የሃገር ሉአላዊነት የዜጎች ሉአላዊነት ድምር ውጤት ነው! (ይመር ሙሄ)

June 4, 2021

1280px Ethiopia 1991 1995.svgሰሞኑን አሜሪካ የባለስልጣኖችን ቪዛ የተመለከተና አንዳንድ መለስተኛ ግን በጣመ ጠቃሚ ለሆኑ ነገሮች ማስኬጃ የምትለግሰንን የገንዘብ እርዳታ አስመልክታ በጣለችው ማእቀብ ዙሪያ ትልቅ አቧራ አስነስታለች። አገርቤትም ሆነ ዲያስፖራ የምንኖር አብዛሃኛዎቻችን ይህን የአሜሪካ ውሳኔ እንደትልቅ ድፍረት በመቁጠር ቁጣችንን በሰልፍ፣ በፅሁፍ፣ በቃለመጠይቅ፣ በመግለጫ፣ ወዘተ በመግለፅ ላይ እንገኛለን። የአሜሪካን ባንዲራ እናቃጥላለን ከማለት ጀምሮ ከአሁን ቀደም የሰጠችንን የእርዳታ ዓይነት በማንቋሸሽ ( ነቀዝ የበላው ስንዴ ማለትን ይመስል) እና ሌሎችም የስድብ ውርጅብኝ በአሜሪካ ላይ እያወረድንባት ነው። አንዳንዶች በድፍረት ብታስቀረውስ በገንዘቧ ልትሰደብ አይገባትም በማለት ለሃቅ ወይም ለአሜሪካ ሲቆሙ፣ ሌሎች ድሃ ብንሆንም ኩሩ ቆፍጣናና ባለታሪክ ሕዝብ መሆናችንን ረስተው የአሜሪካ ገንዘብ እንዳይቀርብን ሰፊ ዘመቻ በማስተባበር ላይ ይገኛሉ።

ዋናው ምክንያት አሜሪካ ሉአላዊነታችንን ተዳፍራለች፣ ተጋፍታለች የሚል ሲሆን የቁጣውን ፈረስ በመጋለብ ላይ ያሉት የተለያየ አጀንዳ እንዳላቸው ግልጽ ነው። እጅግ በጣም አስቂኙ ሕወሃትም ከኤርትራና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እኩል በማዕቀቡ ውስጥ በመግባቱ በመደሰትና በመኩራራት ፋንታ የሚደፈር ሉአላዊነት ያለው ይመስል እንደሌሎቹ ለምን ተነካሁ ማለቱ ነው። በእርግጥ በእዚህ አስቂኝ ድራማ ውስጥ ሊያሳስበን የሚገባ ነገር ቢኖር አሜሪካ በጓሮ በር ገብታ እገነጠላለሁ እያለ የሚፎክረውን ሕወሃት ከተሳካለት እውቅና ለመሰጠት እያሰበች እንዳይሆን ነው። ይህም ብቻ ሳይሆን ከሕወሃት ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት አልደራደርም ማለቱን ከቀጠለ እንቢተኛዋ ኢትዮጵያ ናት በሚል ሰበብ አሜሪካ ሕወሃትን በተለያየ መንገድ የምትረዳበት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ከወዲሁ ግልጽ ይመስላል። ይህም ማለት ሕወሃት ግዛት የለለው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከማዕቀቡ ውስጥ በመግባቱ ለጊዜው ቢያላዝንም ውስጥ ውስጡን በደስታ እየፈነደቀ እንድሆነ መገመት ይቻላል።

