እነ እስክንድር ነጋ ለመጪው ምርጫ በእጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ የሰበር ሰሚ ችሎት ወሰነ

Eskinderበቅድስት ሙላቱ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ሰበር ሰሚ ችሎት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደመሌ ለፓርቲው በእጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ ውሳኔ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ዛሬ ሰኞ ግንቦት 16 በነበረው የችሎት ውሎው ነው።

ችሎቱ ውሳኔውን የሰጠው የባልደራስ ፓርቲ አመራሮችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተላለፈውን እና በስተኋላ ላይም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸደቀውን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ነው። የባልደራስ ፓርቲ እነ አቶ እስክንድር ነጋ በመጪው ምርጫ በእጩነት እንዲመዘገቡለት ምርጫ ቦርድን ቢጠይቅም፤ አመራሮቹ በህግ ከለላ ስር ስለሚገኙ ለምርጫ እጩነት መመዝገብ አይችሉም በማለት ቦርዱ ጥያቄውን ሳይቀበለው መቅረቱ ይታወሳል።

እነ እስክንድር ነጋ ለመጪው ምርጫ በእጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ የሰበር ሰሚ ችሎት ወሰነ 1

የምርጫ ቦርድን ውሳኔ የተቃወመው ባልደራስ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስዶት ነበር። ጉዳዩን የተመለከተው የከፍተኛው ፍርድ ቤት የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በማጽደቁ፤ ባልደራስ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤት ብሏል።

የባልደራስን አቤቱታ በሚያዝያ 29፤ 2013 የተቀበለው የሰበር ሰሚ ችሎት፤ ፓርቲው ያቀረበውን መከራከሪያ መርምሯል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ላይ ማንኛውም በህግ እና በፍርድ ውሳኔ የመምረጥ መብቱ ያልተገፈፈ ሰው በዕጩነት መቅረብ እንደሚችል መደንገጉን ባልደራስ በአቤቱታው አንስቷል። ድንጋጌው ይህን ቢልም ምርጫ ቦርድ ግን በትርጉም አሳብቦ አዲስ ድንጋጌ በአዋጁ ውስጥ ማካተቱ ተገቢ አይደለም ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የከፍተኛው ፍርድ ቤት እና የምርጫ ቦርድ ውሳኔዎች፤ የተከሰሱ ሰዎች በፍርድ ሂደት ውስጥ ባሉበት ጊዜ ንጹህ ሆኖ የመገመት መብታቸውን (presumption of innocence) በጽኑ የሚጎዳ ነው ሲል ፓርቲው በአቤቱታው ጠቅሷል። ስለሆነም ምርጫ ቦርድ በአራቱ የባልደራስ አባላት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ እና የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአብላጫ ድምፅ የሰጠው ውሳኔ ተሽሮ አባላቱ በዕጩነት እንዲመዘገቡ በማለት ጠይቆ ነበር።

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የእጩዎችን ምዝገባ በሚመለከት የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመሆኑ ፓርቲው ይግባኝ የማቅረብ መብት የለውም በማለት ተሟግቷል። በእስር ቤት የሚገኙ እና የዋስትና መብታቸውን የተከለከሉ የፓርቲው አባላት በምርጫ ሂደቱ በነጻነት የመንቀሳቀስ እና ከመራጩ ህዝብ ጋር መገናኘት እንደማይችሉ አገናዝቦ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የወሰነው ውሳኔም ተገቢ ነው ብሏል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የዘንድሮው ምርጫ የችግራችን መፍቻ ሁሉ ቁልፍ ነው።" ጠ/ሚ አብይ አህመድ - ከፊልጶስ ወርቅነህ

የፓርቲው አባላት “በእጩነት ተመዝግበው ቢመረጡ በእስር ቤት እያሉ የመረጣቸውን ህዝብ ማገልገል አይችሉም” መባሉ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጋፋ ውሳኔ አይደለም ሲል ምርጫ ቦርድ በምላሹ ላይ ተከራክሯል። በሌላ በኩል ደግሞ የባልደራስ ፓርቲ፤ አራት አባላቱ በእጩነት እንዲመዘገቡ በጠየቀባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ፤ ሌሎች እጩዎችን ያስመዘገበ በመሆኑ ጥያቄው አግባብ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

አምስት የሰበር ሰሚ ዳኞች የተሰየሙበት የዛሬው ችሎት፤ በምርጫ አዋጁም ሆነ በህገ መንግስቱ ላይ የዜጎች የመምረጥ ወይም የመመረጥ መብት የሚነፈገው በህግ ወይም በፍርድ ቤት ውሳኔ  ካገኘ በኋላ ነው ብሏል። ስለሆነም በተያዘው ጉዳይ የፓርቲው አመራሮች በህግ የተላለፈባቸው ውሳኔ ባለመኖሩ በእጩነት መመዝገብ ይችላሉ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል። አጠቃላይ የምርጫ አላማ የዜጎችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ሆኖ ሳለ፤ በህግ ግልጽ ተደንግጎ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ምርጫ ቦርድ የፓርቲው አባላት በእጩነት መወዳደር አይችሉም ማለቱ የህግ መሠረት የለውም በማለትም ፍርድ ቤቱ የቦርዱን ውሳኔ ውድቅ አድርጎታል።

እነ እስክንድር ነጋ ለመጪው ምርጫ በእጩነት ተመዝግበው መወዳደር እንደሚችሉ የሰበር ሰሚ ችሎት ወሰነ 2

የባልደራስ ፓርቲ አመራሮች አሁን ለእጩነት ለመመዝገብ በጠየቁበት የምርጫ ክልሎች ላይ ሌሎች ተተኪ ተወዳዳሪዎችን ማስመዝገባቸውን በመጥቀስ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ምላሽም እንዲሁ በሰበር ሰሚ ችሎቱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። ችሎቱ ለዚህ በምክንያትነት የጠቀሰው፤ ምርጫ ቦርድ ተተኪ እጩዎች ያላቸውን በዝርዝርና በማስረጃ አስደግፎ አለማቅረቡን ነው።

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞከራሲ ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በአካል ቀርበው ችሎቱን ተከታትለዋል።

 

(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

2 Comments

  1. Why are you crying for this man, when thousands are dying in ethiopia including in Amhara !
    I dnot like these kind of article and i stand only for people with no distinction of their religion, ethnic and gender etc

  2. ለቅድስት ሙላቱ ስንት ኢትዮጵያን ለማያውቀው ህብረተሰቦች መጻፍና ማሳወቅ እያለ እና እየተቻለ አሁን ይህንን ዝብዝዝንኬ እና ፍሬ ከርስኪ ጽፉፍ ብለሽ ታቀርቢያለሺን? ወይስ ባልደራስ የሚባለው እዲመረጥልሽ ነውን?ወይንስ ከተመረጠ ትንሺ ትርፍራፊ አገኛለሁ ብለሺ በማመን? ይልቁንስ ይህንን የመሰለ መግቢያ እና ማሰሪያ የሌለው ለመጻፍ የምታባክኝውን ጊዜ ለሌላ ተግባር ተጠቀሚበት። በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ክብሪት መጫር እና እሳት ማንደዱ ቆሞ፤ቀደም ያለው ውዝግብ ቀርቶ የህብረት እና የአንድነት የሚነገርበት እና የሚሰበክበት ወቅት ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.