የትግራይ ጉዳይ በስርዓት ካልተያዘ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር አላላውስ የሚል እግር ብረት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም

getachew

የትግራይ ጉዳይ በስርዓት  ካልተያዘ (በተለይ ህወሓቶችን ከትግራይ ህዝብ መነጠል የሚያስችል ፖለቲካዊ ስራ ካልተሰራ) ኢትዮጵያን እንደ ሃገር አላላውስ የሚል እግር ብረት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም!!!

መሰረት ተስፉ (Meserettesfu4@gmail.com)

በትግራይና በሌሎች አከባቢዎች ለተፈጠሩት ምስቅልቅሎች ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ህወሓቶች እንደሆኑ አምናለሁ። ስለዚህ እንኳን አሸባሪ የሲኦል ደንብ አስከባሪ ቢባሉ ያንስባቸው እንደሆነ እንጅ አይበዛባቸውም።  ነገር ግን ትግራይ ውስጥ ለተፈጠረው ምስቅልቅል የፌዴራል መንግስቱ ድርሻም ቀላል ነው ብየ አልገምትም። ችግሮችን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ በመለየት፣ ለተለዩ ችግሮች አግባብነት ያላቸው መፍትሄዎች በመስጠት፣ በክትትል፣ በቁጥጥርና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ የፌዴራል መንግስቱ ያሉበት ችግሮች ተዘርዝረው የሚያልቁ አይመስለኝም። ክሁሉም ከሁሉም ግን ህወሃትን ከትግራይ ህዝብ የመነጠል ስራ ላይ ወድቋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንዲያውም ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎች አብዛኛዎቹ የትግራይን ህዝብና ህወሃትን አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ሲጀመር የቀን ጅቦችና ፀጉረ ልውጦች የሚሉ ለትርጉም ክፍት የሆኑ ቃላትን በመጠቀም ህዝቡን የሚያስከፉ ንግግሮችን ማድረግ ተገቢ አልነበረም። እነዚህና የመሳሰሉ አባባሎች በቀጥታም ይሁን በተለያየ መንገድ እየተተረጎሙ ህዝቡ ተገለልኩ ብሎ እንዲያምን አድርገውታል። ይህ ደግሞ ህወሓቶች የትግራይን ህዝብ ድጋፍ እንዲያገኙ አግዟቸዋል። በእርግጥ  ህወሓቶች የትግራይን ህዝብ ድጋፍ እንዲያገኙ የረዷቸው ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፡

 • የኢትዮጵያና የኤርትራ ድንበር ጉዳይ የተያዘበት ሂደት ግልፅ አለመሆን። በተለይም ተደርሶበታል የተባለው ስምምነት የተያዘው በዶ/ር አብይና በአቶ እሳያስ ብቻ እንጅ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንዲያውቁት አልተደረገም የሚለው ጉዳይ ዋነኛው ነው።
 • በጀት መከልከሉ
 • በክልሉ የተደረገው ምርጫ እውቅና መነፈጉ
 • የክክሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ለህዝቡ እንዳይደርሱ ተደረገ እየተባለ ሲናፈስ የነበረው ወሬ በሚገባ ማብራሪያ አለማግኘቱ ተጠቃሾች ናቸው።

በዚህ ሁኔታ ህወሓቶች በተለይ ከህዝቡ አለመነጠላቸውን በተረዱ ጊዜ ከፌዴራል መንግስቱ ሊያፈነግጡ እንደሚችሉ ተገማች ነበር። ከዚህ ጋ ተያይዞ ከፍተኛ ስጋት አድሮብኝ  የፌዴራል መንግስቱ ከትግራይ ህዝብ እንዳይነጠል ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት  ለማሳሰብ ሞክሬም ነበር። ስጋቴ ግን በዚህ ብቻ የታጠረ አልነበረም። ከባህሪያቸው ተነስቸ ህወሓቶች ህዝቡ ደግፎናል ብለው እርግጠኛ በሆኑበት ሰዓት ልክ በ1981 በደርግ ላይ እንዳደረጉት ሁሉ ሰሜን እዝ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይሞክሩ ይሆናል ብየ ስለሰጋሁ ጥቃቱን ከመፈፀማቸው አስቀድሜ ምን አልባት ከሚመለከታቸው ጆሮ ቢደርስ በሚል ይህንኑ ስሜቴን በሚከተለው መንገድ መግለፄን አስታውሳለሁ።

