እንዲጣበቅ አድርጎታል።

በአንድነት፤ ክፍፍልን በማጥፋት ሽፋን የተከናወነው የኢሕአዴግ መፍረስ እና የብልፅግና መመስረት፤ ፖለቲካውን የባሰ ውጥረት ውስጥ ከቶት ነው ያለፈው። ዶ/ር አቢይ ግን የፈለጉትን ውጤት እንዳገኙ ነው የሚሰማኝ። ዶ/ር አቢይ ከፋፍለው የሚገዙ ከሆነ፤ ልክ እንደ ሕወሃት፤ በዋናነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛውን እና ኦሮሞ ብሔርተኛውን፤ ዳር እና ዳር፤ ሁለት ጽንፍ ላይ አስቀምጦ ማጫወት ግድ ይላቸው ነበር። ይህንንም ማድረጉ በጠዋቱ ተሰክቶላቸዋል ማለት የሚቻል ይመስለኛል።

……………………………………..//……………………………………..

ዶ/ር አቢይ፤ ከብልጽግና መመስረት ቀደም ብሎም፤ ከአዲስ አበባ ጉዳይ ጋር በተያያዘ፤ ተመሳሳይ መሳሳብ የፈጠሩበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል። የአዲስ አበባ ጉዳይ መነሳት ከነበረበት፤ ስርአት በያዘ ሁኔታ፤ ሁሉን አቀፍ በሆነ መድረክ፤ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ እስኪስተናገድ በይደር መቆየት ነበረበት። ይህ ሳይሆን ቀርቶ፤ የአዲስ አበባ አጀንዳ በድንገት፤ በግጭት መልኩ በመፈንዳቱ፤ በለውጡ ሂደት ተፈጥሮ የነበረው የመቀራረብ መንፈስ ደፍርሶ፤ ነገሩን በሰከነ እና ስርአት በተበጀለት የውይይት መድረክ ለማየት የነበረው እድል ተደናቅፎአል።

ወደ ኋላ ተመልሰን ካየን፤ የሁሉም ወገን ስሜት እንዲጋጋል እና የአዲስ አበባን ጉዳይ ያለጊዜው ተቀስቅሶ እንዲጦዝ ምቹ ሁኔታ የፈጠረውን የጸጥታ ክፍተት ሲፈጥር የነበረው የዶ/ር አቢይ መንግስት እንደነበር መመልከት ይቻላል። ሌላ ሌላውን ወደ ጎን ብንተወው እንኳን፤ ኦዲፒ ከየት መጣ ሳይባል፤ የአዲስ አበባን ባለቤትነት በተመለከተ ድንገት የለቀቀው መግለጫ እንዴት አለመግባባቱን ወደ ላቀ ሁኔታ እንዳሳደገው ማስታወስ ይቻላል።

እንደማስታውሰው፤ የኦዲፒ መግላጫ፤ ቀደም ብሎ፤ በቡራዩ ከደረሰው አደጋ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የአዲስ አበባ አካባቢዎች፤ በኦሮሚያ ህንጻዎች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ በአምስት የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የወጣን መግለጫ ታኮ ነው የተለቀቀው። ኦዲፒ፤ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ፤ በሌሎች የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች ከተያዘው አቋም ጋር የሚዛመድ መግለጫ ማውጣቱ፤ አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት የሚለውን ሀሳብ በማይጋራው ወገን ሰፈር ከፍተኛ ስጋት እንዲቀሰቀስ እና ይህን እመክታለሁ የሚል አካል፤ አክርሮ ገፍቶ እንዲወጣ ምክንያት ሆኗል። አንዱ ወገን በገፋ ቁጥር ደግሞ፤ ሌላኛው ወገን አጸፋውን እጥፍ ድረብ አድርጎ ይመልሳል። ትንቅንቁ እንደዚህ እያለ ነው የቀጠለው።

ቀደም ብየ እንዳነሳሁት ኦዲፒ ከዶ/ር አቢይ እውቅና ውጭ ያደረገው ነገር ነበር የሚል እምነት የለኝም። አሉበትምም፤ የሉበትምም ተብሎ እንዲተረጎም አመች ተደርጎ፤ ያለ አጃቢ እና ያለ ተጨማሪ ማብራሪያ፤ ከኦዲፒ ጽፈህት ቤት የወጣው መግለጫ፤ በዶ/ር አቢይ ትዕዛዝ እንደተለቀቀ ነው የማስበው። ያም ሆነ ይህ ግን፤ መግለጫው ለሁኔታው መካረር የተጫወተው ሚና የሚካድ አይደለም።

ዶ/ር አቢይም ሆነ ሌሎቹ የኦዲፒ ሰዎች፤ በሕወሃት/ኢሕአዴግ ግዜ፤ የአዲስ አበባን ልዩ ጥቅም ለምን እንደሚያገለግል፤ መቼ መቼ እንደሚመዘዝ ያውቃሉ። የለውጡ ዋዜማ፤ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም በፓርላማ እንዲታይ የወጣውን አጀንዳ፤ “ብዙ አንገብጋቢ ጉዳይ ስላለብን በዚህ አጀንዳ ለመወያየት ዝግጁ አይደለንም” ብለው ያስቆሙት የኦህዴድ ተወካዮች ናቸው። ምክንያቱም፤ በዛ ሰአት የአዲስ አበባን ልዩ ጥቅም መምዘዝ የተፈለገው፤ የቲም ለማን ወደ አራት ኪሎ ግስጋሴ ለመግታት ታስቦ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ግን፤ በፊት ወደ ስልጣን የሚያደርጉትን ጉዞ ያጨናግፋል ብለው የገፉትን የአዲስ አበባ አጀንዳ አምጥተው፤ ወደ ሰከነ ውይይት እና ድርድር የሚወስደውን መንገድ ለመዝጋት ተጠቅመውበታል።

የለውጡ መጀመሪያ ላይ፤ የሁሉም ወገን ቁጣ እና እልኽ በሚገርም ሁኔታ ረግቦ፤ ልዩነቶቻችንን በሰከነ መንፈስ፤ በውይይት እና በድርድር ለመፍታት የሚያስችል ጥሩ ድባብ ተፈጥሮ ነበር። ግርግር ለሌባ ያመቻል። አምባገነኖች የሚፈጠሩት በቀውስ ውስጥ ነው። አንዴ ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላ፤  የዶ/ር አቢይ የመጀመሪያ ስራ የሆነው፤ የተፈጠረውን መሰባሰብ እና መተማመን ማደፍረስ ነው። ቲም ለማ ላይ፤ በኋላም እንደ ሀገር መሪ ዶ/ር አቢይ ላይ የተጣለው ትልቁ ተስፋ፤ በኢትዮጵያ ብሔርተኛው እና በኦሮሞ ብሔርተኛው መካከል ያለው መቆላለፍ ተፈቶ፤ ወደ ጤናማ መስተጋብር እንዲያመራ ድልድይ ይሆናሉ የሚል ነበር። ከመነሻው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ቦታ የማግኘታቸው ሚስጥርም በዋናነት ይሄው ይመስለኛል። ዶ/ር አቢይ ግን፤ ተስፋ እንደተጣለባቸው፤ ድልድይ ሆኖ ሁሉቱን ጎራ ከማገናኘት ይልቅ፤ ትንቅንቁን በአዲስ መልክ አድሰው ማስቀጠል ነው የመረጡት።

……………………………………..//……………………………………..

ጭቆናዉን፤ መገፋቱን ችሎት ሳለ፤ ከገዛ ሀገራቸው ጋር ጥል በገቡ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት፤ የሀገር ክብር ሲጎድፍ፤ ታሪክ ሲወላገድ፤ አንድነት ሲናድ እያየ አንጀቱ ሲቆስል የኖረው ኢትዮጵያዊ ብዙ ነው። ዶ/ር አቢይ ደግሞ፤ እዚህ የተጎዳ ስነልቦና ላይ ካፒታላይዝ ማድረግ ይችሉበታል። በእኔ እምነት፤ ዶ/ር አቢይን ከሕወሃት/ኢሕአዴግ የሚለያቸውም፤ የበለጠ አደገኛ የሚያደርጋቸውም ይሄው ነው። ዶ/ር አቢይ ኢትዮጵያን እንደሚሉት ይወዱ ይሆን ይሆናል። ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር፤ ስልጣን ላይ ተቆናጦ ለመኖር ካላቸው ጉጉት ይበልጣል ወይ የሚለው ግን ሌላ ጥያቄ ነው። ሲቀጥል፤ ለሀገር ያላቸው መቆርቆር ከአንጀት ነው ቢባል እንኳን፤ እሱ በራሱ፤ ዲሞክራት ለመሆናቸው፤ እሱም ቀርቶ፤ የሀገርን ጥቅም ለማስቀደማቸው ዋስትና አይደለም። ሀገር በመሪ አፍ ስትቆለጳጰስ መስማት እርቦን ስለቆየ፤ የዶ/ር አቢይን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዬ ማለት እንደ ጽድቅ ቆጠርንላቸው እንጅ፤ ለስልጣናቸው ሲስገበገቡ፤ ሀገር አቆርቁዘው አንከባለው ከፋፋይ እጅ ጥለዋት ያለፉት መሪዎች እኮ፤ በኢትዮጵያ ስም ይምሉ ይገዘቱ የነበሩ ናቸው። ጊዜው ግን፤ ለዶ/ር አቢይ እነሱንም መሆን ቢፈልጉ እንኳን አይፈቅድላቸውም።

“ሀገር ወዳድ” አምባገነን ለመሆን፤ ሲሆን ኮርኩረው አንድ ላይ የሚያስቁት፤ ሳይሆን ቆንጥጠው እኩል የሚያስለቅሱት፤ በአንድ አዋጅ ከዳር ዳር የሚቀሰቅሱት፤ የተሳሰረ ሕዝብ ያስፈልጋል። እንደ ዛሬው አመላችን ለየቅል ከመሆኑ በፊት የመጡት መሪዎች፤ ከሞላ ጎደል ይህን ማድረግ ተሳክቶላቸዋል። በድህረ ሕወሃት ኢትዮጵያ ግን ይህ አይታሰብም። አማራጩን ፍራቻ፤ ቢያንስ ሀገር ጠል እስካልሆኑ፤ ሰጥ ለጥ አድርገውም ቢሆን ዶ/ር አቢይ ይግዙን የሚለው የአንዳንድ ወገኖች ሀሳብ የማያዋጣው ለዚህ ነው። ዶ/ር አቢይም ይህን ማድረግ እንደማይችሉ ተረድተውታል። ቅራኔው ከመሰረቱ እንዲታከም እድል ሰጥተው፤ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት በር እንዳይከፍቱ ደግሞ፤ ነግሦ የመኖር ምኞታቸው ጋር ይጋጫል። የሕወሃትን የመከፋፈል ስልት እንዳለ እንዳያስቀጥሉ፤ ተበልቶበታል። የብሔር ብሔረሰቦችን ሙዚቃ ሕወሃት እስከ ጥግ ነግዶበታል። ዶ/ር አቢይ ለዚህ የዘየዱት መላ፤ ውስጥ ውስጡን ጠቡን እያስቀጠሉ፤ ከፋፋይነታቸው አይን ውስጥ እንዳይገባ ላይ ላዩን ኢትዮጵያዊነትን መላበስ ነው።

እድሜ ለሕወሃት፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ጸብ መጫር ብዙ ስራ አይጠይቅም። ትንሽ እፍ እፍ ሲሉት ራሱ የሚቀጣጠል ፍም በየጉራንጉሩ ሞልቷል። ለብሄራዊ አንድነት የተፈጠረውን ረሃብ ደግሞ፤ አንዳንድ ተምሳሌታዊ ነገሮችን እያደረጉ እና በጉም ተስፋ እየሞሉ እንዴት ማሳደር እንደሚቻል አውቀውበታል። እንዲያውም፤ ሕዝቡ ውስጥ ሀገር እንዳይፈርስ ያለው ስጋት እና የሀገር አንድነት፤ ብሔራዊ ክብር እንዲመለስ የነበረው ጉጉት፤ ስልጣን የመጠቅለል ውጥናቸውን፤ ኢትዮጵያዊነት እና ብሔራዊ ክብር ውስጥ ለውሶ መሸጡን በጣም አቅልሎላቸዋል።

……………………………………..//……………………………………..

እጣ ፈንታው አንድ ላይ የተገመደን ሕዝብ መከፋፈል ኃጥያት ነው። የከፋው ኃጥያት ግን መሰባሰቢያችን ሊሆን በሚገባው ኢትዮጵያዊነት፤ አንድነት፤ ፍቅር እና እርቅ ስም ተደብቆ መከፋፈል ይመስለኛል። መዘዙም የኋለኛው ይከፋል። ይህንንም ማየት የጀመርነው በጊዜ ነው። በሀገር እና በአገዛዝ መካከል ያለው ልዩነት ውሉ እንዲምታታበት ሆኖ ያደገ ወጣት ባለበት ሀገር፤ የዶ/ር አቢይ መንግስት ኢትዮጵያዊነትን ተገን አድርጎ በሚሰራው አፈና፤ ንጹሃን ዜጎች፤ ሀገር እና ባንዲራ ላይ ሲዘምት አየተናል። የዶ/ር አቢይ ኢትዮጵያዊነትን ሽፋን ያደረገ አምባገነን እና ከፋፋይ አገዛዝ በተለይ፤ ላለፈው ግማሽ ምዕተ አመት ለተጠጋ ዘመን፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በተቀነቀነው የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት፤ የሆነውንም የተፈበረከውንም የሀገሪቱን ኃጥያት፤ ያለ ስርየት እንዲሸከም ተፈርዶበት፤ ስሙ ያለአግባብ ከአገዛዝ በደል ጋር እንዲቆራኝ የተደረገውን የአማራ ሕዝብ፤ በአምሳልነት አብረው የሚፈረጁትን ጨምሮ፤ ለከፋ የፕሮፖጋንዳ ጥቃት እና ለደህንነት አደጋ ተጋላጭ አድርጎል።

የሕወሃት/ኢሕአዴግ ትርክት ሚዛን በሳተ መልኩ የብሔር ማንነት ላይ በመቃኘቱ እና ብሔር ዘለል ለሆኑ የጋራ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ሁነቶች የነበረው አተያይ በጣም የቀጨጨ እና የተዛባ መሆኑ፤ በብሔር ተኮር ፖለቲካው ለመታቀፍ ታሪካዊ ዳራው ሆነ ስነልቦናው የማይፈቅድለትን የአማራ ሕዝብ፤ ከፖለቲካው ስሌት ውጭ ሆኖ እንዲንሳፈፍ አድርጎት ቆይቶአል። አማራው፤ በድሮ ሥርዓት ናፋቂነት ተከሶ፤ ለኢትዮጵያ ያለው ቀናኢነት “ትምክህተኛ” የሚል ተለጣፊ ስም ተሰጦት፤ አላግባብብ በተቀረው ኢትዮጵያዊ አይን ውስጥ ስጋት ሆኖ እንዲታይ የተሰራው ስራ፤ ያስከተለው ስነልቦናዊ እና ማህበራዊ ጫናም ቀላል አልነበረም።

የአማራ ሕዝብ የኔ ብሎ ለብቻው የተዋደቀለት ስርአት ኑሮት አያውቅም። ዘውዳዊውን አገዛዝ ለመጣል በተደረገው ትግል፤ የአማራ ተወላጆች ቀንደኛ ወንበር ነቅናቂዎች ነበሩ። ትምክህቱ በሀገሩ በኢትዮጵያ ላይ ነበር። ሀገር በአንድነት እስከቀጠለች ድረስ፤ ማንም ሂደ፤ ማንም መጣ፤ ችግር ላይ እውድቃለሁ የሚል ሀሳብ ገብቶት የሚያውቅ ሕዝብ አልነበረም። ስጋት የገባው ኢላማ ስለተደረገ ነው። የተከፋው የሕወሃት/ኢሕአዴግ ከፋፋይ ፖለቲካ፤ ሀገሩን፤ ለዘመናት የተገነባውን ኢትዮጵያዊ አብሮነትን ስለገፈፈው ነው። ፍቅሩ ከድሮ ስርአት ሳይሆን ከሀገሩ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ነበር። ቲም ለማ፤ የተዘራውን ቅራኔ የሚሽር፤ ሀገራዊ አንድነትን የሚያድስ፤ አዲስ የስምምነት ዘመን የሚያበስር መልእክት ይዞ ሲመጣ፤ በታላቅ ደስታ እና ጉጉት መቀበሉም ለዚሁ ነበር። ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን ከወጡ በኋላም፤ በዚሁ እሳቤ ፍቅር እና ድጋፉን ሳይሰስት ሰጥቷቸዋል። ዶ/ር አቢይ ግን እምነቱን ለርካሽ የስልጣን ግባቸው መጠቀሚያ ነው ያደረጉት።

ሕወሃት፤ አማራን በአጥፊነት ፈርጆ፤ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ አማራ ላይ በማሳደም ነበር የስልጣን ሚዛኑን ለማስጠበቅ የሚጥረው። ዶ/ር አቢይ ደግሞ፤ ስክሪብቱን ትንሽ ገልብጠው፤ አምኖ ልቡን የሰጣቸውን የአማራ ሕዝብ ስጋት እየጠነቋቆሉ፤ ዙፋን ተሸካሚያቸው ማድረግ ነው የፈለጉት። ቀድሞውኑ ተስፋ እንደተጣለባቸው፤ ለብሔራዊ መግባባት መንገድ በመጥረግ፤ ዘላቂ እርቅ እና መረጋጋት እንዲሰፍን መስራትን ትተው፤ አማራውን በዚህም በዚያም እያላተሙ፤ ዙሪያ ገባው ገደል ሆኖ እንዲታየው፤ በፍራት እንዲሸበብ እና ለህልውናው ያለው ብቸኛ ዋስትና የእሳቸውን መንበር መሸከም ሁኖ እንዲሰማው ነው ሲሰሩ የነበሩት።

እሳቸው ስልጣናቸውን ለማጽናት በሚሰሩት ኃጢያት፤ ኢትዮጵያን ያቀናሉ ብሎ ማን ናቸው፤ ከየት ናቸው ሳይል አምኖ ልቡን የሰጣቸውን የአማራ ሕዝብ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ኢላማ አድርገውታል። በአንድም በሌላ መልኩ፤ በተለያየ አካባቢ የሚኖሩ አማራዎችን፤ ለተደጋጋሚ ጥቃት እና የደህነነት ስጋት እያጋለጠ ያለውም የዶ/ር አቢይ ፖለቲካ ነው። የሕወሃት የሥልጣን ገመድ በዋናነት የተዘረጋው፤ አማራን ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በማለተም ላይ ነበር። ዶ/ር አቢይ እያደረጉ ያሉትም ያንኑ ነው። እንዲያውም፤ አሳቢ መስሎ ቀርቦ ወደ ጥፋት ከሚያግዝ፤ አንድ ፊቱን ተንኮሉ የታወቀ በስንት ጣዕሙ።

……………………………………..//……………………………………..

