“የዘንድሮው ምርጫ የችግራችን መፍቻ ሁሉ ቁልፍ ነው።” ጠ/ሚ አብይ አህመድ – ከፊልጶስ ወርቅነህ

abiy

የጠ/ሚሩን  ስለ ምርጫ ያስተላለፋት መልዕክት ፤
-አንድ ተራ ግለሰብ ቢናገረው  ስለ ዲሞክሲና አገራችን ያለችበት ሁኔታ አልገባውም ሊባል ይችላል።
– ወይም የአንድ ፓለቲካ ፓርቲ አባል ቢናገረው ፓርላማ መግባት የሚፈልገው የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሳይሆን የውሎ አበልና ደመወዝ ” እያወሩ ” ብቻ ለመብላት አማራጭ ስለሆነበት ነው ሊባል ይችላል።

እንደ ኢትዮጵያ ባለ በውስጥም በውጭም በችግር ተወጥሮ ለተያዘና ምንም ዓይነት የዲሞክራሲ መዋቅር ባልተገነባበት፣ እንዲሁም ዜጎች  ወቶ መግባት በማይችሉበትና በማንነታቸው በየቀኑ በሚታረዱበት ፤ እንዲት  አድርጎ ምርጫ የችግራችን ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ሊሆን እንደሚችል ማንም ሰው ማስረዳት የሚችል አይመስለኝም። ከማስረዳት ይልቅ “እመኑ” ማለቱ ይቀላል።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ “የዝሆን ጆሮ”  ይስጠኝ ብለው እንጅ ፤ የዲሞክራሲን መስፈርት አሟልተው ምርጫ የሚያካሄዱ አገሮች እንኳን፣ ችግራቸውን በምርጫ ብቻ አይፈቱትም። የሚፈቱት ነገር ቢኖር ስልጣንን በሰላማዊይ መንገድ ማስተላለፍንና ለህዝብ ድምፅ ተገዥ መሆንን ነው።

ምርጫ የዲሞክራሲ አንዱ ክፍል ነው። እንደ ምሳሌ፤ ከአንድ እጅ አምስት ‘ጣቶች ውስጥ አንዷ ‘ጣት ማለት ነው። ምርጫ ደግሞ በራስ ማሟላት ያለበት ብዙ ነገሮች አሉት። ምርጫ የሚካሄደው “ውክልና” ለመስጠት ነው። ውክልና ስጭ ደግሞ ህዝብ ነው። ስለዚህ ፤

– ዜጎች በነፃነት መምረጥና መመረጥ ቀርቶ በማንነታቸው እየታረዱ አሁን ከሟች የሰው ቆጠራ ወደ ከተማ መውደም ቆጠራ ተሸጋግረናል። ይታየዎት ጠ/ሚ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የራሰዎ የብልፅግና ኦዴፓ/ኦነግ ከውጭ ጠላት ጋር በመተባበር  መሆኑ ይፋ እየውጣ ነው።  ታዲያ አንድ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጠው የዜጎቹን ደህንነት ወይስ ምርጫ? ይቅርታ ያድርጉልኝና   አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ “ተመረጠን”  ብላችሁ ፓርላማ የምትገቡ ፓለቲከኞች ውክልናችሁ በግፍ ለተገደሉት ለሙታን ወገኖቻችን ይመስለኛል።

– በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ጎሳ እንጂ ዜጋ የለም። ውክልና የሚሰጠው በጎሳ ክልል ነው። ሰው በሰውነቱ ” አንድ ሰው አንድ ድምፅ ” የሚለውን የዲሞክራሲ ምሰሶ የለም። እውነት እንነጋገር ከተባለ ህገ መንግሥቱ አሁን ላለንበት መከራ አድርሶናል።

– ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በጎሳ ስላልተደራጁ ወይም በጎሳቸው ክልል ስለማይኖሩ ወይም ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ መምረጥን ሆነ መመረጥ አይችሉም።
የምርጫ ድምፅ የሚሰጠው ደግሞ በአመለካከት ሳይሆነ “የኔ ጎሳ ነው” ተብሎ ነው። ይህ ዲሞክራሲን ሳይሆን እርስ በርስ መባላትን አምጥቶልን ማቅ ለብሰን ውለን እናድራለን።

