ኦባንጎ ሜቶ የ “Failed State” ስጋት ላይ የቀረበ አስተያየት አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ

አንድነት ይበልጣል – ሐዋሳ – ሚያዝያ 2 / 2013

Obangውድ ኦባንግ፡ “እኛን እየጎዳን ያለው ድንጋይ ወርዋሪው ብቻ ሣይሆን ዝምታችንም ነው”

“Ethiopia is at Risk of Becoming a Failed State! What Will You Do?” የሚለውን ጽሁፍህን በዘሐበሻ ላይ አነበብኩት፤ በብዙ ኃሳቦችህ እስማማለሁ፡፡ በተለይም ተባብሮ ከመታገል ውጭ ምንም ዕድልና አማራጭ እንደሌለን አጽንዖት መስጠትህን በጣም ወድጀዋለሁ፡፡ በዚህ ጥረት ውስጥ እኔም ከጎንህ መሆኔን አረጋግጥልሀለሁ፡፡ እየጨመሩ የሄዱ ትልቅ የአደጋ ምንጮች ባልካቸውም ላይ እኔም ተቀራራቢ ስጋት አለኝ፡፡

–  Armed military conflict in the Tigray Region

–  Ethnic-based killing and violence in non-combat zones especially Oromia, Benishangul-Gumuz and the Amhara Region.

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የችግሮቹን ምንጮች፣ ባለቤቶችና የመፍትሔ ሐሳቦችን በሚመለከት የኔን በመጠኑ ለየት ያለ ዕይታ ደግሞ ላሳይህ እወዳለሁ፡፡ ዕውነቱን ለመናገር፤ እነዚህ የግጭት ምንጮችና አስፈሪ አደጋዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ትናንትም ነበሩ፣ ዛሬም አንዳንዶቹ ቀንሰው ሌሎቹ ደግሞ እንዲያውም ብሰው ይታያሉ፡፡ መፍትሔ ለሚፈልግ ሰው ትልቁ ጥያቄ፣ እነዚህ ችግሮች ለምን ትናንትም ዛሬም ኖሩ? የነዚህ ትልልቅ ችግሮችና አደጋዎች ባለቤታቸውና ተሸካሚያቸውስ ማንነው? እናም ያንተው ጥያቄ “What Will You Do?” የሚለውም ይመስለኛል፡፡

ችግሮቹ ወያኔ ሥልጣን ላይ በነበረት 27+3 ዓመታት ውስጥ የነበሩ ናቸው፡፡ ወያኔ ከሥልጣን ከተባረረ በኋላም፣ በዚህ የሽግግር ወቅት ተባብሰው መታየታቸው እጅጉን ቢያሳዝንም፣ ነገር ግን የሚጠበቅ ነገርም ነው፡፡ የችግሮቹ ባለቤቶችና ተሸካሚዎቻቸውን (በውስጠ ታዋቂ ደግሞ ምክንያቶቹንም) እንመልከት

  1. እጅግ የሚበዙትን የትናንትናዎቹን የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና ዝርፊያ ሲፈጽም የነበረው በወያኔ የሚመራው መንግሥት ነበር (ለምን? …)
  2. የሚበዙትን የዛሬዎቹን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የሚፈጽሙትና የሚያስፈጽሙት ደግሞ በዋነኛነት ከመንግሥት ውጭ ያሉ ተዋናዮች ናቸው (Non State Actors)፤ እነዚህም፡

2.1 ወያኔና ትርፍራፊዎቹ (ለምን?)

2.2  ኦነግ / ሸኔና መሰል የብሔር ጽንፈኞች (ለምን?)

