“ ዛሬ ለሃገራችን ብቸኛው መፍትሔና አማራጭ ሁሉን አቀፍ  የሽግግር መንግሥት መመሥረት ብቻ ነው!”

ከኢትዮጵያ አገር አድን ግብረሃይል የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

(April 20, 2021)

weዋሽንግተን ዲሲ

ዛሬ ኢትዮጵያ ሃገራችን በእጅግ አሳሳቢ ሁኔታ በእቶን እሳት ውስጥ  ትገኛለች ፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ በዚህ ልክ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶች ደርተውባት አያውቁም ቢባል ከቶውንም ማጋነን አይሆንም! ሠራዊቷ ሁሌም በተጠንቀቅ  ዘብ ቆሞ ሰላሟን እንዳላስከበርላት  በግብፅ እርዳታና ግፊት ጎረቤታችን ሱዳን ብዙ ኪሎሜትር ወደ ግዛታችን ዘልቃ አገራችንን ከመውረሯም በላይ ከግብፅ ጋር በማበር የአባይን ውኃ እንደፈለጋችሁት አትጠቀሙበትም እያሉን ነው። ሁለቱም ሃገሮች ሉዓላዊነታችንን እየተፈታተኑት ሲሆን ፅንፈኛ ብሄርተኞች በኦሮሚያ ክልልና በጉሙዝ ቤኒሻንጉል ክልል ፣ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ወዘተ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም ብሎም የኦሮሚያን መገንጠል ዕውን ለማድረግ እየሰሩ ሲሆን በተያያዥ በኢትዮጵያ ቀናዒነት የፀናውን  አማራውን ወገናችን ላይ ግፍ ሰቆቃና ግድያ እየፈፀሙበት ይገኛሉ። በአጠቃላይ ዓላማቸውን ለማሳካት አድማሳቸውን አስፍተው  ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር እየተናበቡ ውድ ሃገራችንን ሰላሟን እየነሱዋት ሲሆን ድባቅ የተመታው የሕወሃት ርዝራዦችና ጄሌዎች ከነዚሁ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ጋር በመሆን የሞትና የሽረት ትግል እያደረጉ ይገኛል።

በአገር ውስጥ አገዛዙ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ካለመቻሉም በተለይም በሕወኃት ላይ የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ የድርጅቱን ማንነት ዝቅ በማድረግ ጅንታው ማለትና ሕግ ማስከበር በሚል ቧልት በንፁሐን ዜጎች ላይ የጅምላ ሽብር ፈፅሞ በሽብርተኝነት ለመፈረጅ እንኳን አልቻለም ፤ ይህም ምናልባትም በተመሳሳይ ሽብርተኛው ኦነግን ላለመጨመር እየተፈፀመ ያለ የአገዛዙ ደባ ሊሆን ይችላል!!

ሽብርተኝነት አገሪቷን እየናዳት ዓለም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም ማድረግ ሲቻል ይህንን አገዛዙ ባለመፈፀም ብዙ ዋጋ እንድንከፍል ከመደረጉም በላይ እንደ አንጋፋ አፍሪካዊ አገር ብቃት ባላቸው ዲኘሎማቶች የውጪ ግንኙነቱ ስራውን በአግባቡ ባለመወጣት መንግሥታዊ አቅመ ቢስነቱን አስመስክሯል። የጠላቶቻችንን ኘሮፓጋንዳ ለማክሸፍ የሚመጥን  ፓሊሲም ባለመቀረፁ፣ በሽብርተኛው ቡድንና ደጋፊዎቹ ኘሮፓጋንዳ እንደማርቲን ፕላው የመሰሉ ቅጥረኞቹ በከፈቱት የዲፕሎማሲያዊ  ዘመቻ ምክንያት አገሪቱ በጠላት ተከባ የምዕራቡ ዓለም ታላላቅ መንግሥታት ከኢትዮጵያ ላይ ፊታቸውን ክፉኛ እንዲያዞሩ አስደርጓል። በመሆኑም  እንደዩጎዝላቪያና መሰል አገሮች የአገራችንን ውድቀት  በጉጉት የሚጠብቁ መሆናቸውን ካለመደበቃቸውም በላይ ቀደም ሲል ቃል የተገባላትን እርዳታ በማቀብ  ከዓለም ባንክና ከመሰሉ ድርጅቶች ብድር እንዳይገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ጫና በአገራችን ላይ እያሳደሩባት ይገኛሉ።

