በፈረንጅ ድጋፍ ሾልኮ የወጣውና ለአደባባይ የተሰጣው የቅዱስነታቸው ገመና – መርሓጽድቅ መኮንን አባይነህ

ከመርሓጽድቅ መኮንን አባይነህ

ሰሞኑን በትግራይ ሚዲያ ሀውስና ቢጤዎቹ በሆኑት ጽንፈኛ መገናኛ-ብዙኃን ተቋማት አማካኝነት በሰፊው ሲሰራጭና ከፍተኛ አቧራ ሲያስነሳ የሰነበተው የአባ ማትያስ ዋልታ-ረገጥ ኑዛዜ እንደገና እየታደሰ መነጋገሪያነቱን ቀጥሏል፡፡

176345115 4232006450154284 2036013590367727349 n‘ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም’ እንዲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ፓትሪያርክ ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዘ-ኢትዮጵያ መደበኛውን መንገድ በመስበርና አስቀድሞ ከሚታወቀው የግንኙነት መስመራቸው በማጋደል ወደአደባባይ ብቅ ብለው ‘ዘር ከልጓም ሳይስባቸው’ አልቀረም በሚያስብል ሲቃ ያረገዘ ቅላጼ-ድምጽ ወገኔ ነህ በሚሉት የትግራይ ክልል ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈጸም ላይ መሆኑን እስኪያቅረን ድረስ ነገሩን፡፡

በርግጥ አባ በህ.ወ.ሀ.ት ላይ በተወሰደው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በኋላ አለቅጥ ተስፋፍቶ የተራገበላቸውን ሀረግ የገደል ማሚቶ ያህል ደግመው ከማስተጋባታቸው በስተቀር በጠባዩ ውስብስብ የሆነው የዘር ማጥፋት ወንጀል ራሱ ምን ያህል ከባድና በተፈጸመበት አገር ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ ይፈጸም በየትኛውም የአለም ክፍል የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣ እንደሆነ በውል ለይተው መረዳታቸውን ይህ ጸሀፊ አጥብቆ ይጠራጠራል፡፡

“ያ ህዝብ”፣ (የትግራይን ህዝብ ማለታቸው ነው)፣ ጨርሶ “ከምድረ-ገጽ ይጠፋ ዘንድ ለምን እንደተፈለገ እኔ አላውቅም” በማለት አስደንጋጭ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እምብዛም ያልቸገራቸው አባ ማትያስ እርሳቸው በግል ደፋር የነበሩ ቢሆንም ይህችን አውጥቶ ለመናገር እንኳ በየትኛው ሀይል እንደሆነ ፍንጭ ባይሰጡንም አፈና ሲፈጸምባቸው እንደከረመ ገልጸው ወገኖቻቸው ይህንኑ ጥረታቸውን በክሬዲት መልክ እንዲዪዙላቸው መማጸናቸውን በሚያሳብቅ ድምጸት “የራሴን ችግር የማውቀው ራሴ ነኝ” ሲሉ በአንክሮ አድምጠናቸዋል፡፡

አንዳንድ የዋሃን ወገኖች ታዲያ ደጋግሜ ብሞክርም “መናገር አልተፈቀደልኝም” የሚለውንና ሰሞኑን በቪዲዮ ተለቅቆ በማሕበራዊ የትስስር ገጾች የሚንሸራሸረውን ይህንኑ የአባ ማትያስ መልእክት “ረገጥከኝ፣ መተንፈስ አልቻልኩም” ከሚለውና አሳዛኝ ሲቃ ከተቀላቀለበት የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ የጻእረ-ሞት ድምጽ ጋር ያነጻጽሩት ይዘዋል፡፡