-የውጭ ጠላት አገራችን ሊሰለቅጥ አሰፍስፏል።  የእነሱን ጉዳይ በባንዳነትና በውክልና የዘር ፍጅተን  የሚያስፈፅሙት ደግሞ በእርስዎ ስልጣን ስር የተሰገሰጉ ፣ በኢትዮጵያዊነት ጥላቻ የታዎሩ የራስዎት ሰዎች ወይም ቡድኖች ናቸው። ይታየዎት! ታዲያ በዚህ ሰዓት ባንዳዎችን ማስወገድና  አገርን ከውጭ ጠላት መከላከል ነው ወይስ ምርጫ ይቀድማል?

-ወያኔ ከመቃብር ለመውጣታ በውጭም ሆነ በውስጥ ጠንክሮ እየስራ ነው። ወያኔ ተሸነፈ እንጅ ጦርነቱ አልቆመም። እርስዎም ጫና ስለበዛበዎት ፈቅደውላቸው ይሁን አላውቅም ፤ የዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችም ለወያኔ ሌት-ተቀን እሰሩ ነው።  የምዕራቡ ዓለምም ወያኔን ከመቃብ ፈንቅሎ ለማውጣት ባይችል እንኳ’  ግብፅንና ሱዳንን እየተጠቀሙ ጫና እየፈጠሩ ብቻ ሰይሆን ግዛታችን ወረዋል ወይም አስወርረውናል። ታዲያ እርሰዎ ቅድሚያ የሚሰጡት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠብቅ፣ መከላከያውን በማጠናከርና ለምርጫ የሚባክነውን ገንዘብ ለዚሁ ግባዕት በመጠቀም፣  ግዛት ማስመለስና ጠላትን መከላከል ወይስ የይስሙላ ምርጫ?
የእርስዎ ብልፅግና እንደሚያሸንፍ እኮ ከአሁኑ ጠንቅቀን እናውቃለን። ለምን ” ዶሮ ሲያታሉላት በመጫኛ ጣሏት” እንጫዎታለን?

– በየቦታው “በቃን ” ብሎ የተነሳው ህዝባዊ አመፅ ፣” በማንነታችን አትረዱን። ውሎ መግባት አልቻልንም። ” አለ እንጅ ” ምርጫ አካሄዱ ብሎ አልጠየቀም።  አሁን ለሚታረድ ህዝብ ምርጫ ቅንጦት መሆኑን እርስዎ እውን አ’ተውት ነው? የዘር ፍጅቱ ካልቆመ ፤ ለግዜው ህዝባዊ አመፁ ቢቆምም  የትግል ስልት ቀይሮ እንዱሚመጠ አይጠራጠሩ። ምክንያቱም የህልውና ጉዳይ ነውና። ይህ ደግሞ ለውስጥም ለውጭም ጠላቶቻችን “ሰርግና ምላሽ”  ነው።

ከላይ ከጠቀስኳቸውና ስፍር ቁጥር የሌለው ችግራችን  በተጨማሪ የኑሮ ውድነት ህዝቡን እያሰቃየው መሆኑ ያለንበት የአገራችን ወቅታዊ  ሃቅ ነው።

ስለ ጠቅላላ ዲሞክራሲ ግን በአገሪቱ ውስጥ የዲሞክራሲ ተቋማት ስለ አልተመሰረቱና ሽታቸውም ስለሌ ምንም ማለት አይቻለም። ለማጠቃለል ግን የጎሳ ህገ መንግሥትና በጎሳ ተክልሎ ስለዲሞክራሲ እና ስለ ምርጫ ማውራትና፣ የዘር ፍጅት እተካሄደ፣ እንደ መንግሥት ቅድሚያ ለህግ የበላይነት መስጠት ሲገባ እርስዎ. “ምርጫ” ብለው እርስዎ በሚያሸንፋበት ምርጫ ለባስ ችግር ከመጋለጠ ውጭ የሚፈይደው የለም። ከትላንት ስህተት ያለመማርም  አባዜ ነው።

