ከፓትሪያርኩ ጭምር በአልማዝ አሰፋ – ዘረ ሰው

176345115 4232006450154284 2036013590367727349 n

እስከ መቼ ድረስ : ለምኜ አባብዬ
እስከ መቼስ ድረስ : የራሴውን ደልዬ
የማይፈልገኝን : ልጅ ይሁነኝ ብዬ ::
ብላ ስትናገር : ኢትዮጵያ እናቴ
ማዳመጥ አቃተኝ : አልቻለም አንጀቴ::

ተፀንሶ ተወልዶ : በአገሩ ኢትዮጵያ
ጡቷን ጠብቶ አድጎ : በእናትነት ጉያ
ወንድሙን ሲያጠቃ : ሲፈፅም ግድያ
እናት አስለቃሽ እንጂ : ምን ይባልስ ታዲያ?

የጋራ መሆኗን : እረስቶ አገሬ
በሃሰት ትረካ : በፈጠራ ወሬ
እውነትን በመክዳት : እኔም ለመኖሬ
ከማይፈልገኝ ጋር : እንዴት ልሁን ዛሬ?

ጥቅሙን ለማራመድ : ስልጣንን ፍለጋ
ጎሳን በማስቀደም : እንደከብት ሲንጋጋ
ሰው መሆኑን እረስቶ : እየሆነ መንጋ
ኢትዮጵያን አሳጣት : የእናትነት ዋጋ::

የሚገርመው ጉዳይ : የዚህ ውለታቢስ
ቅድመ አያቶቹ : ደማቸውን በማፍሰስ
ሞተው ተሰውተው : አፈርን በመልበስ
ያቆዯትን አገር : ሲሯሯጥ ለማፍረስ
ሰው ነው ወይ ቢባል : ለጥየቃው መልስ
የሰው መልክ ያዘ እንጂ : እሱ ግን ዲያብሎስ::

ማሰብ የሚያስችል እውቀት: ቀስሟል ከተባለ
የተማረው ትምህርት : ለሰው ጥቅም ካልዋለ
አገራዊነት ትቶ : መንደር ከከለለ
ሰባዊነት ተሰምቶት : ለማዘን ካልቻለ
ሰው ከማዳን ይልቅ : ሰውን ከገደለ
ሰው መሆን ተስኖት : አውሬ ከመሰለ
የሰው እንክርዳድ እንጅ : መች ሰው ሆኖ በቀለ?

አንተ የዲያስፖራ ኗሪ : ስትመጣ ስደት
ነፍስህን ለማዳን : የሰጠኸው ምክንያት
መሆኑ አይረሳህ : የራቀ ከእውነት::
ቃለ መጠየቅ ያረገው : ማመልከቻህን አይቶ
የኤምባሲ ተወካይ : ችግርህን ተረድቶ
እሱ ሲፈቅድልህ : ሃቁን ከጎን ትቶ
ሰውነትህን አስቦ : ስቃይህን ገምቶ
በሰባዊነት ስሜት : ሃዘኔታ ገብቶ
አዱስ ሕይወት ሰጠህ : ውሸትህን ረስቶ::

ያንን ደግ ውለታ : አንተ ግን ረስተህ
ለሰው ልጅ ማዘንን : ሳትማር ቀርተህ
በዲያስፖራ አገር : በምቾት ተቀምጠህ
ጎሳ ጎሳ እያልክ : ሕዝብ እያፋጀህ
አገር ከመገንባት : አገር ታፈርሳለህ
ኧረ ለመሆኑ : እንደ ሰው ታስባለህ?
ወይስ ስንዴ ውስጥ የገባ : ጥራጊ እንክርዳድ ነህ?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወይ አገሬ ሆይ ዝንታለም መከራ ሁልጊዜ ዋይ ዋይ (ዘ-ጌርሣም)

ኦሮሞ እንዲህ እያልክ : ረስተህ ሰው መሆኑን
አማራንም እያልክ : ዘንግተህ ሰው መሆኑን
ትግራይ እንዲህ ሆነ : በማለት ስትቦዝን
ፊታውራሪ በመሆን : ጎሳን ስታስቃኘን
ላስታውስህ ወንድሜ : ታላቅ ጥፋትህን
ለመሻር አትሻ : ፈጣሪ የሰራውን
ኦሮሞ አማራ ትግሬ : የሰው ዘር መሆኑን::

ኦሮሞ አማራ : ትግሬ ነህ ጋምቤላ
በጎሳ ጥላቻ : ራስህን ስትሞላ
ዲያስፖራ ተቀምጠህ : ሕዝብን ስታባላ
አይሰማህ ቅሬታ : ነጭ አንተን ቢጠላ::