ዶ/ር አቢይ እንደሚሉት ሀገራቸውን ይወዱ ይሆናል። ሆኖም የፖለቲካ ስሌታቸው፤ የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም እና የሀገርን ቀጣይ እጣ ፋንታ ታሳቢ ያደረገ አይደለም። በተመሳሳይ፤ ምንም እንኳን ዶ/ር አቢይ ኦሮሞ እና ኦህዴድ ያፈራቸው ፖለቲካኛ ቢሆኑም፤ የኦሮሞ ብሔርተኝነታቸው የፖለቲካ እሳቤአቸው መዘውር ነው ብዬ አላስብም። ይህን ስል፤ ለግልባጩ ሀሳብ አስረጅ ሆነው ሊጠቀሱ የሚችሉ እውነታዎች መኖራቸውን ዘንግቼ አይደለም። ሌላው ቢቀር፤ ሽመልስ አብዲሳ ብልጽግናን የመሰረትነው የኦሮሞ የበላይነትን ለማምጣት ነው ብለው በማያዋላዳ ቋንቋ የተናገሩትን እንዳልሰማን መሆን አንችልም። ዶ/ር አቢይ ባሌ ሂደው ያደረጉት ንግግር ላይም በሌላ አነጋገር ይህንኑ ነው የደገሙት።  ሆኖም፤ ኦሮሞ ብሔርተኝነትን ዶ/ር አቢይ፤ ልክ በሕወሃት/ኢሕአዴግ ጊዜ እንደነበረው ለፖለቲካ ግብ መሳሪያነት እየተጠቀሙበት እንዳል ሆነ ነው የሚሰማኝ።

የሀገሪቱን መሬት በብሔር ሸንሽኖ ኦሮሚያ የሚባል ክልል የፈጠረውም፤ የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ብሎ ውሉ ያልተለየ ነገር የደነቀረውም፤ ሕወሃት/ኢሕአዴግ ነው። በ97ቱ ምርጫ ማግስት፤ ቅንጅት አዲስ አበባን ይረከባል በሚል ስጋት፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን፤ በአንድ ሌሊት፤ ከአዳማ ነቅለው አዲስ አበባ የተከሉትም እነ መለስ ዜናዊ ናቸው። እነ መለስ ዜናዊ ይህን ሲያደርጉ፤ የሚጋጩ ፍላጎቶችን በመፍጠር፤ የስልጣን ሚዛን ለመጠበቅ እንጅ፤ ኦሮሞም፤ የኦሮሞ ብሔሄርተኛም ስለሆኑ አልነበረም። ዶ/ር አቢይም ምንም ኦሮሞ ቢሆኑ፤ ከኦሮሞ ብሔርተኝነት ጋር ያላቸው ዝምድና ከዚህ ብዙ የጠበቀ መስሎ አይታየኝም።

በአንድ በኩል፤ የኦሮሞ ብሔርተኛነት የተሰመረለትን አጥር ጥሶ ወደ መኃል እንዳይፈስ የታሪክ እስረኛ አድረገው እየጠበቁ፤ በሌላ በኩል ከኦሮሞ ብሔርተኝነት ሌላውን ወገን የሚያስፈራሩበት አለንጋ መግመድ፤ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖለቲካ ልዩ መገለጫ ነበር። የአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም አርፋችሁ ተቀመጡ ማለት ባስፈለገ ቁጥር ስንት ጊዜ እየተመዘዘ እንደተመለሰ ማስታወስ ይቻላል። ወቅት እየተጠበቀ፤ በኢቲቪ አናት በአናቱ ይለቀቅልን የነበረው ኦነግ ላይ የሚያውጠነጥን ዶክመንታሪም “እነሱ፤ ሀገር በትነው ከሚያጠፏችሁ፤ እኛ ብንጨቁናቸሁ አይሻልም?” የሚል ቀጭን መልእክት ከማስተላለፍ ውጭ ሌላ አላማ አልነበረውም። በ97ቱ ምርጫ፤ የኢትዮጵያ ብሔርተኛው አይሏል ብለው ሲያስቡ፤ እነ መለስ ዜናዊ እንዴት ሩጠው ኦሮሞ ብሔርተኝነት ውስጥ እንደተወሸቁም የሚታወስ ነው። በተመሳሳይ፤ ዶ/ር አቢይ ኦሮሞነትን፤ በተለያየ ሁኔታ አንድም ለአለንጋነት አንድም ለጋሻነት እየተጠቀሙበት እንደሆነ ነው የሚታየኝ። በርግጥ ኦሮሞነታቸው ከሕወሃቶች በላይም ኦሮሞነትን ለስልጣናቸው መከታ ለማድረግ እድል ይሰጣቸዋል።

ሆኖም፤ ይህንንም ሆነ ያን ታሳቢ አድርጎ ተደረገ ቢባልም፤ እንደዚህ አይነቱ የፖለቲካ ጨዋታ የኦሮሞን ሕዝብ ይጠቅማል የሚል እምነት የለኝም። የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የተለየ ህልውና የለውም። እንደማንኛውም የኢትይጵያ ማህበረሰብ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ዘላቂ ማህበራዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጤና የሚጠበቀው፤ አንድነቷ በተጠበቀ እና ፍትህ በሰፈነባት ኢትይጵያ ውስጥ ነው። የኦሮሚያ ብልጽግና፤ ከብልጽግናዎቹ ሁሉ አፋኙ ብልጽግና ነው። በአሁኑ ሰአት እንደ ኦሮሚያ ከባድ አፈና ውስጥ ያለ ክልል ያለ አይመስለኝም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ ካወጣው ሪፖርት እንኳን ብቻ የአፈናውን ስፋት እና ክፋት መገንዘብ ይቻላል። የኦሮሞ ወጣት፤ ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ ያን ያህል ግዜ የታገለው፤ ለሥርዓት ለውጥ እንጅ አዲስ አውቅልሃለሁ ባይ በራሱ ላይ ለመሾም አይመስለኝም።

ዶ/ር አቢይ፤ ለለውጥ ውድ ዋጋ የከፈለውን የኦሮሞ ወጣት መሰዋእትነት የሚያከብሩትም፤ የኦሮሞን ሕዝብ ሁለንተናዊ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ አስተዎጽዖ ሊያደርጉ ይችሉ የነበሩትም፤ ሀገር አስማምተው ለእውነተኛ የዲሞክራሲ ስርአት መንገድ መጥረግ ቢችሉ ነበረ። ቀድሞውኑ በኦሮሞ እና በተቀረው ኢትዮጵያዊ መካከል ቅራኔ ለመፍጠር ታስቦ በተቀረጸ አጀንዳ ግን፤ ኦሮሞንም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብም ያከስራሉ እንጅ ኦሮሞን ለይተው ሊጠቅሙ የሚችሉበት ሁኔታ የለም።

……………………………………..//……………………………………..

የሽመልስ አብዲሳ የ“ኮንቪንስ” እና “ኮንፊውዝ” ዲስኩር የተለቀቀ ሰሞን፤ ሸወዱን ብሎ ያዘነ የተቆጣ ወገን እንደነበረ ሁሉ “ይህ አይነቱ አካሄድ….ወደ ጫፍ የወጣውን የኦሮሞ ፖለቲካ ለመያዝ….ተቸግረው የሚያደርጉት ነው…በዛ መልኩ ልንረዳቸው ይገባል” የሚል ሀሳብም ከሌላ ወገን ይሰማ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ፤ ይህ እይታ እውነት እንኳን ቢሆን፤ አለመተማመን ክፉኛ በተጠናወተው የእኛ ሀገር ፖለቲካ፤ ቢያንስ መሰረታዊ መርሆዎቹ ላይ ወጥነት ጠብቆ ሀሳብ መሸጥ የማይችል ፓርቲም ሆነ ፖለቲከኛ ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚብሰው። ነገር ግን ሲጀመር፤ ዶ/ር አቢይም ሆነ የበታች ሹማምንቶቻቸው፤ ለከት የለሽ አክሮባት ሲሰሩ የነበሩት፤ ጠርዝ የወጡ አንጃዎችን ለማስታገስ ተገደው ነው የሚለው ምልከታ ወሃ የሚቋጥር አልነበረም።

ከመነሻው፤ ቲም ለማ፤ ወደ መኃል ፖለቲካው ሰንጥቆ መግባት የቻለው፤ ”ዳር ቁሞ መብት ጠያቂ ሆነን፤ የኦሮሞን ሕዝብ ችግር መፍታት አንችልም። ኦሮሞን የምናድነው፤ መኃል ገብተን ኢትዮጵያን ስናተርፍ ብቻ ነው” የሚል መልእክታቸው ኦሮሚያ ውስጥ ተቀባይነት አግኝቶ ገዥ ሀሳብ መሆን ስለቻለ ነው። የተነሱበትን መንገድ አጠናክረው መቀጠል ቢችሉ ኖሮ፤ መልእክታቸው መላው ኢትዮጵያን አጥለቅልቆ አዋጭነቱ በውጤት ከተመሰከረ በኋላ ወደ ኋላ ማፈግፈግ የሚያስገድዳቸው ነገር ይፈጠራል ብየ አላስብም። የተነሱበትን መንገድ እየቀለበሱ፤ ወዲህ እና ወዲያ ማለት ያመጡት፤ ስልጣን ለማስጠበቅ፤ ተቃርኖውን ማስቀጠል ያስፈልገናል ብለው ስላመኑበት እንደሆነ ነው የማስበው።

ዶ/ር አቢይ፤ ኦሮሚያ ውስጥ የነበራቸውን ተቀባይነት መመንዘር የጀመሩት፤ የሕዝብን ትግል፤ ለግል የስልጣን ፍላጎታቸው መጠምዘዝ የጀመሩ እለት ነው። በተለይ ለማ መገርሳን ከፖርቲው ማግለላቸው፤ ኦዲፒን ያለግዜው አፍርሰው እና ኢሕአዴግን በግድ ጨፍልቀው ብልጽግና የሚባል ዉሉ ያልታወቀ ፓርቲ መፍጠራቸው እና ተያይዞ የገቡበት ውንብድና፤ ኦሮሚያ ውስጥ እሳቸውም ፓርቲያቸው ኦህዴድም አግኝተውት የነበረውን ተቀባይነት እና ታማኝነት ለማጣታቸው ትልቁን ሚና የተጫወተ ይመስለኛል። ለውጡ መጀመሪያ ላይ፤ ኦህዴድ እንደ ቡድን፤ ዶ/ር አቢይ እንደ መሪ፤ የኦሮሞን ፖለቲካ ወደ መኃል ለመሳብ ትልቅ እድል ነበራቸው። ዶ/ር አቢይ ግን፤ በተቃራኒው፤ ራሳቸውን ስለ ኢትዮጵያ ግድ የሚለው ብቸኛ ኦሮሞ አድርገው ሹመው፤ በዙሪያቸው መግባት ያልቻለውን የኦሮሞ ፖለቲከኛ ሁሉ ወደ ጽንፍ ሲገፉ ነው የነበሩት።

ለእኔ ዶ/ር አቢይ፤ ከጽኑ የስልጣን ጥማት በስተቀር፤ የምንም አይነት አይዶሎጅ፤ የየትኛውም አይነት ማንነት እስረኛ የሆኑ ሰው ሆነው አይታዩኝም። የሁሉንም ሥሥ ብልት፤ የሁሉንም ጥልቅ ስጋት እየጠነቋቆሉ እንደፈለጉት ማጫወቱ የቀለላቸውም፤ የሁሉም ብብት ውስጥ ለመሸጎጥ፤ ባስፈለጋቸው ግዜ ወደ አስፈለጋቸው አቅጣጫ ለመተጣጠፍ የማያዳግታቸውም ለዚህ ይመስለኛል። የሆነው ሆኖ ግን፤ ለማንም ይወግናሉ፤ ወደ የትም ያዘነብላሉ ቢባል፤ መሰረታዊ ችግሩ አንዱን ወይም ሌላኛውን አስተሳሰብ መያዛቸው አይደለም። ያለ ከልካይ፤ ያለ ተቆጣጣሪ፤ ሀገሩን በፈለጉት ሰአት ወደ ፈለጉት አቅጣጫ ሊጎትቱት የሚችሉበት አቅም መፍጠራቸው፤ ስልጣን መጠቅለላቸው ነው። መተማመን እና ስምምነት በጠፋበት ሀገር፤ ምንም ነገር ቢያደርጉ፤ ወደ የትም አቅጣጫ ቢሄዱ፤ ያለ ጥናት፤ ያለ ሁሉን አቀፍ ምክክር እና ድርድር፤ በገዛ ፈቃዳቸው፤ እየተነሱ የሚያደርጉት እስከሆነ ድረስ፤ እንደ እስካሁን እርምጃዎቻቸው ሁሉ በቀጣይም ውጤቱ ጥሩ አይሆንም። ዞሮ ዞሮ አደጋው እሱ ላይ ይመስለኛል።

……………………………………..//……………………………………..

የአምባገነንነት መሰረት የሚጣለው በግርግር እና በቀውስ መኃል ነው። ዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጡ ማግስት ጀምሮ፤ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ሳያባራ የቀጠለው ቀውስ፤ ግጭት፤ ሞት እና የሰላማዊ ዜጎች እንግልት፤ መንግስታቸው ህግ ለማስከበር ካሳየው ለከት የለሽ ዳተኝነት ጋር ሲደመር፤ ዶ/ር አቢይ ግጭትን፤ አለመረጋጋትን፤ ለፖለቲካ ፍጆታ እያዋሉ ስለመሆናቸው በቂ ማስረጃ የሚወጣው ይመስለኛል።

በርግጥ፤ ዶ/ር አቢይ በብዙ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ችግር ተቀስፋ የተያዘች ሀገር እንደመረከባቸው፤ ጸጥታን የመቆጣጠር ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል ቀድሞውኑ የተፈራ ነው። ከዚህ አንጻር፤  ለሚደርሰው የጸጥታ ችግር መንግስትን ሙሉ ለሙሉ ተወቃሽ ማድረጉ ትክክል አይደለም ሊባል ይችል ይሆናል። ነገር ግን፤ የጸጥታ ክፍተት ፈጣሪው እና ግንባር ቀደም የቀውስ ግባት አቀባዩ ራሱ መንግስት በሆነበት ሁኔታ፤ ይህ ማስተባበያ ብዙም ያስኬዳል ብየ አላምንም።

በሽግግር ወቅት ሰላም እና መረጋጋትን የሚያደፈርስ ሁኔታ ሊያጋጥም መቻሉ የሚታወቅ ነው። ከዚህ አንጻር፤ የዶ/ር አቢይ መንግስት አስተዳደሩን እንደተረከበ ተቀዳሚ ትኩረቱን የጸጥታ ክፍተቶችን መዝጋት ላይ ማድረግ ነበረበት። ይህን ለማሳካት ደግሞ ለውጡን በዝግታ እና በስክነት ማስኬድ ያስፈልግ ነበር። ዶ/ር አቢይ ግን በተቃራኒው፤ የሕዝቡን ስሜት ማጋጋሉን፤ የሞቅታ እና ሆይ ሆይታውን መንገድ ነው የመረጡት። ከመነሻው ጀምሮ፤ በተለይ ከውጭ ተመላሽ ተቃዎሚዎችን ወደ ሀገር ለማስገባት ከነበረውን ወከባ ጋር በተያያዘ ብዙ ጥያቄ የሚያጭሩ ክስተቶች ተፈጥረዋል።

ኦሮሚያን፤ ከለውጡም በፊት ከለውጡም በኋላ የሚያስተዳድረው ኦህዴድ ነው። ሕዝባዊ አመጹ አይሎ በነበረበት ግዜ እንኳን ያልታየ የጸጥታ ክፍተት ከለውጡ በኋላ እንዴት ተፈጠረ? የኦሮሞ ወጣት በባዶ እጁ ሲታገል ደብዛው ያልነበረ የታጠቀ ኃይል፤ ከለውጡ በኋላ ከነ ትጥቁ ከየት ተከሰተ? እውነት መንግስት የታጠቀ ኃይል፤ ትጥቅ ሳያስፈታ አስገብቶ ከሆነ፤ የውትድርና እና የደህንነት ልምድ ያለው ሰው፤ እንዲህ አይነት የጸጥታ ክፍተት በስህተት ይፈጥራል ብሎ ማለፍ ይቻላል ወይ? የሆነውስ ሆኖ፤ ምነው ይህን ያህል ነገሩ ለመፍትሄ አስቸገረ?