መንግሥተዎ ህዝብን ግራ ማጋባቱን ትቶ፤  “ምርጫ ” እያሉ ጉልበትና ገንዘብን ማባከኑን አቁሞ፤ የሚከተሉትን እርምጃ ቢውስድ እንደ አንድ ዜጋ እመክራለሁ፤

ጠ/ሚ አብይ አህመድ  ሆይ፤
1/ምንም ሳያመነቱ ፓርላማውን (ልብ ያድርጉ!  ፓርላማው የኢህአዲግ እንጅ የብልፅግና አይደለም።)  በትነው አገሪቱን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያስተዳድሩ።

2/ማንኛውንም የፓለቲካ እንቅስቃሴና የጎሳ ሚዲያ ይዝጉ፤  በተለይም የዩትዮብ ሚዲያ ለውጭ ጠላቶቻችንም ሆነ ለፀረ-ኢትዮጵያዊያን ባንዳዎች “ነዳጅ” ሆኖ እያገለገለ ነው። አገርና ህዝብ እስኪረጋጋ ድረስ የሚዲያ መዝጋት ተገቢ ነው።  የሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ከመቅጠፍ ሚዲያውን ላልተወሰነ ግዜ መዝጋት ይቀላል።

3/ መከላከያን ይፈትሹ።  አሁን በቅርቡ በአጣዬና በስሜን ሸዋ  በተፈፀመው ግፍ መሳተፍ እየተስማ ነው። ደህንነት መስራቤተዎም ምን ሰርቶ እየበላ እንደሆን እግዜር ይወቅ። በድንብ ይፈተሽ። ተለይም  ” ትላንት የደገፈኝና ለእኔ የሞተልኝ  ህዝብ ዛሬ እንዴት እንቅሮ ተፋኝ?” ብለው ራስዎትን ይፈትሹ። “የምናገረውና መሬት ላይ ያለው፡ የህዝቡና የአገሪቱ  እውነታ ምን ይመስላል?” ብለው ራሰዎትን ጥሞና ወስደው ይጠይቁ።

4/ በየጎሳ ክልሉ ያለውን ” ልዩ ኃይል” እየተባለ የሚጠራውን  ከመከላያ ጋር ይቀላቅሉ።  በተለይ የእርስዎ  የኦዴፓ ብልፅግና  ልዩ ኃይል፣  ኦነግ ሸኔ ተብሎ የዳቦ ስም የተስጠው መሆኑንና  ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። የኦዴፓ ብልፅግና ስዎች ብዙዎቹ ኦነግ መሆናቸውን፤ እርስዎም ኦነግን ይረዱ እንደነበር የነገሩንን ያስታውሱ።

የኢትዮጵያ ህዝብ እልፍ አእላፍ  ያልተመለሱ ጥያቄዎችና ችግሮች  ቢኖሩት፤ አሁን የሚፈልገው  በሰላም ወ’ቶ መግባት ነው። የህግ የበላይነት!

ለተፈጠረው ለአእምሮ የሚዘገንን የዘር ማጥፋትና አሁንም ለሚደርሰው ግፍ  የመጀመሪያው ተጠያቂ እርሰዎ ጠ/ሚ አብይ አህመድ መሆነዎትነ ለአንድ አፍታ እንኳን አይዘንጉት። በግብጽ፣ በሱዳን፣ በወያኔም ሆነ በኦነግ ሸኔ (ይህ ቡድን ሌላው ኦዴፓ ብልጽግና ነው) ማሳበቡ ከተጥያቂነት አያድነዎትም፤ ትንሽ እውነታ እንኳን ቢኖረዎት  ህዝብን መጠበቅና የአገርን ልዋአላዊነት ማስከበር የመንግስተዎ ቅድሚ ስራ ነው። ያለያም ለምን መንግስት አስፈለገ?