እኔ በበኩሌ ከረጅም ጊዜ ወዳጃችን ጋር ሃገራችን እንደዚህ ያለ ፍጥጫ ውስጥ በመግባቷ በጣም ባዝንም፣ ወደአሜሪካ ለመሄድ ፈለጉ አልፈለጉም እንደ ጦር አበጋዙ ሽመልስ አብዲሳ ዓይነቶቹ ላይ የቪዛው ማዕቀብ በመጣሉ ከተደሰቱት መሃል ነኝ። እንዲሁም አገኘሁ ተሻገርን በመሰሉ አሳፋሪ የአማራ ብልፅግና አመራሮች ላይ ማዕቀቡ ተፈፃሚነት ስለሚኖረው ደስታዬ እጅግ የላቀ ነው። ቢሆንም በሃሳብ ደረጃ ካልሆነ በቀር የቪዛው ማእቀብ በማንኛቸውም ላይ ይኸ ነው የሚባል ጉዳት ያመጣባቸዋል ብዬ አላምንም። በሌላ በኩል ካየነው ደግሞ ምንም እንኳን አሜሪካ ማእቀቡ የሚመለከታቸውን የስም ዝርዝር ባታወጣም እነሽመልስ አብዲሳ በሃያሏ አሜሪካ ማእቀብ ስለተጣለባቸውና ከኢትዮጵያ ድንበር ውጭም እውቅና እንዲያገኙ ስለሚያደርጋቸው ሰማየ ሰማያት እንደወጡ እንደሚሰማቸው ይበልጥ እንደሚኮፈሱ መገመት ይቻላል። እንደነታዬ ደንዳአ ያለው ደግሞ ገና ለገና አሜሪካ ከማእቀቡ ረስታኝ ይሆናል ብሎ በመቆጨት የአማራ ፍዳ አሜሪካ ዓይን ስለማይገባና የተበላም ዕቁብ ስለሆነ ሌላ ለወደፊት ጎልቶ የሚታይበትን ፀረ ሰላም ድርጊት ለመፈጸም ወይም ለማስፈጸም ያሰላስል ይሆናል።

የአማራው ፍዳ ከተነሳ ዘንዳ በማእቀቡ ውስጥ አሜሪካ የአማራ ልዩ ሃይል “ከምእራብ ትግራይ” ይውጣ ማለቷ አንዳንድ ጥርጣሬዎችን አጭሮብኛል። ከላይ አሜሪካ ሕወሃት አቋቁመዋለሁ ለሚለው ለትግራይ መንግሥት ከአሁኑ እውቅና ለመስጠት ያሰበች ይመስላል የሚለው ጥርጣሬዬ እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ በአማራ ልዩ ሃይል እንዲህ ያለ አቋም በመውሰዷ ከሕወሃት ሌላ ልታስወስደው የፈለገችው ወገን እንዳለ መገመት ይቻላል። በአጠቃላይ የኦሮሚያ ብልጽግናን ብናስብ ከመሃላቸው አሜሪካ በአማራው ላይ በማነጣጠሯ የሚከፋው ያለ አይመስለኝም። በኢትዮጵያም ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዲያስፖራ ተሰግስጎ “ተስፋፊው”፣ “ሰፋሪው”ና “አዲሱ ነፍጠኛ” አማራ ለሚለው ሁሉ ይህ የአሜሪካ አቋም ለጆሯቸው ሙዚቃ ነው። ሱዳንና ግብፅንም አሜሪካ በድንበር አስከባሪውና አይበገሬው አማራ ላይ ወይም ልዩ ሃይሉ ላይ የወሰደችው አቋም የደስታው ተቋዳሾች ያደርጋቸዋል። ምንም እንኳን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ያስከበሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ቢሆኑም አማራው ባለበት በኩል ጠላት ደጋግሞ ስለሚገባ አማራው  የመስዋዕትነት ገፈታውን በመቅመስ ግንባር ቀደሙ መሆኑ አይካድም። ዛሬ ሱዳን ድንበር ገፍታ በመግባቷ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ያለው አማራው ነው። የሆነው ሆኖ የአማራ ልዩ ሃይል ነፃ ያወጣቸውና የተቆጣጠራቸው ወልቃይት ጠገዴ፣ ቃብታ ሁመራ የዛሬ ሰላሳ ዓመት ሕወሃት በጉልበት ከአማራው የወሰደቻቸው መሆናቸውን አሜሪካኖች አጥተውት ሳይሆን ከጂኦፖለቲካዊ ጥቅማቸው አንፃር የአማራ ሕዝብ የዓይን ብሌን የሆነውን የአማራን ልዩ ሃይል በማዕቀቡ ውስጥ ለማካተት በቅተዋል።