ወንጀለኛን ይዞ በአግባቡ መቅጣት፤ የህግ ማስከበር ቁልፍ ተግባር ነው። ይህን ማስፈጸም ላይ ችግር ካለ፤ ስርአት አልበኝነት መረን መልቀቁ ሳይታለም የተፈታ ነው። ከጅምሩ የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል፤ በድንጋይ ተቀጥቅጦ ሲሞት እና መሰል ለጀሮ የሚሰቀጥጡ ወንጀሎች በዚህም በዚያም ሲከሰቱ፤ አጥፊዎቹን ይዞ፤ ለሕዝብ እይታ ክፍት በሆነ የፍርድ ሂደት ተገቢውን ቅጣት መስጠት፤ የመንግስት ተቀዳሚ ትኩረቱ ሊሆን ይገባ ነበር። በወቅቱ የዶ/ር አቢይ መንግስት ይህን ለማስፈጸም በቂ ተቀባይነት እና ታማኝነት ነበረው። የሆነው ግን ይህ አልነበረም።

ያ ሁሉ ለጀሮ የሚሰቀጥጥ ግድያ ሲፈጸም፤ የጅምላ እልቂት መደበኛ ክስተት እስኪመስል በዙር ሲደጋገም፤ ሴት ልጆች በወጡበት ደብዛቸው ሲጠፋ፤ ከተሞች እንዳለ ሲወድሙ፤ ስንት አይነት እንግልት እና በደል ሲደርስ፤ መንግስት የተጠናከረ ሪፖርት ያቀረበበትን፤ ወንጀሉን አጣርቶ፤ እከሌ እከሌ የሚባሉ ተጠርጣሪዎችን ከነማስረጃቸው አቅርቦ ፍርዱን ለሕዝብ ይፋ ያደረገበትን ግዜ አላስታውስም። ይህን ወይም ያን ቡድን በደፈናው ወንጅሎ፤ አደባብሶ ከማለፍ በስተቀር ጥርት ያለ የወንጀል ምርመራ እና የፍርድ ሄደት አልነበረም። አብዛኛው ነገር ተድበስብሶ ነው የሚያለፈው። በሰኔ 16ቱ ሰልፍ ከደረሰው ፍንዳታ ጀምሮ፤ ፖለቲካዊ አንድምታቸው ከፍተኛ የነበሩ፤ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የታዋቂ ግለሰቦችን ግድያ ጭምር፤ የወንጀል ምርመራው መጨረሻ ሳይታወቅ ተድበስብሶ ነው የቀረው። በወቅቱ፤ ስለክስተቶቹ፤ ከመንግስት በኩል የተለቀቁ ጥቂት መረጃዎችም፤ ከመልስ ይልቅ ጥያቄ የሚጨምሩ ነበሩ።

ዶ/ር አቢይ፤ ሕዝብ ሲዘረፍ፤ ሲፈናቀል፤ ሲሞት፤ ሀገር ሲረበሽ፤ ለምን መንግስት ህግ አያስከብርም ሲባሉ፤ ዲሞክራሲ ሰው ማዋከብ መግደል ይፈቅድ ይመስል፤ ዲሞክራሲ እናላምድ ብለን ነው፤ ቆሻሻው ይውጣ ብለን ነው ገለመሌ ገለመሌ እያሉ፤ በሕዝብ ሰቀቀን ሲዘባበቱ ከርመው፤ ሲላቸው ደግሞ የድምጻዊ ሀጫሉን ሞት ተከትሎ፤ ተቃዎሚ ፖለቲከኞችን ጋፈው ያሰሩበትን ሁኔታ፤ ይሄ ነገር እውነት ለፍትህ ነው ወይስ ህግ በማስከበር ሰበብ የፖለቲካ ባላንጣን ለማስወገድ የሚያስብል ነበር። በወቅቱ ከሀጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ የተያዙት ሰዎች፤ በዶ/ር አቢይ በሚመራው የለውጥ ሂደት ላይ፤ ጠንካራ ትችት እና ተቃውሞ ያሰሙ ሰዎች ከመሆናቸው በቀር ሌላ ብዙም የሚያስተሳስር ነገር አልነበራቸውም። የሰዎቹ የፖለቲካ አመለካከት መራራቅ እና የአንዳንዶቹ ክሶች ይዘት፤ ነገሩ ፖለቲካዊ እርምጃ እንደነበር በማያወላዳ መልኩ የሚጠቁሙ ነበሩ።

ደረቅ ወንጀልን የፈጸመን ሰው አለመቅጣት፤ ስርአት አልበኝነትን ማበረታታት፤ ዲሞክራሲን ከማላመድ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በተቃራኒው ግን፤ የፖለቲካ ባላንጣዎችን ሰበብ እየጎነጎኑ እስር ቤት ማጎር የዲሞክራሲ ሄደትን የሚያጨናግፍ ተግባር ነው። ዶ/ር አቢይ እውነት ለዲሞክራሲ መጎልበት የሚጨነቁ ቢሆን ኖሮ፤ ማድረግ ያለባቸውን ትተው፤ ማድረገ የሌለባቸውን ነው ያደረጉት። ይሄ አካሄድ፤ ስልጣን ለመጠቅለል እንጅ፤ ዲሞክራሲ ለመገንባት አይሆንም። በመንግስት ስልጣን ላይ ያለው አካል፤ ከግጭት እና አለመረጋጋቱ ፖለቲካዊ ትርፍ በሚያገኝበት ሁኔታ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ ከግጭቶቹ ጀርባ እጁ አለመኖሩን እርግጠኛ መሆንም አይቻልም። እንዲያውም የሆነው ነገር፤ መንግስትን ግንባር ቀደም የወንጀሉ ተጠርጣሪ የሚያደርግ ነው። ሆን ብሎ አደጋ ጥሎ በሰበቡ ተቀናቃኝ ወገኖች ላይ መዝመት፤ ታሪክ ደጋግሞ የታዘበው የተስፈኛ አምባገነኖች ታክቲክ ነው።

ዶ/ር አቢይ፤ የሀጫሉ ግድያን ተገን አድርገው፤ በጠራራ ጸሐይ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው ላይ የሰነዘሩት ጥቃት፤ ኦሮሚያ ውስጥ ህግ በማስከበር ስም የሚደረገው አፈና እና እስር ላይም ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድደን ይመስለኛል። ኦሮሚያ ውስጥ እየተጋፈፈ ከሚታሰረው ወገን መኃል፤ ምን ያህሉ እውነት በወንጀል የሚጠረጠሩ መሆናቸው እጅግ አጣያያቂ ነው። እንደ እኔ፤ ከታሳሪዎቹ መካከል ጭራሹኑ ወንጀለኞቹ ስለመኖራቸው እርግጠኛ መሆን የሚቻልም አይመስለኝም።

ይህን ሦስት ዓመታት፤ ከአንዱ እልቂት ወደ ሌላው እልቂት፤ ከአንዱ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ፤ ከአንዱ ግጭት ወደ ሌላ ግጭት ስንገላበጥ ነው ያሳለፈነው። ግጭቶቹ፤ ጥቃቶቹ ያስከተሉት ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እና የፈጠሩት የደህነነት ስጋት እንዳለ ሆኖ፤ በእያንዳንዱ ክስተት ውስጥ፤ የዶ/ር አቢይ መንግስት፤ ጸጥታን ለማስጠበቅ፤ ወንጀልን አጣርቶ ወንጀለኛውን ለመቅጣት እና ግጭትን ለመግታት ያሳየው ልግምተኝነት፤ ቸልተኝነት ንዝህላልነት ተብሎ መታለፍ የሚችል አይመስለኝም። መንግስት ለእርምጃ የፈጠነባቸው ጥቂት አጋጣሚችም፤ ከህግ ማስከበር ይልቅ ፖለቲካዊ አንድምታቸው ያመዝን ነበር። ዶ/ር አቢይ ሕዝብ ያስጨነቀ ያስጠበበን ነገር አላየሁም አልሰማሁም ብሎ አድበስብሶ በማለፍ ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም። ሲላቸው ደግሞ፤ የዜጎች ሞት እንግልት፤ የሕዝብ ቁጣ ለእሳቸው ፖለቲካ ግባትነት ሲፈለግ፤ ዋና ያዙኝ ልቀቁኝ ባይ የሚሆኑበት፤ ፓርላማውን ሳይቀር ልቅሶ ያስቀመጡበት ጊዜም ነበረ። ብቻ በጥቅሉ፤ በንጹሃን ዜጎች ሞት እና እንግልት፤ ሲቀለድ እና ሲነገድ ነው የነበረው።

ግጭቱ፤ ቀውሱ፤ የሁሉንም ወገን ስሜት በመስረቅ እና በመበታተን፤ ለውጡ ለውጥ መሆኑን ትኩረት ሰጥቶ የሚቆጣጠር፤ የዶ/ር አቢይን መንግስት ወደ መስመር የሚገራ አካል እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። ከቡራዩ ጥቃት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ አላባራ ያለው አደጋ እና ግጭት፤ ሁሉንም ወገን አቅጣጫ እያሳተ፤ ጣት እያቀሳሰረ እና ይብስ እየከፋፈለ ነው የቀጠለው። ለዘላቂ መንግስታዊ ስርአት መሰረት ይጣልበታል ተብሎ በታሰበው የሽግግር ግዜ፤ ሁሉም ቀልቡን አጥቶ  ሲፈራ፤ ግራ ሲጋባ እና ሲፈራረጅ ነው የከረመው። ወደ አንድነት መንገድ እንጀምረበታለን ተብሎ ተስፋ በተደረገበት ግዜ ይባስ በየምክንያቱ ምንቅርቅራቸን ነው የወጣው። ሀገሪቱ ከቀን ቀን እየተናጠች ነው የሄደችው። ኢትዮጵያ ውስጥ ጊዜ ባለፈ ቁጥር እየተደላደለ የሚሄደው፤ የዶ/ር አቢይ ስልጣን ብቻ ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት፤ በማያባራ ግራመጋባት፤ ቀውስ እና ግጭት ውስጥ የመዘፈቃችንን ሚስጥር፤ ከዚህ እውነታ ነጥሎ ማየት የሚቻል አይመስለኝም።

……………………………………..//……………………………………..

በተለያዩ አካላት ለዓመታት ሲደረግ የነበረው ትግል፤ የሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ በስተመጨረሻ ለደረሰበት መብረክረክ ያደረገው አስተዋጾ የሚካድ አይደለም። ያ እንዳለ ሆኖ፤ ትግሉን መቋጫ የሰጠው ግን፤ በየአቅጣጫው የተጋጋለውን ሕዝባዊ አመጽ ተገን አድርጎ፤ ራሱ ኢሕአዴግ ውስጥ የተፈጠረው የኃይል ሚዛን መገለባበጥ ነው። ሀገራዊ ለውጡ፤ ከምንም በላይ፤ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፤ በተለይ ኦህዴድ እና ብአዴን ውስጥ በተናጠል የተፈጠረው ለውጥን፤ እንዲሁም የድርጅቶቹ ከሕወሃት ጋር እና እርስ በእርስ የነበራቸው መስተጋብር መቀየርን ማዕከል ያደረገ ነበር። በወቅቱ ኢሕአዴግ ውስጥ፤ ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከርም ሆነ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት መንገድ ከመጥረግ አንጻር ተስፋ የሚያሰንቁ ብዙ መልካም ጅምሮች ታይተው ነበር። በሂደት ግን፤ ለተስፋ ምክንያት የነበሩት ነገሮች በሙሉ ለፍሬ ሳይበቁ ተራ በተራ ከስመው፤ የለውጡ ብቸኛ አርማ ዶ/ር አቢይ ሆነው የዘለቁበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው።

የለውጡ አስኳል ከነበረው የኦህዴድ/ቲም ለማ ብንጀምር፤ እንደ ቡድን የተነሳበትን መስመር ይዞ መቀጠል አልቻለም። በወቅቱ በቲም ለማ በኩል፤ የሕወሃት/ኢሕአዴግን የተቃርኖ ትርክት ምሶሶዎችን ነቅሶ መለየት እና በተለዋጭ ዕይታ መገልበጥ ላይ እጅግ የተዋጣለት ስራ ነበር የተሰራው። መሪዎቹ ያደርጓቸው የነበሩ ንግግሮች፤ ፓርቲው ያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎች፤ በኦቢኤን(OBN) ይለቀቁ የነበሩ ዝግጅቶች፤ ዶክመንታሪዎች፤ ምን ያህል የሁሉንም ወገን ቀልብ መያዝ ችለው እንደነበር የሚታወስ ነው። ሁሉም ወገን በበጎ የተቀበለው የብሔራዊ አንድነት ትርክት ይዘው ነበር የተነሱት። በዚህም፤ በአንድ በኩል ለኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተስማማ አዲስ መንገድ መክፈት፤ በሌላ በኩል ሌላው ወገን በኦሮሞ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ላይ ያለበትን ስጋት ማርገብ ችለው ነበር። ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን መልእክቱ አነሳሱ ላይ በነበረው ወጥነት እና ጥልቀት መቀጠል አልቻለም። ቀስ በቀስ እየሳሳ እና እየተወላገደ ሂዶ፤ አሁን ዶ/ር አቢይ ወደያዙት….ኢትዮጵያ አትፈርስም! በኢትዮጵያ አልደራደርም! አንገቴ ይቀላ! አጥንቴ ይከካ! አይነቱ፤ ግልብ እና ፍሬ ቢስ ሽንገላ ወርዷል። ኦህዴድ/ኦዲፒ እንደ ቡድንም ዶ/ር አቢይን አራት ኪሎ ካደረሰ በኋላ ወደ ቀደመ ነገሩ አፈግፍጓል።

በርግጥ፤ ቀደም ብየ በስፋት እንዳነሳሁት፤ የዶ/ር አቢይ እና ኦዲፒ/የኦሮሚያ ብልጽግና ሁለት መልክ መላበስ፤ የማታለል እና የማደናገር፤ የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካ አካል እንጅ እውነተኛ የሀሳብ ልዩነት ውጤት ነው የሚል እምነት የለኝም። ከዶ/ር አቢይ የተለየ አቋም መያዝ ምን እንደሚያስከትልማ በለማ መገርሳ ጉዳይ አየን። በተቃራኒው ዶ/ር አቢይ እና የኦሮሚያ ብልጽግና የበታች አመራሮች ወደ ውጭ የሚያስተላልፉት መልእክት ሲጋጭ እንጅ እርስ በእርስ ሲጋጩ ያየንበት ግዜ የለም። ሲጀመር፤ ዶ/ር አቢይ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ መስመር ስለሌላቸው፤ በዘይቤአቸው ካልሆነ፤ በመሰረታዊ ሀሳብ ደረጃ ከዚህ ጋር ይስማማሉ ከዚህኛው ጋር ይጣረሳሉ ብሎ መበየን የሚቻልም አይመስለኝም። ስለ ዶ/ር አቢይ አስተሳሰብ፤ በተለይ ስለ ሀገራዊ አንድነት ተቆርቋሪነታቸው ያለው ዕይታም፤ እሳቸው ሆን ብለው በዚህ መንገድ እንዲሳሉ በተለያየ መንገድ ከሚፈጥሩት “ኢሉዥን” የሚቀዳ እንጅ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ነገር ላይ የተመሰረተ ነው የሚል እምነት የለኝም።

……………………………………..//……………………………………..

ብአዴን ውስጥ ለለውጥ እና ለሰከነ ፖለቲካ የታየው ተነሳሽነት፤ የኢሕአዴግን ለውጥ ለውጥ ያደረገው ሌላው ተስፋ ሰጭ ነገር ነበር። በሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ የመጨረሻ ዓመታት፤ ብአዴን፤ በድርጅቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ፤ ተላላኪነቱን ትቶ ወገንተኝነቱን ወደ ሚያስተዳድረው ሕዝብ ለማዞር፤ ከሕወሃት ጣልቃ ገብነት ተላቆ በራሱ እግር ለመቆም አቅም መፍጠር ችሎ ነበር። በወቅቱ የብአዴን ሰዎች፤ ሕወሃት አፍንጫ ስር፤ ከሕወሃት በላይ ሕወሃት የሆኑ ሰዎች ድርጅቱ ውስጥ ተሰንቅረው ባሉበት ሁኔታ፤ የሕወሃትን ጫና ከመቋቋም ትግል ተሻግረው፤ ሕወሃት አዛዥ ናዛዥ ሆኖ ከኖረበት የማዕከላዊ ስልጣን ተገፍቶ፤ ለመሰረታዊ ለውጥ በር እንዲከፈት ወሳኝ ሚና ለመጫወት ድፍረት እና ብቃት አግኝተው ነበር።

ሕወሃቶች፤ ኢሕአዴግ ውስጥ የዘረጉት የበላይነት፤ መቸም ተግዳሮት ሳይገጥመው ለዘላለም ይቀጥላል የሚል ቅዠት ውስጥ የነበሩ አይመስለኝም። ያ ባይሆን ከጅምሩ ኢሕአዴግን በብሔር ከፋፍሎ ማደራጀቱም ባላስፈለገ ነበር። ስሌቱ ማፈንገጥ ከመጣ፤ የሚመጣው በተናጠል ነው፤ ተራ በተራ ይመከታል የሚል ነው። የኦህዴድ እና የብአዴን፤ በየፊናቸው የጀመሩትን የማፈንገጥ አዝማሚያ አቀናጅቶ ግንባር ፈጥሮ መውጣት መቻል ይህን የሕወሃትን የፖለቲካ ቀመር አፋልሶታል።

በብአዴን እና በኦህዴድ መካካል የታየው መናበብ፤ በወቅቱ ኦሮሚያ ውስጥ የነበረው ተቃውሞ የአማራ እና የኦሮሞ የብሔር ግጭት መልክ እንዲይዝ ይደረጉ የነበሩ ትንኮሳዎች ለማምከን የነበረው አስተዋጾ በቀላል የሚታይ አልነበረም። ከዚያም አልፎ የሁለቱ ድርጅቶች መቀራረብ በአጠቃላይ በለውጡ መባቻ ላይ ለተፈጠረው የመተማመን እና የመቀራረብ መንፈስ መሰረት ነበር። የብአዴን አመራሮች፤ በተለያዩ ቦታዎች በአማራ ተወላጆች ላይ ይደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን፤ በቦታው በመገኘት ከአካባቢው መስተዳድር እና ሕብረተሰብ ጋር ተነጋግሮ ችግሩን በጋራ ለመፍታት ያደርጉት የነበረው ጥረትም የሚመሰገን እና ተስፋ የሚሰጥ ነበር። የብአዴኖች የፖለቲካ እንቅስቃሴ፤ ወቅታዊ ውጥረቶችን በማስተንፈስ ብቻ የታጠረም አልነበረም። የብአዴንን እጩ ከኢሕአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ በማግለል፤ የብአዴን ድምጽ ሳይበታተን ወደ ዶ/ር አቢይ እንዲሄድ እና የለውጥ ኃይሉ ይዞታውን ከክልል ወደ ፌደራል እንዲያሰፋ የተጫወቱት ወሳኝ ሚና ለዚህ ዋና ተጠቃሽ ይመስለኛል።

ከዶ/ር አቢይ መመረጥ ጥቂት ወራት በኋላ፤ ገዱ አንዳርጋቸው፤ ዶ/ር አንባቸው እና ሌሎች ሁለት የብአዴን አመራሮች በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች እየተዘዋወሩ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ውይይቶች አድርገው ነበር። በወቅቱ ወልቃይትን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ፤ አንዳንዴም ስሜት በተቀላቀለበት ሁኔታ ከተሳታፊዎቹ ይሰነዘርላቸው ለነበሩ ጥያቄዎች ይሰጡት ከነበረው የበሰለ እና የሰከነ መልስ፤ በለውጡ፤ ሁሉም ነገር በሂደት፤ በውይይት እና በድርድር የሚታይበት ቀን እንደመጣ የነበራቸውን ጥልቅ እምነት መገንዘብ ይቻል ነበር። አጠቃላይ በለውጡ ጉዞ እና ለውጡ መጀመሪያ ላይ የብአዴን ሰዎች የተከተሉት አካሄድ፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ውስብስብነት የተገነዘበ፤ ለአዲስ ፖለቲካ ጅማሬ በር የሚከፍት እና ተስፋ ሰጭ ነበር። አሁን ላይ ነገር ተቀያይሮአል። ብአዴን/የአማራ ብልጽግና እዚህ ግባ የሚባል፤ በአውንታዊ ጎኑ የሚጠቀስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም። ይህ ለመሆኑ ሁለት ዋና ምክንያቶች ማንሳት የሚቻል ይመስለኛል።