2.3 ቂም የያዙና ለበቀል ቅርብ የሆኑ ቁጥራቸው የበዛ ዜጎች፤ የብሔርና የጎሣ ልዩነትን ያነገሠው ሕገመንግሥት በፈጠረው የወዳጅና ጠላት፣ የነባርና መጤ/ሰፋሪ የውሸት ትርክት ምክንያት ለ27 ዓመታት ለዘር ጥቃት ሲጋለጡ የኖሩ፣ ብዙ ግፍ የተፈጸመባቸው ዜጎች፤

2.4 ወጣቱ ትውልድ ከሰላምና ከአንድነት ይልቅ ለመከፋፈል፣ ለጥላቻና ለግጭት ቅርብ እንዲሆን ተደርጎ ተጣሞ በመቀረጹ፣ በሕገመንግሥት፣ በፖሊሲ፣ በሥርዓተ ትምህርት፣ በፌዴራልና በብሔር ሜዲያ ሥርዓታዊና ተቋማዊ በሆነ መንገድ በተዘራው ጎሠኝነት ምክንያትና በዕምነት ተቋማት ሣይቀር በተሠራውና ባልተሠራው ሥራ ምክንያት፤

2.5 ለዘመናት ችግርና ስሜቱን የመግለጽና የመተንፈስ ነጻነት ተከልክሎ የቆየ የሕብረተሰብ ክፍል፣ የነጻነትና የመብት አጠቃቀም ልምምዱ ገና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆንና ከነጻነት ጋር አብሮ ያለውን ግዴታም በቅጡ ያለመረዳት ችግር፤

2.6 ሥር የሰደደው የኑሮ ውድነትና የሥራ አጥነት ችግር ያስመረረው ወጣትና ሌላም የሕብረተሰብ ክፍል፣

2.7 በመንግሥት / ገዢው ፓርቲ ውስጥ በየእርከኑ (በየብሔሩ) የተሰገሰጉና

–   የተጀመረው ለውጥ (የጥቅም መቅረትና የተጠያቂነት አይቀሬነት ) ያስፈራቸው

–  የተጀመረው ለውጥ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም በባለተራነት ስሜት አዲስ ገዢ ለመሆን የቋመጡ

2.8 ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ በሐብት ማግበስበስና በኢፍትሐዊ አጠቃቀም ጉድለት የተመረዘችው ግብጽ፣ መረጋጋትና አንድነት እንዳይኖር የምትፈጥረው ግልጽ ሻጥር

2.9  ኢትዮጵያ አድጋ (ሕዳሴ ግድብ ወዘተ) በኢኮኖሚና በሁሉም ዘርፍ ራሷን ብትችልና የቀጠናው የኃይል ማዕከል ብትሆን የሚቀርባቸው ጥቅም ያሳሰባቸው ምዕራባውያን ያላቸው አለመረጋጋትን የማስፈን ፍላጎት

2.10 የችግሮቹ ዋነኛ ሰለባ የሆነው፣ የሚበዛው የሕብረተሰብ ክፍልም ጣት ከመቀሰር፣ ከማላከክና ከመክሰስ በስተቀር ኃላፊነት ወስዶ የድርሻውን ገንቢ ሚና በበቂ ሁኔታ አለመጫወት፤

2.11 እዚህ የተጠቀሱት አብዛኞቹ ኃይሎች፣ አንዳንዶቹ በእርግጥም የጋራ በሆኑ ጥቅሞች  ዙሪያ፣ ሌሎቹ ደግሞ የጋራ በሚመስሉ ጥቅሞች ዙሪያ በመሰባሰብ የሚፈጥሩት ቀውስና አለመረጋጋት፤

ከወቅቱ ትልልቅ ችግሮችና ፈተናዎች መካከል የሚበዙት ከ30 ዓመቱ የወያኔ አገዛዝ ያደሩና የተላለፉ ግዙፍ ሸክሞች (Back Log) ናቸው፤ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ በአንድ ወይም በሌላ መልክ ከለውጡ ጋር የተቆራኙ ፈተናዎች ናቸው፤ ለምሳሌ ገና ለጋ ከሆነው ለውጥ የጠበቁትን ብዙ ውጤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለማግኘት የሚፈጠር ቅሬታ አለ፤ የጅምሩን ለውጥ ትሩፋቶች የአረዳድ፣ የአያያዝና የአጠቃቀም ክፍተትም አለ፡፡ ለውጡን በእርግጥም ከመጥላትና ከመፍራት የሚመነጭ የጸረ ለውጥ ኃይሎች ሻጥርና የማሰናከሉ ጥረት የጎላው ፈተና ነው፤ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

