“ሳይደወል ቅዱስ …” መኮንን  ሻውል  ወልደጊዮርጊስ

ህወሃት /ኢህአዴግ ድፍን ኢትዮጵያን በጠመንጃ አሸናፊነት ” በፈላጭ ፣ ቆራጭነት ” እየገዛ  በነበረበት ወቅት ፣አንድ የአፋር ሽማግሌ እንዲህ ብለው ለምሳሌ የሚበቃ ፣ንግግር ተናግረው ነበር ይባላል ። እንግዲህ እሳቸው እንደ አለቃ ገብረሃና ወይም እንደ ሙላ ነስሩዲን ለምን ሆኑ ማለት አይቻልም ። በምሣሌ የተናገሩትን ስሙትና እናንተው ፍረዱ ።

” ወያኔ / ኢህአዴግ አገሪቱን በጥቂት ቋንቋዎች አንድ ጎሳን ፈላጭ ቆራጭ በማድረግ ፣  ክልል ብሎ በቋንቋ  ቢላዎ ሲሸነሽናት ፣ ባለ ቋነቋው የጥቂት ሰዎች ስብስብ  ክልል ተብየው  ራሱ   የፈጣሪው ወያኔ ተላላኪ እንደነበር ይታወቃል ፡፡ ” ለምን እንዲሆ ሆነ ? ” ብትሉ ፣ ሲጀመር የወያኔ ተልዕኮ በእውርና በደንቆሮ ስብስብ አማካኝነት አገርና ጠቅልሎ በመግዛት ፣ መበዝበዝና ማስበዝበዝ ነበር :: ወያኔ በዘረፋ የመበልፀግ ራእዩን ማሳካት እንጂ ፣  ለየነገዱና ጎሣው ሙሉ መብትና ነፃነት መስጠት ከቶም ግቡ አልነበረም ፡፡ የተለያየ የዘር ሥያሜ እየሰጠ ና  የድንቆሮ ና በህሊና እውርነት የሚሰቃይ ፣በዘረኝነት ያበደ ግለሰብን  ከየጎሳው እየመረጠ  በመሪ ወንበር አስቀምጦ ስኳር እንደፈለገው እንዲቅም በማድረግ  ፤ በሆዱ እየደለለ ፣  በእጅ  አዙር  ለመግዛት አስቦ ና አቅዶ ነበር 27 ዓመት ሙሉ በአገዛዝ ወንበሩ ላይ በጠመንጃ እያስፈራራ ሊቀመጥ ችሎ የነበረው ፡፡” በማለት  የአፋሩ  ሽማግሌ ወጋቸውን ጀመሩ ፡፡

” ወያኔ / ኢህአዴግ ፣ በተጨቋኙ ሥም ሥልጣን ቢይዝም  ለብዙሃኑ ፤ የኑሮ ጭቆና ላደቀቀው  ዜጋ ህይወት መቀየር ኢምንት አሥተዋፆ አላደረገም   ። በብሔር / በብሔረሰቦች እያመካኘ   እንደልቡ ለመመዝበር  እንዲያመቸው  ግን ፣  በየክልሉ የሚኖር  በንቃተ ህሊናው ደካማ የሆነ ግለሰብን በመብራት ማደንን እንደ ዋና አማራጭ ወስዶ በዘመኑ ሁሉ    ሲንቀሳቀስ እንደነበር ይታወቃል  ።  ”  በማለትም የወጋቸውን ጭብጥ ማብራራት ጀመሩ ፡፡

“ወያኔ ፣  በእያንዳንዱ ዜጋ መኖሪያ ቤት አንኳኩቶ በመዝለቅ ፣ በምሥጢራዊ  እንቅሥቃሴ  በፍፁም  ነፍሱና  ልቡ ለወያኔ ለማገልገል የሚችል መፈለግ ነበር ።  የምርጫ መሥፈርትም አውጥቶ  በየመኖሪያ ቤቱ እየዞረ  እርሱ ብቻ በሚያውቀው ምሥጢር የራሱን ሎሌ መመልመል ጀመረ ።

