በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት – ክፍል 15

ለተከበራቹህ ወገኖች                                                                           

የኮሮና ልምድ ከጀርመን – የፌደራሉ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እገዳ፣ ክትባት፣ ቅጣቶች እና የኢትዮጵያ ሁኔታ                     

22.04.2021

ካለፈው በመቀጠል በልውጡ የኮሮና ተዋህሲ እና ሊገታ ባልተቻለው ሶስተኛው ዙር ወረርሽኝ ምክንያት በ21.04.2021  የጀርመን ፓርላማ ከፍተኛ ተቃውሞ በታጀበው ስብሰባ ላይ ቀጣይ ጥብቅ የሆነ የፌደራሉ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እገዳ (emergency brake/Notbremse) የተባለውን የያዘ የኢንፊክሽን ህግን ማሻሻያ አጽድቋል። የፓርላማውን ውሳኔ የፌዴሪሽን ምክር ቤቱ አጽድቆት እና የጀርመን ፕሬዝዳንት ፈርመውበት ከሚቀጥለው ቅዳሜ 24.04.2021 እስከ ሰኔ 2021 መጨረሻ  ድረስ በሙሉ ጀርመን ተግባራዊ ይሆናል።  ይህንን ለመቃወም የጀርመን ፓርላማን ከበው የነበሩ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የተቃውሞ ሰልፈኞችን የሰልፍ መመሪያውን በተለይም ርቀትን ደንብን አላከበራችሁም በማለት ፖሊስ በትኗቸዋል።

በጀርመን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትም በዚህ ሳምንት ሳይሻሻል በከፍተኛ በመጨመር 3ኛውን ዙር ተያይዞታል። በሰባት ቀናት ውስጥ ከ100,000 ነዋሪዎች መካከል የተገኘው ኢንፌክሽን በአማካይ በቁጥር 13 ጽሁፌ ከገለጽኩት 65 እና በቁጥር 14 ከ ጻፍኩት 108  አሁን ወደ 160 ጨምሯል። የሚያዙትም በቀን ወደ 30ሺ ይጠጋል። የሟቾቹ ቁጥር በቀን አሁንም ቢሆን ከ300 በላይ ነው። ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በጀርመን 3.2 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሲያዙ 2.8 ሚሊዮን አገግመዋል። ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 80,4ሺ ደርሷል። የታማሚዎችም ከዕድሜ አንጻር በእድሜ ከገፉት ወደ ወጣቶች መቀየሩ ቀጥሏል። ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው በእድሜ የገፉት አስቀድመው እየተከተቡ በመሆኑ እና የተቀየረው የቫይረሱ አይነት ከባድ አጥቂነት አለው ስለሚባል እና ወጣቶች ላይ ቸልተኝነት ስለሚበረታ ነው። ባለፈው እሁድ በኮሮና ወረርሽኝ ህይወታቸውን ላጡት ሰዎች መታቢያነት ፕሬዝዳንቱ ባስጀመሩት ብዙ ሰው በመኖሪያ ቤቱ መስኮት ላይ ሻማ በማብራት ተካፍሏል።

በተከታታይ ሰባት ቀን 100,000 ነዋሪዎች መካከል አዳዲስ ኢንፌክሽኖች ከ100 በላይ በሚሆኑባቸው ወረዳዎች፣ ሪጅኖች፣ ከተማዎች እንደሚከተለው ይህ የፌደራሉ አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ እገዳ” ተግባራዊ ይሆናል።

 1. ማህበርዊ ግንኙነት

ከገዛ ቤተሰብ በተጨማሪም አንድ ሰው ከሌላ አንድ ቤተሰብ ጋር ብቻ የሚደረጉ ማህበራዊ ግንኙነቶች ብቻ የተፈቀዱ ሲሆን እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆች ከዚህ ነፃ ናቸው። ለቀብር የሚፈቀደው 30 ሃዘንተኛ ብቻ ነው።

 1. ሰዓት እላፊ

ለሰባት  ቀናት በተከታታይ ከ100 አዳዲስ ኢንፌክሽኖች በላይ በሚከሰትባቸው ወረዳዎች፣ ከተማዎች ውስጥ ከምሽቱ 4 ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት (10 p.m. – 5 a.m.) ጠንካራ ገደብ ሲኖር ከቤት ወይም ከግቢ መውጣት አይፈቀድም። ቢሆንም ድንገትኛ፣ ለአስቸኳይ ስራ፣ ​ወይም ውሻን ለማናፈስ እና አንድ ሰው ለብቻው የሚደረግ የሩጫ ስፖርት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ይፈቀዳል።

