/

የኢትዮጵያ ዘመን ኣቈጣጠር – በዶ/ር ኣበራ ሞላ

የኢትዮጵያ ኮምፕዩተሮችና ሶፍትዌር

The Ethiopian Calendar

By Dr. Aberra Molla

Ethiopian Computers & Software

በመጀመሪያ እንኳን ለኣዲሱ ዕሥራ ምዕት ዋዜማ ዓመት በሰላም ያደረሰን እላለሁ። ስለ ዘመን ኣቈጣጠርም እንድናገርም በመጋ፠በዜና በመካከላችሁ በመገኘቴም ደስተኛ ነኝ።

ፈረንጅ ሞኙ ሚለንየምን በየሺህ ዓመቱ ያከብራል። ብልጦቹ ኢትዮጵያውያን ግን ይኸው በየሰባቱ ዓመት ይደሰታሉ¡ በሦስተኛው ሺህ ዓመት (Millennium) ሦስት ጊዜ የምናከብርበትን መፈለግ ኣለብን¡

በቅድሚያ ስለ ዘመን ኣቈጣጠር ወይም ቀለንጦስ እንድጽፍ ለምን እንደጀመርኩ በትንሹ ላሰማችሁ። ግዕዝን ኮምፕዩተራይዝ ሳደርግ ከዛሬ ሃያ ዓመታት በፊት ከሠራኋቸው ኣንዱ የግዕዝ ዜሮ ወይም ኣልቦ ኣኃዝ ነበር። ዜሮ ወይም ኣልቦ ያስፈለገው ለኮምፕዩተሩ ኣሠራር እንጂ ለዘመን ቈጠራ ኣይደለም። (ቢሆኖም ዜሮን ባለማወቅ የዜሮን ዓመት ሳንሳት ኣልቀረንም።) በተጨሪም በግዕዝ የሚሠራ ኮምፕዩተር የግዕዝ መቊጠሪያ ስለሚያስፈልገው የግዕዝ ዜሮ ጠቃሚ ነው።

የቀን መቍጠሪያችን የዩልዮስ ወይም ጁልያን (Julian) መሆኑንና ወደኋላም የቀረነው የእየሱስ ክርስቶስን (Jesus Christ) መወለድ ኢትዮጵያውያን የሰሙት ከሰባት ዓመታት በኋላ ስለሆነ በሰባት ዓመት ግድም ወደኋላ ቀርተናል እየተባልኩ ማደጌን ኣስታውሳለሁ። ታሪኩ ስላላጠረቃኝ እነሆ ጥቂት መረጃዎችን ኣንብቤ ትክክል የመሰለኝን ኣቅርቤያለሁ። እንዲህም ሆኖ ፈረንጆቹ የዩልዮሱን ትተው ወደ ጎርጎርዮስ (Gregorian) ካላንደር ሲዞሩ ኢትዮጵያውያን ሰባት ዓመታት ያጎደለውን የዩልዮስ ካለንደር ይዘው ተቀምጠዋል በማለት ትክክል ያልሆነ ታሪክ የጻፉም ኣሉ። ኢንተርኔት ላይም ስለ ቀን መቍጠርያዎች ሳነብ ስለ ሌሎቹ ብዙ ሲኖር እኛ እንደሌለንና ስለ እኛው የተጻፉ ከጥቂት ዓረፍት ነገሮች በስተቀር ምንም ስላልነበረ የማቀርብላችሁ ኣንብቤ የጻፍኩትን ስለሆነ የተሻለ የሚያውቁ ሊያሻሽሉት ይችላሉ። ስለዚህም ታሪክ እነ ዶ/ር ጌታቸውና ሌሎችም ስለጠቃቀሱና ዕውቀቴም መጠነኛ ስለሆነ ገለጻዬ ኣጭር ነው።

