አብን ከተመረጠ አካታች የገጠር ልማት ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ገለጸ

አብን

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) «ጊዜው አሁን ነው!» በሚል መሪ ቃል የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም የጀመረውን ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ በተለያዩ የገጠር ቀበሌዎችና ታዳጊ ከተሞች አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።
በዚህም በደቡብ ወሎ ዞን ቦረና መካነሰላምና ደብረሲና ወረዳወች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያ ገምዛ ወረዳ ባታ ቀጠና፣ በቀወት ወረዳ የገጠር ቀበሌዎች፤ በአንኮበር ወረዳ በጎረቤላ፣ በአልዩአምባ፣ በጎርጎ፣ በዘንቦና በመሀል ወንዝ፤ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ገነት አቦ ከተማ፣ በድጉና ላምጌ፣ ጓንቻ፣ ዋሚትና አርዲስ ቀበሌዎች፤ በይልማና ዴንሳ ወረዳ በጉቤ፣ በደብረ መዕዊ እና ጃን ከበር ቀበሌዎች፣ ጎንጅ ቆለላ ወረዳ ዜጋንሳ፣ ደብረ ድላሎ፣ ይናጭ አቦ፣ ወይዛዝርት ቀበሌዎች፣ በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ፣ በመቄት ወረዳ ደብረዘቢጥ ቀበሌ፣ በራያ ቆቦ ገጠር ቀበሌወች፤ በደቡብ ጎንደር ዞን በወረታ ከተማ፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን እናርጅእናውጋ ወረዳ በኮሶ ዝራና በወፊት ቀበሌ፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ዱባባና ቢኛኛ ቀበሌ፣ በመተማ ወረዳ ኮኪት፣ ኩመር አፍጥጥ፣ ወዲ ገምዞ፣ አዲስ ዓለም፣ ሽመልጋራ፣ ደለሎ ቁጥር 1 እና ሌሎች አካባቢዎች የተሳካ ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳ አድርጓል።
በይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳውና በሕዝባዊ ውይይቶች ላይ አብን ከተመረጠ የሕዝባችን ኹለንተናዊ ተጠቃሚነትና ደኅንነቱን ማረጋገጥ የሚያስችሉ አማራጭ የፖሊሲ ኃሳቦችን ማቅረቡ የተገለጸ ሲሆን ሕዝቡ ለተሻለ ነገው ኃቀኛ ወኪሉን አብንን እንዲመርጥ ተጠይቋል።
አብን ከተመረጠ አካታች የገጠር ልማት ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ የአርሶና አርብቶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት በማሳደግ ሕይወቱ እንዲሻሻል የገጠር ሽግግር ስትራቴጂዎችን ነድፎ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ብሎም ስትራቴጂዎቹ ከድኅነት ቅነሳ በዘለለ ቀጣይነት ያለው እና የገጠሩን ማኅበረሰብ ኹለንተናዊ እድገትና መሻሻል የሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጿል፡፡
በተጨማሪም አብን ከተመረጠ የገጠር ልማት ፕሮግራሞች በማኅበረሰብ ደረጃ ተግባራዊ ሲያደርግ ውጤታቸው የአርሶና አርብቶ አደሩን ኹለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥና ለአርሶና አርብቶ አደሩ ልጆች በርካታ የሥራ እድሎችን በሚፈጥር እንዲሁም የአካባቢ ብክለትን በሚከላከል መልኩ እንዲሆን እንደሚሰራም ተገልጿል።
#በምርጫ ካርድዎ የመዋቅርና ሕግ ሰራሽ ችግሮችን ሰንኮፍ ነቅሎ ዲሞክራሲን ማስፈኛ ጊዜው አሁን ነው!

2 Comments

 1. አብኖች በምንም ይሁን ኢትዮጵያ ከሥልጣንም ከምንም ነገር በላይ እንደሆነች ለማሳየት ወሳኝ በሆኑ ወቅቶች የምትወስዱት አቋምና እንቅስቃሴ ያስደንቀኛል። ታስታውሳላችሁ? የምርጫውን መተላለፍ ደግፋችሁ የወያኔን ወሽመጥ የበጠሳችሁበትን ዉሳኔ? ያኔ ነው “አብኖች የልጅ አዋቂዎች” ብዬ ሃሳቤን የቀየርኩት። “ባልመርጣቸውም ልቃወማቸው አይገባም” ብዬ ማለት ነው። እናንተ ላይ ለውጥ አመጣለሁ ለማለት ሳይሆን የግል መብቴን ለመጠቀም ነው።
  አሁን ደግሞ ለሰላም እና ለዲሞክራሲ አስተውጾኦ ማድረግን እያስተማራችሁን ነው። ልክ ሙስሊም ወንድሞቻችን የኢድ እለት ያሳዩት የጽንፈኝችንም “ኢትዮጵያ ትፍረስ” ብለው የወሰኑትንም ቅስም የሰበረ ነው። አሁን አብን ሲደግመው ደግሞ በጣም ደስ ይላል።
  ምርጫው “የተበላ እቁብ ነው” እያላችሁ ህዝብ የምታዘናጉና የምታላዝኑ ከአብን ትምህርት ቅሰሙ። እንዲያውም አሁን አሁን ይህንን የሚያላዝኑት ያፈነገጡ የብልጽግና ሰዎች ይሆኑ እንዴ? ብሎ መጠርጠሩ አይከፋም። መራጩን ተስፋ ለማስቆረጥ ማለት ነው። ከዚህ በኋላ የሸግግር መንግስት፣ አቢይ በጉልበት ይውረድ ጂኒ ጃንካ እያላችሁ የምታደነቁሩን ሰዎች you are MINORITY and none other than Balderas members/supporters and ADMIRORS of Major Dawit W/Giorgis. ካላስ!
  ባልደራሶች የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ከምትሉ የምትፎክሩባትን አዱ ገነት “ነጻ” ለማውጣት ታገሉ። በተለይ አዲስ አበባ ላይ ምንም ሰበብ አያስፈልግም። ህዝብ የሚመርጣችሁ ከሆነ ይቻላል!!!!! ካልተመረጣችሁም ህዝቡ አልፈለጋችሁም ማለት ነው። አዲስ አበባ ላይ ምርጫው በፍጹም ሊጭበረበር አይችሂልም፣ ብልጽግ ናም ለይቶለት ላላበደ በስተቀር አይሞክረውም። ካላስ!
  #በምርጫ ካርድዎ የመዋቅርና ሕግ ሰራሽ ችግሮችን ሰንኮፍ ነቅሎ ዲሞክራሲን ማስፈኛ ጊዜው አሁን ነው!”
  ይመቻችሁ አብኖች፣ ቃላችሁን ጠብቁ።
  በምርጫ ብቻ!
  ማሳሰቢያ፣ ፎቶውን ፈረንጅ ቢያየው እጅ አወጣጡን ከሌላ በዓለም ላይ ከተከለከለ ነገር ጋር እንዳያገናኘው ጥንቃቄ ይደረግ።

 2. አብን ከተመረጠ ተስፋ ያለዉ ድርጅት በመሁራን የተሞላ ባለፈዉ ጥልፍልፎሺ ዉስጥ ያልተሳተፈ በመሆኑ ነገሮችን በማስተዋል በቅንነት በኢትዮጵያዊነት ይመለከታል ከዚያም አልፎ በእርጅና በማንነት ፍለጋ በስራ ፍለጋ በኦሮሞ መሪዎች የተዸናቆረዉን የኦሮሞ ወጣትም ነጻ ያወጣዋል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.