ይህ እንኳ በእውነት ተገቢ ንጽጽር ነው ብዬ በበኩሌ አላምንም፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ምእመናን የእምነት አጥር እንኳ ያን ያህል ሳይገድበን ብጹእነታቸውን የሁላችንም የመንፈስ አባት እንደሆኑ አድርገን ነው የምንቆጥራቸው፣ የምንተማመንባቸውም፡፡ በርግጥ ይህንን የምናደርገው ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ፓትሪያርክ ርእሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዘ-ኢትዮጵያ፣ ሊቀ-ጳጳስ ዘ-አክሱም ወእጬጌ ዘ-መንበረ ተክለ-ሀይማኖት ከዓመታት በፊት አክሱም ጽዮን ላይ በአካል ተገኝተው ለያኔው የህ.ወ.ሀ.ት ፊታውራሪ ለዶ/ር ደብረ-ጽዮን ገብረ-ሚካኤል አክሊል እንደደፉለትና ‘ሺህ ዓመት ንገስ’ ብለው እንደባረኩት ፈጽሞ ሳንዘነጋው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሌላው ቀርቶ ቀደም ባለው ጊዜ እኮ በጠቅላይ ቤተ-ክህነት ስር ከተዋቀሩት 14 መምሪያዎች ውስጥ 12 የሚሆኑት እርሳቸው ከበቀሉበት ብሔር ተመርጠው በተሰባሰቡ የመንደር አሽከሮች የተያዙ እንደነበሩ ማስታወስ ይሳናቸዋል ተብሎ አይታመንም፡፡ ይህንንም ያልተቀደሰ ፕሮጀክት ጀምረዉላቸው ያለፉት በዘር የሚሻረኳቸው አባ ጳውሎስ እንደነበሩ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

እንግዲህ ይህንን ሁሉ ማስታወሱ የማይገዳቸው ከሆነ ዛሬ ላይ ብቅ ብለው “አፈና ተፈጸመብኝ” በማለት የአለሙን ሕብረተ-ሰብ አንጀት ለማራራት ዴኒስ ዋድሌ የተባለን አንድ አውሮፓዊ ነጫጭባ ወደቢሯቸው በምስጢር ከጠሩ በኋላ ድምጽና ምስላቸውን ቀርጾ ለጠላት ሚዲያ በማቀበል ረገድ እንዲተባበራቸው የጠየቁበትና ያስፈጸሙበት ኩነት ግብዝነታቸውን ያሳያል፡፡ በተለይ በቪዲዮ የተሰራጨው የቅዱስ ፓትሪያርኩ መልእክት ማእከላዊ ይዘቱ በጥልቀት ሲመረመር ከመንፈሳዊነታቸው ይልቅ ፖለቲከኝነታቸውን የሚያሳብቅ መስሎ ታይቷል፡፡

ብጹእ አባታችን ተፈጥሯዊ የሆነው ሃሳብን የመግለጽ ነጻነታቸው በተደጋጋሚ እንደተጣሰ አደባባይ ወጥተው በምሬት ነግረዉናል፡፡ ነገር ግን በዚሁ ተወዳጅ መብት ያለአግባብ ተጠቅመው የነዙት መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ከተከበረው መንበረ-ፕትርክናቸው ወርደው ኀላፊነት በጎደለው አኳኋን ለህ.ወ.ሀ.ት ማደራቸውን አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል፡፡

በመሰረቱ አባ በጎውን ማወደስና ክፉውን ማውገዝ ወይም መገዘት ይጠበቅባቸው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ለአንድ ብሔር ወግነው የቆሙ በሚያስመስላቸው አኳኋን (ለያውም ሽብርተኛው ህ.ወ.ሀ.ት በግብረ-በላዎቹ አማካኝነት በሚዘውረው የውጭ ሚዲያ በኩል ተጋንኖ ከሚቀርብላቸውውጭ እምብዛም ባላረጋገጡት ጉዳይ)፣  ያን ያህል ሽንጣቸውን ገትረው እንዲሟገቱ ጨርሶ አይፈቀድላቸውም፡፡

አቡነ ማትያስ ለርስበርስ ፍቅር፣ ለሀገር ሠላም፣ ለዜጎች ደህንነትና ለማሕበረ-ሰቦች አንድነት ዘወትር መጸለይና ምእመናንን ሳይታክቱ ማስተማር መደበኛ ስራቸው ነውና ይህንን ለመፈጸም ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ከሀይማኖታዊ ተግባራቸው እላፊ በመሄድ እንደወያኔ ያለ ሕገወጥና አረመኔ ቡድን በአንድ አገር ሉኣላዊነትና በመከላከያ ሰራዊቷ ላይ የለየለት ክህደት በመፈጸም ከፍ ያለ ጉዳት ማድረሱን ተከትሎ ሥልጣን ላይ ባለ መንግሥት ከተወሰደ አጸፋዊ የመከላከል እርምጃ ጋር ተያይዞ በተጓዳኝ ያጋጠመን ሰብኣዊ ጥፋትም ሆነ የሀብት ውድመት ሆን ተብሎ በአንድ ብሔር ላይ የተነጣጠረ የጅምላ ጥቃት አስመስለው ሊያቀርቡና አለምን በሀሰት ሊያሳምኑ በድፍረት የተጓዙበት ርቀት አስተዛዛቢ ሆኖ ተመዝግቦባቸዋል፡፡