አሜሪካ የአማራውን ስቆቃ በትግራይ ላይ እየደረሰ ነው እንደሚባለው ስቆቃ በማዕቀቧ ሃተታ ውስጥ አለማካተቷ ሌሎችን ለማስደሰት እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ሻሸመኔ፣ ወለጋና መተከል ላይ የተፈፀመው የአማራን ዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የአጣዬን፣ የሸዋሮቢትን፣ ካራቆሪን ጨምሮ መደምሰስ አለማካተቷ ሁሉም የሚያላጋውን አማራውን እንደመደራደሪያ ወይም የፋሲካ በግ አድርጋ  በማቅረብ የምትፈልገውን ውጤት ያስገኝልኛል ብላ እንዳሰበች ያመላክታል።  ሌላው አማራውን የአሜሪካ ጥርስ ውስጥ ያስገባው ይህ ሁሉ ቀውጢ ሲያልፍ ከኤርትራ ጋር ሊኖረው የሚችለው መልካም ግንኙነት ነው። የአማራ ልዩ ሃይልና የኤርትራ መከላከያ ሕወሃት የሱዳንን ድንበር አቋርጦ እንዳይወጣ ኤርትራ በኦማሃጀር በኩል፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚልሻ በሁመራ በኩል አፍነው ስለያዙት፣ እንዲሁም በተባበረ ክንድ ከሁመራ ስለመነጠሩት አሜሪካ ደስተኛ እንዳልሆነች ግልጽ ነው። እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው አሜሪካ እሳያስ አፈወርቅን እንደቀጣና አደፍራሽ ስለምታየው አማራው ከኤርትራ ጋር እየተናበበ በመሥራቱ ለአማራው ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ሆኖበታል። ስለዚህ አሜሪካ የአማራን ስቆቃ በሃገሪቱ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ እንዲጣሩ ከሚል ባሻገር የሆነኝ ብላ የተለየ ትኩረት ላለመስጠት የፈለገች ይመስላል።

ሌላው አሜሪካም ሆነች ሌሎች የአማራውን ስቆቃ ክብደት እንዳይሰጡ ያደረጋቸው አገር ቤት ውስጥ የአማራ ብልፅግና አማራውን ከኦሮሙማ ተስፋፊዎች ጋር በማበር እንደነሽመልስ አብዲሰ ያሉትን እያሞግሰ ስለሚያስመታው ሲሆን እንዲሁም ዲያስፖራ ያለው አማራ ከብዙ ቦታ የተከፋፈለ ስለሆነና ስለማይስማማ የወገናቸውን ስቆቃ ለአሜሪካ መንግሥት በአንድነት ማቅረብ ስላልቻሉ ነው። አማራው እራሱ ግራ ተጋብቶ ሌላውን ተመልካች ግራ እያጋባው ነው። ስለሉአላዊነት በሚነሳበት በአሁኑ ሰዓት አማራው ምዕራብ ወለጋ ውስጥ እንደተለመደው እየታረደና እየተፈናቀለ ነው። ዛሬ ስለአማራው ወገናቸው መጨፍጨፍ ምንም ሳይሉ ስለሉአላዊነት ከሁሉም በላይ ድምፃቸው በማህበራዊ ሚድያ ከፍ ብሎ የሚሰማው የአማራ ሊሂቃኖች ናቸው። ይህ ወትሮ በመንግሥት ተቃዋሚነታቸው የሚታወቁ በስሜን አሜሪካ የሚገኙ አንቱ የተባሉ እውቅ የአማራ ሊሂቃንን ይጨምራል። እነዚህ ሊህቃኖች አጋጣሚውን በመጠቀም ወደመንግሥት ጠጋ ጠጋ የማለት አዝማሚያ እያሳዩ ነው ማለት ይችላል። በሌላ አነጋገር ይህ የሰሞኑ የአሜሪካ ማዕቀብ ብዙ እምቅ “አገኘሁ ተሻገሮች” ብቅ እንዲሉ ያደረጋቸው ይመስላል። ግን ሌሎች የብሄር አጀንዳ ያላቸው ስብስቦች ስለሉአላዊነት ሲደነፉ ቢውሉ ከአንገት በላይ እንደሆነና “እቅድ- ለ” (Plan-B) እንዳላቸው ማንንም ሊያታልሉ አይችሉም፡፡ እየገፉበትም ነው። ሰሞኑን እንሺመልስ አብዲሳ የፊንፊኔ ወረዳ ዙሪያ ፍርድ ቤት ብለው ያቋቋሙትን ማየት ብቻ ይበቃል።

