/

የኢትዮጵያ ምጥ (ዶ/ር መኮንን ብሩ)

ኢትዮጵያ የልጆቿ እናት ብቻ ሳትሆን የልጆቿም ባሪያ ሆና የመከራ ምጧን ከተያያዘችዉ ዘመናት ተቆጥረዋል። አንዳንዶች ልዩ ወራሽ ነን ብለዉ ዘወትር ቀስፈዉ እንደሚይዟት ሁሉ ጥቂት የማይባሉትም እራሳቸዉን የእንጀራ ልጅ አድርገዉ የእስትንፋሷን መቆም የሚማፀኑም በርክተዋል። የሚጠሏት ስቃይዋ ላይ ሌላ ስቃይ ለመጨመር  ቁስሏ የመሰላቸዉ ላይ ሁሉ ክብሪት ሲጭሩበትና ቤንዝን ሲጨምሩበት፤ እንወዳታለን የሚሉትም ቁስሏን እየጨመቁ መከራዋንና ምጧን እያበራከቱ ይገኛሉ። ግን ለምን? …..

የኢትዮጵያ ምጥ

የሚጠሏት ለምን አምርረዉ ሊጠሏትና ሊበታትኗት መረጡ? …..  የሚወዷትስ ለምን የእኔ ብቻ በማለት ጭንቋን ሊያበዙ ፈለጉ? …. አጭሩ መልሱ ኢትዮጵያ በደም ተሰርታ በደም የተጠበቀች የደም ዉጤት ብቻ በመሆኗ ሳይሆን መለኮታዊ ኃይልንና ዕምነቶችን አቅፋት እና አቻችላ ለመኖር እየተፋለመች ያለች ያልሰከነችና በማዕበል የምትናወጥ ዉቅያኖስ በመሆኗ ነዉ። ማዕበሉ ግን መስከኑ አይቀርም።

በ 1529 ዓመተ ምህረት ወይንም ዐፄ ቴዎድሮስ ከመወለዳቸዉ ሁለት መቶ ዘጠና ዓመታት በፊት በወቅቱ በኢትዮጵያ ነግሰዉ በነበሩ ክርስትያን ገዢዎች (ወይም the so-called Christian Ethiopian Empire) እና በሙስሊም የአዳል ሱልጣኖች (Adal Sultanate) መካከል ረዘም ያለ የአስራ አራት ዓመታት ጦርነት (1529 – 1543) ተደርጎ ነበር። ያኔ ገና ከጅምሩ የኢትዮጵያን ዕድገትና ማንነት በእንጭጩ ለማስቀረት በተለይም የክርስትና ኃይማኖትን አከርካሪ ለመምታት ግብፅና ቱርክ ከፍተኛዉን ሚና ተጫዉተዋል። ያኔ የኢትዮጵያ ወይም አቢሲኒያ ክርስትያን ገዢ የሚባሉት አማራ፣ ትግሬ፣ አገዉ እና አሁን በዉል የማይለዩት ማያዎች ነበሩ። የአዳል ኃይሎች ይባሉ የነበሩት ደግሞ ሐረሪ፣ ሱማሌ፣ አፋር፣ እና አርጎባዎች ነበሩ። የኢትዮጵያ ምጥና መከራ ከዚህ ጊዜ ወዲህ የጀመረ ባይሆንም ከዚህ ጊዜ ወዲህ ግን ኢትዮጵያ ከምጣዱ ወደ ፍሙ የገባችበት የታሪክ ምህራፍ ነዉ ብንል ብዙም አልተሳሳትንም።

