ሻለቃ ሰከን ይበሉ እንጂ! – ባይሳ ዋቅ-ወያ

bayisa wak woya `
ባይሳ ዋቅ-ወያ

ውድ ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ!

ባለፈው ዓመት ያገራችንን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክተው ላቀረቡት አንድ ጽሁፍ “ከጅብ ጅማት የተሠራ ክራር ቅኝቱ እንብላው እንብላው ብቻ ነው” በሚል ርዕስ መልስ ሰጥቼዎት ነበር። ባለፈው ሳምንት ደግሞ ከጋዜጠኛ አበበ በለውና ቀጥሎም በኢትዮ 360 ካሃብታሙ አያሌው ጋር ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ሰምቼ፣ ዛሬ አገራችን ካለችበት ሁኔታ ጋር ሳመላክት ዝም ብዬ ማለፉ ከበደኝ። በኔ ግምት፣ የአሁኑ ቃለ መጠይቅዎ ከመቼውም ጊዜ በላይ እውነተኛ ማንነትዎን ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠ ይመስለኛል። ሌሎችም የርስዎን ጽንፈኝነት የሚደግፉ ግለሰቦች “አይዞዎት” እያሉ ለድጋፍ ሰልፍ ወጥተዋል። ሁላችሁም ከአንድ ወንዝ ስለ ተቀዳችሁ፣ በአንድ ድንጋይ፣ ከቻልኩ አሳምኜ ልገድላችሁ (ሃሳብችሁን ማለቴ ነው) ካልቻልኩ ደግሞ ለጊዜውም ቢሆን ላደነዝዛችሁ ከማለት ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ ወሰንኩ። በዚህ ጽሁፌ “ሻለቃ” እያልኩ ደጋግሜ ባነሳ እስዎን ብቻ ማለቴ ሳይሆን ተመሳሳይ ጽንፈኝነትን የሚያስተናግዱትን መሰሎችዎን ጭምር መሆኑ ከወዲሁ ይታወቅልኝ። ሳይታክተኝ የምዋጋው ጽንፈኛ አስተሳሰብዎን እንጂ እስዎን በግል አይደለም። የጠላሁት የጥላቻና የአክራሪ ብሔርተኝነት የቅስቀሳ ንግግርዎን እንጂ ሃሳብዎን በነጻ የማቅረብ መብትንማ በሙሉ ልቤ እደግፋለሁ። እሟገትልዎታለሁም።

ሻለቃ! ያሁኑ ቃለ መጠይቅዎ ያው እንደ ተለመደው፣ ዝም ብሎ ኦሮሞ-ጠል እና በተፈጠረው አገራዊ ፖሊቲካና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ አሳብበው የራስዎንና የመሰሎችዎን የፖሊቲካ ሥልጣን ጥማት ለማርካት ተብሎ የታቀደ ቢሆን ኖሮ፣ “እኚህ ሰውዬ ምነው በዚህ ዕድሜ ስለ ብሔራዊ ዕርቅ፣ ካልሆነም ደግሞ ለወዲያኛው ዓለም ቤታቸው ስላላቸው ዝግጅት እንደ ማውራት፣ በሆነ ባልሆነው ገብተው ለምን ይቀባጥራሉ” ብዬ አልፍ ነበር። የቃለ መጠየቅዎ ይዘት ግን በርግጥም እጅግ በጣም አሳሰበኝ! አገራችን የምትገኝበት ማህበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ እንኳን እኛን ልጆቿን ቀርቶ፣ ጎረቤቶቻችንና የዓለሙን ማህበረሰብ ሳይቀር እያሳሰበ ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ ጽንፍ የረገጠውን አስተሳስብና በጽንፈኞች ቅስቀሳ ምክንያት ተከፋፍሎ በዝቅተኛ ደረጃም ቢሆን መገዳደልና መፈነቃቀል የጀመረውን ሕዝባችንን በአጠቃላይም ይህንን ወደ የርስ በርስ ግጭት ሊያመራ የሚችለውን የሕዝቦችን አለመግባባት እንዴት አድርገን በጋራ እናረጋጋው እንደ ማለት፣ በነባልባሉ ላይ ቤንዚን መርጨትዎ ዕንቅልፍ የሚነሳ ነው። ይመኑኝ ሻለቃ፣ እስዎም ራስዎ ቃለ መጠይቅዎን እንደ ገና በሰከነ መንፈስ ቢያዳምጡትና ቢያላምጡት በሰላም ተኝተው የሚያድሩ አይመስለኝም። የአስተሳሰብ ክራርዎ ከጅብ ጅማት የተሠራ ካልሆነ በስተቀር!

ሻለቃ! ወቅታዊ ችግሮቻችንን ለስዎ ማስረዳት ለቀባሪ የማርዳት ያህል ትርጉም አልባ ይሆንብኛል። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በአብዛኛው የዛሬው የቀውስ ምርታችን ላይ የርስዎ አሻራ አለበትና! አገራችን ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መልኩ በማህበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች። ዕድሜ ለስዎና እስዎን ለመሳሰሉ የአማራ የኦሮሞና የትግራይ ብሔር ጽንፈኞች እንጂ፣ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ ትናንት በመልካም ጎረቤትነት አብረው ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬ በጎሪጥ ከመተያየት አልፈው መጎዳዳት ከጀመሩ ሰንብተዋል። የበላይነት እንጂ እኩልነት ጭቆና የሚመስላቸው አንዳንድ ቡድኖች በሚዘሩት የጽንፈኛ ብሔርተኝነት መርዝ ሳቢያ፣ ወገን በወገን ላይ ሲነሳሳ ማየት እየተለመደ መጥቷል። በአገራችን “ግልጽነት” ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅግ ውድ ሸቀጥ ሆኗል። እንደ ጠላ ቤት በየሠፈሩ የፈሉት የዩቲዩብና የፌስ ቡክ መደብሮች ቀኑን ሙሉ በሚዘሩት በአብዛኛው የውሸት፣ አለያም እጅግ በጣም በተጋነነ “ዜና” ምክንያት የዋሁ ማሕበረሰባችን የመረጃዎቹን ትክክለኛነት እንኳ ሳያረጋግጥ እንዳለ እየተጋተው ይገኛል። የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህን የሚዲያ አውታሮች ከሞላ ጎደል የሚያንቀሳቅሱት የአማርኛ ተናጋሪው ጽንፈኞች ስለሆኑና ሰፋ ያለ ተደራሽነት ስላላቸው አብዛኛውን ሕዝባችንን ወገናዊ በሆነ አስተሳሰብ አስታጥቀው አንዱን ሕዝብ በሌላው ላይ ለማነሳሳት ችለዋል። ግልጽነትንና እውነተኛ ዘገባን በማቅረብ መንግሥትም ከነዚህ ወፍ ዘራሽ ማሕበረሰባዊ ሚዲያዎች እምብዛም ተሽሎ አልተገኘም።

