ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለዬቅል (ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ)

Globalግንቦት 10 ቀን 2013 ዓም(18-05-2021)

በሥልጣን ላይ ያለው ጎሰኛ ቡድን ከያቅጣጫው ያይንህ ላፈር ዘመቻ ተከፍቶበት ጭንቅና ምጥ ውስጥ ይገኛል።መሪውን አብይ አህመድን  የሰላም አባት ብለው ሾመው ሸልመው፣ ለሥልጣን ያበቁት ሳይቀሩ የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።ከዚያም ባለፈ አገራችንን ለመበታተን ካሴሩት የውስጥና የውጭ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ የዓለም አቀፉን ሕግ ጥሰው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት የክተት ዘመቻ አውጀዋል።ይህ የዲፕሎማሲና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ኢትዮጵያ አገራችን ላይ ለሚሰነዘር ወታደራዊ ጥቃት መንደርደሪያ  ቅድመ ጦርነት አድማ መሆኑንን ድርጅታችን ያምናል።

ይህ የተቀናጀ የውጭ ሃይሎች አሰላለፍና የክተት አዋጅ ለሃያሰባትና ላለፉት ሦስት ዓመታት በጠቅላላው ለሰላሳ ዓመታት በሕዝቡ ጫንቃ ላይ ሰፍረው ሕዝቡን ቁም ስቃዩን ሲያሳዩት የነበሩትን ጸረ ሕዝብና ጸረ አንድነት የሆኑና በሥልጣን ሽኩቻ የተራራቁትን የአንድ ድርጅት የኢሕአዴግ ቤተሰቦች፣ ህውሃትንና ኦህዴድ/ኦነግን አቀራርቦና አስታርቆ የግፍ፣የዘረፋና የስቃይ ኑሮ እንዲቀጥል ከመሻት የመነጨ ተቃውሞ ነው። ይህ በአሜሪካ ግንባር ቀደምትነት፣በአውሮፓ አጃቢነትና በግብጽና በሱዳን ተላላኪነት የሚፈጸመው ኢትዮጵያን የማጥቃት ዘመቻ፣ለአገር አንድነት፣ለዴሞክራሲና ለስርነቀል ለውጥ የሚካሄደውን የኢትዮጵያውያን አገር ወዳዶች ትግል አብሮ ለመጨፍለቅ የታሰበ ተንኮል መሆኑን እናምናለን።በዋናነት ዒላማ ያደረጉትም በኢትዮጵያዊነቱ  የማይደራደረውን በተለይም የአማራውን ማህበረሰብ ነው።ከራሱ መኖሪያ መሬቱ ይልቀቅ የሚለው ጫጫታም የዚያ አካል ነው።የአገሩን አንድነትና ሰላም ለማስከበር የተሰማራውንም ጦር ሃይል ወንጀል የፈጸመ የውጭ ሃይል አድርገው ስለውታል።

እኛም በሥልጣን ላይ ያለውን ፣ለዚህ ችግር የዳረገንን ጎሰኛ ቡድንና ስርዓት አጥብቀን እንቃወማለን፤ከሚመራበት አገር አፍራሽ፣ሕዝብ አጫራሽ ከሆነው “ሕገ ጥፋት”(ህገመንግሥት ልንለው አንችልም)ጋር ተወግዶ አገራችን በአንድነትና በሰላም የምትቀጥልበትን የፖለቲካ ጎዳና  እንድትከተል እንሻለን።የአሜሪካና ጭፍሮቹ፣የህወሃት፣የግብጽና የሱዳን ምኞትና ሰልፍ የእኛ ሰልፍና ምኞት እንዲሁም ፍላጎት አይደለም።ለዚያም ነው የጽሁፋችንን ርዕስ “ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለዬቅል” ያልነው።

እኛ ለኢትዮጵያ አንድነትና ለሕዝቡ መብት ስንል እነሱ በተቃራኒው የቆሙ ናቸው።የሚፈልጉትን በተረኛው መንግሥት ካገኙ ለሕዝቡ ደንታ የላቸውም፤እንደቀድሞው እጅና ጓንት ሆነው ይቀጥላሉ።መንግሥት ተብዬውም አሁን ዳር ዳር ቢልም በቀጣዩ መንበርከኩና  ታማኝነቱን በተግባር መግለጹ አይቀርም።

በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ግን ከግራም ሆነ ከቀኝ፣ከላይም ሆነ ከታች፣ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘርበትን ተቃውሞ በአንድ ቅርጫት ላይ ጠቅጥቆ በእኩል ያወግዛል፣ይፈርጃል።ለዴሞክራሲ  መብት፣ለአገር አንድነት የቆሙትን ሁሉ ጥላሸት እዬቀባ በቅርቡ ያሉትን እያሳደደ በእስር ቤቱ ያጉራል፣በሚስጥርም ይገላል።በውጭ አገር ያሉትንም በተላላኪዎቹ በኩል ለማስፈራራት ይሞክራል።ለእሱ አገር ማለት ቤተመንግሥቱ ነው።

እነዚህ የዴሞክራሲ ቁንጮና የሰብአዊ መብት አስከባሪ ነን ባዮች ምዕራባውያን  “ያዛኝ ቅቤ አንጓች” እንደሚባለው ለትግራይ ተወላጅ ያሰቡና የተጨነቁ በመምሰል የአዞ እምባ እዬረጩ ነው። ኢትዮጵያና ሕዝቧ ያለባትን ችግር ክደው ለጥቅማቸው ሲሉ በተባባሪነት ያገለገላቸው ህወሃት በሥልጣኑ ላይ ካልተመለሰ በማለት ያዙን ልቀቁን ይላሉ።ለነሱ ዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት ማለት በፈለጉበት አገር ያሻቸውን ሲያደርጉ፣ሲዘርፉ አብሮ የሚዘርፍና የሚተባበራቸው ቡድን በሥልጣን ላይ እስከተቀመጠ ድረስ ነው።ከዚያ ሌላ አገር ወዳድ ያገሩ ባለቤት ከሚሆን፣ሕዝብ መብቱ ተከብሮ የባለጸጋ አገር ዜጋ ከሚሆን አገር ብትፈራርስ ይመርጣሉ።የነሱ ብልጽግና በሌላው አገር ክስረትና ድህነት ላይ የተመሰረተ ነው።ይህ በሌሎች አገሮች ያዬነው ሃቅ ነው።ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በኢሕአዴግ/ብልጽግና አረመኔዎች እጅ ሲገደል፣ደሙ ሲፈስ፣ሲፈናቀል ድምጻቸውን አላሰሙም፣የሕዝቡንም ጩኸትና አቤቱታ አላዳመጡም።አሁንም ቢሆን ከእውነት የራቀ የፈጠራ ትርክት እያራገቡ ይገኛሉ።ምን ጊዜም ቢሆን ሰልፋቸው ከአምባገነኖችና ከወራሪዎች ጋር እንጂ ከሕዝብ ጋር አይደለም፤ሆኖም አያውቅም።ኢትዮጵያን በቀውጢ ቀን መካድ ልማዳቸው ነው።እኛ ኢትዮጵያውያን የነዚህን ጣምራ ጠላቶቻችንን ትርክት ማክሸፍና አገራችንን ለዚህ የተባበረ ጠላት ዘመቻ የዳረጋትን የጎሰኞች ስርዓት ለማሶገድ መታገል ግድ ይለናል።

“ከባዕድ የጎረሱት በሶ ይወጣል ደም ጎርሶ” እንደሚባለው እነሱ ለሚወረውሩት ፍርፋሪ፣እርዳታና ድጋፍ እራሳችንንና አገራችንን መሸጥና አሳልፈን መስጠት አይኖርብንም።ውጤቱን እያዬነው ነው።የነሱ እርዳታ አገራችንን ፈቀቅ አላደረጋትም፤የነሱ ብድር በዕዳ ውቅያኖስ እንድንዘፈቅ አደረገን እንጂ ሕዝቡን ከድህነት አሮንቃ አላወጣውም።የተጠቀሙት አቀባባይ ባለሥልጣኖችና አበዳሪዎቹ ብቻ ናቸው።ተዋርዶ ከመኖር በድህነት ተከብሮ መኖር ይሻላል።ሊኖረን የሚገባው ግንኙነት የዓለም አቀፍ ሕግና ደንብ በሚያስቀምጠው ግንኙነት ደረጃ እንጂ በጌታና በባሪያ መካከል የሚኖር ግንኙነትን አይደለም፤ እስከወዲያኛው እምቢ ልንለው ይገባል።ይህ የጎሰኞች ቡድን በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ የአገራችን አንድነቷ ፣ክብርና ደረጃዋም ሊጠበቅ አይችልም፣የሕዝቡም መብት አይረጋገጥም።በአሜሪካ ፊትአውራሪነት የተሰለፉት ሃይሎች በተሳሳተ አመለካከት የአማራው  ማህበረሰብ በህወሃት/ኢህአዴግ ተነጥቆ የነበረውን ታሪካዊ መኖሪያ መሬቱን አስመልሶ ለመቋቋም ጥረት ሲያደርግ እንደ ወራሪ ቆጥረው ለድጋሚ መፈናቀል ነጋሪት እዬጎሸሙበት ነው።ከዚያም በዘለለ ትግራይ ክፍለሃገርን እንደ ነጻ አገር በሚያሳይ መልኩ የኢትዮጵያን አንድነት እዬተፈታተኑት ነው።

