“አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ (ከአዲስ አበባ

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ (ከአዲስ አበባ
ma74085@gmail.com)

ራስ ቢትወደድ እንዳልካቸው መኮንን ከአፄ ኃይለ ሥላሤ የካቢኔ አባላት አንዱ የነበሩና በርከት ያሉ ልቦለድ ድርሰቶችን የጻፉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡  ፀሐይ መስፍን፣ ያይኔ አበባ፣ አርሙኝ፣ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም፣ የድሆች ከተማ፣ ዦሮ ጠቢና የህልም ሩጫ የሚሰኙ ድርሰቶች ከኚህ በየዣነሩ በርካታ የልቦለድና የኢልቦለድ ጽሑፎችን ካበረከቱ የቀድሞ ደራሲና ከፍተኛ የሀገር ባለሥልጣን የተገኙ ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ስለዚህኛው “ከድር ሰተቴ”ዎች ዘመን ግን ብዙም አላውቅም፡፡ ግን ስለሆዱ አብዝቶ ከሚጨነቅ ባለሥልጣን ብዙም አይጠበቅም፡፡

የዛሬውን ርዕሴን በአንደኛው ድርሰታቸው የሰየምኩት አለምክንያት አይደለም፡፡

ባለፈው ዓመት ይመስለኛል፡፡ አንድ “ጉዱ ካሣ” በሚባል የብዕር ስም የሚታወቅ ወንድሜ ከዚህች ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ያልፋል፡፡ ነፍሱን በገነት ያኑርልኝ፡፡ በእውነተኛ የመዝገብ ስሙ “አለማየሁ በላይነህ” ይባል የነበረውን ጸሐፊና ምናልባትም የመድረክ ሰው ሕይወት ማለፍ ተከትሎ በኢካድፎረምና በተለያዩ ሌሎች ድረገፆች የሀዘን መግለጫዎች ወጥተው ነበር፡፡ የኔ የብዕር ስም ዳግማዊ ጉዱ ካሣ ነው፤ የርሱ ደግሞ ጉዳ ካሣ ነው፡፡ ማንም እንደሚያስተውለው በጣም ተቀራራቢ ስሞች አሉን፡፡ ስለዚህም ያን የሞት ዜና ለኔ የሚያደርግ ቢኖር አይገርምም፡፡ ሊገርም የሚችለው እኔ ዳግማዊ ጉዱ ካሣ አለመሞቴን ጠቅሼ ሳስተባብል መቀበልና እንዲያውም ከመጠነኛ ይቅርታ ጭምር የሀዘን መግለጫውን ማንሳት አለመቻል ነው፡፡ በዚያን ወቅት አካባቢ አንድ የምወደው ድረገጽ እኔ እንደሞትኩ በማርዳት አንዳንድ ሥራዎቼንም ርዕሦቻቸውን ከሥር በማስቀመጥ የሀዘን መግለጫ አወጣ፡፡ እኔም “አይ፣ የስም መመሳሰል ያመጣው ስህተት ነውና ይስተካከልልኝ፤ እኔ ገና አልሞትኩም፤ ባይሆን ስሞት ሞቴን ለማሳወቅ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፤ አሁን ግን ግዴለም ይለፈኝ” ብል ማን ሰምቶኝ! ኢትዮጵያውያን በዚህን መሰሉ ቀላል ነገር እንኳን እንዳንግባባ እንደቀደምት ባቢሎናውያን ቀልበ-ብትኖች ሆነናልና ለራሴ ጥቅም ስል “የሞትኩና የተነሳሁ” ተደርጎ ሳይቆጠር(ብኝ) አልቀረም፡፡ “ምን አጨቃጨቀኝ” ብዬ ነገሩን ንቄ ተውኩት፤ ረሳሁት፡፡ ለዚያ አላስፈላጊና  ተሳስቀንበት በቀላሉ ሊታረም በሚችል ስህተት ሲባል ስሜን ሳይቀር ዘነጋሁት፡፡ ዛሬም ያወጣሁት በይሉኝታ የማላልፈው ጉዳይ ገጥሞኝ ነው፡፡