የተሳሳተን መረጃ ለሕዝብ አቅርቦ አስተሳሰብን ከመሞረድ የከፋ ወንጀል የለም። የታሪክ አጋጣሚን ተጠቅሞ በተገኘ የሚዲያ ባለቤትነት የመላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ብሶት ለሕዝብ አቅርቦ መፍትሔ ፍለጋው ላይ ከመትጋት ይልቅ፣ የአገሩ ሕዝብ ሁሉ ተስማምቶ አንድን ብሔር ብቻ ለይቶ ለማጥቃት እንደ ተዘጋጀ አድርጎ በማቅረብ ሕዝብን በሕዝብ ላይ እንዲነሳሳ ማድረግ ግን ወንጀሉን ከሚፈጽሙ እኩል ወንጀለኛ ያስደርጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሶስት ዓመታት ደረጃው ይለያይ እንጂ ሰብዓዊና የቡድን መብቱ  ያልተጣሰበት ሕዝብ የለም ማለት ይቻላል። ወደ ሶስት ሚሊዮን ከሚጠጉ ተፈናቃዮች ውስጥ የኦሮሞ፣ የሶማሌና የጊዴኦ ተፈናቃዮች በቁጥር የመጀመርያውን ደረጃ ቆይተው ኖሮ፣ አሁን በቅርቡ በትግራይ ክልል ውስጥ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ደግሞ 1.06 ሚሊዮን ሰላማዊ ሕዝብና በአማራ ክልል ውስጥ ደግሞ አሥራ አራት ሺህ ዜጎች መፈናቀላቸውን የተባበሩ መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽን አረጋግጧል። በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ላለፉት ሶስት ዓመታት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ምክንያት የሚፈናቀለው፣ የሚታሠረውና የሚገደለው ዜጋ ቁጥር እጅግ ብዙ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የራሳቸው የሆነ የማሕበረሰባዊ ሚዲያ ተቋም ስለሌላቸውና ስለማይዘገብ ነው እንጂ በቅርቡ በአፋርና በሶማሌ ክልል መካከል በተካሄደውና እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ዜጎች ከሁለቱም ወገን ተፈናቅለዋል፣ ብዙዎች ተገድለዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ከላይ እንደ ጠቀስኩት አብዛኛው ማህበረሰባዊ ሚዲያችን በዋናነት በአማርኛ ተናጋሪው፣ ዝቅ ብሎ ደግሞ በኦሮሚኛና ትግርኛ ተናጋሪ ጽንፈኛ ብሄርተኞች በመያዛቸው ምክንያት አገራችን ውስጥ መፈነቃቀሉና መገዳደሉ በነዚህ ሶስት ሕዝቦች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው የሚል የተሳሳተ ግምት ላይ ደርሷል። እርስዎም ለዚህ ነው እንግዲህ ወገብዎን ይዘው የአማራ ሕዝብ ብቻ ከሌሎች ተነጥሎ እየተጠቃ ስለሆነ “ጠንካራ ድርጅት ፈጥረን የቀድሞ ርስቱንና ገናናነቱን በማስመለስ መብቱን ማስከበር አለብን” እያሉ የሚወትውቱት!

ሻለቃ!  በኔ ግምት ትልቁ ያገራችን ችግር እስዎን የመሳሰሉ ጽንፈኞች የሚዘሩት “የድሮ ዝናን ለማስመለስ” የሚለው ኋላ ቀርና ፋሺስታዊ አስተሳሰብ ነው። ከታሪክ እንደ ተማርነው ከሆነ ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻና መድረሻ ሆኖ ከኸያ ሚሊዮን በላይ ሕዝቦች እንዲያልቁ የተደረገው ሂትለርና ደቀ መዛሙርቱ “የጀርመንን ገናናነት መልሶ ለማስፈን” ሲባል የነደፉት መርሃ ግብር ነበር። በግሌ ካስተዋልኳቸው ጦርነቶች መካከል ደግሞ የዩጎዝላቪያው ጦርነት የተቀስቀሰውና እዚያ አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰው ሚሎሼቪች “የቀድሞ የሴርቢያን ገናናነት መስሎ ለማስፈን” በማለት ባካሄደው የዕብደት ፖሊቲካ ነበር። ለዚህ ነው ዛሬ እስዎም፣ “ጠንካራ ድርጅት አቋቁመን ወለጋና ኢሉባቦርን ሳይቀር አስመልሰን” ወዘተ ሲሉ መልክዎ ጠቆረ እንጂ ሚሎሼቪች ራሱ አሰቃቂውን ጦርነት ሊጀምር አካባቢ በዩጎዝላቪያ ቲቪ ቀርቦ የሚደሰኩር መስለው ነው የታዩኝ። አያድርገው እንጂ እስዎ የሚያቋቁሙት ጠንካራ የርስት አስመላሽና የቀድሞ ዝናን መልሶ የሚያጎናጽፍ ድርጅት ተፈጥሮ በስዎ ፊታውራሪነት ጦርነቱ ቢጀመር፣ የሚያልቀው ሕዝብና የሚወድመው ንብረት እየታየኝ፣ ይህ ዕብደት በስዎና በስዎ ዙርያ ብቻ ተወስኖ ይቅር ዘንድ ዘወትር እጸልያለሁ።

ሻለቃ፣ የእርስዎ ሰዓት መቁጠር ያቆመው የካቲት ኸያ አራት ቀን 1967 ዓ/ም እኩለ ሌሊት ላይ ይመስለኛል። ባይሆን ኖሮማ፣ በነጋታው የካቲት ኸያ አምስት ቀን 1967 ዓ/ም ላይ የታወጀውና የምዕተ-ዓመቱ ሥር ነቀል ዓዋጅ ተብሎ የተነገረለት የመሬት ላራሹ ዓዋጅ እኮ በተለያዩ የታሪክ ኣጋጣሚዎች ሰበብ፣ በአብዛኛው የአማርኛ ተናጋሪ ኤሊት የሆኑ፣ አርበኛና አርበኛ ተብዬዎች እንዲሁም አፍቃሬ ቄሳሮች ሁሉ ሳይቀሩ ወደ ደቡብ ሄደው ከነዋሪው ሕዝብ መሬቱን ቀምተው ገባር ያደረጉበትን አስከፊ ሥርዓትን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ ከሰማኒያ በመቶ በላይ የሆነውን አርሶ አደሩን የደቡብ ሕዝብ ከባርነት ነጻ ስላወጣው ዓዋጅ ይዘት በቅጡ ተረድተው ዛሬ “ርስት ለማስመለስ” ጠንካራ ድርጅት ለማቋቋም ደፋ ቀና አይሉም ነበር። ለዚያውም በዚህ ዕድሜ! የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ደግሞ፣ የድሮ ጠቅላይ ግዛቶች ፈርሰው አዳዲስ አስተዳደራዊ ድንበሮች ሲከለሉ አንዳንድ ግዛቶች ጥንት ከነበሩበት አካል ተነጥለው ወይ ራሳቸውን እንዲችሉ ወይም ደግሞ ከሌላ አካል ጋር እንዲዳበሉ ተደርገዋል። ድርጊቱ ትክክል ነው ወይም አይደለም ብዬ ለመሞገት ሳይሆን፣ ግዛቶቹ በኢትዮጵያ ወሰን ውስጥ እስከሆኑ ድረስ፤ መቆርቆር ያለብን ስለነዚህ ሕዝቦች እዚያው ባሉበት ቦታ ሰብዓዊና ቡድናዊ መብታቸው እንዳይጣስ መታገል ነው እንጂ፣ “የለም ይህ ቦታ እኮ ድሮ በዚህኛው ግዛት ሥር ነበርና ወደ ቀድሞ ግዛቱ መመለስ አለበት” ብሎ ለጦርነት ቅስቀሳ መጀመር አነሰ ቢባል ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ይመስለኛል።