አባ በሁላችንም ዘንድ የተከበሩ የአንድ ገናና ሀይማኖት ቁንጮ መሪ ናቸውና አለማዊውን መንግሥትም ቢሆን ሲያጠፋ ቢገስጹና የተሳሳተ መስመር ተከትሎ ከሆነም ሀገሪቱን ላላስፈላጊ ኪሳራ ከመዳረጉ በፊት ወደቀልቡ እንዲመለስ አባታዊ ምክራቸውን ቢለግሱት እኮ እናደፋፍራቸዋለን እንጂ አናሸማቅቃቸውም፡፡

በእውን የሆነው ግን እርሱ አይደለም፡፡ ‘ከምን ጋር የዋለች ጊደር’ እንዲሉ ከመንበረ-ፓትሪያሪክ ጽ/ቤታቸው አንድ ማይል እንኳ ፈቀቅ ሳይሉ የመልሶ ማጥቃት እርምጃው ካስደነገጣቸው ዋሾ የህ.ወ.ሀ.ት አፈ-ቀላጤዎች የሰበሰቡትን ያልተጣራ የእንቶ-ፈንቶ መረጃ ከአንድ መንፈሳዊ አባት በማይጠበቅ ድምጸት በህቡእ አስቀርጸው በአደባባይ ለቀቁልን እንጂ፡፡

ከዚህ ጋር አብሮ ሳይወሳ መታለፍ የሌለበት ሌላም ቁምነገር አለ፡፡

አስደማሚው መግለጫ አፈትልኮ በወጣና አየር ላይ በዋለ ማግስት አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ አባ ማትያስን በእንግድነት ጠርቷቸው ነበር ይባላል፡፡ እርሳቸውም የኋላ ኋላ ዙሩ እየከረረ የሄደ እንደሆነ ጥላ ከለላ ሳይሆነኝ አይቀርም ብለው ወደገመቱት ወደዚያው የሀያሏ አገር ኤምባሲ ተቻኩለው ለማምራት እምብዛም አላቅማሙም ነበር፡፡

እንግዲህ አባ አውቀዉትም ሆነ ሳያውቁት ከአንደኛው ነጫጭባ ወደሌላኛዋ ወጥመድ መረማመዳቸው ነው፡፡ እኔ በበኩሌ እንደአንድ ተራ ምእመን ይህንን ነጭ አምላኪነታቸውን ፈጽሞ አልወደድኩላቸውም፡፡

ለማናቸውም እዚያ በተገኙበት ወቅት በቅርቡ ስራዋን የጀመረችው አሜሪካዊቷ እንስት አምባሳደር፣ (ጌታ ፓሲ ትሰኛለች)፣ ተፈጸመብኝ ከሚሉት አፈና ጋር በተያያዘ አንዳች አይነት ስጋት ይሰማቸው እንደሆነ አባን በጠየቀቻቸው ጊዜ በረዥሙ ከተነፈሱ በኋላ “እምብያው፣ አሻፈረኝ” እንዳሏትና ከዚህ የባሰ ፈተና ቢያጋጥማቸው እንኳ የመንፈስ ልጆቻቸውንና ሀገራቸውን ጥለው የራሳቸውን የግል ደህንነት በመሻት ብቻ ለስደት ዝግጁ አለመሆናቸውን እንደተናገሩ በበጎ ጎኑ ተዘግቦላቸው አድምጠናል፡፡

መቸም ይህ እውነት ከሆነ አባታችን ‘ጎሽ፣ ደግ አደረጉ’ ነው የምንለው፡፡

አሜሪካስ ብትሆን እዚህ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረጋትና ነው በሀይማኖታቸውና በሀገራቸው ክብር እንዲደራደሩ አባን በግል ጠርታ ያን ያህል የምትወሰውሳቸው?