 1. የዕለታዊ ፍጆታ ጅምላ ሻጮች እና ቸርቻሪዎች፣ የገበያ ቦታዎች፣

ከምግብ ቸርቻሪዎች፣ የሸቀጣሸቀጥ ሱቆች፣ ከመድሃኒት መደብሮች በስተቀር ሱቆችና  የገበያ ቦታዎች ለመሄድ አስቀድሞ የኔጋቴቭ የምርመራ ናሙና በማቅረብ እና አስቀድሞ ቀጠሮ በመውሰድ ብቻ ይሆናል። በተከታታይ ለሰባት ቀን ከ 100,000 ነዋሪዎች መካከል  አዳዲስ ኢንፌክሽኖች ከ160 በላይ  ከሆነ ግን ከገበያ ቦታዎች/ሱቆች አስቀድሞ በኦንላይን የታዘዘው ብቻ ነው ሂዶ ከውጭ መውሰድ የሚቻለው (click and collect)።

 1. ውጫዊ መናፈሻዎች፣ ከቤት ውጭ ዝግጅቶች

በሰባት ተከታታይ ቀናት ከ100 በላይ በሚሆኑ የቫይረሱ ክስተቶች፣ ሁሉም ባህላዊ ዝግጅቶች ቤትም ይሁን ውጭ፣ የታገዱ ናቸው። ውጫዊ የመናፈሻዎች፣ የእጽዋትና የአትክልት ስፍራዎች እና መካነ አራዊት መጎብኘት የሚቻለው  አሉታዊ (የኒጋቴቭ)  የናሙና ሙካራ በማቅረብ ነው።

 1. ጸጉር ማስተካክያ ቦታዎች፣ ስፖርት፣ የቤት ቢሮ

እንደ ፀጉር ማስተካከያ እና እንደ እግር እንክብካቤ ያሉ አገልግሎቶች አሁንም እንደቀጠሉ ቢሆንም አስቀድሞ አሉታዊ ምርመራ ውጤት ማቅረብ ያስፈልጋል።

ንክኪነት የሌለባቸው ስፖርቶች ከቤት ውጭ ለብቻ ፣ ባልና ሚስት ወይም በአንድ ቤት ውስጥ ላሉ ብቻ ይፈቀዳሉ። ቢበዛ ቀጥራቸው አምስት የሆነ ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ንኪኪነት የሌላቸውን ስፖርቶች እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል ፡፡

አሰሪዎች በሚቻልበት ቦታ ለቤት ቢሮ (Homeoffice) ማመቻቸት እና መስሪያ ቤቶች ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ ነጻ የናሙና ምርመራ ማቅረብ ግዴታ አለባቸው ፡፡

 1. ትምህርት ቤቶች

ለሰባት ቀናት በተከታታይ ከ165 አዳዲስ ኢንፌክሽኖች በላይ ከሆነ በአካል የመገኘት ትምህርት ክልክል ነው። እስከዚያው ግን ለትምህርት ቤት ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለመዋዕለ ሕጻናት ሰራተኞች የኮሮና ናሙና ምርመራዎችን  በተቻለ ፍጥነት በሳምንት ሁለት ምርመራዎችን ማድረጋቸው ይቀጥላል።

 1. በኢንፌክሽን መከላከያ ሕግ ጥሰት እና ቅጣቶች

በኢንፌክሽን መከላከያ ሕግ ውስጥ ጥሰቶችን እንደየክብደቱ ከሚመለከተው የወንጀል ቅጣት በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎ ተግባራዊ እየሆነ ነው። የበርሊን ከተማ 67 የቅጣት ዓይነቶች አሉት ለምሳሌ:-