የሩቁ ይቅርና፣ ሻለቃ! የዛሬዎቹ የጋምቤላና የጉሙዝ እንዲሁም የሃረሪና የሱማሌ ክልሎች ትናንት እኮ በአብዛኛው ኦሮሞዎች በሚኖሩበት ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ ነበሩ። ዛሬ ግን እነዚህ ሕዝቦች ከኦሮሚያ ክልል ውጭ የየራሳቸውን ክልል መሥርተው ከፋም ለማም በራሳቸው ቋንቋ እየተናገሩ የየብሔራቸውን ባሕልና ቋንቋ እያሳደጉ አመርቂም ባይሆን ራሳቸውን  በራሳቸው እያስተደዳደሩ ነው። በርስዎ የርስት ስሌት እንግዲህ ይህ መሆን ያልነበረበት ክስተት ስለሆነ በርግጥም አይመችዎትም። በኔ ግምት ግን ዛሬ ለምሳሌ የኦሮሞ ጽንፈኞች ጠንካራ የርስት አስመላሽ ድርጅት ፈጥረን እነዚህን “የቀድሞ የኦሮሞ ርስቶች” ወደ ቀድሞ ባለቤቱ ወደ ሆነው የኦሮሚያ ክልል እንመልስ ብለው ቅስቀሳ ቢጀምሩ ያላንዳች ማወላወል እኮንናቸዋለሁ። እነዚህ ሕዝቦች እኮ አሁን ባሉበት ክልል ውስጥ መሆን አንፈልግም፣ መብታችንም አልተጠበቀልንም ካሉ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ባስቀመጠላቸው መብት መሠረት የራሳቸውን ክልል ወይም አውራጃ ሊፈጥሩ ይችላል። እኔና እስዎ መታገል ያለብን እንግዲህ ሕዝቦቹ፣ ይህ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው እንጂ፣ የዋሁን ሕዝብ “ተነስ” “የቀድሞ ርስትህን አስመልስ” ብሎ ለጦርነት ማዘጋጀት፣ እንኳን ከስዎ የጦርነትን ክፋት በቲዎሪም ሆነ በተግባር ከሚያዉቁ የጦር መኮንን ቀርቶ፣ ከእንደኔ ዓይነቱ አንድም ቀን ነፍጥን ካላነገተ ሰላማዊ ግለሰብም አይጠበቅም። የርስ በርስ ጦርነት የትም ቦታ ቢሆን ጥፋትን እንጂ ልማትን አያመጣምና! እርስዎም ቢያንስ ቢያንስ ከኤርትራ ተልዕኮዎ ይህንን መማር ነበረብዎት!

ከብዙዎቹ ቃለ መጠይቅዎ እንደ ገመገምኩት ከሆነ፣ እርስዎ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሲታገሉና ሲያታግሉ የነበሩት የወያኔ መንግሥት ፈርሶ በሱ ቦታ በሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት ውስጥ አንድ ትልቅ የአመራር ቦታ ለመውሰድ ነበር። ታሪክ ደግሞ የራሱን ቦይ ተከትሎ ማንኛችንም ባላሰብነው መንገድ ከዚያው ከኢሕዴግ ሰፈር የወጡ ቡድኖች የሥልጣን መንበሩን ተረከቡትና የሥልጣን ምኞትዎን አጨለሙት። ከቃለ መጠየቅዎ እንደ ተረዳሁት ከሆነ፣ ያኔ ከተለያዩ የተቃዋሚ ቡድኖች ጋር በየጊዜው እየተገናኛችሁ ስለሽግግር መንግሥቱ እንደምትወያዩና በአንድ ወቅት ላይ አብረዎት ትዶልቱ ከነበሩ ታዋቂ ፖሊቲከኞች መካከል ለምሳሌ እነ ኦቦ ሌንጮ ለታን የመሳሰሉ ግለሰቦች እንዳሉበትና ኋላ ደግሞ ክደዋችሁ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የዓቢይ ደጋፊ ሆነው መገኘታቸው እጅግ በጣም አናድዶዎታል። አዎ! የነደፉት ፕሮጄክት ሳይተገበር ሲቀር ማናደዱ ተፈጥሮያዊ ስለሆነ ንዴትዎ ይገባኛል። እስቲ በቅንፍ ውስጥ የሚከተለውን ላስቀምጥ፣