በእርግጥ ከዚህ ዘመን ወዲህም አቢሲኒያም ኢትዮጵያ ሆና ለመዝለቅና ለመጠንከር በተቻላት አቅም በዓለም የቲያትር መድረክ ላይ ተዋድቃለች። በትግል ዉስጥ መሞት ብቻ ሳይሆን መግደልና ማቁሰልም ስላለ ኢትዮጵያን ያሉ ጀግናዎቿም በደል እንደተፈፀመባቸዉ ሁሉ በተለያዩ የድል አዉድማዎች በደል ፈፅመዋል። ይህ ደግሞ በሁሉም የዓለም ሀገራት አመሰራረት ሂደት ዉስጥ ልንማር የምንችለዉ ሐቅ መሆኑ ይታወቃል። ለምሳሌ ያኔ የአቢሲኒያ ክርስቲያኖች ከአዳል ሱልጣኖች ጋር ጦርነት ሲገጥሙ አሜሪካ የምትባል ሀገር አልነበረችም። በሰፊዉ የዛሬ የአሜሪካ ምድር ላይ የነበሩት ሬድ ኢንዲያን (Native Indians) ነበሩ። የዓለም ታሪክ ይህ ነዉ።

የአቢሲኒያ ክርስትያኖች ከሙስሊም የአዳል ሱልጣኖች ጋር ለዓመታት ሲፋለሙ በነበረ ጊዜ ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ እስራኤል፣ስፔን፣ ካናዳ፣ ወዘተ እንደ ሀገር አይታወቁም። ሁሉም የራሳቸዉን የመኖርና ያለመኖር ተጋድሎ አድርገዉ ሀገር ሆኑ። የአቢሲኒያም የመዉረርና የመወረረር ታሪክ ከዚሁ የመኖርና ያለመኖር ትግል ጋር የተያያዘ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

በኢትዮጵያ ታሪካችን ሁሉም ሊሆን የቻለዉ ሀገር ሆኖ ለመወለድና ባለመኖርና በመኖር መካከል በነበረ ፍልሚያ ነዉ። በዓለም ታሪክ ሀገር የነበሩ ግን የጠፉትን እንደ ሳይሎን፣ ቺኮዝሎቫኪያ፣ ሜሶፖታሚያ፣ ኒዉፍዉንድላንድ፣ ታቮላራ፣ ሲኪም፣ ትሪፖሊታንያንና የመሳሰሉትን ሀገሮች ይመስል እንደ ሀገር እንዳንጠፋ ዛሬ ማረጋገጫ እያጣን በመሆኑ ዓለም የመጣበትን ታሪክ የመሰለዉን ታሪካችንን ዛሬም እያጋነኑ በርካታ ኃይሎች ሊያጠፉን ወይም ሊያጠፋፉን መሆናቸዉን መገንዘብ ያስፈልጋል።

የእኛ አንድ መሆን ከሌላዉ በተለየ ሁኔታ ካለመለያየት ዉጪ ሌሊ መፍትሔ የሌለዉ ታሪክ የተሸከምን በማስመሰል የእራሳችንን አላዋቂነትና ቸልተኝነት በመጠቀም ገፍተዉ የመበታተን ጫፍ አድርሰዉናል። የሽምብራ ኩሬም ይሁን የመቅደላዉ መስዋዕትነት፣ የአኖሌም ይሁን የአዉዜን ትርክት፣ ከማዕዲስቶች ይሁን ከእንግሊዞች፣ ከግብፆች ይሁን ከጣሊያኖች ጋር እንደ ሀገር እርስ በእርስ የተዋደቅንባቸዉ ታሪካችን ይክፋም ይልማም የዛሬዋን ሀገር ፈጥሮልናልና ያለንን ይዘን በጋራ ለጋራ ለመሄድ ካልመረጥን መጪዉ ለማናችንም ጥሩ አይሆንም።

ዘጠነኛዉ የግብፅ ባሕሪ ማምልኩ ሱልጣን በ 1320 ክርስትያኖችን እያሳድደ መሆኑን የሰማዉ የአቢሲኒያዉ ንጉስ ዓምደ ፂዮን አንደኛ ወደ ግብፅ መልህክተኞችን ይልካል። በመልህክቱም ሱልጣኑ ክርስትያኖችንን ማሳደድ ካላቆመ የአባይን ዉሃ በመጥለፍ ግብፅን በዉሃ ጥም እንሚቀጣ ብሎም በሚያስተዳድረዉ ምድር የሚገኙትን የይፋትን ሙስሊም ሱልጣን ግዛቶች በርሃብ እንደሚቀጣ የታሪክ ተመራማሪዉ ሪቻርድ ፓንክረስት ፅፈዋል (Richard Pankhurst The Ethiopian Borderlands: Essays in Regional History from Ancient times to the End of the 18th Century, 1997)።

