በኢትዮጵያ የምርጫው አስፈላጊነት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ ነው

Peace and Reconilation በኢትዮጵያ የምርጫው አስፈላጊነት የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ ነው

የምርጫው አስፈላጊነት አንደኛው ምክያት

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት የመሆን መብቱ ተነፍጎት እስከአሁን ድረስ እድሜውን ሲገፋ ኖሯል። በ”97”ቱ ምርጫ ሥልጣኑን ጭብጦ በእጁ ካስገባ በኋላ፣ ህወሃት፣ በመለስ ዜናዊ መሪነትና ትእዛዝ ከእጁ ተፈልቅቆ ተወሰደበት፡ በ”97”ቱ  ምርጫ  የሕዝብ ተሳትፎው በስፋትና በጥልቀት ተከናውኖ ስለነበረ የብሄረሰብ የፖለቲካ መሪዎችን  ሳይሆን የህብረብሔር የፖለቲካ መሪዎችን በመምረጥ የብሄረሰብ የፖሊቲካ መረዎችን አንገዋሎ ተፋቸው ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንክሮ የሚያዳምጥና የሚከታተል ባለመኖሩ ነው እንጂ እስከዛሬው  ቀን ድረስ የሚያገለግል ትምህርት ሰጥቶ ነበር ያለፈው። በአሁኑ በሰኔ 14/2013 ምርጫም ይህን የ”97”ቱን የምርጫ ሂደት እንደሚደገም ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን ሲያደርግ ብቻ ነው በሰላማዊ መንገድ የሥልጣኑ ባለቤት መሆኑ የሚረጋገጠው። ምርጫው ቀኑን ጠምቆ የመፈጻሙ አስፈላጊነቱም፣ ይህንን እውነተኛ ዴሞክረሲያዊ ሂደት ማለትም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሥልጣኑ ባለቤት ለማድረግ ሂደቱን ማመቻቸት ግዴታ የሚሆነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት፣ በኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ ቋሚ አስተዳደር አለመኖሩ ነው።

የምርጫ አስፈላጊነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣አሁን በተቃና መልክ ለማለት ይቻላል፣በማስተዳድር ላይ ያለው ሃይል፣ ከአናቱ ጀምሮ እስከመሰረቱ ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ አይደለም። ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዳለ አስተዳደሩ ጭምር የሚናገረውና የሚመሰክረው ነው።ስለዚህ ሕዝቡና አስተዳዳሪዎቹ ሳያውቁት የሚጓዝ ክስተት እንዳልሆነ ግልጽ ነው።የምርጫው መካሄድ አስፈላገነት ጠንካረ ጎኑም ይህን ጎልቶ የሚታየውን ድክመት ለማስወገድ ነው። አልፎ አልፎ የሚታየው የተብሰከሰከ የአስተዳድር ይዘት ከዚሁ ድክመት የመነጨ ነው።ከዚህ በመነሳት ለማለት የሚቻለው፣በውስጠታዋቂነት ቢሆንም ምርጫው እንዲካሄድ የሚፈልገው አስተዳደሩ፣ ሕዝብና ደጋፊው ምሁራን፣ በህዝብ የተመረጠ መንግስትን የመመሥረት አስፈላጊነት በመረዳቱና በማመኑ ነው። የምርጫው ሂደት ሲጠናቀቅ፣ በመከናወን ላይ ያለው ለውጥ ሙሉበሙሉ በኢትዮጵያ ሕዝብ እጅ ይገባል። ባለቤቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው ማለት ነው። ከዚህም በመነሳት የዶ/ር አቢይ አህመድ ስጋት ሊቀንስ ይችላል። የተንኮለኞቹ ይተንኮል ሥራ በሕዝቡ መጋለጥ ቀላል ይሆናል።

ሶስተኛው ምክንያት፣  በሕዝብ የተመረጠ አስተዳዳር ከሌለ፣ከፖለቲካው፣ ከኢኮኖመውና ከሶሻሉ አቅጣጫ የሚመነጩ ችግሮች ቋሚ ባለቤት የላቸውም፣ አይኖራቸውምም። ሕዝብ የመረጠው አስተዳደር እስከሌለ ድረስ፣ኢትዮጵያ ምድር ላይ ተባዝተውና ተራብተው የሚታዩ ህወሃት በቀል፣ ወፍ ዘራሾቹን ጭምሮ፣ሕገመንግሥቱንም ጨምሮ ፣ባለቤት የሌላቸው ችግሮች መሆናቸውን መረዳት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህም የአስተሳሰብ ሂደት በመነሳት፣የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫውን ሲያጠናቅቅ፣እነዚህ ባለቤት የሌላቸው ችግሮች፣ ሕገመንግሥቱን ጭምሮ፣ባለቤት አገኙ ማለት ነው።ችግሮቹ በላቤት አገኙ ማለት ደግሞ፣የሚከተለው አስተሳሰብና እርምጃ፣መፍትሄም ተገኘላቸው ማለት ነው።የመፍትሄውን ቅደምተከተል፣እንደአስፈላጊነቱ የሚወስነውና በሥራ የሚተረጉመው በህዝቡ ተመርጦ አስተዳድሩን የጭበጠው ሃይል ይሆናል ማለት ነው።በመሠረተ ሃሳብ ደረጃ፣የምርጫውን አስፈላጊነት በዚህ መልክ መተንተኑ፣ጥሩ ጥርጊያ ጎዳናን ያሳያል። የተጀመረውንም የለውጥ ሂደት ያልምንም ጥርጣሬ እንዲሳካ ያደርገዋል።