በኔ ግምት ግን፣ ስለሌሎቹ ግለሰቦች ማንነት እምብዛም ባላውቅም፣ ኦቦ ሌንጮን በተወሰነ ደረጃ ስለማውቀው፣ ምናልባት እስዎ ያኔ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእኩልነት ስለሚኖሩባት ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያ ሲሰብኩ ከጎንዎ ቆሞ ካልሆነ በስተቀር ዛሬ ጭንብልዎን አውልቀው እውነተኛው የጽንፈኛ መልክዎ በአደባባይ ሲገለጥ እንዳየነው አስቀድሞ ቢያውቅ ኖሮ፣ ኦቦ ሌንጮ በምንም ተዓምር ከስዎ ጋር እንኳን በአንድ የጋራ ውይይት መድረክ ቀርቦ መታየት ይቅርና ባካባቢዎ ዝር ለማለት ስብዕናው የሚፈቅድለት አይመስለኝም። አዎ! እስዎ ገና አሁን ሀሁ እያሉ የሚያጠኑትን የጽንፈኛ ብሔርተኝነት 101 ኮርስ፣ ኦቦ ሌንጮ ከአምሳ ዓመት በፊት አንግቦት የትጥቅ ትግል የጀመረና፣ ከዓመታት በኋላ የአሓዳዊው ሥርዓት ፈርሶ የኢትዮጵያን ሕዝብች እኩልነት ሊያረጋግጥ የሚችል የለውጥ አጋጣሚ ሲገኝ ደግሞ፣ የትግል ጓደኞቹን በሙሉ አሳምኖ፣ የኦሮሞ ሕዝቦች፣ ልክ እንደ ሌሎቹ ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትንም የፌዴራል ሥርዓት ለመመሥረት የሚያስችል የሽግግር መንግሥት ቻርተር አዘጋጅቶ፣ መለያየትን ሳይሆን አብሮነትን አንግቦ ለመታገል ፊንፊኔ የገባ ሰው ነው። የነደፈውን የሽግግር ቻርተር ተግባራዊነት ሳያይ በወያኔ ተገፍቶ ከወጣ በኋላ እንኳ፣ ለኸያ ሰባት ዓመታት ሙሉ ስለ እንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንደ ሰበከ፣ ወያኔ ከሥልጣን ስትወርድ ደግም ከሌሎች ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት በቆራጥነት ለመታገል “እስዎን ክዶ” ወደ አዲስ አበባ ያመራ የዘመናችን ታላቅ የፖሊቲካ ምሁር ነው። ዛሬ እስዎ ከኢትዮጵያዊነት መድረክ ወርደውና የጠባብ ብሔርተኝነት 101 ኮርስ በመውሰድና “የድሮ ርስት የሚያስመልስ ጠንካራ” ድርጅት ለማቋቋም ደፋ ቀና ሲሉ፣ ኦቦ ሌንጮ ግን ከፖሊቲካ ንቁ ተሳታፊነት በጡረታ ተገልለው በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ፣ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ እናም ለሁሉ አቀፍ ብሔራዊ ምክክር (All-inclusive National Dialogue) እጅግ በጣም ጉልህ የሆነ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ታላቅ የዘመኑ የፖሊቲካ ሰው ናቸው። ለዚህ ነው እስዎንና ኦቦ ሌንጮን የሚያገናኝ አንዳችም የአስተሳሰብም ሆነ የዓላማ ተመሳሳይነት የለም ያልኩት! ቅንፉን ዘግቻለሁ።

አዎ ሻለቃዬ! ችግርዎ ይገባኛል። ጀማሪ ብሔርተኛ ስለሆኑ አይፈረድብዎትም። ለዘመናት “የኢትዮያዊነት ደረጃ መዳቢ እኛ ብቻ ነን” ብለው ሌሎችን በዚያ መለኪያ እየገመቱ፣ “ኑ እኛ ባስቀመጥንላችሁ የኢትዮጵያዊነት መለኪያ ተለክታችሁ አብረ እንኑር” ሲሉ ከነበሩበት የኢትዮጵያዊነት ከፍታ ወደ ታች ዘቅጠው “የአማራ ሕዝብ ጠንካራ ድርጅት ፈጥሮ የጥንት ግዛቱን መመለስ አለበት” ብለው ሲሰብኩ መስማት ለጆሮም ይከብዳል። ምንም ቢሆን የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ይሻልዎታል። ያኔ የመገንጠልን መሪህ አንግበው በየዱሩ ይታገሉ የነበሩ ከላይ የጠቀስኳቸው ብሔራዊ ድርጅቶች እኮ ኢትዮጵያ በፌዴራሊዝም ሥርዓት እስከተዳደረች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እኩልነት በተግባር እስከ ታየ ድረስ ለመገንጠል መፋለሙ አስፈላጊ አይደለም ብለው ወደ ሰላማዊ ትግል ሜዳ ሲመጡ እስዎ ግን፣ “የለም ይህ ለአሥር ክልሎች ተስማሚ የሆነው አስተዳደራዊ አወቃቀር አይመቸንምና ጠንካራ ድርጅት ፈጥረን የድሮ ዝናችንን እናስመልስ” ብለው በአደባባይ ሲፎከሩ የሰሙ የነዚህ ብሔርተኛ ድርጅቶች አመራር፣ “እኛንም ያኔ እንደዚሁ አርጎን ነበር፣ ቆይተን በሂደት ስናየውና በሰላምና በእኩልነት አብሮ የመኖር አጋጣሚው ሲፈጠር ግን የመገንጠሉን መንገድ ትተን ያለፈውን የተዛባን የታሪክ ፍትሕ እያስተካከልን አዲሲቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ እንገነባታለን” ብለን ተመልሰናል ብለው ሲያሾብዎት ይታየኛል። ነገሩ ጓደኛዬ መክብብ “ያየ ሲሄድ የሰማ ይመጣል” የሚለው ዓይነት መሆኑ ነው።

የኔና የስዎ ትውልድ ማድረግ ያለብን፣

በመጀመርያ ደረጃ እኔና እስዎ የሕይወት ሎተሪ ከወጣላቸው እፍኝ ከማይሞሉ ኢትዮጵያውያን መካከል የምንሰለፍ ነን። የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ፣ ጓደኞቻችን በተለያየ ምክንያት ከጎናችን ያለዕድሜያቸው ሲቀጠፉ እኔና እስዎ ግን የዕድሜ ባለጸጋ ብቻ ሳይሆን፣ በምቾት አገር እየኖርን ልጆቻችንንም በቅንጦት አሳድገን አስተምረን ለመዳር የበቃን ነን። የኛን ዓይነት ዕድል ያላገኙ አብዛኛው ወገኖቻችን ደግሞ እኔና እስዎ ከዓመታት በፊት ትተናቸው የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ወደ ባሕር ማዶ ስናቀና ዛሬም እዚያው እነበሩበት የድህነት አዙሪት ውስጥ እንደ ተዘፈቁ ነው ያሉት። እንደ ደንቡ ቢሆን ኖሮማ እኔና እስዎን የመሳሰልን ባለ ሎተሪዎች ወደ አገራችን ተመልሰን የቀሰምነውንና ያካበትነውን ልምድ ለሕዝባችን አጋርተን ማበልጸግ እንኳ ባንችል ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ ጠግበው እንዲያድሩ ማድረግ በቻልን ነበር። ባለማድረጋችን ማፈር ነበረብን። ከማሳፈር አልፎ እጅግ በጣም የሚያናድደው ደግሞ፣ እዚህ ባህር ማዶ የተደላደለ ኑሮ እየኖርን፣ አገር ቤት ያለውን ቀውስ ለማርገብ ሳይሆን የጽንፈኛ መፈክር አስነግበን ወጣቱን ለአስከፊ የርስ በርስ ጦርነት “ተነስ ርስትህን አስመልስ” ብሎ መቀስቀሱ ነው። ለዚያውም ራሳችንም ሆንን ልጆቻችን ለማይካፈሉበት የርስ በርስ ጦርነት! ኃላፊነት የጎደለውና ታሪክም ይቅር የማይለን ወንጀል!

