ለመንግሥቱ የምትመሰክርለት በዐቢይ ላይ የምትመሰክርበት መተከል (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ማስገንዘቢያ፤;- ይህ ጽሑፍ ራሳቸውም አድላውያን፣ ወንጀለኞች፣ ግፈኞችና ዘራፊዎች ስለሆኑ ምድራዊ ኃያላን ፍርድ ሳይሆን ስለ ሕዝባዊ፣ ታሪካዊና ሰማያዊ ፍርድ ነው የሚያትተው።

ሰዎች ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። የተከበረውን የሰው ልጅ ሕይወት ማጥፋት ግን እጅግ የከፋ ኃጢአትና ወንጀል ነው። የሰው ሕይወት ከጠፋ መመለስ የሚቻል ነገር አይደለምና። በተደጋጋሚ የስውን ሕይወት ያጠፋ “በላኤ ሰብእ” በመባል ይጠራል።

መተከል ተፈናቃዮች 4 ለመንግሥቱ የምትመሰክርለት በዐቢይ ላይ የምትመሰክርበት መተከል  (ከአሁንገና ዓለማየሁ)
መተከል ተፈናቃዮች 4

ዐቢይ አህመድና መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለቱም በላዔ ሰብ የሚያስብላቸው የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ/ያስቀጠፈ ሥራ እንደሠሩ እሙን ነው። በላዔ ሰብእ ወይም ስምዖን የተባለው ሰው በኦሮቶዶክስ አስተምህሮ ሰዎችን ሲበላ ኑሮ ለአንድ በውሃ ጥም ለተቸገረ ሰው ያደረገው የእፍኝ ውሃ ማጠጣት ተግባር ኃጢአቱ እንዲሠረይለት ምክንያት እንደሆነው ይገለጻል። በቀዝቃዛ ደም ጓዶቹን በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ያለርኅራኄ በመግደል፣ ያለፍርድ ባላሥልጣናትን በመጨፍጨፍ በሌላም በሌላም ኢትዮጵያን የተማረ ሰው ደሃ የሚያደርጉ ሥራዎችን በመሥራት ጨካኝ ወንጀሎችን የፈጸመው መንግሥቱ ኃይለማርያም እንደበላዔ ሰብእ ለድኅነት (ለመዳን) ምስክር የሚሆነው አንድ ሥራ ቢፈለግ መተከልን ለመጥቀስ ያለ ጥርጥር ይቻላል።

ይቺው ለመንግሥቱ መዳኛ የምትሆነው መተክል ለዐቢይ አህመድ ግን ሲዖል እንዲወርድ በብርቱ ከሚፋረዱት ምስክሮች ግንባር ቀደሟ ለመሆኗ አያጠራጥርም። ለምን?

መጀመሪያ መንግሥቱ ኃይለማርያምን እንይ። እግጅ አስከፊ በነበረው የሰባሰባት አመት ድርቅ፣ ሀገራችን ዙሪያዋን በእርስ በእርስ ጦርነት ተወጥራ ባለችበት የተሟላ አቅም እና ዝግጅት ባይደረግበትም፣ ብዙ የአፈፃፀም ጉድለት ቢኖረውም፣ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በተደጋጋሚ ድርቅ ከሚጠቁበት ተቀንሰው ወደ ዝናብ ጠገብ ባዶ ሥፍራዎች ተወስደው ዘራቸው እንዲተርፍ ትልቅ ዘመቻ አቅዶ ተግባራዊ አድርጓል። በዚህ ታላቅ ሥራ መንግሥቱ ከመቶ ሺህ በላይ ሕይወት ታድጓል። እነዚህ ገበሬዎች ከሞት መዳፍ ወጥተው ምርታቸውን በአይሱዙ የሚጭኑ፣ ሃያ ሰላሳና ከዚያም በላይ ከብቶችን የሚያረቡ አምራች ዜጎች ሆነው ለማየት ከስደትም ሆኖ መታደሉ ምናልባትም ለመንግሥቱ መተከል “የእፍኝ ውሃ ጽድቁ” ሆናለታለች ለማለት የሚያስደፍር ተጨማሪ ምክንያት ነው።

መተከል ተፈናቃዮች 3 ለመንግሥቱ የምትመሰክርለት በዐቢይ ላይ የምትመሰክርበት መተከል  (ከአሁንገና ዓለማየሁ)
መተከል ተፈናቃዮች 3

