ሰው መሆንን ያሳዩንና የሚነግሩን፣ የኔሰው ገብሬ እና ታሪኩ ጋንኪስ – ኤልያስ ገብሩ

የኔሰው ገብሬ እና ታሪኩ ጋንኪስ፣ የፓለቲካ ልሂቅ ነን ከሚሉ ብዙዎች ይሻላሉ – በእኔ እምነት።
– በኢትዮጵያ ውስጥ፣ ታይተው/ብቅ ብለው የከሰሙ እንጂ፣ ዘልቀው የሰመረላቸው አንድም የብሔር ብሔረተኞች የሉም።
Yenesewከጥቂት ዓመታት በፊት መምህር የኔሰው ገብሬ፣ የብሄር ዘረኛ አገዛዞችን ድርጊትን ተቃውሞ፣ እንደ ቱኒዚያዊው ቦአዚዚ ራሱን በቤንዚል አርከፍክፎ ምኒሊክ አደባባይ ላይ አቃጠለ። የካቲት 12 ሆስፒታል ለህክምናም ገባ። ያኔ እኔም፣ በአገዛዙ ጥብቅ ቁጥጥር ስር በነበረቸው ፍትህ ጋዜጣ ላይ እሰራ ነበር፤ የየኔሰውን የጤና ኹኔታ ልመለከት ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል አመራኹ። እርሱም ሕይወቱ አልፏል – ታሪክ ሰርቶ።
እነዛ የያኔ ብሔረተኛ አምባገነኖች ግን፣ ዛሬ አከርካሪያቸው ተመትቶ፣ ከድንጋይ ድንጋይ እየዘለሉ የቆቅ ኑሮን ይገፋሉ። ይኼ፣ ብሔር ተኮር ብሔረተኝነት ፍጻሜው እንደማያምር አንድ ማሳያ ነበር/ነውም። ልብ ያለው ልብ ይበል፣ ልብ የሚል ብዙም ባይኖር ….Short term memory ለአገሬው ብዙ ሰው በደንብ ትሰራለች ….
በሕይወት ብዙ ውጣ ውረድ ያሳለፈው ታሪኩ ጋንኪስ (ድስታጊና)፣ ከመሐል ከተማ 700 ኪሎ ሜትር ርቆ በጅንካ የተፈጥሮ ደን ውስጥ እየኖረ ስለ አዳም እና ሂዋን፣ የሰው ልጆች፣ አንድ የሰው ዘር መሆናችንን በቅንነት ሰው ኾኖ ይሰብካል። ዛሬ፣ ወረተኛ አዳማጩ ብዙ ነው፣ ከልብ አድምጦ ከልብ የማይተገብርም እንዲኹ። በዚህ ታዝናለህ።
ኢትዮጵያ ውስጥ፣ በየትኛውም የብሔር ብሔረተኝነት ዘልቆ የሰመረለት ማንም የለም። ቢገባቸው፣ ለአጭር ጊዜ ታይተው የሚከስሙ ናቸው። የኾነውም ይኸው ነው።
ለማንኛውም፣ መምህር የኔሰው ገብሬም ሆነ ገበሬው ታሪኩ ጋንኪስ፣ በእኔ አረዳድ እና እምነት፣ የፓለቲካ ልሂቅ ነን ከሚሉ ክሹፍ እና ተንተፋትፈው ከሚከስሙት ብዙሃን የተሻሉ ናቸው። የኔሰው እና ታሪኩ፣ ሰው መሆንን በተግባር አሳይተዋል፣ በቻሉትም ጥረዋል። አንዱ በሕይወት የለም፣ አንዱ አለ።
ፈጣሪ፣ ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉትን ዝቅ፣ ቅን በመሆን ዝቅ ዝቅ የሚያደርጉትን ደግሞ ከፍ የሚያደርግ ነው። ሥራው ከእኛ የተለየ ነው። አውቄያለኹ፣ ስንል እንደምናውቅ ያሳየናል፣ በእንደነ ታሪኩ ጋንኪስ በኩል መልእክት ይነግረናል። እሱም በተግባር ከገባን ነው።
በአሁኑ ወቅት፣ የእኔ ብሔር የምንለው ብዙ ሲኾን፣ በተግባር የኔሰው የምንለው ሰው ግን፣ ኢምነት መኾኑን ልቤ ያምናል።
ሰው ሆነን ተፈጥረናል፣ ሰው ነንና በተግባር እንደሰው ለመኾን ልቡና ይስጠን!
ኤልያስ ገብሩ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.