እንደ እኔና እስዎ ዓይነት ዕድሜ ጠገቦች መስበክና መሞገት የነበረብን ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት መከበር እንጂ በጽንፈኞቹ የማህበረሰባዊ ሚዲያ ተቋማት ዋልታ ረገጥ የተሳሳተ ዘገባ ብቻ ተመርተን የየራሳችንን ብሔር ብቻ ነጥለን በማውጣት ሙግት መግጠም አይመጥነንም ባይ ነኝ። በኔ እምነት የሰው ልጅ ነፍስ በምንም መልኩና ለማንኛውም ምድራዊ ዓላማ መጥፋት የለበትም። ማንም ያድርገው ማን፣ በጦር ሜዳ በሁለት በታጠቁ ቡድኖች መካከል ከሚደረገው መገዳደል ውጭ፣ ያለፍርድ ሂደት የሰላማዊ ሰውን ነፍስ ያጠፋ ግለሰብም ሆነ መንግሥት በሕጉ መሠረት መቀጣት አለበት። ስለሆነም፣ በኔና በርስዎ ዕድሜ ያለን ኢትዮጵያውያን ከልባችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የምንወድ ከሆነ፣ ሙሉ ጊዜያችንን ማዋል ያለብን፣ አገሪቷን እያናወጠ ያለውን አገር አቀፋዊ ውጥረት እንዴት ማርገብ እንደምንችል መመካከር ነው። መመካከር ስል ደግሞ፣ ይህ ሁሌ እስዎ የሚያነሱት የሽግግር መንግሥት ዓይነት ማለቴ አይደለም። ይህ የሥልጣን ጥያቄ ነው። የሥልጣን ወንበር ላይ ካልተሆነ ደግሞ ለውጥ ሊመጣ አይችልም የሚለውን ያረጀ አስተሳሰብ ወደ ጎን ትተን ታች ወርደን (grassroots level) ሕዝቦች ልዩነቶቻቸውን አቻችለው እንዴት አብረው በፌዴራላዊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም መኖር እንደሚችሉ ማስተማር አለብን። ሁሌም እንደምለው፣ እስዎን የመሳሰሉ የብሔር ጽንፈኞች በሚረጩት መርዝ ተመርዘው ነው እንጂ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል አንዳችም ዓይነት ልዩነት ወይም ጥላቻ ኖሮ አያውቅም። ይህ ማለት ግን በጽንፈኞች ቅስቀሳ ምክንያት ዓይናቸው ታውሮ ለዘመናት በሰላምና በመልካም ጉርብትና አብረው በኖሩት የሌላ ብሔር ተወላጅ ላይ ቢላ አያነሱም ማለት አይደለም። ለዘመናት አብሮ በጓደኝነት መኖር ብቻ ሳይሆን በአማችነትና በአበልጅነት እኔ ልብስ አንተ ትብስ ተባብለው በፍቅር ይኖሩ የነበሩ ዩጎዝላቮች፣ በብሔር ጽንፈኞች ቅስቀሳ ምክንያት በርስ በርስ ላይ ተነሳስተው ሲተላለቁ እዚያው በቦታው ሆኜ አይቻለሁና።

ይህን ካልኩ ዘንዳ ሻለቃዬ አንድ በጣም ቀላል የሆነ፣ ግን ደግሞ ያለማቋረጥ የሚከነክነኝን ነገር ልጠይቅዎ። ያደራጁትን ጠንካራ ጦርዎን ይዘው ወደ ወለጋ ከማቅናትዎ በፊት ስለ ጠቅላላው የውጊያው ሂደት ያለዎትን ፍኖተ ካርታ በጭንቅላቴ ለመቅረጽ ብሞክር ብሞክር አልታይህ ስላለኝ ነው። ምናልባት እንደስዎ የጦር መኮንን ስላልሆንኩ ይሆናል መሰለኝ ይህንን ከዘጠና ዘጠኝ በመቶ በላይ የኦሮሞ ብሔር የሚኖርበትን ወለጋን እንዴት አድርገው ወደ አማራ ርስትነት እንደሚያጠቃልሉ ባስብ ባስብ አልመጣልህ አለኝ። በውጭ ወራሪ ኃይል ለምሳሌ በቅርቡ በሱዳን የተወረረውን በአማራ ክልል ውስጥ ያለውን የኢትዮጵያን መሬት ወራሪውን አሸንፎ የተወሰደን ግዛት መልሶ ወደ አማራ ክልል መመለስ ይቻላል። ያ ይገባኛል። የወለጋው ጉዳይ ግን ምናልባትም ከዚያ ክፍለ ሃገር ስለሆንኩ ነው መሰለኝ ከስዎ ወረራ በኋላ ዘመዶቼን ምን እንደሚገጥማቸው መገመት አቃተኝ። ግዛት እኮ ጨርቅ አይደል ወለጋን ቆርጠው አማራ ክልል ላይ አይቀጥሉት ነገር! ወይስ ሕዝቡን በጉልበት ካስገበሩ በኋላ በንጉሡ ዘመን እንደ ነበረው ከአማራ ክልል አስተዳዳሪዎች መርጠው ሊልኩባችወ ነው? ወይስ የኦሮሞዎቹን ደም በቀሰም መጥጦ አውጥቶ በአማራ ደም መተካት? ወይስ ሕዝቡ በትውልድ ኦሮሞ እንደሆነ ይቀርና መሬቱ ብቻ ግን ወደ አማራ ክልል ይጠቃለላል? ወይስ ያንን ያክል ሕዝብ አፈናቅለው ወደ ሌላ የኦሮሚያ ክልል ከሰደዱ በኋላ መሬቱን በአማራ ብሔር ተወላጅ ሊሞሉት ነው? ርስት ማስመለስ የሚሉት ግራ የገባ ነገር!

