እንንቃ!!! – በህይወት አበበ መኳንንት

altayeለማንኛዉም ችግር መፍትሔ ለማግኘት በመጀመሪያ ችግሩን ማወቅ እና እዉቅና መስጠት ያስፈልጋል። ሀገራችን የገባችበት ማጥ ቀላል አይደለም። የወደፊቱም እስካሁን ከሆነው የበለጠ አስጊ ነዉ። ህዝቦቿ ተጨንቀዋል አብዛኛዉም ግራ ተጋብቷል።ትላንት በሩቅ እንሰማ የነበረዉ መጥፎ ዜና ባንድም በሌላ በራችንን አንኳክቶ እየመጣ ነዉ። ታድያ ለዚህ ሁሉ ለደረሰ መከራ እና ስቃይ ሀላፊነት የሚወስደዉ ማነዉ? ለምንስ ዓላማ ነዉ? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ጥያቄዉን እንደተረዳንበት መንገድ እና ለነገሮች ካለን አመለካከት በመነሳት የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፦ አንዳንድ ሰዎች ሀገሪቷ ታላቅ የለዉጥ ሂደት ላይ ናት ስለዚህ ይህ መንገጫገጭ የሚጠበቅ ነዉ ብለዉ ያምናሉ። ሃገሪቷ እየገጠማት ያለዉ ነገር የሂደቱ አካል ነዉ እንዲሁም በዚህ ሂደት ዉስጥ ጥቂቶች መስዋእት መክፈላቸዉ የማይቀር ነዉ ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታይ መልኩ ግፍ አና መከራ እያስተናገደች እንደሆነ እንዲሁም በ21ኛው ክፍለ ዘመን ሀገርን ለመለወጥ ግፍ እና መከራን ማሳለፍ ተቀባይነት የለዉም ብለዉ ያምናሉ። ዜጎችም ለዚህ መሰዋእትነት መክፈል የለባችውም ብለዉ ይሞግታሉ። ሰለዚህ እነዚህ ሁለት ጽንፍ ከያዙ አስተሳሰቦች የሚገኘዉ የመፍትሄ ሀሳብ ለየቅል እንደሚሆን ግልጽ ነው። አሁን ሀገራችን ላይ እየሆነ ያለዉ ነገር ይህ ነው። ዜጎች ሀገራቸዉን ወደ ተሻለ መንገድ ለመለወጥ ሳይሆን በማንነታችዉ ብቻ መስዋእት እየሆኑ ነዉ። አርሰዉ፣ ዘርተው፣ አጭደዉ፣ ወቅተው፣ ከምረው ባሉበት እጃችው ዛሬ አስክሬን እየተሸከሙበት ነው። በርግጥ አስክሬን ለመሸከምም በህይወት መትረፍ ያስፈልጋል። ታድያ በየትኛው ስሌት ነዉ ይህ የለዉጥ ጉዞ የሚሆነዉ። ይህ በማንነቱ በቻ [አማራ በመሆኑ ብቻ] እየተጨፈጨፈ ያለዉ ማህበረሰብ ሀገሪቷን በታላቅ የለዉጥ ጎዳና ለማስኬድ ሲባል መስዋእት ለመሆን ፍቃዱን ሰጥቷል ወይ ብሎ መጠየቅ የእያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ገዴታ ነው። አዎ!! ፈቃዱን ሰጥቷል እንዳይባል ጠዋት ማታ በየአደባባዩ የድረሱለኝ ጥሪ እያቀረበ፣ መንግስት ከለላ ይሁነኝ እያለ እየተማጸነ ነው። በርግጥ የመንግስት ተቀዳሚ ሀላፊነትም የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ማስከበር ነው። ሌሎች መብቶች ከዛ በኋላ የሚተገበሩ ናቸዉ። በአሁኑ ሰአት ግን በህይወት የመኖር መብት ህልም የሆነባቸው በርካታ ሰዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ለችግሩ እዉቅና ከመስጠት እና አፋጣኝ እርምጃ ከመዉሰድ ይልቅ ችግሩን ማቃለል ተያይዟል። በየጊዜዉ የምንሰማው የፕሮጀክት ምርቃት እና የመሰረተ ድንጋይ መጣል ወሬ ብቻ ነው። ፕሮጀክት መታቀዱም ሆነ መጀመሩ ክፋት ባልነበረዉ ነበር ነገር ግን እያንዳንዱ ኢትዮጲያዊ ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ ለመሆን ዛሬን በህይወት መኖር አለበት። እነዚህ ፕሮጀክቶች ዛሬ ያጣናቸዉን ሰዎች አይመልሱልንም ወይም ነገ እንዳናጣቸው አያደርገንም። ታድያ አንድ የሀገር መሪ ይሄ ይጠፋዋል ብሎ ማሰብ ዘበት ነዉ። ማንኛዉም ሰው ዛሬ ተነስቶ የሀገር መሪ ልሁን ቢል የማይቻል እንደሆነ ብዙዎቻችን እንስማማለን። ምክንያቱም የአመራር እዉቀት እና ብቃት ያስፈልጋል። በርግጥ ይህ እድል ቢሰጣቸዉ ሀገሪቷን ቀጥ አድርገዉ የሚመሩ ጥቂት ሰዎች አይጠፉም። ታድያ ይህ እዉቀት አለኝ ብሎ ሀላፊነትን የተቀበለ ሰው በእሱ የስልጣን ዘመን ይህ ሁሉ ለመናገር የሚሰቀጥጥ ግፍ ሲፈጸም እንዴት ተቀብሎት ተመቻችቶ ይቀመጣል ብለን ስንጥይቅ ደግሞ የተወሰኑ ምክንያቶችን መዘርዘር እንችላለን።  1) ስልጣኑ የይስሙላ ነው ማለት ዋናው ሰልጣን ያለው የራሳቸዉን አላማ ለማሳካት አማራዎችን እየጨፈጨፉ ያሉ አካላት ጋር ነው። 2) መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ይዞት የመጣዉን ዓላማ ለማሳካት ሀገሪቷ ላይ እየሆነ ያለውን ቀዉስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመዉሰድ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ችግሩን ማቃለል እና ሊሰጠዉ የሚገባዉን ትኩረት መንፈግ እንደ አቋም ወስዶታል። 3) በተለያዩ ክልሎች በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አማራዎችን ክልሉን ለቀዉ እንዲወጡ አለበለዚያ ገድሎ እና አፈናቅሎ መጨረስ ከመንግስት ድጋፍ ያገኘ ዓላማ ነው። 4) መንግስት ችግሩን የተረዳበት መንገድ እጅግ በጣም የተሳሳተ እና እየወሰደ ያለዉ እርምጃም በዛዉ ልክ የተሳሳተ ነው ወይም ባጭሩ የመምራት ችሎታዉ የወረደ ነዉ ማለት ነው።