ምሥጢራዊ መሥፈርቱ ግን ከእኛ ከሽማግሌዎቺ አልተሰወረም ። የወያኔ ሎሌ ሆኖ ለማገልገል የሚመረጠው      ሰው  በወያኔ   አይን የሚያይ ፤ በወያኔ  ጆሮ የሚሰማ ና ‘ አጣጥሜዋለሁ ዋጠው ሲባል የቀረበለትን ምግብ ሁሉ የሚጎሰጉስ  እና እንደኮሶ የሚጎፈንን የውሸት ፅዋ ፣ ይጣፍጣል ጠጣ   ‘ ሲባል እውነትህን ነው ማር ፣ ማር ፣ ይላል  እያለ  ፣ ፊቱን ሳያጨፈግግ የሚጨልጠውን እንዲሆን ተወሰነ ።

”  አመራረጡም እንዲህ  ነበር ።መቸም ነበር ሩቅ ነው ። …ወያኔ ያለሌላ አማራጭ ነጭ እና ጥቁርን ብቻ እየለየ  ለመመረጥ የሚያበቃ መሥፈርት አውጥቶ ፤  ካድሬዎቹን በአያንዳንዱ ኗሪ ቤት  እየዞሩ ፣ በየቤቱ  ከላይ የጠቀሥኩት ደካማ ሰው መኖሩን  ለማረጋገጥ የሚያሥችላቸውን የድንቁርናና የህሊና እውርነት ችግር ያለበትን ሰው እንዳለ  እንዲጠይቁ ያደርግ ነበር ።

”  እንበልና የወያኔ / ኢህአዴግ  ካድሬዎች   ቤትህ መጥተው  በር ያንኳኳሉ። በሩን ሥትከፍትላቸው  ‘ እዚህ ቤት ደንቆሮ ና ዐይነ ሥውር አለ ወይ ? ” ብለው ይጠይቃሉ ። በድንቁርናውና በህሊናው እውርነት የተቸገርክበት ለአቅመ አዳም የደረሰ የቤተሰብ አባል ካለህ አለኝ ብለህ ሥሙን ታሥመዘግባለህ። ከሌለህም ወይም ጥያቄያቸው ካልገባህ ፣ በጥያቄያቸው ተገርመህ ‘ኧረ ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የምጠይቁኝ ? ‘ በማለት የመገረም ጥያቄ ልትጠይቅ ትችላለህ ። የምትባለው ግን አንተ ‘… የተጠየቅኸውን ጥያቄ በቀጥታ መልሥ  ” እዚህ ቤት ደንቆሮ ወይም አይነ ሥውር አለ ? ‘ ይሉሃል ። በቁጣ ና በግልምጫ ። ‘ኧረ የለም …’ እያልክ በመተባተብ ትመልሳለህ ።አለ ወይም የለም  ነው ።ቀጥተኛው መልሥ ።ከዚህ ወጪ ከሠለሥክ ግን ቁጣና ግልምጫ ፣ ባሥ ካለም ፣ ታርጋ ይለጠፍብህና ትዘበጣለህ ።

እናም ወያኔዎች በኩራት እና በፍፁም ግብዝነት የየመደሩን ቤት እያንኳኩ ፣ በአነገቱት ጠመንጃ እያሥፈራሩ ፣ የጠየቁትን ጥያቄ መልሥ ይዘው ፣ የግለሰቦቹን ሥም ዝርዝር ለግምገማ  ያቀርባሉ ።