ከላይ በመግቢያው ለመግለፅ እንደተሞከረው ሃገራችን ሕልውናዋ እጅግ አሥጊ ሁኔታ ላይ ሲሆን ሥልጣን ላይ ያለው ብልፅግና የተባለው የኢሕሃደግ ውርስ ድርጅት እራሱም የተከፋፈለ ስለሆነ በዘግናኝ ሁኔታ በተደጋጋሚ በገፍ የሚገደለውን ወገናችንን ሊታደገውና ከአራጆቹ ሊከላከለው ካለመቻሉም መኖሪያ ከተማውን ጭምር በእሳት ዶጋ አመድ ሲደረግ ከፅንፈኞቹ ሊያድን አልቻለም። ዛሬ የክልሉ መንግሥት ያሰማራው የኦሮሚያ  ልዩ ሃይል ከኦነግ ጋር በመሆን አማራው ዘግናኝ ጭፍጨፋው ክልሉን ለቆ ዳግም እንዳይመለስ አንገቱን በመቅላት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ በተደጋጋሚ ጊዜ እየተካሄደበት ስንከታተል ይህንኑ በዕማኝነት በብዙኃን መገናኛ  ከሰለባዎቹ አንደበት በቀጥታ እየሰማን ነው። ለመሆኑ በርግጥ አገራችን ወደየትስ እያመራች ነው?

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ ባለሥልጣናት በስፋት በተለያየ መንገድ በክልሉ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው የወገናችን ዘር ማጥፋት ላይ ተካፋይ እንደሆኑ ብዙ ማስረጃዎች ብቅ እያሉ ነው። የፌደራል መንግሥትም የዘር ማጥፋቱን አስመልክቶ በስም ድርጊቱን ላለመጥራት የሚያሳየው ነውረኝነት የዘር ማጥፋት እየተካሄደ መሆኑን አለማመኑ ለፅንፈኛ ወንጀለኞቹ የኦነግና ጉሙዝ ወዘተ ታጣቂዎች እንደዚሁም ለክልሉ መንግሥት ለድርጊቱ እልባት እንዳያገኝ ሽፋን እየሰጠ እንደሆነ ተጢኗል። ስለሆነም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ባለው ተሳትፎ የፌዴራሉ መንግሥት በዘር ማጥፋት ወንጀል ከመጠየቅ ከቶውንም አያመልጥም።

የኢትዮጵያ ሕልውና አደጋ ላይ ሆኖ የመጨረሻ እስትንፋሷን በምትስብበት ሰዓት አገዛዙ በተፅዕኖ የዲሞክራሲ ተቋማትን ቀፍድዶ በመያዝ የጠቀለለውን ስልጣን በምርጫ ስም እንደገና ለማስቀጠል ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተጣደፈ ነው።

እናት አገራችን አሁን የምትገኝበት ቀውጢ ሁኔታና ሰላም መጥፋት እንደዚሁም የጠላቶቿ ከበባ እንኳንስ ምርጫ ለማካሄድ ይቅርና ዜጎች በአብዛኛው የአገሪቱ ግዛቶች በሰላም ከቤታቸው ወጥተው በሰላም መመለስ በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ እንዴትስ በውጥረት ውስጥ ምርጫን ማካሄድ ይቻላል የሚለው የሁሉም ጥያቄ ነው። በሰሞኑ በአጣየ ፣ ምዕራብ ኦሮሚያ ቤንሻንጉልና ጉሙዝ በተጠናና በተቀናጀ ሁኔታ በወገኖቻችን የጅምላ ዘር ማጥፋት እርምጃ ተወስዶ ከሰለባው ተርፈው የቤተሰባቸውን ዕርም አውጥተው ሳይጨርሱ በሳምንቱ ሰሞኑን በከሚሴ የነበረው የአማራ ኃይል እንዲወጣ ተፅዕኖ በማድረግ በድጋሚ በአጣዬ የኦሮሞ ተስፋፊዎች ወረዳ ግዛቶችን ለመቆጣጠር ከአገዛዙ ሠራዊት ጋር የለየለት ጦርነት ከፍተው የወገኖቻችንን ሕይወት አሁንም ከመቅጠፍ አልፈው አማራ ክልል ሠራዊት ልዩ ኃይል አባላት በድንገተኛ ጥቃት ጭምር በገፍ መገደላቸውን እየሰማን ታጣቂው ዕውነት ተራ ሽፍታ ወይስ የአዛዙ እገዛ አለበት የሚያስብል ነበር።

የምርጫ ቅስቀሳ ሲካሄድ  የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዕጩ ተመራጮች እየታሰሩና እየተገደሉ በምንስ ሁኔታ ነው ዜጎች በሰላም ወጥተው መምረጥ የሚችሉት?