 • ርቀትን አለመጠበቅ፣ ከአንድ ሰው በላይ ማህበራዊ ግንኙነት ማድረግ ከ100-500 ዩሮ፣
 • ስምና አድራሻን አለመመዝገብ እስከ 10ሺ ዩሮ፣
 • የተሳሳተ አድራሻ ማስመዝገብ ከ5መቶ- 1ሺ ዩሮ፣
 • በመስሪያ ቤቶች፣ በሱቆች የኮቪድ ማስጠንቀቂያ ምልክቶችን አለመለጠፍ እስከ 50ሺ ዩሮ፣
 • ለሰራተኞች የናሙና ምርመራ በሳምንት እንድ ጊዜ አለማቅረብ ከ10ሺ-25ሺ ዩሮ፣
 • ከ50% በላይ የቢሮን ቦታ መጠቀም እስከ 50ሺ ዩሮ፣
 • ከተፈቀደው በላይ ሰዎችን ያስገባ እስከ 15ሺ ዩሮ፣
 • ሰዎች በአካል የሚገኙበት የቤት ውስጥ ቲያትር ሲኒማ የመሳሰሉት ያሳየ እስከ 10ሺ ዩሮ፣
 • ሪስቶራንት መክፈት ወይም ውስጥ ማብላት፣ ሆቴል ወይም ማደሪያ ለቱሪስት ማከራየት ከ1ሺ-10ሺ ዩሮ፣
 • ሴተኛ አዳሪ ቤቶች፣ የኢሮቲክስ መታሻ ቤቶችን መክፈት እስከ 10ሺ ዩሮ፣ ለተጠቃሚው ከ250-5ሺ ዩሮ
 • ካራንቴና መጣስ 5ሺ ዩሮ፣
 • የሃሰት ናሙና ማቅረብ እስከ 10ሺ ዩሮ፣
 • የበሽታው ምልክት ታይቶበት አለመመርመር ከ1ሺ ዩሮ፣ ወዘተ ናቸው።
 1. ቀጥይ ውሳኔዎች

ከዚህ በፊት የነበሩት ዝግ ቦታዎች፣ የሎክዳውን እርምጃዎች እና በገደብ የተፈቀዱ እርምጃዎች እንደጸኑ ይቆያሉ። ይህ የሃይማኖት ቦታዎችንም ይጨምራል። ምንም የተቀየረ ነገር የለም።

 

 1. ክትባት

እስከዛሬ ወደ 17.3 ሚሊዮን ሰዎች አንድ ጊዜ ያህል የተከተቡ ሲሆን 5.6 ሚሊዮን  ሰዎች ደግመው ተከትበዋል። አሁንም ቢሆን ይህ ዝግተኛ አካሄድ እንደተጠበቀው ሊፈጥን አልቻለም። የAstraZeneca ክትባት የደም መርጋትን ሊያመጣ ይችላል በሚለው ክስተት የተነሳ ለጊዜው ተቋርጦ የነበር ሲሆን አሁን ግን እድሚያቸው ከ60 በላይ ለሆኑት እንዲሰጥ በመታዘዙ የ66 ዓመቷ ቻንስለር ሜርክለም ባለፈው ሳምንት ይህንን ተከትበዋል። ቢሆንም ሰው አሁንም ቢሆን AstraZeneca  የመከተብ ፍላጎቱ ዝቅተኛ ነው። የተሻለ ክትባት ለማግኘት ብለው እንደቱሪዝም በአስጎብኚ ተሰባስበው ሩሲያ ሂደው የተከተቡም አሉ። ክትባት ቢኖርም ርቀትን መጠበቅ እና ማስክ ማድረግ ግዴታ ነው። በበርሊን ከተማ ደግመው ከተከተቡት 300ሺ ሰዎች መካከል 150 ሰዎች ወረርሽኙ የያዛቸው ሲሆን 88ቱ በጽኑ ሲታመሙ ሌሎቹ 6 ታማሚዎች ሆስፒታል ሲገቡ ህይወቱ ያለፈ ግን የለም።

ጀርመን ውስጥ ከ400 በላይ የመከተቢያ ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን ይህም ተንቃሻቃሾችን አይጨምረም። በቅርቡም ክትባት በግል ክሊኒኮች፣ የቤት ሀኪሞች መሰጠት ተጀምሯል። መስሪያ ቤቶችም ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው።  ከሰኔ ጀምሮ የተለያዩ እድሜ እና ጤና ተኮር ለሆኑ ቅድሚያ መስጠት ሂደቱ እንደሚያበቃ እና ለመከተብ የሚፈልግ ማንም ሰው እንደሚመዘገብ ነው የሚጠበቀው።