አንደኛው ምክንያት በለውጡ ሂደት ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው ሰዎች፤ በፌደራል ሹመት እና በደረሰው የግድያ አደጋ ከቦታው መጥፋት የፈጠረው የአመራር መሳሳት ነው። ለውጡን የመሩት ሰዎች ለውጡ እስኪጠና ቦታቸው ላይ ቢቀመጡ ጥሩ ነበር። የገዱ አንዳርጋቸው ከርዕሰ መስተዳድርነት ተነስተው ውጭ ጉዳይ ውስጥ መግባት በዚህ ረገድ የራሱ ጉዳት የነበረው ይመስለኛል። በለውጡ ሂደት በጣም የተሳካ የሕዝብ ግንኙነት ስራ ይሰሩ የነበሩት ንጉሱ ጥላሁን፤ ከክልሉ ቃል አቅባይነት ተነስቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መሸጎጥም፤ ክልሉ ላይ ከነበራቸው ንቁ እንቅስቃሴ ተገተው ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። የተገደሉት አመራሮችም፤ ቀደም ብሎ በጤና እክል ምክንያት ያረፉትን አቶ ተስፋየን ጨምሮ በብአዴን የውስጥ ትግል የግንባር ሚና እንደነበራቸው የሚነገርላቸው ሰዎች ናቸው። የእነሱ በድንገት መታጣት እና አጠቃላይ ሁኔታው፤ የቀረቱንም ሳይቀር ሽባ ማድረጉ እና አቅጣጫ ማሳጣቱ የሚጠበቅ ነው።

ለብአዴን ፖለቲካ አቅጣጫ መሳት ሁለተኛው እና ምንአልባትም ዋነኛው ምክንያት በዶ/ር አቢይ መመረጥ ይከፈታል ተብሎ የታሰበው አዲስ የፖለቲካ መድረክ እውን አለመሆኑ ነው። የዶ/ር አቢይ መመረጥ፤ ሕወሃትን ከፌደራል ይዞታው በማፈናቀል፤ ብአዴንኖች ከሕውሃት ጫና ለመላቀቅ ያደረጉትን ትግል ለአንዴ እና ለመጨረሻ ግዜ ፍጻሜ ሰጥቶታል። ቀጣዩ ምዕራፍ የሚሆነው፤ ቢያንስ ኢሕአዴግ ውስጥ፤ ሁሉም በነጻነት እና በእኩልነት የሚያሳትፍ አዲስ የፖለቲካ መድረክ ማመቻቸት ነበር። ብአዴኖች ከኦህዴድ ጋር ዶ/ር አቢይን እስከማስመረጥ የዘለቀ ቅንጅት ሲፈጥሩም ይህን ታሳቢ አድርገው ይመስለኛል። የዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ ወጥቶ፤ እንደታሰበው ለአሳታፊ የፖለቲካ መድረክ መንገድ ከመጥረግ ይልቅ፤ ራሳቸውን በሕውሃት እግር ተክተው አዲስ አምባገነንነት መገንባት መጀመራቸው የብአዴንን ፖለቲካዊ ጉዞ አውላላ ሜዳ ላይ ጥሎታል።

የዶ/ር አቢይ እቅድ ልክ እንደ ሕወሃት በተቃረኑ አካላት መካከል ራስን ብቸኛ ገላጋይ አድርጎ ስልጣን ማራዘም ነው። ይህ ማለት ብአዴንን ጨምሮ ማንም አካል ጥጉን ይዞ ብሶት ከማሰማት፤ ከመክሰስ ከመካሰስ፤ ከመታዘዝ አልፎ የመፍትሄው አካል እንዲሆን አይፈቀድለትም። ምክንያቱም “ዳኝነት” “አዳኝነት” ለዶ/ር አቢይ ብቻ የሚተው ሥራ ስለሆነ። ለዚህ እንዲያመች ደግሞ፤ ብአዴን ውስጥ በራስ እግር ለመቆም እና የበሰለ ፖለቲካ ለማራመድ የታየው ተነሳሽነት መቀልበስ ነበረበት። ሲሆን የነበረውም ይሄው ነው። በተለይ፤ በተገደሉት የክልሉ አመራሮች ምትክ፤ የዶ/ር አቢይ ጓደኛ ተመስገን ጥሩነህ ክልሉን እንዲያስተዳድሩ ከተሾሙ እና ብልጽግና ከተመሰረተ በኋላ ብአዴን የራሱ ህልውና አለው ለማለት ያስቸግራል። በዶ/ር አቢይ አጀንዳ ተጠምዝዞ ነገር አለሙ ዙሮበታል።

ብአዴኖች፤ ሕወሃት ጥግ ከያዘ በኋላ የሚኖረው ቀጣይ ምዕራፍ ምን መልክ ሊኖረው እንደሚገባ፤ ለውጡ የታሰበውን ውጤት እንዲያመጣ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ቀድመው አስበው፤ በቂ ቅድመ ዝግጅት እና ጥንቃቄ ማድረጋቸውን እጠራጠራለሁ። የዶ/ር አቢይ አካሄድ፤ ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንዲሉ፤ በጣም ሲስተማቲክ፤ ከቀጥተኛ ጫና ይልቅ ስነልቦናዊ ማጨናበር እና የእጅ አዙር ጥቃት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ደግሞ፤ አዲስ ወጥመድ ውስጥ እየገቡ እንደሆነ ለመረዳት እንኳን እድል የሰጣቸው አልመሰለኝም። በወቅቱ ትኩረቱ ሁሉ ወደ ዶ/ር አቢይ መሄዱም፤ የብአዴን ሰዎች የራሳቸውን ድምጽ እንዲያጡ የራሱን አሉታዊ ተጽእኖ ያደረገ ይመስለኛል። ያም ሆነ ይህ፤ ብአዴን ውስጥ አቆጥቁጦ የነበረው ተስፋ፤ ለአማራ ሕዝብም ለኢትዮጵያም ሳይሆን፤ የዶ/ር አቢይ ስልጣን መወጣጫ ብቻ ሆኖ በአጭሩ ተቀጭቷል። የብአዴን ስብርባሪ ላይ የተሰራው የአሁኑ የአማራ ብልጽግና አመራሮች፤ ተረዱትም አልተረዱትም፤ ዶ/ር አቢይ በቀየሱላቸው መንገድ ጭልጥ ብለው ተወስደው፤ የዶ/ር አቢይን ቲያትር በመተወን ላይ ናቸው። ከመካከላቸው ነገሩ ያላማራቸው ሰዎች ሊኖሩ ቢችሉም እንኳን፤ አሁን ባለው ሁኔታ ተጋፍቶ ለመውጣት አቅም ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው።

……………………………………..//……………………………………..

ኢሕአዴግ በውጫዊ ግፊት ከሥሩ ተመንግሎ፤ ሀገሩን አብሮ ይዞ ከመውደቁ በፊት፤ እዛው ኢሕአዴግ ውስጥ በተደረገ የኃይል ሽግሽግ፤ የድርጅቱ ቁንጮ የነበረው ሕወሃት በሰላም ጥግ የሚይዝበት አጋጣሚ መፈጠሩ፤ በወቅቱ የነበረውን ውጥረት አስተንፍሶ፤ ለጊዜውም ቢሆን ሀገር አትርፎአል። ከዚያም አልፎ ክስተቱ፤ ሳይጠፋፉ የመተካካትን የፖለቲካ ባህል ለመላመድ ጥሩ እርሾ የመሆን እድል የነበረው ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ ነበር። በሕወሃት እና በአዲሱ የዶ/ር አቢይ መንግስት መካከል እያደር የተፈጠረው ፍጥጫ ጡዞ ጡዞ ወደ ለየለት ጦርነት ሲያድግ ግን ሁሉም ነገር እንዳይሆን ሆኗል።

የሀገር የጦር ኃይል ላይ ጥቃት ማድረስ ቀላል ወንጀል፤ ቀላል ክህደት አይደለም። ሕወሃት በመከላክያ ሰራዊቱ ላይ ያደረሰውን ጥቃት መነሻ አድርገን ከመዘነው፤ ጥፋተኝነቱን ሙሉ ለሙሉ ለሕወሃት መስጠቱ ያስኬዳል።  ወደ ኋላ ተመልሰን አጠቃላይ በሕወሃት እና በፌደራል መንግስቱ መካከል የተፈጠረውን ትንቅንቅና የተጓዘበትን መንገድ ከቃኘን ግን፤ ዉጥረቱ ከሮ ከሮ እዚህ ለመድረሱ ዶ/ር አቢይ የነበራቸው አስተዋጽዖ ከሕወሃት ቢበዛ እንጅ የሚያንስ አይደለም።

ሕወሃት ከአራት ኪሎ የተነሳው በደረሰበት የፖለቲካ ጫና እንጅ በጦር አልነበረም። በቀጣይም፤ ከሕወሃት በኩልም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ሊመጣ የሚችል ስጋትን ለመከላከል አዋጩ እና ዘላቂው መፍትሄ፤ በለውጡ የተፈጠረውን የስምምነት መንፈስ አጠናክሮ፤ ሁሉን አቀፍ የብሔሄራዊ ውይይት መድረክ በማመቻቸት፤ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር መንገድ መጥረግ ነበር። ዶ/ር አቢይ ነገሩን ወደ ስልጣን ሽኩቻ ባይቀይሩት እና ይህን ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ ሕወሃት ወይ ራሱን ከሁኔታው ጋር አስማምቶ አብሮ ይጓዝ ነበር፤ ያለዚያም በአጠቃላይ ሀገራዊ ፖለቲካው ተጽእኖ ውስጥ ወድቆ በጊዜ ሂደት ተፈጥራዊ የፖለቲካ ሞቱን ያገኝ ነበር። ዶ/ር አቢይ አደራ የተሰጣቸውን ሀገርን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የማሻገር አጀንዳ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው፤ የግል ስብዕናቸውን የመገንባት እና የራስን ስልጣን የማደላደል ተግባር ላይ መጠመድ ስለመረጡ ይህ የሰላም መንገድ እድል አላገኘም።

ለውጡ ሦስት አመት አለፈው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አንድ የረባ ሀሳብ ላይ ፍሬ ያለው ውይይት እና ክርክር አልተደረገም። አንድም ነገር ውል ያለው ማሰሪያ አልተበጀለትም። ለውጡ ዶ/ር አቢይ ጭንቅላት ላይ ብቻ በተቀመጠ ፍኖተ ካርታ ነው እየተንጠራወዘ ሲጓዝ የነበረው። ቀጥለው ወዴት አቅጣጫ እንደሚቀዝፉ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። በዚህ ምክንያት፤ ሌላው ወገን የሳቸውን እጥፋቶች እየተከተለ ወዲያ እና ወዲህ ከመላተም ውጭ፤ ግልጽ አቅጣጫ ተከትሎ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማድረግ አልቻለም። ተቀራርቦ በመነጋገር ልዩነቶችን ማስታረቅ የሚቻልበት መንገድ ሲዘጋ መጋጨት የማይቀር እዳ ይሆናል። ሀቀኛ እና ሁሉንም ያሳተፈ ውይይት እንዳይደረግ መንገድ መዝጋታቸው በራሱ፤ ዶ/ር አቢይን ብዙ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ ሀዲዱን ስቶ ወደ ግጭት እና ጦርነት ለመግባቱ ዋና ተጠያቂ ያደርጋቸዋል።

መንግስት፤ የሰኔ 16ቱን የመስቀል አደባባይ የቦንብ ፍንዳታ ጨምሮ ሌሎች አካባቢዎች ላይ ለደረሱ አደጋዎች የሕወሃት ሰዎች እጅ እንዳለበት መረጃውን ማቅረብ ከቻለ፤ ከሁኔታው ጋር የቀጥታ ንኪኪ ያላቸው ሰዎችን አጣርቶ፤ በዛ ወንጀል ዙርያ የታጠረ ክስ መመስረቱ ተገቢ ይሆናል። አልፎ ሄዶ፤ በይፋ ተዘግቷል የተባለን የኋላ ፋይል በመምዘዝ፤ በደህንነት እና በሜቴክ ሰዎች ላይ አነጣጥሮ የተጀመረው ክስ እና እስር ግን አላስፈላጊ ጠብ አጫሪነት ነበር። በዚህ ድርጊታቸው፤ ዶ/ር አቢይ ሕወሃቶችን ለህልውናቸው የሞት ሽረት ሲወራጩ ይባስ ሀገር ወደሚያተራምሱበት መንገድ ገፍተዋቸዋል። እግረ መንገዳቸውን፤ የትግራይ ሕዝብንም፤ ከሕወሃት ጎን ከመሰለፍ ውጭ ለደህንነቱ ሌላ ዋስትና እንደሌለው እንዲሰማው አድርገውታል። አጠቃላይ በለውጡ ተፈጥሮ የነበረውን የመተማመን መንፈስም ትርጉም ለሌለው ነገር ክፉኛ ጎድተውታል።

ዶ/ር አቢይ ኢሕአዴግን አፍርሰው ብልፅግናን የመሰረቱበት መንገድ፤ ሌላው በዶ/ር አቢይ እና በሕወሃት መካከል የነበረውን ግንኙነት ላይጠገን የሰበረው ክስተት ይመስለኛል። ለውይይት እና ክርክር እድል ኑሮ፤ በሀሳብ አለመስማማት መለያየት አንድ ነገር ነው። የሆነው ግን ይህ አይደለም። የውህደቱ አጠቃላይ ሂደት በዶ/ር አቢይ ፍላጎት ተጽእኖ የወደቀ ነበር። ለሀቀኛ የሀሳብ ፍጭት ክፍተት አልነበረም። ብልጽግናን የመመስረቱ እቅድ ዜና እየገፋ መምጣትን ተከትሎ፤ ከሕወሃት በኩል ጠንካራ ተቃውሞ ሲሰማ፤ ዶ/ር አቢይ ሁኔታውን ፊት ለፊት ተጋፍጦ መልክ ከማስያዝ ይልቅ፤ “ገና ሀሳብ ላይ ላለ ነገር ምንድን ነው ይህን ያህል ጫጫታ” እያሉ ማድበስበስ እና ማዘናጋት ነው የመረጡት። ይህን ባሉ ሁለት እና ሦስት ሳምንት ውስጥ ግን፤ ኢሕአዴግ መፍረሱ እና ብልጽግና መመስረቱ በይፋ ታወጀ። አይደለም እንዲህ ስንኩሉ በበዛበት ሁኔታ፤ ውህደቱ እንከን የለሽ በሆነ ሂደት አልፎ ቢሆን ኖሮ እንኳን፤ ሕወሃቶች የፈጠሩትን ድርጅት ለማክሰም ፖለቲካዊ እና ስነልቦናዊ ዝግጅቱ የነበራቸው አይመስለኝም። ሆኖም በነበረው ሁኔታ፤ ሕወሃትን ከውህደቱ አፈንግጦ ወጣ ብሎ መኮነን አይቻልም።

ሕወሃቶችን፤ አለቃ ሆነው በኖሩበት ድርጅት ውስጥ እኩልነትንም ማላመድ ቀላል ስራ ይሆን የነበረ አይመስለኝም። ዶ/ር አቢይ ግን ጭራሽ ኢሕአዴግን አፍርሰው፤ እሳቸው እንደ አዲስ በቀረጹት ፓርቲ ውስጥ ገብቶ ጀሌ የመሆን ምርጫ ነው ያቀረቡላቸው። ሕውሃቶች ይህን አሜን ብለው ሊቀበሉ አይችሉም። የዶ/ር አቢይም፤ ፍላጎት ይህ እንዲሆን እንደነበር ነው የማስበው። ምን አልባትም፤ የውህደቱ አንዱ አላማ፤ ሕወሃትን ከውስጥ የፓርቲ ስራቸው የማስወገጃ ሽፋን ፍለጋ ሳይሆን አይቀርም። ዶ/ር አቢይ ብልፅግና በተመሰረተ ሰሞን ባሌ ላይ አደረጉት በተባለ የኦሮምኛ ንግግር  “ከኦሮሞ ጠላቶች ጋር አብረን ላለመስራት ነው ብልጽግናን የመሰረትነው” ሲሉም “ለኦሮሞ ብለን” የሚለው ሽንገላ ሲቀር፤ ከሕወሃት መፋታት ግን፤ እውነትም የእቅዳቸው አካል እንደነበር በራሳቸው አንደበት አረጋግጠዋል።

ዶ/ር አቢይ በዚሁ የባሌ ንግግራቸው፤ “ትናንት ያዋረዱንን አዋርደናቸዋል” “ትናንት መግባት መውጣት የከለከሉን፤ ዛሬ ከእኛ ፈቃድ ውጭ ካልሆነ ገብተው መውጣት አይችሉም” እያሉ ያዥጎደጎዱትን ንግግር ይዘት እጅግ ኢፍትሃዊነት፤ እጅግ ጸረ ዲሞክራሲዊነት መሆኑን ብንተወው እንኳን፤ የኢትዮጵያ መዳን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ግድ ከሚለው አንድ የሀገር መሪ አንደበት በፍጹም ሊወጣ የሚችል ንግግር አይደለም። ዶ/ር አቢይ ያሉትን ሲሉ፤ ከሕወሃት ሰዎች ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ወደፊት ለእሳቸው፤ ለአቢይ አህመድ አልካድምም ብሎ ከሚያስቸግር ማንም ግለሰብም ሆነ ቡድን ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር ምን እንደሚመስል ቁልጭ አድርገው ነው ያሳዩት። ሕወሃቶች ይህን እየሰሙ ቢደነብሩ አይገርምም። ይህን መሰሉ የዶ/ር አቢይ ንግግር፤ ለሁሉም ወገን፤ የሰውየው ማንነት ላይ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባ ነበር።

አንድ ጊዜ፤ ያለብዙ ትርምስ ሕወሃትን ከፌደራል መንግስት ይዞታው ማስለቀቅ ከተቻለ በኋላ፤ ቢያንስ ለቋሚ ሀገራዊ ስርአት መሰረት እስኪጣል ድረስ፤ ልዩነትን አስታሞ አብሮ መቀጠሉ ለሀገር መረጋጋት የተሻለው መንገድ ነበር። ሕወሃቶች በቀድሞ ቁመናቸው ላይ አልነበሩም። ያ ባይሆን ኑሮ ቀድሞ ነገር፤ ኦህዴድ እና ብአዴን አይናቸው ስር ጥርስ ማውጣት ባልጀመሩ ነበር። ከነሱ ፈቃድ ውጭ ዶ/ር አቢይን በሊቀመንበርነት ማስመረጥም ባልተቻለ ነበር። የለውጥ ኃይሉ፤ ከለውጡ በፊት በዚህ ደረጃ ሕወሃትን መጋፋት ከቻለ፤ ጭራሽ የፌደራል ስልጣን በእጁ ካስገባ በኋላ ከሕወሃት በኩል የሚመጣውን ተግዳሮት ለመቋቋም የሚያስችለው አቅም ያጣል ብሎ ማሰብ ይቸግራል። ኢሕአዴግ ውስጥ ያሉት ሌሎቹ ድርጅቶች እና አጋር ድርጅቶች በነጻነት እና በእኩልነት የሚሳተፉበት ሁኔታ ቢመቻች ኑሮ፤ ዞሮ ዞሮ ሕወሃት ኢሕአዴግ ውስጥ ሁኖ ቢቀጥልም የሚኖረው ተጽእኖ ያን ያህል አይሆንም ነበር። እንዲያውም የድርጅቱ አካል ሆኖ መቀጠሉ እንቅስቃሴውን በፓርቲ ህገ ደንብ ማዕቀፍ ውስጥ ለመገደብ የተሻለ አቅም ይፈጥርላቸው ነበር። ዶ/ር አቢይ፤ ያለምንም ተገዳዳሪ እንዳሻቸው የሚያዙት ፓርቲ ሰለፈለጉ ይህን ማድረግ አልፈለጉም።