ህዝብ የሚፈልገውን እያወሩ ነገር ግን  ዜጋ  በማንነቱ እንደ ከብት እየታረደና  በገዛ ምድሩ እየተሳደደ እስከዚች ሰዓት ደርሰዋል።  ደርሰናል።ብዙዎቻችን ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊነት ክብር ሲደሰኩሩ ስንሰማ ” ልባችን ቀለጠና” መሬት ላይ የምናየውን  እውነታ ላለማየት ዓይናችን ጨፈን።

አሁን ግን ተስፋችን ተሟጠጠ። ቀዩ መብራትም በርቷል። ”በቃ!” ማለት  ” በቃ!”  ነው። ህዝብ ” ስለ ኢትዮጵያ ስንል ሁሉን ታገስን!” ብሎ ነበር።  እንደሚያዩት  የግፍ ፅዋው ሞልቶ ፈሰሰ።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ ሆይ!
በቅድሚያ የህዝቡን ደህንነትና የአገሪቱን ልዋአላዊነት ያስከብሩ። ከዚያ በኋላ ስለ ኢትዮጵያዊነትም ሆነ ስለ ምርጫ ቢያወሩ ሰሚ ያገኛሉ።  የኢትዮጵያ  ህዝብ  በራሰዎ ገዥ መንደርተኛ  ፓርቲና በታሪካዊ ጠላቶቹ   እንድ ገና ዳቦ በውስጥም በውጭም እየነደድ ነው። ስለዚህ ሳይውል ሳያድሩ  በመላው አገሪቱ ያለውን ህዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ  ቆርጠው ይነሱ። እስከ አሁን ያወሩላትን  ኢትዮጵያን በተግባር ያስመስክሩ። ከተግባር ውጭ አደራዎትን ከአሁን በኋላ ስለ ኢትዮጵያዊነት  አንደበተዎን ባይከፍቱ እመርጣለሁ።  ኢትዮጵያ እኮ በፀና ታማለች።

መንግስትዎ ለውጦችን ለማድረግ “ህጋዊ” መሆን አለብኝ የሚላትን ፌዝ ማቆም  አለበዎት። ወያኔ የሰራለትን የኢህአዴግን ካባ አውልቆ የብልፅግና ካባ ሲለብስ ህጋዊነት ያኔ አክትሟል።  ህግዊነትም ከህዝብና  ከአገር በላይ ሆኖ አያውቅም። ዓላማውስ ለህዝብ ለአገር አይደለም ወይ?

ቅድሚያ ለሚሰጠው ሳይሰጡ ቢቀሩና “ምርጫ የችግራችን ሁሉ ቁልፍ  መፍቻ ነው ”  ብለው በዚሁ ከቀጠሉ ግን አገርን፣ ህዝብን እና ራስንም ለውድቀት እንዳይዳርጉ በእጅጉ እፈራለሁ።

ዛሬ እናት ምድራችን በታሪካዊ ጠላቶቻ ተክባ መፈናፈኛ ባጣችበት ወቅት ቅድሚያ የሚሰጠው ልዋአላዊነትን ማስከበርና በየቀኑ እንደ ከብት ለሚታረደው ህዝብ የደህንነት ዋስትና ማስገኘት ነው።

እናም እባከዎ! መጀመሪያ ለህዝብ ደህንነትና ለአገር አንድነት ቅድሚያ ይስጡ። ከዚያ በኋላ ለሁሉም ነገር ይደርሱበታል።

ኢትዮጵያ ለዘላ’ለም ትኖራለች!!!

—–/——
ከፊልጶስ ወርቅነህ
e-mail: [email protected]

 

3 Comments

 1. ተራ ቁጥር #3 እና #4 ጥሩ ምክሮች ናቸው። #2 ከቁጥጥር ዉጭ ነው። #1 ግን አሁን ለመፈጸም አይቻልም፣ ሃገር ሊአፈርስ ይችላል። የሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ መንግስት የመገልበጫ ስትራቴጂ መሆኑም ይታወቃል። ምርጫው ችግር ሁሉ ይፈታል ባይባልም የመጀመሪያው ስቴፕ ነው። አለማድረጉም የራሱ አደጋ አለው።
  በምርጫ ብቻ!