ስለ ኢትዮጵያ ካለንደር ለመጀመሪያ ጊዜ መጻፍ የጀመርኩትና ኢንተርኔት ላይ በእንግሊዝኛ ያቀረብኩት በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. ነበር። ከዚያም ወዲህ እየተሻሻለና እየተስፋፋ ያለው The Ethiopic Calendar በሚል ርዕስ ያለው የእንግሊዝኛ ጽሑፌ ኢትዮፒክ.ኮም (Ethiopic.com) ድረገጼና በየቦታው ስላለ ማንበብ ይቻላል።

የዘመን ቈጠራ ጉዳይ ኣስቸጋሪ ነገር ነው። ምክንያቱም ቈጠራው በኣንድ በኩል በእምነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ያንን ማናጋትና የሌላውን እምነት መዳፈር ትክክል ኣይደለም። በእምነት ላይ የተመረኰዘ ነገር ላይ ብዙ ባንመራመር ሳይሻል ኣይቀርም። በኣንድ ጎኑ ደግሞ በታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው። ኣንዱ እምነቱን  ኣንዱ ታሪኩን ሲከተል በኢትዮጵያውያንና ኤውሮጳውያን መካከል የኣቈጣጠር ልዩነት ተፈጥሯል ይባላል። በሌላ በኩል መረጃ ያለው ሳይንስ ነው። ይኸን ሁሉ ኣካክሶ መጓዝ ቀላል ስላልሆነ ሁለት ሰዎች በቀጠሮ መግባባት እስከቻሉ መጨነቅ የለብንም የሚሉም ኣሉ።

ኢትዮጵያ የተለያዩ የዘመን መቍጠሪያዎች ሳይኖሯት ኣልቀረም። የሄኖክ (Enoch) ዘመን መቍጠርያ ኣለ። የኦሮሞ ነገዳችን መቍጠሪያና የቤተ እሥራኤልና እስላሞች ወገኖቻችን ካለንደሮች ኣሉ። ከእነዚህ የጥንቱና የመጀመሪያው የሄኖክ የዘመን መቍጠሪያ ሳይሆን ኣይቀርም። የሄኖክ መንፈሳዊ መጻሕፍት ሙሉውን ያሉትና የተገኙት ኢትዮጵያ ብቻ (እና በግዕዝ ቋንቋ) ነው ይባላል። ሄኖክ (ከክርስቶስ ልደት በፊት 3350 ዓመት መሆኑ የሚታመንበትና) መላዕክት ኣሳዩኝ ብሎ ያቀረበው የቀን መቍጠሪያ መጽሓፈ ሄኖክ ውስጥ ኣለ። የሄኖክ ዓመት 364 ቀናት ነበሩት። የኢትዮጵያ መጽሓፍ ቅዱስ ውስጥ መጽሓፈ ሄኖክ ምዕራፍ ፲፰ ቍጥር ፲፩ ስለ 364 የዓመት ቀናት ይናገራል።