አሁንም ከእነዚህ ምክንያቶች ተነስተን የምናመጣው መፍትሄ ወይም የምንይዘዉ አቋም የተለያየ ነዉ የሚሆነው። ለምሳሌ፦ ለምክንያት አንድ መፍትሄዉ ሰልጣን መልቀቅ ነው። ሀላፊነት ቦታን ይዞ ነገር ግን የዜጎችን ሞት ለማስቆም እንኳን ስልጣን ከሌለዉ ትክክለኛው እርምጃ ስልጣን መልቀቅ ነው። ካልሆነ የፕሮጀክት መክፈቻ ንግግር እያደረጉ እና ሪቫን እየቆረጡ ብቻ ሀገር መምራት አይቻልም። ለምክንያት ሁለት እና ሶስት ደግሞ ባለጊዜ መሆን ነገ ከተጠያቂነት አንደማያድን ማስተዋል ነው። ይህንን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የሰራዉ ፍግ ህወሃትን የት እንዳደረሰዉ ማየት በቂ ነው። ምንም ይሁን ምን ዘለዓለም የሚገዛ ሰዉ የለምና። ለምክንያት አራት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የያዘዉን የመደመር ፍልስፍና ቆም በሎ መፈተሽ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ሀገር እየመራ እስከሆነ ድረስ ለእያንዳንዱ ዜጋ ህገመንግስታዊ መብት መከብር ሀላፊነት አለበት። ይህ ካልሆነ ግን በተለያዩ ሀገራት እንዳየነው ሙሉ ሃላፊነት የሚወስድበት ጊዜ ይመጣል።

እኛም እንደዜጋ የተለያየ አቋም ቢኖረንም አንድ የሚያደርገን ጉዳይ ግን በምንም አይነት መንገድ የዜጎች መሞት ምክንያታዊ ሊሆን አለመቻሉ ነው። ይህንን ደግሞ ከእስካሁኑ በተጠናከረ መልኩ ልንታገልለት የሚገባ ጉዳይ ነው። አሁንም ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ስለሚደርስባችው ግፍ እና መከራ በአንድነት ቁመን ልንቃወም ይገባል። በእያንዳንዱ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ የመንግስት ባለስልጣናት ሀላፊነታቸዉን እንዲወጡ ልንሞግታቸዉ እና ጫና ልናሳድርባቸው ይገባል። ሀገሪቷን ከገባችበት ቀዉስ ማዉጣት ግዴታቸው ነዉ። የተኛንም ከእንቅልፋችን ልንነቃ ይገባል። ነገ በቤታችን ሲመጣ መንቃታችን አይቀርም ነገር ግን ዛሬ ላይ ቀድመን መንቃታችን ነገ በቤታችን ላይ እንዳይመጣ ለማድረግ ያስችለናል።

እያንዳንዷ ነፍስ ዋጋ አላት!!!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.