መፍትሔው ኢትዮጵያውያን በሁለተኛና በሦስተኛ ደረጃ ሊታዩ በሚችሉ ልዩነቶች ተወጥረን እርስ በርስ መገፋፋትና መጓተታችንን ማቆም ነው፤ በጋራ ችግሮቻችንና መፍትሔዎቻችን ዙሪያ በመተማመንና በመቻቻል፣ በሕብረት ትግል ጸረ ለውጥ ኃይሎችን ማሸነፍ ነው፡፡ በለውጡ ሂደት የሚታዩ ጉድለቶችን እንደራስ ጉድለቶች እየተመለከትን በባለቤትነት ስሜት ለውጡን ማጠናከርና ዳር ማድረስ ብቻ ነው ለማሸነፍ ያለን ብቸኛ ምርጫ፡፡ አንድነታችንን፣ ዕድገታችንንና ሰላማችንን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት ባህላችንን ለማጎልበት በአሁኑ ጊዜ ያለን ብቸኛ ምርጫና ዕድል አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም (አንተም/ኦባንግ እንዳልከው) ልዩነቶቻችንን፣ አጥብበን፣ አቻችለን / አሳድረን፣ በጋራ የሕልውና ጉዳዮች ላይ ጠንካራ መግባባትን ፈጥረን ከላይ የተዘረዘሩትን ኃይሎች ማሸነፍና የደቀኑብንን ፈተናዎች በጋራ መሻገር ነው፡፡

አሁን ያለንበት ሁኔታ የሴት ልጅን ምጥ ያስታውሳል፤ ልዩ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆኖ፣ ምጥ ምጥ ነው፣ ነገር ግን ጨቅላ መወለዱ አይቀርም፤ ጨለማም መንጋቱ አይቀርም፡፡ የተፈጥሮ ሕጎች ናቸው፡፡  ይዋል ይደር እንጂ በጎ ኃይል ክፉ ኃይልን  ማሸነፉ አይቀርም፡፡ እኛም አንድነታችንን አጥብቀንና ወጥረን ከታገልን ይህንን ፈተና እንሻገረውና ታሪክ እናደርገዋለን፡፡ በመንግሥት ውስጥ ያሉና ከመንግሥት ውጭ ያሉ የለውጥ፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የዕድገት፣ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት ኃይሎች በአንድ ልብ፣ በአንድ አእምሮ፣ በአንድ እጅ፣ በአንድ ኪስ፣ በአንድ መንፈስ ታግለን የኢትዮጵያንና የሕዝቧን ህልውናና ሉዓላዊነት ማስከበር ነው፡፡

በተለይ አሁን ይህ ሁሉ ግርግር የበዛበት ምክንያት የሚጠፋን አይመስለኝም፡፡

1ኛ) የግንቦቱ ምርጫ እንዳይሳካ

2ኛ) የአባይ ግድባችን 2ኛ ዙር ሙሌት እንዳይፈጸምና ግድቡ ወደ ሥራ እንዳይገባ ነው፡፡

እነዚህን ሁለት ፍላጎቶች ለማሳካት እንዲቻላቸው ጠላቶቻችን “ፕሮጀክት ጄኖሣይድ” የተባለ የጥፋት ፕሮጀክት ነድፈው የሚንቀሳቀሱ ይመስላል፡፡ የሚከተሉት ምልክቶች ይታያሉ፡፡

 

 “የጄኖሣይድ” ፕሮጀክቶች – “ፕሮጀክት ጄኖሣይድ”