“እንደሚታወቀው የደርግ ሰራዊት በአጠቃላይ የህዝብ ድጋፍ አጥቶ፣ የአላማ ፅናቱ ተሸርሽሮና የመዋጋት ፍላጎቱ ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም አከርካሪው በዋነኛነት የተሰበረው ግን 1981 ላይ 604ተኛ ኮር ትግራይ ውስጥ በትግራይ ህዝብ ድጋፍ በህወሓት ከተደመሰሰ በኋላ ነበር።

አሁንም የህወሓት ሰዎች መከላከያ ሰራዊቱ ከትግራይ ንቅንቅ አይልም የሚል መግለጫ እየሰጡ ያሉት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የትግራይን ህዝብ በማነሳሳት የአስራ ዘጠኝ ሰማንያ አንዱን ታሪክ በመድገም የሰሜን እዝን ከበተኑ በኋላ ይህ ሰራዊት እየተጠቀመበት ያለውን መሳሪያ ሁሉ በጃቸው ለማስገባት አልመው ይመስለኛል።

በእኔ እምነት ይህ ሃላፊነት የጎደለው እሳቤ በዚህም በዚያም በኩል ያለውን ህዝብ ለሌላ እልቂት ይዳርግ እንደሆነ እንጅ የታሰበውን ግብ ያሳካል አልልም። ከዚህ ይልቅ መፍትሄ የሚሆነውኢትዮጵያን አሁን የምትገኝበት መቀመቅ ውስጥ እንድትገባ ያደረግናት ዋነኞቹ ተዋናዮች እኛ ነንበሚል ለህዝቡ ግልፅ የሆነ ይቅርታ ጠይቀው ለሰላማዊ ውይይትና ድርድር ልባቸውን በቀና መንገድ ክፍት ማድረግ ነው።…”

 

እንዳለመታደል ሆኖ ግን በፌዴራል መንግስቱ እንዝህላልነት ሊባል በሚችል ሁኔታ ስግብግቦቹ ህወሓቶች ሃያ አመትና ከዚያ በላይ ሲጠብቃቸው በነበረው ሰሜን እዝ ላይ አሳፋሪ፣ አሳዛኝና የትም ተደርጎ የማያውቅ ድርጊት ፈፀሙ። ክብር አሁንም ለጀግናው መከላከያ ሰራዊታችንና ለአማራ ልዩ ሃይል ይሁንና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የህወሃቶችን እኩይ ምግባር አክሽፈውታል።