የወለጋ ሕዝብ እንኳን እንግዳ ይቅርና ዛፍን እንኳ ያከብራል ተብሎ ይነገርለታል። ሆኖም ግን ሻለቃ፣ እንደው ሲያስቡት በርስዎ ወይም በልጅዎ የሚመራው የአማራ ርስት አስመላሽ ጦር ሲዘመትበት ዘመዶቼ በሙሉ በኦዳ ዛፍ ሥር ተሰብስበው “እንኳን ደርሳችሁ ከሺመልስ አብዲሳ ጨቋኝ አስተዳደር ገላገላችሁን” ብሎ እጁን ዘርግቶ አንጮቴና ጩኮ በመሶብ አቅርቦ የሚቀበላችሁ ይመስላዎታል? እኔን አይመስለኝም። ለማንኛውም በፍቅርም ሆነ በጠብ ሲቀበሏችሁ፣ የወረራዎን ዓላማ ኦሮሚኛ ብቻ ለሚናገረው የወለጋ ሕዝብ ለማስረዳት እንዲረዳዎት የርስት አስመላሽ ጦርዎን አባላት ሲያሠለጥኑ ቢያንስ ቢያንስ ሶስት ወር የሚፈጅ መሠረታዊ የኦሮሚኛ ቋንቋ ኮርስ ቢሠጧቸው ጥሩ ይመስለኛል። አለበለዚያ፣ ሊያበሉን ነው ብላችሁ ቁጭ ስትሉ እንዳይበሏችሁ ለማለት ያህል ነው። አንድ ሕዝብ እኮ የፈለገውን ያህል እንግዳ አክባሪና ደግ ነው ቢባልም፣ ጦር ይዞ የመጣበትን ጸጉረ ለውጥ ኃይል፣ ዱላ ወይም ጦሩን ይዞ በመውጣት ቄዬውንና ማህበረሰቡን ከወራሪው ኃይል ይከላከላል እንጂ ቄጤማ ጎዝጉዞ “በሞቴ ብሉልኝ ጠጡልኝ” ብሎ ወደ ጎጆው አያስገባም። በሌላ አነጋገር፣ የርስት አስመላሹ ጦርዎና “በርስትዎ ላይ በሕገ ወጥነት ሰፍሮ የሚገኘው” የወለጋ ሕዝብ ሁለታችሁም ያው ኢትዮጵያውያን ስለ ሆናችሁ፣ የርስ በርስ ጦርነት ትጀምራላችሁ ማለት ነው። ፍርሃቴ አሁን ገባዎት?

ይልቅስ ማድረግ ያለብን፣

ሻለቃዬ! ዕድሜ ጠገብ፣ አምላክ በቸርነቱ ከሙሉ ጤና ጋር ያኖረን እንደኔና እስዎ ያለን ሰዎች ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተሻለ ኑሮ የምንኖር ዕድለኛ ፍጡራን፣ ለሁሉም ነገር አምላክን እያመሰገንን፣ ሰላምና መረጋጋትን ላጣች አገራችን የተማርነውንና በሙያችን በየዓለም አካባቢ የቀሰምነውን ልምድና ዕውቀት ወደ አገራችን አምጥተን፣ ሰላም የሚሠፍንበትን መንገድ ማስተማር ነው እንጂ “ተነስ” “ግደል” “ውጋው” “ቁረጥ” “ተደራጅና ያንን የጥንት ያባቶችህን ርስት አስመልስ” ማለት አይጠበቅብንም። ደጋግመው እንደነገሩን ከሆነ በአንድ ሁለት የአፍሪካ አገራት “ግጭትን በማስወገድ” ረገድ ልምድ አለዎትና፣ ይህንን ልምድዎን በኢትዮጵያ ምድር ላይ በተግባር ቢያውሉ አምላክም ደስ የሚሰኝብዎት ይመስለኛል። አለበለዚያ ግን፣ እኔና እርስዎ ጥላቻን ወርሰን ጥላቻን ማውረስ፣ ድህነትን ወርሰን ድህነትን ማውረሳችን አንሶ፣ በድህነቱ እንኳ የሰላም ዕንቅልፍ እንዳያድር ሕዝባችንን “ለርስት ማስመለስ” ጦርነት እንዲነሳሳ መቀስቀስ እጅጉን ሊያሳፍረን ይገባል። ያኔ በጡንቻ እንጂ በጭንቅላት በማናሰብበት የወጣትነት ዘመን ደብተርና ብዕራችንን አንግተን የፊውዳሉን ሥርዓት “ስናርበደብድ” በአገሪቱ የፖሊቲካ ባህልም ሆነ ልምድ ያለው የፖሊቲካ ፓርቲ ባለመኖሩ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የምትመራበትንና ተግባራዊ የሆነ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ፕሮግራም ለመንደፍ ባለመቻላችን አገራችንን ከነበረችበት ቀውስ ልናድናት አልቻልንም። ዛሬ ግን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ፣ በየዩኒቬርሲቲውና በሥራም ዓለም የቀሰምናቸውንና ያካበትናቸውን ልምዶች ወደ አገራችን አምጥተን፣ የሕዝባችንን ኑሮ የምናሻሻልበትን ሁኔታ ተመቻችቶልን እያለ፣ ጥንት አንግበን እንሰለፍ ከነበረው ዓለም አቀፋዊ ራዕይን ካዘለ መፈክራችን እንኳ ዝቅ ብለን እስዎን የመስሉ ጽንፈኛ ብሔርተኞች በሚቀዱልን ቦይ ስንፈስ ማየቱ እጅግ በጣም ያማል።

ሻለቃ! እርስዎ የርስ በርስ ግጭትን በወረቀት ደረጃ ያው እንደ ተለመደው ከሩቅ ሆነው ከግጭቱ ጠንሳሾችና መሪዎች ጋር በሞቀ ሶፋ ላይ ሆነው ተወያይተውበት ምናልባትም “መፍትሔ” አግኝተውለት ይሆናል። የግሌ የሕይወት ተሞክሮ ግን ከርስዎ እጅግ በጣም የተለየ ይመስለኛል። ባለፉት ጽሁፎቼ ደጋግሜ ለማስረዳት እንደ ሞከርኩት፣ ከሰላሳ ዓመት በላይ የፕሮፌሽናል ሕይወቴን ያሳለፍኩት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የርስ በርስ ግጭቶች በተካሄዱባቸው አገራት ነው። በአፍጋኒስታን፣ በፓኪስታን፣ የሶቪዬት ጂኦርጂያ (አብካዚያና ደቡብ ኦሴትያን ጨምሮ)፣ ቼችኒያ፣ ክራይሚያና ምሥራቅ ዩክሬይና፣ ሞልዶቫ (ትራንስ ድኔስትራ)፣ ዩጎዝላቪያ፣ (ሴርቢያ፣ ክሮዬሺያና ቦስኒያ)፣ ሚያንማር (በርማ)፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ኮንጎ የተከሰቱትን የርስ በርስ ግጭቶች በቦታው ተገኝቼ አስተውያቼዋለሁ። ድምዳሜዬ፣ በአጭር ቋንቋ፣ የርስ በርስ ግጭት ከጦርነቶች ሁሉ እጅግ በጣም የከፋና ግጭቱ እንኳ ካበቃ በኋላ የተቆሳሰሉትን ወገኖች መልሶ አንድ ላይ በሰላም ለማኖር እጅግ በጣም አዳጋች የሆነ ሁኔታን የሚፈጥር በማንም ማህበረሰብ ላይ እንዲደርስ የማይመኙት ሰው ሰራሽ የጥፋት ጎተራ ነው። እንዴት እንደዚህ ዓይነት መደምደምያ ላይ እንደ ደረስኩ ማወቅ ለሚፈልጉ ወገኖቼ የምመክራቸው፣ ጊዜና አቅሙ ካላቸው ወደ ቦስኒያ ሄርሴጎቪና ሂደው ከርስ በርስ ጦርነቱ በፊት በሰላም አብረው ይኖሩ በነበሩት የሴርቢያ፣ ክሮኤሺያና ቦስኒያክ ሕዝቦች መካከል ያለውን የዛሬውን አኗኗራቸውን ተመልከቱ እላለሁ።