በኦሮሚያ ክልል በ178 ግድም የምክር ቤት መቀመጫ ለብልፅግና በችሮታ ላለመስጠት የትኛው የአንድነት ድርጅት ነው ሕይወቱን ሰጥቶ በዚህ እሳት ውስጥ ገብቶ ቀስቅሶ የሚመረጠው? ሰላምና ዲሞክራሲ በሰፈነባቸው ሃገሮች እንኳን ምርጫ ብዙ ውዝግብ ሲያስከትል እያየን፣ ዲሞክራሲ ባልዳበረባትና በተለይም በከፍተኛ የፅንፈኞች ሽብርና ውጥረት ውስጥ በምትገኝ ሃገራችን ውስጥ እንዴት ሕዝብ ዕውነተኛ ናቸው የሚላቸውን ወኪሎቹን በአስተማማኝ ሊመርጥ ይቻላል ተብሎ ይታሰባል?

አሁን በመሬት ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የኢሕአዴግ ውርስ የሆነው ብልፅግና ከቀበሌ እስከ ወረዳና ክልል በዘር በተቃኙ ከ750 ሺህ በላይ ካድሬዎቹ ሰንገው በያዙበትና ሁሉን ተቋማት በነዚሁ ተቀፍድዶ በተያዘበት  የኢትዮጵያን ሕዝብ መሠረታዊ የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ፣ የሰላምና ደሕንነት ጥያቄ ለመፍታት የሚያስችል በምርጫ ስም ሕዝባዊ ይሁንታ የሚያሥገኝ የእኔ ነው የሚላቸውን የድርጅት ተወካዬች በሰላምና በነፃነት ለመምረጥ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ከቶውንም አይታመንም። ጠ/ሚ አብይ አህመድ “እኔ አሸጋግራችኋለሁ” በማለት በየሥፍራው ተንቀሳቅሰው የገቡት ቃል ኪዳን ተዘንግቶና ተክዶ በዘመነ ሕወኃት/ ኢሕአዴግ የነበረው ተረኝነት በርሳቸው አመራር በስፋት ተመልሶ ዕውን እየሆነ ነው!

ከላይ እንደተጠቀሰው የአማራን ሕዝብ ዘር የማጥፋት ፕሮጀክት በስፋት እየተካሄደ ነው ፤ የይስሙላ በሚደረገው ምርጫ ለአገሪቱ በጎጥ መከፋፈል መንስዔ የሆነው ሕገመንግሥትና የዚህ ተዋናይ የሆኑት በዚሁ ስሌት የተቀናጀው የክልልና ማዕከላዊ መንግሥት ቅርፅ ተቀይሮ የአገራችንን ሉዓላዊ አንድነት በዕውን የሚያስጠብቅ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከፍ የሚልባት አገር ከፊታችን ዕውን ይሆናል ብሎ መቀበል በመሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ካለመገንዘብና ጥቅል የኃይል አሰላለፉን ካለመረዳትና ካለመገንዘብ ካልሆነ በስተቀር ምርጫው ይቀጥል ማለት በተለይም በኦሮሙማ የበላይነት አሁንም የወገኖቻችን ሰቆቃ እንዲቀጥል፣ በአጠቃላይ ቀውሱ አገር አቀፍ ሆኖ ኢትዮጵያ ከቶውንም እንደ ሶርያ፣ የመን ወዘተ ህልውናዋን እንድታጣ መፍቀድ እንጂ ሌላ ትርጉም ሊኖረው ከቶውንም አይችልም።

የጠ/ሚ አብይ አህመድ አገዛዝ ሥልጣን ላይ የቀጠለው ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሕዝባዊ አመጽ በመንተራስ የተጠበቀውን ሥር ነቀል መንግሥታዊ ለውጥ ማምጣት ሳይችል የሕዝቡ የለውጥ ስሜት ተቀልብሶ በጥገናዊ ለውጥ ባለፈው ሶስት ዓመት የፓለቲካ እስረኞች ከመልቀቅ ጀምሮ የሕዝብን ቀልብ በመሳብ ብዙም ሳይውል ሳያድር  ሰላማዊ የድርጅት መሪዎችን እንደ እስክንድር ነጋ ወዘተ መልሶ የማሰርና እንዲሁም ከእስር ፈተናል ብለው በውጪ የሕክምና ዕርዳታ እንዳያገኙ ጭምር በሕይወታቸው አገዛዙ በመወሰን የበቀል እርምጃ ከማጧጧፍ ወዘተ የተገባውን ፍትህ የማስፈን  ቃሉን ሰብሮ አልፎ አቅጣጫ ቀይሮ ይባሱኑ የአማራን ዘር የማጥፋት ፕሮጀክት አባብሶ በሥራ ላይ እንዲውል ከማድረግ በዘለለ አንድም ለውጥ ተብየው የፈየደው ነገር የለም።