ይህ በፀጥታ ዘርፍ የተገኘው ድል ግን በፖለቲካዊ ስራ የታጀበ ነበር ማለት አይቻልም። አሁንም ቢሆን የፌዴራል መንግስቱ የሚመጥን ፖለቲካዊ ስራ ሰርቶ ህዝቡን በመያዝ ህወሃት መሰረት እንዲያጣ እያደረገ ነው ብየ አላምንም። በዚያ ላይ የኤርትራ ጦር መግባቱ ብቻ ሳይሆን ከገባ በኋላም እየፈፀማቸው ናቸው የሚባሉ ግድያዎች፣ አስገዶ መድፈሮች፣ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የንብረት ውድመቶችና ዝርፊያዎች በህዝቡ ላይ ያሳደሩት ተፅዕኖና ቅሬታ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አልመሰለኝም። የኤርትራ ሰራዊት ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱን በተመለከተም ፌዴራል መንግስቱ ይሰጣቸው የነበሩ እርስ በእርሳቸው የተጣረሱና ከእውነት የራቁ መግለጫዎች በትግራይ ህዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ክልሉን እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው ጊዜያዊ አስተድደርም ከክልል ጀምሮ እስከ ጣቢያ ድረስ መዋቅር ዘርግቶ ህዝቡ ራሱ ሰላሙን፣ ፀጥታውንና ደህንነቱን ሊያስከብር እንዲችል ያደረገው ስራ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ እየታዘብን ነው። በዚያ ላይ አገር ውስጥና ውጭ ባሉ የህወሃት የፕሮፖጋንዳ ማሽኖች ተቆርጦ እየተቀጠለ የሚቀርበው የሃስት ፕሮፖጋንዳ ህዝቡን በተለይ ወጣቱን ለትግል እያነሳሳው እንደሆነ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ሁኔታ በጊዜ ካልታረመ ግጭቱ በፌደራል መንግስቱና በህወሓቶች መካከል ሳይሆን በፌዴራል መንግስቱና በትግራይ ህዝብ መካከል የመሆን እድሉ ዝግ ላይሆን ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብኛል። እንዲያ ከሆነ ደግሞ ህወሃቶች ህዝቡን እንደጫካ በመጠቀም በፈለጉ ጊዜ አድፍጠውም ሆነ መደበኛ በሆነ መንገድ የፌዴራሉን የፀጥታ ሃይል የሚወጉ ሲቪል ለባሽ የትግራይ መከላከያ ሃይል (በነሱ አጠራር TDF) በውጊያ ውቅት ሲገደሉ ደግሞ ምንም የማያውቁ ንፁሃን ተጋሩ እያሉ ህዝቡን የበለጠ ለማነሳሳትና  የአለም አቀፍ ማህበረሰቡን ለማደናገር ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ይህ መንገድ ደግሞ ትግራይ እንደ ቤርሙዳ ትሪያንግል የ(Bermuda Triangle) ወይም ሩቅ ሳንሄድ “የናቅፋ” አይነት ትሆንና በሁለቱም በኩል ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ህይወት እየዋጠች አላየሁም የምትልበት ደረጃ ልትደርስ ትችላለች። እዚህ ላይ ቬትናምና ሶማሊያ ውስጥ በአሜሪካ ላይ የደረሱትን ታሪካዊ ክስተቶች ማስታወስም ወቅታዊ ነው ብየ አምናለሁ።

ይህ ደግሞ እዛው ሳለ የትግራይን ህዝብ ለስቃይ ኢትዮጵያን እንደሃገር ደግሞ  በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና  በማህበራዊ ዘርፉ ትኩረት አድርጋ እንዳትንቀሳቀስ እግር ከወርች አስሮ እንደፈለገች እንዳትንቀሳቀስ ሊያደርጋት ይችላል። ከሁሉ በላይ ግን ከውጭ የሚቃጣባትን ጥቃት ለመመከት የሚያስችላትን ሃይል ሊከፋፍልባት የሚችል ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። 