በየቀበሌው እየዞሩ ይህንን ጥያቄ ጠይቀው ፣ ከየቤቱ ከተሰጣቸው የሥም ዝርዝር ውስጥ በታላቅ  ‘ ግምገማ  ‘እውነቱን በራሳቸው መንገድ ያጣሩና የበለጠ ደንቆሮ ፤ የበለጠ በህሊና ዕውርነት የሚሰቃይ የዛ ክልልን ቋንቋ ተናጋሪ ከዝቅተኛ አመራር   ጀምሮ እሥከ ከፍተኛ አመራር ያለውን የሥልጣን ቦታ ይሰጡታል ።

”  ወያኔዎች  በማጭበርበረ ፣ በሌብነት ፣ በዘረፋ ፣ በቆርጦ ቀጥልነት ፣በጨካኝነት ፣ ወዘተ የታወቀውን ፤  ህሊ ና እና የሚያዳምጥ ጆሮ የሌለውን ፣ በእንከን የታጨቀ ግለሰብን ሥልጣን ሰጥተውት ሲያበቁ ፣  ሰውየው ፣  እንደራሳቸው ፈቃድ የሚሰራ ፣ የእነሱ ዕቅድ ፈፃሚ ፣ ጠብ እርግፍ ብሎ ያሉትን አድራጊ ታዛዥ እንደሆነ በአርባአምሥት ቀን ተግባራዊ ፈተና ያረጋግጡና ሹመቱን ያፀኑለታል ።  ከዛ ወዲያማ ምን ይጠየቃል  ?  በ27 ዓመት በአገር ውሥጥ እና በውጪ አገር ያከማቹትን ሀብት ሥለምታውቁት ፣ መናገር አይስፈልገኝም ።…” በማለት ወጋቸውን ደመደሙ ።

ከ 27 ዓመት በኋላ በድንገት ፣  እንዲህ አይነቱን ማፍያዊ  የብዝበዛ መረብ የዘረጋ  ፣ ፀረ ኢትዮጵያ መንግሥት ፣ በህዝባዊ ተቃውሞ መጋቢት 24/ 2010  ዓ/ም ላይ ከዙፋኑ እንደቀልድ ቢገፈተርም ፣በኢንዶመት ሥም የመግሥትን ሽፋን ተጠቅሞ በዝባዠነት ፤በሙስና ፤ በሌብነት ፤ በዘረፋ ፤ በኮንትሮባንዲስትነት ፤ በአሥመጪና ላኪነት ፤ በብላክ መርኬት ኤክስፐርትነት ፤ በህገወጥ መሣሪያ ንግድ ፤ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች በዝባዠነት ፤ በሜቴክ ሥም  የሀገር ሀብት ዘራፊነት ፤ ወዘተ። የተሰማሩ   የህወሓት /ኢህአዴግ  ቱጃሮችን ማንም በህግ ተጠያቂ አላደረጋቸውም ። ይህም የሆነበት ምክንያት “ትልቅ የሙሥና ጫካ በመፈጠሩ የተነሳ ፣ የመንግሥት ሌቦች ና የጥቅም ሸሪክ ሆነው የተባበሯቸው ቱጃር ነጋዴዎች በዛው ጥቅጥቅ  ጫካ ውሥጥ በአንድ ላይ በመገኘታቸው ነው ። በዛ ጫካ ግማሽ ሚሊዮን የሰረቀም ቢሊዮን ብርም የሰረቀ ከህጋዊው ነጋዴ ጋር ተመሳስሎ ይተረማመሳል ።  እናም በቀላሉ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለህግ ለማቅረብ ይቸግራል ። ” የሚሉን አሉ ? ይህ መልሥ ግን መለሥ ዜናዋ ከመሞቱ በፊት የመለሰው መልሥ ነው ። ይህ የሰው ጫካን አግዝፎ የማሳየት አምክንዮ ሌቦች በብዙሃኑ ህዝብ ድህነት ላይ እያሾፉ እንዲቀጥሉ በገደምዳሜ  መፍቀድ እንጂ እውነትን ፊለፊት ተጋፍጦ ሌቦችን ከተሸሸጉበት ጫካ እያደኑ በመልቀም ለፍርድ ማቅረብ ለነመለሥ ተሥኗቸው አይመሥለኝም ።

