የዓለም ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ›› እንዴት ይፈፀማል – ቴዎድሮስ ጌታቸው /ደራሲ/ ድሬዳዋ

ቀን፡ 26/09/2013

ለዘሐበሻ ሚዲያ ድረ-ገፅ  ዝግጅት ክፍል (ለአልዩ ተበጀ)
ለግዮን መጽሔት ዝግጅት ክፍል
አዲስ አበባ                        

spower

‹‹የዓለም ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ›› እንዴት ይፈፀማል?

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዘሐበሻ ድረ-ገፅ ‹‹የባይደን መውደቅ›› በሚል፤ ጥቂት የፅሑፍ መረጃዎች ተለዋውጠን ነበር፤ ከመረጃዎቹም ውስጥ የጆ. ባይደን አስተዳደር፤ በመሀከለኛው አፍሪካ፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በአፍሪካ ቀንድና በኢትዮጵያ፤ እያራመደ ያለው ከአሜሪካን ዓላማ ያፈነገጠና በግለሰቦች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የውጭ ፖሊሲ፤ ከዓለም-አቀፉ የንግድ ትብብር ድክመቱ ጋር ተደማምሮ፤ አሜሪካን ‹‹የዓለም ልዕለ ኃያልነት›› እየከዳት እንደሚገኝ የተጠቆመበት፤ በዚህ ‹‹አልሞት ባይ ተጋዳይነት›› ውስጥም፤ አሜሪካን በታዳጊ አገራት ላይ ጥፋት ልታስከትል እንደምትችል፤ በመላ-ምትና በጥያቄ መልክ ሀሳብ የቀረበበት፤ እንዲሁም ይህን ስጋት ለማቃለል በቀጠናችን በሚከናወነው እንቅስቃሴ ላይ ዝግጁነት እንዲኖረን የተጠቆመበት ተጠቃሽ ነው፡፡ አሜሪካን በነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች፤ ልዕለ-ኃያልነቷን በገዛ እጇ ልታጣ መሆኑን ተከትሎ፤ ከልዕለ-ኃያልነት ርክክብ በፊት ሊኖር የሚችለውን ክንውን አስቀድመን እንቃኛለን፡፡

የተከበራችሁ አንባቢያን እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልፅ ላደርግላችሁ እወዳለሁ! ያም ‹‹ከልዕለ-ኃያልነት ርክክብ ቅድመ ክንውን እስከ ልዕለ-ኃያልነት ርክክብ›› ያለውን ፖለቲካዊ መላምት የማስቃኛችሁ፤ አሜሪካን በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰችባት ባለው ፖለቲካዊ ጫና፤ በቁጣ ተነሳስቼ የመልስ-ምት ለመስጠት አይደለም! ይህ ጉዳይ ቀደም ሲል ትኩረት ያደረኩበትና ዓለም-አቀፉን እንቅስቃሴ ተመልክቼ በሰኔ 2011 ባሳተምኩት፤ ‹‹አልወልድም-የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫዎች›› በተሰኘው ቅጽ1 መፅሐፍ ተከትቦ የተቀመጠ፤ የአፈፃፀሙንም ቅርፅ እየለወጠ እውን ወደመሆን እየሄደ ያለ መላምት /ፖለቲካዊ ትንበያ/ ነው፡፡ በመሆኑም አሁናዊ አህጉራዊና ቀጠናዊ የፖለቲካ፤ እንዲሁም የሚሊተሪ እንቅስቃሴዎችን አካተን፤ የ‹‹ልዕለ-ኃያልነት›› ቅኝታችንን እንቀጥላለን፡፡ እንሆ፤

ከኢራቁ ዘመቻ መልስ!