በመሠረቱ ሞት ዓይነቱ ብዙ ነው፡፡ ሁሉን ነገር አጥቶ እንደኢትዮጵያውያን በቁም መሞትም አለ፡፡ እንደነመለስ ዜናዊ በውሸት ኖሮ በእውነት ሞቶ መቀበርም አለ፡፡ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆኖ በሥነ ልቦናዊ የቁም ሞት መንከላወስም አለ፡፡ እናም አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ነፍሳችን ከሥጋችን አልተለየችም ለማለት ያህል እንጂ አልሞትንም ብለን ልንዋሽ አይገባንም፡፡ መንግሥት የለንም – አራጅና አሳራጅ በቤተ መንግሥት የመሸገ ኦነግ-ሸኔ የሚባል የአጋንንት መንጋ እንጅ (የዚህ ቡድን አለቃ ግን ይህን አራጅ ኦነግ-ሸኔ፣ በነጠላው “ሸኔ” በሚል ቁልምጫ ብቻ ነው ሊጠራው የሚፈልገው)፡፡ ሃይማኖት የለንም ፤ ከዲያቢሎስ ጋር የተቆራኘ በሃይማኖት ስም የሚያጭብረብር የቀበሮና የተኩላ መንጋ እንጂ፡፡ የመተሳሰብና የመተዛዘን ባህላችን፣ አብሮነታችን፣ ፍቅራችን፣ “በሞቴ፣ በሥላሤ፣ በአላህ፣ በነቢ…” ላይ የተመሠረተው ማኅበራዊ መስተጋብራችን፣ የነበረን አንጻራዊ የትምህርት ጥራት፣…. ሁሉ በወያኔና በኦነግ ተሸርሽሮ ባዶ ቀፎ ሆነናል፡፡ በኑሮም እየተጠበስን፣ በዘረኝነት እየተገረፍን፣ በዘር ማንነት እየተለየን በሜንጫ እየታረድን፣ በመታወቂያችን ሰበብ ከደሴ አዲስ አበባ ወይንም ከደጀን ጎሓ ጽዮን ለመግባት ከፍተኛው የሕይወት አደጋ የሚገጥመን የቁም ሙታን አልሞትንም ብንል ውሸታችንን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር እኔም አንተም ሞተናል ቢባል አልተጋነነም፤ ነፍስንና ሥጋን የሚለየው የእውነት ሞት ግን እግዚአብሔር ይመስገን ገና አልጎበኘኝም፤ ደግሞም የኢትዮጵያን ትንሣኤ ሳላይ ሞት የሚባል ነገር ጫፌን እንዳይነካ የጴጥሮስ ሥልጣነ ክህነት ባይኖረኝም በፈጣሪ ስም እገዝተዋለሁ!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኤሜሪካ ኤምባሲ በምርጫ 2012 ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሄደ

የተረሳውን ሞቴን ያስታወስኩት አንድ ወንድሜ በጻፈው ሰሞነኛ መጣጥፍ ነው፡፡ አሁንገና ዓለማየሁ ይባላል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየድረገፆች ጽሑፍ በመላክ ይታወቃል፤ እኔም አንባቢ ደምበኛው ነኝ፡፡ አንዱ ደከም ሲል ሌላው እየተነሣ ሀገራችንን ያስባታል፡፡

አንድ እውነት በዚህ አጋጣሚ ልናገር፡፡ አንድ ሰው በሚሠራው መልካም ሥራ ሲወደስ፣ በሚያጠፋው ጥፋት ወይም ስህተትም ሲወቀስ ከአክብሮታዊ ምሥጋና ጋር በፀጋ ካልተቀበለ ሰው የመሆን ትርጉምን ያፋለሰ ያህል ይቆጠራል፡፡ “ሲያጎርሱት የማያላምጥ” የለም፤ ሊኖር ከቻለም ከዲያሌክቲክሱ ውጪ ነውና እማሆይ የሚበልጡት የቁም ሙት ነው፡፡ ምሥጋናም ወቀሳም ላወቀው ዋጋ አላቸው፡፡ አንድ ሰው ሲመሰገን እንዲኩራራና መሬትን እየተጠየፈ እንዲጀነን ሳይሆን ለበለጠ ሥኬት እንዲተጋ ለማበረታታት መሆኑን መረዳት አለበት፡፡ ሲወቀስም አሠራሩን እንዲያሻሽልና ወደትክክለኛው መስመር እንዲገባ ለማድረግ ነው፡፡ ይህም ሲሆን አመስጋኙና ተቺው ወይም ወቃሹ ነገሮችን የሚመለከትበት መነጽር ወሳኝ መሆኑን ሳንዘነጋ ነው፡፡ “አመስጋኝ አማሳኝ” ይባላልና ለወቀሳም ሆነ ለውዳሤ ትክክለኛ ሚዛን ይኑረን ታዲያ፡፡