በግልባጩ፤ ዶ/ር አቢይ፤ ሕወሃትን ፈተው ሜዳ ላይ በመልቀቃቸው፤ ሕወሃት ከወደቀበት ተነስቶ፤ እንዲያንሰራራ መንገድ ከፍተዋል። ምንም ብልፅግና የዶ/ር አቢይን የአገዛዝ እቅድ ከማሳካት ውጭ ሌላ ፋይዳ ባይኖረውም፤ የኢሕአዴግን መፍረስ የብሔር ተኮር ፌደራሊዝሙ ላይ የተቃጣ አደጋ አድርገው የወሰዱ ሌሎች ወገኖች በሕወሃት ዙርያ እንዲሰበሰቡ እና “አሀዳዊ መንግስት ሊመለስ ነው” የሚል ውጥረት እና ዘመቻ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። ሕወሃት የፖለቲካ ካፒታሉን አንጠፍጥፎ የጨረሰ ድርጅት ነበር። ዶ/ር አቢይ ፊታቸውን ሀገራዊ ስርአት መዘርጋት ላይ አዙረው፤ ሕወሃት ጣረሞቱን ጨርሶ ተፈጥሮአዊ የፖለቲካ ሞቱን እንዲያገኝ መተው ይችሉ ነበር። ነገር ግን፤ ተቀናቃኞቻቸውን በፍጥነት ደምስሶ፤ መላ ሀገሩን በእጃቸው መዳፍ ለማስገባት ባላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ፤ ሞት አፋፍ የነበረን ድርጅት እየተነኮሱ እንደገና ነፍስ እንዲዘራ አድርገዋል።

ዶ/ር አቢይ፤ ሀገር ለመጠቅለል በሚያደርጉት ጉዞ፤ አጋር ድርጅቶችን ጨምሮ ከሕወሃት ውጭ ያለውን ኢሕአዴግን በብልጽግና ጥላ ሥር በእሳቸው የእዝ ሰንሰለት ውስጥ ማስገባቱ በጊዜ ተሳክቶላቸዋል። ሀገር በብቸኘነት የሚያስተዳድረው ብልፅግና እስከሆነ ድረስ፤ ፓርቲያቸውን ጠቀለሉ ማለት፤ የመንግስት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በእጃቸው አስገቡ ማለት ነው። የቀረው ትግራይ ነው። ሕወሃት ትግራይን በተቆጣጠረበት ሁኔታ፤ የዶ/ር አቢይ፤ ያለምንም ተቀናቃኝ መላ ሀገሩ ላይ አድራጊ ፈጣሪ የመሆን እቅድ አይሟላም። ኦህዴድን እና ብአዴንን በጠለፉበት መንገድ በውስጥ በኩል ገብተው ሕወሃትን ሊያንበረክኩ የሚችሉበት መንገድ የለም። ስለዚህ ያላቸው ብቸኛ አማራጭ ሕወሃትን ከውጭ በኩል አዋክቦ ማሽመድመድ ነው። ወደ ጦርነት የተጎተትንበት መሰረታዊ ምክንያትም ከዚህ የገዘፈ አይደለም።  

ይህን የምለው መከላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰውን ጥቃት አቅልሎ ከማየት አይደለም። የተፈጸመው ከባድ የሀገር ክህደት ወንጀል ነው። ሕወሃቶች ጥቃቱን ያደረሱት፤ የኃይል አማራጩ ይሻለናል ያዋጣናል ብለው አስልተው እስከሆነ ድረስ፤ የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ለደረሰው ጥቃት፤ ለጦርነቱ መቀስቀስ እና ላስከተለው መዘዝ በሙሉ ተጠያቂ ናቸው። እነሱ ሦስት አስርት ዓመታት፤ የሁሉንም ማንቁርት ይዘው፤ መፈናፈኛ አሳጥተው በገዙበት ሀገር፤ መገፋፋቱን ታግሶ፤ ሌሎች አማራጮችን እያዩ ጥቂት ለመቆየት አቅል አጥተው፤ ጦርነት ጭረው፤ የሕዝብ እና የሀገር ደህነነትን አደጋ ላይ መጣላቸው የበደል በደል ነው። የሆነው ሁኖ ግን፤ የሕወሃት ጥፋተኝነት የዶ/ር አቢይን ጥፋት አያጣፋውም። የሕወሃት ኃጥያት ዶ/ር አቢይን ጻድቅ አያደርጋቸውም። ዶ/ር አቢይ፤ ሕወሃቶችን ይተነኩሱ የነበሩት፤ ተደናብረው እና እልኸ ውስጥ ገብተው፤ በማያዳግም ሁኔታ ለመምታት የሚያመቻቸውን አሳማኝ ሰበብ እንዲሰጡአቸው ነበር። ሕወሃቶች የሰሜን እዝ ላይ በሰነዘሩት ጥቃት፤ ዶ/ር አቢይ በተጠንቀቅ ይጠባበቁት የነበረውን አጋጣሚ አበርክተውላቸዋል። የመከላከያ ሠራዊቱ የተከዳው በሁለት ወገን ነው። የሰሜን እዝ ላይ ለደረሰው ጥቃት እና ለተቀሰቀሰው ጦርነት፤ ዶ/ር አቢይ ከሕወሃት ባልተናነሰ መልኩ ተጠያቂ ናቸው።

……………………………………..//……………………………………..

ምንም የዶ/ር አቢይ እና የሕወሃት ግብ ግብ የሕዝብ እና የሀገርን ጥቅም ማዕከል ያደረግ ባይሆንም፤ ኪሳራው ለሕዝብ እና ለሀገር መትረፉ ግን አልቀረም። የሰሜን እዝ ላይ በደረሰው ጥቃት የጠፋው ሕይወት እና ንብረት ኪሳራው ለሀገር ነው። በዚህም በዚያም በኩል ተሰልፎ ህይወት እና አካሉን እየገበረ ያለውም የኢትዮጵያ ወጣት ነው። በጦርነቱ የደረሰው አጠቃላይ የንብረት ውድመትም እንዲሁ ኪሳራው ለሕዝብ ነው። ለሀገር ነው። በማይካድራ ጭፍጨፋ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡት ንጹሃን ዜጎችም የዚሁ ግጭት ሰለባ ናቸው። የሱዳን ወረራም፤ ጦርነቱ የመዘዘው ሌላ የሀገር ራስምታት ነው። ግጭቱ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ቀውስ፤ ከሁሉም በላይ የጦርነቱ አስከፊ እና አሳሳቢ ገጽታ ሆኖ እንደቀጠለ ነው።

ጦርነቱ በዚህም ሆነ በዚያ ምክንያት ተፈጠረ ተባለ፤ ጦርነቱ ሊያስከትል የሚችለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመቀነስ አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ የማዕከላዊ መንግስት ኃላፊነት ነበር። ይህ አልሆነም። የዶ/ር አቢይ መንግስት፤ ለጦርነት ቅስቀሳው የፈጠረውን ወከባ በጥቂቱ እንኳን የሚመጥን ትጋት እዚህ ላይ አልታየበትም። በተቃራኒው ጦርነቱ ያስከተለውን ጥፋት የማድበስበስ ዘመቻ ላይ ተጠምዶ ነው ጊዜውን ያሳለፈው። የኤርትራ ሰራዊት ሳይቀር፤ የሀገሪቱ ሜካናይዝድ ጦር የተሳተፈበትን ጦርነት፤ “ህግ የማስከበር እርምጃ” በሉ የሚል ድርቅና ውስጥ ነው የከረምነው። ጦርነትን ጦርነት የሚያሰኙት ጥቅም ላይ የዋለው የጦር መሳሪያ አይነት እና መጠን፤ የሚያስከትለው ውድመት እና መሰል ነገሮች ናቸው። በተረፈ፤ የግጭቱን ባህሪ መደበቅ ካልተፈለገ በስተቀር፤ ለጦርነት ከጦርነት ሌላ ስያሜ የለውም።

አጠቃላይ የዶ/ር አቢይ መንግስት፤ ጦርነቱን፤ የሰላማዊውን ሕዝብ ኑሮ በምንም መልኩ ያላስተጓጎለ፤ ጥቂት ተፈላጊ ሰዎችን ለቅሞ እንደመያዝ የቀለለ የፖሊስ ኦፕሬሽን አድርጎ ለማሳየት ልክ ያጣ ርቀት ነው የተጓዘው። “99% ታርጌት መተናል 99% ኮላተራል ዳሜጅ አላመጣም” እያሉ ይህን የሕዝብ ሰቆቃ የማዳፈን ዘመቻ ከፊት ሆነው የመሩት ደግሞ ራሳቸው ዶ/ር አቢይ ናቸው። የጦርነቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ ለፓርላማው ባደረጉት ገለጻ፤ ሰለ ተፈናቀሉ ዜጎች አንስተው የተናገሩት “መፈናቀል ብርቅ ነው እንዴ” አይነት ማላገጥ፤ ከመነሻው የሕዝብ እንግልት ለማጣጣል ለሄዱበት ለከትየለሽ ጥግ አንዱ ማሳያ ነው። ይባስ ብለው፤ ይቀጥሉና፤ በወቅቱ በትንሹ ሠላሳ እና ሃምሳ ሺህ ይገመት የነበረን ስደተኛ፤ በጅምላ “ገዳይ” በሚል ተለጣፊ ለቅልቀው ያልፋሉ።

መደበኛም ጦርነት ቢሆን እንኳን በሰላማዊ ዜጋ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ የሚያስከትለው እክል ቀላል አይደለም። ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሳምንታት የተከሰተው የኮሚውኒኬሽን፤ የሕክምና እና መሰል የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መስተጓጎል ብቻ እንኳን ሰላማዊው ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ጭንቀት እና እንግልት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። ሆኖም፤ እንደተባለው የፌደራል መንግስቱ ጦር መደበኛውን ጦርነት በቀላሉ ማጠናቀቅ ችሎ ይሆናል። ችግሩ ግን፤ መከላከያ ሰራዊት መቀሌን በተቆጣጠረ እና መንግስት የጦርነቱን ፍጻሜ ባወጀበት ጊዜ ግጭቱ አልተጠናቀቀም። መልኩን ቀይሮ እስካሁን እንደቀጠለ ነው። የትግራይ ሕዝብም በዚህ ትንቅንቁ እና ምስቅልቅሉ መቋጫ ባጣ አስከፊ ግጭት መኃል ተቀርቅሮ ከባድ ዋጋ እየከፈለ ነው።

ለጦርነት መንገድ አለመክፈት የመጀመሪያው ኃላፊነት የሞላው ተግባር ነበር። ያ ሳይሆን፤ ጦርነት ውስጥ ከተገባም፤ ቢያንስ የሰላማዊ ዜጎች ደህነነት ግድ መስጠት አንድ ነገር ነበር። በማንም ተፈጸመ ይባል በማን፤ ሁኔታውን ለመቆጣጠር መንግስት ኃላፊነት መውሰድ ነበረበት። የዶ/ር አቢይ መንግስት ግን፤ ሌላው ሌላውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ቀውስ አይደለም፤ የምግብ እጥረት መከሰቱን በገደምዳሜውም እንኳን ለማመን እና አካባቢውን በተወሰነ መልኩ ለእርዳታ ለመክፈት የወራት ግዜ ወስዶበታል። በመንግስት በኩል ግልጽነቱ ቢኖር፤ በጉዳቱ መጠን ዙርያ የሚታየው ውዥንብር እንዲጠራ እና ሁሉም ወገን ትኩረቱን ችግሩን ማቃለል ላይ እንዲያደርግ ይረዳም ይሆን ነበር። ነገር ግን፤ የተመተረ የተመጠነ፤ “ሰርጅካል ኦፕሬሽን” እያሉ ሲያቆለጳጵሱት የከረሙት “የህግ ማስከበር እርምጃቸው” እውነተኛ ገጽታ ተገልጦ፤ የዶ/ር አቢይ ፖለቲካ እንዳይበላሽ ሲባል፤ የትግራይ ሕዝብ በጨለማ ውስጥ እንዲሰቃይ፤ ሌላውም ሕዝብ የወገኑን ስቃይ ተረድቶ እንዳይጋራ ተደረጓል።

……………………………………..//……………………………………..

በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት እና ያስከተለው ምስቅልቅል ግንባር ቀደም ሰለባ የትግራይ ሕዝብ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። የጥፋቱ መዘዝ ግን በትግራይ የታጠረ አይሆንም። ከዚያ አልፎ፤ በሀገር ቀጣይ እጣ ፋንታ እና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት ላይ አደጋ የጋረጠ ክስተት ነው። ጦርነቱ፤ ድሮም በቋፍ ላይ የነበረውን የሀገሪቱ ፖለቲካ መላ ቅጡን ነው ያሳጣው። ግጭቱ በሀገር አንድነት ላይ የደቀነውን ፈተና ለማየት፤ ሌላ ሌላውን ትተን፤ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ በሕዝብ መካከል የተፈጠረውን የእይታ መራራቅ እና ቅራኔ ማጤኑ በቂ ይመስለኛል።

ከሕወሃት/ኢሕአዴግ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ፤ በአመዛኙ፤ ካልሆነም ቁጥሩ ቀላል በማይባል የትግራይ ተወላጅ እና በተቀረው ኢትዮጵያዊ መካከል የእይታ ልዩነት መፈጠሩ ከማንም የተደበቀ ነገር አይመስለኝም። አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ፤ ኢሕአዴግ ተመችቶት ነበር እንኳን ባይባል፤ በሌላው አካባቢ በታየው መጠን ከአገዛዙ ጋር የመረረ ቅራኔ ውስጥ አልገባም። ልሳሳት እችላለሁ ነገር ግን፤ ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ እና እኩልነት አስፍኗል። በጊዜ ሄደት የሚፈታ የልማት አለመሳለጥ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይኖራሉ። ከዚያ በተረፈ፤ በኢሕአዴግ በደል አፈና ታሪክ ሆኗል። ዲሞክራሲ እውን ሆኗል”  የሚለውን የሕወሃት/ኢሕአዴግን ፕሮፖጋንዳ የገዛው የትግራይ ተወላጅም ቁጥሩ የሚናቅ የነበረ አይመስለኝም። ይህ ግን እንደሚታወቀው የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እውነታ አልነበረም።

ይህን ስል፤ የትግራይ ሕዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ የተለየ ነጻነት ነበረው እያልኩ አይደለም። በርግጥ ሕወሃት፤ በእጅ አዙር ከሚያስተዳድራቸው ሊሎች አካባቢዎች በተለየ መልኩ፤ ትግራይ ውስጥ የተሻለ ተቀባይነትን አጣጥሟል። ያ ማለት ግን፤ የትግራይ ሕዝብ ቢፈልግ ሕወሃትን የመቃወም መብት ነበረው ማለት አይደለም። ቀን ጥሎት ከሕወሃት ጋር የተላተመ ትግራዋይ፤ ለሌላው ዜጋ የሚደርሰው ጡጫ እና ቁንጥጫ አይቀርለትም ነበር። በኢኮኖሚውም በኩል እንደዚያው ነው። በሕወሃት ዙርያ ከተኮለኮሉ ግለሰቦች ውጭ ያለው ሰፊ የትግራይ ተወላጅ የተለየ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ አልነበረም። ከሕወሃት የብሔር ተኮር ፖለቲካ፤ የትግራይ ሕዝብ ያተረፈው በጎ ነገርም አይታየኝም። ሲጀመር፤ የሕወሃት ፖለቲካ የሕወሃት ሰዎችን የስልጣን እድሜ ማራዘምን እንጅ የትግራይን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ታሳቢ አድርጎ የተቀመረ አልነበረም። የሕወሃት መሪዎች፤ ለትግራይ ሕዝብ ያላቸው ተቆርቋሪነት ከነሱ የኢጎ ጣራ አልፎ አያውቅም። ያ ባይሆን፤ የትግራይ ሕዝብ ትርፍ ሀገር ያለው ይመስል፤ ዘለአለም ነግሰው ላይኖሩበት ነገር፤ የአንድ ሀገሩን ህልውና አስይዘው ለስልጣን ባልቆመሩ ነበር።

የሆነው ሆኖ ግን፤ ሕወሃት በትግራይ ሕዝብ ስም፤ የትግራይ ነጻ አውጭ ነኝ ብሎ የተነሳ ድርጅት ነው። ከዚህ አንጻር፤ የትግራይን ሕዝብ በአንድም በሌላ መልኩ ከጎኑ ማሰለፍ መቻሉ ብዙም አይገርምም። ከማንነት ትስስሩም በላይ፤ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን እና ጥሪቱን ገብሮ ነው ሕወሃትን አራት ኪሎ ያደረሰው። ውጤቱ ከታለመው ነገር ጋር ገጠመም አልገጠመም፤ ውጣ ውረድ ያሳለፉበትን፤ ትዝታ ያካበቱበትን ነገር በነጻነት መመዘን ለማንኛችንም አዕምሮ ቢሆን አዳጋች ነው። ሕወሃቶችም፤ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሁሌም በትግሉ ግዜ ትዝታ እንደተቃኘ እንዲዘልቅ በትጋት ነው የሰሩት። ሕዝቡን፤ ከዚህ ማዕቀፍ ተሻግሮ ግራ ቀኙን እንዲያማትር፤ እነዚህ ሰዎች የሚሰሩት ስራ እውነት ይጠቅመኛል ወይ? ያዋጣልስ ያዛልቃል ወይ? ብሎ እንዲመረምር ፋታ ሰጥተውት አያውቁም። ከሌላው ማህበረሰብ አንጻር የትግራይ ተወለጆች አካባቢ፤ ለሕወሃት አገዛዝ የነበረም ምልከታ በአመዛኙ ቀና ሆኖ የዘለቀበት ዋና ምክንያት ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።

……………………………………..//……………………………………..