ሌላው ከምርጫ በኋለ ባለቤት ማግኘት የሚያስከትለው አዎንተዊ ጉዳይ፣ ፓርላማውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተጠሪነታቸውና ታዛዥነታቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚሆን ለማንም ግልጽ ነው፣ መሆንም አለበት። የኢኮኖሜውና የሶሻሉ እድገትና መሻሻል፣ የፖለቲካ ሂደቱንም ጨምሮ፣የእነዚህ የሁለቱ ዘርፎች ጥምር ሃለፊነት መሆኑም ግልጽ ነው። ከምርጫው በኋላ፣ የሕዝብ መሪነት በደንብ ስለሚረጋገጥ፣ የውጪ መንግሥታትም አመላካከትና አስተያየት፣ አክብሮትም ጭምር፣ በእጅጉ ይሻሻላል። ሊለወጥም ይችል ይሆናል። ጠቅላህ ሚኒንትሩ ዶር አቢይ አህመድም ተደማጭነትን ያገኛሉ።ሚዛን ያጣውንም የውጭ ጉዳይ ሆኔታ ለማስተካከል ከተመቸም ለመምራት ድፍረት ይኖራቸዋል። ለምን ቢባል? ከበስተኋላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለ ተሰልፏልና።ስለዚህ፣ምርጫው የታቀደለትን ጊዜ ጠብቆ፣ ያልምንም ማመንታት መተግበር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣የፖለቲካና የሶሻል እድገትና ሂደት ላይ ለያደርግ የሚችለው አስተዋጻኦ በፍጹም በቀላል መተያት ያለበትም። ስለዚህ ያለምንም ማመንታት በጥንካሬ ወደፊት መግፋት አማረጭ የሌለው ተግባርና ግዴታ ነው።

  1. II) የምርጫውን ሂደት የሚያመቻቹ ግንዛቤ የሚያስፈልጋቸው ነጥቦች፣

የምርጫውን አስፈላጊነት፣ጥልቀትና ስፋት የመገንዘብ ችሎታን ለማዳበር የሚጠቅሙ አበይት ጉዳዮች፣በተለይ በመለስ ዜናዊ/ህወሃት የአስተዳደር ዘመንና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ዘመን ያሉት የምርጫ ሂደቶች ልዩነቶችን እንመለክታለን። አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ የተያያዘውን ታሪካዊ የምርጫ ሂደት በመለስ ዜናዊ/ህወሃት ጊዜ የነበረውን የምርጫ ሂደት መለስ ብሎ መጎብኘቱ አሁን በመካሄድ ላይ ያለውን የምርጫ ሂደት ጥንካሬና ድክመት፣ሕዝብ አቀፍ መሆን አልመሆኑንንም ጭምር በጥልቀትና በስፋት ለመገንዘብ እጅግ በጣም ይረዳል።ከዚህ መሪ መንደርደሪያ ሀሳብ በመነሳት ሁለት አበይት ነጥቦች እዚህ ይገለጣሉ።

አንደኛው፣ የቅራኔዎች አሰላለፍ ለዩነቶች መኖር፣

በመለስ ዜናዊ/ህውሃት አስተዳድር ጊዜ በሕዝቡና በአገዛዙ መሃል ጥላቻንና የጠላትነት መንፈስን ያካተታ የማይታረቅ ቅራኔ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ አንዣቦ ይሰማ ነበር። በህዝቡና በአስተዳድሩ መሃል በጣም የከፋ ጥላቻ ነበር። እስከ አሁንም ድረስ በኢትይጵያ ሰማይ ላይ አንዣቦ ይገኛል። ለዚህም ነው ለማለት ይቻላል በ”97”ቱ ምርጫ ወደ 26 ሚሊዮን ሕዝብ ወጥቶ የተሳተፈው።የኢትዮጵያ ሕዝብ በመለስ ዜናዊ/ህወሃት ላይ እልሁን ለመወጣት የብሄረሰብ ድርጅቶችንና መሪዎቻቸውን ሳይመርጥ ህብረብሄር ድርጅቶችን የመረጠው።ቅንጅት የሚባለው የፖለቲካ ግንባር ድርጅት ይህን የቅራኔ ሁኔታ በደንብ ተጠቅመውበታል። የአጠቃቀሙን ዘዴ እዚህ መዘርዘሩ ምንም ጥቅም የለውም።መለስ ዜናዊ/ህወሃት በጉልበቱ የምርጫውን ውጤት ባይነጥቅ ኖሮ አቶ ሃይሉ ሻውል ከአሸናፊዎቹ መሀል ብዙውን መቀመጫ ካገኘው ፓርቲ ጋር የጥምር መንግሥት በመመሥረት ኢትዮጵያን የመምራት እድሉ ነበራቸው።

በዶር አቢይ አህመድ በወቅቱ አስተዳደር ዘመን፣ በህዝቡና በአስተዳድሩ መሃል ምንም አይነት ቅራኔ የለም፡፡ ቅራኔ የለም ማለት ደግሞ ጥላቻ የለም ማለት ነው።ይህን አስተሳሰብ የሚያጠናክሩ ሶስት የተከናወኑ ድርጊቶችን እዚህ መጥቀስ ይቻላል።በዶክተር አቢይ አህመድ የሥራ ጠባይ፣ አያያዝና ትህትና ላይ ተመስርቶ  የተከናወነ ግንባታዊ ሂደት ነው ።