የመፍትሄ ሃሳቦች፡

 • የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከክልል ጀምሮ እስከጣቢያ ድረስ በሚገባ የተዋቀረና የተደራጀ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መዋቅሩን መዘርጋት ብቻም ሳይሆን ከሙስና፣ ከአድሎ፣ ከኢ-ፍትሃዊነትና ከአምባገነንነት በፀዳ መልኩ ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ከፌዴራል መንግስቱ ጋር በመቀናጀት በተለይ ፖለቲካዊ ስራዎችን በሚገባ በመስራት ህወሓቶች ከህዝቡ እንዲነጠሉ ለማድረግ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ቢያንስ ቢያንስ ግን ከህወሓት የተሻለ ሆኖ መገኘት አለበት።
 • የኤርትራ ጦር በሃገር ውስጥ የፀጥታ ሃይሎች ሊተካ የሚችልበትን ሁኔታ ማፋጠን ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት የትግራይን የፖሊስ ሃይል በሚገባ አደራጅቶ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ቁልፍ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ከዚህ ጎን ለጎንም ህዝቡ ራሱ ተደራጅቶ ከክሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የየአከባቢውን ሰላም፣ ደህንነትና ፀጥታ በባለቤትነት ሊያስጠብቅ ይችል ዘንድ ሁነታዎች ሊመቻቹለት ይገባል።
 • የኤርትራን ጦር በተመለከተ ይሰጡ ለነበሩ እርስ በእርሳቸው የተጣረሱና እውነትነት የሌላቸው መግለጫዎች የፊዴራል መንግስቱ የትግራይን ህዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል። በነገራችን ላይ ዛሬ ላይ የኤርትራ ጦር ትግራይ ላይ ገብቶ ያሻውን እያደረገ እንዲቆይ ከተፈቀደለት ነገ ከነገ ወዲያ ወይ ራሱ የኤርትራ ካልሆነ ደግሞ የሌላ አገር ጦር ሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ገብቶ እንዲጨፍር የማይፈቀድለት ስለመሆኑ ዋስትና የለም የሚሉ ድምፆች መሰማት ጀምረዋልና ቢታሰብበት መልካም ነው።
 • የትግራይ ህዝብ በፌዴራል መንግስቱ ተቋማት ደረጃ የሚገባውን ውክልና ማግኘቱን ማረጋገጥ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይደለም።
 • የህወሓቶችን አፍራሽ ባህሪና የደጋፊዎቻቸውን የቆርጦ ቀጥል ሮፖጋንዳ በማስረጃ እያረጋገጡ ህዝቡ እንዲያውቀው መደረግ አለበት። ይህ በተለያየ መንገድ ሊፈፀም ይችላል። ዋና ዋናዎቹ ግን ህዝባዊ ኮንፈረንሶችና ሚዲያዎች ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።  በዚህ ረገድ አንድ ግብረሃይል ቢቋቋምና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ተመራጭ ይሆናል።
 • የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀየዎቻቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መፈጠር አለበት። በተጨማሪም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ችግር ዋስጥ ያሉ ዜጎችም የዕለት ደራሽ እርዳታ የሚያገኙበትና በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
 • የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክቶች እየተቀረፁ የወደሙ ተቋማትን እንደገና የመገንባት እንቅስቃሴ መጀመር አለበት።
 • በማንኛውም አካል የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ንብረት ውድመቶች ባስቸኳይ ባስቸኳይ ተጣርተው እንዲቆሙና ፈፃሚዎችም ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።
 • ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች በተገቢው መንገድ እየተሰጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይገባል።።
 • ህወሓቶችን በአሸባሪነት የሚፈረጅ አዋጅ የሚወጣ ከሆነ ንፁሃንን ለማጥቃት ጥቅም ላይ እንዳይውል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መከታተል ያስፈልጋል።

ጠቅለል ለማድረግ ያህል ትግራይ ላይ የተፈጠረውን ችግር በፀጥታ ሃይሉ ብቻ ለመፍታት መሞከር አዋጭም ዘላቂም  እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው። በተጨማሪም ምናልባትም ደግሞ በዋናነት ሰፊና ጥልቀት ያለው የፖለቲካ ስራ ሰርቶ ህዝቡ የለውጥ ባለቤትነት ስሜት እንዲያድርበት ማድረግ ያስፈልጋል። በተለይ ህወሓቶችን ከትግራይ ህዝብ  የመነጠል ስራ አማራጭ እንደሌለው መረዳት ይጠቅማል። ይህ ሲሆን ህዝቡ ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በመተጋገዝ ሰላሙንና ደህንነቱን እያስከበረ ፊቱን ወደልማት የማዞር ፍላጎቱ መጨመሩ አይቀርም።

 

2 Comments

 1. you were one of the supportter of the war against all Tegaru under the guise of attacking TPLF !! please donot abandon PP as you bandon Tegaru! I loved and advocated Amhara and lived with amhara for years and I believe amhara still need to be protected but you people, lihikanoch, le fird mekreb alebachuh !!

  giticha hula yetenebersh mamitu ye gonder , ye shewa weyis ye goje lij man libel ????

 2. እንደው ቀስ እያለ ነገር እየተረሳ መጣ። ህወአት የተባለ መርገም የኢትዮጵያን ህዝብ ሙጥጥ አድርጎ የበላ፣ትግሬ ጠፋ ተብሎ ለሚናፈሰው ወሬ ቀልቡን ለሰጠ ዜጋ ምን ቢያደርጉት ይሻላል? አሁን ትግሬ እፍረቱን ገፍፎ የሚወጣበት ጊዜ ነበር? ትግሬንስ በመገላገያው ገላግሎናል አህመዲን ጀበል ኡስታዝ አቡ በከር መራራ ጉድና ጁዋርና በቀለን በመገላገያው ይገላግለን

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.