ስለሆነም የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አገዛዝ በሁሉም መመዘኛ ሊታመን ሳይችል ቀርቶ የሃገሪቱን ችግር ከዕለት ወደ ዕለት ተባብሶ መቀጠሉ፣  ቀውሱ በዋና ከተማችን አዲስ አበባ አቅራቢያ ሸዋ ዙሪያ አጣየና ደብረብርሃን መዝለቁን በኦነግና ሸኔ የኦሮሞ ግንጠላ ግቦች በርካታ መንደሮች በሸዋ ሮቢት አካባቢ መጋየታቸውን የመከላከያ ልዩኃይል አካባቢውን ለቆ ማፈግፈጉን በሰሞኑ ተከታትለናል። የአገራችን ዕጣ ፋንታ ወደ መጨረሻው የጥፋት ምዕራፍ መሸጋገሩን ለመገንዘብ የማያዳግት ከመሆኑም በላይ በውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋትና ውኃችንን ለመጠቀም በሕዳሴ ግድብ ዕውን መሆን ድርድር ፍፃሜ ከማጣቱም በአጠቃላይ የአገራችን ሉዓላዊነት ለውጭ ጠላቶች ክፉኛ መጋለጡን ከልብ እናት አገራችንን የምንወድ ሁሉ በእጅጉ እያሳሰበን ጭምር ይገኛል።

የጠ/ሚ አብይ አህመድ አገዛዝ ኢትዮጵያን አሸጋግራለሁ የሚለው ቃል ተክዶ ከሕወሃት ዘመን እጅግ ወደከፋ የመከራ ዘመን የመለሰን ስለሆነ ሁሉን አካታች የሽግግር ሂደት ባስቸኳይ ዕውን ካልሆነ በስተቀር ሃገራችን ለዘመናት አይታ በማታውቀው ደም መፋሰስ የታጀበ ቀውስ ውስጥ እንደምትገባ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል።

የኢትዬጵያ አገር አድን ግብረኃይል በደረሰበት ድምዳሜ ሃገራችንን ከዚህ ነውጥ ሊያድናት የሚችለው የዕርቅና ሰላም የጋራ ውይይትና በተለይም ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥትመመሥረት ብቸኛው  መፍትሔ ነው። እናት አገራችንን ኢትዮጵያን ለኦሮሙማ ግብ አመቻችቶ ለመሰንጠቅ የተጀመረው ፕሮጀክት ዛሬም ይሁን ነገ በሌላው ኢትዬጵያዊ ዜጋ ለአንድ አፍታም ብዥታ ውስጥ በመግባት መዘናጋትና እንደ ተራ ግጭት ፈፅሞ ማየት ከቶውንም አይገባም። ስለሆነም ኢትዮጵያን ግባቸው የአደረጉ የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች ከተናጥል ጉዞአቸው ተቆጥበው በአንድ ስብስብ መክረው አገሪቱ የምትገኝበትን ሁኔታ ከልብ በማጤን በምርጫ ውጤትና ለውጥ ይመጣል ከሚለው ሕልም ወጥተው ገዢው መንግሥት የእርቅና የሰላም የሽግግር መንግሥት እንዲቀበል በአንድነት ሊቆሙ ተፅዕኖ ሊያደርጉ ይገባል እንላለን።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአገር ውስጥም በውጪም የምንገኝ አገራችን በአደገኛ ምዕራፍ ውስጥ የምትገኝ መሆኗ ገፈቱን እየተቀበልን ሊነገረን አይገባም። የኢትዮጵያን ሕልውና የምንሻ ሁሉ ባለድርሻ አካላት ሁሉ በአንድ የጋራ መድረክ ወጥተው በጥልቀት በመምከር በዘላቂነት የእናት አገራችንን ሕልውናን ለማስቀጠልና ብሎም ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ተፅዕኖ እንድናደርግናሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት  እንዲመሠረት ድምፃችንን ከፍ አድርገን እንድናሰማ የኢትዮጵያ አገር አድን ግብረኃይል አገራዊ ጥሪውን ያቀርባል።

ኢትዮጵያን በፅናታችን እናስቀጥላታለን!

                                                     ኢትዮጵያ አገር አድን ግብረሃይል

——————————————————————————————————————————————-

ስሜን አሜሪካ Contact- ethiopiahageraden@gmail.com

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.