1)  በተለይ ቀደም ብሎ፣ ዶር አቢይ በየክልሉ በሚገኙ ቀበሌዎች መድረክ እየተዘጋጀ ህዝቡን ያወያዩ ነበር፣ ይመካክሩ ነበር ለማለትም ያስደፍራል፣በዚህም ጊዜ እሳቸውን ለማየትና ለማዳመጥ የሚሰባሰበው ሕዝብ ብዛት ቀላል አልነበረም። በዚህም ጊዜ ዶር አቢይ አህመድ ማን እንደሆኑና ለሕዝባችው ምን እንደሚያስቡ ሕዝቡ በግልጽ ስለተረዳ የቅራኔና የጥላቻ ሁኔታ ፈጽሞ ቦታ አልነበረውም።ዶር አቢይ አህመድ ከሕዝቡ ጋር የቅርብና የፊትልፊት ግንኙነት ስለነበራቸው ህዝቡ ውስጥ ስምጥ ብለው ገብተው ነበር ለማለት ይቻላል።  2) አሁን በቅርቡ ዶር አብይን ለመደገፍ የወጣው የሰው ብዛት፣ 3) የአድዋን የድል በዓል ለማክበር ከዳር እስክዳር፣ ከሰሜን፟/ደቡም፣ ከምሥራቅ/ምአራብ፣ትንንሽ ቀበሌዎች ሳይቀር ግልብጥ ብለው ወጥተው በመሰለፍ ሲከበር ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር።አነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ የሚጠቁሙት በኢትዮጵያ ሕዝብና ባለው መንግስት መሃል ምንም ያይነት ቅራኔና ጥላቻ እንደሌለ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት ዶክተር አቢይ አህመድ ባስተዳደሩ ላይ መሰየማቸውና ባሳዩት ከህዝብ ጋር መሬት የነካ የግንኙነት አያያዘቸው ነው።

ሁለተኛው ልዩነት፣ የምርጫ አስፈላጊነትና በተግባር የመተርጎሙ ሁኔታና የምርጫ ቦርድ አመራረጥና አሰያየም ልዩነቶች ናቸው። የመለስና የዶር አቢይ የአስተዳድሮች ልየነቶች በተካታታይ ቀጥሎ ቀርበዋል።

1) መለስ ዜናዊ/ህወሃት ምርጫን በሚመለከት እቅዱና ዓላማው ምን እንደነበረ ቀጥሎ እንደሚታየው ግልጥ አድርጎ አስቀምጦታል።እንደዚህ ነው ያለው፣

…. Only by winning election successfully and holding power without letup can we securely establish the hegemony of Revolutionary Democracy. If we lose in the elections even once, we will encounter a great danger. So in order to permanently establish this hegemony, we should win in the initial elections…. In the subsequent elections, too, we should be able to win without interruption.          በእንግሊዝኛ ተጽፎ የነበረው እንዳለ ገብቷል። ቢተረጎም ሊዛባ ይችል ይሆናል ከሚል ጥንቃቄ የተነሳ ነው። የምርጫ ቦርዱንም አመራረጥና አሰያየም ይህንኑ የመለሰ ዜናዊ/ህወሃትን እቅድና አላማ ለማሙዋላት ብቻ ነበር። የምርጫ ቦርዱ ምን ማድረግ እንዳለበትና ምን ማድረግ እንደሌለበት መመሪያውና ትእዛዙ ይሰጠው የነበረው ከመለስ ዜናዊ/ህወሃት ነበረ።የቦርዱ ተግባር ትእዛዝ መፈጸም እንጂ ከራሱ አፍልቆ የመሥራት  መብትና እድል አልነበረውም። የመለስ ዜናዊ/ህወሃት ሥራ አስፈጻሚ መሳሪያ ነበር።

2) በዶር አቢይ አህመድ አስተዳደር ውስጥ፣የምርጫ አስፈላጊነትና የምርጫ ቦርድን መሰየም ዳያሌክቲካዊ ንኙነት አላቸው።ሁለቱን ለያይቶ ማስቀመጥና መተንተን ተሰካኪ ተግባራቸውን ማላላትና ማዳከም ነው የሚሆነው።ለአንዱ ያለው አስተሳሰብና አተናተን ከደከመ የሌላውም የደከመ ነው የሚሆነው። በዶክቶር አቢይ አህመድ አስተዳደር ውስጥ፣ ከምርጫ በፊት፣በምርጫ ጊዜ፣ ከምርጫ በኋላ የሚሉ ሂደቶች ተስካክተው፣ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች በደንብ ታስቦባቸው የመርጫ ቦርዱ ከሚያካሂደው ልዩ ልዩ ቁልፍ ተግባሮች፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጣምረው እየተከናወኑ ይገኛሉ። ለምሳሌ፣ ዶክተር አቢይ አህመድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ከምርጫው እራሳቸውን እንዳያገሉ፣ ከዚያም አልፎ ለምርጫው ያሚያስፈልጋቸውን ልዩ ልዩ መሣሪያዎች፣ቁሳቁሶች እንደሚሟላላቸው እስከማለት የደረሰ አሳባዊ ምክር በመስጠት የተሳታፊው ፓርቲ እንዲበዛ ለማድረግ ሞክረዋል።በምርጫው መጨረሻም ከተሸነፉ በደስታ እንደሚያስረክቡ ሁሉ በተደጋጋሚ ቃል ገብተዋል። አንጠራጠር። አሁን በቅርቡ ምርጫው ተጠናቆ ውጤቱን ለማየት ስንችል፣ ለምን ከአሁኑ እንጠራጠርና ልዩ መንፈስ ውስጥ እንገባለን?