በሌላ ገጹ ግን፤ የተቀረው ማህበረሰብ፤ ራሱን የትግራይ ነጻ አውጭ ብሎ ከሚጠራ አካል ጋር የሚያስተሳስር ምንም ጉዳይ አልነበረውም። ኢሕአዴግ የሚለው ጭንብልም ማንንም አላታለለም። ልጅ አዋቂው የሚያውቀው ወያኔ ሀገር እንደተቆጣጠረ ነው። በረሃ ሳሉ ጀምሮ ስለ ፖለቲካቸው ይሰማ የነበረውም ነገር፤ በጥርጣሬ እንዲታዩ እንጅ ተስፋ እንዲጣልባቸው የሚያደርግ አልነበረም። ሀገር ከተቆጣጠሩ በኋላ፤ ብቸኛ አድራጊ ፈጣሪ ሆነው፤ ሀገሩን እንዳሻቸው መገለባበጥ፤ መነቃቀል፤ ያልወደዱትን ማሳደድ መጀመራቸው ደግሞ ምሬት የሚጨምር እንጅ የሕዝቡን እይታ ለማስቀየር የሚረዳ ነገር አልነበረውም። የሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ወለዱ ብሶት፤ እንዲህ እንዲህ እያለ፤ ለአመታት ሲበስል፤ ሲሞቅ ሲቀዘቅዝ ቆይቶ፤ በስተመጨረሻ ወደ ለየለት አመጽ ሲያድግ፤ ሕወሃት የድጋፍ መሰረቱ ባደረገው የትግራይ ሕዝብ እና በሌላው አካባቢ ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረው ውጥረትም አብሮ እየከረረ የመጣበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው።

ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ በመላው ኢትዮጵያ ያገኙት ተአምር የሚመስል ተቀባይነት የሚረሳ አይደለም። የትግራይ ሕዝብም እንዲሁ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በተስፋ ነው የተቀበላቸው። መቀሌ በሄዱበት ጊዜ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። የትግራይ ሕዝብ መሪዬ ብሎ፤ አክብሮ፤ አምኖ ችግሩን ሀሳቡን አጋርቷቸው ነበር። ዶ/ር አቢይ ይህን በሁሉም ዘንድ ያገኙትን ተቀባይነት እና ታማኝነት ተጠቅመው፤ በሕዝቡ መካከል የተፈጠረውን የስሜት መሻከር ለማከም እና ሕዝብ ለማቀራረብ ወርቃማ እድል ነበራቸው። ሌላ አጀንዳ ስለነበራቸው አልተጠቀሙበትም። ለጊዜው የትግራይን ሕዝብ ወርቅ ነው፤ ሞተር ነው፤ እንደዚህ ነው እንደዚያ ነው ብለው ሸንግለው ቢመለሱም፤ ሕወሃትን የመምቻው ጊዜ ሲደርስ ግን፤ የትግራይን ሕዝብ ከሕወሃት ጋር ደርበው ቅርቃር ውስጥ ከመክተት ወደ ኋላ አላሉም።

ዶ/ር አቢይ ሕወሃትን በማዋከብ ሂደት ውስጥ አብረው አጣብቂኝ ውስጥ እየከተቱት ስለነበር፤ የዶ/ር አቢይ እና ሕወሃት የነገር ውርዋሮሽ፤ ግብ ግብ ውንጫፊ በቀጥታ እየደረሰው ስለነበር፤ የትግራይ ሕዝብ፤ ከጦርነቱ ቀደም ብሎም፤ ቢያንስ ሕወሃት ጋር ከነበራቸው መስተጋብር አንጻር፤ የዶ/ር አቢይን የፖለቲካ ሴራ ለመታዘብ፤ ለእይታ አመች የሆነ ቦታ ላይ ነበር። ከለውጡ በኋላ፤ ነገር ተገላብጦ፤ በመንግስት ፕሮፖጋንዳ ከእውነታው የመጋረድ ተራ የሆነው ለሌላው ሕዝብ ነው።

ሕወሃት ለሦስት አስርት አመታት ፖለቲካውን፤ ንግዱን፤ መውጫ መግቢያውን፤ የሀገሪቱን ሁለ መና ተቆጣጥሮ ሕዝብ ሲገፋ፤ አንገት ሲያስደፋ የኖረ ድርጅት ነው። እነሱ ሀገሩ ላይ እንዳሻቸው ለማድረግ ከልካይ አልነበራቸውም። ሌላው ዜጋ ግን ድምጹን አጥፍቶ፤ እነሱ ሁን ያሉትን ሆኖ ከመኖር ውጭ ሌላ ምርጫ አልነበረውም። ያለ እነሱ ቡራኬ ምንም ነገር ለመስራትም ሆነ ለማሰብ መሞከር የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አልነበረም። በገዛ ሀገሩ ላይ እንዲህ ተሸብቦ መኖር በእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ የሚከምረው ምሬት እና ቁጣ ቀላል አይደለም። ያም ሆኖ፤ ለውጡ ሲመጣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ፤ ቁጭት እና ቁጣውን ደስታ አጥቦለት፤ የኋላውን ትቶ ወደ ፊት ለማየት ዝግጁ የሆነ ስሜት ውስጥ ነበር የነበረው። ዶ/ር አቢይ፤ ይህን የታደሰ መንፈስ ተመርኩዘው፤ ለአዲስ መግባባት እና ለአዲስ ስርአት መንገድ መጥረግ ሲገባቸው፤ የሕዝቡን ስሜት ወደ ኋላ እየጎተቱ፤ አይኑን ከነገ እድሉ ላይ ነቅሎ፤ አቅሙን አሟጦ ጨርሶ፤ ንብረቱን አስረክቦ የሸሸ ቡድን ላይ እንዲያደርግ፤ በትናንትና ፍርሃት እና ቁጣ ውስጥ እየዳከረ እንዲቆይ ሲያደርጉ ነው የነበሩት።

ሕወሃት ብዙ የወንጀል ዶሴ ያለው ድርጀት እንደመሆኑ፤ ሕወሃትን በምንም ነገር ከሶ ሌላውን ሕዝብ ማሳመን ከባድ ስራ አልነበረም። በግልባጩ ዶ/ር አቢይ፦ 1) በአንድ በኩል ጦር እየሰበቁ፤ በሌላ በኩል ለእርቅ ሽማግሌ የሚያንጋጉ አስመሳይ መንታ ምላስ ስለሆኑ 2) አብዛኛው ሰው የዶ/ር አቢይን እንቅስቃሴ የሚረዳው የለውጡ መጀመሪያ ላይ በነበረው ስሜት እና ተስፋ ውስጥ ሆኖ ስለነበር 3) ዶ/ር አቢይ የግል የስልጣን ራዕያቸውን በኢትዮጵያዊነት፤ በብሔራዊ ክብር ስብከት ውስጥ ጀቡነው ማሳለፍ ስለሚችሉበት፤ ሕወሃት ላይ ያደርጉት የነበረውን አላስፈላጊ ትንኮሳም ሆነ ሌሎች ጤናማ ያልሆኑ አካሄዶቻቸው ከአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እይታ ውስጥ እየገቡ አልነበረም። ሕወሃቶች፤ ዶ/ር አቢይ ቀለበት ውስጥ ገብተው የሚያሰሙት ፉከራ፤ ሌሎች ድርጅቶችን አሰባስበው ሲፈጥሩት የነበረው ግርግር እና ያደርጉት የነበረው ወታደራዊ ዝግጅት ደግሞ፤ ለአብዛኛው ሰው አይን፤ የዶ/ር አቢይ መንግስት፤ ሕወሃቶች ላይ በለውጥ አደናቃፊነት የሚያቀርበውን ክስ ታማኝነት ይባስ የማጠናከር ሚና ነበር የነበረው።

ይህን ስል ሕወሃት እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ነበር እያልኩ አይደለም። ሌላው ቢቀር፤ ጎንደር አካባቢ ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ለተቀሰቀሰው ግጭት ያቀብሉት የነበረው ግብዓት ብዙም የተደበቀ አልነበረም። ነገር ግን፤ በሕወሃት በኩል ሊፈጠሩ የሚችሉ ስጋቶችን ለመዝጋት የጦርነትን ያህል ዋጋ የማያስከፍሉ ብዙ አማራጮች ነበሩ። እየዘነጋን ካልሆነ፤ ቀድሞውኑ ሕወሃት ከስልጣን የለቀቀው በተፈጠረበት ፖለቲካ ጫና እንጅ በጦር አልነበረም። በሰላም አፈግፍገው መቀሌ የገቡት እንደተሸነፉ፤ ፖለቲካል ካፒታላቸውን መንዝረው እንደጨረሱ ስለተረዱ ነው። ዶ/ር አቢይ ስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ባይገቡ ኖሮ፤ ለቀው ከሄዱም በኋላ፤ በሕወሃት በኩል ሊመጣ የሚችል ማንኛውም ስጋት በፖለቲካ ሥራ ብቻ መገደብ የሚቻልበት እድል በጣም ሰፊ ነበር።

ሕወሃት ከሀገር ጫፍ ጦር ይዞ ተነስቶ፤ መላ ሀገሩን ማስገበር የቻለ ድርጅት እንደመሆኑ፤ አሁንም ወደ መቀሌ ከሸሹ በኋላ ሲያደርጉ የነበሩትን የጦር ነጋሪት ጉሰማ፤ መጨረሻም ላይ ሰሜን እዝ ላይ ያደረሱት ጥቃት፤ የቀደመ ቦታቸውን ለመያዝ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ተደርጎ መፈራቱ መሰረተ ቢስ አልነበረም። የዶ/ር አቢይ የፕሮፖጋንዳ ማሽንም ይህን እይታ ለመፍጠር በትጋት ሲሰራ ነው የነበረው። ጦርነቱን በመጀመር ሊያሳኩት የፈለጉትን ግብ በትክክል የሚያውቁት ራሳቸው ሕወሃቶች ናቸው። ነገር ግን፤ ወደ ኃይል ጥቃት የወሰዳቸው የፌደራል መንግስቱን ተመልሰን እንቆጣጠራለን የሚል ቅዠት አይመስለኝም። ስሌታቸው ትክክል ባይሆንም፤ ሠራዊቱ ላይ ያደረሱትን ዘግናኝ ጥቃት ባያቀለውም፤ በእውር ድንብር፤ ዶ/ር አቢይን የሚገዳደሩበት መንገድ የፈጠሩ መስሎአቸው የገቡበት ነገር እንደሆነ ነው የሚሰማኝ።

ለውጡ በጥሩ አነሳስ ነበር የጀመረው፤ ከአገዛዙ ላይ የመረረ ቁጣ ካነገቡ የውጭ ኃይሎች ይልቅ፤ እዛው ኢሕአዴግ ውስጥ፤ ከሕወሃቶች ጋር ትስስር ያላቸው አካላት የለውጥ መሪ ሆኖ መውጣት፤ በትግራይ እና በተቀረው ማህበረሰብ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ለማስታረቅ መልካም አጋጣሚ ነበር። በለውጡ ዋዜማ፤ በኦሮሚያ እና አማራ ቴሌቪዥን ላይ ይቀርቡ የነበሩ ፕሮግራሞች፤ ከተለመደው ሕወሃት/ኢሕአዴግ ትርክት ማፈንገጣቸው እንዳለ ሁኖ፤ ሕወሃትን በቀጥታ ከማውገዝ ግን የተቆጠቡ ነበሩ። አመራሮቹም እንዲሁ፤ በሕወሃት/ኢሕአዴግ መሪነት ሲቀነቀን የነበረውን አስተሳብ የሚቀለብስ እንጅ ሕወሃቶችን በቀጥታ የሚተናኮል መልእክት ሲያስተላልፉ አይሰሙም ነበር። ዶ/ር አቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጥቂት ግዜያት በኋላ፤ እሳቸው አራት ኪሎ እስኪደርሱ ድረስ ለውጡ የመጣበትን መንገድ ቀኝ ኋላ ጠምዝዘው የትናንቱን ብቻ ሳይሆን በእሳቸው አስተዳደር ለሚደርሰው ቀውስ ሁሉ ሕወሃት ላይ ጣት መቀሰር መጀመራቸው ነው ሁሉንም ነገር ያበለሻሸው።

ዶ/ር አቢይ ባለፉት ሦስት አመታት በየአካባቢው ለተከሰቱት ግጭቶች እና ግድያዎች ግንባር ቀደም ተጠያቂ ሲያደርጉ የነበሩት የሕወሃትን ሰዎች ነው። ከለውጡ በኋላ ሕወሃት ላይ ያለው ቁጣ ከመቀዝቀዝ ይልቅ እየናረ የቀጠለበት ዋና ምክንያትም ይሄው ይመስለኛል። በርግጥ ግጭት እንደ ችግኝ የሚፈላበትን መደብ ማን ደልድሎት እንደሄደ ለማንም ግልጽ ነው። ዛሬ ዶ/ር አቢይ እነሱንም፤ ሀገር ምድሩንም እየተረኩሱበት ያሉበትን ፍም አቀጣጥለው ጥለውላቸው የሄዱት ሕወሃቶች ናቸው። ያ እንዳለ ሆኖ ግን፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተፈጠረውን ክስተት በሙሉ በሕወሃት የሚቀናበር እና ፋይናስ የሚደረግ፤ ሕወሃት ሲወገድ ሁሉም ነገር መፍትሄ የሚያገኝ አድርጎ ማቅረቡ እውነትን የተመረኮዘ አልነበረም። ዛሬ ሕወሃት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቸኛው ተዋናይ አይደለም። ሕወሃት ስልተወገደ የሚፈጠር ተአምር የለም። ዶ/ር አቢይ፤ ሆን ብለው የሕወሃትን ወቅታዊ ሚና ያላግባብ አግዝፎ በማሳያት፤ ሕዝብን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ መርተዋል።

ሕወሃት ኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሰ ቡድን መሆኑ አይካድም። የእነሱ የስልጣን ምኞት እንዲሳካ አሥራ ሰባት አመት የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦርነት ታምሷል። ስልጣን ላይ ከወጡ በኋላም፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ በስንት ሀገር ወዳድ ዜጎች የዘመናት ልፋት የተገነቡ የሀገሪቱን ተቋማት አውድመዋል። ለእነሱ አገዛዝ የተመቸ ሀገር ለመፍጠር፤ የሀገር መሰረት የሚያናጋ ብዙ ተግባር ፈጽመዋል። የሀገር ሀብት ዘርፈዋል። ትውልድ አቆርቁዘዋል። ሕዝብ አንገላተዋል። ከሁሉም በላይ፤ በኢትዮጵያዊያን መካከል የመፈራራት እና የአለመተማመን መንፈስን በመዝራት የሀገሪቱን መጻኢ እድል ፈተና ውስጥ አስገብተዋል። ነገር ግን፤ አይነቱ እና መጠኑ ይለያይ እንደሆን እንጅ፤ ጭካኔ እና ተንኮል በሕወሃት የተጀመረ በሕወሃትም የሚጠናቀቅ ነገር አይደለም። ስልጣን የመጠቅለል ከባድ ፍላጎት ውስጥ የወደቀ የትኛውም አካል፤ ለእቅዱ መሳካት አስፈላጊ መስሎ እስከታየው ድረስ፤ ማንኛውምንም ሴራ እና ግፍ ከመፈጸም የሚገታው የሞራል ልጓም አይኖረውም። የሰው ልጅ ታሪክ ደግሞ ደጋግሞ የሚያስገነዝበን ይህንን ነው።

……………………………………..//……………………………………..

በሕወሃት እና በዶ/ር አቢይ መንግስት ማካከል የተፈጠረው ትንቅንቅ ወደ ጦርነት ከማደጉ በፊትም፤ በሁለቱም በኩል ጠባቸውን ለመርህ እና ለህግ መከበር የሚደረግ ትግል አድርጎ የማቅረብ ሁኔታ ይታይ ነበር። ነገር ግን፤ ምርጫ አታድርግ አደርጋለሁ እሰጣገባውን ጨምሮ፤ አንዳቸውም ሲወዛገቡባቸው የነበሩ ጉዳዮች፤ በዶ/ር አቢይ በኩል ሕወሃትን ለማንበረከክ፤ በሕወሃቶች በኩል ለዶ/ር አቢይ ጫና ላለመበገር ከሚደረግ ትንቅንቅ ባለፈ፤ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ከመወሰንም ሆነ ህግን ከማስከበር አንጻር ሚዛን የሚደፉ አልነበሩም። ጦርነቱም በተመሳሳይ የዚሁ መጓተት ተቀጥላ እንደመሆኑ ምንም ሀገራዊም ሆነ ህዝባዊ ፋይዳ አልነበረውም።

የራሱ ሕወሃት ድርጊት አስተዋጽዖ ታክሎበት፤ ዶ/ር አቢይ ከሕወሃት ጋር የገቡትን ግብ ግብ ለሀገር አንድነት፤ ለህግ መከበር፤ የተደረገ ዘመቻ አስመስሎ ማቅረቡ ተሳክቶላቸዋል። እውነታው ግን ይህ አይደለም። ከዚህ ምስቅልቅል ሀገር የምታተርፈው አንዳች ነገር የለም። ሕወሃት ስለተወገደ የሚፈጠር ተአምር የለም። ለኢትዮጵያ ቀን ወጥቶላት የነበረው፤ የዛሬ ሦስት ዓመት፤ ሕወሃት ከፌደራል መንግስት ይዞታው ተነስቶ፤ ለአዲስ መግባባት እና ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ በር ተከፈቶ የነበረ ግዜ ነው። ያን እድል አልተጠቀምንበትም። አሁን ከሕወሃት ጋር የሚደረገው ትንቅንቅ፤ ልክ ደርግ ወደ ስልጣን ሲወጣ፤ ዘውዳዊውን አገዛዝ ነቃቅሎ መጣል አልበቃ ብሎት፤ አዛውንት ባለስልጣኑን መረሸን፤ ባላባቱን ብቻ አይደለም በገዛ ጉልበቱ ሰርቶ ገንዘብ ያፈራውን ሁሉ አድሃሪ እያለ ማሳደድ እንዳስፈለገው ሁሉ፤ ኢሕአዴግ  የኢትዮጵያን ወጣት እና የሀገር ንብረት ባስፈጀ ጦርነት ደርግን ደምስሶ ስልጣን ላይ ሲወጣ፤ ከኪነት ቡድን አቅም ሳይቀር፤ ከደርግ ኢሰፓ ጋር ንክኪ አላቸው የተባሉትን ተቋማት ሁሉ ማፈራረስ፤ የደርግ ርዝራዦችን በመንቀል ሰበብ በሕዝብ ሀብት የተማሩ ባለሟያዎችን ከየቦታው መንቀል እና ማሳደድ እንዳስፈለገው ሁሉ፤ አሁንም እያየን ያለነው፤ አዲሱ አምባገነን አሮጌውን አምባገነን ከሀገር ምድሩ መንጥሮ አውጥቶ፤ የራሱን አገዛዝ በመልኩ በአምሳሉ የሚተክልበት፤ የተለመደውን የአምባገነኖች የመተካካት ሄደትን ነው።