ከ2003ቱ Operation Iraqi Freedom ከሚለው ‹‹የማይተገበር መፈክር››፤ አሜሪካን ከኢራቅ ይዛ የተመለሰችው የሳዳምን ሞት የሚያረጋግጥ ሰርቲፊኬት ብቻ አይደለም፤ የኢኮኖሚ ድቀቷን /Economic Recession/ ጭምር ነው፤ እድሜ ለቻይና፣ ለቻይና ባለሀብቶችና ለባራክ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ትበል፤ በረጅም ጊዜ ብድር ከጉድ ወጥታለች! በኢራንና በቬኒዙኤላ ታስቦ የነበረውን ወታደራዊ አማራጭ ያስቀረችውም፤ ከኢራቁ ዘመቻ የከፋ ውጤት የሚያስከትልና ይዛ በምትመለሰው የኢኮኖሚ ድቀት፤ ዳግመኛ የማገገሚያ ብድር የሚያቀርብላት አገር እንደማይኖር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የኢራቁ ዘመቻ ለአሜሪካን የሸለማት የኢኮኖሚ-ድቀት ‹‹ያንስብሻል›› ብሎ ፖለቲካዊ ኪሣራንም አጎናፅፏታል፤ ብዙ ጊዜ እንደታዘብነው አሜሪካን በኢኮኖሚ ስትደቅ ኑሯቸው የሚቃወስ፤ በኢኮኖሚ ስታንፀባርቅ ደግሞ ፊታቸው የሚበራ አውሮፓውያን አገራት ጥቂቶች አይደሉም፤ ለዚህ ተጨባጭ ምሣሌ የምትሆነን ዩክሬይን ናት፤ የአሜሪካን ‹‹የኢኮኖሚ ድቀት›› በወረርሺኝ መልክ ዩክሬይን ውስጥ ሲገባ፤ ከኢኮኖሚ በሽታ ወደመለያየት በሽታ እንዲቀየር አድርጎታል፤ ይህንን ‹‹የዩክሬን በሽታ›› ስትጠባበቅ የነበረችው እና ‹‹የሶቪየት ሕብረት ስልታዊ ተሸናፊነት›› የሚያንገበግባት የሩሲያ ፌዴሬሽን፤ በሽታውን አባብሳ ‹‹ክሬሚያ›› የምትባለውን የዩክሬይን ግዛት ፍቃደኛነቷን ጠይቃ አፈፍ /Annex/ አድርጋ ወደግዛታ ጨምራታለች፡፡ ይህ እንግዲ ለሩሲያ ፌዴሬሽን ትርፍ ሲሆን፤ ለዩክሬይንና አሜሪካን ኪሣራ መሆኑ ነው፡፡ እንቀጥል!

አሜሪካን እ.ኤ.አ. በ2011 በሊቢያ ላይ ያከናወነችውን ዘመቻዋን ስንቃኝ ደግሞ፤ ሞሀመር ኤል ቃዳፊን ከሥልጣን ከማውረድ ያለፈ ግብ ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፤ ያም ዘመቻ የሊቢያ ከፍተኛ ተቋሞችን እና መሠረተ-ልማቶችን ከአየር ላይ በሚጣሉ ቦንቦች እንዳልነበሩ አድርጎ በማውደም፤ ሊቢያን በመልሶ መገንባት /Re-Construction/ ቢዝነስ ውስጥ ያለማንም ተወራራጅ ‹‹ግንባር ቀደም የግንባታ ተቃራጭ›› በመሆን፤ የግንባታ ሥራ ትርፍ ማግበስበስ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጭምር ነበር፤ ነገር ግን ይህ የአሜሪካን የተሳሳተ ‹‹የግንባታ ትርፍ ጦርነት›› እንደተጠበቀው ሳይሆን፤ ሞሀመር ቃዳፊን የተካው የሊቢያ መንግስት ‹‹የግንባታ ዋጋችሁ ውድ ነው›› በማለት፤ ‹‹ለመሠረተ-ልማት ግንባታዎች ተመጣጣኝ ዋጋ ታቀርባለች›› ላሏት ቻይና የግንባታ ሥራውን ሰጥተዋታል፤ በዚህም የሊቢያ መሠረተ-ልማቶችን ለማፈራረስ ‹‹ከአየር ላይ የተጣሉ ቦንቦች›› በአሜሪካን ኪሣራ ተመዝግቦ ለታሪክ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡

የልዕለ-ኃያልነት ክፍተቶች!