የርስ በርስ ግጭትን የሚፈለገውን መሥዋዕት ከፍለን ማስወገድ ካሉብን ነገሮች የመጀመርያው ነው። በመሆኑም፣ ይህን ሁሉም የሚጠፋፋበት፣ ከሩቅ ሆነው በእሳቱ ላይ ቤንዚን እየረጩ ከሚደሰቱ እፍኝ የማይሞሉ ጽንፈኞች በስተቀር አሸናፊ የሌለበት የአብሮ መጥፋት (collective vanishment) ኋላ ቀር ፖሊቲካ መሆኑን ተገንዝበን ሕዝቡን ለአመጽና ርስት ለማስመለስ ማነሳሳቱ አቁመን ልዩነትን አቻችሎ አብሮ መኖርን በማስተማር ላይ ጉልበታችንን እናስተባብር እላለሁ። እስዎም ደግሞ በግል እባክዎን፣ “የቀድሞ ርስትዎን ወለጋን ለማስመለስ ጠንካራ ድርጅት” ለመፍጠር ውድ ጊዜዎን ከሚያጠፉ፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና የሕዝቦቿን አብሮነት ሊያጠነክር በሚችል አገር አቀፋዊ እንቅስቃሴ ላይ ያተኩሩ። ይመኑኝ ሻለቃ፣ እየተጓዙበት ያለው ጎዳና መድረሻው ጥልቀቱ አዕምሮ ከሚገምተው በላይ የጠለቀ መቀመቅ ነው። ስለዚህ እባክዎን ሰከን ይበሉና ከጥፋት ይልቅ ስለ ልማትና መረጋጋት ያስቡ! በዚህ ዕድሜ የሚያምርብዎትም ይኸው ብቻ ነው። አይ አይሆንም፣ ያባቶቼን ርስት ወለጋን ሳላስመልስ ሞቼ እገኛለሁ የሚሉ ከሆነ ደግሞ፣ “ጠንካራውን የርስት አስመላሽ ጦር” አዘጋጅተው ወደ ወለጋ ከማቅናትዎ በፊት መልካም ፈቃድዎ ሆኖ አስቀድመው ቢነግሩኝ፣ ግምቢ አውራጃ ውስጥ ለሚገኙ ዘመዶቼ “በሻለቃ ዳዊት የሚመራ የርስት አስመላሽ ጦር እየመጣ ነውና ቡና አፍልታችሁ፣ ቄጤማ ጎዝጉዛችሁ እጃችሁን ዘርግታችሁ በደስታ ተቀበሉት” ብዬ መልዕክት ላስተላልፍ እሞክራለሁ። ፈረንጅ አገር ሂዶ ተምሮ መጠቀ ብለን የምንኮራበት ልጃችን ብሎ ብሎ “ሊወርህ የመጣን ጠላት በሰላም ተቀበሉት የሚለን ከሆነ፣ መማሩ ቢቀርበት ይሻላል” ብለው እየረገሙኝ ጦርና ጋሻቸውን ጥንት ከሰቀሉበት አውርደው መወልወል እንደሚጀምሩ ቢታየኝም።  እባብ ያየ በልጥ በረየ እንዲሉ፣ የርስ በርስ ጦርነት የሚያደርሰውን ጥፋት ከማንም ኢትዮጵያዊ በላይ አይቻለሁ ብዬ ስለምገምት፣ እንኳን በኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ይቅርና በማንም ጠላት ተብሎ ሊፈረጅ በሚችል ወራሪ ኃይል ላይ እንኳ እንዲደርስበት አልመኝምና።

(ስለ የርስ በርስ ጦርነት ያለኝን ፍራቻ በበለጠ ለመረዳት “የርስ በርስ ግጭት መንስዔውና  መፍትሔው” በሚል አርዕስት በቅርቡ በአንዳንድ ማህበረሰባዊ ሚዲያዎች ላይ ያሳተምኩትን መጣጥፍ እንዲያነቡ እጋብዝዎታለሁ)።

እግዜር ለጦርነት ሳይሆን ለሰላም ግንባታ የሚረዳንን ጥንካሬና አስተውሎት ያብዛልን።

******

ጄኔቫ፣ ሜይ 10 ቀን 2021 ዓ/ም

[email protected]

10 Comments

 1. አቶ ዋቀዮ የተረኝነት መንፈስ ነጠር ነጠር አድርጓሃል፡፡
  ምናለብህ የሞተው የሻለቃ ወገን አማራው ነው! ያንተ ወገን በገጀራ እየቀጨ እሬሳ የሚጎትት ተጉልበት በቀር ሐሳብ የማይገባው የአበደ አውሬ ነው፡፡
  ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል! በል ደንፋ!
  ሻለቃ ስራዎን ይቀጥሉ ለዚህ ከንቱ መልስ መስጠት የለብዎትም፡፡ ጊዜ ይፈርደናል፡፡

  • Very truly!
   Bravo ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ! Keep it up.
   Thank you for your excellent work. Go go go…………..
   God bless you.

   Derbi Belachew

 2. You Wakeyo very nasty monkey can go hell. Piss off. We ‘ll never ever allow savages to butcher our people as before. You self called Oromo barbarians have to be dealt with. Just wait for a while. You gonna perish same as TPLF. That is the only solution for the existence of Ethiopia. Your Oromuma nightmare is doomed to failure. We will reconquer our ancestral land from Bale to Tigre. Abiy Ahemed/s Galla/ OLF/OPDO regime is responsible for Amhara genocide in Ethiopia. We ‘ve to avenge by all means.. Bravo captain Dawit W/ Giowergis. He is doing an excellent job. The perpetrators of Amhara genocide will be brought to justice. This act is causing you the highest state of confusion and paranoia. After all we are no more one people. Thus, you have no right to blame Captain Dawit. Please shut up ur bad mouth.

  Derbi Belachew

 3. አቶ ዋቀዮ አልገባዎትም እንጂ እርሶም በዚህ ጽሁፎ ጨንበሎን አውልቀው ማንነቶን አጋልጠዋል፡፡ የኦሮሞ ዘረኝነቶንና ተረኝነቶን፡፡

 4. Ato Wokayo:

  The hate, blatant lies, vulgarity and character assassination you showed towards Shaleka Dawit says a tone about your personality. It would have been better if your choice of words had reflected your age and the academic training you claim you have.