ቢሆንም በአብዛኛው የጀርመን ግዛቶች AstraZeneca መከተብ የሚፈልጉ ያለ ወርፋ እንደሚያገኙ ይነገራል።

 1. ክትባት እና የሴራ ቲዮሪ

ክትባቱን በተመለከት ብዙ የሚባሉ የሚገርሙ ነገሮች አሉ። በእርግጥ  መውሰድ አለመውሰዱ የእያንዳንንዱ ግለሰብ መከበር የሚገባው መብት ቢሆንም ሁሉም ባይሆኑ የክትባት ተቃውሚዎች በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ ሃገሮች የሚያሰሙት ከሎጂክ ውጭ የሆኑ አባባሎች አሉ። በተለይም ፈሳሹ ክትባት ወደ ማይክሮቺፕነት ይቀየራል የሚሉት በምን አይነት የቴክኖሎጂ ሂደት አንድ ፈስሽ ስጋ ውስጥ ገብቶ ኤሌክትሮኒክስ እና የመገናኛ መስሪያ ሆኖ መቀየር እንደሚችል ይህም በሚሊዮን ሊትር የተዘጋጁት ፈሳሽ ክትባቶች ነው ብሎ ማሰብ አለም ጠፍጣፋ ነች ክሚለው የከፋ ይመስለኛል። ማይክሮቺፕ ማለት በጣም የተወሳሰቡ የማይክሮ ኤሌክትሮኒክስ ክፍሎች ፣ የተቀናጁ ሰርኩይቶች ፣ ትራንዚስተሮች እና ዳዮዶች እንዲሁም አብዛኛው ከሲሊኮን የተሰሩ ዳሳሾች  ሴሚኮንዳክተሮች የያዘ ነው። ሰውን ለመጉዳት ወይም ኢትዮጵያን ለመጉዳት ነው የሚባል ከሆነም ሌላ አገሮችን እንደምሳሌ እስራኤልን መውሰድ ይበቃል። እስራኤል ካሏት 9 ሚሊዮን ነዋሪዎች ከ5 ሚሊዮን በላይ ተከትበዋል።  እስራኤል ለህዝቧ ምን ያህል እንደምትጨነቅ የታዋቀ ነው። ታዲያ እንዴት ህዝቧን የሚጎዳ ነገር ታደርጋለች? አውሮፓውያን የህዝባቸው ቁጥር በመቀነሱ እና እንደ አፍሪካ እና እስያ ባለማደጉ እየተቆጩ ባሉበት ሁኔታ እንዴት ብለው ያውም የራሳቸውን ህዝቦች ይቀንሳሉ? ለህዝቧ ጥቅም ስትል በታሪኳ በመስፋፋት የምትታወቀው እንግሊዝ 33 ሚሊዮን ህዝቧን ስትከትብ አሜሪካ ደግሞ 133 ሚሊዮን ከትባለች። እነዚህ አንድ ዜጋቸው ከተነካ መብቱን ለማስከበር ጦር ለመማዘዝ የሚቃጣቸው አገሮች የራስቸውን ዜጋ „ሙሉ በሙሉ“ እንዴት ያጠፋሉ? ይህስ ካስፈለገ ለምን እስከ ኮሮና ክትባት ይጠበቃል? ቁጥራቸው የበዛ መድሃኒቶች፣ የመጠጥ ውሃ፣ ምግቦች፣ የምንተነፍሰው አየርን በቀላሉ መበከልም የሚችሉ ናቸው። ጀርመን ውስጥ ብቻ  ከምድር በታች በከፍተኛ ጥበቃ በሚገኘው ወረርሽኞች እና  ተላላፊ በሽታ ባዮሎጂካል የምርመራ ማዕከል ውስጥ በዓለም ጠፍተዋል የተባሉት እንደ ፈንጣጣ እና አደገኛ የወረርሽኝ ዝርያዎች የተከማቹበት ቦታዎች አሉ።  እነዚህን በከፍተኛ ጥበቃ የተያዙም ናቸው።

 1. የኢትዮጵያ ሁኔታ

እስካሁን ግማሽ ሚሊዮን ሰው ኢትዮጵያ መከተቡ ትልቅ እርምጃ እና የሚያስመሰግን ነው። ቢሆንም ኢትዮጵያ ውስጥ የወረርሽኙ መጨመር እና አካሄዱ እጅግ የሚያሳዝን አስጊ ነው።