ከዚህ አኳያ አምና በዚህ በያዝነው ወር ውስጥ የጻፍኩትን አንድ መጣጥፍ መነሻ በማድረግ ወንድሜ አሁንገና ዓለማየሁ በድረ ገፆች ያስነበበንን ማለፊያ ጽሑፍ ስመለከት የተሰማኝ የደስታ ስሜት ወደር አልነበረውም፡፡ ብዙ ቁም ነገሮችንም አካቷል፡፡ እርግጥ ነው – “ይህ ሁሉ ለኔ አይገባም፤ ሆድ ያመስግን፣ ሙያ በልብ፣ ኧረ ይሄ ሁላ ምሥጋና ለኔ ይበዛል…” የሚሉ የትኅትና መግለጫዎች መኖራቸውን አልዘነጋሁትም፡፡ ደምብ ነውና ይባላል፤ የሚመሰገኑ ሰዎችም እንደዚህ ያለ ምላሽ ሲሰነዝሩ ይደመጣል፡፡ በሀገራችን በብዙዎች ዘንድ ክፉኛ ከሚፈሩ ነገሮች አንዱ ምሥጋና ወይም ውዳሤ እንደሆነ እገምታለሁ – ነቀፌታ ወይም አሉታዊ ትችትም እንደዚሁ በጣም ይፈራል፡፡ ምናልባት ሁለቱም እንዴት እንደሚሰጡ ብዙዎቻችን አናውቅበት ይሆናል፤ ፈረንጆቹ ግን በዚህ ረገድ ጎበዞች ሣይሆኑ አይቀሩም – እኛን የሚያበላሸን ይሉኝታና የጥቅምና ፍላጎት ትስስር ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ብቻ ብዙዎች ሲመሰገኑ የመሸማቀቅ ነገር አይባቸዋለሁ፤ አንዳንዶች ደግሞ በተቃራኒው ባልሠሩበትም ጭምር ቢሞካሹና ሲሞካሹም ፈንጠዝያቸው ሌላ ነው – ተፈጥሯችን የሚገርም ነው፡፡ ባልዋለበት ጦር ሜዳ፣ ባልገደለበት የጦር መሣሪያ፣ ባላስመዘገበው ግዳይና የጦር ምርኮ … በባዶ ሜዳ ሲወደስ ደስ የሚለውና ጮቤ የሚረግጥ “ጀግና” ከገጠመህ በሰዎች ተፈጥሮ ከማዘንና ምናልባትም ከመደነቅ ውጪ ምንም ማድረግ አትልም – እንዲህ ያለው ዜጋ እየበዛ ከሄደ ግን ለሀገር ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ለማንኛውም ከፍ ሲል የጠቀስኩት “አመስጋኝ አማሳኝ” የሚለው ብሂል ወርቃማ ብሂል ነውና ልብ ብንለው ደስ ይለኛል፡፡ “አመስጋኝ ሰውን ያበላሻል” ለማለት ነው፡፡ እውነት ነው – ምሥጋናንም ሆነ ወቀሳን እንደጥሩ መሣሪያ ካልተጠቀምንባቸው ሁለቱም አጥፊዎች ናቸው፡፡ የተመሰገነ ሊኩራራና በሕዝብ ወይንም በአድናቂዎቹ ላይ ሊጨመላለቅ ይችላል፤ ተወቃሽም አእምሮውን ትቶ ጉልበቱን በመጠቀም ተቺውን በአካል ወይም በሥነ ልቦና ወይም በሁለቱም ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ ስለሆነም ምሥጋናንም ወቀሣንም በአግባቡ መስጠትና መቀበልን መልመድ የሁላችንም ድርሻ ነውና ሰዎችን ስናበረታታም ሆነ ለማስተካከል ስንሞክር በጨዋነትና ሰውን ሊያማግጥ በማይችል መልኩ እንዲሆን መጣር አለብን፤ ስንወቅስ በተለይ አስተማሪነት ባለውና ስሜትን በማይጓጉጡ ቃላት ቢሆን ጥረታችን ፍሬያማ ይሆናል፡፡ እንዲህ የምለው አግባብ ባለው ሁኔታ መመሰጋገንና መወቃቀስ ለዕድገታችን ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ከመገንዘብ አንጻር እንጂ አንዳችን ሌላኛችንን በውዳሤ ከንቱ እየካብን እንድንበላሽ ለማበረታታት አይደለም፤ ያ ዓይነቱ ጉዞ ወደ ገደል ነው፡፡ ጥሩ የሠራን ማበረታታት ደመወዙን የመክፈል ያህል ነው፤ መጥፎ የሠራን መንቀፍ ደግሞ ሰውዬውን ከማነጽ በተጓዳኝ ማኅበረሰብን ከጥፋት መታደግ ነው – ሁለቱም በእኩል ደረጃ ጠቃሚዎች ናቸውና አያሣፍሩም፡፡ ሲመሰገን የሚያፍር ካለ በሠራው አኩሪ ተግባር አላመነበትም እንደማለት ነው፤ በሠራው ስህተት ሲወቀስ የማይደነግጥና ከስህተቱ የማይመለስ ካለ ደግሞ የለዬለት ደንቆሮና ራሱን የማያውቅ የማኅበረሰብ ሸክም ነው፡፡  ከዚህ አኳያ የወንድሜን የማበረታቻ ቃላት (compliment/s) በታላቅ አክብሮት የተቀበልኩ መሆኔን በመግለጽ ልሰናበት፡፡ የአሁንገና ሰሞነኛ ጽሑፍና እርሱ የጠቀሰው የአምናው ጽሑፌ አድራሻ እንዲሁም በጊዜው አለመሞቴን የገለጽኩበት ጽሑፍ የተለጠፈበት ምንጭ/ሊንክ ከዚህ በታች አስቀምጫለሁ፡፡ ልድገምላችሁ – የሞተው ጉዱ ካሣ እንጂ ዳግማዊ ጉዱ ካሣ አይደለም!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ የዕንቆቅልሽ ምድር - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