ሌላው በሰፊው የታወቀው የዘመን መቍጠራያችን በኣሁኑ ዘመን የምንጥጠቀምበት የኢትዮጵያ የዘመን መቍጠሪያ ነው። (ኣንዳንድ ሊቃውንት ይኸንን የዘመን መቍጠሪያ ከክርስትና ኃይማኖት ጋር ከግብጾች ሳንወስድ ኣልቀረም የሚሉ ቢኖሩም ኢትዮጵያና ግብጽ ከነበራቸው መቀራረብ ሌላ የእራሳችን ነው የሚሉም ኣሉ።) በዚህ ቀለንጦስ መሠረት እግዚኣብሔር ኣዳምንና ሔዋንን ከፈጠረ ከ5500 ዓመታት በኋላ እየሱስ ተወለደ ይላል የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ኃይማኖታችን። በዚህም የተነሳ 5500 እና 1999 ዓመታት ሲደመሩ የ7499 ዓመተ ዓለም ስምንተኛው ሺህ መሃል ነን። የግብጾች ዓመትም ልክ እንደ ኢትዮጵያው የሚጀምረው መስከረም ፩ ቀን ስለሆነ ዓመቱ 365 ቀናት ከስድስት ሰዓታት የሆነው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ239 ዓመታት በፊት ነው ይባላል። ስድስቶቹ ስዓታት በእየኣራት ዓመታት ተደምረው የጳጉሜ ስድስተኛው ቀን ይሆናሉ።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያና የግብጽ ካለንደሮች ኣንድ ዓይነት ቢሆኑም በሮማውያን ገዥዎች እጅ የደረሰባቸውን ግፍ ለማስታወስ ግብጻውያን ክርስቲያኖች የዘመን መቍጠሪያውን ትተው ኣንድ ብለው በ276 ዓ.ም. መቈጠር ስለጀመሩ የእነሱ ዘመን ኣሁን ከ1999 ላይ 276 ሲቀነስ 1723 ዓመተ ሰማዕታት መሆኑ ነው። ኢትዮጵያውያን ክርስቶስ ተወለደበት የሚባለውን ዓመተ ምሕረትም እየቆጠሩ ያልተለወጠውን ቀለንጦሳቸውን እንደያዙ ቆይተዋል።

ሮማውያን ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ 753 ዓመት ግድም በሮማ ከተማ መቈርቈር የጀመረውን የዘመን መቍጠሪያቸውን ትተው ዓመቱ 365.25 ቀናት የሆነውን ካለንደር ከግብጽ ወስደዋል። በ325 ዓ.ም. የኒቅያ ጉባዔ ክርስቲያኖች በመተባበር ከወሰኗቸው መካከል የፋሲካ በዓል ዕለት ኣወሳሰንና ኣንዳንድ በዓላትና ኣጽዋማትን ይመለከታል። ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ በሰፊው ስለዚህ በ“ባሕረ ሓሳብ” መጽሓፋቸው ኣቅርበዋል።

በ525 ዓ.ም. ዲኖስዮስ ኤክሲጅዮስ (Dionysius Exiguus) የሚባል የሩስያ መነኩሴ የሮማው ጳጳስ መልዕክተኛም በመሆን የፋሲካን በዓል ኣወሳሰን ከግብጻውያን እንዲማር ተልኮ ነበር። እንደሚመስለኝና ኣንዳንድ ፀሓፊዎችም እንደሚሉት ኤክሲጅዮስ በ525 ዓ.ም. 532 ዓመትን ሳይጠቀም ኣልቀረም። ዲኖስየስ ኣኖ ዶሚኒ (Anno Domini ወይም ኤ.ዲ.) የሚባለውን ካለንደር በጃንዋሪ 1 ፣ 1 ኤ.ዲ. እንዲጀምር በ525 ቢወስንም በኋላም ፀሓፊዎች ጁልያን (ዩልዮስ) ካለንደር ያሉት የግብጾችንና የኢትዮጵያን ዘመን መቈጠርያዎች ስለማይመለከት እራሱን የቻለ ካለንደር ሆኖ ቆይቷል። ኤክሲጅዮስ ወደኋላ በመቍጠር ሲጀምር ይመስለኛል ኣዲሱ ካለንደር ላይ ሰባት ዓመታት ግድም የጨመረበት። የዓመታቱም ቍጥር ከግብጽ ይልቅ ወደ ኢትዮጵያ የቀረበ ነው። ጨረቃ መሬትን ስትዞርና መሬት ፀሓይን ስትዞር የሚወስዱት 532 ዓመታት (19 X 28) ተደጋጋሚ ናቸው።