 2. ጠቅላይ ሚኒስትሩ የችግሮቻችን ሁሉ ቁልፍ .. ምርጫ..አሉ??
  “የችግሮቻችን” ሲሉ የጠቅላላ ኢትዮጵያን ችግር ነው ያሉት ወይንስ የእነ ማንን ችግር ነው ለማለት የሞከሩት??

  የትግራይ ክልል ህዝቦች ሚሊየኖች እኮ ዘንድሮ አይመርጡም ፣ የሚታረደው በየጥሻው ተደብቆ ያለው የዘር ፍጅት ሰለባዎች እኮ አይመርጡም ፣ የኮሮና ፍራቻ ያለበት እኮ ለምርጫ ተሰልፎ አይመርጥም ፤ እስከአሁን በነቂስ የተባለለት የተመዘገበው መራጭ ህዝብ ብዛት ቁጥርም ከፓርቲያቸው ከብልፅግና አባላት ቁጥር ያነሰ መሆኑንስ ተገንዝበው ይሆን? ስለዚህ “የችግሮቻችን” ሁሉ መፍቻ ቁልፍ ሲሉ አራጆቹን “ቀጥሉበት ግፉበት መራጭ-አማራን-ሰልፈኛን እያደናችሁ ገድላችሁልኝ ስልጣኔን እንዳራዝም እርዱኝ : እኔም ስልጣን ላይ ከቆየሁ እንደተለመደው በኮንዶ እና በሌላም እየካስክዋችሁ የአረዳችሁልኝን ዘረኞችን ችግሮቻችሁን አስወግጄ ወሮታችሁን እከፍላለሁ” ማለታቸው ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያውያንን ችግር ለማለት አይመስለኝም “ችግሮቻችን” ሲሉ። ምክንያቱም የኢትዮጵያውያንን ችግር የሚፈታበትን ቁልፍ ምርጫ ቢሆንማ ለምን ምርጫን በታቀደለት ጊዜ እንዳይካሄድ አራዘሙ ያኔ ገና? ያኔ ቢያክያሂዱት ይሄኔ ብዙ ህዝብ ለምርጫ ይወጣ ነበር ዘንድሮ ለምርጫ ይወጣል ተብሎ ከሚጠበቀው ህዝብ ቁጥር በበለጠ። በኮሮና አሳበው አራዘሙት ምርጫውን ያኔ ፤ አሁንስ ከኮሮና የበለጠ አደጋ መሀከል ውስጥ ኢትዮጵያኖች እንዳለን ያውቁስ ይሆን?

