እነ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ባሉበት የምርጫ ቅስቀሳ እንዲያደርጉ ፍርድ ቤቱን ጠየቁ

eskinder nega sentayehu chekol 768x517
eskinder nega sentayehu chekol 

በቅድስት ሙላቱ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ለመጪው ሀገራዊ ምርጫ ካሉበት እስር ቤት ሆነው የተለያዩ የምርጫ ቅስቀሳ ሂደቶችን እንዲያደርጉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ጠየቁ። አመራሮቹ ጥያቄውን ያቀረቡት በትላንትናው ዕለት የሰበር ሰሚ ችሎት በመጪው ምርጫ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ነው።

አራቱን የባልደራስ ፓርቲ አመራሮችን ወክለው ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ያቀረቡት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ከእስር ቤት ሆነው መግለጫዎች እንዲሰጡ እና የተለያዩ የቅስቀሳ ወረቀቶችን እንዲበትኑ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል። አቶ ስንታየሁ ጥያቄውን ያቀረቡት እርሳቸውን ጨምሮ የአምስት ተከሳሾችን መደበኛ የክርክር ሂደትን ለመመልከት ለተሰየመው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የጸረ-ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ነው።

ችሎቱ ዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው በእነ እስክንድር ነጋ ላይ የተቆጠሩ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን የአሰማም ሂደት በሚመለከት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ተመልክቶ ሂደቱን ለመወሰን ነበር። ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባለፈው ግንቦት 4 በነበረው ችሎት፤ ዐቃቤ ህግ በምስክሮቹ ላይ ይደርሳል የሚላቸውን ተጨባጭ የደህንነት ስጋቶች ለከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርቦ ጉዳዩ ክርክር እንዲደረግበት ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው፤ ዐቃቤ ህግ የደህንነት ስጋቶች የሚላቸውን በሬጅስትራር በኩል ሐሙስ ግንቦት 19 ቀን እንዲያቀርብ አዝዟል። ዐቃቤ ህግ ለፍርድ ቤቱ የሚያስገባው ማመልከቻ የሚሰጣቸው የተከሳሽ ጠበቆች፤ መልሳቸውን ለሰኞ ግንቦት 23 አዘጋጅተው ለችሎት እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ቀጠሮ በመሰጠቱ ቅር የተሰኙት የተከሳሽ ጠበቆች፤ በቀላል ነገሮች ቀጠሮ እየበዛ ተከሳሾች እየተጉላሉ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። “ስንጠብቅ የነበረው ክርክር እናደርጋለን ብለን ነበር” ሲሉም ተደምጠዋል። ነገር ግን ፍርድ ቤት ሁለቱም ወገኖች በትዕግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ ጉዳዩን በአጭር ጊዜ እንደሚቋጨው ለጠበቆች ቃል ገብቷል።

በዛሬው የችሎት ውሎ ላይ አራቱም የባልደራስ ተከሳሽ አመራሮች በአካል ተገኝተዋል። አመራሮቹን ወክለው የተናገሩት አቶ ስንታየሁ ቸኮል፤ ፍርድ ቤቱ ይሄን ሁሉ ጊዜ እነሱን ለማዳመጥ ለሚያደርገው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል። “እንደዚህ አይነት ባህል ሊለመድ ይገባል” ሲሉም የችሎቱን አካሄድ አሞካሽተዋል። አቶ ስንታየሁ በዚሁ ንግግራቸው ለመጪው ሀገራዊ ምርጫ በዕጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ በፍርድ ቤት እንደተፈቀደላቸው ጠቅሰው፤ ከእስር ቤት ሆነው “ከውስጥ ወደ ውጭ” በተወካዮቻቸው በኩል የምርጫ ቅስቀሳዎችን እንዲያደርጉ ችሎቱን ጠይቀዋል።