በዚህ ዘመን እየታመስን ያለነዉ ከዛሬ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የኖረ የአቢሲኒያ ክርስትያን ንጉስ ዕምነቱን ለመጠበቅ የላከዉን መልህክትና ማስፈራሪያ ዛሬ ላይ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች እንዲቆጩበት አልያም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንዲያሻጥሩበት ሳይሆን በታሪክነቱ ተመዝግቦ በዘመናት የሚፈራረቅን የትዉልድ ፍቅርና ጥል በመረዳት ነገን በጋራና ለጋራ ያሳምሩበት ዘንድ ሊሆን ይገባል። ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችም በዚህ የሚያኮራ ታሪክ አላቸዉ።

በተመሳሳይም በበደኖ፣ በሐዉዜን፣ በጨለንቆ፣ በመተከል፣ በማይካድራ፣ በአጣዬ፣ በወልቃይት፣ በቄለም፣ በሻሸመኔና ወዘተ በቅርብና በርቀት እንደ ሀገር የወረስናቸዉን ትርክቶች ነገን ለማስተካክያ ሳይሆን ሌላ ዕልቂትን በመፍጠር ማስተካከያ ማበጀት አለመቻሉን ልንረዳ ይገባል።አቢሲኒያ ኢትዮጵያ ሆናለች። ይህ ታሪክ ነዉ። ኢትዮጵያ ግን አቢሲኒያ አይደለችም፤ ልትሆንም አትችልም። ይህን አምኖ ታሪክንና ትዉልድን ከማጎሳቆል ልንወጣ ግድ ይላል።

በህዳር ወር 1529 የተደረገዉ የሽምብራ ኩሬ ጦርነት ላይ በኢማም አህመድ ቢን ኢብራኢም አልጋዚ የተመራዉ የአዳል ኃይል በዐፄ ልብነ ድንግል የሚመራዉን የአቢሲንያ ወታደር ለማሸነፍ መቻሉን ቢሆንም ግን የንጉሱን ይዞታ መያዝ እንዳልቻሉ ሪቻርድ ፓንክረስት ፅፈዋል። ታሪክ ፀሐፊዉ በጊዜው በስልጣኔ ጠንካራ የነበረችዉ ቱርክ የአዳል ሱልጣን ሰራዊትን እሳት የሚተፋ መሳሪያ ማስታጠቋን ፅፈዋል።

ከዚያ ጦርነት በኋላ በተደረጉ ጦርነቶችም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክልል በርካታ ከተሞችና ቤተ ክርስትያኖች መቃጠላቸዉን ታሪክ መዝግቦታል። ልብነ ድንግል ሞቶ አድማስ ሰገድ ከነገሰ በኋላም ብዙ ቃጠሎ ቢደርስም በፓርቱጋሎች እርዳታ የአዳል ሱልጣን ጦር ተሸንፏል።

በ 1577 ሰርፀ ድንግል የአዳሉን መሪ ሱልጣን መሐመድ አምስተኛ ከገደለ በኋላ በቦታዉ የተተካዉ ኢማም መሐመድ ጃርሳ የአዳልን ከተማ የበቀድሞ ስሟ አዉሳ ወይም አሳይታ በማድረግ ሲወሰን ሱሱኒዮስ አንደኛም ጎንደርን የአቢሲኒያ ዋና ከተማ ያደርጋል። ጄ ስፔንሰር እንደፃፈዉ የአዳልም የጎንደርም ገዢዎች በወቅቱ እየመጣባቸዉ የነበረዉን የኦሮሞ ኃይል ለመቋቋም ማተኮሩን በመምረጣቸዉ መፋለማቸዉን ጋብ እንዳደረጉ ፅፏል (Islam in Ethiopia. By J. Spencer TRimingham. London: Oxford University Press).