 3. ይህቺ አገር አሁን ከበፊቱ የባሳ አደገኛ ሁኔታ ላይ ነች፡፡ ትህነግ ሲባል በዛ ኦነግ ሸኔ ይባላል፡፡ መተከል፣ ቤሻንጉል፣ ሱዳን ፣ ግብፅ ሲባል ሌላ ደግሞ ጉድ እየመጣ ነው፡፡ ስንት ኮንቴነር ገጀራ በባንክ ተፈቅዶ ቅድመ የጉምሩክ ዲክለራሲዮን ተሞልቶ ከወጪ አገር እዚህ እሲኪመጣ ምን አይነት ሰንሰለት ነው ያለው፡፡ በዚህ ቼን ላይ ያለ መስመር በደንብ መፈተሸ አለበት፡፡ ኡሁንም መንግስት በተለያየ እርከን ላይ ያለውን ውስጡን በደንብ ካልፈተሸ ገና አስቸጋሪ ሁኔታ ከፊት አለ፡፡ ያመለጠ ገጀራ አለ የተባለውንም በአስቸከይ ቤት ለቤት አሰሳ ሊደረግ ይገባል፡፡
  ይህ ሴራ አገሪቷን እንደ ሩዋንድ ፍጅት በማድረግ አፈራርሶ እንደ ግብፅ ያሉ እና የውስጥ ጠላቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመጠቀም ነው፡፡ በጣም አሳፋሪ ድርጊት አየተሰራ ነው ያለው ቀድሞ በተዘረጋ የተበላሸ አስተዳደር እና አሁን ያለው መንግስትም በውስጡ ብዙ ችግሮች ስላሉበት አገረቷ የመጨረሻ ውድቀት ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡ ማንስ ነው ከዚ የሚጠቀመው??? አሁንም የደህንነት እና መረጃ መረቡ በጣም መጠናከር አለበት ትክክለኛ የመረጃ መስመር ያስፈልጋል ከውስጥ ችግር ፈጣሪ ስላለም፡፡
  መንግስት አሁን ማድረግ ያለበት ምርጫው የግድ መካሄድ ካለበት፣
  1. የሰራዊት አባልን በአስቸኳይ ማጠናከር ስንት ወጣት በየክልሉ አዲስ አባበ ጭምር እና የቀድሞ የተገፉ ወታደሮች ለአገራችን እንውደቅ እያሉ ነው፡፡ ይህን ጥሪ ማፋጠን አለበት፡፡
  2. ያሉትን እውነተኛ የአገር ስሜት ያላቸውን የሰራዊት አባላት ወታደር፣ ፖሊስ በመለየት በየአካባቢው አልፎ አልፎ በመመደብ ከህዝቡ ጋር የጥበቃ ስራ በመሳሪያ ታዞ እንዲያከናውኑ ማድረግ፡፡
  3. በየወረዳው፣ ክፍለ ከተማ እና ክልል ወረዳዎች ያሉ የመንግስት አካለት፣ ፖሊስ ሃይል፣ መከላከያ ሰራዊት ቢሮ የተቀመጡት ጭምር እየወጡ ከህዝብ ጋር የተቀናጀ ስራ መስራት ሲስተሙ እንዲዘረጋ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቸኳይ ትዕዛዝ መስጠት፡፡ ይኽው አማራ ክልል እኮ አማራጭ ቢያጣ በጎበዝ አለቃ ለመመራት እየሞከረ ነው፡፡ መንግስት አሁን መተኛት የለበትም፡፡ ቀን ለሊት ከህዝብ ጋር መስራት አለበት፡፡ ነገ አዛኝ ከመመሰል አሁኑኑ ይሰራ ገዳፋው ደግሞ ለሁሉም ነው፡፡ አገርም ትፈርሳለች፡፡ መንግስት ምርጫው ይደረጋል እያለ ስለሆነ ህዝብ አካባቢውን ይጠብቅ ብች ማለት ዋጋ የለውም፡፡ አብሮ ከህዝብ ጋር መስራት አለበት በአስቸኳይ በደርግ ጊዜ እኮ ጥበቃ እየተባለ ቤት ለቤት ተዘርግቶ ነበር፡፡ በጣም ይታሰብበት፡፡ ህዝብ ከባድ ስጋት ላይ ነው ያለው፡፡ በመንግስት ስልጣን ውስጥ ተቀምጠው ሴራ የሚጠነስሱም ነገ ለነሱ ልጆችም መዘዘ እያመጡ እንደሆነ ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ መቼም የሩዋንድን፣ ሶሪያን የሚመኝ አንዴ ለይቶለት ስለበደ ከአሁኑ ያለው አማራጭ በሙሉ መሰራት አለበት፡፡

  4. በመጨረሻም የገጀራው ጉዳይ እንዲህ በቀላል የሚታይ አይደለም ሌላ ማጣራት መከናውን አለበት፡፡ መንግስት ከህዝብ ጋር መስራት ያለበት ወቅት ላይ ነው፡፡ በአስቸኳይ ስርዓቱ ቢዘረጋ ጥሩ ነው፡፡ ይህች አገር ጠላት እንደበዛበት ይታወቃል፡፡ ሁሉም ይህን ጋሪጣ ለመታገል ይተባበራል፡፡ የፌዴሬሽን እና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በውስጣቸው ችግር ቢኖርባቸውም ዝም ብለው ቁጭ ማለት የለባቸው፡፡ ነገ የባሰ እልቂት ቢፈጠር ሀገር ብትፈርስ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ማወቅ ያለባቸው ይመስለናል ታዲያ የደሃ ህዝብን ብር በደሞወዝ እና ጥቅማጥቅም መውሰድ ብቻ ምን ፋይዳ አለው??? በአጎረስኩኝ ሆነና የዚህች አገር ተስፋ፡፡

  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.