ግብጾች ሲቀንሱ ኤውሮጳውያን የዩልዮስን ዓመታት ሲጨምሩ ኢትዮጵያውያን የዘመን መቈጠሪያቸውን እንደጠበቁ ቆይተዋል። በ1582 ኤ.ዲ. የሮማው ጳጳስ ጎርጎርዮስ ዩልዮስ ካለንደር እንዲሻሻል ከኦክቶበር 5 እስከ 14 ያሉትን ቀናት በመዝለል ኣዲስ ካለንደርና የሠግር (Leap Year) ደንብ ኣወጣ። በዚህም የተነሳ ዛሬ በዩልዮስና በኣዲሱ ጎሮጎርዮስ (Gregorian) ካለንደር መካከል ያለው ልዩነት ወደ 13 ቀናት ከፍ ሲል ሁለቱም ከኢትዮጵያ ዘመን ኣቈጣጠር የሚለዩት በሰባት ዓመታት ግድም ነው። የኢትዮጵያ ካለንደር ዩልዮስ ወይም ጎርጎርዮስ ኣይደለም። በእነዚህና ሌሎችም ልዩነቶች የተነሳ ይህ ሚለንየም የግብጽም ኣይደለም። ይህ ሚለንየም የዩልዮስም ኣይደለም። ይህ ሚለንየም የኢትዮጵያውያን ነው።

ዛሬ በኢትዮጵያ ዘመን ኣቈጣጠር ጳጉሜ ፫ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. ነው። ይሀው ቀን በዩልዮስ ዘመን ኣቈጣጠር ኦገስት 26, 2007 (August 26, 2007) ሲሆን በግብጾች ኤልየስ ፫ 1723 ዓመተ ሰማዕታት፣ በጎርጎርዮስ ደግሞ ሰፕቴምበር 8, 2007 (September 8, 2007) ነው። የሦስተኛው ሺህ ዓመት (ኣዲሱ የኢትዮጵያ ሚለንየም) የሚጀምረው መስከረም ፩ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. ነው።

የኢትዮጵያና የዩልዮስ ካለንደሮች የሚለዩት በሰባት ዓመታት ግድም ቢሆንም የማን ትክክል እንደሆነ ባይታውቅም ብዙዎቹ ተመራማሪዎች እንደሚሉት እየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ሌሎቹ ተወለደ ከሚሉት ሰባት ዓመታት ግድም ቀደም ብሎ ነው ስለሚባል የኢትዮጵያውያኑ ወደ ትክክለኛው የቀረበ ሳይሆን ኣይቀርም ነው የሚባለው። ያም ሆነ ይህ ታሪኩም ይሁን ሳይንሱ ትክክልም ባይሆን ምንም ኣይደለም። (እንዲህም ሆኖ የእኛን ወደኋላ ከጎተትን የእናንተንም ጎትቱ ብለው ኣዳምና ሄዋን የተፈጠሩት ከክርስቶስ ልደት በፊት በኤውሮጳውያን 5493 ነው ስንል ሌሎቹ የእኛውን ከ5500 ወደ 5507 ግድም መግፋት የሚፈልጉም ኣሉ።)