በቅርቡ የሚታዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚያደርጉት ሰልፎች  ሃዘናቸውን እና  ስሜታቸውን የሚገልጹበት ቢሆንም እንኳ አዘጋጆቹ በማንኛቸውም መልኩ ቢሆን፣ ተሳታፊዎቹ ማስክ አድርገው እንዲገኙ መምከር እና ማስጠንቀቅ የመጀመሪያው ስራ መሆን የሚገባው ነበር። ማይንማር የሚባለው ሀገር በየቀኑ የሚደርገውን ሰላማዊ ሰልፍ ያውም ከፖሊስ ጋር ያለውን ደም አፋሳሽ ግጭት እንኳን ስናይ ተሰላፊዎች ማስክ እንደማይለያቸው ነው የታዬው።  ሌላው ኢትዮጵያ የሚታየው ማስክ አድርገናል ለማለት ኦፊሻል ካሜራ ላይ በማስክ የሚነሱ ግን የግል የሶሻል ሚዲያ ፎቶዎች ተሰብስብው ተቃቅፈው ያለማስክ ወይም አገጭ ላይ ባሉ ማስኮች የሚነሱ ታዳሚዎችን ማየቱም ያሳዝናል። ስለ ኮሮና እየጻፉ፣ እያወሩ፣ በጉልበት፣ በገንዘብ እየረዱ እና ችግሩን በአይን እያዩ ይህንን ምስል ማየት ተስፋ የሚያስቆርጥና የአመለካከት ለውጥ እንዳልመጣ የሚያረጋግጥ ነው። ሌላው ደግሞ እኛን አይነካንም፣ አሁን ሌላ ችግር አለብን፣ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ጋር አናወዳድር የሚሉ አዘናጊ ገለጻዎች ይስተዋላሉ። ወጣቶችም አይዘንም ብለው እንኳን ቢያስቡ አባቶቻቸውን፣ እናቶቻቸው፣ አያቶቻቸው፣ ዘምዶቻቸውን ማስያዝ እንደሚችሉ ማወቅ እና ማህበራዊ ሃላፊነትን መውሰድ እንደሚገባቸው ማሳወቅ አስፈላጊ ነው። በቅርቡ በጀርመን ቴሌቭዥን አንድ አምቡላንስን ያጀብ ዘጋቢ ፊልም የሚያሳየው ኮሮና የታመሙ ሰዎች እንዴት በጽኑ ታመው በአምቡላንስ እንደሚመጡ፣ በጽኑ ህሙማን ክፍል የሚደረግላቸው ህክምና፣ በተለይም ሀኪሞች የመጨረሻውን ህልፈት ህይወታቸውን ሲከታተሉ፣ የልብ ምታቸው እየተስለመለመ ሲጠፋ፣ መሳሪያዎችን ሲያስቆሙ እና ቤተሰቦቻቸውን ሲያረዱ የሚያሳይ እና የአእምሮ የማይረሳ ምስል የሚፈጥር ነበር። መሰል ዘጋቢ ፊልሞችን በአገራችን ማሳየቱ ማስተማሪያ ይሆናል።

አንድ ኢትዮጵያ ያለ ቅርብ ጓደኛዬ እና ከፍተኛ የህክምና ዶክተር በኮሮና ወረርሽኝ ተይዞ በሞት እና በህይወት መሃከል በጽኑ ህሙማን ክፍል ለሳምንታት ያሳለፈውን አስከፊ ጊዜ ሲያጫውተኝ ምን ያህል የህክምና ሰዎች ተጋላጭ እንደሆኑ እና ኢትዮጵያ ገና ብዙ የተወሳሰቡ ችግሮች እንዳሉ ያሳያል። እንደሰማሁት ከጥቂት ወራት በፊት ደም እንዳይረጋ የሚሰጠው ሂፓሪን Heparin ዋጋ 45 ብር የነበር ሲሆን ከጥቂት ሳምንታት በፊት 500 ብር የደረሰው አሁን 1500 ብር ገብቷል። የኦክስጂን መተነፈሻ የሚያገልግሉ ስሊንደሮችን የመኪና ጋራዦች በከፍተኛ ዋጋ እንደሚያከራዩ፣ የመተንፈሻ መሳርያዎች እጥረቶች ምን ያህል ችግሮቹ እንደፈጠሩ የሚያሳይ ሲሆን በውጭም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን በዚህ ላይ ልንረዳ የምንችልበት ሁኔታ ቢፈጠር መልካም ሲሆን ከኮሮና ጋር በተያያዘ መልኩ መድሃኒቶች እና መመርመሪያዎች ላይ ዋጋን መቆጣጠር እና መደጎም ተገቢ ነው።

ለመደምደሚያም በጀርመን በየና ከተማ ያለው ሆስፒታል ማክሮባዮሎጂስት እና ኢፕዶሞሎጂስት ሃላፊ የሆኑት ኢትዮጵያዊ ዶ/ር ስንታየሁ አሰፋ ከጋዜጠኛ ሀይሉ ማሞ ጋር ያደረጉትን ውይይት ትምሀርት ሰጪ የሆነና በዚህ ሊንክ ሊታይ የሚገባው መሆኑን እጠቁማልሁ። https://youtu.be/cwoOH29bl2g

መፍትሄዎች በእጃችን ሲሆኑ በዋናነት ክትባት፣ ፈጣን ናሙና ምርመራ፣ ማስክ፣ ርቅት መጠበቅ፣ እጆቻችንን በተደጋጋሚ መታጠብ፣ አየር ማናፈስ፣ ህጉን ማክበር እና ትዕግስት ናቸው።

የመጀመሪያው ሀብት ጤንነት ነው።
– ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን

ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.