ዛሬ ኦሮሞም አዳልም ጎንደርም ኢትዮጵያ ሆነዋል። ተስፋፊም በለዉ ጦረኛ፣ እስላምም በለዉ ክርስትያን፣ ሰሜኑም በለዉ ደቡቡ የአንድ ሀገር ልጆች ተብለዋል። ታሪኩ ታሪክ ሆኑ፤ መተላለቁም የትናንት ሩጫ ዉጤት ተብሎ ጊዚያችን እስኪያበቃ ድረስ ዛሬ በሕይወት ያለን ለዘመኑ የሚመጥን የመለያየትን ታሪክ ልንፅፍ ይገባል። አዉሮፓ ለሶስት ምዕተ ዓመታት በኃይማኖት ጦርነት በደም ተጨማልቀዋል። ዛሬ ግን በመላዉ አዉሮፓ እስላምና ክርስትያኑ ተከባብሮ ይኖራል። ኢትዮጵያም የዚህ ዘመን የሚመጥን ታሪክ ባለቤት በመሆን ወደፊት ትጓዝ ዘንድ ልንተባበር ግድ ይላል።

የባሪያ ንግድ በዓለም ላይ ተንሰራፍቶ ሰዎች እንደ ዕቃ በሚሸቀጡበት ዘመን ነበር አቢሲኒያም በዘመነ መሳፍንት ዉስጥ ትዳክር የነበረችዉ። ጥቁር በሁሉም የዓለም አቅጣጫ ቋንጃቸዉ ሲቆረጥና እንደ ጋማ ከብት ሲያገለግሉ በነበረበት ዘመን ተወልዶ የአንዲት ታላቅ ሀገር የመፍጠር ሕልም የነበረዉን ጎንደሬም በለዉ ቋራዊ ካሳ ኃይሉ በኃላም ንጉስ ቴዎድሮስ ሁለተኛን በታሪክ ዉስጥ ስትረዳዉ ሊሰማህ የሚገባዉ አድናቆት እንጂ ብሔርተኝነት ከሆነ ትክክል አይመስለኝም። የጦረኛዉን ናፖሊዮን ገድል አልያም የሞናሊዛን ፈጣሪ ዳቬንቺ ጥበብ ስታጣጦጥም ጎጠኝነት እንደማይሰማህ ሁሉ የትናንት ሰዎች ትልቅ ሐሳብ ሊያስኮርፍህ አይገባም። ዐፄ ቴዎድሮስ ግብፆችንም ቱርኮችንም እንግሊዞችንም የተዋጋዉ ለሀገር ሲል ነዉ።ንጉሱ ጦረኛ ብቻ ሳይሆን ሰነፍ የማይወድ ቁጡ ስለነበር ዛሬ ያሉ ሰነፎች ቢያጣጥሉት ሞኝነታቸዉና ታሪክን ማጎሳቆላቸዉ ብቻ ሳይሆን መጪዉን ትዉልድ ማደንቆራቸዉና ማስነፋቸዉ መሆኑን ሊረዱት ይገባል።

ዐፄ ቴዎድሮስ በጉልበት ጎጃምን ትግሬን ሸዋንና ወሎን ማስገበራቸዉ ምናልባት ዛሬ ጅቡቲን የመሳሰሉ በቅኝ ግዛት የተያዙ የአፍሪካ ሀገሮችን የመሳሰሉ ጥቃቅን ሀገራት ከመሆን  እንደጠበቀን መረዳት ይገባል። ፊደል ያልቆጠረ እንጭጭ ሁሉ በስመ ዐፄ የትናንትን ዉጣ ዉረድና ገድል ሁሉ በፌስታል ጠቅልሎ እንደ ቆሻሻ ለመጣል  ይሽቀዳደም ዘንድ ክፋት የተፈፀመባትን ሀገር መረዳትና ማወቅ  ግድ ይለናል።