እስካሁን ያስተናገድናቸው የአምባገነን ንቅለ ተከላዎች ሀገሩን ክፉኛ አቁስለዋል። የሀገር መሰረት አናግተዋል። ሕዝብ አንገላተዋል። የዛሬውም፤ የዶ/ር አቢይ ሕወሃትን የመንቀል ዘመቻ፤ በተመሳሳይ ሁኔታ እየተካሄደ ያለው በሀገር እና ሕዝብ ኪሳራ ነው። መደበኛ ጦርነት በራሱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚያስከትለው ምስቅልቅል እና ድንጋጤ ከባድ ነው። ደርግን ለመጣል በተደረገው ጦርነት፤ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከመግባቱ ወራት በፊት ቀድመው የተያዙ የሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች ያሳለፉት ጊዜ ቀላል አልነበረም። ሆኖም ያኔ መደበኛው ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ፤ የቀጠለ ውጊያ ባለመኖሩ፤ አለመረጋጋቱን በጊዜ ማስከን ተችሎ ነበር። አሁን ትግራይ ላይ ያለው ሁኔታ ግን እንደዛ አልሆነም። ሕወሃትን ከትግራይ ጠርጎ ማውጣት፤ ደርግን ከመላው ኢትዮጵያ ጠርጎ እንደማውጣት ቀላል አልሆነም። ግጭቱ መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል። ዶ/ር አቢይም የትግራይን ሕዝብ የትኛውንም ዋጋ አስከፍሎ የቀድሞ አልቆቻቸውን ሙሉ ለሙሉ የማንበርከክ እቅዳቸውን ገፍተውበታል። ብቻ በጥቅሉ፤ ይህ ጦርነት፤ የአንድ ግለሰብን የስልጣን ጥማት ከማርካት ባለፈ ምንም እርባና ለሌለው ነገር፤ ንጹሃን ዜጎች ለስቃይ የተዳረጉበት፤ አብሮ የኖረ ሕዝብ አላግባብ ጎራ ለይቶ እንዲቃቃር የተደረገበት፤ ኢትዮጵያን በማዳን ሽፋን፤ ኢትዮጵያዊነት እምብርቱ ላይ የተመታበት አሳዛኝ ክስተት ነው።

………………………………………….//………………………………………………

ለውጥ ያስፈለገው እየተጓዝንበት የነበረው መንገድ ወደ አደገኛ አቅጣጨ እየመራን ስለነበር ነው። ለለውጥ የተደረገው ትግል የሥርዓት ለውጥን እንጅ የግለሰቦችን መገላበጥ ታሳቢ ያደረገ አይመስለኝም። ለዶ/ር አቢይ የተሰጠው ድጋፍ እና ፍቅርም ለተረጋጋ መንግስታዊ ሥርዓት መንገድ ይጠርጋሉ ከሚል ተስፋ የመነጨ እንደነበር ነው የሚገባኝ። ወደ ስልጣን ካመጣቸው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር፤ ዶ/ር አቢይ የሚመሩት መንግስት የሽግግር መንግስት ባህሪ ሊኖረው ይገባ ነበር። ሌላ ጉዳይ ውስጥ ከመግባታችን በፊት፤ እንደ ሀገር፤ ፋታ ወስደን፤ የትናንቱን ስህተት መርምረን፤ አዲስ መንገድ የምንቀይስበት ጊዜ ያስፈልገን ነበር። ይህ ግን አልሆነም። በተቃራኒው፤ ዶ/ር አቢይ ያለፉትን ሦስት ዓመታት፤ በአጋጣሚ እጃቸው ውስጥ የገባውን ስልጣን በዘላቂነት ይዘው የሚቀጥሉበትን መንገድ ሲቀይሱ ነው ያሳለፉት። የሦስት አመቱ የለውጥ ጉዞ፤ በሕወሃት እግር ሥር ዶ/ር አቢይን በመተካት ነው የተጠናቀቀው።

ዲሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ፤ ምን እንደሚመስል፤ እንዴት እንደሚሰራ በቅጡ ለሚያውቅ ማንም ሰው፤ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ያደረጉ ሀገራት ያለፉበት ሂደት ምን ይመስል እንደነበር ለሚያውቅ ሰው፤ ኢትዮጵያ፤ ያለፉትን ሦስት ዓመታት፤ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እያደረገች ሳይሆን አምባገነን እያዋለደች እንዳሳለፈች ለመረዳት የሚቸገር አይመስለኝም። የዶ/ር አቢይ ስልጣን ላይ መቀጠል የተሻለው አማራጭ ነው ብለው የሚያምኑ ወገኖች መካከልም እንኳን፤ የዲሞክራሲያዊ ጎዳና ላይ ነን ብሎ አፉን ሞልቶ የሚናገረው ሰው እምብዛም አይደለም። የድጋፍ መሠረቱ በዋናነት፤ ሀገር ወዳድ ናቸው፤ ለኢትዮጵያ ከፍተው አይከፉም ከሚል መተማመን የሚመነጭ ነው የሚመስለው። ይህም ቢሆን ግን ትክክለኛ እይታ ላይ የተመሰረተ አይደለም።

ከንግግሮቻቸው፤ ከአንዳንድ ድርጊቶቻቸው እና እቅዶቻቸው፤ በአጠቃላይ ከሚያሳዮት ባህሪ አንጻር፤ ብዙ ሰው፤ የዶ/ር አቢይን ሀገር ወዳድነት፤ የበለጸገች፤ የታፈረች ኢትዮጵያን ለመገንባት አለኝ የሚሉትን ራዕይ ማስመሰል ነው ብሎ ለመቀበል ይቸገራል። ጉዳዪ ግን የማስመሰል እና ያለማስመሰል አይደለም። ችግራቸው ሀገር የመውደድ እና የመጥላትም አይመስለኝም።  ሀገራቸውንም ይወዱ ይሆናል። እንደ ማንኛውም መሪ፤ የሚመሩት ሀገር ላይ ሊያሳኩት የሚመኙት ራዕይም ይኖራቸዋል። አጠያያቂው ጉዳይ፤ የራዕያቸው፤ የሀገር ወዳድነታቸው አድማስ የት ድረስ ነው የሚለው ነው?

ሂትለር የተነሳውም፤ ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ ማግኘት የቻለውም፤ ጀርመንን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከደረሰባት ውድቀት ለማንሳት፤ አሽቆልቁሎ የነበረውን የጀርመን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት እና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረት ባሳየው ቁርጠኝነት ነበር። ሆኖም፤ የሀገር ተቆርቋሪነቱ፤ ለጀርመን ያነገበው ህልም፤ በራሱ በሂትለር ኃያል መሪ የመሆን ጽኑ ፍላጎት ላይ የተንጠለጠለ ስለነበር፤ የኋላ ኋላ አውሮፓን የመቆጣጠር ህልሙ ቅዠት ሁኖ፤ የአላይድ ሀገራቱ ጦር ጀርመንን ሊይዝ እንደተቃረበ እና እንዳበቃለት ሲያውቅ፤ ጀርመንን ዶግ አመድ የሚያደርግ ውሳኔ ከማስተላለፍ አላቀበውም። የሀገሩን ኢንደስትሪ፤ መሠረተ ልማት፤ የትራንስፖርት መገናኛ በሙሉ አውድሞ ሀገሩን ምድረ በዳ እንዲያስቀር ትእዛዝ የተላለፈለት ሚኒስትር፤ በመጨረሻውም ሰአት ቢሆን፤ ያለቃው የጤና መቃወስ ጥግ ስለተገለጸለት እና ትዛዙን ሳያስፈጽም እጁን ለመስጠት በመወሰኑ ጀርመን ከውድመት ተርፋለች። የሂትለር እና የጀርመን ‘ፍቅር’ መጨረሻ ግን እንዲህ ነው የሆነው። አንዳንዶች ለወደዱት ነገር ራሳቸውን ይሰዋሉ። ሌሎች ደግሞ ከምንም ነገር ጋር ያላቸው ‘ፍቅር’ እነሱ እስከያዙት፤ እንሱ እስከደመቁበት ድርስ ብቻ ነው።

ዶ/ር አቢይ ንጉሥ የመሆን የልጅነት ህልም እንዳላቸው አልደበቁንም። ባይናገሩትም ባህሪያቸው ያሳብቅባቸዋል። ንጉሥ ለመሆን ደግሞ የሚነግሡበት ሀገር ያስፈልጋቸዋል። ኢትዮጲያዊ ሆነው እስከተወለዱ ድረስ፤ የኬንያ ንጉሥ ሊሆኑ አይችሉም። ንግሥስናቸውን ሊያስቡት የሚችሉት በኢትዮጵያ ፖለቲካ አውድ ውስጥ ነው። ሀገር መምራት መመኘት በራሱ ክፈት የለውም። ችግሩ፤ እሳቸው መላበስ ሲመኙ የኖሩት የመሪ ገጽ ባህሪ እና አሁን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አመራር አለመጣጣማቸው ነው።

ዶ/ር አቢይ፤ ሕዝብ አቀራርቦ፤ ለዘላቂ መንግስታዊ ሥርዓት መሠረት ጥሎ ለማለፍ ከማንም በላይ እድል አግኝተው ነበር። ህልማቸው ናዛዝ አዛዥ ሁኖ መኖር ስለነበር አልተጠቀሙበትም። ወደ ዲሞክራሲ የሚያሻግረውን መንገድ ያልመረጠ መሪ ደግሞ ያለው አማራጭ አምባገነን ሁኖ መግዛት ነው። እንደ እኛ አይነቱን የተከፋፈለ ሕዝብ ደግሞ ወጥ በሆነ መልኩ ሰጥ ለጥ አድርጎ መግዛት አዳጋች ነው። ወደዱም ጠሉም ያላቸው አማራጭ ከፋፍሎ መግዛት ነው። የሕወሃት የብሔር ብሔረሰቦች ሙዚቃ እንደወረደ ማስቀጠል አይችሉም። አንዴ ተበልቶበታል። የነበራቸው አማራጭ፤ ሁለቱንም አዳቅሎ፤ ላይ ላዮን ስለ አንድነት እያወሩ ውስጥ ውስጡን ተቃርኖውን ማስቀጠል ነው። የመረጡትም እሱኑ ነው።

የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣናት ያደርጉት እንደነበረው፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነትን በግላጭ ስለማያብጠለጥሉ ጀሮ ውስጥ ሳይገባ እየታለፈ እንጅ፤ ዶ/ር አቢይ ራሳቸው ከፋፋይ እና መርዛማ ነገር የሚናገሩበት እና የሚያደርጉበት ጊዜ ቀላል አይደለም። ሆኖም፤ በተቻለ መጠን የሀገራዊነት ገጽታቸውን ጠብቀው፤ የመከፋፈሉን ስራ በዋናነት የሚያስፈጽሙት በተልዕኮ ነው። ዋናው ተላላኪ ከፋፋይ ደግሞ ፓርቲያቸው ብልጽግና ነው።

የብልጽግና ብልሽት ካናቱ ነው። ብልጽግና ውስጥ ያለው ትርምስ ከዶ/ር አቢይ ፍላጎት ውጭ የሚካሄድ አይደለም። የትኛውም ብልጽግና ከዶ/ር አቢይ የተነጠለ ህልውና የለውም። ያ ባይሆን፤ ፓርቲው ውስጥ የዶ/ር አቢይን ሀሳብ የመገዳደር ነጻነት ቢኖር፤ ያለምንም ተጨባጭ ነገር፤ ያለምንም ድርድር እና መግባባት አፈራርሰው ሲሰሯቸው አሜን ብለው ባልተቀበሉ ነበር። ተረድተውትም ይሁን ሳይረዱት፤ ተባባሪም ሆነው ይሁን ተጨናብረው፤ ሁሉም የብልጽግና ቅርጫፎች፤ በተፈቀደላቸው ሜዳ፤ ዶ/ር አቢይ ያስቀመጡላቸውን መስመር ተከትለው ነው የሚጠዛጠዙት። የማይፈቀድላቸው እና ሲያደርጉት የማናያቸው ወደ ላይ መራገጡን ነው። ውጭ ያለው የፖለቲካ ተዋናይም ቢሆን፤ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የሚፋለጥበትን እለታዊ አጀንዳ ከዶ/ር አቢይ ነው የሚቀበለው። ቅጥረኛ አበጣባጮች እንደሌላቸውም እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እንዲህ ሁሉንም አንገት ለአንገት ካስተናነቁ በኋላ እሳቸው ከደሙ ንጽህ እንደሆነ ሰው መካሪ ገላጋይ ገፋም ሲል ከሳሽ ሆነው ብቅ ይላሉ።

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለመቀጠል ያላት ብቸኛ ተስፋ የሕዝብ አንድነት ነው። ዘላቂ መንግስታዊ ሥርዓት ለመትከልም መሠረቱ የሕዝብ ስምምነት እና መተማመን ነው። ያለ አንድነት ያለ ስምምነት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግረውን መንገድ ማግኘት አይታሰብም። ዶ/ር አቢይ፤ የሕዝብ ጥምረት ስልጣን ላይ ያወጣቸው ሰው ናቸው። ሕዝብ ሲናበብ እና ሲተባበር ምን እንደሚሰራ ከማንም በላይ ይረዳሉ። እንደምኞታቸው በንግሥናው ለመዝለቅ፤ ወንበራቸውን ከማንኛውም ስጋት ለመጠበቅ ያላቸው ሁነኛ መንገድ ሕዝብ መከፋፈል እንደሆነም ያምናሉ። ተግተው እያደረጉ ያሉት እሱን ስለሆነ። እሳቸው የስልጣን አምሮታቸውን ከተወጡ በኋላ፤ የእሳቸው የንግሥና ዘመን ሲያበቃ፤ ሕዝብ ተከፋፍሎ ሀገር እንዴት ይቀጥላል የሚለው ግን ጭንቀታቸው አይደለም። ከስልጣናቸው በላይ የሚያስቡላት ሀገር የላቸውም።

ቀድሞ ነገር ችግር ውስጥ የወደቅነው፤ ሕወሃት/ኢሕአዴግ፤ የሀገር አንድነት መሠረቶችን እየናደ፤ አስተሳስረው ያያያዙንን ገመዶች እየበጣጠሰ፤ የሀገር ህልውናን ከአገዛዙ ህልውና ጋር እንዲጣበቅ በማድረጉ ነው። የለውጡም ቁምነገር፤ ከዚህ ቅርቃር ወጥተን፤ የሀገር ህልውና ሕዝባዊ እና ተቋማዊ መሰረት ላይ እንዲያርፍ ነበር። ያ መሆኑ ቀርቶ፤ የተነሳንበት ቦታ ዙረን ተመልሰናል። አሁንም ለሀገር ህልውና እና ለሕዝብ ደህነነት ዘላቂ ዋስትና አልተገኘም። ከሦስት ዓመት በፊት ከነመፈጠራቸው እንኳን የማናውቃቸውን ሰው፤ ዛሬ እሳቸው ከሌሉ ሀገሩ ምን ይሆናል ብለን እንድንጨነቅ ተገደናል። ሀገር መውደድ ማለት፤ የሀገርን፤ የሕዝብን ጥቅም ከጊዜያዊ የራስ ፍላጎት ማስቀደም እንደሆነ ነው የሚገባኝ። ትውልድ አልፎ ትውልድ ይተካል። ዘላቂ የሆነውን የሀገር እና የሕዝብ ህልውናን፤ አላፊ ከሆነው የግለሰቦች ስልጣን ጋር ማቆራኘት፤ ትናንት ሕወሃት ሲያደርገው ሀገር መውደድ አልተባለም፤ ዛሬ ዶ/ር አቢይ ሲያደርጉት ሀገር መውደድ የሚሆንበትም ምንም ምክንያት የለም።

በሕወሃት ግዜ እርስ በእርሱ የሚፈራራ፤ የሚጠራጠር ማሕበረሰብ ለመፍጠር ብዙ ስራ ተሰርቷል። ሆኖም ያኔ ምንም ሕዝብ እንዲስማማ ባይፈለግም፤ ቢያንስ እንደ አሁኑ ውጥረቱ ወደ ለየለት ግጭት እያደገ እርስ በእርሱ እንዲጠፋፋ አልተደረገም። መግደል ካስፈለጋቸውም እነሱው ነበር የሚገድሉት። አሁን ጭራሽ ተዛምዶ እና ተጋምዶ የኖረ ሕዝብ እንዲጋደል እና ደም እንዲቃባ የሚደረግበት ጊዜ ላይ ነን። ሕወሃቶች በጣጥሰው የቀጣጠሉት ሀገር፤ ከነሱ የስልጣን ዘመን በኋላ እንዴት ሁኖ እንደሚቀጥል ግድ ባይላቸውም፤ ቢያንስ እስካሉ ድረስ ሀገሪቱን እንዳትሞት እንዳትድን አድርገው ወጥረው መያዝ ችለው ነበር። ዶ/ር አቢይ ምንም እንኳን ሀሳባቸው እንደ ሕወሃት የጫሩትን ጸብ እየገላገሉ፤ የለኮሱትን እሳት እያጠፉ፤ ከፋፍሎ መግዛት ቢሆንም፤ ለራሳቸው ስልጣን አደጋ እንዳይሆን ሲሉ እንኳን ሚዛን ጠብቆ ለማስኬድ እውቀቱ እና ስክነቱ አላቸው ለማለት አያስደፍርም። በእስከዛሬው አያያዛቸው፤ ነገሩ ሁሉ ከቁጥጥራቸው ውጭ ወጥቶ፤ ሀገር ይዘው የሚጠፉበት ግዜ ሩቅ አይሆንም። ይኸ ሁኔታውን ይባስ አስፈሪ ያደርገዋል።

………………………………………….//………………………………………………

ፖለቲካችን የብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ ሁሉንም አይነት መስተጋብር፤ ሁሉንም አይነት ክስተት፤ በማንነት መነጽር እንድናይ እያደረገን፤ ሀገርን ከመውደድ እና ከመጥላት፤ ይህኛውን ወይም ያኛውን ማህበረሰብ ከመጥቀም እና ከመጉዳት ውጭ ላለ ሌላ ጉዳይ ግርዶሽ እየጣለብን እንጅ፤ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ የተጓዘበትን አቅጣጫ ከመወሰን አንጻር፤ የግለሰቦች ስግብግብ የስልጣን ፍላጎትን ያህል ወሳኝ ሚና የተጫወተ ነገር ያለ አይመስለኝም። የደርግ አብዮት ላስከተለው ምስቅልቅል እና እልቂት የዳረገን፤ የአጼ ኃይለስላሴ የቀደሙት አጼዎች ባላደረጉት መልኩ፤ መላ ሀገሩን በመዳፌ ካላስገባሁ ማለት እና በኋላም ጊዜው ላመጣው ለውጥ በጊዜ በቂ ክፍተት መስጠት አለመቻል ነው። በተመሳሳይ፤ ሕወሃትን ለስልጣን ያበቃው፤ ለሕወሃት ዘመኑ አምባገነንነት እና ክፍፍል መንገድ የጠረገው፤ የመንግስቱ ኃይለማርያም ለማንኛውም አይነት ፖለቲካዊ መፍትሄ በር መዝጋት፤ የራሳቸው ሰዎች እንኳን መፈናፈኛ ማሳጣት ነው።