“ለብዙ ጊዜ የተገፋውን የአዲስ አበባ ህዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በመረጠው እንዲተዳደር የበኩላችሁን እንድትወጡ እጠይቃለሁ” ለሚለው የአቶ ስንታየሁ ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ምንም አይነት ምላሽም ሆነ አስተያየት ሳይሰጥ የዛሬው ችሎት ተጠናቅቋል። በዛሬው ችሎት ላይ በርከት ያሉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ደጋፊዎች ተገኝተው ሂደቱን ተከታትለዋል።

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

2 Comments

 1. ምርጫው ለአመት ይራዘም ፤ በቂ ጊዜ የለም ነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ ለማክያሄድ ።

 2. እስኬ! እንዴት አለፈ?
  ጉዝጉዞ አመጡልህ
  ሐምሌ አቦ እንዴት ነበር?
  ሙሉሙሉ ገባልህ
  ቡሄስ እንዲከበር?
  ሩፋኤል ዝናቡ ምን አለ ሲናገር
  ስለመጪው አመት ስለ እናት ሀገር?
  እንቁጣጣሽ ብሎ ዘበኞቹን አልፎ
  የመጣ ወፍ የለም?
  ደማቅ ሰማያዊ
  መስቀልን ሊያበስር ለሸገር ሊፋለም
  ገናስ በምን መልኩ
  በወህኒ አለፈ
  ከሰፊው ወህኒ ቤት ለእስኬ ምን ተጻፈ?
  የጥምቀት ከተራስ ምን ነበር ሁኔታው
  የጎሳ ታቦቶች ወረዱ በቦታው
  የሰማእታት ቀን ያዲሳባ እልቂት
  የሰላቶ ሽማ የፈትሉ ልቃቂት
  እንዴት ተዘከረ
  አድዋስ የድል በዐል ከቶ ተከበረ?
  ለማን ነጻነት ነው
  የሞቱት ተባለ
  ሕዝቡ ሰፊም ጠባብ ወህኒ ገብቶ እያለ?
  ጾሞቹ ሲገጥሙ
  የአማራ የእስላሙ
  ሀገር እየናዱ በካድሬ ጉባኤ
  እንዴት ሆኖ አለፈ የወህኒው ሱባኤ?
  ጾምም እንደ በዐል ድርብ አለው ለካ
  በምን መልክ አለፈ የወህኒው ፋሲካ?
  ከትህነግ የባሰው የኦህዴድ ምርጫ
  ድቤ እያስመታ ቃልቻ እያንጫጫ
  ከቃሊቲ ማዶ
  የክርፋት መዓዛው ውቅያኖስ ዐውዶ
  እስኬ እንዴት አለፈ
  ይህ አመት ይህ ዘመን
  በጠባቡ ወህኒ በታጋዮች ተመን
  ካድሬዎች ሲዘፍኑ ነጻነት እያሉ
  በተዋቡ ቃላት ሕዝቡን ሲያማልሉ
  ሌሊት ሌሊት ግና
  የካቴና አዋጅ በሰው ደም ሲጽፉ
  ይረብሻል አይደል ዛሬም በደጃፉ
  ፊትም የረበሸህ
  የከተማው ብረት ወጥመድ ሰንሰለቱ
  የቃሊቲን አጥር በጥሶ ጩኸቱ?
  የተዋደቅህለት ያ ወገንህ ደግሞ
  መብቱን እንዳይጠይቅ የያዘው ደራሞ
  ሳይለቀው ተቀድሞ
  የተገኘ እንደሆን
  ከብረቱ ቀንበር እግረ ሙቅ ካቴና
  በከፋ ፀፀት ነው
  ሰንሰለት ሆኖበት የሚያስረው ኅሊና።
  ወይስ ድብት ሰብሮ
  ድል ይነሳ ይሆን መብቱን አስከብሮ?
  የሚሉ ሃሳቦች
  ተኝተህ በማውጣት በማውረድ ስታድር
  እንዴት ከርመህ ይሆን ወንድሜ እስክንድር?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.