ያንኑ ሽርፍራፊ የንዋይ ድጋፍና እርዳታዋን ተመክታ ምን ያህል ጢባጢቤ እንደምትጫወትብን ታያላችሁ?

ድህነት የዘለአለም ደዌ መሆኑን ይህ ብቻ ሊያስገነዝበን ይገባል

በመሰረቱ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ አዘውትራ ራሷ እንደምትለፍፈው የአለም ፖሊስ አይደለችም፡፡ ልሁን ብትልና ይህንኑ ከፍታ በአንድ ድምጽ ተስማምተን ብንፈቅድላት እንኳ ገለልተኛና እምነት የሚጣልበት ሕግ አስከባሪ የመሆን አቅምም ሆነ ሞራል የላትም፡፡

‘ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል’ እንዲሉ ብሔራዊ ጥቅሞቿ ይከበሩልኛል ብላ እስካመነች ድረስ የሰውን ቤት ካላፈረሰች በስተቀር ምን ጊዜም ቢሆን አርፋ የማትተኛው ያቺ ግብዝ አገር አጉል ልማድ ሆኖባት እንጂ እንደአምባሳደር ጌታ ፓሲ ያልተቀደሰ አቀራረብ አባ ማትያስ በሀገራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ እያሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ያለፈ የባእድ አገር ጥበቃ አያሻቸውም፡፡

ይልቁንም ታላቁ የህዝበ-ክርስትያን እረኛ ናቸውና በዋነኝነት ጠባቂያቸው ልኡል እግዚአ-ብሔር ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ግፋ ቢል በመሬት ላይ አባ ለሚያስፈልጋቸው የግል ደህንነት አጠባበቅ ቀዳሚውንና የአንበሳውን ድርሻ ኀላፊነት የሚወስደው ከነችግሮቹም ቢሆን እርሳቸውን ጭምር በስሩ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ መንግሥት መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ጠንከር አድርገን እንነጋገር ከተባለና በሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ላይ አተኩሮ  እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር April 18 ቀን 1961 ዓ.ም የወጣውን የቪዬና ስምምነት በዝርዝር ከተመለከትን በአዲስ አበባ ውስጥ የተጠለለውን ራሱን የአሜሪካን ኤምባሲስ ቢሆን በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠብቀውና የደህንነት ከለላ የሚሰጠው ከኢትዮጵያ መንግሥት በስተቀር ሌላ ማን ሆነና ነው?

እርግጥ ነው፣ U.S አሜሪካ በምድራችን ታላቅ፣ ባለጸጋና ሀያል አገር መሆኗ አይካድም፡፡ ይህ ግን እስከመጨረሻው ጫፍ ድረስ ያለአግባብ ተለጥጦ ያች አገር ባፈተታት ጊዜና አጋጣሚ በማይመለከታት ጉዳይ ሁሉ እንደእርጎ ዝንብ ዘው ብላ በመግባት ራሷን እየነከረች የነጻና ሉኣላዊ መንግሥታትን ሥልጣን በዘፈቀደ እንድትጋፋና ህልውናቸውን እንድትዳፈር ያልተገደበ መብት የሚሰጣት አይሆንም፡፡ እንዲህ ያለውን ያፈነገጠ አሰራር የሚያበረታታ ወይም የሚደግፍ አለም-አቀፍ የሕግ ስርአትም ሆነ የዳበረ ልምድ ጨርሶ የለም፣ አይታወቅምም፡፡

አበቃሁ፡፡

 

3 Comments

  1. አይ አቀራረብ አይ እውቀት እንደ ሙዚቃ እየሰረሰር ወደ ውስጥ የሚገባ ጌታዬ እውቀት ያብዛልን ስምዎ የንግድ ምልክት ሁኗል ጽሁፎ ፍቱን መድሀኒት ነው ልቦናውን ለእውቀት የከፈተ አንባቢ ካገኘው ይህን ያለማድነቅ የእውቀት ክፍተት ያለበት አንባቢ ነው። ታላቅ ክብር።

  2. Article is nonsense and full of lies like its owner

    ethiopia and orthodox church leaders are descending to the hell

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.