 5. ባይሳ ዋቅ፟፟፟፟፟ ወያ የጻፉት እኮ በወጣትነት ጊዜአቸው የነበረውን የአስተዳደር፤ በወቅቱ የነበረውን ትግል እና ከእውቀትና ከልምዳቸው በአሁኑ ወቅት ለኢትዮጵያ መሆን የሚገባውን ለወጣቱ ትውልድ በዕድሜ ጠገብች መሰጠት ያለበትን ምክር እንጂ ” እንደሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ያረጀ ያፈጀ የእርስት እንካለል ጦረኛ እንመስርት” አይደለም ያሉት።በመሆኑም ሻለቃው በደርግ አስተዳደር ጊዜ በስልጣን ጥም የተራቡ ስለነበረ ደርግም ጥማቸውን ለማርካት ሲል የዕርዳታ ማስተባብሪያ እና ማቋቋሚያ ኮሚሺን ኮሚሺነር አርጎ ቢሾማቸውም የሥልጣን ጥማቸውን በለመርካታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያ እያለቀ የርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሺንን ባዶ ጠረጴዛ አስቀርተው በሥራቸው ድክመት በኢትዮጵያ ህዝብ ህይወት የነገዱ ሲሆኑ ደርግን ለመጣልም በስማ በለው ወሬ በማናፋት ፤ፕላን የለሺ አስተባባሪነት እነ ጀኔራል ፋንታ በላይ እንዲሁም የሌሎችን ህይወት በጭር እንዲቀጠፍ የስተባብሩ የነበር ሲሆን አሁን ደግሞ ወጣቱን ለማስፈጀት ጦር እናቋቋም እርስት እናስመልስ ማለታቸው ታላቅ ስህተት ነው። እንዲሁም ምንም እንኳን ከሰላሳ አመታት በፊት ወታደር ቢሆኑም እንኳን በአሁን ሰኣት ግማሽ ኪሎ ሜትር እንኳን ተጉዘው ማዋጋት አይችሉም። ዕድሜም ክቡር ነውና በዕድሜአቸው መካሪ ዘካሪ መሆን ይገባል። ታዲያ አቶ አንተነህ አንተም ከዕርስት አስመላሹ የጦሮ መሪ አጃቢ ከሆንክ የሚተርፍህ ነገር ቢኖር የዕርስት አስመላሹ ጦር መሪ የሻለቃ ሁይልቸር ገፊነትን ነው።

 6. የእነ ሳዳም ሁሴንን፣ ጋዳፊን ፣ኒኮላይ ቻውቼስኮን ጥጋብና መወጣጠር አይተናል። ትዕቢት የወጠራቸውን ህዝብ አስተንፍሷቸዋል። ጊዜው ደርሷል አይዞህ ።

 7. Dear Mr Bayissa,
  I hope you are growing old wisely and humanly though I am not sure.
  You are a professional, well trained and sophisticated man who lives in Switzerland comfortably. Unfortunately you failed to get rid of the hate inside your persona which you try to hide through polite approach, good use of Amharic language and “international experience”.

  You are a smart but dangerous man who can spoil the clear water with his ink. If you remove your cover, you will see the naked narrow ethnicism, Oromumma (Oromo first) and hate towards Amhara people..

  You claim to work in UN and lived most of your adult years in Europe, didn’t learn about how people in modern world live among themselves while your mind is still entrapped with the hate you have had since childhood about Amhara and how to avenge it.

  You never uttered or wrote on your beautiful Amharic or Afan Orommo condemning the atrocities committed by the OLF on innocents citizens in animalistic way.
  Through your language sophistication and street smart approach, you actually tried to be little people who expose the Oromo (OPDO +OLF) massacre of Gedwo people. When Tamagne Beyne brought the issue to public knowledge (mainly to help displaced people), Mr Bayissa tried to use his nice Amharic to blur the right information about what was happening to Gedeo people. He tried to belittle Tamage Beyene appearing as if he was a fair critic.

  When the famous OMN media preaching hate, inciting inter communal, ethnic and religious conflict, he declared in his own articles that “the oppressed Oromo people got its own media”. He tried to defend OMN’s hateful, irresponsible propaganda and divisive propaganda.(published in Ethiomedia, Ethioforum.org)

  We now know that the Oromumma advocates have made unique approach to use nice words to appease Ethiopians while they implant and grow Oromo dominance in Ethiopia or with long term aim of forming new country called Oromia by dismantling Ethiopia. The sweet talk of Colonel Abiy (Phd), Lemma and your fellow used that deceived people for 2 or more years but now you will no longer deceive as that startgy is overt.

  At last, Mr Bayissa, I encourage you to get rid of the “hate” you have since childhood which grew and now in reality in the position of power which your brothers daily practicing it in Ethiopia. I wish you will not die or lose your mind (dementia) before you get a good therapy to get rid off the hate which you failed to remove through education, working in UN or living in advanced World.

  I prey to you to be Human than an ethnicity propagandist with smart language and polite approach.

 8. ባይሳ ነገር ብታበርድ ምናለበት ስድብን የብቃት መለኪያ አድርገኸው ቁጭ አትበል። ሻለቃው በባንዲራው የማለ መኮንን በመሆኑ የገባው ቃል ኪዳን እረፍት ነስቶት እንጅ ለሌላ አይደለም ዶር አብይን ለመደገፍ ብለህ የደርግ ቤት ስራውን ማንሳት መሞከር ለዶ/ር አብይ ነብሴን እሰጣለሁ ደጋፊ የሚበጅ አልመሰለኝም ካልረሳሁት “እዛም ቤት እሳት አለ” የሚል ብሂል አለ ሻለቃውን ስትቆፍር ብትውል ምንም አታገኝበትም። ለማንኛውም ሁላችንም የኢትዮጵያ ልጆች በመሆናችን ከአንድነት የተሻለ ምርጫ የለንም። ኦነጋውያን እነ መራራን ጨምሮ ያለን ጊዜ አጭር በመሆኑ አጥፍተን እንጥፋ የሚል እሳቤ ላይ መሰሉኝ።

 9. ክቡር ሻለቃ
  ባይሳ ተረኝነት ተሰምቶት እንደ ገንፎ ውሀ እየተንፈቀፈቀ ነው፡፡ ጥጋቡ ቱግ እያል እንደ ልጅ ትውኪያ ሲወጣ ይታየኛል፡፡ መስከንን ታወቀማ መስከን የነበረበት እርሱ ነበር፡፡ በመደዳ በታረደው አማራ እየተሳለቀ ነው! አማራ የባይሴን ጉዳይ መዝግበህ ያዝ! ሙያ በልብ ነውና ልብ በል!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.