ከእዚህ ሌላ ኤውሮጳውያን የዩልዮስን ኣቈጣጠር በማሻሻል ወደ ጎርጎርዮስ ኣቈጣጠር ስላሻሻሉ እኛም የኢትዮጵያውን ጥለን የጎርጎርዮሱን እንድንወስድ በየጊዜው ከመገፋፋት ኣላቋረጡም። በግራኝ ወረራ ዘመን ሊረዱን የመጡ ፖርቱጋሎች ኣፄ ሱስንዮስንና ደጋፊዎቻቸውን ወደ ካቶሊክ ኃይማኖት ካስለወጡ በኋላ ካለንደሩንም ወደ ጎርጎርዮስ ካለንደር ለማስቀየር ሞክረው ኣልተሳካላቸውም። ወደ ጎሮጎርዮስ ኣቈጣጠር እንድንቀይር የሚያቀርቡት ዋናው ምክንያት ዓለም ፀሓይን ኣንዴ የምትዞረው በ325.25 ቀናት ሳይሆን በ325.2422 ሆኖ ሳለ የሠግር ቍጥሮችን በየ400 ዓመታት 100 ከማድረግ ወደ 97 ዝቅ በማድረግ ኣሻሻልን ባዮች ናቸው። እዚህ ስሌት ላይ የደረሱት ዓለም የጀመረችበትን ኣንድ ሥፍራ ብንወስድ ፀሓይን ዞራ ተመልሳ እዚያ ቦታ የምትደርሰው በ365 ቀናት 5 ሰዓቶች 48 ደቂቃዎችና ከ46 ሰከንዶች ስለሆነ የጥንት ኢትዮጵያውያንና ግብጻውያን 365 ቀናት ከ6 ሰዓቶች በማድረግ ስተዋል ነው የሚሉት። የተጨመሩት ትርፎቹ 11 ደቂቃዎችና 14 ሰከንዶች ከ325 እስከ 1582 ባሉት ዓመታት ተደምረው 10 ቀናት ስለሆኑና ሮማውያን ስለቀነሷቸው ነው። ከዩልዮስ ካለንደር ላይ 10 ቀናት ከቆረጡ በኋላ ኣዲሱን ካላንደር ጎርጎርዮስ ኣሉት። ስሕተቶቹም ከዚያ ጊዜ በኋላ እንዳይቀጥሉ በ400 በሚከፈሉ መቶኛ ዓመታት እንጂ በየምዕት ዓመታት ሠግር እንዳይሆን ወሰኑ። ይህ በየ400 ዓመታት ውስጥ ያሉትን የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖቹን ዓይነቱን 100 ሠግሮች ወደ 97 ዝቅ በማድረግ የዩልዮሱን በመተው የጎርጎርዮስን ኣዲስ ካለንደር በ1582 ኤ.ዲ. ኣስጀመረ። እነዚህን የቀን ቈርጥራጮች ለማግኘት በመጨረሻው ቀን ያሉትን ሰዓታት ወደ ሰከንዶች ቀይሮ በቀን ውስጥ ባሉት ሰከንዶች በማካፈል 0.2425 ቀን ማግኘት ይቻላል። ሌላው ዘዴ ዘጠና ሰባትን ሠግሮች በ400 ዓመታት ማካፈል ነው። ሮማውያን የቀየሩት የዩልዮስን እንጂ የኢትዮጵያን ቀለንጦስ ስላልሆነና ኢትዮጵያውያንም ስላልተስማሙበት የዓመቱም ቍጥሩ ጭምር ከድሮውኑ የተለየ ስለሆነ ለውጡ የኢትዮጵያን ኣቈጣጠር ኣልተመለከተም። ዛሬ በዩልዮስና በጎርጎርዮስ ካለንደሮች መካከል ያለው ልዩነት ወደ 13 ቀናት ከፍ ቢልም ዓመታቸውም የሁለቱም 2008 ኤ.ዲ. ነው። እንዲህም ሆኖ በሳይንሱ በታወቀው በ365.2422 እና በጎርጎርዮሱ 365.2425 የዓመት ቀናት መካከልም ልዩነት ስላለ የጎርጎርዮስም ካለንደር ቢሆን ትክክል ኣይደለም።

እዚህ ላይ ወደኋላ ልመለስና የሄኖክን ባለ 364 ቀናት ዓመት ወስደን በየ293 ዓመታት የኣንድ ዓመትን ሠግር ብንበትን ከ400 ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተሻለ ቀን መቍጠሪያ ይወጣዋል። የሄኖክን 107016 ቀናት በ293 ዓመታት ብናካፍል የዓመት 365.2423 ቀናት ከጎርጎርዮሱ የተሻለ ነው። ዓላማዬ ይቅር ኣይቅር ለማለት ሳይሆን ሳይንሱንም ለማቅረብ ነው።