እዚህ ላይ ተያይዞ መታየት ያለበት መሰረታዊው የምርጫው ሂደት፣ ከምርጫ ቦርድ አሰያያም ጋር የተያያዘ ጉዳይ፣አሰያያሙ የተከናወነው፣ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሉ፣ ለጥራት ከመቀነሳቸው በፊት፣በተገኙበት የምርጫ ቦርዱ ከተሰየመ በኋላ፣ የምታስተዳድረውንና የምትመራውን ወ/ት ብርቱካን ሚደክሳን ከሰየመ በኋላ ነው። በብርትኳን ሚደቅሳ የሚመራው የምርጫ ቦርድ፣ መለስ ዜናዊ/ህወሃት ይመራው ከነበረው የምርጫ ቦርድ እጅግ በጣም የተለየ ነው። ማነጻጸሩም አግባብ አይደለም።ብርቱካን ሚደቅሳ ሕግ አዋቂ፣የሕዝብ አገልጋይ፣በራሷ የምትተማመን ስለሆነች፣ በመለስ ዜናዊ/ህወሃት ጊዜ ይካሄድ እንደነበረው፣ በዶክተር አቢይ አህመድ ትእዛዝና መመሪያ፣ ወሳኝ ሆኖ እስካልተገኘ ድረስ፣ የምትታዘዝ አትሆንም።ይህም ሁኔታ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ አመኔታን ያሳድራል። አሳድሯልም ለማለት ይቻላል። በእርሷ አመራር ሥር ያለው የምርጫ ቦርድ በማድረግ ላይ ያለውንና ብሎም ያከናወናቸውን በብቃት እዚህ ለመዘርዘር ይቻላል። ዞሮዞሮ ይህ ሁሉ የምርጫው ክንውን ያሚያሳየው፣ የዶ/ር አቢይ አህመድን የአመራር ብቃትና ችሎታ ዘዴ መሆኑን ማጤኑ እምነትንና ትብብርን ያጠናክራል።በመካሄድ ላይ ላለውም ለውጥ ጠንካራ ግፊት ይሰጠዋል።

III.  በአሜሪካን መንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መሃል የማይታረቅ ቅራኔ እየተመሠረተ ይገኛል።እጅግ በጣም ያሳዝናል።

ፕሬዚዳንት ባይደን ፈጽሞ ባልገባችው የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ በመነከር በሁለቱ ሐገሮች መሃል የነበረውን ዘመን የቆጠረ ጠንካራ ግንኙነት መስመር እያሳቱት ነው። በሃያ አንደኛው ከፍለ ዘመን ከአንድ ትልቅ ሀገር መሪ ፈጽሞ የሚጠበቅ አይደለም። የህወሃትን መልእክት ነው እያስተላለፉ የሚገኙት። በጣም ያሳፍራል። የአሜሪካን መንግሥት፣ ኮንግረስን ጨምሮ፣ህወሃት የሚባል መርዘኛ ለገዛ ብሄረሰቡ የማይሳሳና የማይጠቅም፣ ከአፍንጫው አርቆ ለማሰብ የማይችል ድርጅት፣ ለሁለቱም እያቀነባበረ በሚመግባችው ዘርፈ ብዙ መሰረተቢስ ተንኮሎች፣ ሁለቱም፣በሚያሳዝን ሁኔታ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በተለይ በውጭ ጉዳይ አስተዳደሩ፣  ነዳፊና አቀነባባሪነት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለውም። የቅንብሩን ንድፈ ሀሳብ አመቻችተው በሥራ ለመተርጎም ከመጠን በላይ፣ምንም ሳያፍሩ፣ሽርጉድ የሚሉት ግለሰቦች አንቶኒ ብሊንከንና ጄፍሪ ፊልትማን ናቸው።ለመሆኑ የአሜሪካንን መንግስት፣ኮንግሬስን ጨምሮ፣እስከዚህ ድረስ እያንገበገቡት ያሉ በኢትዮጵያና በአካባቢዋ እየተፈጸሙ ያሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? እስቲ እነሱን ጠለቅ ብለን እንመልከት፡፡ከዚያ በፊት ግን የትግሉን ሁኔታ ጠቅለል አድርጎ ለማስቀመጥ ያህል፣ የኢትዮጵያ ሰላምና እርቅ ምክር ቤትን በሚመለከት፣ አሁን ትግሉ በነጭና በጥቁር መኻል ሆኗል ነው።

አንደኛውና ምናልባትም ዋነኛው ምክያትህወሃት ከሥልጣን መባረሩ ነው። በ1983 (May 1991) ህወሃትን ኢትዮጵያ ወስዶ ዙፋን ላይ ያስቀመጠው በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አማካኝነትና በሄርማን ኮኸን አጋፋሪነት ነበረ። በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በተራቀቀና ሳይንሳዊ በሆን ዘዴ በመጨረሻም የትጥቅ መሳሪያ ታክሎበት፣ የአሜረካን መንግሥት ያስቀመጠውን የህወሃት መንግሥት ድራሹን አጠፋው።በመሆኑም ህወሃት በየአህጉሩ መንግሥታዊ አመራር እግር ላይ  እየተደፋ ልመናውን እያጧጧፈው ይገኛል። የአሜሪካን መንግሥትም በማያገባው ሥራ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ፣ በመጨረሻ መዋረዱ አይቀርም፣እየፈተፈተ ያለው ይኸው የህወሃት እግር ላይ እየወደቁ ልመና ነው።የአሜሪካ መንግሥትም እንዴት እኔ የሾምኩት መንግሥት ከሥልጣን ወርዶ እንዲባረር ይደረጋል በሚል እልህ ውስጥ ገብቶ እየዋኘ ይገኛል፡፡የአሜሪካን መንግስት ያል ምንም ይሉኝታ መንጦልጦል፣ በጥፍሩም በጥርሱም ያገኘችውን ሁሉ መቧጠጥ አንደኛው ምክንያት ይኽ ነው።