ግራን ኮሎምቢያ ዐፄ ቴዎድሮስ በኖረበት ዘመን የነበረ ትልቅ ግዛት ነበር። ግራን ኮሎምቢያ የዛሬዋን ኮሎምቢያ ጨምሮ ቬኒዚዮላን፣ ኢኳዶርን፤ ፓናማን፣ ሰሜናዊ ፔሩን፣ምህራባዊ ጉያናን እና በከፊል ብራዚልን ያማከለ ሀገር ነበር። አንድ ላይ የሚያቆማቸዉ ጠንካራ ቴዎድሮስን መሰል ባለመኖሩ ተበታትነዉ አብዛኞቹ ዛሬ በድህነት ይዳክራሉ። መጣመር እንጂ መበጣጠስ ዳቦ እንደማይሆን አጠገባቸዉ ካለችዉ አሜሪካ ሳይማሩ የቀረ ባይመስለኝም ጅብ ከሄደ ሆነና ነገሩ ዛሬ የብዙዎቹ ዜጎች አሜሪካ በስደት ለመግባት ፍዳቸዉን ያያሉ።

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ‘የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ’ (2008) ብለዉ በሰየሙት መፅሐፋቸዉ የኦሮሞን መስፋፋት ሲገልፁ “የኦሮሞ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ነባር ሕዝቦች አንዱ ነበር እንጂ ከዉጭ በደቡብ በኩል በ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን የገባ እንዳልሆነ፥ የመስፋፋት አቅጣጫዉም ከብዙ ዘመናት ከ 16ኛዉ ክፍለ ዘመን በፊት ከሰሜን ወደ ደቡብ አቅጣጫ እንደሆነ ይገልፃሉ።” ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለፁሑፋቸዉ ምስክር ይሆናቸዉ ዘንድ ሲገልፁ “በ 13ኛዉ ክፍለ ዘመን በንጉሥ ይኩኖ አምላክ አገዛዝ ዘመን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀ መዛሙርት በሸዋ አካባቢ ክርስትናን ሲያስፋፉ በሰሜን ሸዋ ገላንና ያያ የሚባሉ ሕዝቦች ቆርኬ ለሚባል አምላክ ሲሰግዱ እንደነበር ስሰማ የ 16ኛዉ ክዘመን የኦሮሞ ፍሰት ጥያቄ ዉስጥ መግባት እንዳለበት ስለተረዳሁ በዚህ ምርምሬም መልስ ስላገኘሁ ይህንኑን አንባቢዎች ቢያዉቁት መልካም ነዉ።” ብለዋል።

ኦሮሞ የእራሱን አምላክ (Waaqayoo or Waaqa) የሚያመልክ ሕዝብ የነበረ ሲሆን በአብዛኛዉ ክርስትናም እስልምናም ፈጣሪ (God) ከሚለዉ ጋር ተመሳሳይ ነዉ። Waaqa ሁሉን ፈጣሪ ሲሆን ኃጥያትንም አይታገስም። በስሩም መለኮታዊ የሆኑ የእሱ መገለጫ አምላካቶች ወይም አያና (Ayyaana) ሲኖሩ እነኚህም ከኦሮሞ ሰዉ ጋር በአምልኮ መልህክት የሚለዋወጡት ቋሉ (Qaallu) ወይም ወንድ እና ቋሊቲ (Qaalitti) ወይም ሴት ነዉ። ቋሎ ማለት በክርስትና እንደ ጳጳስ አልያም በእስልምና እንደ ኢማም ማለት ሲሆን የሚለየዉ ግን ይህ ቃሎ አልፎ አልፎ በአያና መለኮታዊ ኃይል ራሱን ይስታል።  ቃሎ በኦሮሞ በጣሙን የተከበረና ንፁሕ ነዉ።

የጥንታዊዉን የኦሮሞ ዕምነት ከክርስትያኑ በጣሙን ከሚለይባቸዉ አንዱና ዋንኛዉ በቀደመዉ ኦሮሞ ዕምነት (Waaqeffanna) ሰዉ ከሞተ በኋላ ነፍሱ ቅጣት የሚባል አይጠብቃትም፤ ኃጥያተኛ የሆነ ሰዉ የሚቀጣዉ ምድር ላይ ነዉ። ማንም ሲሞት መንፈሱ (ekerraa) በሕይወት በኖረበት አካባቢ መኖሩን ይቀጥላል።  ስለዚህም በሕይወት ያሉት ቤተሰቦቹ አልፎ አልፎ ከብት በማረድ ስጦታ ይሰጣሉ። በተለይም በወርሃ ትህሳስ  የሙት መንፈስን (ekerraa) በዳቦ፣ በኃይብ፣ በቅቤ፣ በአረቄና በማር መቀበል የተለመደ ነዉ።