የዳግማዊ ጉዱ ካሣ ትንቢት (ከአሁንገና ዓለማየሁ https://zehabesha.info/archives/118553

ጦር ሰባቂው ስዬ አብርሃ አሁን ደግሞ ምን እያለን ነው? – ዳግማዊ ጉዱ ካሣ  https://zehabesha.info/archives/105393

አፄ ምኒልክንና አማራን መሳደብና ማዋረድ – የዘመናችን ፖለቲካ የይለፍ ቃል! ዳግማዊ ጉዱ ካሣ    https://zehabesha.info/archives/118569      በዚህ መጣጥፍ ያ የማነ ንጉሤ የሚባል የፈንቅል መሪና ሃጫሉ ሁንዴሣ አፄ ምኒልክን የተሳደቡበት አፍላ ወቅት ስለነበር በነሱ ላይ ነበር ያን ጽሑፍ የጻፍኩት፡፡ ከተጠቀምኩባቸው ሕዝባዊ ሥነ ቃሎች ውስጥ “የማያድግ ልጅ በአባቱ ብልት ይጫወታል” የሚለው አንዱ ነበር፡፡ አሁን ወደኋላ ዞሬ ስታዘብ እኔ ባላሰብኩት መንገድ ተረቱ እውን ሆኖ የማነ ብቻ ሣይሆን ሃጫሉም አሁን በሕይወት የለም፡፡ የሚገርም አጋጣሚ ነው፡፡ መጋረጃ ጥዬ ልቀመጥ ይሆን እንዴ እናንተዬ! (ስቀልድ ነው!)፡፡ አዎ፤ እሰው አፍ መግባት መጥፎ ነው – የሰው አፍ ሁለቱንም ነጠቃቸው፡፡ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ላይ የቀለደና ግፍና በደል የፈጸመ ይዋል ይደር እንጂ ገና ብዙ አሣና ፈተና ይገጥመዋል – ባለፉት ጥቂት አሠርት ዓመታት እንኳን ስንት ጉድ አየን፡፡ የአሁኑንም ይሁን መጪውን ጊዜ በሚመለከት መናገር ትንቢት አይደለም – ማንም የሚገምተው ነባራዊ እውነት እንጂ፡፡ የዘራውን የማያጭድ ገበሬ በዚህች ምድር ተፈጥሮ አያውቅም፡፡

https://zehabesha.info/archives/118583

5 Comments

 1. ወንድሜ ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
  ይቅርታ ይደረግልኝ። ግዙፍ ሥህተት ነው። በወቅቱ ወጥቶ በነበረው የተሳሳተ ዜና እጅግ መደንገጥና ማዘኔን አስታውሳለሁ። ማስተባበያውን ግን አላየሁትም፣ አላነበብኩትም ነበር። የተጠቀሰውንና መነሻ የሆነኝን ጽሑፍ እጅግ በመገረም መላልሼ አንብቤ አስቀምጬው ነበርና ትንቢቱ ሲፈጸም ታወሰኝ። እንዳጋጣሚ ልክ የዛሬ አመት ነበር የተጻፈው። እግዚአብሔር ይስጥልን። በድጋሚ ይቅርታ። እንኳን ኖርክልን። እንኳንም አለህ። ፈጣሪ የኢትዮጵያን ትንሳኤ ሳያሳይ አይውሰደን።
  ወንድምህ አሁንገና