የልዕለ-ኃያልነት ክፍተቶችን ለመፈተሽ ወደ2014 ጎራ ማለት ጠቃሚ ይሆናል! እ.ኤ.አ. ከMarch-May 2014 የካፒታሊዝም ንጉሰ-ነገሥት አሜሪካን፤ እንዲሁም ንግስተ-ነገሥታት የሆነችው ታላቋ ብሪታኒያ፤ በልጆቻቸው ባራክና ካሜሮን አማካኝነት፤ ከአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት አመራሮች ጋር ሲወያዩ፤ በሌላ በኩል የሠሜን አትላንቲክ ቃል-ኪዳን ጦር /NATO/፤ የሩሲያ አጎራባች በሆነችው ፖላንድ ውስጥ ‹‹ቅድመ ጦርነት ልምምድ›› እንዲያደርግ አዘዋል፤ በፖላንድ የፖለለቲካ መፈትፈቻቸው በሆነችው ‹‹ዋርሳው›› ደግሞ ‹‹ሄድ-መለስ›› ሲሉ ነበር የከረሙት፡፡ አላማውም ሁለት ነበር! አንደኛው ሩሲያ አፈፍ አድርጋ ‹‹ግዛቴ ነሽ›› ያለቻትን ‹ክሬሚያን› ለሚገባት አገር ዩክሬይን እንድትመልስ ለማስገደድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ‹‹የካፒታሊዝም ሥርዓት ወዴት እየተጓዘ ነው?›› የሚለውን ከባድ ጥያቄ፤ ከBrussels ስብሰባ፣ ከWarsaw ‹‹የፖለቲካ ፍትፍት›› እና ከNATO የአየር-ኃይል ጀቶች ‹‹የመገለባበጥ ትዕይንት›› ውስጥ መልስ ማግኘት ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው!! የቀድሞው የኢራቅ የጦር ሠራዊት አባላትና በአሜሪካን ይደገፉ የነበሩት የሶሪያ አማፂያን፤ በቅፅበት ተጣምረው I.S.I.S. የተባለ የሽብር ቡድን በመመሥረት መሀከለኛ ምሥራቅን አንቀረቀቧት፤ እነዚህ የሽብር ቡድኖች ባራክንና ካሜሮንን ለክሬሚያና ለካፒታሊዝም ሥርዓት ላነሱት ጥያቄ፤ መልስ ለመሻት ያደረጉትን ሙከራ ከማናጠባቸው ባሻገር፤ ጥያቄውን እርግፍ አርገው እንዲተውት አስገድደዋል፡፡ እዚህ ላይ ከምናያቸው ክፍተቶች አንዱ፤ ‹‹ቀደም ሲል የተከናወኑ የተሳሳቱ ድረጊቶች›› የሚያስከትሉትን ውጤት ‹‹ቀድሞ ያለማሰብ›› ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እንቀጥል!

ወደ2016 ስንመጣ በአሜሪካን የፕሬዚደንትነት ምርጫ ውድድር፤ አንዱን እየዘለፈ፣ ሌላኛውን እያዋረደ፣ የቀረውን ደግሞ እያሸማቀቀ፤ ውድድሩን በማሸነፍ የአሜሪካን ፕሬዚደንትነት መንበር የጨበጠውን ዶናልድ ትራምፕን እናገኛለን፤ ፕሬዚደንት ትረምፕ ከምርጫ ውድድር ጀምሮ ‹‹ዓላማዬ›› ብሎ ከያዛቸው ጉዳዮች አንዱ፤ የሠሜን አትላንቲክ ቃል-ኪዳን ጦር አባል አገራት ‹‹ለድርጅቱ ተመጣጣኝ የገንዘብ መዋጮ ያድርጉ›› የሚል ነው፤ ይህ የትረምፕ አቋም ‹‹አሜሪካን ብቻዋን እዳ የለባትም›› የሚል ሆኖ እናገኘዋለን፤ በርግጥ ይህ አቋም በቀድሞው ፕሬዚደንት ባራክ ተይዞ ሲራመድ የነበረ አቋም ነው፤ ልዩ የሚያደርገው ባራክ አለሳልሶና ዲፕሎማሲያዊ ጥበብን ተንተርሶ ሲሆን /We Can’t Do It Alone-Jun 3-2014/፤ ትራምፕ ደግሞ አስጨንቆና አስጠብቦ የሚያራምደው አቋም መሆኑ ነው፡፡ ይህ የትረምፕ አስጨናቂ አካሄድ ፈረንሳይና ጀርመንን፤ Europe Great Again እና Franco-German Condominium የሚለውን ሀሳብ እንዲያብላሉት ያስገደደ ሆኗል /The Washington Post-Nov.8-2019/፤ ቱርክና መሰል አባል አገራትንም ብንመለከት ለNATO ተጨማሪ ገንዘብ ከማዋጣት ይልቅ፤ የራሳቸውን የሚሊታሪ አቅም ቢያጠናክሩና ሌላ ጥምረት ቢፈፅሙ የሚመርጡ ሆነው ይታያሉ፤ ‹‹ልዕለ-ኃያልነት›› በNATO ውስጥ የሚታይበት ክፍተት በጥቂቱ ይህን ይመስላል!!