የክርስትናን መፅሐፍ ቅዱስ እና የእስልምናን ቁርሃን የታዘበ ሰዉ የኦሮሞን ቀደምት ዕምነት መፅሐፍ መጠየቁ አይቀርም። እንደ ዕምነቱ አስተምሮ ፈጣሪ ለኦሮሞ ቅዱስ መፅሐፉን ቢሰጠዉም ላም ዋጠችዉ በዚህም ፈጣሪ ተበሳጭቶ ሌላ መፅሐፍ አልሰጠዉም የሚል አፈ ታሪክ አለ (ይህ አፈ ታሪክ ሐሰት ከሆነ ከወዲሁ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ)። በወቅቱ አማኞችም ከላሟ ሆድ ዉስጥ አንጀቷን በማዉጣት ዕምነታቸዉን ተማሩባት። (አሁንም ድረስ በአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ክፍል የከብት አንጀት ለማንበብ የሚጥሩ እንዳሉ ይታወቃል።)

ይህም ሆነ ያ የቀደመዉ ዕምነት ይሁን ሌሎች የኦሮሞም ይሁን የሌሎች ብሔሮች ባሕሎች ዘመን የሚያነሳቸዉና የሚጥላቸዉ ሕሴቶች በመሆናቸዉ ትዉልድ በታሪክ ብቻ ሊያዉቃቸዉ አልያም በመኖሩ ሊተገብራቸዉ ይችላል። ባሕል ሳይለወጥ ፀንቶ የሚቀር አዉልት ይመስል ባሕልን ምክንያት በማድረግ በደምና አጥንት የተዋቀረን ሀገር በሌላ ደምና አጥንት አፍርሶ ለመስራት መመኘት ዘመኑን አይመጥንም።

ዛሬ የእኔ ቤት ያረፈበት የቴክሳስ መሬት ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት ሜክሲካዊያን ከብት ያረቡበት ነበር። ዛሬ ግን ግዛቱ የአሜሪካ ሲሆን ሜክሲካዊያን ያለ ቪዛ  ቢገቡ እንደወንጀለኛ ይቆጠራሉ። ይህ ያስቆጫል ግን ወደኃላ ሊመለስ የማይችል የትዉልድ ሂደት ነዉ። ታሪካችን ምንም ይሁን ምን የሚያዋጣን አብረን ወደፊት መጓዝ ብቻ ነዉ።

ኦሮሞ ሆንክ አማራ፣ ትግሬ ሆንክ ሱማሌ፣ ወላይታ ሆንክ አፋር፣አገዉ ሆንክ ሲዳማ፣አኙሃክ ሆንክ ጌዲዮ፣ አላባ ሆንክ አርቦሬ፣ አርጎባ ሆንክ ባቻ፣ ባስኬቶ ሆንክ ቤንች፣ በርታ ሆንክ ቦዲ፣ ቡርጂ ሆንክ ቢና፣ ጫራ ሆንክ ዳዉሮ፣ጉምዝ ሆንክ ጉራጌ፣ ኮሞ ሆንክ ኮንሶ፣ ኩሬ ሆንክ ኩናማ፣ ቃሮ ሆንክ መዠንገር፣ ሙርሲ ሆንክ ኑር፣ ሺናሻ ሆንክ ሱርማ፣ ወርጂ ሆንክ የም፣ ክርስትያን ሆንክ እስላም ሁላችንም የሚበጀን ደም ለማፍሰስና ሀገር አፍርሶ ለመተላለቅ ቢላ ማዘጋጀት ሳይሆን ሁላችንም በኢትዮጵያ ጥላ ስር አንዳችን ጤና አዳም ሌላችን ባሕር ዛፍ፤ ሌሎቻችንም የየራሳችንን ዉበትና ፀጋ እያጎለበትን በመተባበር መኖርን ዘመኑ ይጠይቃልና በታሪክ ቁርሾ የሚከፋፍሉን አእምቢ እንላቸዉ ዘንድ ይገባል።

ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትኑርልን። አሜን።

(ዶ/ር መኮንን ብሩ)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.