ባለቤት ያቃለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም ነውና አገራችንን በጎሳ ተዋረድ ሸንሽኖ ለዚህ ውርደት የዳረጋትን በሥልጣኑ ላይ ያለ ቡድን አሶግደን የአገር አንድነትን፣የሕዝቡን ትስስር፣ታሪኳንና ዳርድንበሯን  የሚያስከብር አገር ወዳድ መንግሥት ለማምጣት በአንድነት መቆምና መታገል ይኖርብናል።ትግላችን ጣምራ ትግል ነው።አንደኛው በውጭ ሃይሎች የመጣ ጠላትን ለመቋቋም፣ ሌላው በአገር ውስጥ ያለ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አንድነት የጎሰኞች ስብስብ ለማሶገድ።ትግሉም ቀላል አይሆንም።ግን ህብረት ካለ የማይቻል የለም።እኛ የተረከብናትን ኢትዮጵያን ለልጅ ልጆቻችን ማውረስ የትውልዳችን ግዴታና አደራ ነው።ትልቅነት የመሣሪያ ጋጋታና የገንዘብ ብዛት ብቻ አይደለም ፤የሞራልና የጀግንነት ከዛም በላይ የእውነት ባለቤት መሆን ለድሉ ዋስትናና ጉልበት ነው።ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ሊወሯት የመጡትን ጠላቶቿን አሳፍራ የመለሰችው እውነትን ባነገቡ፣ በቆራጥና አገር ወዳድ ልጆቿ ትግል ነው።የቬትናም ሕዝብ የናፓል ቦምብ ውርጅብኝን ተቋቁሞ ነው እየተፈራረቁ የመጡበትን የምዕራብ ቅኝ ገዢዎች በዃላም ግዙፏን  አሜሪካንን ድባቅ መትቶ የነጻነቱና የአገሩ ባለቤት የሆነው።እርግጥ ነው ወቅቱ የተለዬ ነው።ከወቅቱ ጋር የተገናዘበ የትግል አቅጣጫ መከተል ተገቢ ነው።ዱሮም ሆነ አሁን ጊዜ የማይሽረው ትልቁ መሣሪያ ግን አገር ወዳድነቱ ነው።ለፍትሃዊ ዓላማ መቆሙ ነው።ያንን ካነገብን ውጣ ውረዱ ፣ችግሩ ቢበዛም የማታ ማታ ድሉ የእኛ ይሆናል።

በሥልጣን ላይ ላለው ቡድን የመጨረሻ ዕድል ለመስጠት ሲባል፣ አሁንም ሁሉንም በኢትዮጵያዊነቱና በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን፣የጎሳ ፖለቲካን  የሚቃወመውን ያካተተ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ፈቃደኛ እንዲሆንና እንዲተባበር እንጠይቃለን።ከዚህ የተለዬ አማራጭ መፍትሔ የለም።ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር ምርጫ ማካሄድ እብደት ነው። በሕዝብ ጭፍጨፋ ወንጀል ያልተሳተፉ፣ያልቀሰቀሱና ያልተጠረጠሩ በእስር ላይ የሚገኙት በነጻ እንዲለቀቁ የዓለም አቀፍ ኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ  ጥያቄ  ያቀርባል።

አገር ወዳዶችን ማሰርና  ማሳደድ ይቁም!የዘር ማጥፋት ዘመቻው ይቁም!!ወንጀለኞች ለፍርድ ይቅረቡ!!!

የተባበረን ጠላት በተባበረ ክንድ እንመልስ!!