ሌላው ክፍተት ‹‹ወዳጅ የማስከፋት ጣጣ›› ነው! በቀዳሚነት ኪዩባን ስንመለከት፤ የኪዩባው ‹‹ሶሻሊስታዊ መሪ›› የነበረው ዶ/ር ፊደል ካስትሮ ሩዝ፤ በእርጅናና ጤና ማጣት ምክንያት በትረ-ሥልጣኑን ወንድምና የትግል ጓዱ ለሆነው ራውል ካስትሮ ለማስረከብ ሲገደድ፤ ራውል ከቀድሞው የአሜሪካን ፕሬዚደንት ባራክ ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በMarch 2016 ተፈራርመው ነበር፤ ምን ዋጋ አለው!! ኪዩባ የስምምነቱን 1ኛ ዓመት አክብራ ሁለተኛውን ሳታጣጥም፤ ፕሬዚደንት ትረምፕ እዚያው ኪዩባ አቅራቢያ በምትገኘው ግዛት Miami ተገኝቶ ስምምነቱን ሽሮታል /June 2017/፤ ፕሬዚደንት ትረምፕ በዚህ ተግባሩ ኪዩባን ወደቀድሞው 50 ዓመታት ‹‹በአሜሪካን የመከፋት በሽታ›› ውስጥ ሊከታት ችሏል፡፡ ትረምፕ ይቀጥላል! ፓኪስታንን ደግሞ ‹‹በተ.መ.ድ. እኛ ያቀረብነውን ሀሳብ አልደገፍሽም›› በሚል፤ ወደ300 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ቋሚ ድጋፍ እንድታጣ አድርጓታል፤ ፓኪስታን በዚህ የአሜሪካን ተግባር ቢን-ላደንን ለመግደል በአገሯ ከተከናወነው ‹‹ፍቃድ የሌለው ኦፕሬሽን››፤ የበለጠ የተከፋችበትና እሪታ ያሰማችበት ነበር፡፡ ስንቀጥል ጃፓንና ሕንድ በአሜሪካን ቢከፉም ‹‹የሆዳቸው በሆዳቸው›› ያደረጉ፤ ሩሲያና ቻይና በአሜሪካን ተግባር ጭራሽ ‹‹ደማቸው የሚፈላ››፤ ፊሊፒንስ ደግሞ የአሜሪካንን ተንኮለኛነት ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ ሳትጠቀም በቀጥታ የምትመሰክር አገር ሆና ትታያለች፡፡ አሁን ደግሞ በጆ. ባይደን አስተዳደር ሥር የምትገኘው አሜሪካን፤ ‹‹ወዳጅ የማስከፋት ሱሷን›› ተራውን በሀገራችን ኢትዮጵያ ላይ አድርጋው ትገኛለች!! ዘርዝረን ስለማንጨርሰው የአሜሪካን ‹‹ወዳጅ የማስከፋት ጣጣ›› እዚህ ላይ ቢበቃን ይሻላል!! ነገር ግን መርሳት የሌለብን! እነዚህ የተመለከትናቸው የአሜሪካን ስህተቶች በሙሉ ‹‹የልዕለ-ኃያልነት ክፍተቶች›› ላይ ተደማሪ ሆነው፤ አሜሪካንን ‹‹የልዕለ-ኃያልነት ጉዞ ማብቂያ›› ላይ የሚያደርሷት መሆናቸውን ነው!! እባካችሁ ይህን ጉዳይ በአገራችንና በአፍሪካ ላይ የተመሠረተ ‹‹ቀጭን መጠቅለያ›› እናብጅለት፡፡ እንሆ፤

ቀጭን መጠቅለያ!