የአሜሪካን መንግሥት በደንብ እንዲረዳው የሚያስፈልገው ታሪክ የጨበጠው ጉዳይ፣ ህወሃት አዲስ አበባ ድረስ ተጉዞ ሥልጣን የያዘው በትግራይ ሕዝብ ደም ላይ እየተረማመደ መሆኑን ነው። እስከ አሁን ድረስ የህወሃት አጅ በትግራይ ሕዝብ ደም የተለወሰ ነው።አልጸዳም። በሀውዚን ያፈሰሰው ደም እንዴት ይረሳል? በረሃቡ ጊዜ በብዙ ሺህ የሚቆጠረውን የትግራይ ሕዝብ ወደ ሱዳን በረሃውን አቋርጠው እንዲሄዱ ገፋፍቶ በረሃ ላይ ብዙ ሺህ ሰው ነው ያልቀው። ነገዱበት፡፡ ይህ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው አረመኔያዊ በደል እንዴት ይረሳል? በቀይ ሽብር ጊዜ 80%ቱን የትግራይ ወጣት የፈጀው ህወሃት ነው። ይሄስ እንዴት ይረሳል። የትግራይ ሕብረተሰብ እንዲቸገር የቴሌፎን መስመር መቁረጥ፣ የመብራት ሃይል መስመር መቁረጥ፣ የውሃ ቧንቧ መቁረርጥ፣ ከሁሉ የሚያስገርመው ደግሞ ድባቅ በተመታበት ጊዜ አብረውት የነበሩትን 10 ሺህ እስረኞች በህብረሰቡ ውስጥ ገብተው እንዲዘርፉ፣ ሴት እንዲደፍሩ እቃ እንዲሰባብሩ ህወሃት ለቀቃቸው። እነዚህ የህወሃት አረሜኔያዊ ሥራዎች እንዴት ይረሳሉ።እነዚህን አረሜኔያዊ ድርጊቶች፣ በገዛ ብሄረሰቡ ላይ የፈጸመውን ድርጅት ነው የአሜረካን መንግሥት ሥልጣን እንዲይዝ የሚታገለው። ከአብረካቸው የወጣው ህወሃት፣ የእናቱ፣ የአባቱ፣ የእህቱ፣የወንድሙ፣ የአክስቱ፣ የአጎቱ እርግማንና ጩኸት ነው ህወሃትን እዚህ ስቃይና ውርደት ላይ ያደረሰው። እጅግ በጣም የሚያሳዝነው፣ለማመንም የሚያስቸግረው ደግሞ ፣አሁንም፣ በመግደል፣ በመዝረፍ፣በማስፈራራት ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ኑሮውን እንዳይሻሽል እያደረገው ነው።

ሁለተኛው ምክያት፣ በአፍሪቃ ቀንድ ያለምንም ጥርጣሬ ሥራቸውን ሰደው የሚገኙት መንግሥታት፣ ኢትዮጵያ፣ሶማሌና ኤርትራ፣ የትብብር ግንኙነት የመፍጠር አዝማሚያ ላይ ስለታዩ፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ ተበላሁ፣የአፍሪቃ ቀንድን የመሪነት ቦታ ማጣቴ ነው በማለት  ሶስቱም ቦታ ሽብር እንዲፈጠርና አለመረጋጋት እንዲኖር ሙከራ ከማድረግ ወደኋለ አላለም።ሱማሌ አሁን ያልችበት የፖለቲካ ችግር ላይ መድረሷ አንዱና ዋናው ምክያት ይህ ነው። አንቶኒ ብሊንክንና ጄፍሪ ፌልትማን፣ በየጊዜው በተለይ ስለኤርትራና ስለኢትዮጵያ የሚለፍፉትን እዚህ ላይ ማጤን ይበጃል።

ሶስተኛው ምክያት፣  የአሜሪካንን መንግሥት ያንገበገበው፣ ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር የፈጠረችውና በማጠናከር ላይ ያለችው የንግድና የሶሻል ግንኙነቶች ናችው።  በአለም አቀፍ መድረክ አሜሪካና ወገኖቿ ግንባር በመፍጠር ኢትዮጵያ ላይ ርብርቦሽ ባደረጉበት ወቅት፣  ቻይና፣ ሩሲያና ህንድ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን በመወገን በኢትዮጵያ ላይ የተደረገውን ሽረባና ርብርቦሹን አክሽፈዋል።ይህም ሁኔታ አሜሪካንን በጣም ሳያስሸብራት እንዳልቀረ መገመቱ ቀላል ነው፣ በተለይ ቻይና በግንባሩ ውስጥ ስለነበረችበት። የአሜሪካኑ ፕሬዝዳንት ባይደን “ኢትዮጵያን አንለቅም” ለማለት ያደረሰው፣ እነዚህ ሶስቱ ሃያል መንግሥታት በተደጋጋሚ በወሰዱት እርምጃ ተረብሾ ነው ለማለት ይቻላል።ለዚያውም ዝርዝር የፖሊቲካ ሁኔታው ከገባው ነው።

አራተኛው ምክንያት፣ ኢትዮጵያ በአድዋው ጦርነት ጊዜ ነጭ ሕዝብ፣ በጥቁሩ ሚኒሊክ  መሪነት አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ፣ ጭራውን ሸጉቦ  ወደ ሃገሩ እንዲሸሽ ተደርጓል። ማን ቢባል? ነጩ ሕዝብ። የአሜሪካን መንግሥት የዚህን አዋራጅ ቅጣት ቁርሾ ይዛ እስከ አሁን ድረስ እያመነዥከችው ትገኛለች፡፡ የአሜሪካ ዘረኛው መንግሥት እንዴት ይቹ ትንሽ ጥቁር አገር ነጭን ታዋርዳለች በማለት ነው፣ ሌሎች ምክንያቶችም ይኑሩ እንጂ፣ አሁን በመቅበዝበዝ ላይ የምትገኘው። የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ያላት ንቀትና ዘረኝነት በቀላል መታየት የለበትም። ነጻ በሆነች አገር ውስጥ ጣልቃ በመግባት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫውን እንዳያካሂድ ሁሉ ቅስቀሳ እስከማድረግ ደርሳለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሜረካ መንግስት በምንም አይነት መናቅ እንደሌለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የሚክተለውን ታሪካዊ መልእክት አስተላልፈዋል፣