 2. በፍጹም፣ በፍጹም… ይቅርታ የሚያስብል ነገር የለውም። ማንም ሰው ትክክል ነው ውድ ወንድሜ አሁንገናም ሌላውም። በዚህ ጽሑፍ እንደገለጽኩት ሥማችን በእጅጉ ስለሚመሣሰል የተፈጠረው ግጥምጥሞሽ (ስህተት ማለት እሥኪቸግር ድረሥ ይዘልቃል) በጣም የሚጠበቅ ነው።
  ከዚህ አንጻር እንኳን እኔ ሟች አለመሆኔ ቆይቶም ቢሆን- ዕድሜ ላንተ – ታወቀልኝ እንጂ በማንም ላይ ቅሬታ የለኝም። ዘሀበሻንም አንተንም በጣምና ከልብ አመሰግናለሁ። በዚህ አጋጣሚ ከሁለት ዓመት በፊት የከተብኳትን “ትግራይ – ቀጣይዋ የሱማሌ ክልል” የምትል መጣጥፍ ብታያት አምና ከጻፍኩትና ሰሞኑን በሚገባ ከተነተንከው ጽሑፍ ጋ በእጅጉ ትመሣሰላለች። ለመረጃ ልውውጥ ያህል ነው።
  ሁላችንንም ለተቃረበው የሀገራችን ትንሣኤ ያድርሰን!

  • Sorry, the article written about Tigray ““ትግራይ – ቀጣይዋ የሱማሌ ክልል” was posted on Sept. 10, 2018. Therefore, it is not only 2 years since it was posted; it is rather nearly three years or 2 years and 8 months, to be exact.

 3. እውቁ የእለም አጫዋች Mark Twain በለንዶን ኑሮውን እየገፋ በነበረበት ጊዜ አንድ ጋዜጠኛ ታውቃለህ ወይ በኒወርክ በድህነት ላይ ሆነህ በዚህ ከተማ ውስጥ እየሞትክ እንደሆነ በማለት ለጠየቀው ጋዜጠኛ ምላሽ ሲስጥ “Just say the report of my death has been grossly exaggerated.” በማለት መልሶለታል። የአቶ ጉዶ ካሣም ጉዳይ ከዚህ የሚዘል አይደለም። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ሰበር የተባለው ወሬ እግርም አይንም አፍንጫም የተነፈገው ጉንድሽ ነው። ታዲያ አንድ ለሌላው እያቀባበለ ሲናፈስ እውኑን ከውሽት፤ ገለባውን ከስንዴ መለየት ምንኛ ይከብዳል። ዘመኑ ዝም ጭጭ የምንልበት ጊዜ እንጂ ቡታ ነጋሪነት የቀን ሥራችን ሊሆን አይገባም። ከሚወራው ይልቅ የማይነገረው የዜና ክምር ይበልጣል። በአቶ ጉድ ካሳ የተጠቀሰው መጽሃፍና “አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም” የሚለው የአቶ ተማቹና የወ/ሮ ጽጌረዳ ታሪክ በውሸት ከሚነዛ የሞት ወሬ ጋር ታሪኩ አይገናኝም። አቶ ተማቹ ሚስቱን ሰላቶ አግብቶበት በግድ እሱም በጦር ሜዳ ልጆቹንና ጓደኞቹን ገብሮና ቆስሎ በልመና መልክ ቤቱ ደጃፍ ላይ ቀርቦ በተመለከተው የግድ ድርጊት ራሱን ሰቅሎ ወ/ሮ ጽጌረዳም የሆነውን ስትረዳ በፋስ የጣሊያኑን አንገት ቆርጣ የተያዘችበት ታሪክ እንጂ። እንደሚታወቀው ሁሉም ክስና ወቀሳ የሃሰት ወሬና ጋጋታ ምላሽ የሚሻ አይደለም።
  ምንም አትበሉ ዝም ዝም ይሻላል
  አፍ የከፈቱ ለት ሞትም ይከተላል ያለችው አስለቃሿ ተናጋሪ ሰው ቀብር ላይ ቆማ ነው። ዝምታ ማለፊያ ነው። ልብ ያለው ዝም ይበል። የሞቱ ወሬ ጭራሽ እኔን አያስደንቀኝም። እድሜ ለኢንተርኔት ነገሩ ሁሉ አስረሽ ሚችውና ሸቀጥ እንደሆነ እያየን ነው። ዳግማዊ ጉድ ካሳም ኑር። እድሜህን የማቱሳላ ያርግልህ እስከዛ ድረስ የምትኖርበት ካለህ!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.