  • የፕሮጀክቱ ርዕሥ፡ “የትግራይን ጄኖሣይድ”፣ “የአማራን ጄኖሣይድ”፣ “የኦሮሞን ጄኖሣይድ”፣ “የቅማንትን ጄኖሣይድ”፣ “የወላይታን ጄኖሣይድ”፣ “የጉሙዝን ጄኖሣይድ” … ለዓለም ማጋለጥ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለተቃውሞ ማነሳሳት” ይመስላል፡፡
  • የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ፡ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ (በነጻ ምርጫ) እና ወደ ዕድገት – ራስን መቻል (የአባይ ግድብ) የምትሸጋገርባቸውን ትልልቅ ዕድሎችና ተስፋዎች ማምከን
  • የፕሮጀክቱ ትልቁ ግቡ፡ ሐገራችንን የባርነትና የድህነት መናኸሪያ፣ የአምባገነኖችና የምጽዋት አቅራቢዎች መፈንጫና ጥገኛ ሆና እንድትቀር ማድረግ ነው፡፡
  • የፕሮጀክቱ ፈጻሚዎች፡ “We are minorities of the Ethiopian people from Oromiya, Tegaru, Kimant and Eritrean Refugees”) – ይህ ቃል ከቀናት በፊት የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግሥታት ለመቃወም በአንድ የአሜሪካ ጎዳና ላይ የወጡ በመቶ የሚቆጠሩ ሠልፈኞች ስለራሳቸው ማንነት የገለጹበት ቃል ነው፡፡
  • የፕሮጀክቱ ዋና አስፈጻሚ፡ ማርቲን ፕላውት…፤ ይህ ሰው፣ ከላይ የተጠቀሰው ሰልፍ ከመካሄዱ 2 ቀን በፊት ለወያኔ ትርፍራፊዎችና ለኤርትራ ተቃዋሚዎች ስለ ተቃውሞ ዘዴዎች ሥልጠና ይሰጥ የነበረ “ነጭ ወያኔ” ነው፡፡ በሥልጠናውም ላይ ሁለት ዋና ዋና ምክሮችን ሲሰጥ ተስተውሏል፤

1ኛ) “ቪኦኤና ቢቢሲ ትግርኛ (ጣቢያዎች) ዜና ተርበዋል፤ እናንተ ዜና እየፈጠራችሁና እየፈበረካችሁ፣ እነዚህን የተራቡ ጋዜጠኞች (Single celled Organisms) መቀለብና ማጥገብ አለባችሁ”፣

2ኛ) “የኤርትራ ተቃዋሚዎችም ከእንግዲህ እንደቀድሞው ተቃውሞ ብቻ ለማሰማት ኤርትራ ኤምባሲ ደጅ መሄድ የለባችሁም፤ ከሄዳችሁ የምትሄዱት ኤምባሲውን ለማቃጠል መሆን አለበት” እያለ ለኃይል እርምጃ ሲያነሳሳቸው ነበር፡፡

እርግጥ፣ ከፊታችን የተደቀነው ፈተና እጅግ ከባድና አስፈሪም ነው፤ ይህ አያጠያይቅም፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ዕድል ከፈጣሪ በታች፣ በኛ በልጇቿ እጅ ላይ ነው፡፡ ከተባበርን እንቆማለን ፈተናውንም እንሻገረዋለን፡፡ ከተከፋፈልን እንወድቃለን፡፡ ጸጥታን፣ አንድነትንና ሉዓላዊነትን ከማስከበሩ ወሣኝ ትግል ጎን ለጎን በልዩ ትኩረትና በአንድነት ተረባርበን ልናሳካቸው የሚገቡት ሁለቱ ፈተናዎቻችን የግንቦቱ ምርጫና የሐምሌው የግድቡ ሙሌት ናቸው፡፡ እነርሱ ላይ ያለ ልዩነት ተረባርበን ማሳካት የዛሬን ብቻ ሣይሆን የነገን ትልልቅ ስጋቶች ያስወግዱልናል፡፡ ብርሐንና ሰላምም ያመጡልናል!

ውድ ኦባንግ፣ “እኛን እየጎዳን ያለው ድንጋይ ወርዋሪው ብቻ ሣይሆን ዝምታችንም ነው” አላልክም? ተስፋ መቁረጥ የለም!! በዚህ ፈተና ውስጥና በጥረቱም ላይ አብረን ነን!! በርታ የኔ ወንድም! ማሸነፋችን የማይቀር ነገር ነው!

ፈጣሪ ወደብርሐንና ሰላም ያሸጋግረናል፡፡ (ወደ ማተሚያ ቤቱ ማለቴ አይደለም)

ከአክብሮት ጋር

አንድነት ይበልጣል
https://amharic.zehabesha.com/ethiopia-is-at-risk-of-becoming-a-failed-state-what-will-you-do/

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.