ይልቁንም ገዢው ፖርቲ እያወቀ ፣በሌቦች ለታጨቀው የሰው ጫካ ከለላ የሚሰጠው ራሱ መሆኑንን ፣ ሌብነት ተሥፋፍቷል ባዩን የራሱን ሰው ፣ ሥዪ አብርሃን ” ሌባ ነው ! ” ብሎ በሃያአራት ሰዓት ውሥጥ በሙሥና የተከሰሰ ፣ የዋሥትና መብት አይገባውም የሚል ህግ በምክርቤት አሳውጆ ዘብጥያ እንዲወርድ ማድረጉ በግልፅ ይመሰክርልናል ።..

ኢህአዴግ ፣ “የራሱን ሌቦች ሲመክር “ሥትሰርቁ ፣ እንዳትያዙ ተጠንቀቁ ። በግልፅ አትስረቁ ። ከተደበቃችሁበትም ከሰው ጫካ አትውጡ ። ከህዝቡ ጋር ተመሳሰሉ ። ሥለእናንተ የሐሰት ወሬ በመንዛት ፣ ያልሆናቸውን እንደሆናችው በማወጅ መልካም ስብዕናን የሚገነቡላችሁን ፣ በምላሳቸው ጤፍ የሚቆሉትን ” ቀጣፊ  ደላሎች” ጓደኛ አድርጉ ። እንደውም በእነሱ እየተጠቀማችሁ ብዝበዛችሁን አፋፍሙ ።

ይባሥ ብሎ ፣ ወያኔ /ኢህአዴግ በካድሬዎቹ በኩል ፣  ህዝቡ  በራሱ አእምሮ እንዳያስብ ፣ ጠብታ ውሃና ቅንጣት ስንዴ በማያሥገኝ ተሥፋ ተሞልቶ ወያኔንን እንዲያምን ማድረግ የሚያሥችል ፣ እሥከ አንድ ቤተሰብ የሚዘልቅ ” ልጎም ” የአንድ ለአምሥት ጥርነፋን ፣ ቢያሰፍንም ፣ በሁሉም ክልሎች እንዲህ ዓይነቱ ህሊናን አጣቢ ፣የጥርነፋ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተብዬ  ለመተግበር   ሌት ተቀን ቢጥርም ሊሳካላቸው አልቻልም ።

የአቶ መለሥ ዜናዊ  ሌጋሲ (ውርስ)፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣የፖርቲው አባል ፣   ያልተማረ ቢሆንም ፣ ፖርቲው ከመነበት    ሚኒሥቴር  አድርጎ የሚሾመው መሆኑንን ሥናሥታውሥና   ዘሬ ላይ ሆነን ትላንት ወያኔ ሥልጣን ወንበር ላይ ሆኖ በብዙሃኑ ህዝብ የተጠላበትን እና ከሥልጣን የተወገደበትን ሂደት ሥናጤን ዛሬ በወያኔ ወንበር የተቀመጠው አሻጋሪው መንግሥት ፣ የነበሩትን የወያኔ መዋቅሮችን ይዞ ፖለቲካዊ  ለውጥ ለማዋለድ የሚጥር እንጂ ከቀበሌ ጀምሮ ያሉትን 27 ዓመት ሙሉ ተጠርንፈው ያሉ ካድሬዎቹን በመለወጥ አዲስ ፖለቲካዊ ለውጥ ሙሉ ለሙሉ አምጥቶ እንዳልሆነ እንገነዘባለን ።

ይህ ማለት ከላይ የአፋሩ ሽማግሌ ባሉት መንገድ የተመለመሉ ካድሬዎች ዛሬም በሚጢጢው ና በግዙፉ በሥልጣን ኮርቻ ላይ የሉም ማለት እንደማይቻል ያረጋግጥልናል ።