ቀጥለን ዐቢይ አህመድን እንይ። ሥልጣን ከያዘበት ማግሥት አንስቶ በመተከል የዛሬ ሠላሳ አመት የመጡትን ዜጎች ብቻ ሳይሆን በዚያው ቦታ ነባር የነበሩትን ሳይቀር ለዘር ተኮር ጭፍጨፋ የሚያጋልጥ አስተዳደርን በመደገፍ የጭካኔ ጥግ የተባለውን ሁሉ በተለይ በአማራና አገው ተወላጆች ላይ እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል። ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ የሚገመት ሕዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል። ከአንድ ሺህ የማያንሱ ዜጎች ተገድለዋል፣ ተቃጥለዋል፣ ተበልተዋል፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈዋል። ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ ሙታን በጅምላ ተቀብረዋል። አካል ተጠራቅሞ፣ በግሬደር ተዝቆ በዶዘር የተቀበረበትን ሪኮርድ ሰባሪ ውርደት መተክል እንድታስመዘግብ የተደረገው አቢይ አህመድ መተከል ደርሶ በተመለሰ ማግሥት ነበር። ስድስትና ስምንት ሰው ካንድ ቤት ታርዶ፣አዝመራና ንብረታቸው በወደመባት መተከል ዐቢይ በጭፍጨፋው መሳተፋቸውን ያመኑ ገዳዮችን ተሃድሶ እየሰጠ በመንግሥት መዋቅር በመሾምና ቤትና መሬት በመሸለም በቁስል ላይ አሲድ ሲነሰንስ ማየት ያማል። ወለጋ ደምቢ ዶሎ ላይ የኦሮሞ ባለሥልጣን ገድሏል ተብሎ ያለፍርድ ባደባባይ የተረሸነውን የአማኑኤል ወንድሙን እጣ ከነዚህኞቹ እጣ ጋር በማስተያየት የመተከል አሳራጅ ማን መሆኑን ለማወቅ አያዳግትም።

መተከል በአውሮፕላን ተዘርቶ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች የሚታጨድበት የትንሹና የትልቁ በለስ የሚባሉ የግድብና የመስኖ ልማቶችን መንግሥቱ ኃይለማርያም የዘረጋባት ስትሆን ዐቢይ አህመድ በኦህዴድ ጄኔራሎች ኮማንድ ፖስት የሰው ሬሳ የሚታጨድበት፣ አዝመራ ተቃጥሎ የገበሬ ከብቶች ወደ ሱዳን የሚነዱበት “ልማትን” ነው የዘረጋላት።

በመተከል ከላይ ከተጠቀሱት የትግራይ እና የወሎ ገበሬዎች በተጨማሪ ከከምባታ፣ ከወላይታ እና ሌሎችም አካባቢዎች የመጡ ሰዎች ከነባሩ የአማራ፣ የአገው፣ የኦሮሞ፣ የሽናሻ እና የጉምዝ ሕዝብ ጋር በልማት ተጣምረው የሚኖርበትን መርሐ ግብር ተግባራዊ አድርጓል። መንግሥቱ ኃይለማርያም። እንኳን የሌላ አካባቢ ሰው መጥቶ ሊኖርባት መተከል ከነባሩ የአማራና ከአገው ዝርያ የምትጸዳበትን የሽብር፣ የጭፍጨፋና የማፈናቀል ተግባር አመቻችቷል። ዐቢይ አህመድ።

ቤት ሠርቶ ያሰፈረ /\ ቤት አቃጥሎ ያበረረ

የተራበን ያጠገበ /\ የጠገበን ያስራበ

የጎሰቆለን የፈወሰ /\ ደህነኛውን ያጎሰቆለ

ንጹሐን ደሃ ገበሬዎችን ከድርቅ ለመታደግ ያስፈረ፣ ልማትን የዘረጋ በአንድ በኩል / ንጹሐን ደሃ ገበሬዎችን በጅምላ ያስፈጀ፣ ያፈናቀለ፣ ልማታቸውን ያስወደመ በሌላ በኩል  –  ይህ ነው በላኤ ሰብእ በችሎት ሲቆም የሚቀርበው የመተከል ዶሴ ።

Metekel ለመንግሥቱ የምትመሰክርለት በዐቢይ ላይ የምትመሰክርበት መተከል  (ከአሁንገና ዓለማየሁ)
metekel

እነዚህ መሪዎች የጉዳዩ ባለቤቶች መሆናቸውን ለሚጠራጠር መንግሥቱ የድርቁን ዘመን ሰፈራ በስኬት ያስፈጸሙትን መሾም መሽለሙን የዐቢይም መንግሥት በዘር ጭፍጨፋና ጽዳት የተሳተፉትን ሥልጣን፣ የከተማ ቤትና የእርሻ ቦታ መሸለሙን በማየት ማረጋገጥ ይችላል።

እንደብዙ ሰዎች ይህ ጸሐፊም መንግሥቱ ኃይለማርያምን በብርቱ የሚኮንን “ያ ትውልድ” ላስከተለው የሀገር ውድቀትም መንግሥቱ ኃይለማርያምን  አንዱና ዋነኛው ተጠያቂ አድርጎ የሚያየው ሲሆን ከላይ የቀረበው ንጽጽር መተከልን ብቻ ወስዶ የቀረበ ንጽጽር መሆኑ ይታወቅ።

ይቅርታ። አንቱታ ተገቢ ባሕላችንም ቢሆን የዚህ ጽሑፍ ትኩረት የሆነውን የበላዔ ሰብእ ገጽታ በአንቱታ ለመጻፍ ስለማይመች ነው መሪዎቹ አንተ በሚል የተጠቀሱት።

ለሌላ ንጽጽር “ኮሎኔሉና ኮሎኔሉ” በሚለው ጽሑፍ እንገናኝ።

2 Comments

  1. Nice observation dear Ahoon. I was a university student at that time and was forced to join the campaign in Metekel. We students constructed clumsy cottage houses for resetlers who came from different drought stricken parts of the nation especially Tigray and Wollo.
    What strikes me now is that – why does this Abiy, the vampire, kill his own fellows since their presence there is not their fault, if at all it is fault? This question has been one major headache as of the time the problem begun after the vampire ascended to his nightmarish political seat.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.