እውነት እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መደፈር የጀመረው የአሁኑ የሃገሪቱ ሕገመንግሥት ከተፀነሠሰበትና ሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ሕገመንግሥቱ የመገንጠል መብት ያላቸውና የራሳቸውን ሕገመንግሥት በፈለጉት መልክ የሚጽፉ ክልልሎች (መንግሥቶች) ባቋቋመ ጊዜ የኢትዮጵያ ህልውናና ሉአላዊነት ተጥሷል፣ ተደፍሯል፣ ተሸራርፏል። ሌሎች እንደአሜሪካ ያሉ ሃገሮች ሉአላዊነታችንን ተዳፍረው ከሆነ በእርግጥም እኛ በከፈትንላቸው በር ገብተው ነው። ሉአላዊነታችንን ተዳፍራችኋል ብለን የምንከሳቸው ሁሉ ይህንኑ ሃቅ የተገነዘቡ ይመስለኛል። ለዘውግ ፖለቲካ ተብሎ፣ አማራውን ለመጉዳት በማሰብ ሱዳን አልፋሽቃን ድንበር አቋርጠሽ ያዢ ስትባል ሉአልዊነታችንን እንዴት ነው እኛው ራሳችን ደፍረን አላስደፈርነውም ማለት የምንችለው? ክልሎች የራሳቸው ከብዙ የአፍሪካ ሃገሮች የሚበልጥ የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉበት ልዩ ሃይል ሲኖራቸው እንዴት ነው የሉአላዊነት ጠላታችን እኛው ራሳችንን ነን ማለት የማንችለው? የሱማሌና የአፋር ክልሎች ውጊያ ሲገጥሙ እነሺመልስ አብዲሳ በተለያየ መንገድ ይደግፉታል የሚባለው ሃይል አጣዬን፣ ካራቆሪንና ሸዋሮቢትን ሲደመሥ እንዴት ነው ሉአላዊነታችንን መጫወቻ አላደረግነውም ማለት የምንችለው? ሉአላዊነታችንን የውጭ ሃይሎች ደፈሩት ብለን የምንከስ ከሆን፣ የደፈሩት እኛው ልዩልዩ ዘውጌ አገር አፍራሽ አጀንዳዎች በማንገብ የጎዳነውን ሉአላዊነታችንን እንደሆነ ማመን አለብን።

የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለዘመናት ዋና መርሁ አድርጎ የሚንቀሳቀሰውን አማራን እየጨፈጨፍንና እያፍናቀልን ሉአላዊነቴ ተደፈረ ብሎ መጮህ የአዞ እንባ ማፍሰስ ነው። “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም” እንደሚባለው እኛው እራሳችን የተጫወትንበትን ሉአላዊነት ሌሎችን ቢደፍሩት ለምን ይደንቀናል? የሉአላዊነታችን ዋና ጠላቶች በችግር ጊዜ የምትደርስልን አሜሪካና ጎረቤታችን ሱዳን ሳሆኑ በመጀመሪያ ደረጃ እኛው እራሳችንና ሕገመንግሥታችን ነው። የአንድ አገር ሉአላዊነት የየአንዳንዱ ዜጋ ሉአላዊነት ድምር ውጤት ነው። ሕገመንግሥቱን ተገን በማድረግ፣ ይህንን የዜጎች ሉአላዊነት መዋቅራዊ በሆነ መንገድ በመግደል፣ በመዝረፍ፣ በመውረርና በማፈናቀል የምትጥስ ሃገር ሉአላዊነቴ ተደፈረ ብላ ሌሎችን የመክሰስ የሞራል ልዕልና አላት ወይ ብሎ መጠየቅም ከተገቢነት በላይ ነው።