ኢትዮጵያ ዛሬ ቁርሷን ምን መብላት እንዳለባትና ማታ ስትተኛ ምን መልበስ እንዳልባት ታሪክ የሌላችው አገሮች የገንዘብ አቅማቸውን መሠረት አድርገው ሊያዙ እየዳዳቸው ነው።እኛ ያልተገዛን፣ ያልተንበረከክንና የማንበረከክ ታሪክ ያለን ሕዝቦች ነን። ስለሆነም ተሪክ የሌላቸው አግሮች በገንዘባቸው አቅም ሊያዙን አይችሉም።መላው ኢትዮጵያዊ በፖለቲካ፣በብሄር በሃይማኖት ሳይከፋፈል አንድ ሆኖ እኛ ኢትዮጵያውያን ነጻ የነበርንና፣ ነጻ ሆነን የምንቀጥል ኩሩ ሕዝቦች መሆናችንን በከፍተኛ ማስተዋልና ትብብር ለእነዚህ ጎርማሶች ማስተማርና ማሳየት ያስፈልጋል።እነሱ ሳይፈጠሩ የነበርን፣ከነሱ ቀድመን ዴሞክራሲንም ሆነ ዲፕሎማሲን ቀድመን የተገበርን መሆናችንን ዓለም እንዲረዳው እንድታደርጉ እጠይቃለሁ።በቀጣይ አመታት ያለ ምንም ጥርጥር የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽና እናረጋግጣለን።አሁን በቂ ልምድና ብቃት ያካበትን በመሆኑ ይህን ከማሳካት ለማስቆም የሚችል ምንም ምድራዊ ሃይል እንደሌለ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

በአሜሪካ ሕዝብና በአሜሪካ መንግሥት መሀል ልዩነት አለ፣

በአሜሪካን አገር የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ይህን ልዩነት በደንብ ሊገነዚቡት ይችላሉ።ትውልደ ኢትዮጵያኑም የሚመደቡት ክዚሁ ከአሜሪካኑ ሕዝብ ጋር ነው።በአሜሪካን ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ጥቅምና ጉዳት በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ላይም ይደርሳል። የአሜሪካን ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት፣ በየዘርፉ ተሳካ ማለት ለትውልደ ኢትዮጵያንም ያለ ምንም ጥርጥር ተሳካ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሰላምና እርቅ ምክር ቤት ይህን ተጨባጭ ሁኔታ በመገንዘብ፣ በዚህ ሰነድ ውስጥ “የአሜሪካን መንግሥትን” ስም ብቻ ነው የተጠቀመው።

አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን፣ ተደማጭነትንና ለማንኛውም የኢኮኖሚና የሚሊታረ ሃይል ተጠሪነትንና ተጠቃሽነትን  ለመያዝ የቻለው፣ በሕዝቡ፣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ቡድን ሥራ የሚደርስ ልዩልዩ አስተዋጻኦ በማድረጉ ነው። ጨረቃ ለይ የማረፍ፣ ማርስ ላይ የማረፍ፣በትመህርቱ፣ በጤናውና በሌሎች ጥናቶችና ምርምሮች ሁሉ የተከናወኑትና በመከናወን ላይ ያሉት በሕዝቡ ያልተቆጠበ ተሳትፎ ነው።ሌላው ቀላል የሚመስል ምሰሌ፣ ለመጥቀስ ያህል፣ባለ 18 ተሽከርካሪ ጎማ (eighteen wheelers) የጭነት መኪናዎች፣ሌሊት ሰው ተኝቶ የአሚረካንን አህጉር እየተምዘገዘጉ ከዳር እስከዳር ለሕዝብ የሚያስፈልጉ የምገብ አይነቶችና ቁሳቁሶች ሲያዳርስ ያድራል።ሌላው በዚሁ መልክ መታየት ያለበት የቧቡር ሀዲዱ ተመሳሳይ ተግባሩ ነው።ከእነዚህ ከባድ የንግድ መሣሪያዎች ጋር፣ ነጂውን፣ ጠጋኙን፣መሃንዲሱን ወዘተ፣ ማያያዙ የተሳትፏቸውን ጥልቀትና ሰፋት ያሳያል።የአሜሪካ ሕዝብ ማለት በጠቅላላው እነዚህንም የጨመረ ነው።

መደምደሚያ፣

መደምደሚያው በሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ይሆናል።የመጀመሪያው ምርጫ ሲሆን የሚቀጥለው ደግሞ “የአሜሪካን መንግስት” ጣልቃ ገብነት ይሆናል።