በማህል አገርም ሆነ በ10ም ክልሎች ፣ በእነዚህ ካድሬዎች    ፖለታካ ዛሬም አገር እየተተራመሰ ነው ።   ወያኔ / ኢህአዴግ ከሥልጣን ቢገለልም ቅሉ ፣ በሁሉም  ክልል ይህ የድንቁርና ሂደት ቀጥሏል ። ህዝብ የወያኔን የ27 ዓመት አደንቋሪ የዘረኝነት ፕሮ ፖጋንዳ ፣በደናቁርት ና ህሊና ቢሰሰ ካድሬዎች እየተጋተ ፣ የማሰብ ነፃነቱን ተገፎ መኖሩ እሙን ነው ። ለ27 ዓመት የተጋተውን ፕሮፖጋንዳ በሦሥት ዓመት ያውም በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ተመሥርቶ መለወጥ ና መሻሻል ያለባቸው ሳይሻሻሉ  ፣ የተጋተው መርዝ ወጥቷለት እፎይ ለማለት ከቶም አይችልም። ገና፣  አሁን ከምናያቸው የባሱ  ፈተናዎች ከፊታችን ተደቅነዋል ። አይደለም በገዣው ፖርቲ በብልፅግና ውሥጥ በህጋዊ ፖርቲዎች ውሥጥም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ዜጎች በማያምኑበት የዘር ግጭት ውሥጥ ገብተው እንዲጨራረሱ ትጥቅና ሥንቅ የሚያቀብሉ ዛሬም አሉ። ዜጎች ከተጨራረሱ በኋላ ማንን እንደሚያሥተዳድሩ ባይገባኝም ።

ባንጨራረሥም እኮ ህይወት በራሷ አጭር ናት ።ለመሆኑ ሥንት ዓመት ነው ያሻንንና ያሰኘንን በማድረግ የምንኖረው ? ከ70 ዓመት የሚበልጥ አይደለም እኮ !?… ። ከዛ በኋላ ወጣቶቻችን እንደልባቸው  ሲፈነጩ እኛም እንደቀደሙት አባቶቻችን ፣ በተራችን ቁጭ ብለን ማየት ይሆናል  እጣ ፈንታችን ።

ዛሬ በህይወት ያለ ሰው ሁሉ ችግር የሚሞት መሆኑንን ያለሠገንዘቡ ነው ። የሰው ሁሉ የክፋት ምንጪ  የሚሞተው ሌላ እንጂ እኔ ዛሬ አልሞትም ብሎ ማሰቡ ይመሥለኛል ። በድንገተኛ አደጋ እና በሰውነቱ ውሥጥ በሚፈጠር  ድንገተኛ በሽታ  ( በኮሮና መሠል ቫይረሥ ጭምር  ) እንደሚሞት  አሥቀድሞ  የሚያምን እምብዛም የለም ።  ይህም የተሳሳተ እና ከእውነት ጋር የሚጋጭ እምነቱ  በቃላት ተደልሎ ፣ በንዋይ ተታሎ ፣በቀቢፀ ተስፋ ነሁልሎ ክብሩን አምሳያውን ሰው ፣ እዚህ ግባ በማይባል በድንቁርና አስተሳሰብ ተገፋፍቶ ህይወቱን ይቀማዋል ። ያውም ለጆሮ በሚቀፍ ፣ ለአይን በሚዘገንን ጭካኔ ።

ይህንን የጭካኔ ድርጊት እንዲፈፅም የሚያበረታታው  ደግሞ  ልሂቅ ወይም በቂ የፖለታካ ዕወቀት ያለው ምሁር ሆኖ መገኘቱ ያሳዝናል ። በህቡ በሚያገኘው ገንዘብ ” ዓለም በጎኔ አለፈች ። ” እያለ ፣  ከህዝብ እልቂት በመጨረሻ አትራፊ እንደሚሆኑ ከሚያውቁት ከአውሮፖና አሜሪካ ቱጃሮች እንዲሁም ” የኢትዮጵያ ብልፅግና ፣ የእኛ አገዛዝ ማክተማያ ይሆናል ። ” ብለው ከሚያምኑት አንዳንድ የጎረቤት አገር ጠላቶቻችኝ ጋር በማበር ይህ የፖለቲካ ሊሂቅ ተብዬ ፣ አገራችንን የደም መሬት እያደረጋት ነው ።