3 Comments

  1. ህወሀት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የትግራይ ነዋሪዎችዋን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከምዕራብውያን በሚመጣ የምግብ እርዳታ ስትዶግም ሰላሳ አመታት አሳልፋለች። የትግራይ ነዋሪም በወልቃይት ፣ በራያ እና በሁመራ ጥቂትም ቢሆን የምግብ ዋስትናም ያገኝ ነበር ፤ የትግራይ ፖለቲከኞች ሙሉ በሙሉ ለአማራ ክልል ፖለቲከኞች እንዳሳሰቡት ፤ ወልቃይትን እና ራያን ለቅቃችሁ ውጡ ብለን ስንነግር ወራት ተቆጥረዋል ፤ የትግራይ ህዝብ የአማራ ብልፅግናን ቢመክርም የአማራ ብልፅግና በመከላከያ እና በኤርትራ ጦር አይዞህ ባይነት ተማማኖ ወልቃይትንም እና ራያንም እንደተቆጣጠረ ይገኛል።

    የኤርትራ ጦር እና መከላከያ ካላገዛቸው በእንድ ጀንበር የትግራይ ልዩ ኃይሎች በቦታዎቹ ዘምተን የአማራ ልዩ ኃይልን ጠራርገን ከወልቃይት እና ከራያ እንደምናባርር እየታወቀ የአማራ ባለስልጣናትም ሆኑ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ከአሁኑ ወልቃይትን እና ራያን ለቀው የአማራ ልዩ ኃይሎችን አስወጥተው አስወጥተውቸው ፤ የአማራ ልዩ ኃይሎች ብዙ ዕልቂት ሳያጋጥማቸው ወልቃይት እና ራያን ለቀው ወደ አማራ ክልል ለመመለስ ያልፈለጉበት ምክንያት ሊጠና ይገባዋል። በሰላማዊ መንገድ ትግራይን ለቀው ካልወጡ የአማራ ልዩ ኅይሎች በትግራይ ኃይል የሚደርስባቸውን ጥቃት እና ውርደት እንዲደርስባቸው ፈልገውስ ይሆን እንዴ?ያስብላል።

    “መንታ መንታ” እየተባለ በትግራይ እየተዘፈነ የትግራይ ህዝብ ብዛት ስላሸቀበ የትግራይ ህዝብ ነዋሪ ህዝብ ቁጥርን የምግብ ዋስትና ሁልጊዜ የአሜሪካ መንግስት ሊያሙዋላ ስለማይችል ወልቃይትን እና ራይን ለትግራይ መንግስት አስተዳደር መሰጠቱን የአሜሪካ መንግስት መደገፉ ለትግራይ ብቻ አድልቶ ሳይሆን ፤የአማሪካ መንግስት በዋንነኝነት ስጋቱ የወልቃይት እና የራያን አማራዎችን በትግራይ ልዩ ኃይል ይደርስባቸዋል ብሎ ለሚገመተው ሽንፈት ፣ ውርደት እና ዕልቂት ሰግቶ መሆኑን ያሳየ ነው። ይህም ታውቆ የወልቃይት እና የራያ ሰላማዊ ህዝብ ለማይቀረው የትግራይ እና የአማራ ክልል የሽምቅ ውጊያ እና የመሳሰሉት አይነት ጦርነቶች ማምለጫውን ያዘጋጅ ፤ በሁዋላ በእኛ እንድታመካኙ ፥ውርድ ከትግራይ ጀግኖች ብለናል!!!

    • ምኞት አይከለከል! ይልቅ የአሜሪካ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ ሁሌ ቀለብ አቅርቦ ስለማይዘልቀው ከለምለሙ ወልቃይት ጠገዴ የአማራ ልዩ ሃይል ይውጣ ያለው ያለ ምክንያት አይደለም ያልከው የምትገርም ናት። እኔ በዛ በኩል አስቤው አላውቅም ነበር።

  2. ብርሀኑ ነጋ ከፖለቲካ ክልተባረረ አገር እንደታመሰ ይኖራል

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.