በኢትዮጵያ የታቀደውን ብሄራዊ ምርጫ፣የምርጫውን የዝግጀት ሂደት በጥሞና፣ ማለትም ተንኮልና ጥላቻ በውስጣችን በሌለበት ሁኔታ የምንከታተል ከሆነ ቁልጭ ብሎ የሚታየው የምርጫ ሂደት ተስፋና እምነት የሚጣልበት ሆኖ ነው የሚገኘው።እስከ ብሄራዊው ምርጭ ድረስ ሂደቱ ማለትም ከምርጫ በፊትና በምርጫ ጊዜ  በትክክል መካሄዱን መከታተል አማራጭ የሌለው ሃለፊነትና ግዴታም ነው።በምርጫ ቦርድና በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚተላለፉ መግለጫዎችና ጥቆማዎችን ልብ ብሎ መከታትልና በትክክል ያልተገልጸው  እንዲስተካከል የግል ሓላፊነታችንን የመወጣት ግዴታ አለብን።እዚህ ላይ መሠመር ያለበት ጉዳይ፣አስተያየታችን ገንቢ መሆኑንና የምርጫውን ሂደት የሚያደናቅፍ እንዳይሆን መጠንቀቁ ነው።ይህ በስፋትና በጥልቀት በመካሄድ ላይ ያለው ብሄራዊ ምርጫ ሲከናወን ለብዙ ድክመቶች መፍቻ ቁልፋቸው እንደሚገኝ አንጠራጠር።ከዚህ እምነት በመነሳት፣ ለምርጫው ጊዜውን ጠብቆ በቶሎ የመጠናቀቁ አስፈላጊነት ያለን የተቃጠለ ጉጉት የበረታ ይሆናል። ስለዚህም፣በውስጥና በውጭ የሚገኙትን ምርጫው እንዳይሳካ የሚታገሉትን የኢትዮጵያ ጠላቶች ሽንጣችንን ገትረን እንደምንታገል ቃል እንግባ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከዳር ስለአሜሪካው መሰሪ መንግሥት እርኩስ ተግባር በግልጥ እንዲያውቀው ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል። ዋናው የአሜሪካን መንግሥት ዓላማ፣ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ሃይሏ እንዳይጠነክርና ተደማጭነት እንዳይኖራት ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይና የማይቆፍረው ጉድጓድ የለም።ከዚህም የተነሳ፣ ኢትዮጵያ ከየአቅጣጫው የሚመጡባትን ችግሮች ተቋቁማ በራሷ እንድትተማመን የአሜሪካን መንግሥት ምንጊዜም ፈልጎ አታውቅም። ይህ ጉዳይ በፍጹም መዘንጋት የለበትም!!!

የአሜሪካን መንግሥት ይህንን ከይሲ ተግባሯን ለማሟላት፣ ማለትም ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማንበርከክ ከፈጸመቻቸው ውስጥ፣ አንደኛው፣ ከብዙ አመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት፣በታህሣስ 1953 በሁለቱ ወንድማማቾች፣ በገርማሜና በመንግሥቱ ነዋይ ኩዴታ ደግሳ ከሽፎባታል፣ ሁለተኛው፣ በግንቦት 1981 በመንግሥቱ ሓይለማርያም፣ “60” የኢትዮጵያ አለኝታና እፍታዎችን፣ ጸሓፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድን፣ የኢትዮጵያ ጭንቅላት የነበሩትን ያካተተ ማስረሸን፣ ሶስተኛው፣ በ1969 የሱማሌው መሪ ሲያድ ባሬ ኢትዮጵያን ወሮ ሐረርን ገንጥሎ ለመውሰድ በቃጣበት ጊዜ፣ ኢትዮጵያ የአሜሪካንን መንግሥት፣በጦርነቱ ምክንያት የጎደለባትን የጦር መሣሪያ ለመተካት የአሜረካንን መንግሥት ጠይቃ ተከልክላለች፡፡ሩሲያ አሟልታላት ነው ያሸነፈችው። ሩሲያ አሁንም ከኢይዮጵያ ጎን በመሰለፍ የአሜሪካንን መንግሥት እያርበድበደች ነው፡፡ የአሜሪካን መንግሥት ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ያለ ምንም ጥርጥር በጣም እንደምታስፈልጋት የኢትዮጵያ መከላከያ ሓይል በተለይ በዚያ አካባቢ ባሳየው ጀግንነት ተገንዝባለች፡፡ አራተኛው፣ አሁን ደግሞ በ2013፣እስከአሁን ከተዘረዘሩት ተንኮል ከተሞላባቸው አረመኔያዊ ተግባሮች ያላነሰ፣ድፍረት፣ ንቀትና ዘረኝነት በተሞላበት ድርጊት ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማንበርከክ በማካሄድ ላይ ያለችው እቅዷ፣ ለ27 ዓመት ሰላም ነስቶ አንድነቷን ለማሳጣት አቅዶ ይጓዝ ያነበረውን ህወሃት፣ ድባቅ ተመቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ እፎይ ብሎ ከተገላገለ በሗላ፣ መልሶ ሥልጣን እንዲይዝ ለማድረግ የአሜሪካ መንግሥት በማስፈራራትና በመሯሯጥ ላይ ትገኛለች፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማንም ተንበርክኮ አያውቅም፣ አሁንም ወደፊትም አይንበረከክም በማለት፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ታሪካዊ አመጣጥና አመሠራረት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም ብሎ የተመዘገበውን ለአሜሪካን መንግሥት የሰጡትን መልስ እዚህ ላይ ማጤኑ ተገቢ ነው። የአሜሪካን መንግሥት ይህን ተገንዝባ አደብ ብትገዛና በኢትዮጵያ ሕዝብና በአሜሪካ ሕዝብ መሃል ወደነበረው ተገነባቢ ግንኙነት የአስተያየቷን አቅጣጫ ብታስተካክል ለሁለቱም ሕዝቦች ጠቃሚ ይሆናል።