ለምን ይሆን ፊደል የቆጠረው ፣ ተጃጅሎ ለራሱ ሥጋ ጥቅም ሲል ብቻ ፣ ፊደል ያለቆጠረውን የዋህ ዜጋ ፣ በቀቢፀ ተሥፋ  በመደለል  የንፁሐንን ደም በከንቱ እንዲፈሥ ቃታ እንዲስብ በማድረግ ፣  የንፁሐን ደም  ምድሪቷ ፈሶባት  በኡኡታ እንድትናወጥ የሚያደርጋት ?

ለምን ይሆን ፣ፖለቲከኞች ሁላ  ሰው ሁሉ    ፣በማህበራዊ መስተጋብር ተዋህዶ ፣ አንዱ ሰው ከሌላው ጋር ካልተሳሰረ በስተቀር   መኖር እንደማይችል  ለማወቅ ተሥኗቸው የምድሪቷን ጩኸት እንደሙዚቃ የሚቆጥሩት ?   ለምን ይሆን ዜጎችን ፣ለመከፋፈል ፣ ለመነጣጠል ፣ ለማጋጨት ፣ ለማጨፋጨፍ  ዘወትር ሢያደቡና  ሲያሴር የምናስተውላቸው ?

abiy
The new Prime Minister of Ethiopia, Abiy Ahmed, during his visit to Somali, Mogadishu, Saturday, June16, 2018.(AP Photo/Farah Abdi Warsameh)

አሻጋሪው የለውጥ መንግሥት ዛሬም ከላይ የአፋሩ ሽማግሌ ያጫወቱንን የወያኔ የፖለቲካ መንገድ የሚከተሉትን ይዞ በመጓዝ ፣ የማይደመሩትን በመደመር ለውጥ አመጣለሁ ብሎ በማሰቡ ነውን  ?… ወይስ ፤    የምትሉትን ፣ የምታቀርቡትን ገንቢ ሃሳብ ሁሉ እገነዘባለሁ ። በካርዳችሁ አምሥት ዓመት እንዳገለግላችሁ ዕድል ሥጡኝ እና ከአሻጋሪነት ወደመሪነት ስታመጡኝ ፣ ያን ግዜ ፣” የህዝብ ሥልጣን ወይም ዴሞክራሲ ” እንዴት እንደሆነ በተግባር ካለሳየኋችሁ ፤ የዛን ጊዜ ትወቅሱኛላችሁ ። ዛሬ ግን በሥሜት የምታወሩት እውነት አይደለም ። ነገርየው ከኑግ ጋራ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ነውና በህግ አግባብ ሳትፈትኑኝ በከንቱ አትወቀሱኝ ። እያለን ይሆን ፤ መሪው በገደምዳሜ ንግግሩ ? የማስተዋሉን ጥያቄ እናንተን በመጠየቅ የዛሬውን ፅሁፌን እቋጫለሁ ፡፡  “ሳይደወል ቅዱስ ” አትበሉ ፡፡ በማለት  …

2 Comments

  1. Mekoonnen: Are you a paid propagandist or a a victim of ahmed`s lies? The traitor ahmed has shown us his true color several times. If you belong to the latter group, how long are you going to be cheated? Think a little. Ahmed told us several times that he was spying for OLF and he was proudly saying. The blood of thousands of Amharas killed by ahmed`s OLF army is you and your likes to come to your sense. If not, we take you as a collaborator of perpetrators of genocide.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.