የሕወሃት/ኢሕአዴግን አገዛዝ የፈሰሰበትን መንገድ በዋናነት የቀየሰውም የመለስ ዜናዊ የስልጣን ጥማት ነው። መለስ ዜናዊ በፊት አውራሪነት ኢሕአዴግንም ሆነ መንግስት ሲያዋቅሩ፤ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ከእሳቸው እንዳይወጣ ከማረጋገጥ በላይ ያስጨነቃቸው ነገር የነበረ አይመስለኝም። የሕወሃት ፀሐይ መጥለቅ የጀመረችው መለስ ዜናዊ ያለፉ ዕለት ነው። የመለስ የስልጣን ስስት፤ አይደለም ሀገርን፤ ድርጅታቸው ሕወሃትን እንኳን ከእሳቸው እድሜ የዘለለ እድሜ እንዲኖረው የሚያስችለውን ቁመና እንዲላበስ መፍቀድ አላስቻላቸውም። አዲሱ የስልጣን ህልመኛ ዶ/ር አቢይ ደግሞ፤ መለስ ዜናዊ አመሰቃቅለው እና ተብትበው የሄዱትን ሀገር ተረክበው ለትውልድ እንዳይተርፍ አድርገው እያነፈሩት ነው። በአጭሩ ባለፉት መቶ አመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ እጣፈንታ የተወሰነው በሦስት ግለስቦች የስልጣን ጥማት ነው። አሁንም በዋናነት፤ ወደ መፍትሄ የሚወስደውን መንገድ ጥርቅም አድርገው ዘግተው፤ ወደ ጥፋታችን እያጋዙን ያሉት አንድ ግለሰብ ናቸው።

የሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ወሳኝ ሰዓት ላይ በመቀላቀል ፍጻሜው ሰላማዊ እንዲሆን ከተጫወቱት ሚና አንጻር፤ አረረም መረረም የቅርብ ግዜ ሀገር የማስተዳደር ልምድ ስላላቸው፤ ውጭ ካለው ተቃዋሚ በተሻለ እርስ በእርስ ስለሚተዋወቁ፤ ከሁሉም በላይ የኢሕአዴግ መዋቅር ከሀገረ መንግስቱ ጋር ያለቅጥ በመጣበቁ የኢሕአዴግ በአንዴ ከቦታው መልቀቅ የሀገር ህልውና ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ስጋት አንጻር፤ አዲስ የሽግግር መንግስት ከማቋቋም ይልቅ የለውጥ ኃይል ሁኖ የወጣው የኢሕአዴግ ክንፍ በመንግስትነት ቀጥሎ የሽግግሩን ሂደት መምራቱ፤ ለሀገር መረጋጋት የተሻለ አማራጭ ነው የሚለው ሀሳብ በወቅቱ ምክኒያታዊ ነበረ ባይ ነኝ። የለውጥ ኃይሉ፤ ጠንካራ ጎኖቹን አጎልብቶ፤ ሽግግሩን በኃቀኝነት መምራት ቢችል፤ ከሽግግሩ ጊዜ መጠናቀቅ በኋላ በሚኖረው ምርጫም ለሕዝብ የተሻለው አማራጭ ሁኖ በምርጫ ስልጣኑን የሚያድስበት እድልም ሰፊ ይሆን እንደነበር አስባለሁ። ሆኖም ዶ/ር አቢይ፤ ያልተመጠነ እና በጊዜ ያልተገደበ ስልጣን ለመያዝ ባላቸው ፍላጎት የተነሳ፤ ፓርቲያቸውንም ሳይቀር አኮላሽተው፤ እሳቸውም ፓርቲያቸውም ድልድይ ሁኖ ሀገር ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመሻገር ያገኙትን ታሪካዊ እድል በማምከናቸው ሁሉም ነገር እንዳይሆን ሆኗል።

ምንም ቁልፉ እና ወሳኙ ምክንያት እሱ ቢሆንም፤ ለለውጡ መክሸፍ እና ለገባንበት አጣብቂኝ፤ የዶ/ር አቢይን የስልጣን ስግብግብነት ብቻ ተወቃሽ አድርጎ ማለፉ ግን የተሟላ ግምገማ አይሆንም። ዲሞክራሲ የተሳትፎ ፖለቲካ እስከሆነ ድረስ ወደ ዲሞክራሲ ስርአት የሚደረገውም ሽግግር የጋራ ስራ እንዲሆን ግድ ይላል። ዶ/ር አቢይ በዚያም በዚህም እያምታቱ፤ በየጊዜው ፋታ የሚነሳ አጀንዳ እየለቀቁ፤ የሽግግር ይሆናል ተብሎ የታሰበው ጊዜ በግርግር እና በወከባ ሲጨርሱት፤ እንደወዘወዙት እየተወዘወዘ፤ ወደ መስመር እንዲገቡ በቂ ጫና መፍጠር ያልቻለው ሌላው ፖለቲከኛ እና ልሂቅም ለለውጡ መክሸፍ የራሱን ሚና ተጫውቷል።

ባለፉት ሦስት ዓመታት፤ ከለውጡ በፊት ድልድይ ሆነው ሁሉንም ወገን ለማቀራረብ፤ መፍትሄ ለማፈላለግ ይጥሩ የነበሩ ወገኖች ሳይቀሩ፤ በአንድም በሌላ መልኩ መኃል ሜዳውን ሙሉ ለሙሉ ለዶ/ር አቢይ ለቀው ጥግ የያዙበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የዶ/ር አቢይ መንግስት በአግባቡ እና በስርአት እንዲራመድ መግራት ይጠበቅባቸው ከነበሩት አካላት ገሚሶቹ፤ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን፤ መዋቅራዊ አሰራር መዘርጋቱን አረጋግጠው፤ ራሳቸውን ችለው የራሳቸውን ሀሳብ ከመወከል ይልቅ፤ እምነታቸውን በሙሉ በዶ/ር አቢይ ላይ ጥለው፤ ከእሳቸው ጀርባ መሰለፍን መርጠዋል። ዶ/ር አቢይ ጉያ ውስጥ ከመወሸቅ የተረፈው ሌላው ፖለቲካኛ እና ልሂቅም፤ እሳቸው በቀደዱለት ቦይ እየፈሰሰ እርስ በእርሱ ከመተራመስ አላመለጠም። ዶ/ር አቢይ እንደጠመዘዟቸው ሳይጠመዘዙ፤ አቅጣጫ ሳይስቱ፤ በደረጀ መልኩ አማራጭ ሀሳባቸውን እያቀረቡ፤ ወደ እውነተኛ የሽግግር ሂደት እንዲገባ ግፊት ለመፍጥር ሲሞክሩ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው።

………………………………………….//………………………………………………

አሁንም፤ የሚያስተማምን፤ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለበት እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከመገንባት ውጭ አማራጭ ያለን አይመስለኝም። አብሮ ሊያኗኑረን የሚችለው እሱ ብቻ ነው። የእስካሁኑ የለውጥ ጉዞ እንደታሰበው ወደዚያ አቅጣጫ አልወሰደንም። ይባስ ብሎ አይቀሬ ወደ ሆነ ጥፋት እየመራን ነው። ብዙ ሰው ይህን እየተረዳው የመጣ ይመስለኛል። ነገር ግን ምንም በዶ/ር አቢይ ላይ የነበረው ተስፋ ከዕለት ተዕለት እየተመናመነ ቢሆንም፤ ደፍሮ ሌላ አማራጮችን ለማየት ፈራ ተባ ማለቱ እንዳለ ነው። ወደ አዲስ የሽግግር ሂደት እንዲገባ ጨከኖ የሚገፋ ብዙ አካል የለም።

በርግጥ፤ እንዲህ ሁሉም ተበታትኖ እና ተቋስሎ ባለበት ሁኔታ የተሳካ የሽግግር ሂደት ውስጥ መግባት ይቻላል ወይ? የሚለው ስጋት መሰረተ ቢስ አይደለም። በጅምላ እየተፈራረጅ እና ጣት እየተቀሳሰሩ ወደ ስምምነት መሄድ የሚታሰብ አይደለም። ሁሉም በራሱ ለቅሶ በደነቆረበት ሁኔታ ተናቦ ወደ አንድ መዳረሻ መጓዝ አዳጋች ነው። ነገር ግን፤ ተግዳሮቶቹን ተጋፍጦ መውጫ መንገድ ከመፈለግ የተሻለ ምን ምርጫ አለ? እንጦሮጦስ እንዲነዱት ሀገሩን ለዶ/ር አቢይ መተው ያዋጣል ወይ?

አማራጭ መንገድ ቀይሶ መንግስት ላይ ጫና መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ፤ በዶ/ር አቢይ መንግስት ላይ ብሶት ማሰማቱ ምን እርባና ይኖረዋል? ሲጀመር፤ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚያስፈለገው፤ አንድ ኃይል ብቻውን ሀገር ተቆጣጥሮ ያሻውን የሚያደርግበትን ሁኔታ እንዳይኖር ነው። ቁጥጥር እና ግልጽ አሰራር ወዳለበት መንግስታዊ ስርአት ሊመራን የሚችል የሽግግር ሂደት ውስጥ እንድንገባ ግፊት ማድረግ ካልተቻለ፤ ዶ/ር አቢይ ይህን ወይም ያን ይበድላሉ፤ የዚህኛውን ወይም የዚያኛውን አጀንዳ ይጭናሉ እየተባባሉ መካሰሱ፤ የአገዛዙን እድሜ ከማራዘም፤ አልፎም ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲፈራራ እና እንዲጋጭ ከማደረግ በስተቀር ሌላ ምን ፋይዳ አለው? የችግሩን አናት፤ ዋናውን ሰውየ አስቀምጦ፤ ከክልል፤ ከዞን ከወረዳ የበታች አመራሮች ጋር መካሰሱስ መፍትሄ ይሆናል ወይ?

አምባገነን መንግስታትም ቢሆኑ፤ ነጻነት ሲነፍጉ በምትኩ ቢያንስ የሰላማዊ ዜጎችን ሰላም እና መረጋጋት ማስከበር እንደሚጠበቅባቸው ይረዳሉ። ዶ/ር አቢይ ግን፤ ይህንንም እንኳን ማድረግ ይጠበቅብኛል ብለው የሚያስቡ መሪ አይደሉም። ራሳቸውን ከግጭቱ፤ ከእልቂቱ፤ ከስደቱ፤ ከረሃቡ፤ ከአጠቃላይ ቀውሱ ነጥለው፤ ገጽታቸውን በሌሎች ብልጭልጭ ፕሮጀክቶቻቸው ጥላ ውስጥ እስከደበቁ ድረስ፤ ሞቱ፤ ግፉ፤ እንግልቱ አይመለከተኝም ብለው ያስባሉ። ገፍቶ ሲመጣባቸው የሚያደርጉትንም እያየነው ነው፤ ወይ አድበስብሰው፤ ወይ በሌሎች አካላት አላከው፤ ካልሆነም ማባበያ መሰል ነገር አድርገው፤ ገፋም ሲል አትንጫጩ ብለው አስፈራርተው ያልፉታል። ሕዝብ አደናብረው እና ከፋፍለው ሁሉንም መውጫ ቀዳዳ እስካሳጡ ድረስ፤ የሕዝብን መሰረታዊ የኑሮ ዋስተና የማስጠበቅ ግዴታ እንኳን አይኖርብኝም ብለው ራሳቸውን አሳምነዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ደረጃ ንቀት ላይ የወደቀበት ጊዜ መኖሩን እርግጠኛ አይደለሁም። የሰው ልጅ ሕይወት፤ የሕዝብ ሰቆቃ እንዲህ መቀለጃ እየሆነ፤ ምን ያህል ጊዜ ነው መቀጠል የሚቻለው?

ዶ/ር አቢይ ከአንድ ግርግር ወደ ሌላ ግርግር፤ ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እያገላበጡ፤ ፋታ እየነሱ እዚህ አድርሰውናል። መቋጫ ያጣ ጦርነት ውስጥም ነን። በዚህ ሁሉ ቀውስ እና ግጭት ላይ ደግሞ፤ ምርጫ ካልጨመርኩ ብለው ሌላ ቀውስ እየጋበዙ ነው። ምርጫ ርግጫ አለው። አለመግባባት ግጭት ይጋብዛል። ምዕራባውያኑ ቢራገጡ አያት ቅድመ አያቶቻቸው አስተካክለው በሰሩላቸው መደብ ላይ ነው። ባልተደለደለ መሬት፤ ባልተስማሙበት የጨዋታ ህግ፤ በዚህም በዚያም እሳት እየነደደ ባለበት ወቅት፤ ምርጫ ካላደረኩ ሙቼ እገኛለሁ ከማለት በላይ ኃላፊነት የጎደለው ነገር ያለ አይመስለኝም። አሁን ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከስልጣን እንዲለቁ ከተገደዱበት ቀውስ፤ በብዙ እጥፍ ቢብስ እንጅ አያንስም። ዶ/ር አቢይ እንጥፍጣፊ ፈሪሃ እግዚአብሔር ቢኖራቸው፤ “ይሄ ነገር አልሆነልኝም፤ በጋራ መፍትሄ ይፈለግለት ወይም የሚችል ሰው ይረከበኝ” የሚሉበት እንጅ፤ ስልጣናቸውን ለማጸደቅ የሚሯሯጡበት ግዜ አልነበረም። በዚህ ሁኔታ፤ ሀገሪቱ ይህ ሁሉ ቀውስ እየተፈራረቀባት፤ ሳትፈረካከስ ምን ያህል ርቀት መጓዝ ትችላለች?

እርግጥ ነው አዲስ ነገር ይዞት የሚመጣው ነገር ያስፈራል። ሆኖም በጥንቃቄ መራመድ እንጅ መጭውን ፈርቶ በጥፋት ጎዳና መቀጠል አዋጭ አይደለም። የሚሻለው ችግሩን ተጋፍጦ፤ መውጫ መንገድ ማፈላለግ ነው። በሀገር ሰላም፤ ሁሉም ዝግጁ ሁሉም ስንዱ በሆነበት ሁኔታ፤ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ የተኬደበት ሀገር መኖሩን አላውቅም። ከጽንሰቱ እስከ ዛሬ ዲሞክራሲ በጭንቅ ውስጥ፤ በአንድ በኩል ከጥቂቶች አምባገነንነት፤ በሌላ በኩል ከስርአት አልበኝነት እና ከመበታተን በሚደረግ ሽሽት መካከል ነው የሚወለደው። ምንም ችግራችን ቢወሳሰብ፤ የሰው ልጅ ያላለፈበት ነገር ገጥሞናል ብየ አላስብም። ሰው ሰው ነው። ማንም የክፋት ሞኖፖሊ፤ ማንም የቅንነት ሞኖፖሊ የለውም። በዚህ ተግባብተን፤ መወነጃጀሉን ቀንሰን፤ ትኩረታችን የመፍትሄ ሀሳብ ማፈላለግ ላይ ብናደርግ፤ ሂደቱ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን እርግጥ ቢሆንም፤ የእንቆቅልሻችን ፍቺው ጠፍቶ አይጠፋም።

መሠረቱ እየነደደ ባለ ቤት፤ ይህን ወይም ያንን ክፍል ማዳን አይቻልም። ብቸኛው የድኅነት መንገድ ለጋራ ህልውናችን በጋራ መቆም ነው። በዚህም በዚያም ያሉ ብሶቶችን፤ ቀውሶችን በአንድ አጀንዳ ጥላ ሥር የሚተሳሰሩበትን መላ ከመፈለግ በስተቀር ሌላ መውጫ ቀዳዳ ያለን አይመስለኝም። ተወደደም ተጠላም ታሪክ እና ተፈጥሮ አስተሳስሮ ያስቀመጠው ሕዝብ አለ። ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነ ሕዝብ መጻኢ እድል አደጋ ውስጥ ወድቋል። ሌላው ሌላው ሁሉ ነገር ቢቀር፤ ሰብዓዊነት፤ ሕዝብን ከሚመጣው መከራ የመታደግ ኃላፊነት የጋራ ጉዳይ ሁኖ ሁሉንም ወገን ሊያስተሳስር ይገባል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘረኛ አይደለም። ተላምዶ ተዛመዶ የኖረ ሕዝብ ነው። ምንም ክፍፍሉ የብሔር ማንነት መስመርን የተከተለ ቢሆንም፤ ቅራኔው ከመሬት የተነሳ፤ መናናቅ እና ጥላቻ የወለደው አይደለም። መቃቃሩን ያመጣው፤ ለፖለቲካ ፍጆታ የሕዝቡ እይታ እንዲዘበራረቅ፤ እንዳይደማመጥ እና እንዳይተማመን ስለተሰራ ነው። መከፋቱ ላይ፤ በዚህ መጣብህ፤ በዚያ ወጋህ የተባለ፤ ነገረ ሰሪ የጣለበት ሰው ከእናቱ ልጅም ጋር ይጋጫል። በተረፈ፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አስማምቶ የሚያኖረው ቢያገኝ አይጠላም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተሸበበበት ፍርሃቱ አላቆ የሚያሰባስበው ሲያገኝ፤ የመተባበር የመሰባሰብ ችግር እንደሌለበት፤ በለውጡ መጀመሪያ ላይ፤ ለለውጥ ኃይሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሰጠው ድጋፍ እና ፍቅር አስመስክሯል። ሕዝብ እንዲተያይ እና እንዲናበብ የማድረጉ እዳ የፖለቲካ ተዋናዮ፤ የኢሊቱ ነው።

ጭቆና ግዜ ይሰጣል፤ አሁን የተጋረጠብን አደጋ የመኖር እና ያለመኖር ነው። እንደ እስካሁኑ አያያዛቸው፤ ዶ/ር አቢይ ሀገሪቱን ተመልሳ እንኳን እንዳትጠገን አድርገው ማፈራረሳቸው አይቀሬ ነው። ሳይመሽ፤ የሕዝብን ደህንነት፤ የሀገር አንድነት መታደግ ያሻል። ያለበለዚያ፤ የዶ/ር አቢይ ድራማ ሳይጨርሰን የሚያልቅ አይደለም።

ከናፍቆት ገላው

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.