አሜሪካን ይህን ያህል ደሀ አገርን የማስጨነቅ! ደሀ አገር ላይ የመደንፋት! ‹‹ክብር የሌለው ደረጃ›› የወረደችው፤ ‹‹በኛው ደሀዋ እናት-አገራችን›› ጉያ አድገው ጎርምሰውና ጎልምሰው፤ ሀሳብ በማፍለቅ፣ በምርምርና በፈጠራ አስተዋፅኦ አበርክተው፤ አሜሪካንን ቀዳሚ ባደረጓት ልጆቻችን በሰበሰበችው ጡንቻ አማካኝነት ነው፤ በመሆኑም እነዚህ ልጆቻችን ምንም እንኳ ዛሬ አሜሪካዊ ቢሆኑም ‹‹የቀዳሚት እናታቸውን ጉያ አይረሱም››፤ ‹‹ቀዳሚት እናታቸው በአሜሪካን እንድትጨነቅና እንዲደነፋባት አይፈቅዱም››፤ የሚል እምነት በመላው ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ አለ ብዬ አምናለሁ፤ ‹‹የበለፀገ አዕምሮ ባለቤት›› እና አሜሪካዊ በሆኑ ልጀቻችንም ልብ ውስጥ የሚኖረው ከኛ የተለየ አይሆንም!!

የአፍሪካ አመራሮች ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸውን ተጨባጭ ኩነቶች ‹‹ይመረምራሉ›› ወይም ‹‹እየመረመሩ ይገኛሉ›› ተብሎ ይታመናል፤ አመራሮቹ ከዚህ ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ወይም እየደረሱ ይገኛሉ ካልን፤ የሚያመላክተን ነገር አለ ማለት ነው! ያም የአፍሪካ አመራሮች ‹‹የሶቺ አፈር ይብላኝ›› የሚለውን መዝሙር ‹‹እየተለማመዱ ነው›› ወይም ‹‹ሊለማመዱ ነው›› የሚለውን ያመላክተናል!! የሩሲያ ፌዴሬሽኗን ሶቺ!! የአፍሪካ አመራሮቹ ከዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ አያቅማሙም ከሚያስብሉ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፤ የሩሲያ ፌዴሬሽን ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የሚሊተሪ ትብብርና ‹‹ተናቦ መሥራት›› ውጪ፤ በአፍሪካ ላይ ልትጭነው የምትችለው ይህ ነው የሚባል የተፈተነ ‹‹ዓለም አቀፍ ሥርዓት›› የሌላት በመሆኑ፤ አመራሮቹ ‹‹አፍሪካዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት ፍልስፍና›› ቀርፀው፤ በአገራቸውና በአፍሪካ ማራመድ የሚያስችላቸው በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ የ‹‹መደመር›› ፍልስፍናን አንርሳ! Clarity ይጎድለዋል ቢባልም!! ጤና ይስጥልኝ፡፡

ማስታወሻ፡-

የተከበራችሁ አንባቢያን፤ ከላይ በዝርዝር የተገለፁትን ጉዳዮች በሚገባ ከተረዳን፤ ‹‹የዓለም ልዕለ-ኃያልነትን›› ማረካከብ ይከብደናል ብዬ አላስብም፤ ስለዚህ በሚቀጥለው ጊዜ በማቀርበው ፅሁፍ አብረን የምናረካክብ ይሆናል፤ በፈጣሪ ፈቃድ!!

ሠላም ለኢትዮጵያ ሠላም ለአፍሪካ

ቴዎድሮስ ጌታቸው

/ደራሲና የፖለቲካ ተመልካች/

ድሬዳዋ

 

 

1 Comment

  1. The article sounds a good description about what the developed world and specifically the so called super powers have to do with the very competitive and of course unfair international politics and relations . This is the very tough game which desperately needs very critical , well-determined and smart way of playing wherever and whenever critical situations could arise . To do so, one has to make his or her own home in the right and productive manner . And the best way to do so is to help the people or citizens make their dream for a democratic system a realty .
    What has happened and continued to happen in our country has been and still is characterized by an extremely disturbing suffering of innocent people because of those politicians of the former EPRDF who renamed themselves as Prosperity .
    Most of us just talk about the the very national interests , position and decision of the super powers as if it is a new finding in world politics . We do not seriously and substantially argue and counter -argue about our own politicians who cynically if not stupidly try to make people believe that whenever their (the ruling elites’) ruthlessly dictatorial political power is threatened , and so does the national interest of the country . They never acknowledge let alone admit that the very reasons for the very deterioration of Ethiopia’s international place and role are nobody else but they themselves!
    What is sad is that in all these very disturbing situations , most of our intellectuals keep focusing on a very generalized and monotonous theoretical literature and rhetoric as if the situation in our country is not so vivid that reveals itself in the day to day lives of the people ! I hate to say but I have to say that as long us we do not try hard to go beyond this kind of talk about talk but not talk about how to walk , there won’t be any step of moving forward !

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.