ኢትዮጵያውያን የተለያዩ በዓላት የዋሉባቸውን ቀናት ወደኋላም ተመልሰው የሚቀምሩበትና 5500 ዓመተ ዓለምን (ዓ.ዓ.) ጭምር ለሒሳቡ የሚጠቀሙባችው ዘዴዎች ኣሏቸው። ለምሳሌ ያህል በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. መስከረም ፩ ቀን በምን ዕለት እንደዋለ ለማወቅ የሚያስፈልገው 7494 ዓ.ዓ. ላይ 1873 ደምሮ በ7 ኣካፍሎ ቀሪው ኣንድ ከሆነ ውጤቱ ማክሰኞ መሆኑ ነው። 1873 የ5500 እና 1994 ድምርን በ4 በማካፈል ነው የተገኘው። በዚህ ስሌት የ፳፻፩ ቀሪ ፫ በመሆኑ እንቁጣጣሽ ሓሙስ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዕለት 12 የቀንና 12 የሌሊት ሰዓቶች ኣሉት። የኤውሮጳውያን ዕለት ኣኩለሌሊት ስለሚጀምር የእነሱን ሰዓት ለማስላት ከግዕዙ 6 ሰዓታት መቀነስ (ወይም መጨመር) ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከኣልቦ ሎንጂቱድ (Longitude) ምሥራቅ 45 ዲግሪ ላይ ስለምትገኝ ሰዓትዋ ከእንግሊዞቹ በሦስት ይቀድማል።

 


ዋቤ

1. ዓሥራት ገብረ ማርያም እና ገብረ ሕይወት መሓሪ፦ የዘመን ኣቈጣጠር፣ ኣርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፣ ኣዲስ ኣበባ፣ ፲፱፻፹፯ ዓ.ም.
2. በቀለ ሞላ (፲፱፻፺፫) የኢትዮጵያ ቀን መቍጠሪያ ፲፱፻፺፬ ዓ.ም. http://www.fettan.com/Ethcalendar/Ethcalendar94.htm

3. ኣበራ ሞላ (፲፱፻፺፫) ስመ ኣኃዝ http://www.ethiopic.com/ethiopic/numbers.htm

4. መጽሓፈ ግጻዌ ትንሳዔ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፣ ኣዲስ ኣበባ፣ ፲፱፻፺ ዓ.ም.
5. ጌታቸው ኃይሌ፣ ባሕረ ሓሳብ፣ ኮሌጅቪል (ሚኒሶታ) ፲፱፻፺፫ ዓ.ም.

6. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሓዶ ቤተክርስቲያን እምነት፣ ሥርዓተ ኣምልኮና የውጭ ግንኙነት፣ ትንሳዔ ማተሚያ ድርጅት፣ ኣዲስ ኣበባ፣ ፲፱፻፹፰ ዓ.ም.

7. Aberra Molla (2002), The Ethiopic Calendar, http://www.ethiopic.com/calendar/ethiopic.htm

8. Jesus (2007), http://en.wikipedia.org/wiki/Jesus

9. Dionysius Exiguus (2007), http://en.wikipedia.org/wiki/Dionysius_Exiguus

10. ኣበራ ሞላ፣ (፲፱፻፺፫)፣ የኢትዮጵያ ዘመን ኣቈጣጠር http://www.ethiopic.com/calendar/acalendar.htm

11. ዊኪፐዲያ – (፲፱፻፺፱)፣ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር

12. Aberra Molla (2007), Ethiopic is not Julian, http://www.ethiopic.com/julian.htm

13. Pratt, J.P. (2001). Enoch Calendar Testifies of Christ, Part II, http://www.meridianmagazine.com/sci_rel/010912enoch2.html

14. Wikipedia – (2007), Ethiopian Calendar http://en.wikipedia.org/wiki/Ethiopian_calendar

ጳጉሜ ፫ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም.
September 8, 2007


https://am.wikipedia.org/w/index.php?title=%E1%8BB5%E1

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.