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ

3 Comments

  1. “የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል” አሉ እማማ አረጋሽ። አርማችሁ በግልጽ እየተናገረ፣ የተምታታው ሃሳባችሁ በግልጽ የባልደራስ መሆኑ እየታወቀ “አለም አቀፍ ትብብር…….” ገረ መሌ ነን ስትሉ ትንሽም ሼም የለም እንዴ? ድሮ ድሮ ታይዋኖች “adidas”ን በ”abidas” ቀይረው ያምታቱን ነበር። ምዕራባውያንንም መቃወም ትፈልጋላችሁ። አቢይንም ማስወገድ [ከምርጫ ዉጭ] ያምራችኋል። ወይ ከምርጫው ውጡና “የሽግግር መንግስት” ጫጫታችሁን በሻለቃው መሪነት ግፉበት። አሜሪካም ያግዛችኋል። አሜሪካ “የአማራ ልዩ ሃይል ከወልቃይት እና ራያ ይውጣ” የሚለውን ባትጨምር ኖሮ “አቢይን ወዲያ አሽቀንጥረሽ ጣይልን” ትሉ እንደነበር ግልጽ ነው። ይህንንም ያላችሁት ለአማራ አስባችሁ ሳይሆን “የህይል ምንጭ” ይሆነናል ብላችሁ ስለምታስቡ ነው። ዋናው የግድቡ ጉዳይ ላይ አባን ከና ሳትሉ “አያገባንም” የምትሉ ይመስላል። ሻለቃው እኮ ሲአይኤ ደርግን ለማስወገድ ብዙ ተልዕኮ ሰጥቷቸው ነበር። ሳይሳካላቸው ቀረ፣ ያ ሁሉ ምርጥ ጀነራል በግንቦት 8 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኮሎኔሉ የተሳለ ካራ ተበላ። ከዚያ በኋላ የኮሎኔሉም ካራ ዶሎድመ፣ ወያኔም አዲሳባ ገባች፣ ኤርትራም ተገነጠለች። አሁን ደግሞ “አቢይን አስወግድልን” ተብለው ጭራሽ ሃገር ሊያሳጡን እየተራወጡ ነው። አቢይን ማስወገድ ይቻላል፣ በምርጫ! በተለይ ባልደራሶች አዲስ አበባ ላይ አንዳችም ሰበብ ልታመጡ አትችሉም። ሁልጊዜ ግን “ህዝብ ጥቅሙን ያውቃል” የሚለውን አትርሱ። ሰው ጥቅሙን ለማስላት የግድ እስከ ፔኤችዲ መማር ወይም ዲያስፖራ መሆን አያስፈልገውም።
    ለማንኛውም መግለጫችሁ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ካሰፈሰፉት ለመታደግ ቅንጣት ታህል ትርጉምም ሆነ ጥቅም የለውም። አብዛኛው ዲያስፖራ ከናንተ እጅግ በላቀ ቁጥር ለሃገሩ ዘብ ለመቆም በትክክለኛ አቋም ላይ ይገኛል። ስለዝሆነ የናንተን የሰንበቴ ማህበር መግለጫ – INCONSEQUENTIAL ብለን አልፈነዋል።
    በምርጫ ብቻ!

  2. “እኛ ኢትዮጵያውያን የነዚህን ጣምራ ጠላቶቻችንን፣ በሥልጣን ላይ ያለው ጎሰኛ የአብይ አህመድ መንግሥትን፣ በአሜሪካ ፊትአውራሪነት በአውሮፓ አጃቢነትና በግብጽና በሱዳን ተላላኪነት የተሰለፉት የውጭ ሃይሎችን እና የህወሃትን ትርክት ማክሸፍና የጎሰኞችን ስርዓት ለማሶገድ መታገል ግድ ይለናል” ብላችሁ ሦሥት ጣምራ ጠላቶች አሳይታችሁናል። እነኝህ ሦሥት ጠላቶች ደግሞ እርስበርሳቸውም እንደማይስማሙ በየቀኑ እያየነው ስለሆነ መነገር አያሻንም። ስለዚህ በዚህ ውስጥ እኛ ስንታከልበት የአራት ማዕዘን ትግል ሊሆን ነው ማለት ነው። እንኳንስ በፖለቲካው መድረክ ቀርቶ በድራማው መድረክ ይሄ ይቻላል? “ትግሉም ቀላል አይሆንም። ግን ህብረት ካለ የማይቻል የለም … ውጣ ውረዱ፣ ችግሩ ቢበዛም የማታ ማታ ድሉ የእኛ ይሆናል” ስትሉ ታበረታቱናላችሁ። የአራት ማዕዘን ትግል እንኳንስ በጎሣ ተሰነጣጥረን ቀርቶ (አሁን የጎሣ ችግር ደግሞ ሕገመንግሥቱን ከመቀየር በላይ አልፎት ተሻግሮ ሄዷል) እንደዱሯችንም ብንሆን …

  3. “ከድር ሰተቴ ” ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለዬቅል” ተብሎ ለተጻፈው አጭርም ቢሆን የሰጠኸው አስተያየት እውንና ተግቢ ተወዳጂ ነው።በመሆኑም በአንተ በኩል ” የሰንበቴ ማህበር መግለጫ” ብለህ ብታልፈውም በበኩሌ ደግሞ ” የዓለም አቀፍ የድድ ማስጫ ማህበር መግለጫ ” እንደዱባ የተረከሸ እንደ ማሺላ አገዳ የቀሸመ መግለጫ ነው ቢባልም አይከፋ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.