በአሜሪካን ሕዝብና በአሜሪካን መንግሥት መሀል ልዩነት እንዳለ ቀደም ብሎ ታይቷል።የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለአሜሪካን ሕዝብ ሌላው በአንጻሩ መገንዘብ ያለበት ጉዳይ፣ በሁለቱ ሕዝቦች መሃል በብዙ ዘመናት የሚቆጠር ጠንካራ ግንኙነት እንዳለ ነው። ለምሳሌ  በአሜሪካን ሕዝብ የተቋቋሙ የምርምርና የጥናት ተቋሞች፣ ዩንቨርሲቲዎችና ኮሌጆች በብዛት ይገኛሉ።ኢትዮጵያውያኖች፣ ሴትና ወንዶች፣ በእነዚህ ተቋሞች በኢኮኖሚ ግንባታ፣በጤንነት ማሻሻል፣ በትመህርት ማሻሻል፣ በየዘርፎቹ በብቃትና በጥልቀት በአሜሪካኖቹ ሰልጥነው ወደ ኢትዮጵያ ሕዝብ በመመለስ በየዘርፉ የሰለጠኑበትን ወደሥራ በመተረጎም የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጥቀም ላይ ይገኛሉ። አሁንም በእነዚህ በአሜሪካ ሕዝብ በተቋቋሙ የጥናትና የምርምር ተቋሞች፣ ዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች ኢትዮጵያውያኖች በመሰልጠን ላይ ይገኛሉ። ይህ የአሜሪካን ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ በመቶ አመት የሚቆጠር  ግንኙነት የኢትዮጵያን ሕዝብ በሚጠቅም ሁኔታ ወደፊትም ይቀጥላል። በሳይንስና ምርምሩ፣ በኢኮኖሚው ግንባታ፣ በሕዝቡ ጢአንነትና ትምህርት መሻሻል የተደረገው ሰማይ ጠቀስ ግንባታ በውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አማካኝነት፣በህወሃት ጠምዛዥነት ፈጽሞ አይፈርስም።

ማፍረስ ቀርቶ አያነቃንቁትም። የአሜሪካን ሕዝብና የኢትዮጵያ ሕዝብ  ግንኙነት ተጠናክሮ፣ ጸንቶ ይኖራል።

June 7, 2021

 

 

2 Comments

  1. አስቸኳይ መልዕክት ለብልፅግና ፓርቲ እና ምርጫ ቦርድ

    ሁሉም ፓርቲ ስለምርጫው አስፈላጊነት አምነው እና ሽንፈትን በሰላም ተቀብለው አገሪቷ እንትቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህንን ቃለ-መሃላ በማይፈፅሙ ላይ ምርጫ ቦርድ ከህግ አካለት ጋር በመተባበር አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው፡፡ በቅድመ ምርጫና በምርጫ ወቅት ውጤት እስኪገለፅ ድረስ ማንኛውም ፓርቲ ተጭበርብሯል፣ ውጤት ተሰርቋል የሚል መግለጫ ወይም ቅስቀሳ ማድረግ እንደሌለበት እና የሚያደርግ የፓርቲ አባል ካለ በፍጥነት በቁጥጥር ስር እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቀልድ አይደለም የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ውጤቱም ተገልፆ ለረብሻና አመፅ የሚያነሳሳ ፓርቲ ካለ ብልፅግና ጨምሮ በአስቸኳይ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት በዚህ ቁርጥ ቀን አገራዊ ፍቅራቸውን ማሳየት አለባቸው፡፡ ከወገናዊነት በፍፁም በፀዳ ሁኔታ፡፡ ነገ የሁሉም ልጆች በሰላም እኒዲኖሩ ዛሬ ሁሉም ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል፡፡ መቼም ለልጆች መጥፎ የሚመኝ አይኖርም እና፡፡ ምርጫ ተጭበርብሯል የሚል ሃሳብ እንኳን ቢኖር በአግባቡ እንዲጣራ ማድረግ እንጂ ፓርቲዎች አላስፈላጊ የሆነ መግላጫ በፍፅሙ መስጠት የለባቸውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምንም እንኳን በምርጫ ቦርድ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ፓርቲዎች ሊፈርሙ ቢችልም ምርጫ ቦርድ ከአሁኑ ይህንን አስመልክቶ ተከታታይ መግለጫና ማሳሳቢያ በሚዲያ ለህዝቡ በአፋጣኝ መስጠት ይኖርበታል፡፡ ማንኛውም ከምርጫ ጋር ተያይዞ ፓርቲዎች መግለጫ፣ ተቃውሞ እና የአመፅ ቅስቀሳ መስጠት እንደሌለባቸው በፍጥነት ሊነገር ይገባል፡፡ ህዝብ እንደሆነ ከተወሰነ ግሩፕ በስተቀር ብጥብጥ እና ግጭት ሰልችቶታል፡፡ ስለዚህ ለጊዜውም ቢሆን አገር እየመራ ያለ ብልፅግና ፓርቲና ምርጫ ቦርድ በዚህ ላይ በደንብ መስራት አለባቸው፡፡ ነገ በዚህ ምርጫ አላስፈላጊ ነገር ቢፈጠር ከተጠያቂነት በተጨማሪ የህሊና ወቀሳም ሰላም አይሰጣቸውም፡፡

    ለሁሉም አምላክ አገሪቷን ይጠብቅ፡፡

  2. ውድ ወዳጀ በምርጫ አማካይነት አንድ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሆኖ አያውቅም። ምርጫው የውክልና ስለሆነ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ በፖሊሲ ነክ ነግሮች ላይ የመወሰን መብት የለውም። ስልጣንን የሚቀዳጀው ኃይል ከውጭ የሚመጣለትን ትዕዛዝ በመቀበል ነው በህዝቡ ጫንቃ ላይ ማንኛውውንም ፖሊሲ የሚጭነው። ይህ ምርጫ እንደገና የንዑስ ከበርቴው አምባገነናዊ አገዛዝ ስልጣንን እንዲቀዳጅና አገራችንን እንዲያተረማመስ ሁኔታውን የሚያመቻች ነው። ድህነትና ረሃብም በምርጫው አማካይነትና በውጤቱ ከኢትዮጵያ ምድር አይወድሙም። እንዲያውም በተቃራኒው ድህነት የሚጠናከርበት ሁኔታ ይፈጠራል። ጦርነቱና አገርን ማተረማመሱ ይቀጥላሉ። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንደዚህ ዐይነቱ ምርጫ የሚጠብቀው ምንም ነገር የለም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.