ለሃያ ሰባት ዓመት : አገር ተሰቃይታ
እንዳላዩ ሆነው : ሕዝብ ሲንገላታ
ወያኔ በገፍ ሲገድል : ያላንድ ሃዘኔታ
በህወአት ዘመን : ሳያሳዩ ቅሬታ
ጁንታውን በማገዝ : ሲሉት ጎበዝ በርታ
ቅዱስ ጳጳሳችን : ተሞልተው ዝምታ
ምክንያታቸው ምን ይሆን : ለአሁኑ እሮርታ?

ወያኔ ሲፈፅም : የአረመኔ ስራ
ኦሮሞ ፅንፈኞች : ሲያነሱ ጎጀራ
በኦሮሞ ክልል : ሲገደል አማራ
ሱማሌ ሲያፈናቅል : ኦሮሞን በተራ
ቤንሻንጉል ጉሙዝ : ጎሰኛ ሲያቅራራ
በሌላ አካባቢም : ሲከሰት መከራ
የፓትሪያርክ ቅሬታ : ምነው አልተወራ?

የሰው መብት ተገፎ : በወያኔ ዘመን
ዲሞክራሲ ጠፍቶ : ጭቆናን ለብሰን
አገር ተከፋፍላ : አንድነት አጥተን
ከአንድ ባንዲራ ይልቅ : ዘጠኝ ተሸክመን
ሁሉም ሚግባባበት : አንድ ቋንቋ ትተን
እንደ ባቢሎን ገንቢዎች : እንዲያ ተበታትነን
ባለንበት ወቅት : ሰብሰብ የሚያደርገን
የፍቅር ጎዳና : አስተማሪ አጥተን
ታዲያስ የትነበሩ : የሃይማኖት መሪያችን
ምነው አልተቆጩ : ብፁእ አባታችን?

ጎሰኛ ዘረኛ : አይጣል ነው መዘዙ
የኔ የኔ እያሉ : አድሎትን ሲያበዙ
የጎሳ ጥላቻ : መራራ ነው መርዙ
ሰውን አውሬ ያደርጋል : በዘር ከተያዙ::

ከሰሜን ጀምሮ : እስከ ደቡብ ድንበር
ከምእራብ ተነስቶ : እስከ ምስራቅ ዳር
አንድ ሕዝብ መሆናችንን : እንዲሁም አንድ አገር
መረዳት እቅቶን: መኖር በፍቅር
ፈጣሪ ሲያዝንብን : በያዝነው ነገር
እሱ የሰራውን : የአዳም ሄዋን ዘር
መቀበል አቅቶን : ጎሳ ስንቆጥር
መስቀል ሚያሳልመን : ለፈረሃ እግዚአብሔር
ባለማግኘታችን : እውነት ሚያስተምር
በኃጢአት ታጥነናል : ከፓትሪያርኩ ጭምር::

ተጨማሪ ያንብቡ:     " የቋንቋ ንግሥ" እና "እሥቲ ተጠየቁ" - ከመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ለእግዚአብሔር አማኞች:-

ምንጊዜም : ለራሳችን የምንመኘውን
ለሌሎች እንድንመኝ ፈጣሪ ይርዳን
የእግዚአብሔር ምህረት አይለየን::

በእግዚአብሔር ለማያምኑ:-

የምትመኙትን ለራሳችሁ
ለሌሎች መመኘት አይሳናችሁ::

1 Comment

 1. ወቸው ጉድ
  ከተማ ሲነድ
  ብዙ ቤተክርስትያን እና ቅርስ እየወደመ ዝም አይልም ነበር
  የተጠላው የቀድሞው መለስ ዜናዊ እራሱ በህይወት ቢኖር
  የመደመር ተቋማዊ ለውጥ አመጣሁ የሚለው ብልፅግና
  ኃይማኖትን እና ፖለቲካን አንድ ላይ ደምሮ በአንድ ጉድጓድ ተከለና
  ፓትሪያርኩንም እዋርደው ቀን ከሌሊት ሊያሳርዱዋቸው እየዛቱባቸው
  ለነፍስቸው ያደሩትን የቁም እስር አውርደዋቸው
  እንዴት ዝም ይላሉ ፓትሪያርኩ ፈርተው ለሥጋቸው?
  እኛም በቃን ዝም አንልም ፤ ቅዱስ ፓትሪያርካችንን እየሰደቡዋቸው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.